በሶስት ምድብ ተከፍሎ ሲካሄድ የቆየው የ2014 ዓ/ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የእግር ኳስ ውድድር በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት መጠናቀቁ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በቀጣዩ 2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የሚሳተፉ ሶስት አዳዲስ ክለቦች ማደጋቸውን አረጋግጠዋል። ወደ አንደኛ ሊግ የወረዱ ክለቦችም ሙሉ ለሙሉ ተለይተዋል።
በሶስት ምድቦች 36 ክለቦችን ያፋለመው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ሲጠናቀቅ ምድብ”ሀ” ተደልድለው ሲወዳደሩ ከነበሩ 12 ክለቦች መካከል ኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ ጨዋታ እየቀረው ነበር ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጉን ያረጋገጠ የመጀመሪያው ክለብ የሆነው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጨረሻውን ጨዋታም ባህርዳር ስቴድየም ላይ ባቱ ከተማን ሁለት ለዜሮ በመርታት ከጥቂት አመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለሱን አረጋግጧል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ 1990 ጀምሮ እንደ አዲስ መካሄድ ከጀመረ አንስቶ ቻምፒዮን በመሆን ጭምር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ታሪክና ስም ካላቸው ክለቦች አንዱ የሆነው የቀድሞው መብራት ሃይል የአሁኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሶስት አመት በፊት ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱ ብዙዎችን ያስቆጨ እንደነበር ይታወሳል።
ያም ሆኖ ከፕሪሚየር ሊግ ወርዶ መመለስ ከባድ ፈተና በሆነበት የከፍተኛ ሊግ ፉክክር ባለፉት አመታት ሲፋለም ቆይቶ ዘንድሮ ወደ ትልቁ ሊግ ማደጉን እውን አድርጓል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ማደጉን ባረጋገጠበት ከዚሁ ምድብ ጌዲኦ ዲላ እና አምቦ ከተማ ወደ አንደኛ ሊግ መውረዳቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ሆነዋል።
ተቀራራቢ ነጥብ ይዘው በከፍተኛ ፉክክር ከምድብ “ለ” ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ እድል የነበራቸው ለገዳዲ ለገጣፎ እና ቤንች ማጂ ቡና የመጨረሻ ፍልሚያቸውን በድል ተወጥተዋል። የነበረውን የሶስት ነጥብ ልዩነት ማስጠበቅ የቻለው ለገዳዲ ለገጣፎ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል። ባቱ ስቴድየም ላይ ሰንዳፋ በኬን አራት ለዜሮ በመርታት ወደ ትልቁ ውድድር ማለፉን ያረጋገጠው ለገዳዲ ለገጣፎ በ2015 የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፍ ብቸኛው አዲስ ክለብ ሲሆን ሼር ሜዳ ላይ ኮልፌ ቀራኒዮን ገጥሞ ሁለት ለዜሮ ያሸነፈው ቤንች ማጂ ቡና በሶስት ነጥብ ልዩነት እዚያው ከፍተኛ ሊግ ተፋላሚ ሆኖ ለመቆየት ተገዷል። በዚህ ምድብ ከንባታ ሽንሽቾ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወደ አንደኛ ሊግ መውረዳቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ሆነዋል።
በመጨረሻው ምድብ “ሐ” በተደረጉ ፍልሚያዎች እስከ መጨረሻው ጨዋታ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድገው ክለብ አለመለየቱ አጓጊ ነበር። በአንድ ነጥብ ልዩነት ምድቡን ሲመራ የቆየው ኢትዮጵያ መድሕን በ37 ነጥብ እንዲሁም ነቀምት ከተማ በ36 ሰንጠረዡ አናት ላይ የሚገኙ ቡድኖች ሆነው የመጨረሻውን ወሳኝ ጨዋታ ውጤት ጠብቀዋል። ሃዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስን የገጠመው ኢትዮጵያ መድሕን አንድ ለዜሮ በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፎ ከስምንት አመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያሳድገውን ጣፋጭ ድል አጣጥሟል። ነቀምት ከተማ በበኩሉ ወሳኙን ፍልሚያ ከየካ ክፍለ ከተማ ጋር ሁለት አቻ በመለያየት ወደ ፕሪሚየር ሊግ የማደግ ተስፋው ሳይሰምር ቀርቷል። የካ ክፍለ ከተማና ጅማ አባ ቡናም ወደ አንደኛ ሊግ የወረዱ ክለቦች መሆናቸው ተረጋግጧል።
በምድብ “ሀ” የተካሄደው የመጨረሻ ፍልሚያ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ሲጠናቀቅ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የሲዳማ ክልል ስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፣ የኢትዮጵያ መድሕን ድርጅት እና የደቡብ ፖሊስ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቦታው ተገኝተው ጨዋታዎችን በማስጀመር ለተሳታፊዎች ሽልማት አበርክተዋል። በሌሎቹ ምድቦች የፍጻሜ መርሃግብርም የእግር ኳስ ፌዴሬሽንና ሌሎች የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተው ሽልማቶችን አበርክተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 27 /2014