የፊፋ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በተከፈተ ቁጥር የታላላቆቹ አውሮፓ ክለቦች ገበያ ሁሌም የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ እንደገዛ ነው። ከዚህ የደራ የተጫዋቾች የዝውውር ገበያ ጀርባ ሆነው የሚዘውሩ ሁለት ሰዎች በዓለም ላይ ገናና ስም ይዘው መነሳታቸው አይቀርም። ሆርጌ ሜንዴዝና ሚኖ ራዮላ።
እነዚህ ስመ ጥር የተጫዋች ወኪሎች በታሪክ የታላላቅ ተጫዋቾች ዝውውር ላይ እጃቸው ማረፉ ብቻ ሳይሆን የአለማችን ከዋክብት ተጫዋቾች እጣ ፋንታ በእጃቸው ላይ መሆኑ በእግር ኳሱ ዓለም ብርቱ ክንድ እንዲኖራቸው አስችሏል። ባለፈው ሳምንት ግን አንዱ ዝነኛና ቱጃር የተጫዋቾች ደላላ ሚኖ ራዮላ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ተሰምቷል።
የአውሮፓን እግር ኳስ የሚዘውረው ቱጃር ‘ደላላ’ ማን ነበር? የዛሬው ስፖርት ማህደር አምዳችን ከብዙ በጥቂቱ ዳሶታል። ሚኖ” በተሰኘ ቅፅል ስሙ ይታወቃል፤ የሆላንድና ጣልያን ጥምር ዜግነት ያለው ካርሚን ራዮላ በተጫዋቾች የረጅም አመት የድለላ ሕይወቱ የታዋቂዎቹ ፖል ፖግባ፣ ዝላታን ኢብራሂሞቪች፣ ሄንሪክ ሚኪታሪያንና ዴ ሊት የመሳሰሉ ከዋክብትን የዓለምን ክብረወሰን በሰበረ የዝውውር ገንዘብ ጭምር በመሸጥ ትልቅ ስም ያለው ወኪል ነው።
ይህ እሳት የላሰ ደላላ ጣልያን ተወልዶ በኔዘርላንድስ ሃርለም ከተማ እንዳደገ ይነገርለታል። ከትንሽ ሕይወት ተነስቶ የአለማችንን ውድና ድንቅ ከዋክብት ተጫዋቾች ከትንሽ ተነስተው ትልቅ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ያደረገ ‘ምርጥ ደላላ’ ነው ሲሉም ብዙዎች ይመሰክሩለታል።
ሚኖ በልጅነቱ አባቱ በከፈቱት ሬስቶራንት ውስጥ ደፋ ቀና ብሎ አስተናግዷል። ጎን ለጎንም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በመከታተል በሕግ መመረቅ ችሏል።
ዛሬ ላይ ዓለም እንዲያውቀውና የታላላቅ ክለቦችና ተጫዋቾችንም እጣ ፋንታ እንዲወስን ወዳደረገው ስራም በሂደት ነው የገባው። ሚኖ ለአንድ የተጫዋቾች ወኪል ድርጅት ተቀጥሮ ይሠራም ጀመር። የመጀመሪያው ሥራ የሆነው ደግሞ ተስፋ የሚጣልባቸውን ታዳጊ ኔዘርላንድስ ተጫዋቾችን ለጣልያኑ ሴሪ ኤ ማሻሻጥ ነበር። ሚኖ በሂደት ተቀጥሮ ይሠራበት የነበረበትን ድርጅት ለቆ የራሱን የውክልና ድርጅት ሊያቋቁም ቻለ።
ጣልያንኛ፣ ጀርመንኛ፣ ስፓኒሽ፣ ፈረንሳይኛ፣ ፓርቹጊዝ፣ ደች እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ መናገሩም የኋላ ኋላ ለድለላ ሕይወቱ ትልቅ ሚና አበርክቶለታል። ገና የ18 ዓመት ለጋ ሳለ በኔዝርላንድስ ውስጥ የሚገኝ አንድ የታዳጊዎች እግር ኳስ ኃላፊ ሆኖ መስራቱም ለስኬታማ የድለላ ስራው ትልቅ ፋይዳ ነበረው።
በታዳጊነታቸው በሚኖ ደላይነት ወደ ጣልያን ብሎም ወደ እንግሊዝ ክለቦች አቅንተው ስማቸውን በጉልህ መፃፍ ከቻሉ ተጫዋቾች መካከል የቀድሞው የአርሰናል ታሪካዊ ተጫዋች ዴኒስ ቤርግካምፕ ሳይጠቀስ አይታለፍም። በቼክ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ቡድን ባሳየው ድንቅ ብቃት የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ዓይን አርፎበት የነበረው ፓቬል ኔድቬድ ከስፓርታ ፕራግ ወደ ላዚዮ እንዲዛወር በማድረግም ሚኖ ይታወሳል። አሁን ላይ አውሮፓ ውስጥ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች ትልልቅ ስም ያላቸው ከሃያ በላይ ኮከቦች ውክልናቸው የሟቹ ሚኖ ነው።
ሚኖ እኤአ 2016 ላይ የሰራው ታሪክ በብዙዎች ዘንድ ዛሬም ድረስ ይታወሳል። በወቅቱ የዓለም ክብረወሰን በነበረ ዋጋ ፖል ፖግባን ከዩቬንቱስ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ እንዲዛወር ያደረገ ሲሆን ዋጋውም 105 ሚሊዮን ዩሮ ነበር። ሚኖም ከዚህ ዝውውር 25 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወደ ኪሱ እንዳስገባ ይነገራል። እኤአ 2017 ላይ ሮሜሉ ሉካኩ ከኤቨርተን ወደ ማንችስተር ዩናይትድ በ75 ሚሊዮን ፓዎንድ፣ እኤአ 2019 ላይ ማቲያስ ዲ ላይት ከአያክስ ወደ ጁቬንቱስ በ67 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓዎንድ የፈረሙበት ታሪክ በሚኖ የድለላ ዘመን ዝነኞቹ ናቸው።
ታላላቆቹን የአውሮፓ ክለቦች በስሙ ብቻ የሚያስደነብረው ሚኖ፣ የሚኖ ስም በእርሱ ውክልና ሥር ያሉ ተጫዋቾችን እንዳሻው ማዟዟር መቻሉ ትልቅ ሀይል ሆኖታል። ይህም ያሻውን ከመናገር ወደኋላ የማይል አድርጎታል። “አትንኩኝ” ባይ መሆኑ የሚነገርለት ሚኖ በእርሱ ውክልና ሥር ያሉ ተጫዋቾችን የሚተቹ የቀድሞ እግር ኳስ ኮከቦችም ሆኑ ተንታኞችን በመወረፍ ይታወቃል።
በአንድ ወቅት ሚኖ በጣልያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከውክልና ሥራ መታገዱን ተከትሎ ፊፋም የጣልያን አቻውን ፈለግ በመከተል ራዮላ ላልተወሰነ ጊዜ ከወኪልነት ሥራው እንዲታገድ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። የጣልያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ውሳኔ ለምን እንዳስተላለፈ ግልፅ ያልነበረ ቢሆንም ሚኖ «እገዳው ብርቅ አልሆነብኝም። እኔ ያልተመቸኝ ውሳኔው ፖለቲካዊ መሆኑ ነው» ሲል ተደምጧል። አክሎም «የጣልያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአገሪቱን ኳስ ወደኋላ አስቀርቷል ብዬ የተናገርኩት ነገር ሳትቆረቁራቸው አልቀረችም፤ በአገሪቱ ስላለው የእግር ኳስ ዘረኝነት ጉዳይ አሳስቦኛል ማለቴም ይቅርታ ሳያስነፍገኝ አይቀርም» ሲል መሳለቁ ይታወሳል።
በወቅቱ ይህ ውሳኔ ያስደሰታቸው ቢኖሩም የሚኖ መታገድ ለአንዳንድ ክለቦች ትልቅ እንቅፋት ፈጥሮ ነበር። ሚኖ እገዳው ተጥሎበት የነበረው የአውሮፓ እግር ኳስ የዝውውር ገበያ በሚደራበት ወቅት መሆኑ በጊዜው ፖል ፖግባን መግዛት ይፈልጋሉ ከሚባሉት ሪያል ማድሪዶች ጀምሮ የአያክስ ወጣቶችን ለመቀራመት የቋመጡ ክለቦች የራስ ምታት ሆኖባቸው ነበር።
ሚኖ እውቅ የተጫዋቾች ወኪሎችን የሚወክለው ‘ፉትቦል ፎረም’ ፕሬዝደንት ነበር። ፎርብስ የተሰኘው የቢዝነስ ጋዜጣ 2018 ላይ ባወጣው ዘገባ ሚኖ ስልሳ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር አመታዊ የተጣራ ገቢ እንደነበረው አስቀምጧል። በእርሱ ውክልና ሥራ ያሉ ሰባ ተጫዋቾች ብቻ 629 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጡ እንደሚችሉም ጠቁሟል።
በሃምሳ አራት አመቱ ባለፈው ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ሚኖ፣ ከፖል ፖግባ ዝውውር በኋላ በአሜሪካዋ የባህር ዳርቻ ግዛት ማያሚ ዘጠኝ ሚሊየን ዩሮ በማፍሰስ በገዛው የመኖሪያ መንደር ቅንጡ ሕይወት ይመራ ነበር።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30 /2014