ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር ስትሰራ ቆይታለች። ለዚህም የግሉ ዘርፍ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚደርገው ኢንቨስትመንት እንዳለ ሆኖ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ እየሰራች ትገኛለች። የዘርፉን ተግዳሮቶች ለመፍታት ርብርብ በማድረግም በተለይ ለኢንቨስትመንት በሚውል መሬት አቅርቦትና መሰረተ ልማት ላይ ተሰርቷል።
በሀገሪቱ ተገንብተው ወደ ስራ የገቡ በርካታ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችንም ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በውጭ ባለሀብቶች በኩል ከቦታ፣ ከመሰረተ ልማት ጋር ተይይዞ ይቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን መፍታት ችለዋል። ይህም ዘርፉን የሚቀላቀሉ ግዙፍ ታዋቂ የውጭ ሀገር ኩባንያዎችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ካፒታል የመደቡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በፓርኮቹ ገብተው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ኩባንያዎቹ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ከጀመሩም ቆይተዋል። ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት በኩልም የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ ናቸው።
እንዲያም ሆኖ ዘርፉ ዛሬም በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱበት ይገኛል። በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ የሆኑት የዘርፉ ችግሮች፤ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና በአጠቃላይ የሕዝቡን የተቀናጀ ጥረት የሚፈልጉ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል። ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ብዙ ሙከራዎች ተደርገው የማይናቁ ውጤቶች ቢመዘገቡም፣ ከአገሪቱ አቅምና ከችግሮቹ ስፋት አንፃር ግን መፍትሄዎቹ የሚፈለገውን ያህል ውጤት አስገኝተዋል ብሎ መናገር አይቻልም።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልል ከተሞች እየተካሄደ የሚገኘው የ ‹‹ስለ ኢትዮጵያ›› መድረክ አካል የሆነውና የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተዋንያን፣ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ያተኮረ የውይይት መርሃ ግብር ሰሞኑን በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደበት ወቅትም የዘርፉ መልካም አጋጣሚዎች፣ ችግሮች ተመላክተው ሰፊ ውይይትም ተደርጎ መፍትሄዎች ተጠቁመዋል።
በውይይቱ ላይ የአምራች ዘርፉ እድሎችንና የመንግሥትን ትኩረት በተመለከተ ገለፃ ያቀረቡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ የኢትዮጵያን የሕዝብ ብዛት፣ የአምራች ኃይል አቅም፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ሕጋዊ ማዕቀፎችና ለዘርፉ እድገት አወንታዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችንና አስቻይ ሁኔታዎችን በመጥቀስ አገሪቱ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ግዙፍ አቅም እንዳላት አስረድተዋል። በዘርፉ ከተፈጠረው የሥራ እድል ባሻገር በኢንዱስትሪ ፓርኮች አማካኝነት ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ጥቅል አገራዊ ምርት የስድስት ነጥብ ስምንት በመቶ ድርሻ አለው፤ ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ ነው። ይህን እቅድ ማሳካት ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የውጭ ምንዛሪ እጥረትንም ለማቃለል አይነተኛ መፍትሄ ነው።
‹‹አሁን ያለው የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም 50 በመቶ ነው፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠረው የማምረት አቅም ማነስ ምርት በሚፈለገው ደረጃ እንዳይቀርብ አድርጓል። በቀጣይ የአምራቹን አቅም ወደ 85 በመቶ ለማድረስ ውጥን ተይዟል›› ሲሉ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
አገሪቷ ያላትን ትልቅ የዘርፉን እምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር በቅርቡ የ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ መጀመሩን ገልጸዋል። የዚህ ንቅናቄ ምሰሶዎችም ባለድርሻ አካላትን ማሣተፍ፣ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ ለዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እና የሀገር በቀል ምርቶችንና አመራረትን ማሳደግ መሆናቸውን አብራርተዋል። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግርን ለመፍታት የመጀመሪያውና መሠረታዊው መፍትሄ የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ እንደሆነ ያስረዱት አቶ መላኩ፣ ከዚህ አንፃር ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
አገሪቱ ያላትን የኢንዱስትሪ አቅም ገቢራዊ ለማድረግ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍና ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል። ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› እንዲሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍና ተወዳዳሪ የማድረግ ጉዳይ በምጣኔ ሀብት ትብብርና በእርዳታ ስም የሚደረግን የሀብታም ሀገራትንና ተቋሞቻቸውን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ሉዓላዊነትን እስከማስከበር ድረስ የዘለቀ ትርጉምና ፋይዳ አለው።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ፣ የግሉ ባለሀብት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ስላለለው ተሳትፎ፣ ስላበረከተው አስተዋፅኦ እና ስላሉበት ችግሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ለአንድ አገር ዘላቂ እድገት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ያላቸው ሚና የማይተካ መሆኑን አቶ ጀማል ይጠቅሳሉ፤ የውጭ ባለሀብቶች ለውድድር እና ተሞክሮዎች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረው፣ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
ዋና ስራ አስፈፃሚው መንግሥት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ ማሳደግ እንዳለበት ጠቁመው፤ ‹‹የአገር ውስጥ አምራቹ ከውጭ አገራት ግብይት ከሚያገኘው የንግድ ሥራ ያገኛትን የውጭ ምንዛሪ ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት የማዋል ፍላጎት አለው። ችግሮች በአንድ ጊዜ አይፈቱም፤ ቢሆንም ግን ለውጭ አገር ባለሀብቶች የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ሊሠጠን ይገባል›› ብለዋል።
አምራች ኢንዱስትሪው ለዘላቂ ልማት ዋነኛ ሞተር ነው ያሉት አቶ ጀማል፤ በዘርፉ ያለውን እምቅ ሀብት ለመጠቀም የባለሀብቱ ችግሮች ተለይተው ሊታወቁና መፍትሄ ሊፈለግላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የአጠቃቀም ፍትሃዊነት መጓደል፣ የሥራ ባህል ደካማነት እንዲሁም ዘርፉን ለማበረታታት የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበር የዘርፉ ባለሀብቶች ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን አቶ ጀማል አስረድተዋል።
እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ አምራች የግል ባለሀብቶችን ይበልጥ ለመደገፍ በግሉ ዘርፍ የሚቀርበውን የውጭ ምንዛሬ በፍትሐዊነት ማከፋፈል ይገባል። በተለያዩ ጊዜያት እንደሚታየው በአገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች እጥረት አለ በሚባልበት ወቅት በዚያው ልክ ደግሞ የቅንጦት ዕቃዎች በብዛት ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ። ፋብሪካዎች በመለዋወጫና በግብዓት እጥረት በሚዘጉበት አገር፣ የቅንጦት ዕቃዎች በብዛት መግባታቸው የውጭ ምንዛሬ ድልድል በፍትሐዊነት እንደማይቀርብ ያሳያል።
ደሃ ሀገር ላይ እንደመሆናችን የጥሬ ዕቃ ችግር አለብን፤ በመሆኑም ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት ያስፈልገናል። ይህን አይነት ችግር ያለበትን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መንግሥት ለመደገፍ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም በውጭ ምንዛሬ ጉዳይ ላይ ያለውን ችግር ማስተካከል ይገባል›› ብለዋል።
‹‹ሁሉም ችግሮቻችን በአንድ ጊዜ ይፈቱልን አንልም፤ አንጠብቅምም›› ያሉት አቶ ጀማል፤ መንግሥት ከባለሀብቱ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ችግሮቹን መፍታት እንደሚገባውም ተናግረዋል። ‹‹በተለይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን በፍትሐዊነት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ዘርፉን ማሳደግ ይገባል›› በማለት ተናግረዋል።
አቶ ጀማል መንግሥት የአገር ውስጥ አምራቾች እንዲበረታቱ ለዓመታት ያከናወነው ስራ በተለያዩ ዘርፎች የግል ባለሀብቱ እንዲጠናከር አቅም መፍጠሩን ተናግረው፣ በሕዝቡም ሆነ በመንግሥት በኩል የአገር ውስጥ ምርት በመጠቀም ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚገባ ገልጸዋል። ለዚህም ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ ትኩረት ተሰጥቶት በትክክል ከተተገበረ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
‹‹ኢትዮጵያን ከኢንዱስትሪ ውጭ ማሰብ አይቻልም›› ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ፣ መንግሥት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ ዘርፉን ለማጠናከር በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የአቅም ማጠናከር ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። ከመንግሥት ጥረት ባለፈ ባለሀብቱም ተገቢውን የኢንዱስትሪ አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በዘላቂነት ለመፍታት በመፍትሄነት ከተለዩ ቁልፍ አማራጮች መካከል የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ አንዱ ነው። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴም የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ሲቻል እንደሆነ አስረድተዋል። መንግሥት የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ቅድሚያ ማግኘት ያለባቸውን ዘርፎች ለይቶ እየሰራ መሆኑን ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ግን ያመነጩትን የውጭ ምንዛሬ መጠቀም መብታቸው ነው የሚል አሰራር ፈቅዶ ተግባራዊ አድርጓል ብለዋል። ባለሀብቶች የሚያነሱትን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በቅድሚያ ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።
እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፤ የመንግሥት ዋና አላማ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን መደገፍና ማብቃት ነው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሌሎች አገራት ኢንቨስትሮች በተሻለ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ጽኑ ፍላጎት አለው። የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ አቅም ሲጠናከር መዋዕለ ንዋዩንም መልሶ ለሀገር ለማዋል ይችላል፤ በዚያው ልክም አካባቢውን በመጥቀም የስራ ዕድሎችንም በስፋት ለመፍጠር አቅም ይኖረዋል።
‹‹ከዚህ አንፃር፣ ከአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አንስቶ እስከ ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶች ድረስ መንግሥት የመስሪያ ቦታ በማመቻቸት፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን በማሳደግ እና በልዩነት በተመረጡ የንግድ ስራዎች ላይ ኢትዮጵያውያንን ብቻ እንዲሰሩ በማድረግ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል›› ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ‹‹የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ ይበልጥ እንዲጠናከር ድጋፍ ይደረግለታል ሲባል ግን ኢንዱስትሪው በሀገር ውስጥ አቅም ብቻ ይሳካል ብሎ ማሰብ አይገባም›› ሲሉ አስገንዝበዋል። ‹‹ምክንያቱም የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅማችን ገና ውስን በመሆኑ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት ያስፈልጋል። በመሆኑም ሁለቱም ተቀናጅተው እንዲሰሩ መደገፋችንን እንቀጥላለን። የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች በቅንጅት እንዲሰሩ ማድረግ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጤት ማምጣት ተችሏል›› በማለት ስለሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ቅንጅት ፋይዳ ገልጸዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዘላቂ የቴክኖሎጂ እድገትና የሥራ እድል የሚፈጥር እንዲሆን በሀገር በቀል ኢኮኖሚው ዋነኛ ትኩረት እንደተሰጠው የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ በመንግሥት በኩል መሠረተ ልማትን ለማሟላት፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሳደግና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቢሮክራሲ ለማቅለል የሚረዱ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አመልክተዋል።
እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት የመጀመሪያውና መሠረታዊው መፍትሄ ምርትን ማሳደግ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል። የሌሎች አገራት ተሞክሮም የሚያሳየው ይሄንኑ በመሆኑ ምርት ላይ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል።
በእኛ ዘንድ ያለው ችግር የፖሊሲ ሳይሆን ያሉትን ፖሊሲዎች በጥራት ያለመፈፀም እና የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ ነው። በባለሀብቱ በኩል ያለው የማስፈጸም አቅም ማነስ ችግር ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል እንዳያመርት አድርጎታል። አንድ ባለሀብት ብዙ ገንዘብ አውጥቶ የገነባውን ፋብሪካ የተማረና አቅም ያለው ሠው እንዲመራው ከማድረግ ይልቅ የትምህርት ደረጃው ብቁ ያልሆነን ዘመዱን በማስቀመጥ ወደ ኪሳራና ብክነት ይገባል፤ ይህ መስተካከል አለበት።
በድሬዳዋ ከተማ ስላለው የኢንዱስትሪ ዘርፍ አቅም፣ የዘርፉ ልማትና እንዲሁም የከተማዋ አስተዳደር ስለሚያደርገው ክትትልና ድጋፍ ማብራሪያ የሰጡት የከተማዋ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ ድሬዳዋ ለኢንቨስትመንት የተመቸች እንዲሁም አመራሩም ባለሀብቱን በቅርበት የሚከታተልና የሚደግፍ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከተማዋ ለጅቡቲ ወደብ ቅርብ እንዲሁም ለባቡር ጭነት አገልግሎት የተመቸች መሆኗን ከንቲባው ጠቅሰው፣ ይህም ከተማዋን ለባለሀብቱ ሥራ እጅግ ተመራጭ እንዳደረጋት ይገልጻሉ። በዚህም ምክንያት በቅርብ ዓመታት ውስጥ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ በመግባት በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ መሰማራታቸውን ይጠቅሳሉ።
የተለያዩ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ በማድረግ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአምራች ኢንዱስትሪው የውሃ እና የሲሪንጅ ማምረቻ ፋብሪካ፣ ሆስፒታል፣ ሆቴሎች እና ሌሎች ፋብሪካዎች ተገንብተው ሥራ መጀመራቸውን ከንቲባው ገልጸዋል። የከተማው ሕዝብ የሠላሙ ዘብ በመሆን ለባለሀብቱ ኢንቨስትመንት ጥበቃና እንክብካቤ ያደርጋልም ብለዋል።
የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት በብዙ ርቀት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ለወቅቱ የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ የማምረት አቅምን ማጎልበት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ የመፍትሄ አቅጣጫ ነው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2014