በዛሬው አዲስ ዘመን ዱሮ ዓምዳችን በ1962 አ.ም የወጡ እትሞች አገላብጠን ብትናቧቸው መልካም ነው ያልናቸውን ዘገባዎች ይዘን ቀርበናል። ዘገባዎቹ አሁን ካለንበት የኑሮ ውድነትና ህገወጥ ግብይት ጋር የተያያዙ መሆናቸው ቀልባችንን ይበልጥ ስቦታል፤ አንዱ ዘገባ ከአንድ ግለሰብ የተላከ ጽሁፍ / የግል አስተያየት/ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ ዜናዎች ናቸው። መልካም ንባብ።
በአገራችን የዘይት ተፈላጊነት
በአገራችን በየጊዜው በዘይቶች ላይ እየጨመረ የሚሔደው ዋጋ በጠቅላላ የኢትዮጵያን ሕዝብ በተክል ቅባት (ዘይት) እንዲጠቀም አስገድዶታል። እንደዚሁም በየዓመቱ የሚመላለሱቱ የጾም ወራቶች ማለት እንደ ዐቢይ ጾም ያሉት በእህል ዘይት መጠቀምን ይጠይቃሉ። የወደፊት የዘይት ሥራን ለማስፋፋት በአሠራሩም በአመራረቱም ረገድ ታላቅ ተስፋ ሊጣልበት ከሚችሉ አንዱ የገቢ ምንጭ ነው።
በእህል ዘይት በኩል ኢትዮጵያ ራስዋን የቻለች እንደምትሆን የተረጋገጠ ነው። በአገራችን ውስጥ የእህል ቅባት አወጣጥ ዘዴ ጎጃም በጣም የተመሰገነ ነው። ኢትዮጵያ በትንሹ የወይራ ዘይት ከውጭ አገር ታስመጣለች። እንደዚሁም ሆኖ ለተክል ቅባት (ዘይት) ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመሄዱ የእህል ዘይት ተፈላጊነት በማናቸውም ዘንድ ታውቋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለምግብ የሚሆነውን ዘይት የሚያወጣው ከዘራቸውና ከአመረታቸው የእህል ዓይነቶች ነው። እንደዚህም የእህል ዓይነቶች ኑግ፤ ተልባና ሱፍ፤ ሰሊጥ ናቸው።
የቅባት እህላችን ኢትዮጵያ ወደ ውጭ እንደመላኩዋ መጠን፤ የነጠረ ዘይት ወደ ውጭ አትልክም። ምክንያቱም የአገራችን ገበሬዎች ለዘይት ማውጫ የሚሆኑትን የእህል ዓይነቶች በብዛት ስለሚያመርቱና ለገበያ ስለማያወጡ ብቻ መሆኑ ተረጋግጧል። በአገራችን ላይ አሁን በብዛት የሚገኙት የእርሻ መኪኖች ለዘይት መውጫ የሚሆኑትን የእህል ዓይነቶች በብዛት እንዲገኝ የሚያስችሉ ሆኗል። ምንም እንኳ ሲሴም የሚባለው ተክል በብዛት በአገራችን ላይ ባይገኝም፤ እንደነዚህ ያሉት ተክሎች፤ ጥሩ ዘይት የሚያስገኙ መሆናቸው ስለተገመተ፤ በብዛት ገበሬ እንዲዘራቸው ተደርጓል። የጥጥ ፍሬ ዘይት የሚያስገኝ ሆኖ ስለተገኘ ተንዳሆ ከሚገኘው የጥጥ አዝመራ በብዛት ለማግኘት ይችላል። የጐመን ዘር፤ የጉሎ ፍሬ የጥጥ ፍሬ ከሳር ዘሮች ተልባ በኢትዮጵያ ለዘይት ማውጫ የሚሆኑና በይበልጥ ጠቃሚ ሆነው የተገኙ ናቸው። ከእነዚህም ሌላ ፩ኛ. ሰናፍጭ ፪ኛ.ኑግ ፫ኛ.ለውዝ ፬ኛ.የዱባ ፍሬ ፭ኛ. ሱፍ ለዘይት ማውጫ በብዛት ይጠቅሙናል።
(መጋቢት 8 ቀን 1962 ዓ.ም )
በጐጃም ጠቅላይ ግዛት በሀሰት የሚሠራባቸው 182 ሚዛኖች ተያዙ
ደብረ ማርቆስ፡(ኢ/ዜ/አ/) በጐጃም ጠቅላይ ግዛት በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቅርንጫፍ መ/ቤት 182 ሚዛኖች ሀሰተኛ የሸቀጣ ሸቀጥ መመዘኛዎች እንዳይሠራባቸው ማድረጉን አቶ ገብረ ጻዲቅ ተክለ ጊዮርጊስ በሰጡት መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።
የጠ/ግዛቱ ቅርንጫፍ መ/ቤት ረዳት አላፊ አቶ ገብረ ጻዲቅ ከዚሁ በማያያዝ በሰጡት መግለጫ ‹‹እነዚሁ ሐሰተኛ መመዘኛዎች የተያዙት ከደብረ ማርቆስ ከተማ ፶፯፤ ከቡሬ ከተማ ፲፬ ፤ ከባህር ዳር ከተማ ፷፰ ፤ ከዳንግላ ከተማ ፳፪ ፤ ከደጀን ከተማ ፳፩ መሆናቸውን ገልጠዋል።
ከነዚህ መመዘኛዎች መካከል የብረታ ብረት ብሎኖች፤ ጠጠሮች የባትሪ ድንጋዮችና እነዚህን የመሳሰሉ ሕገወጥ መሥፈሪያዎች ይገኙባቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ እውነተኛ ኪሎ ግራም መስለው በሞረድ የተሞረዱና እውነተኛ መስለው የሚታዩ ናቸው። በነዚሁ ሀሰተኛ በሆኑ መመዘኛዎች ሲጠቀሙ የተያዙትም ነጋዴዎች ጥቂቶቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ሲቀጡ፤ ግማሾቹ በክስ ላይ የሚገኙ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ ገብረጻዲቅ ቀጥለውም ሲናገሩ አንዳንድ ዕውነትን የማይከተሉ የጨርቃ ጨርቅ ነጋዴዎች ልክነቱ ያልተረጋገጠ እንጨት ዘርግተው እውነተኛ ሜትር ነው በማለት በማታለል ለሕዝብ ሲሸጡ ተደርሶባቸው፤ ከዚሁ አድራጐታቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ካሉ በኋላ፤ ነጋዴዎችን በሚገባ ለመቆጣጠር ተጨማሪ ሠራተኞችና በተለይ የፖሊስ ረዳት የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጠዋል።
ከዚህም በማያያዝ፤ ሸማቹም ሕዝብ ቢሆን ሚዛን ማወቅና በተለይም ከንግድ ሚኒስቴር ሰዎች ጋር መተባበር ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ የኛው ብቻ ቁጥጥር አጥጋቢ አይሆንም፤ እንዲሁም የምግብ ዘይትና ቅባት የሚሸጡ ነጋዴዎች ትክክለኛውን ሊትር አዘጋጅተው መሸጥ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።
ደላላዎችም እንደዚሁ ከባላገር የሚመጣውን ገበያተኛ እንዳያዋክቡ ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ ጠቅሰው የጥጥ ሻጮችም ቢሆኑ ከወንዝ በሰበሰቡት ድንጋይ እንዳይገበያዩ አደራ ብለዋል።
(መጋቢት 4 ቀን 19 62 ዓ.ም )
ጤፍን ከአሸዋ ቀላቅሎ ያቀረበው 50 ብር ተቀጣ
ደብረ ማርቆስ ፡(ኢ/ዜ/አ/) በጤፍ ውስጥ አሸዋ ቀላቅሎ ለመሸጥ ሲያስማማ የተያዘው ሽፈራው የስጋት 50 ብር መቀጫ እንዲከፍል ተፈረደበት።
ሽፈራው ገንዘቡን መክፈል ባይችል ግን በ፶ ቀን እሥራት እንዲቀጣ የደምበጫ ወረዳ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ውስጥ ባዋለው ችሎት በይኖበታል።
በሽፈራው የስጋት ላይ ይህ የፍርድ ውሳኔ የተሰጠው፤ በሁለት ስልቻ ውስጥ አፈርና አሸዋ ቀላቅሎ ገበያ አውጥቶ ለመሸጥ ከተስማማ በኋላ ሲመዘን 170 ኪሎ ስለሆነ ያለመጠን ክብደት በማምጣቱ በጥርጣሬ ሲፈተሽ አፈርና አሸዋ ቀላቅሎ የተገኘበት መሆኑ ስለተደረሰበት ነው።
(መጋቢት 30 ቀን 1962 ዓ.ም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 /2014