ጣሊያን ሰሐጢ ላይ እግሩን ቢዘረጋ፣
አንገብግቦ ቆላው አሉላ አባነጋ።
***
አሉላ አባነጋ የደጋ ላይ ኮሶ፣
በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተቀምሶ።
***
አሉላ አባነጋ ካስመራ ቢነሳ፣
ቢቸግረው ጣሊያን አለ ፎርሳ ፎርሳ።
***
ጣሊያን በአገርህ አልሰማህም ወሬ፣
የበዝብዞች አሽከር የነሞት አይፈሬ፣
ዘለው ጉብ ይላሉ እንደጎፈር አውሬ።
ከላይ ያለው ግጥም ጀግንነታቸውን በቃላት ለመግለፅ ለሚያዳግቱት፣ ለቆራጡ፣ ለታማኙ፣ ለኃይለኛው የጦር መሪና ተዋጊ፣ በጉንደት፣ በገራዕ፣ በኩፊት፣ በዶጋሊ፣ በዓድዋ … ከወራሪዎች ጋር ተፋልመው አንፀባራቂ ድሎችን ላስመዘገቡት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ለራስ አሉላ እንግዳ (አባ ነጋ) የተገጠመ የምስክርነት ውዳሴ ነው።
ራስ አሉላ የተወለዱት በ1840 ዓ.ም ተምቤን ውስጥ ዙቅሊ ሚካኤል በተባለ ቦታ ነው። አሉላ የገበሬ ልጅ ናቸው፤ የመሳፍንት ዘር አይደሉም። አባታቸው እንግዳ ቁቢ አሉላን ጨምሮ ሌሎች ልጆቻቸውን ራስንም ሆነ አገርን ከጥቃት መከላከል እንዴት መማር እንደሚቻል ያስተምሯቸው ነበር። አሉላ ግን ከሁሉም የላቁ ነበሩ። አሉላ በልጅነታቸው በዙቅሊ ሚካኤል ደብር ከመምህር ወልደጊዮርጊስ ዘንድ ሐይማኖታዊ ትምህርት ተምረዋል።
በወጣትነታቸው የንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ አጎት፣ የራስ አርዓያ ድምፁ፣ ባለሟል ሆነው ማገልገል ጀመሩ። የባለሟልነታቸውን ዘመን የጀመሩት የራስ አርዓያ ልጆች አገልጋይ በመሆን ነው። ራስ አርዓያ አልሞ ተኳሸና አዳኝ ይወዱ ነበር። አሉላም በአዳኝነታቸውና በአልሞ ተኳሽነታቸው እጅግ የተመሰገኑ ስለነበሩ ይህ ችሎታቸው በራስ አርዓያ ዘንድ ተወደደላቸው። ራስ አርዓያም በዘመኑ ብርቅና ተወዳጅ የነበረች ጠመንጃ ለአሉላ ሸለሟቸው። አሉላ ከአዳኝነታቸውና ከአልሞ ተኳሽነታቸው በተጨማሪ ለጌታቸው ታማኝና ተቆርቋሪ ስለነበሩ እጅግ ተወዳጅ ባለሟል ሆኑ፤ በዚህም የራስ አርዓያ ምስጢረኛና አንጋች መሆን ቻሉ።
በየአውራጃዎቹ እየተዘዋወሩ የጌታቸውን ጉዳዮች ያስፈፅማሉ፤ ሕዝቡ ለአለቃቸው የሚያቀርበውን ጉዳይ ይቀበላሉ፤ ከነጋዴዎች ጋር ወደ ምጽዋ እየሄዱ የባህር ማዶ እቃዎችንና የጦር መሳሪያዎችን ይገዛሉ። እነዚህ ተግባራት የአሉላን እውቀትና የዕይታ አድማስ አሰፉላቸው። በተለይም ከተለያዩ አገራት ተነስተው በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፉ መርከቦች ወደ ምፅዋ ጎራ ብለው ያራግፏቸውና ይጭኗቸው የነበሩ ሸቀጣ ሸቀጦችና የጦር መሳሪያዎች ለራስ አርዓያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑና አካባቢውን ከውጭ ጠላቶች መጠበቅና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ በሚገባ ተገነዘቡ።
ፕሮፌሰር ንጉሴ አየለ ‹‹Ras Alula and Ethiopia’s Struggle Against Expansionism and Colonialism፡ 1872-1897›› በተሰኘ ጽሑፋቸው እንዳብራሩት፤ አሉላ ወደ ደጃዝማች ካሣ ምርጫ (በኋላ አፄ ዮሐንስ ፬ተኛ) ቤት ከተዛወሩ በኋላ ሹመትን በሹመት ላይ በመደረብ ወደፊት ገሰገሱ። በመጀመሪያ እልፍኝ አስከልካይ ቀጥሎም አጋፋሪነትን ተሾሙ። ደጃዝማች ካሣ በ1864 ዓ.ም አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ተብለው ሲነግሱ አሉላ የሻለቅነትን ማዕረግ አገኙ፤ የንጉሰ ነገሥቱን ሊጋባነት ማዕረግም ደርበው ያዙ።
በከዲቭ እስማኤል የሚመራው የግብፅ መንግሥት ኢትዮጵያን የመውረር የረጅም ጊዜ ዓላማውን ለማሳካት ሰፊ ዝግጅት ካደረገ በኋላ የኢትዮጵያን ግዛቶች ወረረ። በኅዳር 1868 ዓ.ም ጉንደት ላይ ጦርነት ተደርጎ ወራሪ የግብፅ ጦር በንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ጦር ተደመሰሰ። የግብፅ ጦር ዋና አዛዡ አረንድሮፕን ጨምሮ በርካታ የወራሪው ኃይል አዛዦችና ወታደሮች ተገደሉ፤ ግማሹ ተማረከ፤ ጥቂቶቹ ብቻ ሸሽተው አመለጡ። በውጊያው ላይ አስደናቂ ጀብዱ ከፈፀሙት የጦር አበጋዞች መካከል አንዱ አሉላ ነበሩ።
በጉንደቱ ሽንፈት ክፉኛ የተበሳጨውና ያፈረው የግብፅ መንግሥት ሽንፈቱን ለመበቀል ለዳግም ወረራ ተሰናዳ። በመሐመድ ራቲብ ፓሻ የተመራው የግብፅ ጦር በመጋቢት 1868 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ገጥሞ የለመደውን ሽንፈት ተጎነጨ። በጉንደቱ ውጊያ የገጠሙትን መሞት፣ በኢትዮጵያውያን መማረክና መሸሽ ፈርዶበት ጉራዕም ላይ ደገማቸው። ለዚህም ድል መገኘት የአሉላ ሚና እጅግ የገዘፈ ነበር።
ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ የዶጋሊ ጦርነት ድል 100ኛ ዓመት መታሰቢያን በማስመልከት በተዘጋጀው ልዩ የመታሰቢያ ታሪካዊ ጉባዔ ላይ ባቀረቡት ጽሑፋቸው አሉላ የኢትዮጵያን ሰራዊት በአምስት በመክፈልና ግብፆቹን በማስጨነቅ ከምሽጋቸው ወጥተው ሜዳ ላይ እንዲዋጉ እንዳስገደዷቸው ገልፀዋል። የግብፆች ኢትዮጵያን የመያዝ ምኞታቸው በጉራዕ ሽንፈታቸው ምክንያት ቅዠት ሆኖ ቀረ።
ዘሪሁን አበበ ይግዛው በ2006 ዓ.ም ‹‹አሉላ አባ ነጋ፡ የጉራዕው አንበሳ ከ138 ዓመታት በኋላ›› በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ ‹‹… የጉራዕ ውጊያ ለግብፃውያን እጅጉን አስተማሪ የሆነ ጦርነት ነበር። ደጋግመው ከጉራዕ በፊት የሞከሯቸው ጦርነቶች በሰው ቁጥር ማነስ የመጣ የመሰላቸው ግብፃውያን መሪዎች እጅግ ብዙ የሚባል ቁጥር የነበረውና በአውሮፓውያን፣ አሜሪካውያን እና ቱርካውያን ምክር እየተደገፈ ከዘመናዊ የጦር መሣሪያ ጋር የዘመተው ጦራቸው ድባቅ እንደተመታ አስተውለዋል። ኢትዮጵያን የመያዝ ጉራቸውም የጉራዕ ጦርነት ላይ አሉላ በመራው ጦር ጉራ ሆኖ ቀርቷል። የኢትዮጵያም ሉአላዊነት በቆራጥ ጀግኖች ልጆቿ ተከበረ …›› ብለዋል።
በ1870 ዓ.ም ሻለቃ አሉላ በራስ ማዕረግ የሐማሴንና የሰራዬ ገዥ ሆነው ተሾሙ። ኃይላቸው እየደረጀና ዝናቸውም እየናኘ ሄደ። ከንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ጋር የተጣሉ ባላባቶችን እያስታረቁና ለንጉሰ ነገሥቱ ያልገበረውን አካባቢ እያስገበሩ አገር ማቅናታቸውንም ቀጠሉ።
ከግብፆች በተጨማሪ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት ዝርፊያ ይፈፅሙ የነበሩት ማህዲስቶች (ደርቡሾች) ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አደጋ ነበሩ። በ1877 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ዋና የጦር አለቃቸውን ራስ አሉላን ከ10ሺ ወታደሮች ጋር ወደ ኩፊት ላኳቸው። ማሸነፍ የዘወትር ተግባራቸው የሆነው ራስ አሉላም የማህዲስቶቹን ጦር አሸንፈው በሕይወት የተረፈውንም ከአካባቢው ጠራርገው አባረሩት። በዚህ ጦርነት ላይ ከኢትዮጵያ በኩል የደረሰው ጉዳትም ከፍተኛ ስለመሆኑና ራስ አሉላም ቆስለው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
የራስ አሉላን ክንድ የሚቀምሰው ተረኛው የኢትዮጵያ ጠላት የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ነው። ራስ አሉላ እጅግ በረቀቀ ሴራ ከምፅዋ ጀምሮ ሌሎች አካባቢዎችን የያዙት ጣሊያኖች አካባቢዎቹን ለቅቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ አሳስበዋቸዋል። ራስ አሉላን አጥብቀው የሚፈሯቸውና የሚጠሏቸው ወራሪዎቹ ጣሊያኖች ግን አሻፈረን ብለው ቀሩ። ከነበሩበት አልፈው ቦታ በመውረር ምሽግ መቆፈርና ለውጊያ መዘጋጀት ጀመሩ። ራስ አሉላም ትዕግስታቸው በማለቁ ጣሊያኖችን ለመቅጣት ተዘጋጁ።
ራስ አሉላ ማህዲቶችን ለመውጋት ከሄዱበት ከከሰላ ሲመለሱ ጊንዳ በኩል ወደ ሰሀጢ ወርደው በሰሀጢ በመሸገው የኢጣሊያ ጦር ላይ ውጊያ ከፈቱበት። ጣሊያኖች ከምሽጋቸው ወጥተው ለመዋጋት ሳይደፍሩ ቀሩ። ራስ አሉላም የሰሀጢን ምሽግ ትተው ወደ ዶጋሊ ወርደው ሰፈሩ። በሰሀጢ ምሽግ ውስጥ ከነበረው የኢጣሊያ ጦር ባሻገር ሌላ ተጨማሪ ኃይል ከምንኩሉ ተነስቶ ዶጋሊ ደረሰ። የራስ አሉላ ጦር ስፍራውን ይዞ ይጠባበቅ ስለነበር የኢጣሊያ ጦር ሳያስበው ከራስ አሉላ ጦር የእሩምታ ተኩስ ላይ ወደቀ። በውጊያው የኢጣሊያ ዋና የጦር አዛዥ ቶማሶ ክሪስቶፎሪስን ጨምሮ ከ400 በላይ የኢጣሊያ ወታደሮች ሞተዋል።
ከዶጋሊው ድል በኋላ ስለራስ አሉላ ጀግንነት ከተገጠሙ ግጥሞች መካከል፡-
ዮሐንስ መብቱን ላሉላ ቢሰጠው፣
እንደቀትር እሳት ቱርክን ገላመጠው፣
ጣልያንም ወደቀ እያንቀጠቀጠው፣
አጭዶና ከምሮ እንደገብስ አሰጣው።
***
ተው ተመከር ጣሊያን ይሻልሃል ምክር፣
ሰሀጢ ላይ ሆነህ መሬት ብትቆፍር፣
ኋላ ይሆንሃል ላንተው መቃብር፣
ይቺ አገር ኢትዮጵያ የበዝብዝ አገር፣
ምንም አትቃጣ እንደአራስ ነብር።
የሚሉት ይጠቀሳሉ።
ራስ አሉላ ዶጋሊ ላይ ወራሪውን የኢጣሊያ ሰራዊት ዶጋአመድ ቢያደርጉትም ‹‹ያለፈቃዴ ተዋጋህ›› የሚል ቅሬታ በንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ዘንድ አሳደረ። ንጉሰ ነገሥቱም የጦር አዛዥነቱን ከራስ አሉላ በማንሳት ለታላቅ ወንድማቸው ልጅ ለራስ ቢትወደድ ኃይለማርያም ጉግሳ ሰጥተው ራስ አሉላን በሐማሴን ገዢነታቸው ብቻ ወሰኗቸው።
ራስ አሉላ የመሳፍንት ዘር ሳይኖራቸው በችሎታቸው ብቻ ለከፍተኛ ስልጣን መብቃታቸው ያልተዋጠላቸው የንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ መሳፍንትና መኳንንት እንዲሁም የራስ አሉላ ተፎካካሪዎችና ጠላቶች ራስ አሉላን ለመወንጀል አጋጣሚ ስላገኙ ንጉሰ ነገሥቱ ከላይ የተመለከተውን ውሳኔ እንዲወስኑ ሳይገፋፏቸው እንዳልቀሩ ይገመታል።
በሌላ በኩል ‹‹ጥቁር ነጭን አያሸንፍም›› ባዮቹና የቅኝ ገዢዎች ሽንፈት አፍሪካን የመቀራመት ሕልማቸውን እንዳያጨናግፍባቸው የፈሩት እነእንግሊዝም በራስ አሉላ ድርጊት ደንግጠውና ተናደው ስለነበር ጉዳዩን በሴራ አጅበው ለንጉሰ ነገሥቱ ስሞታ ሳያቀርቡ አልቀሩም።
ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ በመጋቢት 1881 ዓ.ም መተማ ላይ ከማህዲስቶች ጋር ሲዋጉ መሞታቸው ለራስ አሉላ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ክስተት ሆነባቸው። ከአፄ ዮሐንስ ፬ኛ በመቀጠል የንግሥናውን ዘውድ በጫኑት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥትም የራስ አሉላ የጀግንነት ተግባርና አበርክቶ ቀጠለ።
ኢትዮጵያን የመውረርና ቅኝ ግዛቷ የማድረግ ሕልሟን ለማሳካት ሰፊ ዝግጅት ስታደርግ የቆየችው ኢጣሊያ በየካቲት 1888 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጋር ባደረገችውና እጅግ አሰቃቂ ሽንፈትን በተከናነበችበት የዓድዋ ጦርነት ላይ አኩሪ የጀግንነት ታሪክ ከፈፀሙት ኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎች መካከል አንዱ ራስ አሉላ ነበሩ። ራስ አሉላ በጦርነቱ የጀኔራል ቪቶሪዮ ዳቦርሜዳን ጦር በመደምሰስ የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ከሌሎቹ ወራሪዎች በተለየ መልኩ ክንዳቸውን ደጋግሞ እንዲቀምስ አድርገውታል።
ከዓድዋ ድል በኋላ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ (ከራስ መንገሻ ጋር በመስማማት) ራስ አሉላን የዓድዋና አካባቢው ገዢ አድርገው ሾሟቸው። ይሁን እንጂ ከባላባት ወገን ያልሆኑት ራስ አሉላ ሰፊ ግዛት ሊሰጣቸው አይገባም የሚለው የተፎካካሪዎቻቸው ተቃውሞ ቀጠለ። ሕዝቡ ግን ራስ አሉላን በጀግንነታቸውና በፍርድ አዋቂነታቸው ይወዳቸው ስለነበር ገዢነታቸው ፀደቀላቸው።
ብላቴንጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ‹‹የሕይወት ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹ … ራስ አሉላ አባነጋ የሐማሴንና የአውራጃዋ ሁሉ ገዢ ነበሩ። በጀግንነታቸውም እጅግ የተፈሩና የታወቁ ስለሆኑ በሐማሴን በኩል የመጣውን የውጭ ጠላት ሁሉ ድል እያደረጉ ይመልሱት ነበር። በጨዋታ ላይ የጀግንነት ስራ በተነሳ ጊዜ ‹ራስ ጎበና በሸዋ፣ ራስ አሉላ በትግሬ እና ራስ ደርሶ በጎጃም› እየተባሉ ሲመሰገኑ ይኖራሉ … ›› በማለት ገልጸዋል።
ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ‹‹አሉላ አባነጋ›› በተሰኘው ታሪካዊ የልብ ወልድ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ራስ አሉላን የሚያውቋቸውን ኤርትራውያን አዛውንቶችን ጠይቀው እንደጻፉት፤ ራስ አሉላ ቆራጥ፣ ጀግና፣ ፍትሕ አዋቂ፣ ትሁት፣ ሩህሩህ፣ ሐይማኖተኛ … ነበሩ። በመከራና በጭንቅ ጊዜ እውነተኛና ኃይለኛ አርበኛ ነበሩ። የጦርነት ጉዳይ ይወዱ ስለነበር በየጊዜው ሰራዊታቸውን እየሰበሰቡ ጠመንጃ፣ ጎራዴና ሰይፍ እያደሉ ‹‹ጠመንጃህን ተኩስበት፤ ጎራዴህን ምዘዝ፤ ባለሰይፍም ሩጥ›› እያሉ የወታደሮቻቸውን ቁመና የመፈተሽ ልማድ ነበራቸው። በአካላዊ ቁመናቸውም የቀይ ዳማ፣ ባለመጠነኛ ውፍረትና መካከለኛ ቁመት ነበሩ። ሹሩባ ይሰሩ ነበር፤ በእግሮቻቸው ላይም የወርቅ አልቦ ወርቀዘቦ ያደርጉ ነበር። በርካታ የውጭ አገራት የታሪክ ፀሐፊዎች ለራስ አሉላ ያላቸውን አድናቆት በመጽሐፎቻቸው ውስጥ አካትተው ጽፈውታል።
እንግሊዛዊው ዋይልድ ‹‹ … ራስ አሉላ ቁመታቸው አምስት ጫማ ከዘጠኝ አፅቅ ይሆናል። ደረታቸው ሰፋ ያለና ትከሻቸው የሞላ ስለነበር ቁመታቸውን ውጦታል። ጎበዝ እንዲሁም ፈረስ መጋለብና ተኩስ የሚያዘወትሩ ነበሩ። ቀልጣፋ፣ አፍንጫቸው ቀጥ ያለ፣ አፋቸው ጠባብ፣ ጥርሶቻቸው የሚያማምሩ እንዲሁም ፀጉራቸው ወርቃማ ነበር። በግል እንግዳ ሲያነጋግሩ ካሆነ በቀር ከአሽከሮቻው ፊት አይስቁም ነበር። ፈገግ ሲሉ ያስደስታሉ። ተጨዋችነት የሚታይባቸው ቢሆኑም በቁም ነገር ንግግር ላይ ዝንፍ የሚሉ እንደሐውልት ድርው ያሉ ናቸው። በጣም ዝነኛ ናቸው፤ ፈጣንና የተመሰገኑ አዝማችም ናቸው። የውጊያ ስልት ያውቃሉ። የአገራቸውን ጉዳይ ቸል የማይሉ ስለነበሩ የግብጾችን ተንኮል ስለደረሱበት ድል ሊያደርጓቸው ችለዋል … ›› በማለት ስለራስ አሉላ አካላዊ ቁመና፣ ግላዊ ባህርይና ችሎታ ጽፈዋል።
ብዙዎች ‹‹አፍሪካዊው የጦር ጀኔራል›› የሚሏቸው ራስ አሉላ፤ ከሶስት ዋና ዋና የኢትዮጵያ የወቅቱ ጠላቶች ጋር ተዋግተዋል። በኅዳር 1868 ከተደረገው የጉንደት ጦርነት ጀምሮ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም እስከተደረገው የዓድዋ ጦርነት ድረስ ራስ አሉላ አባ ነጋ አስራ ሁለት ጦርነቶችን ከውጭ ወራሪ ኃይሎች ጋር የተዋጉ ሲሆን በዋናነትም ከኦቶማን ግብጽ ተስፋፊዎች፣ ከማህዲስት ወራሪዎች እና ከኢጣሊያ ቅኝ ገዥዎች ጋር ያደረጓቸው ናቸው።
አሉላ ገና በራስ አርዓያ ድምፁ ቤት ባለሟል ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕለተሞታቸው ድረስ ብዙ የመረሩ ጠላቶችና ተፎካካሪዎች ነበሯቸው። በካርቱም፣ በካይሮ፣ በለንደንና በሮም የነበሩትን የኢትዮጵያ ጠላቶች እንዲሁም በንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ቤተ መንግሥት ዙሪያ አሰፍስፈው የነበሩትን ተቃዋሚዎቻቸውን በትዕግሥት፣ በቆራጥነትና በዘዴ ተቋቁመዋቸው አልፈዋል። ምንም እንኳ የራስ አሉላ ጠላቶችና ተፎካካሪዎች ተራ በተራ ቢወድቁም ከተፎካካሪዎቻቸው አንዱ ከነበሩት ከራስ ሐጎስ ጋር የገቡበት ጠብ ለታላቁ ጀግና ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሊሆን ችሏል። ራስ አሉላና ራስ ሐጎስ ባደረጉት ጦርነት ራስ ሐጎስ ወዲያውኑ ሲሞቱ ክፉኛ ቆስለው የነበሩት ራስ አሉላ ከወራት ሕመም በኋላ በየካቲት ወር 1889 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ስርዓተ ቀብራቸው በተፈፀመበት አባ ገሪማ ገዳም በወታደራዊው መንግሥት (ደርግ) የአገዛዝ ወቅት የመታሰቢያ ሐውልት ተሰርቶላቸዋል። ሐውልቱን የመረቁትም የወቅቱ የአገሪቱ መሪ ሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ነበሩ። መቐለ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ‹‹መቐለ አሉላ አባነጋ ኤርፖርት›› ተብሎ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የጀግናውን ስም ለማስታወስ በርካታ ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸውን ‹‹አሉላ›› እያሉ ሰይመዋል። አንጋፋው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትም ወንድ ልጃቸውን ‹‹አሉላ›› ብለው ስም አውጥተውለታል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2014