ካለን ብናካፍል የሕጻናት፤ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በራሳቸው መመገብ መጸዳዳትና መንቀሳቀስ የማይችሉ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መንከባከቢያ ማዕከል ነው።
ማዕከሉ ከተመሠረተ አጭር ግዜው ቢሆንም በርካቶችን ከከፋ ችግር ለመታደግ በቅቷል። እኛም የማዕከሉን ሥራ አስኪያጅ ወጣት ዳዊት አየነውን በማነጋገር ለዛሬው የአገርኛ አምዳችን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል። ማዕከሉ የተመሰረተው ሐምሌ ሃያ አራት ቀን ሁለት ሺ አስር ዓመተ ምህረት ነበር። የማዕከሉ መስራች የአሁኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ወጣት ዳዊት በጎንደር ዩኒቨርስቲ የሳይኮሎጂ ተመራቂ ሲሆን ከተመረቀም በኋላ በተማረበት መስክ በተለያዩ ቦታዎች ሲያገለግል ቆይቷል።
ከእነዚህም መካከል በተለይ አዲስ አበባ በነበረበት ወቅት ከግል ሥራው በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሁለት ዓመታት። እንዲሁም በመቄዶንያ የአዕምሮ ሕሙማን መርጃና መንከባከቢያ ማዕከል ከሁለት ሺህ አምስት መጨረሻ አንስቶ እስከ ሁለት ሺ ዘጠኝ ዓመተ ምህረት ድረስ በነጻ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
ከዚህ በኋላ ነበር ዳዊት በሁለት ሺ አስር ዓመተ ምህረት ወደ ጎንደር በመመለስ አሁን እየሠራ ያለውን ካለን ብናካፍል የሕጻናት፤የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ለመጀመር የበቃው። ከዓመታት በፊት ዳዊትና ጓደኞቹ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት ወቅት የተቸገሩን የመርዳት ልምድ ነበራቸው። በተለይም ዓመታዊ በዓላትን ተንተርሰው በጾም ፍቺ ቀናት ጿሚዎችን የማስገደፍ እንዲሁም ከተለያዩ ቦታዎች ልብስ በማሰባሰብ የታረዙትንም ያለብሱ ነበር።
ይህን የሚያደርጉት ግን በበዓላት ቀናት ብቻ ለዚያውም ሁሉም እጁን ለተቸገረ በሚዘረጋበት ዕለት መሆኑን እንደ ክፍተት ይገነዘቡት ነበር። ዳዊት ይህንን ክፍተት መነሻ በማድረግ በጎንደር ከተማ በራሱ ተነሳሽነት እንደ አዲስ ሁሌም ከተቸገሩት ጎን ለመቆም ሥራውን ለመጀመር ወደ እንቅስቃሴ ይገባል። በዚህ ወቅትም የመጀመሪያ መነሻው ያደረገው ያስተማረውን የጎንደር ዩኒቨርስቲን ነበር።
በወቅቱም ለዩኒቨርስቲው ባስገባው ደብዳቤ በተማረበት መስክ የስነ ልቦና ማማከር አገልግሎትና አስታማሚ የሌላቸውን ሰዎች በበጎ ፈቃደኝነት ለመንከባከብ እንደሚፈልግ ያሳውቃል። ለማኅበራዊ አገልግሎትና ለበጎ ፈቃድ ሥራዎች ሁሌም በሩን የማይዘጋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲም የዳዊትን ጥያቄ በመቀበል የመጀመሪያ ሥራውን የኤች አይ ቪ ቫይረስ ታማሚ የሆኑ ወገኖችን በማማከር እንዲጀምር ያደርገዋል።
ከዚህም በተጓዳኝ ባገኘው አጋጣሚ አስታማሚ የሌላቸውን ሰዎች መንከባከቡንም ይቀጥላል። ዳዊት ከዪኒቨርሲቲው ጋር የጀመረው ሥራ እንዳለ ሆኖ በፌስቡክ ገጹ ላይ አጠቃላይ እየሠራቸው ስላሉ ሥራዎችና ወደፊትም ሊሠራ ስለሚያስባቸው ነገሮች ለጓደኞቹና ለሚያውቁት ያካፍላቸው ስለነበር ከቁሳቁስ እስከ ሀሳብ ይደግፉት ነበር። በዚህ መካከል እያሉም ይህ እንቅስቃሴ ወደ ማኅበርነት ቢያድግ ብዙ በመሥራት ብዙዎችን መታደግ እንችላለን ወደሚል ሃሳብ ይመጣል።
ይህንንም በመቀበል በሁለት ሺ አስር ሐምሌ ሃያ አራት ቀን «ካለን ብናካፍል» በሚል ስያሜ የተቸገሩትን መርጃ ማኅበሩን ለመመሥረት ይበቃሉ። እነ ዳዊት ካለን ብናካፍል የሚለውን ስያሜ ለማኅበራቸው የሰጡት ያሳለፉትን ልምድና ገጠመኝ መነሻ በማድረግ ነበር። በቀደመ ሥራቸው ያገኟቸው በጎዳና ያሉ ችግርተኞች ከገንዘብና ከምግብ በላይ ሰው ይቸግራቸው እንደነበር ይነግሯቸው ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ እነ ዳዊት በተለያዩ ግዜያት ለሥራ ሲንቀሳቀሱ እንደተገነዘቡት ከጎዳና ላይ የሚነሱ አንዳንድ ችግርተኞች በኪሳቸው ብዙ ብር ያላቸው ነበሩ።
ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በሚያሳዝን ሁኔታ የለመኑት ገንዘብ እጃቸው ላይ እያለ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ ምግብ ይዘውላቸው እንዲመጡ ሌሎችን የመለመን አልያም ገንዘብ ከፍለው ማስመጣት ይጠበቅባቸው ነበር። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ይቸግራቸው የነበረው ቁሳዊ እርዳታ ብቻ ሳይሆን አብሯቸው የሚሆን ሰውም ነበር። በአንጻሩ አብዛኛው ሰው ቀናነቱ ካለ ቢያንስ ካለው ግዜ ላይ ብቻ ለእነዚህ ሰዎች ማካፈል ቢችል ብዙ በመሥራት ብዙዎችን ለመታደግ እንደሚችል ግልጽ ነበር።
በሌላ በኩል እንደ ግለሰብ በርካታ ሰዎች ሌሎችን ለመርዳት ፍላጎቱ ቢኖራቸውም የአቅማቸውን ጉዳይ መነሻ በማድረግ ይሄ ያንሳል፤ ይህን እንዴት እለግሳለሁ በሚል እንኳን ሳያደርጉት ሳይሞክሩት ይቀራሉ። ይህ ባህላችን ደግሞ ጠንካራ መሠረት የያዘ በመሆኑ እንኳን የውጪ ሰው ባዕድ ለመደገፍ ይቅርና ዘመድ አዝማድም ለመጠየቅ ባዶ እጅ አልያም ትንሽ ነገር የማይታሰብ በመሆኑ የብዙ ሰዎች መራራቂያ እየሆነ መጥቷል።
ይህን እያራራቀ ያለን ባህል በማስወገድ ካለን ሀሳብ፤ ካለን ዕውቀት፤ ካለን ግዜ ብቻ ለሰዎች ብናካፍል ብዙ መሥራት እንችላለን በሚል እሳቤ ነበር ማህበሩ «ካለን ብናካፍል» የሚለውን ስያሜ ያገኘው። ዳዊት እንደሚለው ለዚህ እሳቤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዋነኛ ማሳያ ናቸው። ብዙ ጊዜ አብዛኞቹ በእጃቸው ገንዘብ አልያም ቁሳቁስ አይኖራቸውም ነገር ግን ያላቸውን እውቀት ጊዜና ጉልበት በመጠቀም ውስጣቸው ፈቃደኝነት ስላለ ብቻ ብዙ ሰዎችን በቀላሉ ገላ አጥበው ጥፍር ቆርጠው ብዙዎችን ለመታደግ በቅተዋል።
በዚህ ረገድ በበርካታ ሆስፒታሎች ትኩረት የሚሻ የተለመደ ትዕይንት ወይንም ገጠመኝ አለ አንዳንድ ሕመምተኞች በርካታ አስታማሚ ያላቸው ሆነው ዘመድ አዝማድ እኔ ካላደርኩ። እኔ ካልዋልኩ እያለ ሲነታረክ ይታያል። በአንጻሩ ደግሞ በቀናት ልዩነት እየመጣ ልብስ እንኳን የሚቀይርላቸው አንድም አስታማሚ የሌላቸውን ሕመምተኞች በተመሳሳይ ሆስፒታል ማየት የተለመደ ነው።
በዚህ አይነት እነ ዳዊት የጀመሩት ሥራ ፍሬ እያፈራ ሲመጣ በአንድ ግቢ ለምን እንወስናለን በሚል እሳቤ እንቅስቃሴያቸውን ከዩኒቨርስቲው ግቢ ውጪም ለማስፋት መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። በዚህም ቤት ለቤት በመዘዋወር የመንከባከብና እንዲሁም በተለያዩ ጎዳናዎች የወደቁ ማንሳት ላይ ያተኩራሉ። ሥራቸውን ወደ ጎዳና ተዳዳሪዎች ለማዞር ያነሳሳቸው ግን አንድ አጋጣሚ ነበር።
ለተለመደ ሥራቸው ያለውን ሁኔታ ለመገንዘብ አንድ ቀን ጎንደር ከተማ እየተዘዋወሩ አዛውንቶችና አቅመ ደካሞችን ሲያናግሩ ገላችሁን የሚያጥባችሁ ማን ነው እያሉ ይጠይቋቸዋል። በወቅቱ የአብዛኞቹ ምላሽ ግን የተማከሩ ይመስል ፈጣሪ ነው «ዝናብ እያወረደ» የሚል ነበር።
ይህንን መነሻ በማድረግም በአንድ ወገን የደከሙትን ገላቸውንና ልብሳቸውን በማጠብ በሌላ በኩል በተለያዩ ምክንያቶች ስንፍናና ሱስን ጨምሮ አቅም እያላቸው የማይታጠቡትን በማስተማር በመገሰጽ ጽዳታቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ይጀምራሉ። ሥራቸውን ሲጀምሩም መነሻ ያደረጉት ጎንደር ከተማ ፒያሳ መስቀል አደባባይ ላይ የነበሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በመሰብሰብ ነበር።
በዚህ ሂደት እያሉ የጎንደር ከተማ አስተዳደሮች እየሠሩ ያሉትን ሥራ በማየታቸው አንድ ሺ ሁለት መቶ አርባ ሰባት ካሬ ሜትር ቦታ ማራኪ ክፍለ ከተማ ሸዋ ዳቦ አካባቢ ይሰጧቸዋል።
በዚህ ዓይነት የበጎ አድራጎት ሥራቸውን በስፋትና በጥራት ለማከናወን በሩ የተከፈተላቸው እነዳዊትም በቀጥታ የተቀበሉትን ቦታ በማጽዳት ማዕከል ለመገንባት ወደ ሥራ ይገባሉ። በዚህም አቅሙ ካላቸውና ፈቃደኛ ከሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት የሕንጻ መሣሪያዎችን ማሽነሪዎችን ጨምሮ በማሰባሰብ ቦታውን አጽድተው ሥራቸውን ይጀምራሉ።
በዚህ ዓይነት ማዕከሉ ተገንብቶ ሥራውን ሲጀምርም በወቅቱ ማዕከሉን እንዲቀላቀሉ የተደረጉትም በከፍተኛ ደረጃ ራስን መቆጣጠር በማያስችል የሕመምና የእርጅና ደረጃ ላይ በሚገኙ በጎንደር ዪኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል ሕክምናቸውን የሚከታተሉ።
እንዲሁም ከጎንደር ከተማ በተጨማሪ ከአጎራባች ከተሞች መተማ ደባርቅ ዳባት ጋይንትና ሌሎችም አካባቢዎች ነበር። በዚህ ሂደትም በተለይ በጎዳና የተደፈሩና የአዕምሮ ሕሙማን ሴቶች ላይ ትኩረት ያደርጉ ነበር። በዚህ አይነት ማዕከሉ ለችግር የተዳረጉ የሕጻናት፤ የአረጋውያን፤ የሴቶችና የአዕምሮ ሕሙማንን የመንከባከብ ሥራውን ይቀጥላል። ከጎዳና የሚነሱት ዜጎችም በቅድሚያ አስፈላጊው ጠቅላላ ሕክምና እንዲያገኙ የሚደረግ ሲሆን ከተነሱበት ዕለት አንስቶም በሚገቡበት መጠለያ አንጻራዊ በሆነ መልኩ የተመጣጠነ ምግብና አልባሳት እንዲያገኙ ይደረጋል።
ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ያቋረጡ ካሉ ትምህርት እንዲቀጥሉ ያልጀመሩም ካሉ እንዲጀምሩ በቂ ቁሳቁስ የማሟላትና ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራም ይሠራል። እንዲህም በተለየ ትኩረት የአዕምሮ ሕመም ያለባቸውን በቂ ሕክምና እንዲያገኙ የማድረግና ከሕክምና በኋላ ከሕመማቸው ያገገሙትን በማዕከሉ በተደራጀው የዕደ ጥበባት ስልጠና መስጫ ራሳቸውን የማብቃት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ወደማዕከሉ መግባት ላልቻሉና በየጎዳናው ለሚገኙ ችግርተኞች በየሳምንቱ የንጽሕና ማስጠበቅና አቅም ሲኖር ምገባ ይካሄዳል።
እንዲሁም በቤት ለቤት በመዘዋወርም የወር ቀለብ ልብስና ሌሎች ድጋፎችን የማድረስና በማዕከሉ በጎዳናና በየቤታቸው ለሚገኙ የሕክምና አገልግሎትና ተማሪዎች ላሉበት ቤተሰብም ባሉበት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ቋሚ የገቢ ምንጭ የሌለው ማዕከሉ እስካሁን እነዚህን ድጋፎች እያደረገ ያለው ሕዝቡ በቀጥታ በሚያደርገው የገንዘብ፤ የአይነትና የጉልበት ድጋፍ ሲሆን አንዳንድ ግዜ ለጋሾች በማዕከሉ በመገኘት ልደት፤ ተስካርና መሰል ዝግጅቶችን ስለሚያደርጉ ይህንን በመጠቀም ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ሁለት ወፍጮዎችን ለማዕከሉ ድጋፍ አድርጓል።
እነዚህን ወደ ሥራ ለማስገባት ቦታና የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሲስተካከል ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ በአንድ ወገን የማዕከሉን ወጪ በመቀነስ በሌላ በኩል እንደ ገቢ ማስገኛ በመጠቀም ማዕከሉን ለማጠናከር መታሰቡን አቶ ዳዊት ይናገራሉ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማዕከሉ ላሉም ሆነ በማዕከሉ ስር ለሚቀርቡ ሕሙማን ነጻ የሕክምና አገልግሎት የሚያደርግ ሲሆን የማዕከሉ በጎ ፈቃደኞችም በማዕከሉ አስታማሚ የሌላቸውን የመንከባከብ ሥራ ይሠራሉ። ባጠቃላይም በከተማዋ ያሉ አንዳንድ ሆቴሎች፤ በኮንስትራክሽን ሥራና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች አጠቃላይ የከተማው ነዋሪ እንዲሁም በአሜሪካ፤ እሥራኤልና አውሮፓ ያሉ የአካባቢው ተወላጆች በሚያደርጉት ድጋፍ ማዕከሉ ሥራውን እየሠራ ይገኛል።
ይህም ሆኖ ማዕከሉ ለሕጻናት ወተት ለአንዳንድ ጉዳዮች የሚጠቀምባቸው ተሽከርካሪዎች፤ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር እንዲሁም ለጽዳትና የንጽሕና መጠበቂያ እቃዎች፤ አብዛኞቹ ጠንካራ የጤና እክል የገጠማቸው በመሆኑ መንቀሳቀሻ ዊልቸር፤ ክራንች እጥረት እንዳለበት ወጣት ዳዊት ተናግሯል። በአሁኑ ወቅት ከሁለት መቶ አስር በላይ ተደጋፊዎች በማዕከሉ ይገኛሉ። በተጨማሪም በጎንደር መስቀል አደባባይና በየቤቱ በመዞር በሚሰጡት አገልግሎቶችም ከሁለት መቶ አርባ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው። እነ ዳዊት ከወር በፊትም ማዕከሉ የተመሰረተበትን ሁለተኛ ዓመታቸውን ለማክበር በቅተዋል።
በእነዚህ ግዜያትም በማዕከሉ ከቆዩት መካከል አንድ ከፍተኛ የአዕምሮ ሕመም የነበረባቸው አባት ኅብረተሰቡን ያስቸግሩ የነበሩ ወደ ሙሉ ጤንነት ተመልሰዋል። ከመተማ በአደጋ በከፍተኛ ጉዳት አጥንታቸው ተሰብሮ የነበሩ በማዕከሉ በነበራቸው ቆይታ ሙሉ ለሙሉ ጤናቸው ተመልሶ በአሁኑ ወቅት ወደሥራቸው ለመመለስ በቅተዋል።
ተጥለው ከተገኙ ሕጻናት መካከል ሁለት እስካሁን በማዕከሉ እያደጉ ሲሆን በርካታ አረጋውያንና ሕጻናት ከቤተሰባቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏል። ማዕከሉ በቦርድ የሚመራ ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በከተማዋ ያሉ ከፍተኛ ኃላፊዎችና የከተማዋን ነዋሪዎች ያካተተ ነው።
ችግሩ አገራዊ እንደመሆኑ ሁሉ መፍትሔውም አገር በቀል ሊሆን ይገባል የሚለው ወጣት ዳዊት የግለሰቦችን የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ እንደ ጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ከሪፖርት የዘለለ ፍሬውን ሕዝብ የሚቀምሰው የሚያየው ሥራ መሥራት ተችሏል።
እንዲሁም ሼልፍ የሚያሞቁ ምርምሮች ላይ ብቻ ትኩረት ከመስጠት እንደ ጎንደር ዩንቨርስቲ አመራሮች በቀጥታ በማኅበራዊ አገልግሎት በስፋት የሚሳተፉ ሊኖሩ ይገባል ይላል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን የካቲት 18 /2014