አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሥራ ቅልጥፍና እና በሰራተኞች ሥነ ምግባርና ትህትና በተደጋጋሚ ሲታሙ ይሰማል። ተገልጋዩን የበለጠ የሚያማርረው ደግሞ የሰልፍ ብዛት አንዱ ነው። በሁሉም ቦታ ወረፋ አለ፤ በተለይም እንደ ባንክ እና ገቢዎች ያሉ ገንዘብ የሚንቀሳቀስባቸው መገልገያዎች ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚጠይቁ ወረፋ ይበዛባቸዋል።
የአገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ችግር እንዳለ ሆኖ (በተደጋጋሚ ስንወቅሳቸው ስለኖርን) እስኪ ዛሬ ደግሞ ራሱ ተገልጋዩ ጋ ያለውን ችግር እንታዘብ። ልብ ብላችሁ አስተውላችሁ ከሆነ ከተገልጋዩም ብዙ ችግር አለ። የሚሞላ ቅጽ በትክክል አለመሙላት፣ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን ሳያጣሩ መምጣት፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋሙን ሕግና ደንብ አለማወቅ፣ ከሕግና ደንብ ውጭ አገልግሎት ለማግኘት መጨቃጨቅ…. የመሳሰሉት አግልግሎቱን ያጓትታሉ።
21ኛው ክፍለ ዘመን ሥራዎችን ሁሉ ቀላል አድርጓል። ከዓመት ወደ ዓመት በተሸጋገርን ቁጥር አዳዲስ የቴክኖሎጂ ዓይነቶች ብቅ እያሉ ነው። በብዙ ተቋማት ውስጥ የወረቀት አገልግሎት እየቀረ ነው።
እንግዲህ በአገራችንም ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ብዙ ተቋማት አገልግሎታቸውን ወረቀት አልባ ካደረጉ ዋል እደር ያሉ ብዙ ናቸው። ወረቀት ሙሉ በሙሉ ባይቀር እንኳን የቴክኖሎጂ አማራጮች እየተሰጡ ነው። ለምሳሌ ባንኮች ወረፋን ለማስቀረት ብዙ የቴክኖሎጂ አማራጭ ሰጥተዋል።
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ተገልጋዩን ማሕበረሰብ የምንታዘበው። ብዙዎቻችን ለቴክኖሎጂ ነክ ነገሮች ሩቅ ነን። አንዳንዱ እንዲያውም ጭራሽ ‹‹አልወድም›› በማለት ራሱን እንደ ኩሩ የሚያይም አለ። ሌላው ደግሞ ቴክኖሎጂው አስማት ሆኖበት የሚከብደው አለ። እነዚህን ነገሮች የምንታዘበው የትምህርት ደረጃ በሌላቸው ሰዎች አይደለም። ቢያንስ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ካላቸው ሰዎች ነው።
በትምህርት ብዙም ያልገፉ ወይም ጭራሹንም ትምህርት ቤት ያልገቡ ሰዎች ቴክኖሎጂ እንደማይጠቀሙ ግልጽ ነው። አማራጩ የመጣው መጠቀም ለሚችሉት ነበር። እነዚህ ቴክኖሎጂውን መጠቀም የሚችሉ ሰዎች ቢጠቀሙ፤ ለወረፋ የሚሰለፉት መጠቀም የማይችሉት ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው። መጠቀም የማይችሉት ብቻ ቢሰለፉ ደግሞ የተጋነነ ሰልፍ አይሆንም። አሁን ግን አስቸጋሪ የሆነው የተማረ የሚባለውም ያልተማረውም አብረው የወረቀት አገልግሎት እየተጠቀሙ ነው።
የሕዝብ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ሁሉም የወረቀት አገልግሎት ከተጠቀመ ወረፋው እየባሰው እንጂ እየተሻለው አይሄድም።
የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎች ላይ ብዙ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶች ሲተዋወቁ እናያለን። የውሃ፣ የመብራት፣ የትራፊክ ቅጣት… የመሳሰሉ ክፍያዎች በሞባይል ባንኪንግ፣ በሲ ቢ ብር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቴሌ ብር መከፈል እንዳለባቸውና ይሄውም ጊዜና የሰው ጉልበትን ድካም እንደሚቀንስ በተደጋጋሚ ይተዋወቃል። ተጠቃሚው ግን ትንሽ ነው። ባንክ ቤቶች ውስጥም ሆነ ሌላ የክፍያ አገልግሎት ያለባቸው ቦታዎች ላይ አሁንም ረጃጅም ወረፋ ነው ያለው።
የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ከተጀመረ ብዙ ጊዜ ሆኖታል፤ ዳሩ ግን አሁንም የማይጠቀመው ሰው ብዙ ነው። እንኳን የሞባይል ባንኪንግ ኤ ቲ ኤም ካርድ የማይጠቀም ብዙ የተማረ የሚባል ሰው አለ። በነገራችን ላይ አንዳንድ ሰዎች ለምን የኤ ቲ ኤም ካርድ እንደማይጠቀሙ ሲጠየቁ ብር ለመቆጠብ አይመችም የሚል ምክንያት የሚያቀርቡ አሉ። ይሄ በራስ አለመተማመን ነው። ኤ ቲ ኤም ማሽን ባገኘ ቁጥር ያለአስፈላጊ ጉዳይ ብዙ የሚያወጣ ሰው በሒሳብ ደብተርም ቢሆን ያወጣዋል።
ወረፋው ከአቅም በላይ ሲሆንበት እተወዋለሁ ብሎ ከሆነ ደግሞ ሌላ ጉዳት ነው። አስገዳጅ የሆነ ጉዳይ ቢያጋጥም ብሩን ማግኘት ባለበት ሰዓት ላያገኝ ነው ማለት ነው።
ብዙዎቻችን ለቴክኖሎጂ ነገሮች ራቅ ያልን ነን። ይሄ ማለት ግን በአገልግሎት ሰጪው ተቋም በኩልም ችግር የለም ማለት አይደለም። በተለይም ከኮኔክሽን ጋር በተያያዘ ችግር አለ። ባንኮች የወሩ መጨረሻ ሰሞን የሰራተኞች ደሞዝ መግቢያ ስለሆነ ሞባይል ባንኪንግ ሥራ ያቆማል። ተፈላጊነቱ በሚጎላ ጊዜ ጭራሽ ሥራ ያቆማል። የዚያን ሰሞን በሒሳብ ደብተር እንኳን ለማውጣት ‹‹ሲስተም የለም›› በሚል ወረፋው በጣም ይበዛል።
የኤ ቲ ኤም ማሽኖች ይበላሻሉ። አሁን አሁን የኤ ቲ ኤም ሰልፍ ራሱ የታክሲ ሰልፍ ያህል እየረዘመ ነው። ስለዚህ ባንኮች ደንበኞቻቸው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚወተውቱትን ያህል አገልግሎት አሰጣጣቸውንም እንደዚያው ቀልጣፋ ማድረግ አለባቸው። በተለይም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኛ ብዛት ስላለው ነው መሰለኝ ማሽኖቹ የወር መጨረሻ አካባቢ አይሰሩም።
ሌላው የሚያጋጥመው ችግር ደግሞ ማሽኑ ያልሰጠውን ብር ‹‹ወጪ አድርጋችኋል›› የሚል መልዕክት በመላክ ብሩ ተቀናሽ መሆኑ ነው። በእርግጥ ከቀናት በኋላ (ብዙ ጊዜም ወዲያውኑ) ብዙ ተመላሽ ይሆናል። በበኩሌ አጋጥሞኝ ባያውቁም አልተመለሰልኝም የሚሉ ሰዎችም ሰምቼ አውቃለሁ።
በነገራችን ላይ የትዝብት ትኩረቴን ባንኮች ላይ ረዝም ያደረኩት ከሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሻለ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ስለሆነ ነው። የሚደነቅ ብቻ ሳይሆን የሚወቀስም የሚሰራ ነው። ትችት የሚያጋጥመው የሚሰራ አካል ነው። አየር መንገድ እና ባንኮች ናቸው በኦንላይን መገልገልን ያስለመዱን። በዚህ በኩል በጣም ይመሰገናሉ።
ወደ ሌሎች ተቋማት ስንሄድ እንኳን በመተግበሪያ አገልግሎትን ማፋጠን የማሕበራዊ ትስስር ገጾቻቸው እንኳን የማይታደሱ ናቸው። ለእንቁጣጣሽ ‹‹መልካም አዲስ ዓመት›› ብለው ከአደይ አበባ ጋር የለጠፉት ጽሑፍ ዓመቱን ሙሉ ምንም የማይጨመርበት አሉ። የእነዚህ ተቋማት ሰራተኞች ቴክኖሎጂን እያስተዋወቁና እየተጠቀሙበት አይደለም ማለት ነው።
እዚህ ላይ ግን አንዳንድ ተቋማት አስቂኝ ነገሮች እንደሚለጥፉም ታዝበናል። በተለይም የወረዳ ኮምኒኬሽን ገጾች ብዙ ጊዜ ማሕበራዊ ገጾች እየተቀባበሉ ሲቀልዱባቸው ይታያል። ገጾቻቸው በግለሰብ ስለሚከፈቱ ‹‹Got Married፣ In Relationship›› የሚሉ ግለሰባዊ ነገሮችን ይለጥፋሉ። የማሕበራዊ ገጾች ተጠቃሚዎች ደግሞ በብዛት ወጣቶች ስለሆኑ ትንሽ ነገር ሲገኝ መሳቂያ መሆኑ አይቀሬ ነው። ኦንላይን በባህሪው ፈጣን ስለሆነ ስህተት እንደሚያጋጥም ቢታወቅም አንዳንዶቹ ደግሞ አስቂኝ ከመሆኑ የተነሳ ለምን አዘዋወሩት ብሎ ለመውቀስም አይመችም።
ቴክኖሎጂ ሲባል እንግዲህ የግድ ከኦንላይን ጋር የተያያዙ ነገሮችን ብቻ አይደለም። በአጠቃላይ ሥራን የሚያቀላጥፉ እና መረጃን የሚያፋጥኑ ነገሮችን መጠቀም ማለት ነው። ሰራተኞች በሚሰሩበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ መሻሻል ማለት ነው። በ90ዎቹ የነበረ መገልገያ አሁን ላይ ብዙ ነገሩ ስለሚቀየር ከዚያ ጋር አብሮ መሄድ ማለት ነው። ለምሳሌ በየትኛውም ቢሮ ኮምፒተር አለ። የኮምፒተር ሶፍትዌሮች እንኳን ይቀየራሉ። ቀደም ሲል የነበረው አሁን ላይ የመጡ መተግበሪያዎችን ላይቀበል ይችላል፤ ስለዚህ ያንን አውቆ መቀየር ማለት ነው።
ስለዚህ ተቋማትም ጠንክረው ይስሩ፤ እኛ ተገልጋዮችም ተቋማትን መውቀስ ብቻ ሳይሆን እኛም ከቴክኖሎጂ ፍጥነት ጋር ራሳችንን በማሻሻል ተጠቃሚ እንሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2014