በምግብ ዋጋ መናር የዕለት ኑሮን መቋቋም ያለመቻል ጉዳይ መነጋገሪያ በሆነበት በዚህ ወቅት ስለበልግ የግብርና ሥራ፣እንዲሁም ምርትና ምርታማነቱ የሚገኝበትንና ምርቱ ደርሶ የእለት ኑሮአቸውን ሊያቃልላቸው ይችል እንደሆነ ተስፋ ለማድረግ መረጃው እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሰዎች ጥቂት እንደማይሆኑ እንገምታለን። ይህን ታሳቢ በማድረግም የበልጉ የግብርና ሥራ በምን አይነት መልኩ እየተካሄደ እንደሆነ ትኩረታችንን በልግ አብቃይ ወደ ሆኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አድርገናል። የበልግ መግቢያ ላይ ይጥል የነበረው ዝናብ ዋናው የክረምት ወቅት እስኪመስለን ድረስ ነበር ከባድ እንደሆነ ብዙዎቻችን ስንገልጽ የነበረው፡፡
አሁን ግን ከባዱ ዝናብ በተለይ በከተማ እንደጅምሩ ሳይሆን ቀዝቀዝ ማለቱን ነው ትዝብታችን የሚያሳየው። የእርሻ ሥራ በሚከናወንበት በገጠሩም ቢሆን አጥጋቢ ዝናብ ስለመኖሩ እየሰማን አይደለም። የበልግ ወቅት የሚባለው ከየካቲት እስከ ግንቦት ያሉት ወራቶች በመሆናቸው ዝናቡ ቀጣይነት እንደሚኖረው ተስፋ ይደረጋል። የበልግ ዝናብ አብዛኛውን የሀገሪቱን አካባቢዎች የሸፈነ መሆኑና መዘናጋት ሳይኖር የተገኘውን እርጥበት በመያዝ በአግባቡ ለግብርና ሥራ ማዋል እንደሚጠበቅ ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ማሳሰቡ ይታወሳል። በልግ አብቃይ የሆኑት የደቡብና አማራ ክልሎች ወቅታዊውን ዝናብ ለግብርና ሥራ በማዋል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረጉ ስላለው እንቅስቃሴና በአካባቢያቸው ስላለው ወቅታዊ የአየር ፀባይ መረጃውን አጠናክረን እነሆ ወደእናንተ አድርሰናል፡፡
በልግ ቀድሞ ከሚገባባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አንዱ በመሆኑ በቅድሚያ የክልሉን የግብርና እንቅስቃሴ እንደሚከተለው ቃኝተናል፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹልን፤ ክልሉ ከሌሎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ ቀድሞ ያገኛል። የሚያገኘው ዝናብም ከ60 እስከ 70 በመቶ ይገመታል። የበልግ ዝናብ ቀድሞ በክልሉ የሚገባ በመሆኑ አርሶ አደሩ በልግ አምራች ነው፡፡
ወደ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙት ደቡብ ኦሞ፣ ጎፋ፣ ባስኬቶ፣ ከፊል ጋሞ፣ ኮንሶ፣ደራሼ፣ ታችኛው አካባቢ የሚባሉት ደግሞ ወላይታ፣ ከንባታ፣ ሀዲያ፣ ሀላባ፣ በቅደም ተከተል ዝናብ ያገኛሉ። በዚህ መነሻ የበልግ ዝናብ ከጀመረ አንድ ወር አልፏል። በወቅቱ የተገኘውን እርጥበት ለመጠቀምም አርሶ አደሩ ፈጥኖ ነው ወደ እርሻ ሥራ የገባው። በተከናወነው ሥራም ውጤቱ አንዱ ከሌላው አካባቢ ልዩነት ቢኖርም በአብዛኛው ጥሩ በሚባል ደረጃ እየተከናወነ የሚገኘው። የዘንድሮ የበልግ ወቅት ካለፉት የበልግ የግብርና ሥራዎች ለየት የሚያደርገው እንደ ሀገር በገጠመው የውስጥ ችግር፣ በዓለም ላይ ደግሞ የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ያሳደረው የኢኮኖሚ ተጽእኖና በቅርቡ ደግሞ በሩሲያና ዩክሬይን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት የግብርና ግብአቶችና ምርቶች ዋጋ እንዲንር እንዲሁም ግብአት በበቂ ሁኔታ ላለማቅረብ ምክንያቶች ሆነዋል።
ይህም ማዳበሪያን ጨምሮ የተለያዩ ግብአቶችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ አልተቻለም። የማዳበሪያ አቅርቦት አለመኖር ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ግምት ውስጥ በማስገባት አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ ከመጠቀም ወደኋላ እንዳይልና እንዳይስተጓጎል ያሉትን አማራጮች በተለይም የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲጠቀም የንቅናቄ ሥራ በመስራት ክልሉ የበኩሉን ጥረት አድርጓል። ንቅናቄውን አጠናክሮ በመቀጠልም ውጤታማ ለመሆን እየሰራ ይገኛል።
ሌላው ክልሉ የገጠመው ተግዳሮት የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት መሆኑን ኃላፊው ይናገራሉ። ክልሉ ቀደም ሲል የበቆሎ ምርጥ ዘር ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ከምዕራብ ወለጋ ነበር የሚያገኘው፡፡በዚህኛው የበልግ የእርሻ ሥራ ከአካባቢዎቹ ማግኘት አልቻለም፡፡ እጥረቱ የተፈጠረው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሽመድመድ አልሞ የተነሳው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ትህነግ)በከፈተው ጦርነት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ምዕራብ ወለጋ ውስጥ የነበረው የምርጥዘር ግብአት ሙሉ ለሙሉ በማውደሙ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም ክልሉ የነበረበትን የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት አስተጓጉሎታል።
ክልሉ ቀደም ሲል የያዘውን የበቆሎ ዘር ክምችትና በአርሶአደሩ እጅ የሚገኘውን ጨምሮ አማራጮችን በመጠቀም በበልጉ ያጋጠመውን የበቆሎ ዘር አቅርቦት ችግር ለመፍታት ጥረት ተደርጓል። አቶ ኡስማን እንዳሉት፤ ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ፀጋና ምቹ የሆነ ሥነምህዳር ተጠቅሞ ከሰብል ልማት በተጨማሪ ለሥነምግብ ተመራጭ የሆኑ የሥራሥር ተክሎችን፣አትክልትና ፍራፍሬ የማልማት የቆየ ባህሉን የበለጠ በማጠናከር የበልጉን ወቅት በአግባቡ እንዲጠቀምበትም በንቅናቄው ምክረ ሀሳብ በመስጠት ተጠቃሚነቱ ከፍ የሚልበትን ሁኔታ አመቻችቷል። የበልግ ዝናብ ስርጭትና መጠኑ እየቀነሰ መሆኑ የበለጠ ጥሩ ውጤት እንዳይገኝ ያደርጋል የሚል ስጋት ቢኖርም የበልግ የግብርና ሥራ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥም ሆኖ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል።
ከዚህ በኋላም የሚገኘውን እርጥበት ማሳ ውስጥ በማስቀረት አሟጦ ለመጠቀም አርሶአደሩ ያለውን ግንዛቤ የበለጠ ከፍ እንዲያደርግ የክትትል ሥራዎች ይጠናከራሉ። ክልሉ ያሉትን ክፍተቶች በአማራጭ በማካካስ በበልጉ ዝናብ ለመጠቀም እያደረገ ባለው ጥረት በበልግ ዝናብ በመጠቀም ከስምንት መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማረስ ስምንት አይነት በሚደርሱ ሰብል፣አትክልት፣ፍራፍሬና ስራስሮች ለመሸፈን አቅዶ በመሥራት ላይ ይገኛል። በበልጉ ከሚለሙት ዋና ዋና ሰብሎች መካከል በቆሎና ማሽላ ተጠቃሽ ናቸው። በአንድ ሄክታር በአማካይ ከሁለት መቶ እስከ ሶስት መቶ ኩንታል የሚገኝበት አጋጣሚ በመኖሩ ሰብልን ጨምሮ ከአጠቃላይ የበልግ ግብርና እና የልማት ሥራ ከ70 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ የዝናቡ ሁኔታ ከተስተካከለ የምርት መጨመር ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
በበልጉ ያጋጠሙ ችግሮች በእጅ የሚገኝን ፀጋ ወይንም ሀብት አሟጦ ለመጠቀም እድል በመስጠት ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን የተናገሩት አቶ ኡስማን ‹‹ሳይታይና ሳይመራ የቆየ ነገር ግን አሁን ላይ እየተከናወነ ያለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አዲስ የሥራ ባህል ነው፡፡ነገር ግን መሬቱም ውሃውም ቀድሞ ነበረ፡፡የነበረው ክፍተት ችግሩን ሊፈታ የሚችል ሀሳብ አለመኖሩ ነበር። አዲስ የመጣው ሀሳብ ነው። በተመሳሳይ የአትክልትና ፍራፍሬ የማምረት ባህሉ አለ፡፡ይሁን እንጂ በብዛት አምርቶ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረገው ጥረትና ከውስን አካባቢ የወጣ ልማት አለመካሄዱ ችግር ነው።
ያለንን ፀጋ ቆም ብሎ በማየት አሟጦ በመጠቀም ያሉብንን ክፍተቶች በመሙላት ተጠቃሚነትን ከፍ ማድረግ ይጠበቃል፡፡አጠቃላይ የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ ብሎም እንደሀገር ወደ ብልጽግና ማማ ከፍ ለማድረግ ያለውን አማራጭ አሟጦ መጠቀም ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡አዲስ የሥራ ባህል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡በዓመት አንዴ ለማምረት ይቸገር የነበረ ማህበረሰብ ዛሬ በዓመት ሶስቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ፍላጎት እያሳየ ነው፡፡›› በማለት ሀሳብ ሰጥተዋል።
በአማራ ክልልም በተመሳሳይ በልግ አብቃይ የሆኑ አምስት ዞኖች አሉ። በነዚህ አካባቢዎች እየተከናወኑ ስላሉ የበልግ ግብርና ሥራዎች የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደሚከተው ገልጸውልናል። የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንዳሉት፤ በአምስቱ ዞኖች ወደ 218 ሺ 286 ሄክታር መሬት በበልግ ዝናብ የእርሻ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ ነው ወደ ሥራ የተገባው። በልጉ ከገባ ጀምሮ በተከናወነው የእርሻ ሥራ 196 ሺ 973 ሄክታር መሬት ታርሷል። ከዚህ ውስጥም ወደ 98 ሺ 461 ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ተሸፍኗል። ደቡብ ወሎ፣ሰሜን ወሎ፣ሰሜን ሸዋ ከፊል አካባቢ በልጉ እንደገባ ወደ ሥራ ገብተዋል።
ሥራው በዚህ መልኩ ቢከናወንም የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ የዘነበ ባለመሆኑና ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ዝናቡ በመቋረጡ ተጠብቆ የነበረውን ያህል የእርሻ ሥራ ተከናውኗል ለማለት አያስደፍርም። ከታህሳስ መጨረሻ ጀምሮ እስከ የካቲት ባሉት ወራቶች በአካባቢው የበልግ ዝናብ ይጠበቅ ነበር። ነገር ግን ዝናቡ በስርጭትና በመጠን ከሚጠበቀው በታች ነው የሆነው። ጥሩ ጊዜ የሚባለው የበልግ ወቅት እስከ የካቲት 20 ድረስ ባለው የዘር ሥራ መጠናቀቅ ስላለበት ከዚህ በኋላ ያለው ዝናብ የሚጠቅመው በዘር ለተሸፈነው መሬት ካልሆነ በልጉ እየተጠናቀቀ ክረምቱ እየቀረበ በመሆኑ ገና ለሚታረስ መሬትና በበልግ ዝናብ መቋረጥ በዘር ሳይሸፈን ለቀረው መሬት አይጠቅምም፡፡
የዝናቡ ሁኔታ በተፈጥሮ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ መጠንና ስርጭቱ ከፍ እና ዝቅ ሊል እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ይህን መሰረት በማድረግ በሚከናወን የግብርና ሥራ ወቅቱን ባገናዘበ አቅዶ መንቀሳቀስ ይጠበቃል። የሚጠበቀውን ምርትና በበልግ የሚመረቱ የምርት አይነቶችን በተመለከተ አቶ ቃልኪዳን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የሰብል ልማቱ ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል። ሆኖም ገብስ፣ ምስር በስፋት ከሚጠበቁ የሰብል ምርቶች መካከል ይጠቀሳል። በአማካይ በሄክታር ከ18 እስከ 20 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ነው በዕቅድ የተያዘው። ማዳበሪያን ጨምሮ የግብርና ግብአት አቅርቦት በዚህ የበልግ የግብርና ሥራ ከተነሱ ችግሮች ውስጥ ይጠቀሳል።
ክልሉ የግብአት አቅርቦት ችግር የፈታበትን መንገድ በተመለከተም አቶ ቃልኪዳን እንዳስረዱት፤ማዳበሪያና የግብርና ግብአት የሚያቀርቡ የህብረት ሥራ ማህበራት በወራሪው ኃይል ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ትህነግ) ጥቃት ተፈጽሞባቸው ሥራቸው በመስተጓጎሉና ግብአቱም በወራሪው ኃይል በመዘረፉ እጥረቱ ተከስቷል። በተወሰነ ደረጃ የተረፈ ቢገኝም ለበጋ መስኖ ልማት በመዋሉ ለበልግ የግብርና ሥራ በበቂ ሁኔታ ማዳረስ አልተቻለም፡፡ግብአቱን ከተለያዩ አካባቢዎች በማሰባሰብና የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ጥቅም ላይ በማዋል ነው ለማካካስ ጥረት የተደረገው፡፡
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባጋጠመው ጦርነት የተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች በጦርነት ቀጣና ውስጥ መቆየታቸው ይታወሳል። አሁን በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም የበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የተከናወኑ ሥራዎችን አስመልክቶ አቶ ቃልኪዳን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ጦርነቱ የተካሄደባቸው አብዛኞቹ አካባቢዎች በልግ አብቃይ ሲሆኑ፣ ሰሜን ወሎ፣ሰሜን ሸዋ በከፊልና ዋግ፣ በአጠቃላይ የክልሉ ምሥራቁ ክፍል ጦርነት የተካሄደባቸው ናቸው፡፡አንጻራዊ ሰላም እንደተገኘ በመኸሩ በሰብል የተሸፈነውንና የደረሰውን ሰብል በመሰብሰብ፣ በጦርነቱ ምክንያት ሳይታረስ ጾም ያደረገውን መሬት ደግሞ በመስኖ እንዲለማ በማድረግ፣የበልጉ ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የዝናብ ችግር ያጋጥም ካልሆነ በስተቀር የተቻለው ጥረት ተደርጎ የግብርና ሥራው በመከናወን ላይ ይገኛል።
ከመኸሩ የግብርና ሥራ በኋላ በበጋ መስኖ ልማትና በበልግ የግብርና ሥራው በተከታታይ በመከናወን ላይ ይገኛል። ክረምቱም እየተቃረበ በመሆኑ የግብርና ሥራው ዓመቱን ሙሉ በመከናወን ላይ መሆኑን ማሳያ ነው። በኋላቀር መንገድ እየተከናወነ ባለው የግብርና ሥራ የትም መድረስ እንዳልተቻለ ተደጋግሞ በትችት እየተነሳ ያለው ይህ ዘርፍ ለውጥ እንዲያስገኝ በተከታታይ እየተሰራ ያለው ሥራ ይበል የሚያስብል ቢሆንም፣አሁንም በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ የሚያጋጥሙ ነገሮች በመኖራቸው ብዙ መስተካከልና ከዚህም በላይ ሥራ መስራት ይጠበቃል።
አበረታች በሆነውና በተያዘው እንቅስቃሴ ከበጋ መስኖ ልማት ጀምሮ በክልሉ ስላለው ሁኔታ አቶ ቃልኪዳን እንደገለጹልን፤ መስኖ ከዝናብ ጥገኝነት የወጣ ስለሆነ፣በአካባቢው ያለውን የውሃ አማራጭና ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተከናወነው የበጋ መስኖ ግብርና ሥራ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። ለመኸሩ የግብርና ሥራ ዝግጅትም ጎን ለጎን እየተካሄደ ነው። እነዚህ ተከታታይ ሥራዎች ለምርትና ምርታማነት ማደግ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ስላላቸው፣ የግብርና ሥራው አሁን እየተካሄደ ባለበት ተከታታይ ሥራ ይጠናከራል። አሁን እየታየ ላለው የምግብ ዋጋ መናር ዋና መፍትሄው የግብርና ሥራውን ማጠናከር በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2014