ከቤታቸው ፊት ለፊት ሱቅ አለ ከሱቁ ጀርባ ደግሞ የጓደኛዋ የነትርሲት ቤት ነው፡፡ ሱቅ ብላ ወጥታ እነትርሲት ቤት ሳትሄድ የቀረችበት ጊዜ ትዝ አይላትም፡፡ ትርሲት የልጅነት ጓደኛዋ ባትሆንም ቤት ገዝተው ሰፈራቸው እስከገቡበት ጊዜ ድረስ ተለያይተው አያውቁም፡፡ ሚስጥረኛ ጓደኛሞች ናቸው..፡፡
የሚያምርባትን ቀዩን የቤት ውስጥ ፒጃማዋን እንደለበሰች ሳሎኑን አልፋ በረንዳውን ረገጠች፡፡
‹የት ልትሄጂ ነው? እናቷ ጠየቁ..አይናቸውን ወደ በረንዳ በመወርወር፡፡ በቤት ልብስ እነትርሲት ጋ ወይም ደግሞ ሱቅ ሸምሱጋ ካልሆነ የትም እንደማትሄድ ያውቃሉ፡፡
‹እነትርሲት ጋ…› መለሰችላቸው፡፡
ዝም አሉ እናቷ..፡፡ በእናቷ ዝምታ ውስጥ አንድ መአት ይሁንታ አለ፡፡ እናቷ ከቤት እንድትወጣ ስለማይፈቅዱላት እነትርሲት ቤት ነው ካለች ብቻ ነው የሚፈቀድላት፡፡ ሌላ ቦታ የምትሄድ ቢሆን እንኳን የነትርሲትን ቤት ሰበብ አድርጋ ነው የምትወጣው፡፡ ትርሲት ብዙ ነገሯ ናት፡፡ አንድ ጊዜ እንዳውም ፈተና የጨረሱ ሰሞን ከጓደኞቿ ጋር መዝናናት ፈልጋ እነ ትርሲት ቤት ነኝ ብላ ወጥታ ከእናቷ ጋር ከተማ የተገናኙበትን አጋጣሚ አትረሳውም፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ እናቷም አላምን ብለዋት ከስንት ጊዜ በኋላ ነው እምነቷን የመለሰችው፡፡
‹ሌላ ቦታ ትሄጂና..እዚች ቤት አትመለሻትም› የእናቷ ዛቻ ተሰማት፡፡
‹እማ ደሞ..የአንድ ጊዜ ጥፋቴን ለምን የሁልጊዜ ታደርጊዋለሽ፡፡ ያኔም የሄድኩት ለጓደኞቼ ብዬ ነው፡፡
‹በይ..ቶሎ ተመለሺ..እንዳታመሺ፡፡
‹እሺ አላመሽም..፡፡
ወጣች..የሸምሱን ሱቅ አለፈች፡፡ ከአፏ የማይጠፋውን ማስቲካ እያላመጠች ከነትርሲት ደጃፋ ደረሰች፡፡ የእነትርሲት ቤት የገነት ያክል ያምራታል፡፡ ህዋሶቿ አፍ የሚዘሩት እዛ ነው… እነ ትርሲት ቤት፡፡
ውሻቸው ጭራውን እየቆላ ተቀበላት፡፡ እግሯ ላይ እየተንደባለለ እጅ ከነሳት በኋላ ሳሎን አድርሷት ተመለሰ፡፡ ቤት ስትገባ ትርሲት አልነበረችም፡፡ ጠረጴዛው ላይ የተመሰቃቀለውን
ወረቀት ስታይ ነበር ከሰዓት እንደማትኖር የነገረቻት ትዝ ያላት፡፡ ሚኪያስ ካለ ብላ ወደ ደጅ ስትወጣ የክፍሉ በር ተከፍቶ አየች፡፡
‹ሚኪ..አንተ ሚኪ? ከመንገድ እየተጣራች ወደ ሚኪያስ ክፍል አመራች፡፡
‹አቤት! የምታውቀው አንድ ድምጽ ምላሽ ሰጣት፡፡
ቆመች፡፡ ልግባ አልግባ? አመነታች፡፡
‹ሄሉ…! ጠራት..ወፍራም ጎርናና ድምጽ፡፡
አምድም ቀን በሙሉ ስሟ ጠርቷት አያውቅም፡፡ ስሟ በእሱ አፍ ሲጠራ እንደመስማት የሚያስደስታት የለም፡፡ ድምጹ ውስጥ ትለመልማለች..ድምጹ ውስጥ ታቆጠቁጣለች፡፡ የሆነ ሀይል ወደ ፊት ገፋት..ሳታውቀው ራሷን እየተራመደች አገኘችው፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ ወደ ክፍሉ እየገባች ነው፡፡ ትርሲት ሚኪያስ ናርዶስ የምትባል የሚወዳት ፍቅረኛ እንዳለችው ከነገረቻት ጀምሮ ክፍሉ ገብታ አታውቅም፡፡ ወዳው ነበር..እሱን የግሏ ለማድረግ ብዙ ተጉዛ ነበር እህቱ እውነቱን ስትነግራት ሁሉንም ተወችው፡፡
ሚኪያስ ልብሱን እየቀየረ ቁም ሳጥኑ አጠገብ ቆሟል፡፡ ወደ ክፍሉ ስትገባ ከፈርጣማ ደረቱ ጋር ተገናኘች፡፡ ራቁቱን አይታው አታውቅም ነበር፡፡ የሆነ ሀይል ተናነቃት..የተወችው የረሳችው እውነት ተዋሀዳት..ምን ትሁን?
‹ነይ ግቢ ! አላት ደረቱን ወደ ደረቷ ሰድሮ በር ላይ መቆሟ አሳስቦት፡፡
አፈር..ደፈር እያለች ወደ ውስጥ ገባች፡፡
ልብሱን ለብሶ ስላልጨረሰ ለቀን ውሎው የሚሆነውን ልብስ ከቁም ሳጥኑ ውስጥ እየመራረጠ ነበር፡፡
አይኗ አጠገቧ ካለ አንድ ፎቶ ላይ አረፈ፡፡ ቀይ ቆንጆ ሴት ሴት ናት..ናርዶስ ትሆናለች ስትል አሰበች፡፡ ቅናት ቢጤ ተሰማት..
‹ተጫወቺ..! አላት ቁም ሳጥኑ ውስጥ እየተንደፋደፈ፡፡
‹ምን እያደረክ ነው? ጠየቀችው፡፡
‹ዛሬ የሆነ አንድ ፕሮግራም አለኝ..ለእሱ የሚሆን ልብስ እየመረጥኩ ነው፡፡
‹ታዲያ አገኘህ?
‹ምን አገኛለሁ..ምን ለብሼ እንደምሄድ ግራ ነው የገባኝ፡፡ በተሰላቸ ድምጽ መለሰላት፡፡
‹ከዚህ ሁሉ ልብስ እንዴት አንድ ታጣለህ? ወደ ቁም ሳጥኑ እየማተረች፡፡
‹ችግሩ ልብሱ አይደለም..
‹እና ታዲያ ምንድነው?
ሳይመልስላት ዝም አላት፡፡
ከናርዶስ ጋር እንደሆነ ቀጠሮው አውቃለች፡፡ ናርዶስ በጣም የሚወዳት ፍቅረኛው እንደሆነች ታውቃለች፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ትወደዋለች..ግን ከሚወዳት ሴት ጋር ደስ እንዲለው ትታዋለች፡፡ ‹የቀጠርካት ሴት ምን አይነት አለባበስ እንደሚመቻት አታውቅም?
‹የቀጠርኳት ሴት እንደሆነች በምን አወቅሽ? እፍርታም ሳቅ እየሳቀ፡፡
‹ወንዶች ሴት ስትቀጥሩ ነው እንዲህ የምትጨነቁት ብዬ ነዋ፡፡
እየሳቀ..እየተደነቀ…‹አልተሳሳትሽም አላት፡፡
‹ምን አይነት አለባበስ እንደሚመቻት አታውቅም?
‹አውቃለሁ! ግን አንድም ቀን በአለባበሴ አስደስቻት አላውቅም፡፡ ምን ብለብስ ደስ የሚላት ይመስልሻል? መፍትሄ ሽቶ ጠየቃት፡፡
‹እንደዛ ከሆነ ዛሬ እድሉን ለኔ ስጠኝ..›ብላ ወደ ቁም ሳጥኑ በመሄድ ከተሰቀሉት ሸሚዞችና ሱፎች ውስጥ ጥሩ የምትላቸውን መርጣ በማውጣት ‹እስኪ እነኚህን ሞክራቸው ስትል አቀበለችው፡፡
እሱ ሲለባብስ እሷ ከሸሚዝና ከኮቱ ጋር የሚሄድ አሪፍ ከረቫት እየመራረጠች ነበር፡፡ ልብሱን ለብሶ ስታየው ዓለም ላይ ተወዳጁን ወንድ ሆኖ ነበር፡፡ የረሳው የቀረ ነገር ነበር..የደረቱን ግድም የሸሚዙን አዝራር ለመቆለፍ እድሉን አገኘች፡፡ እጆቿ ደረቱ ላይ ሲርመሰመሱ ሌላ ዓለም ውስጥ ነበረች፡፡ የምትወደውን ሰው ለሌላ እየዳረች እንዲህ መሆኗ አስገረማት፡፡
‹በጣም ነው ያማረብህ! እርግጠኛ ነኝ ደስ ይላታል..ጥሩ ጊዜ እንደምታሳልፉም አልጠራጠርም፡፡ ከልቧ ነበር፡፡
‹እንዲህ አልብሰሽኝ ካልወደደችውስ?
‹እንዲህ ለብሰህ ካልወደደችው ቆንጆ ስትለብስ የማትወድ ቅናተኛ ሴት መሆን አለባት› አለችው በቀልድ፡፡ ደረቱ ላይ ተነጥፋ ከረቫቱን እያስተካከለችለት፡፡ ስታለብሰው እጆቿ ፈርጣማ ደረቱን መንካታቸው ግድ ነበርና..ስታለብሰው በጣቶቿ መነካቱ ግድ ነበርና..ስታለብሰው በመዳፏ መዳበሱ ግድ ነበርና ነፍሷን በፍቅር እሳት ለኮሰች፡፡
‹ደሞ በደንብ ተንከባከባት..ፍቅር ጥሩ ለብሶ መሄድ ብቻ አይደለም፡፡ እንደምትወዳት ንገራት..ስትገናኙ ፍቅረኛህ በመሆኗ
ደስተኛው ወንድ እንደሆንክ ሳትነግራት እንዳትመለስ› አለችው በማስጠንቀቅ አይነት፡፡
ሚኪና ናርዶስ ተገናኙ፡፡
ናርዶስ ገና እንዳየችው በተከፋ ፊት ነበር የተቀበለችው፡፡
‹ምነው! የተፈጠረ ችግር አለ?
‹እንዲህ አይነት አለባበስ እንደማልወድ ስንት ጊዜ ልንገርህ? አንድም ቀን በአለባበስህ አስደስተህኝ አታውቅም፡፡ አለች በተቆጣ ድምጽ፡፡
ምን ይበላት? እሷን ማስደሰት ፈጽሞ የማይችለው ነገር ሆነበት፡፡ እሷ ፊት ጥሩ ሆኖ ለመቆም የማይከፍለው መስዋዕት የለም ግን ሁሌም እንደተነቀፈ ነው፡፡
‹አለባበሴን አልወደድሽውም? ጠየቃት
ዝም አለችው..እሱን ትታ ሌላ ቦታ እያየች፡፡
‹እንዲህ ሆኜ ለመምጣት ብዙ ነው የለፋሁት፡፡ ቀን ሙሉ ምን መልበስ እንዳለብኝ ሳስብ ነው የዋልኩት፡፡ እውነቱን ነገራት፡፡
‹ኧረ ባክህ! ጥሩ ቀልደኛ ነህ!
‹እየቀለድኩ አይደለም..ዛሬ ደስ ይልሻል ብዬ ነበር፡፡ እንዲህ ያለበሰችኝ የእህቴ ጓደኛ ናት፡፡
የእህቴ ጓደኛ የሚለውን ስትሰማ ‹ለካ እስከዛሬ በሌሎች ምርጫ ነበር ወደ እኔ የምትመጣው..ሲጀመር ይሄ ሸሚዝ እንዳለህ አላውቅም ነበር፡፡ ተናደደች፡፡
‹ምን እያልሽ ነው?
‹ጉድህን እየነገርኩህ ነው..እንዳውም አንተን ማየት አልፈልግም ስትል ተናግራ ቦርሳዋን አንስታ ትታው ሄደች፡፡
በነጋታው…
‹እንዴት ነበር! አለባበስክን ወደደችው?
‹እንዳልሽው ሆኗል!
‹እንዴት..?
‹ባሏ ጥሩ ሲለብስ የማትወድ..
‹አልገባኝም! ምን እያልክ ነው? ሄለን በግራ መጋባት ጠየቀችው
እሷ ባለበሰችው ከናርዶስ ጋር እንደተጣሉ ነገራት፡፡
ሄለን አቀረቀረች፡፡
‘ግን ደስ ብሎኛል…
ሄለን ቀና አለች፡፡’
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2014