ኢትዮጵያ ከ17ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ታስተናግዳለች። የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማሕበር (ሴካፋ) የዓመቱን የውድድር መርሃ ግብሮችና አስተናጋጅ አገራትን አሳውቋል።
በበርካታ የምስራቅና ጥቂት የመካከለኛው አፍሪካ አገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች የተዋቀረው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማሕበር (ሴካፋ) ከአህጉሩ የእግር ኳስ ማሕበራት መካከል አንጋፋው ነው። እአአ 1973 የተመሰረተው ማሕበሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ 12 አገራትን በአባልነት አቅፏል። ማሕበሩ በርካታ ቀጠናዊ ውድድሮችን በስሩ የሚያካሂድ ሲሆን፤ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሚሆነውን ቡድን ለመለየትም የማጣሪያ ጨዋታዎችን ያከናውናል። የዚህን ዓመት የማጣሪያ ውድድርም በኢትዮጵያ አዘጋጅነት እንደሚካሄድ ማሕበሩ በድረገጹ አስታውቋል።
ማሕበሩ የዓመቱን የውድድር መርሃ ግብር እና አዘጋጅ አገራትን ያስታወቀ ሲሆን፤ በተያዘው ዓመት ሰባት ውድድሮች ይደረጋሉ። ውድድሮቹን ለማዘጋጀት አገራቱ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረትም የስራ አስፈጻሚው ውሳኔ መስጠቱንም የማሕበሩ ዳይሬክተር አውካ ጌቼዮ አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት ኡጋንዳ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገውን የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ በቀጣዩ የፈረንጆች ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት ታስተናግዳለች። በተጨማሪም የዞኑን የፓን አፍሪካ የትምህርት ቤቶች ውድድርም በአገሯ ታካሂዳለች።
ለረጅም ጊዜያት የትኛውንም የሴካፋ ውድድር ሳታስተናግድ የቆየችው ሱዳን ደግሞ የከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እንደምታስተናግድ ታውቋል። ሌላኛዋ የማሕበሩ አባል ታንዛኒያ በበኩሏ የካፍ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያን፣ ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያን እንዲሁም በዚሁ የእድሜ ክልል የካጋሜ ዋንጫን ታስናዳለች።
ማሕበሩ ውድድሮቹ የሚካሄዱባቸውን ጊዜያት በቅርቡ የሚያስታውቅ መሆኑንም በዳይሬክተሩ በኩል አመላክቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2014