እስራኤላዊው ጋዜጠኛ አሞስ ኦዝ ነገርን አለቅጥ ስለማቃለል ሲናገር፡- «ጥያቄዎች እየጠነከሩ እና እየተወሳሰቡ ሲሄዱ፤ ሰዎች ቀላል መልሶችን ወደ መፈለግ ያዘነብላሉ። በአንድ አረፍተ ነገር የሚያለቅ መልስ ይሻሉ።
ያ መልስ ለችግሮቻችን ሁሉ ተጠያቂ የሆነውን ግለሰብ እንዲጠቁመን እንፈልጋለን። ያ መልስ ያንን አንድ ግለሰብ ወይም አካል ካስወገድን ችግሮቻችን ሁሉ መቋጫ እንደሚያገኙ እንዲያሳየንም እንፈልጋለን።» ሲል ያብራራል።
ኢትዮጵያውያን አሁን እዚህ ዓይነት ስሜት ውስጥ ያለን ይመስለኛል። ውስብስብ ለሆነው ችግራችን አንድ ቁርጥ ያለ መልስ የምንፈልግ ዓይነት ሆነናል። ለአንዳንድ ሰዎች እነ እገሌ ወርደው እነ እገሌ ቢሾሙ ችግራችን በሙሉ በአንዴ የሚቀረፍ ሆኖ ይታያቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ እነ እገሌ ቢታሰሩ ችግራችን በሙሉ መቋጫውን የሚያገኝ ሆኖ ይሰማቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ የችግሩ ምንጭ የሆነ ብሔር እና ሃይማኖት ስለሆነ እሱን መላ ማለት ችግሩን ይቋጨዋል የሚል እምነት አላቸው፤ ወዘተ.።
ብቻ ሁሉም ሰው ችግሩ አንድ ቦታ ላይ እንዳለ ያ ችግር ፈጣሪ ከተኮረኮመ ችግሩ በሙሉ አብሮ እንደሚሸሽ የሚያምን ነው። ሀቁ ግን ከዚያ የተለየ ነው። እንደ አገር ያለንበት ችግር ውስብስብ ነው። አንድ ቀላል እና ቁርጥ ያለ መልስ የለውም።
ችግሩ የመወሳሰቡን ያህል መፍትሄውም እንዲሁ ውስብስብ ነው። ያን አለመረዳት ግን ነገሩን ቀላል አያደርገውም። ይልቁኑ መፍትሄው የችግሩን ግዝፈት እና ውስብስብነት ተረድቶ በዚያው መጠን መስራት ነው። ለምሳሌ የአገራችንን ጦርነት እንመልከት። ብዙ ሰዎች የችግሮች ራስ የሆነውን ሕወሓትን ሙሉ ለሙሉ በመደምሰስ ብቻ ጦርነቱን ማጠናቀቅ እንደሚቻል ያምናሉ፤ ሀሳቡ ችግር የለበትም።
ሕወሓት ችግር ፈጣሪ ኃይል ነው፤ ስለዚህም ሕወሓትን ማስወገድ ብዙ ችግሮችን መቋጨት ያስችላል። ነገር ግን የሕወሓት መወገድ ለብቻው ነገሮችን ይቋጫል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ይሄ ነገርን አቃልሎ መረዳት ነው። ጦርነቱ ወታደራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊ፤ (አቤል ገ/ኪዳን) ዲፕሎማሲያዊ እና ሰብአዊ አንድምታ አለው።
ስለዚህም ወታደራዊው ጎን ብቻ በድል ቢጠናቀቅ እንኳን ሌሎቹ ነገሮች እስኪስተካከሉ ሙሉ ድል ተገኘ ማለት አይቻልም። በጦር ሜዳው የተገኘው ድል በሌሎቹም ዘርፎች እንዲደገም ጠንከር ያለ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ብዙዎች ግን ይሄን አይረዱትም ወይም መረዳትም አይፈልጉም።
በጦር ሜዳ ውሎው ብቻ ነገሩን ሊቋጩት ይሻሉ። ነገር ግን ጦርነቱን በሕወሓት ልክ ብቻ መመዘን ያዋጣናል ወይ የሚለውን ስናየው አያዋጣም። ይሄ ጦርነት ጽንፈኛ ብሔርተኝነት ከህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት የተፋለመበት፤ ኢትዮጵያ ወዳጆቿን የለየችበት፤ ዓለምአቀፍ ተቋማትን ጨምሮ የውጭ ኃይሎች እጃቸውን ያስገቡበት፣ የአገር ውስጥ ፖለቲካ አዲስ አሰላለፍ የያዘበት እና ሌሎችም ብዙ ገጽታዎች ያሉት ጦርነት ነበር።
ስለዚህም ይህ ጦርነት እንዲህ በአንድ ነጠላ እይታ ብቻ የሚታይ አይደለም። ሰፊ ነው፤ ውስብስብ ነው። ሕዝብ የሚያውቃቸውም የማያውቃቸውም፤ የሚገነዘባቸውም የረሳቸውም ብዙ ነገሮች በውስጥ ተካሂደዋል። ያንን መገንዘብ ያስፈልጋል። ነገርን ከትክክለኛ ገጽታው በታች አቅልሎ መመልከት አደገኛ ነው። ለሽንፈት ይዳርጋል። ነገሮችን አለቅጥ የሚያካብዱ ሰዎች ለጭንቀት በሽታ የሚጋለጡትን ያህል ነገሮችን አለቅጥ የሚያቃልሉ ሰዎችም በሽታቸው ሳይታወቅ ደህና ነኝ እያሉ ይሞታሉ።
በሀኪም እና በታማሚው መሀከል ያለው ልዩነትም ይሄ ነው። ታማሚው ህመሙ የሚሰማውን ቦታ ብቻ ነው የሚያውቀው፤ ከሀኪሙ የሚፈልገውም ያን ቦታ ህመሙን የሚያስቆም ነገር እንዲሰጠው እና እርፍ እንዲል ነው። ሀኪም ግን እንደዚህ አያስብም።
የህመሙ ምንጭ ምንድን ነው? ህመሙ ምን ዓይነት ምልክት አለው? ምን ዓይነት መድኃኒት ቢሰጠው እና ለምን ያህል ጊዜ ቢውጠው ይድናል? መድኃኒቱ ሌላ ችግር እንዳይፈጥር ምን መደረግ አለበት? በሽታው ዳግም እንዳያገረሽ ምን መደረግ አለበት? ወዘተ.. ይመረምራል።
አንዳንዴ ለታማሚው ትርጉም የማይሰጥ የሚመስል ምርመራዎችን ያዝዛል። ለምን? ምክንያቱም በሽታውን በትክክል መረዳት የሚቻለው እና ፍቱን መድኃኒት ማዘዝ የሚቻለው በዚያ መንገድ ስለሆነ ነው። ለዚህ የሚሆን አንድ እውነተኛ ምሳሌ እንመልከት። ዲ/ን አቤል ካሳሁን በፌስቡክ ገጹ የጻፈው ነው።
እንደ ጎርጎርዮሳውያኑ አቆጣጠር በ1847 ዓ.ም. በኦስትሪያ ቬና ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ዕውቁ የማኅጸን ሐኪም ኢግናዝ ሴሞቫይስ (Ignaz Semmelweis) በዳይሬክተርነት ይሠራ ነበር።
እርሱም በሚመራው የሕክምና ክፍል (ward) ብዙ ነፍሰ ጡር ሴቶች እየመጡ የጤና ክትትል ያደርጋሉ። በአጠቃላይ ከሚመጡት ነፍሰ ጡሮች መካከል ከስድስቱ አንዷ በዚያ ክፍል ምርመራ የተደረገላት ሴት በኃይለኛ ንዳድ ተይዛ ትሞት ነበር።
የእነዚህም ሟች ሴቶች አስከሬን ምርመራ ደግሞ ከቆዳቸው በታች ባለው የሰውነት ክፍላቸው፣ ደረታቸው አካባቢ ባለው ክፍት ቦታ እና የዓይኖቻቸው ኳሶች በተቀመጡባቸው ሰርጓዳ ክፍሎች ውስጥ መግል ይታይ ነበር። ሴሞቫይስም እርሱ በሚመራው የሆስፒታሉ ዋርድ ሆነ በአጠቃላይ በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙት ሆስፒታሎች ውስጥ እየታየ ባለው የእናቶች ሞት እጅግ ተጨነቀ።
አንዲት ነፍሰ ጡር ለዚህ ሥራ ብቻ በተመደበች አዋላጅ አማካኝነት ስትወልድ የሞቱ መጠን ወደ 3% የሚቀንስ ሲሆን፣ የዚያች እርጉዝ ሴት ምርጫ የተሻለ ልምድና ዕውቀት ባላቸው ሐኪሞች እጅ መውለድ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ የሞቱ መጠን ወደ 18% ያሻቅባል። ዶ/ር ሴሞቫይስ ባረገዙ ሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ይህን እልቂት ለመግታት ብዙ ጥረት ቢያደርግም የሞታቸውን ቁጥር ግን ሊቀንስ አልቻለም።
እንዲያውም ቢጨንቀው ሌሊት ወደ መቅደሱ ሲገባ ካህኑ የሚደውለው የቤተ ክርስቲያን ደወል እያስደነገጣቸው ይሆናል የሚታመሙት ብሎ በማሰብ ካህኑን በጸጥታ ወደ መቅደስ እንዲገባ አድርጎም እንደነበር ተጽፏል። ይሁን እንጂ ነገሩ አንድም መፍትሔ ጠብ አላደረገም።
ታዲያ ዶክተሩ በዚህ አጣብቂኝ መካከል ሆኖ ሲያሰላስል ሳለ አንድ ነገር ተመለከተ። ይኸውም በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ ወጣት የሕክምና ተማሪዎች የተለመደውን የእለት ክንውናቸውን፣ ማለትም የሞቱትን እናቶች አስከሬን መመርመር፣ ቀጥለውም በጎድጓዳ ሳህን ውስጥ ባለ በደም በደፈረሰ ውኃ እጆቻቸውን በመለቅለቅ የጋራ በሆነ ፎጣ አድርቀው በቀጥታ ለሕክምና የመጣችን ሴት የአካል ምርመራ ሲያደርጉ አየ። በርግጥ ይህን የመሰለው ተግባር pathologyን ለተረዳ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለሚገኝ ሰው በጣም እንግዳ ሊሆንበት ይችላል።
‹በጤነኛ አእምሮው ያለ አንድ ሐኪም የሞተን አካል በነካ እጁ ምንም ዓይነት የንጽሕና መጠበቂያ ጥንቃቄ ሳያደርግ እንዴት በሕይወት ያለችን ሴት ሰውነት መልሶ ይመረምራል?› ብሎ መጠየቁም አይቀርም። ነገር ግን በአውሮፓው ዓለም በአሥራ ዘጠነኛው ምእት ዓመት አጋማሽ «ጀርም» የሚባለው በሽታ አምጪ ስውር ሕዋስ የማይታወቅ እንግዳ ሐሳብ ነበር። በማጉያ መሣሪያም አይተውት አያውቁም። ከፍተኛ ጥፋት የማምጣት ኃይሉንም ገና በሚገባ አልተገነዘቡም ነበር።
ዶ/ር ሴሞቫይስም እርሱ ባለበት ዋርድ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ሁሉ ማናቸውንም አካላዊ ምርመራ ከማድረጋቸው በፊትም ሆነ ካደረጉ በኋላ እጃቸውን በክሎሪን ውሕድ እንዲታጠቡ ጥብቅ ትእዛዝ አወጣ። ይህ በሆነ በሦስት ወራት ውስጥም የእናቶች ሞት መጠን ከ18% ወደ 1% ወረደ። ሐኪሙ ሴሞቫይስ የAntiseptic ጉዳይ ወደ ሕክምናው ትግበራ እንዲገባ በማድረግ የብዙ እናቶችን ሕይወት በመታደጉ በዚህ አስደናቂ ግኝቱ እስከ ዛሬ ድረስ በታሪክ ሲመሰገን ይኖራል። እንግዲህ ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን ዶ/ር ሴሞቫይስ ነገሩን አለቅጥ አቃልሎ ቢመለከተው ኖሮ ታሪካዊው መድኃኒት ሊገኝ አይችልም።
ነገር ግን ከጊዜያዊ ቀላል መፍትሄ ይልቅ ጊዜ ወስዶ አሰበ። አስቦም አልቀረ መድኃኒትን አገኘ። የኢትዮጵያም ችግር ልክ እንደነዚህ ሴቶች ችግር ነው። ውስብስብ ነው። ዋነኞቹ ጀርሞች ከፊት ለፊት በአይን አይታዩም። ስለዚህም ጥልቅ ምልከታ ያስፈልገዋል።
ከጥልቅ ምልከታ በኋላም ነው ሁነኛ መፍትሄ የሚያገኘው። ስለዚህም ቀላል መፍትሄ በመፈልግ አንድከም። ይልቁኑ ጊዜያችን እና ጉልበታችን ችግራችንን በቅጡ ለመረዳት እናውለው። ከዚያ መፍትሄው በእጃችን ነው።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ጥር 30/2014