የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአጭር፣ መካከለኛ፣ 3ሺ ሜትር መሰናክል፣ የርምጃና የሜዳ ተግባራት ውድድሩን ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የማዘውተሪያ ስፍራ ላይ ያካሂዳል።
ውድድሩ ዛሬ ሲጀመርም በተለያዩ ርቀቶችና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች በርካታ የማጣሪያና የፍፃሜ ፉክክሮች እንደሚካሄዱ ታውቋል። ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስቲያ በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ በውድድሩ 412 ወንድና 282 ሴት በአጠቃላይ 707 አትሌቶች እንደሚሳተፉ ገልጿል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ማብራሪያ የሰጡት የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያና የተሳትፎና ውድድር የሥራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
በውድድሩ ሁለት ክልሎችና አንድ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ሃያ ሁለት ክለቦችና ተቋማት ተሳታፊ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ውድድሩ አትሌቶች በስልጠና ያገኙትን ክህሎትና እውቀት እንዲለኩበት ታስቦ በየዓመቱ ከሚከናወኑ አገር አቀፍ ውድድሮች አንዱ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ተሳታፊ የሚሆኑትም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙና እውቅና የተሰጣቸው ክለቦች፣ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ተቋማት እንደሚሆኑ ታውቋል። ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ አምና
በአገር ውስጥ የሚካሄዱ በርካታ ውድድሮች መሰረዛቸውን ተከትሎ በርካታ አትሌቶች አቋማቸውን የሚፈትሹባቸው ውድድሮች ማግኘት እንዳልቻሉ ይታወቃል። ዘንድሮም ከፀጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ በርካታ ውድድሮች እንደማይኖሩ ስጋት ቢፈጠርም ፌዴሬሽኑ ለአትሌቶች የውድድር እድሎችን መፍጠር በሚያስችሉ አጋጣሚዎች ተጠቅሞ ይህን ውድድር ሊያዘጋጅ ችሏል።
ይሁን እንጂ ውድድሩ እንዳለፉት ዓመታት አገር አቀፍ ቻምፒዮናዎች ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉበት ሊሆን አልቻለም። ያም ሆኖ በውድድሩ የሚሳተፉ አትሌቶች ቁጥር ሲታይ በርካታ አትሌቶችን በብዙ መልኩ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ውድድሩ በአጭር፣ በመካከለኛ፣ 3ሺ ሜትር መሰናክል፣ የሜዳ ተግባራትና የርምጃ ውድድር አትሌቶች የውድድር እድል መፍጠርን አላማ አድርጎ የሚካሄድ ነው።
ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራትም ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል። በውድድሩ የተለያዩ አርባ ዓይነት ፉክክሮች ይስተናገዳሉ፤ በአጭር ርቀት፣ 3ሺ ሜትር መሰናክል፣ የሜዳ ተግባራት (ውርወራና ዝላይ)፣ በሪሌ(ዱላ ቅብብል)፣ የርምጃ ውድድሮች በተለያዩ ርቀቶች አትሌቶች ተፎካካሪ ይሆናሉ።
ከነዚህም መካከል አስራ ዘጠኙ ፉክክሮች በሴቶች መካከል የሚካሄዱ ሲሆን ሃያ አንዱ በወንዶች መካከል የሚካሄዱ ናቸው። በእያንዳንዱ የውድድር ዓይነት ከአንድ እስከ ሦስት ባለው ደረጃ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች የወርቅ፣ ብርና የነሐስ ሜዳሊያ የሚበረከት ሲሆን፣ የገንዘብ ሽልማትም እንደሚኖር ተገልጿል። በውድድሩ በቡድን ነጥብ የወንድና የሴት አሸናፊ በተናጠል የዋንጫ ሽልማት ይበረከትለታል።
የወንድና የሴት ነጥብ ተደምሮ በአጠቃላይ ነጥብ የቡድን አሸናፊ የሚሆነው ዋንጫ የሚበረከትለት ይሆናል።
ፌዴሬሽኑ ይህን ውድድር በተሳካ ሁኔታ ለመምራት መቶ ስልሳ ሰባት የሰው ኃይል ያዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል። ለሽልማትና ለውድድር ማስኬጃ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
በተያያዘም የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ‹‹ለኢትዮጵያ ሠላም እሮጣለሁ›› በሚል መሪ ቃል ታኅሣሥ 24/2014 ዓ.ም የ10 ኪሎ ሜትር ሕዝባዊ ሩጫ ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቁን የማህበሩ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ማርቆስ ገነቴ በመግለጫው ላይ ተገኝቶ አስታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2014