ሙዚቃ በሁሉም ሰው ውስጥ ያለች ጸጋ ናት።ድምጻዊነት ግን ለጥቂቶች የተሰጠ ልዩ ተሰጥኦ ነው።ግጥምን ጽፈው ፤ ዜማን ቀምሮ ከሙዚቃ ጋር የማዋሀድ ጸጋ ግን በጣም ለጥቂት ሰዎች የተሰጠች ልዩ ጸጋ ናት።ከነዚህ ባለ ልዩ ጸጋ ሰዎች መካከል ዛሬ ስለአንዱ እናወጋለን።ብዙዎች ማሬ ማሬ በሚለው ነጠላ ዜማው ያወቁት እና አልበሙን ያደነቁለት ድምጻዊ እሱባለው ይታየው የዛሬው እንግዳችን ነው፡፡
የተወለደው አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው።አባቱ አቶ ይታየው ምህረቴ እና እናቱ ወይዘሮ የሺ ፋሪስ ከወለዷቸው 5 ልጆች እሱ የመጨረሻው ነው።በ1985 ዓ.ም ታሀሳስ 12 ቀን ነው የተወለደው።ስለ ቤተሰቡ ሲያወራ “ለነጻነት ትልቅ ቦታ በሚሰጥ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግኩት” ይላል።ይህ ነጻነትም እሱባለው እና ገና በልጅነቱ በእናቱ እንጉርጉሮ ውስጥ የተዋወቃት ሙዚቃ በፍቅር እንዲከንፉ አደረጋቸው፡፡
እናቱ ወይዘሮ የሺ የቤት እመቤት ቢሆኑም፣ ሙዚቃ ማንጎራጎርን ይወዳሉ።እንዲያው በልጅነታቸው በሰፈራቸው ከነበሩት ሴቶች ሁሉ ድምጸ መረዋዋ እሳቸው ነበሩ።አባቱ አቶ ይታየው ደግሞ ቀዳሽ እና ተኳሽ ነበሩ።በዘመናቸው ካህን እና የመንግስት ወታደር ነበሩ።ስለዚህም በክህነታቸው የተነሳ ለዜማ ሩቅ አልነበሩም።በነዚህ ሁለት ዜመኞች መሀል የተወለደው ልጅም ልቡ ወደ ዜማ ቢሄድ አይደንቅም፡፡
እንደማንኛውም ልጅ እያንጎራጎረ ያደገው እሱባለውም እንዲሁ የሰው ዘፈን ማንጎራጎር ብቻ አያስደስተውም፤ ገና የ8ኛ ክፍል ተማሪ እያለ የራሱን የመጀመሪያ ሙዚቃ ጻፈ።ከዚያ በኋላ ግን የእሱባለው የሙዚቃ ጸሀፊነት እና ዜማ ደራሲነት አላቆመም።
ለዚህ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ገና በ14 አመቱ የተቀላቀለው የህጻናት እና ወጣቶች ቴአትር ቤት ነው።ህጻናት እና ወጣቶች ቴአትር ለእያንዳንዱ ዝግጅት እና ሁነት አዲስ ዜማ እና አዲስ ግጥም የሚዘጋጅበት እና የሚጠናበት ቤት ነው።ይህ ሁኔታ ደግሞ ግጥም እና ዜማ ለሚወደው እሱባለው አስደሳች አጋጣሚ ፈጠሩለት።እሱም ”ህጻናት እና ወጣቶች ቴአትር እያለሁ ከ400 በላይ ሙዚቃዎችን ጽፌያለሁ” ይላል፡፡
ከህጻናት እና ወጣቶች ቴአትር ሲወጣ ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገባና ሙዚቃን ተማረ።የሚወዳትን ሙዚቃ ከስሜት እና ከጥበብነት በበለጠ ሳይንስ ሆና አገኛትም፤ ተማራት ተመራመራት።በህጻናት እና ወጣቶች ቴአትር ከሚያውቀው በላይም ሙዚቃ የሚፈጠርባቸው የተለያዩ መንገዶች እንዳሉ እወቅ።ከዚያን በኋላ የሙዚቃ ፈጠራው አንድ ደረጃ ከፍ አለ፡፡
የመጀመሪያ ሙዚቃው ኢትዮጵያ የሚል ነበር።ብዙም ሳይዘገይ ወደ አልበም ተሻገረ።ከዝነኛው አቀናባሪ ታምሩ አማረ ጋር ለአልበም የሚሆኑ ሙዚቃዎች መስራት ያዙ።ነገር ግን 9 ሙዚቃ ከተሰራ በኋላ ሙዚቃዎቹን የያዘው የኮምፒውተር ሶፍትዌር ሙዚቃውን ይዞ ጠፋ።
ይሄኔ የእሱባለው ጎረምሳ ልብ አኮረፈ።”ስሜቴ በጣም ተጎድቶ ነበር” ይላል ወቅቱን ሲያስታውስ።ስለዚህም በሙዚቃው መጥፋት የተጎዳውን ስሜቱን ለመጠገን ብቸኛው መድሀኒት ሌላ ሙዚቃ መስራት ነበር።ያኔ ነው ሆያሆዬ የተሰኘው ነጠላ ዜማው የተሰራው።ሆያሆዬ በሙዚቃ ወዳጆች ዘንድ ተወዳጅነትን ቢያተርፍም፣ እሱባለው እና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲተዋወቁ ግን ተጨማሪ አንድ ስራ ያስፈልግ ነበር።ስለዚህም ሌላ ሙከራ ማድረግ አስፈለገ።ይሄኛው ሙከራ ስኬታማ ሆነ።ማሬ ማሬ የተሰኘው ሙዚቃ እሱባለውን ሽቅብ ተተኩሶ በህዝብ አይን ላይ እንዲያርፍ አደረገው፡፡
በሙዚቃዊ ተፈጥሮው ለአልበም ዝንባሌ ያለው እሱባለው ወደ አልበም ስራ ተሰማራ።ትርታዬ የተባለ አልበም አዘጋጅቶም ለህዝብ አቀረበ።አልበሙ ከፍተኛ ተወዳጅነት አገኘ።ስሙንም ከተወዳጅ ድምጻውያን ተርታ አገኘው።እሱባለው ይታየው የሚለው ስምም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተመዘገበ፡፡
ከአልበሙ በኋላ እሱባለው ወደሚወደው ስራ ተመለሰ።ሙዚቃ ማምረት፣ ግጥም መጻፍ ዜማ መቀመር መልሶ ማፍረስ እንደገና ማዜም እንደገና መቀመር … ይሄ ነው የእለታዊ ህይወቱ ኡደት።”በሳምንት ቢያንስ 5 ዜማ ካልሰራሁ ቅር ይለኛል” ይላል ብቸኛ ሱሱ ስለሆነችው ሙዚቃ ሲያወራ።የሚያወራው ስለ 5 ዜማ መዝፈን አይደለም።ይልቁንም አምስት ዜማ ግጥም መጻፍ ፤ አምስት ዜማ ማዘጋጀት ፤ አምስት ቅንብር ስለመስራት እንጂ።ይሄ በትንሹ ነው።ጥሩ መንፈስ ላይ ከሆነ ከዚያም በላይ እንደሚሰራ ይናገራል፡፡
ቤቱ ጎራ ባልንበት ወቅት እንዳስተዋልነው የዜማ መሳሪዎች ቦታ ቦታቸውን ይዘው እሱባለው እስኪነካካቸው ይጠብቃሉ።በባለቤታቸው አእምሮ ውስጥ የተጸነሰ የሙዚቃ ዘርን ለማዋለድ ታጥቀው ነው የሚጠብቁት።እስካሁን ራሱ የሰራቸውን ወደ 20 የሚጠጉ ሙዚቃዎች ጨምሮ ወደ አንድ መቶ ገደማ ሙዚቃዎችን ሰርቷል።ከነዚህም መሀከል ለብዙዎች ህይወት መትረፍ አስተዋጽኦ ያለው እኔ ነኝ ደራሽ ለወገኔ ፤ የዝናር ዜማ “የኔ ሴት” ፤ የዮሀንስ ግርማ “መገን እኔ” ፤ ጌታቸው ሀይለማርያም እና ፍቅረማርያም ገብሩ በጋራ ያቀነቀኑት “ሲንጃለዳ” ፤ የቃለአብ ሙሉጌታ “ጤና አዳሜ” ፤ የነጻነት ለማ “ቶሎ ና” እና መሰል ተወዳጅ ሙዚቃዎች ይገኙበታል።አብዛኞቹ ስራዎች በዩቲዩብ ከሚሊየን በላይ ተመልካች ያገኙ ናቸው፡፡
እሱባለው ወጣ ወጣ ማለት የሚወድ ሰው አይደለም።ብዙውን ሰአት በቤቱ ውስጥ ባሰራው ስቱዲዮ በሙዚቃ ሲመራመር ነው የሚውለው።እንዲያም ቢሆን የእረፍት ቀኑን አያባክንም።”መዝናናት ስፈልግ እወጣለሁ።ከጓደኞቼ ጋር ሻይ ቡና እንላለን ፤ ፊልም አያለሁ ፤ ወዘተ…፡፡ለመዝናናት ጊዜ አጥሮኝ አያውቅም” ይላል፡፡
ብዙ እድሜውን በሙዚቃ ውስጥ ከማሳለፉ ጋር በተያያዘ ስለሙዚቃ የገባው አንድ ሀቅ አለ፤ ልምምድ እና የጋራ ስራ አስፈላጊ መሆናቸው።በተለይ ጀማሪ ድምጻውያን ብዙ ልምምድ ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል።ከሙዚቃ ባለፈ ሌሎች ተሰጥኦዎቻቸውን ማዳበር እንዳለባቸውም ይናገራል፡፡
”ድምጽ ብቻ ተይዞ በሙዚቃው ውጤታማ ለመሆን ይከብዳል” ይላል እሱቤ።በአዲሱ አመት ሁለተኛ አልበሙን ለማውጣት ስራ ላይ እንዳለ የሚናገረው እሱባለው የአልበም ስራው ከ50 በመቶ በላይ እንደተጓዘም ይናገራል።ከዚያ በፊት ግን አንድ ሁለት ነጠላ ዜማዎችን ለአድናቂዎቹ ለማድረስ አቅዷል፡፡
ለአርቲስቱ በአዲሱ አመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልእክት እንዲያስተላልፍ እድል ሰጠነው።እንዲህም አለ።”በአዲሱ አመት ለሁላችንም ልቡና እንዲሰጠን እጸልያለሁ።ከዚያም ደግሞ ወደኋላ ሄደን የምንቋሰልበት ዘምን እንዲያበቃ እመኛለሁ።አብረን በሰራናቸው በጎ ስራዎች እና ስኬቶች ላይ ብናተኩር ይሻላል ባይ ነኝ” በማለት የአንድነት እና የእርቅ መልእክቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ አስተላልፏል፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2014