በዛሬው ሳምንታዊው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1960ዎቹ በጋዜጣው የወጡ አሁን ካለንበት ዘመን ጋር የሚመሳሰሉ ሁነቶችን የያዙ ዘገባዎችን ለመቃኘት ሞክረናል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች ጌም ዞን በሚል በኮምፒውተር ስፖርታዊ ውድድሮችን በማጫወት ገንዘብ የሚቀበሉ እየተበራከቱ መምጣቸው ይታወቃል። ጌም ዞኖች በየህንጻዎቹ መስፋፋታቸውን የተመለከተ አጫዋቾቹ ገበያ እንደደራላቸው መረዳት ይችላል። ጨዋታው ግን ብዙውን ወጣት ብኩን እያደረገው ነው። ባለፉት አመታት መገናኛ ብዙሃን የሰሯቸውን ዘገባዎች ተከትሎ አንዳች ለውጥ ይመጣል ተብሎ ቢጠበቅም የታየ ለውጥ የለም።
በ1963 በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣም ያንኑ ዘመን የሚመስል የቁማር መሣሪያ ተስፋፍቶ አንደነበር የወቅቱ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ይህ ሁኔታ ያሳሰበው የወቅቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መሳሪያዎቹ እንዲወገዱና እንዲታገዱ መመሪያ አስተላልፎ ነበር። ይህንና ሌሎች ዘገባዎችን ለዛሬ ይዘናል፤ መልካም ንባብ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቁማር መሣሪያ እንዲወገድ አዟል
አዲስ አበባ፡(ኢ-ዜ-አ) የኪሣራ (የቁማር) መጫወቻ መሣሪዎች ‹‹ ሕዝቡን በኢኮኖሚ ረገድና በማኅበራዊ ኑሮ በኩል የሚጎዱ›› በመሆናቸው እነዚህ መሣሪያዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡና የገቡትም መሥራት እንዲያቆሙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከዚህ በፊት ወስኖ እንደነበር ትናንት በድጋሚ ተረጋገጠ።
በዚህ ውሳኔ መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ሚያዝያ ፭ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ/ም/ የተባሉት መሣሪያዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ፤ የገቡትም እንዳይሠራባቸው በማሳሰብ ለአገር ግዛት ሚኒስቴርና ለገንዘብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ትእዛዝ አስተላልፎ ለተባሉት መሥሪያ ቤቶች ከተጻፈው ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል።
እንዲሁም ከዚህ ቀደም መሣሪያዎቹን ያስመጡ የነበሩት ነጋዴዎች ፈቃድ እንዲታገድና ለሌላም ሰው የአስመጪነት ፈቃድ እንዳይሰጥ ለሁለቱም መሥሪያ ቤቶች የተሰጠው የተጻፈው ትዕዛዝ አመልክቷል።
የቁማር (የኪሣራ) መጫወቻ መሣሪያዎች ‹‹ ሕዝቡን በኢኮኖሚ ረገድ በማኅበራዊ በኩል የሚጎዱ ሞራልንም የሚነኩ›› በመሆናቸው ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው እንዲታገድ በማለት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሃሳብ የቀረበው የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑ በደብዳቤ ውስጥ ተገልጧል።
የሕግ መምሪያ ምክር ቤት በትናንት በስቲያ ስብሰባው እነዚሁ የኪሣራ መጫወቻ መሣሪያዎች የመንግሥት ቀረጥ የማይከፈልባቸውና ለሕዝብ ኢኮኖሚ ጠንቅ ሆነው በመገኘታቸው ከመሥራት እንዲታገዱ አሳስቦ ነበር።
ይሁን እንጂ አስፈጻሚው ክፍል ከዚሁ ጊዜ ቀደም ብሎ በጉዳዩ አስቦበት ለሚመለከታቸው ክፍሎች ሁሉ አስፈላጊውን ትዕዛዝ መስጠቱ ትናንት ተረጋግጧል።
(ግንቦት 5 ቀን 1963 ዓ.ም)
በአዲስ አበባ የመኪና ሌባ ቁጥር ቀንሷል ተባለ
በአዲስ አበባ ከተማ ገንኖ ይወራ የነበረው የመኪና ስርቆት በጣም እየቀነሰ መሔዱን በከተማ ከሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች አብዛኞቹ ትናንት ገልጠዋል።
የመካከለኛንና የእንጦጦ ወረዳዎች ጉዳይ የሚመለከታቸው የ፪ኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ሻምበል ያደቴ ጉርሙ ከአለፈው ጥር ወር ጀምሮ እስካሁን ‹‹ መኪና ጠፋብኝ ››ብሎ ያመለከታቸው ሰው አለመኖሩን አመልክተዋል። ‹‹እንደሌላው ሌብነት በአዲስ አበባ በርክቶ የነበረው የመኪና ሥርቆት ከመስከረም እስከ ጥር ወር ድረስ ነበር።
በአራቱም ወሮች በብዙ ሺህ ብር የሚገመት ዕቃ ያወላለቀባቸው መኪናዎች በየጎዳናው በየጫካው ወድቀው ተገኝተዋል። ውብ የነበረ አካላቸው ፈራርሶ ከዐይን እስከ እግር እንዲሁም እስከ ውስጣዊ ዕቃ እያጡ ኮፈናቸው ብቻ ወድቆ ይገኝ የነበረበት ጊዜ አሁን የለም። ከሌቦቹ ቴክኒክ የኛ ፖሊሶቹ ቀድሞ ተገኝቷል ›› በማለት አዛዡ አረጋግጠዋል።
ከታኅሳስ እስከ ጥር ወር በአንድ ወር ብቻ ሰባት መኪናዎች በሁለቱ ወረዳዎች ተሠርቀው በከፍተኛ ምርመራ ተገኝተዋል። ከሰባቱ ሰዎች ሁለቱ ሲለቀቁ አምስቱ አሁንም በቀጠሮ ወህኒ ቤት ገብተዋል።›› ብለው ሻምበል ያደቴ ጉርሙ መግለጣቸውን ሲቀጥሉ ‹‹ መኪና ፈንጋዮች ዕድሜያቸው ከ፲፩ – ፳ የሚገመት ነው ብለዋል።
የአራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ምክትል አዛዥ ሻምበል ሉል ሰገድ የመኪና ሌባ በአዲስ አበባ መቀነሱን ገልጠው ዝርዝር ጉዳዩን ለማብራራት አስቸኳይ ስብሰባ የገጠማቸው መሆኑን አመልክተዋል።
ከዚህ ቀደም መኪና ጠፋባቸው ከተባሉት ፲፰ ሰዎች አራቱን ብቻ ለማግኘት ተችሏል። አራቱም መኪናቸውን ትኩር ብሎ የሚያይ ሁሉ ቀምቷቸው የሚሄድ እየመሰላቸው እንደገና ወደ ቆመበት ተመልሰው መስኮቱንና መዝጊያውን እንደሚፈትሹ አረጋግጠዋል። አንዳንዶቹ መኪናቸው ስትነካ የሚያስጠነቅቅ ጡሩምባ ማስገባታቸውን ገልጠዋል።
(ግንቦት 12 ቀን 1963 ዓ.ም )
በሎተሪ ቲኬት በሬ የገዛ 6 ወር ተፈረደበት
ሐረር (ኢ/ዜ/አ) የብሔራዊ ሎተሪ ቲኬት የ፻ ብር ኖት ነው በማለት አታሎ በሬ የገዛበት በ6 ወር እሥራት እንዲቀጣ ተበይኖበታል። ሲራጅ የሱፍ የተባለው ይኸው ሰው ይህን የማጭበርበር ወንጀል የፈጸመው በሐረርጌ ጠ/ግዛት በበደኖ ወረዳ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፷፪ ዓ.ም ነው።
ተከሳሹ ድርጊቱን የፈጸመው ቁጥሩ 04905 በሆነ የብሔራዊ ሎተሪ ትኬት ነው። በትኬቱ የ፻ ብር ኖት ነው በማለት በ፷፭ ብር ሒሳብ ከአሕመድ ዑስማን ላይ በሬውን ከገዛ በኋላ፤ ቀሪውን ፴፭ ብር በሌላ ጊዜ የሚወስድ መሆኑን አስረድቶ በሬውን ይዞ ሔደ። ከዚያም የገዛውን በሬ ለሌላ ሰው በ፶ ብር ሸጧል።
በሎተሪ ትኬት በሬውን የሸጠው አህመድ ዑስማን በዚሁ ትኬት ዚንጐ ቆርቆሮ ለመግዛት ቢጠይቅ፤ የተታለለ መሆኑ ተነገረው፤ አህመድ ወዲያውኑ ጣቢያ ሔዶ ሁኔታውን በመዘርዘር ስለአመለከተ፤ አጭበርብሮ ለመጠቀም የሞከረው ሲራጅ የሱፍ ወዲያው ተይዟል።
ምርመራውም በፖሊስ ጣቢያ እንደተጣራ ተከሶ በደኖ ወረዳ ፍ/ቤት ቀርቦ ለፍ/ቤቱ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል፤ ድርጊቱን መፈጸሙን አምኖ ይህንንም ለማድረግ የተገደደው ሌላው ሰው በ፻ ብር አንድ በሬ ገዝቶት ፶ ብር ጥሬ ገንዘብና ይህንኑ የብሔራዊ ሎተሪ ትኬት የሰጠው መሆኑን በማረጋገጥ ተናግሯል።
እንዲሁም ድርጊቱን ለመፈጸሙ በህግ ምስክሮች የተረጋገጠበት ስለሆነ፤ ፍ/ቤቱ መጋቢት ፳፪ ቀን ፷፪ ዓ.ም.ባዋለው ችሎት ፮ ወር በይኖበታል ሲል አንድ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ገልጧል።
/መጋቢት 30 ቀን 1962 አም/
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2014