መቼም እንደ እዚህ ዘመን እያደር ጉድ የሚሰማራበት ጊዜ ገጥሞንም አያውቅ። ስንት የተልባ ክምር ሰው አየን። እያየናቸው የሚንሸራተቱ ሰዎች በዝተዋል።ጥሩው ነገር መንሸራተታቸው ከላያችን ላይ እንዲወርዱ ያደርጋል።
መንሸራተቱ ግን የግለሰቦች ብቻ አይደለም ፤የቡድኖችም የሀገራትም እንጂ። አሜሪካን የምታህል ሀገር መርህ አልባ እና አስመሳይ መሆኗን ያየነው እኮ ዘንድሮ ነው። በስማም አሜሪካ፤ በስማም መንሸራተት፤ በስማም መርህ አልባነት….። እየደጋገመች ልትታመን የማትችል ሀገር መሆኗን እኮ ነው ያሳየችን።ይገርማል..
አሜሪካኖቹ ሰሞኑን ደግሞ ሌላ አዲስ አስቂኝ እና አሳፋሪ ክስ ይዘው ብቅ ብለዋል። ክሱ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ ያነጣጠረ ነው። አማካሪው ህወሓት ከምድረ ገጽ መጥፋት አለበት ማለታቸውን በጣም አደገኛ ንግግር ነው የሚል አስቂኝ ክስ ነው እያቀረቡ ያሉት።እንግዲህ ፈጣሪ ያመላክታችሁ ይህን የዲያቆን ዳንኤል ንግግር የተቸችው እና በስም ጠቅሳ መግለጫ ያወጣችው አሜሪካ ከዚህ ቀደም የህወሓት መሪ ጌታቸው ረዳ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን ሲል በርታ ከማለት ባልተናነሰ ዝምታ አልፋዋለች እኮ።አይ አሜሪካ!
እስኪ በመጀመሪያ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ተናገረ የተባለውን እንይ፤- “እነዚህ ሰዎች እና እነዚህን የመሰሉ ሰዎች እንዳይደገሙ ማድረግ ነው።እነሱ የመጨረሻ ሆነው እንዲቀሩ ማድረግ ነው።ከዚህ በኋላ እነሱን የመሰለ ሰው እንዳይፈጠር መደረግ አለበት፤ በምንም መልኩ።እንደምታውቁት ሰይጣን ከወደቀ በኋላ ሰይጣንን የመሰለ ሌላ አልተፈጠረም። ሰይጣን የመጨረሻ ሆኖ ነው የቀረው።እነሱም የመጨረሻ ሆነው ነው መቅረት ያለባቸው።ይሄን ሊደግም የሚችል እንዲህ አይነት አረም ሊያፈራ የሚችል ምንም አይነት መሬት መፈጠር የለበትም። ስለዚህ ከአሁን በኋላ ለልጆቻችን የክፉ ነገር ምሳሌ ማስፈራሪያ ማድረግ ያለብን እነሱን ነው።…..ከዚህ በኋላ ስቃዩም ጦርነቱም መፈናቀሉም የማይደገም ሆኖ ማለፍ አለበት። ይሄን ያመጡትም ሰዎች የማይደገሙ ሆነው ነው ማለፍ ያለባቸው።”
እንግዲህ ልብ አድርጉ ይሄ ንግግር ምንም አሻሚነት የለውም። እየተወራ ያለው ስለ አንድ አካል ነው። ኢትዮጵያን አሁን ያለችበት ችግር ውስጥ ስለከተተው አካል ነው የተነገረው። ያ አካል ማነው? ህወሓት።ይህ አካል ከኢትዮጵያ መወገድ እንዳለበት የተናገረው እና የወሰነው ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ናቸው። ህወሓት የሽብር ቡድን ነው።የሽብር ቡድን ደግሞ መደምሰስ አለበት። ሲደመሰስም ደግሞ እንዳይነሳ ተደርጎ ነው።
ልብ አድርጉ የሽብር ቡድን መደምሰስ አለበት እሱን የሚመስል ሌላ ሀይል መፈጠር የለበትም ያለውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የተቹት አሜሪካኖች እነሱ አሸባሪ ስለሚሏቸው አካላት ዳንኤል ከተናገረው የማይለይ ነገር ነው ሲናገሩ የሚውሉት።
ይህንንም በምሳሌ እንይ እስኪ፤ የአሁኑ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በቅርቡ በአፍጋኒስታን በወታደሮቻቸው ላይ በአሸባሪዎች ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ሲናገሩ “አንረሳም፤ ይቅርም አንልም።ያሉብት ድረስ አድነን ዋጋቸውን እንሰጣቸዋለን።” ብለዋል።
የሳቸው ቀዳሚ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በ2017 እ.ኤ.አ የ9/11 ጥቃት መታሰቢያ ላይ ስለ አሸባሪዎች፤- “ከአሁን በኋላ በሀገራችን ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ አሸባሪዎች የሚደበቁበት ቦታ እንዳይኖር እናደርጋለን። ለነዚህ አረመኔዎች ካሁን በኋላ እኛ የማንደርስበት እነሱ የሚደበቁበት ጨለማ ስፍራ እንደሌለ እናሳያቸዋለን።” ሲሉ አስገንዝበዋል።
የትራምፕ ተቀዳሚ የነበሩት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በገዛ ሀገራቸው አሜሪካ መሬት ላይ ሳንበርናንዲኖ በተባለ ቦታ የሽብር ቦታ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በቁጣ መንፈስ ውስጥ ሆነው “በኛ ላይ የሽብር ሴራ የሚሸርቡትን አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ የትኛውም ሀገር ላይ ቢሆን ሄደን እንደመስሳቸዋለን” ብለው ነበር።እንዲህ እያልን የአሜሪካ መሪዎች ስለ አሸባሪዎች የተናገሩትን ንግግር መጥቀስ እንችላለን። ነገር ግን የአንዳቸውም ንግግር “ግጭትን የሚያባበስ” “አደገኛ” “አሳሳቢ” ወዘተ የሚል ታፔላ ተለጥፎለት አያውቅም።
ሁሉም የአሜሪካ መሪዎች ስለ አሸባሪዎች ሲናገሩ ፈሪ (coward)፤ አረመኔ (savage)፤ ኋላ ቀር (barbaric) ወዘተ ቢሉም በጥላቻ ንግግር ግን አይቆጠርባቸም።ዲያቆን ዳንኤል ግን ሀገራችንን ችግር ውስጥ የከተታትን ሀይል ዳግም እንዳይመጣ አድርገን መደምሰስ አለብን ሲል ጉዳዩ በአንድ ቅጽበት ለአሜሪካውያኑ አሳሳቢ ሆኖ ታያቸው።ለምን?
ጉዳዩ ግልጽ ነው።ህወሓትን ማንም እንዲናገረው አይፈለግም።ህወሓት ከሽብር ቡድን መዝገብ እንዲሰረዝ፤ እንደማንኛውም ሰላማዊ ፓርቲ ወደ ድርድር እንዲመለስ፤ ስልጣንም እንዲካፈል የሚፈልጉት እነ አሜሪካ ልጃቸው ህወሓት የሽብር ቡድን ተብሎ ሲጠራ ማዘናቸው የሚጠበቅ ነው።የሽብር ቡድን ከመባልም አልፎ ዳግም እንዳይነሳ ሆኖ መደምሰስ አለበት ሲባል ግን ብስጭታቸውን መቆጣጠር ስላልቻሉ መግለጫ እስከማውጣት ደረሱ።እነ ጌታቸው ረዳ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንገነባለን ሲሉ አሜሪካውያኑ ለምን አልተቆጡም? ምናልባትም የሚፈልጉት ነገር ስለሆነ ይሆናላ።
በዚህ በኩል ደግሞ ዲያቆን ዳንኤል ይደምሰሱ ያለው ተጋሩን ነው በማለት ነገሩን ሌላ ቅርጽ ለመስጠት የሚሞክሩ መሳቂያዎች አሉ።እነዚህኞቹ የትግራይ ህዝብ እና ህወሓት አንድ ናቸው ብለው ራሳቸውን ያሳመኑ ነፈዞች ናቸው።በዚህ ንግግር ውስጥም የተለመደ የፖለቲካ ቁማራቸውን ለመስራት ነው ሙከራቸው።
አላማቸው ዲያቆን ዳንኤልም ሆነ መላው ኢትዮጵያዊ ትግራይን ጠልቷልና እንገንጠል የሚል ያረጀ ያፈጀ መርዘኛ ፖለቲካቸውን መስራት ነው።ሀቁ ግን እንደዚያ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ የጠላው ህወሃትን እና የክፋት ስራውን ነው። ይህን ክፉ ሀይል ደግሞ መልሶ ሊያየው እንደማይፈልግ በተደጋጋሚ አስረግጧል።ትግራይን እና ተጋሩን በተመለከተ ግን የዲያቆን ዳንኤልም ሆነ ኢትዮጵያውያን አቋማቸው ግልጽ ነው።አብረን ኖረናል ፤ አብረንም እንኖራለን የሚል ነው!
ዲያቆን ዳንኤል ከዚህ ቀደም በተለያዩ መጽሀፎቹ ስለ ትግራይ እና ተጋሩ ብዙ መወድሶችን ጽፏል።ትግራይ ውስጥ ሄዶ የወንጌል አገልግሎት ፈጽሟል።በየሚዲያው ብዙ መልካም ነገሮችን ተናግሯል።በመንግስት ስራውም ህወሓትን በድርድር እና በሰላም ለመግራት ከጣሩት መሪዎች መሀከል አንዱ ነው።ግን አንዴ ለክፋት የተሰሩ ናቸውና ህወሓቶች ሰላምን አልወደዱም።ያደረጉትን አደረጉ፤ ኢትዮጵያውንም መልስ እየሰጡ ነው።
የዳንኤል ንግግር የኢትዮጵያውያን ምላሽ የት መድረስ እንዳለበት የሚያመላክት ነው። ትክክለኛ ንግግር ነው፤ ስህተትም የለውም።ኢትዮጵያውያን የሚሰጡት ምላሽ ህወሓት ዳግም እንዳይመለስ እስከማድረግ የሚዘልቅ መሆን ያለበት ነው።አልያም አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነው የሚሆነው። በአረም ላለመመለስ አረሙ የበቀለበትን ቦታ በደንብ ማስተካከል ያስፈልጋል። አሜሪካውያንም ቢሆኑ እነሱ አሸባሪ ስለሚሏቸው አካላት የሚሉት ይሄንን እንደሆነ ቀደም ብለን አይተናል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2014