ወቅቱ በጋ ቢሆንም አርሶአደሩ ሥራ አልፈታም። በአካባቢው የሚገኘውን ወንዝ በመጥለፍ ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ ጥራጥሬዎች በበጋ በማምረት የግብርና ሥራውን ተያይዞታል። አርሶአደር አገኘሁ ታከለ መንደር ስንደርስ በመኖሪያቤታቸው አቅራቢያ በዘሩት የጓያ ምርት ላይ የተባይ ማጥፊያ መድሃኒት ሲረጩ ነበር።
የጓያ ሰብሉን እየጎዳው ያለው ተባይ አስቸግሯቸው ለአራተኛ ጊዜ የተባይ ማጥፊያ ርጭት እያካሄዱ እንደሆነ ነበር የነገሩን።እርሳቸው እንዳሉት የጓያ ምርቱን የጎዳው ተባይ ያልተለመደም በመሆኑ ቀደም ሲል ያገኙት የነበረውን የምርት መጠን ሊያሳጣቸው እንደሚችሉም ስጋት አድሮባቸዋል።
እያካሄዱ ያለው የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት ርጭትም የመጨረሻ ሙከራ ነበር። የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት ግዥ ዋጋ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ተጨማሪ ሙከራ ላለማድረግም በወቅቱ ወስነው ነበር። የጓያ ምርት ገበያ ላይ በጥሩ ዋጋ ይሸጣል። ገለባውም ለከብት መኖ ይውላል።እንዲህ የተለያየ ጥቅም ስለሚሰጥ የአካባቢው አርሶ አደር በዚህ በበጋ ወቅት ጓያ በስፋት ዘርቷል።
አርሶአደር አገኘሁ በሚኖሩበት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ የተለያየ ሰብል የሚመረት ቢሆንም አርሶአደሩ በስፋት ሩዝ ነው የሚያለማው። ከሌላው የሰብል ምርት ምርት በመስጠትና ገበያ ላይ የተሻለ ዋጋ ስለሚያወጣ ነው በአካባቢው ሩዝ ማምረት በአርሰአደሩ ተመራጭ የሆነው። የ2013-2014 ዓ.ም የምርት ዘመን የሩዝ ምርት ህዳር ወር ላይ ተሰብስቦ ጎተራ ገብቷል። የሚቀጥለው የምርት ጊዜ (2014) ሰኔና ግንቦት ወራቶች ላይ በመሆኑ መሬቱ ጾም እንዳያድር በበጋው አትክልት፣ ፍራፍሬና የተለያዩ ሰብሎች ልማት ይካሄዳል። አርሶአደር አገኘሁ እንደነገሩን ሩዝ የማምረት ሥራው ወቅት የሚጠብቀው ለመስኖ አገልግሎት የሚውል አካባቢው ላይ በቂ ውሃ ባለመኖሩ ነው። የሩዝ ምርት ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ይፈልጋል።
አብዛኛው የአካባቢው አርሶአደር ሩዝ አምራች በመሆኑ በበጋው በቂ ውሃ ማግኘት ስለማይቻል ነው አርሶአደሩ በበጋው መጠነኛ ውሃ በሚፈልግ ምርት የማምረት ሥራ ላይ ትኩረት ያደረገው። በ2013-2014ዓም የምርት ዘመን አርሶአደር አገኘሁ ምን ያህል የሩዝ ምርት እንደሰበሰቡና ተጠቃሚነታቸውንም ጠይቀናቸው ‹‹ተመስገን ነው›› ያሉን እንጂ ከጎተራቸው ያስገቡትን መጠን አልነገሩንም።
ከንግግራቸው ጥሩ ምርት መሰብሰባቸውን ነው የተገነዘብነው። ጥሩ ምርት ካገኙ ደግሞ ገቢያቸውም ጥሩ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ከአርሶአደሩ ጋር ቆይታ ሲያደርጉ በተለመደው አይነት ከሚቆጠረው የኩንታል መጠን ሳይሆን፣ ከአንደበታቸው በሚነገረው ነው የምርት ዘመኑ ጥሩ መሆንና አለመሆን የሚታወቀው።በግብርና ሥራው ወቅት የተመጣጠነ ዝናብ መዝነቡ፣ ጎርፍ አለማጋጠሙ፣ ተባይ አለመከሰቱ፣ በአጠቃላይ የአየር ፀባዩ ለግብርና ሥራ ተስማሚ ከመሆኑ ጀምሮ ነው አርሶአደሩ የሚያመሰግነው።
አርሰአደር አገኘሁም ይህን ሁሉ ታሳቢ አድርገው ነው የዘንድሮውን የምርት ዘመን በምስጋና የገለጹልን። አርሶአደር አገኘሁ የተሻለ ምርት ካገኙ ገቢያቸውም የተሻለ ስለሚሆን ኑሮአቸውን ለማሻሻል እቅድ እንደሚኖራቸው በመገመት ጥያቄ አቀረብንላቸው እርሳቸውም እየሳቁ ‹‹አይ እናንተ ገበሬ ምን እቅድ ይኖረዋል። ሸጠን ለቤት የሚያስፈልገውን የምንገዛውም ቀለባችንም ካመረትነው ምርት በመሆኑ ኑሮአችን ይሄ ነው።
ዘንድሮ ልጄን እድራለሁ ብያለሁ። እሺ ካለ እድረዋለሁ። ካላለም መክረሙ ነው። ይህ ነው ሃሳቤ›› በማለት ምላሽ የሰጡን። ከገለባው ያልተለየውን የሩዝ ምርቱን እንዳየነው ቆዳው ወይንም ሽፋኑ ከስንዴ ወይንም ገብስ ጋር ይቀራረባል። ምርቱን ለገበያ ሲያቀርቡ ከገለባው የተለየ ያልተለየ በሚል ነው።ከአርሶአደር አገኘሁ ጋር በነበረን ቆይታ እንደተገነዘብነው የሩዝ ምርቱ ከግብርና ሥራው በተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ሩዙን ከገለባ የመለየት አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። አሁን ላይ ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ለውጦች ቢኖሩም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ምግቡ ከጤፍ የሚዘጋጅ እንጀራ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ከገብስ፣ ስንዴና በቆሎ የሚዘጋጅ እንጀራ ካልሆነ ሩዝ አልተለመደም። በተለይ የገጠሩ ማሕበረሰብ ከእንጀራ ውጭ ከጥራጥሬ ከሚያዘጋጃቸው ቆሎና ንፍሮ ነው የሚጠቀመው።
ይህን ታሳቢ በማድረግ ሩዝ ከማምረት በተጨማሪ ለምግብነት በማዋል እንዴት እየተጠቀሙ እንደሆነና ያላቸውን ፍላጎት በተመለከተ የአርሶአደር አገኘሁን ባለቤት ወይዘሮ አዱኛ እውነቱን ጠየቅናቸው። እርሳቸውም የእንጀራውን ማማርና አንዳንዴም ማጣፈጫ ጨምረው ቀቅለው እንደሚመገቡ አጫወቱን። ሩዙን ከዳጉሳ ጋር ቀላቅለው በማስፈጨት ነው ለእንጀራ የሚጠቀሙት።ብቻውንም ቢሆን ጥሩ እንጀራ እንደሚሆን ነግረውናል።
የሩዝ አሰራሩንም ሆነ ምግቡን እየለመዱት መሆኑና ቀቅሎ ለመመገብም አነስተኛው ሩዝ እንደሚበዛ ነው ወይዘሮ አዱኛ የነገሩን። በአርሶአደሩ መንደር በነበረን ቆይታ እንደቃኘነው በአካባቢው ክረምት ከበጋ በአንድ መሬት ላይ በማፈራረቅ እየተከናወነ ያለው የተለያየ ሰብል፣ የሩዝ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለምርታማነትም እያገዘ መሆኑን ነው የተገነዘብነው።
ስለሩዝ አመራረትና እያስገኘላቸው ስላለው ጥቅምም ከሌሎች የአካባቢው አርሶአደሮች እንደተረዳነው የሩዝ አመራረት ዘዴ ከሌላው የሰብል ልማት ይለያል። ሥራውም ከባድ ነው። መሬቱን ሶስት ጊዜ በመገልበጥና ደጋግሞ ዘር በመዝራት ነው የሚከናወነው። ውሃና ማዳበሪያ በብዛት ይፈልጋል።
አርሶአደሮቹ እንደሚሉት ማረሱ፣ መዝራቱና የማረሙ ሥራ ድግግሞሽ ስላለው ነው ሥራውን ከባድ ያደረገው። ሥራው አድካሚ ቢሆንም ከሌሎች የሰብል አይነቶች ጋር ምርታማነቱ ሲነፃፀር የተሻለ በመሆኑ አርሶአደሩ መርጦት በፍላጎት ያለማዋል። በሄክታር እስከ 40 ኩንታል የሩዝ ምርት ይገኛል። በተለይ ደግሞ ሰፊ የእርሻ መሬት ያለው ገበሬ ብዙ አምርቶ ተጠቀሚ ይሆናል። የሩዝ ምርታማነት ከፍተኛ ሆኖና አርሶአደሩም በፍላጎት እያለማው ነገር ግን የልማቱ ሥራ በቴክኖሎጂ አልታገዘም። በሬ ጠምደው ነው የሚያለሙት። በትራክተር ማረስ በአካባቢያቸው አልተለመደም። የሩዝ ልማት ሥራ ከፍተኛ ድካም የሚጠይቅ በመሆኑ በቴክኖሎጂ ቢታገዝ ድካማቸውን ይቀንስላቸዋል። ከአካባቢው አርሶአደሮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በሊሞ ከምከም ወረዳ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የሩዝ ልማት በስፋት በመከናወን ላይይገኛል።
ዝርያዎቹም ‹‹ኃይላንድ ራይዝ››እና ሎውላንድ ራይዝ››በመባል ያታወቃሉ። ‹‹ኃይላንድ ራይዝ››የሚባለው ዝርያ ውሃ በመጠኑ የሚፈልግ ሲሆን፣‹‹ሎው ላንድ ራይዝ›› ደግሞ ከፍተኛ የውሃ መጠን የሚያስፈልገው ነው። በዚህ መልኩ ተስማሚ በሆነ ቦታ እንዲለማ ይደረጋል።
ምርታማነታቸውም እንዲሁ ይለያያል። የሩዝ ልማት ውሃ የሚፈልግ በመሆኑ በቅድሚያ የእርሻ መሬቱ ውሃ የሚገኝበት አካባቢ መሆኑ ይረጋገጣል። በባለሙያ የተሰጠ ምክርን መሠረት ባደረገ ተገቢ የሆነ ማዳበሪያና ተመሳሳይ የሆነ የምርጥ ዘር መጠቀም፣ በመስመር መዝራት፣ በድግግሞሽ ማረስ፣የበሽታ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ መከናወን ካለባቸው ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ።
ውሃ በአግባቡ ለመጠቀምና ለባለሙያ ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር እንዲያመች እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ይመረጣል። ሩዝ ከሌሎች የሰብል አይነቶች የሚለየው በፀረተባይ የመጠቃት ዕድሉ ጠባብ ነው። ከአነስተኛ ማሳ ከፍተኛ ምርትም ይገኛል።
እነዚህ አርሶአደሩ ሩዝ የማምረት ፍላጎት እንዲኖረው ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል። በኢትዮጵያ የሩዝ ምድር ከተፈለገ ቀድሞ በሰው አዕምሮ ውስጥ የሚመጣው ፎገራ እንደሆነ የአማራ ኢኮኖሚክ ሽግግር ማዕከል (ሴንተር ፎር ኢኮኖሚክ ትራንስፎርሜሽን ኦፍ አማራ) የተባለ ተቋም እኤአበ 2020 ባወጣው መረጃ ማመልከቱ ይታወሳል።
በወቅቱ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ የሩዝ ፍላጎት እያደገ ቢሆንም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያስፈልገውን ከ500 ቶን በላይ የሩዝ ፍላጎትን አያሟላም። ካለው ፍላጎት የሚመረተው 20 በመቶ ብቻ ነው። በመሆኑም 80 በመቶ ምርት ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጭ በግዥ ነው የሚገባው።
በጣና ዙሪያ ብቻ አቅምን አሟጦ መጠቀም ከተቻለ የአገር ውስጥ የሩዝ ፍላጎትን ወይንም ፍጆታን መሸፈንና ከውጭ በውጭ ምንዛሪ በግዥ ከውጭ አገር የሚገባውን ሩዝ በተሻለ ጥራት በአገር ውስጥ መተካት እንደሚቻልም ነው የማዕከሉ መረጃ በወቅቱ የጠቆመው። እንደመረጃው ለሩዝ ልማት ተስማሚ የሆነ በጣና ዙሪያ አንድ ነጥብ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይገኛል።
ይህን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ በአገር ውስጥ ልማቱን ማሳደግ ይቻላል። በደቡብ ጎንደር በፎገራ ብቻ ሳይሆን ደንብያ እና ሊቦ ከምከም ጭምር የጣና ዙሪያ የሩዝ ምርት ቀለበት ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ናቸው።ለሩዝ ልማት የጣና ዙሪያ ሁነኛ ስፍራ እንደሆነ ቢረጋገጥም በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልሎችም ተስማሚ ቦታዎች መኖራቸው ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ ውስጥ 53ሺ ሄክታር መሬት በሩዝ እንደሚሸፈንና ከዚህ ውስጥም በጣና ዙሪያ ብቻ ከ40ሺ ሄክታር በላይ የሚሆነው በሩዝ የሚለማ መሆኑን በመረጃው ተመልክቷል። ሩዝን ለምግብነት በማዋል የደቡብ ምሥራቅና ሩቅ ምሥራቅ ሕዝቦች ተጠቃሽ ቢሆኑም አሁን ላይ የሚያሳዩት መረጃዎች ሩዝን በምግነት በማዋልም ይሁን በማምረት ሩቅ የሆነችው ኢትዮጵያም በማምረቱ ላይ የተጠናከረ ሥራ ብትሰራ ውጤታማ እንደምትሆን ከመረጃዎች መገንዘብ ይቻላል። ኢትዮጵያ የተለያየና በቁጥርም እጅግ ከፍተኛ የሆነ የአገዳ፣ የብርዕ፣የጥራጥሬ፣ የቅባትና ሌሎችም የአዝርዕት ዝርያዎች በማብቀል ትታወቃለች።
የሩዝ ልማቱ በተጨማሪ መከናወኑ ሳይንስ የሚደግፈውን የአመጋገብ ሥርዓት ለመከተል በእጅጉ አጋዥ ከመሆኑ በተጨማሪ በውጭ ምንዛሪ ግዥ ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ በመተካት ወጭን መቀነስ ይቻላል። በተለይም በዚህ ወቅት በዓለምአቀፋዊ፣ በአህጉራዊና አገራዊ ኩነቶች እያጋጠመ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት መቋቋም የሚቻለው እንደሩዝ ያሉ አማራጭ የምርት አይነቶችን በማምረትና ምርታማነትን በማሳደግ እንደሆነም መዘንጋት የለበትም። እንደአገር በምግብ እህል እራስን ለመቻል በሚደረገው እንቅስቃሴ የሩዝ ልማቱ አጋዥ ይሆናል።
ለበጋ ቆላ ስንዴ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራው ሁሉ ለሩዝ ልማቱም በየደረጃው የሚገኘው አስፈጻሚ አካል በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበትም ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያስገድዳል።በተለይም ልማቱ ውስጥ የሚገኙት እንደፎገራ አካባቢ ያሉት የሩዝን ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት በመገንዘባቸው የማምረት ፍላጎታቸው ከፍ ብሏል።
ለምርትና ምርታማነት እድገት የሚያግዙ ግብዓቶችን በማሟላትና የሚያጋጥሟቸውንም ችግሮች በመፍታት፣ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ከፍተኛ እገዛ ያስፈልጋቸዋል።በተለይም የቴክኖሎጂ እገዛው ሊተኮርበት ይገባል። በዘልማድ የሚከናወነው የማልማቱ ሥራ በግብርና ሥራው ላይ በተደጋጋሚ የሚነሳው የኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ በዚህ ላይም መደገም የለበትም።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 /2014