ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረኮች ተሳትፎዋ ከሰበሰበቻቸው 58 ሜዳሊያዎች መካከል 18 የሚሆኑት (10 የወርቅ፣ 3 የብር እና 5 የነሃስ) ሜዳሊያዎች የተቆጠሩት የሯጮቹ መፍለቂያ ምድር በቆጂ ባፈራቻቸው አትሌቶች ነው። የስፖርታዊ ውድድሮች ሁሉ በኩር የሆነው ኦሊምፒክ እንደ ማሳያ ተነሳ እንጂ በቆጂ ያበቀለቻቸው በርካታ አትሌቶች የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ጨምሮ በተለያዩ ውድድሮች ላይ አገራቸውን አኩርተዋል። በማህጸነ ለምለሟ በቆጂ አሁንም በርካታ ታዳጊዎች ራሳቸውን ሊቀይሩ፣ አገራቸውን ሊያኮሩ በመሮጥ ላይ ይገኛሉ።
በቆጂን የአየር ሁኔታዋ፣ የቦታ አቀማመጧ እንዲሁም የአኗኗር ሁኔታው ተዳምሮ የአትሌቶች ምንጭ አድርገዋታል። ይህንን የተረዱና ለአትሌቲክስ ስፖርት ልዩ ፍቅር ያላቸው በርካቶች ይጎበኟታል፤ የውጭ አገራት አትሌቶችም ለልምምድ ብቅ ይሉባታል። የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ጥናት ከማድረጋቸው ባለፈ አትሌቶችን እና አሰልጣኞችን በተናጠል እንዲሁም ስለ በቆጂ የፊልም ባለሙያዎች ‹‹የሯጮቹ ምድር›› በሚል ርዕስ ዘጋቢ ፊልም ሰርተውለታል።
ይህም መልካም ዕድል ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እንደ ቱሪዝም መስህብ ሳይቆጠር አገሪቷም በቆጂም ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል። አሁን ግን የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር አገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሳወቀ ካለው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በበቆጂ የሩጫ መርሃ ግብር መዘጋጀቱ ተሰምቷል።
በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን የምትገኘው በቆጂ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ከፍ ብላ እንድትጠራ ያደረጉ ስመ ጥር ዓለም አቀፍ አትሌቶችን ያፈራች ከተማ መሆኗ አትሌትክስን ለማበረታታት እና ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የበለጠ ተመራጭ ያደርጋታል። ይህን መልካም ዕድል ወደ ተሟላ አገር አቀፍ ስኬታማነት ለመቀየር እንዲረዳም በቆጂን ማዕከል ያደረገ አገር አቀፍ ፕሮግራም ለማካሔድ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኙም ተቋማቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር መርሃ ግብርም ‹‹ኢትዮጵያ ትሮጣለች›› በሚል መሪ ቃል በበቆጂ ከተማ ግንቦት 6 እና 7/2014 ዓ.ም ያካሂዳል። የዝግጅቱ ዋና ዓላማም የስፖርት ቱሪዝምን በተለይም የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ነው። የእውቅ ዓለም አቀፍ አትሌቶች መፍለቂያ የሆነችውን በቆጂ ከተማን ለማስተዋወቅ እና ከተማዋ እንድትነቃቃ ከማድረግ ባለፈም ለአዳጊ አትሌቶች ጥሩ የመወዳደሪያ መድረክ ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም መግለጫው ጠቁሟል።
በመርሃ ግብሩ ላይም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚከናወነው ታላቁ ሩጫ በበቆጂ ጎን ለጎን በአርሲ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ የተራራ መውጣት፣ የብስክሌት ውድድር እና በስመጥሯ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የተሰየመው ‹‹ጥሩነሽ ዲባባ ሻሚፒዎንሺፕ›› ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ የአትሌቲክስ ሰልጣኞች መካከል ውድድር ይደረጋል። በዚህም ላይ ታዋቂ አትሌቶች፣ የበቆጂ እና አካባቢው ነዋሪዎች እና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚጓዙ ጤናቸውን ለመጠበቅ የሚሳተፉ ሯጮቾን ጨምሮ 1ሺ200 ሰዎች ይሳተፋሉ የሚል ዕቅድ ተይዟል።
የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ በቆጂና አካባቢውን የሚገልጽና የቱሪስት መስህብ የሚሆን መለያ ምልክት (land mark) የሚያስቀምጥ ይሆናል። በተጨማሪም ለኬንያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ የረጅም ርቀት አሸናፊዎችን በማፍራት የሚታወቀው ‹‹ኤልዶሬት›› ከተማ ከበቆጂ ጋር የከተሞች እህትማማችነትን ለመመስረት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ታዋቂ ከሆኑት ውድድሮች አንዱ የሆነው ‹‹ኤልዶሬት ሲቲ ማራቶን›› የ2014 ታላቁ በቆጂ ሩጫ ላይ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች በሚቀጥለው ዙር በኤልዶሬት ከተማ ተገኝተው የውድድሩ ተጋባዥ ተወዳዳሪዎች እንዲሆኑም ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
ይህ ዕድል በተለይ ታዳጊ አትሌቶች የተሻለ ተሞክሮ እንዲቀስሙ ከመርዳቱም በላይ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ የመወዳደር ልምድ እንዲያካብቱ ይረዳል። በተጨማሪም የሁለቱን ከተሞች እህትማማችነትን በማጠናከር የቱሪዝም ፍሰትን እንደሚጨምር ይጠበቃልም ተብሏል በመግለጫው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 /2014