ለ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የስታዲየሞችን ደረጃ እየገመገመ የሚገኘው የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን/ ካፍ/ የባህር ዳር ስታዲየምን በድጋሚ ገምግሞ ስታዲየሙ ጨዋታዎችን የማስተናገድ አቅም ላይ አለመድረሱን መግለጹን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። ኢትዮጵያ ይህን ተከትሎ በሜዳዋ ማከናወን ያለባትን የማጣሪያ ጨዋታዎች በሌሎች ሃገራት ሜዳ ላይ የምታከናውን መሆኑን ገለጸ።
በርካታ ስታዲየሞችን በመገንባት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ግንባታቸው በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቁ አለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም ላይ አልደረሱም። በመሆኑም የአፍሪካ እግር ኳስን የሚመራው አካል /ካፍ/ ለባህርዳር ስታዲየም ጊዜያዊ ፈቃድ በመስጠት ውድድሮች ሲደረጉበት መቆየቱም ይታወሳል። በዚህም ስታዲየሞቹ መሟላት ያለባቸውን እንዲሟሉ ግንባታና እድሳት ላይ ያሉትም በሂደት እንዲጠናቀቁ እድል መገኘቱም ይታወቃል።
ይሁንና እድሳቶቹ እሱ ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት እየተፈጸሙ አለመሆናቸውን ካፍ በመጥቀስም በጥቅምት ወር/2014ዓ.ም መስፈርቶቹ እስኪሟሉ ድረስ ኢትዮጵያ በሜዳዋ የምታደርጋቸው ጨዋታዎችን በገለልተኛ ሀገር እንድታከናውን ወስኖ በዚሁ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም መሰረት ከዚህ ቀደም ጨዋታዎች ሲደረጉበት የቆየው የባህርዳር ስታዲየም የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ በድጋሚ ወደ ውድድር እንዲገባ ለማድረግ ሲሞከር ቆይቷል። ከእገዳው በኋላም በአማራ ክልልላዊ መንግሥት የባህር ዳር ስታዲየምን በማሻሻል ውድድር የማስተናገድ ፈቃዱን መልሶ እንዲያገኝ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ፌዴሬሽኑ ጠቁሞ ነበር።
ከመጫወቻ ሜዳ፣ የመገናኛ ብዙሃን ክፍል፣ የቪአይፒ፣ የተመልካች ፋሲሊቲ፣ የህክምና ክፍል እና ተያያዥ ግብዓቶች የተሰሩ ማሻሻያዎች ያሉቡት ሁኔታ በቅርቡ በካፍ በተወከለ የባለሙያዎች ቡድን ምልከታ ተደርጎበታል። ምልከታውን ተከትሎም ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር የምታደርገውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታን ጨምሮ በቀጣይ በሜዳዋ የምታደርጋቸው ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንድታከናውን የሚያስችላት ግብረመልስ ሲጠበቅ ቆይቷል።
ካፍ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው ሰባት ገጽ ያለው ሪፖርት ኢትዮጵያ የማጣሪያ ጨዋታዎችን በሜዳዋ የማስተናገድ አቅም እንደሌላት ማስታወቁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል። በቀጣይ የሚካሄዱ ጨዋታዎችም በየትኞቹ ሃገራት ሜዳዎች ለማድረግ እንደታቀደ እስከ ግንቦት 4 ድረስ እንዲያሳውቅም መጠየቁን አስታውቋል። በመሆኑም በቀጣዩ ዓመት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የሚደረጉት የማጣሪያ ጨዋታዎች በሌሎች ሃገራት ሜዳ ላይ የምታከናውን መሆኑን ፌዴሬ ሽኑ አረጋግጧል።
ሃገሪቷ በማጣሪያው የምድብ ድልድል በምድብ አራት ከግብጽ፣ጊኒ እና ማላዊ ጋር መደልደሏ ይታወቃል። እነዚህ ጨዋታዎች በደርሶ መልስ የሚካሄዱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሶስቱን የመልስ ጨዋታዎች በተለዋጭ ሜዳዎች ላይ የሚያደርግ ይሆናል።
በቀጣይ ሊደረጉ ስለሚገቡና ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት መሟላት ስለሚገባቸው መስፈርቶችም ካፍ በላከው ሪፖርት ተጠቁሟል። በዚህም መሰረት የመጫወቻ ሜዳውን በሚመለከት ሳሩ በአዲስ እንዲተካና በዘርፉ በሚሰራ አካል እንክብካቤ እንዲደረግለት፣ ተንቀሳቃሽ ግቦች እንዲኖሩት፣ የጨዋታ አመራሮች እና የአሰልጣኞች ስፍራ አለም አቀፍ ደረጃን ያማከለ እንዲሆን እንዲሁም የምሽት መብራትን የሚያካትቱ ስራዎች እንዲከናወኑ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ታውቋል።
የመልበሻ ክፍልን በሚመለከትም የካፍን መስፈርት እንደማያሟላ ሪፖርቱ አመልክቶ፣ ሙሉ ለሙሉ እንዲቀየር፣ የማሟሟቂያ ክፍሉ በሰው ሰራሽ ሳር እንዲተካ፣ የካፍ ቢሮ እንዲታደስ እንዲሁም የኳስ አቀባዮችና ባንዲራ የሚይዙ ታዳጊዎች ክፍል እንዲዘጋጅም በሪፖርቱ ተመላክቷል። ከህክምና ክፍል ጋር በተያያዘም አስፈላጊ የሆኑ 23 ቁሳቁሶች እንዲሟሉ፣ የአበረታች ንጥረነገሮች መቆጣጠሪያ ክፍል ከመልበሻው አቅራቢያ እንዲሆንና አስፈላጊ ሁኔታዎች እንዲሟሉም ካፍ አሳስቧል።
ተመልካቾችን በሚመለከትም ጣሪያ፣ ወንበር፣ የመዝናኛ፣ የደህንነትና የመቆጣጠሪያ፣ የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና መስጫ፣ ግዙፍ ስክሪን እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች አመቺ ሆኖ መዘጋጀት እንዳለበት ተገልጿል። የክብር እንግዶች ክፍልም ምቾት ባለው ሁኔታ እንዲዘጋጅ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ክፍል አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎች እንዲሟሉ እና ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥባቸው ስፍራዎች መካተትም እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።
የልምምድ ሜዳውም መብራት እና ቢያንስ አንድ ቡድን ማስተናገድ የሚችል ክፍል ያለው እንዲሆን፣ የአንቡላንስ አቅርቦት እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ መግቢያና መውጫ እንዲኖረውም ተመላክቷል።
በሪፖርቱ የባህርዳር ስታዲየም ለሆቴል እና ሆስፒታል ያለው ቅርበት በመስፈርቱ መሰረት በቂ መሆኑም ተጠቁሟል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የአማራ ክልል መንግሥት ስታዲየሙ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ሲያደርግ ለቆየው ከፍተኛ ጥረት ምስጋናውን አቅርቦ፤ በቀጣይም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሃገሩ እንዲጫወት ጥረት ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 /2014