የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን እየነቀሰ በየሳምንቱ ለንባብ የሚበቃው ፍረዱኝ የተሰኘው አምድ በ2013 በጀት አመት በርካታ ጉዳዮችን አስተናግዶ መልካም ውጤቶችን አግኝቷል፡፡ በፍረዱኝ አምድ ሃሳባቸውን አጋርተውና የአዲስ ዘመን ጋዜጠኞችም ተከሰቱ የተባሉትን የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ነቅሰው ውጤት ካገኙባቸው ስራዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡
የአርሶ አደር የይዞታ መሬት በጉልበተኞች መነጠቅ
ሶስት የአርሶ አደር ልጆች ወይዘሮ አልማዝ በዩ፣ ወይዘሮ ቡሩሴ በዩ እና አቶ በቀለ በዩ የተባሉ የአንድ ቤተሰብ ልጆች በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ሸማቾች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖራሉ። መሬታችን በጉልበተኞች እንዲወሰድ መንግሥት ኃላፊነት የሰጣቸው አካላት ህጋዊ ካልሆኑ ሰዎች ጋር በመመሳጠር በሰሩብን ሸፍጥ ካሳና ምትክ ያላገኘንበትን መሬት በህገወጦች እንድንነጠቅ ተደርጓል፡፡ በዚህም ከእናታችን በውርስ ያገኘነው መሬት ሙሉ በሙሉ በህገወጦች ተወሳዶብናል ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በታህሳስ ወር አቤት ብለዋል ፡፡
የዝግጅት ክፍሉም ከታህሳስ 15 ቀን ጀምሮ እስከ ሐምሌ 14 ድረስ እጅግ አድካሚ እና ውስብስብ ምርመራዎችን በማድወረግ ለሶስት ጊዜ ያህል በፍረዱኝ አምዱ እትሞችን በማውጣት እውነታውን ለሚመለከከታቸው አካለት አጉልተን ለማሳየት ጥረት አድርገናል፡፡
አርሶ አደሮቹ ለዝግጅት ክፍሉ የደረሰባቸውን በደል አቤት በሚሉበት ወቅት መሬታቸውን ከወረሩት አካላት ጋር በፍርድ ቤት እየተከራከሩ ነበር ፡፡ ስለሆነም አርሶ አደሮቹ አቤቱታ ያቀረቡት በወራሪዎች ሳይሆን ለወራሪዎቸ ሽፋን በሰጡ የአርሶ አደር ኮሚቴዎች ፣ የቀጠና ፣ የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች ላይ ነበር፡፡ የወረሩት ሰዎች ጉዳይ በፍርድ ቤት የሚታይ ስለሆነ ዝግጅት ክፍላችን በዚያ ላይ ምንም አይነት ምርመራ አላካሄደም። ነገር ግን ከህገወጦች ጋር ተባበሪ ነበሩ በተባሉት የአርሶ አደር ኮሚቴዎች ፣ የቀጠና ፣ የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች የሰሩትን ያልተገባ ሥራ በማስረጃዎች እና በሰነዶች በማስደገፍ አፍረጥርጦ ለማውጣት ተችሏል፡፡
እነኝህን ምርምራዎች በምናደርግበት ወቅት በህገወጥ ስራው የተሳተፉ የአርሶ አደር ኮሚቴዎች፣ የቀጠና ፣ የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች መርማሪ ጋዜጠኛውን ከእንገልሃለን ፣ ከስራህ እናሰናክልሃለን ከሚል ማስፈራርት ባለፈ ለመደብደብ ሞክረዋል፡፡ አንድ የወረዳ አመራር የነበረ አሁን ላይ ደግሞ በወረዳ ከአመራርነት ተነስቶ ሌላ ስራ የሚሰራ ሰው አመራር በነበረበት ወቅት በሶስቱ የአርሶአደር ልጆች ላይ ተፋጥሮ ስለነበረው ችግር እንዲያስረዳ ጥያቄዎችንን ባቀረብንበት ጊዜ አሻፈረኝ ብሏል፡፡ አልፎ ተርፎ የአርሶአደሮችን መሬት በመዝረፍ አከማችቶ በቀጠራቸው የግል ጠባቂዎች የድብደባ ሙከራ አድርጓል፡፡ ጋዜጠኛው ወደ መኪናው ሮጦ ባያመልጥ እና ሲጠብቀው የነበረ ሹፌር አስነስቶ ባያመልጥ ማርማሪው ጋዜጠኛ ከህገወጦች ዱላ ባልተረፈ ነበር፡፡
ነገር ግን እውነታውን ለህዝብ ለማሳወቅ እና የተበዳዮችን እንባ ለማበስ ከመሻት የተነሳ በፊት የተፈጠረበትን የድብደባ ሙከራ አልፎ በምርምራ ወቅት ሊፈጠር እንዲሚችል በማሰብ ወደ ቦታው በሌላ ቀን ተመልሶ የሚፈልገውን አግኝቷል፡፡
ከአመራሮች ማስፈራራት እና ዛቻ በተጨማሪ በመሬት ወረራው ተሳተፉ የተባሉ የአርሶ አደር ኮሚቴዎች ፣ የቀጠና ፣ የአወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች ቁጥራቸው እጅግ ብዙ በመሆኑ፤ ምርመራ በሚደረግበት ወቅት አብዛኛዎቹ አመራሮች ስራቸውን ለቀው ስለነበር የምርመራ ስራውን እጅግ ውስብስብ እና ፈታኝ አድርጎት ነበር ፡፡
ሆኖም ምርመራው ተጠናቆ አቤት ባዮቹ የሚካሰሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአርሶ አደር ኮሚቴዎች ፣ የቀጠና ፣ የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች ሲሰሩ ከነበሩ ያልተገቡ ተግባሮች መካከል በአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ተፈልፍለው እና ነጥረው የወጡ መረጃዎችን እና ሰነዶቹን አቤቱታ አቅራቢዎች በመያዝ እንደ ግብኣት ተጠቅመው የጠራ መረጃ በማቅረብ በህገወጦች የተወሰደው መሬት የተወሰነውን ክፍል ማስመለስ ችለዋል። አቤቱታ አቅራቢዎቹ ዝግጅት ክፍላችን ድረስ በመምጣት ከፍ ያለ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
የፈጠራ ባለሙያው እና የልማት ባንክ ውዝግብ
የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ሰሎሞን ሰብስቤ በህክምና ሳይንስ ተመርቀው በሙያቸው ለበርካታ አመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ችሎታ በመጠቀም ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ለመስራት የቻሉ ሰውም ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በአህጉር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የፈጠራ ባለቤትነት ሽልማቶችን አግኝተዋል ፡፡ የተወሰኑ ስራዎቻቸው በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈጠራ ባለቤትነት ተመዝግበዋል፡፡ተሰጥኦዋቸውን በመጠቀም ለአገር ብሎም ለተለያዩ ወገኖች የስራ እድል ለመፍጠር በማሰብ፤ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ለማግኘት በ2008 ዓ.ም ፕሮፖዛል አስገቡ ፡፡
አቶ ሰለሞን ብድር ሲጠይቁ ያስገቡት ፕሮፖዛል ለአጠቃላይ ስራ ማስኬጃ 15 ሚሊዮን 571ሺህ 680 እንደሚያስፈልግ ያመለክታል፡፡ ከዚህም መካከል 12 ሚሊዮን 551ሺህ 400 (80 ነጥብ 6በመቶ) ብር ለfixed investment ፣ 550,000 (3 ነጥብ 5 በመቶ ) ብር ደግሞ ለpre-production expense ቀሪው 2 ሚሊዮን 470 ሺህ 280 ብር (15 ነጥብ 9 በመቶ) ደግሞ working capital የሚል ነበር ፡፡
አጠቃላይ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 6 ነጥብ 78 ሚሊዮን የሚሆነው ብር በስራ ፈጣሪው የሚሸፈን ሲሆን፤ 12 ነጥብ 55 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደሚሸፈን ፕሮፖዛሉ ያመላክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ምንምን ማሽን እንደሚያስፈልግ በግልፅ አስቀምጠዋል። ማሽኑ ምን ምን እንደሚያመርት እና ምርት ለማምረት የሚያስችለው በ194ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ እንደሚያስፈልግ በፕሮፖዛሉ ተመላክቷል፡፡ ይህም ቦታ በአዲስ አበባ በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ 02 እንደሚገኝ ፕሮፖዛሉ ግልጽ በሆነ መልኩ ያመላክታል ፡፡
ጥራት ያላቸውን በቴክኖሎጂ ያደጉ ዘመናዊ ህክምና ፈርኒቸሮችን እና ቁሳቁሶች በማምረት የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት፣ የማኑፋክቸሪንጉን ዘርፍ ማዘመንና ለተለያዩ አካላት የስራ እድል መፍጠር እንዲሁም መንግስት ከድርጅቱ ከሚያገኘው ግብር በተጨማሪ በድርጅቱ ተቀጣሪዎች ከሚያገኙት ገቢ ለመንግሥት የሥራ ግብር እንዲያስገኝ ማስቻል እና ሌሎችም የድርጅቱ መነሻ ዋና ዓላማ እና ግቦች በፕሮፖዛሉ ተብራርተዋል፡፡
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአቶ ሰሎሞን ወይም ለሶለሰብ የቤት እና የእቃዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ብድር ይፈቅድላቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር አፅዳቂ ቡድን አጠቃላይ ዋጋ ውስጥ ብር 12,586 231/ አስራ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰማኒያ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ አንድ ብር በፀደቀው የብድር ስምምነት መሰረት የካፒታል እቃው Ethio-Arab International General trading L.L.C ከተባለ የተባበሩት አረብ ኤምሬት (UAE)አቅራቢ ድርጅት እንዲገዛ በተወሰነው መሰረት ግዥ ተፈፅሟል ፡፡
እነዚህ ማሽኖች በሊዝ ብድር ወይም በኪራይ የሚተላለፉ ናቸው፡፡ ማለትም ባንኩ አበዳሪ ወይም አከራይ ሶለሰብ የቤት እና የእቃዎች ማማረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ደግሞ ተበዳሪ ወይም ተከራይ ናቸው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በአከራይ እና በተከራይ መካከል ህዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም የተፈፀመውን የካፒታል እቃ ዱቤ ግዢ እና ኪራይ ውል መነሻ በማድረግ ከEthio-Arab International General trading L.L.C ከተባለ የተባበሩት አረብ ኤምሬት አቅራቢ ድርጅት የተፈቀዱ የማሽን ግዥ ተፈፅመ። የፕሮጀክቱ ሳይት የደረሱ ሰማኒያ ዘጠኝ ማሽኖች መጋቢት 4 ቀን 2010 ዓ.ም ንብረቱ በሚገኝበት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፤ የካ ክፍለ ከተማ ፣ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር 19 በሆነው ቦታ ላይ ጊዜያዊ ርክክብ ተፈፀመ፡፡
ቀድሞ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና በአቶ ሰሎሞን መካከል በተገባው ውል መሰረት ተከራዩ ወይም ተበዳሪው የሚጠበቅበትን በማከናወኑ ማሽኖች በሊዝ ብድር ወይም በኪራይ ውል ሊተላለፍ ችለዋል፡፡ ከተበዳሪው ቀድመው ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል ለስራ ማስኬጃ የሚውል የራሳቸውን መዋጮ ብር 3 ሚሊዮን 146 ሺህ 588 / ሶስት ሚሊዮን አንድ መቶ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ሰማኒያ ስምንት ብር / በጥሬ ገንዘቡ በባንክ በማይንቀሳቀስ ሂሳብ / Blocked Account/ ውስጥ ማስቀመጥ ነበር፡፡
ገንዘቡ መቀመጡ ሲረጋገጥ ደግሞ የእቃው መግዣ ገንዘብ ለአምራቹ ወይም ለአቅራቢው በውሉ መሰረት ባንኩ ይከፈላል፡፡ የተገዛው ዕቃ እና የማምረቻ መሳሪያውን መረከቡን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ለባንኩ ማቅረቡ ሲረጋገጥ ለስራ ማስኬጃ እንዲውል በዝግ አካውንት የተቀመጠው ገንዘብ ብር 2 ሚሊዮን 667 ሺህ 112 / ሁለት ሚሊዮን አንድ መቶ አስራ ሁለት ብር / ለስራ ማስኬጃ ለተከራይ ይለቀቃል፡፡ በተጨማሪ ባንኩ ከማሽኖች ባሻገር በካፒታል ዕቃ ዱቤ እና ኪራይ ውል መሰረት ቶዮታ ፒካ አፕ Ethio-Arab International General trading L.L.C መግዛት ይጠበቅበታል፡፡
ነገር ግን አቶ ሰለሞን እንዳሉት፤ ከተከራዩ የሚጠበቀውን ነገር ቢያሟሉም የኪራይ እቃውን እና የማምረቻ መሳሪያውን ባንኩ መረከቡን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት አልሰጣቸውም፡፡ ለስራ ማስኬጃ ይለቀቅልሃል የተባሉት ገንዘብ ሳይለቀቅላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ የሚጠይቅ ደብዳቤ በሚያዚያ 05ቀን 2010 ዓ.ም ከምስራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ደርሷቸዋል፡፡
ለዝግጅት ክፍሉ ከቀረቡ የምስጋና ደብዳቤዎች አንዱ ‹‹የመስሪያ ካፒታል እንዲለቀቅልኝ ብጠይቅም የጠየኩትን ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ለሁለተኛ ጊዜ ከባንኩ የዲስትሪክት ኃላፊ በሚያዚያ 26 ቀን 2010 ዓ.ም የማሽነሪ ተከላ ስራ አጠናቀው ማምረት እንዲጀምሩ የሚያሳሰብ ደብዳቤ በድጋሚ ተፃፈልኝ›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተንዛዛ እና ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ የስራ ማስኬጃ ገንዘባቸውን ስለያዘባቸው የተገዛው ማሽን ከስራ ውጭ በመሆኑ አቧራ ውጦት ለብልሽት ሊዳረግ መሆኑን እንዲሁም እርሳቸው በብስጭት እስከ መታመም መድረሳቸውን ጠቅሰው፤ ፍትህ ይሰጠኝ ሲሉ አቤቱታቸውን ለዝግጅት ክፍሉ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ተበዳይ ነኝ ያሉትን አቶ ሰለሞን አቤቱታ ከመቀበል በተጨማሪ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን በማነጋገር በፍረዱኝ አምዱ አስተናግዶ አቶ ሰለሞን አቤቱታቸው ሊፈታላቸው ችሏል፡፡ አቶ ሰለሞን እንደገለፁት የሥራ ማስኬጃው ገንዘብ ተለቅቆላቸው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
‹‹አንዲት ዛፍ መቁረጥ ያቃተው የወረዳ አስተዳደር እና የነዋሪዎች የዘመናት እሮሮ››
በታኅሣሥ 7 ቀን 2013 ዓ.ም እትማችን እና ረቡዕ ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም ‹‹አንዲት ዛፍ መቁረጥ ያቃተው የወረዳ አስተዳደር እና የነዋሪዎች የዘመናት እሮሮ›› በተሰኘ ርዕስ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ስሙ ርግብ ሆቴል አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የአንድ መንደር ነዋሪዎች የደረሰባቸውን ችግር የሚመለከት ዝግጅት ይዘን መቅረባችን የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች በወቅቱ ያጋጠማቸውን ችግር አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍሉ ባደረጉት ጥቆማ መሠረት ቦታው ድረስ በመገኘት የነዋሪዎች እሮሮ አስመልክቶ ያዘጋጀነውን ዘገባና የአራዳ ክፍለከተማ ወረዳ 4 ጽሕፈት ቤት ምላሽ የሚያስቃኝ ጥንቅር ለአንባቢያን አቅርበናል፡፡
በመጀመሪያ ዘገባ ወቅት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ጽሕፈት ቤት ችግሩን እንድያዉቁት መግለጻችን ይታወስ ነበር፡፤ በሁለተኛው ዘገባ ወቅት ደግሞ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ጽሕፈት ቤት እና በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መካካል መሆኑን ለማሳየት ችለናል፡፡ የእነዚህ ነዋሪዎች ችግር ሁለት አይነት እንደነበር ቀደም ሲል አስነብበናል፡፡ አንደኛው ችግር ከጎረቤት የሚመጣው የፈሳሽ ችግር በወረዳው አስተዳዳር አማካይነት እንዲስተካከል የተደረገ ሲሆን፤ ሁለተኛው የመጸዳጃ ቤት ችግር ግን በሁለቱ ጽህፍት ቤቶች መካካል ባለው ምልልስ ምክንያት ሳይፈታ ቆይቶ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን በመጸዳጃ ቤት በፍሳሽ ምክንያት የተቸገሩት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ስሙ ርግብ ሆቴል አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የአንድ መንደር ነዋሪዎች እሮሮ ተፈቷል። የፍሳሽ ማስወገጃ መኪና ወደ ውስጥ ለመግባት አስቸግሮ የነበረው ዛፍ እንዲቆረጥ በማድረግ አሁን ላይ ጊዜያዊ መፍትሔ አግኝቶ መጸዳጅ ቤቱ ፍሳሽ በመወገዱ የነዋሪዎች እሮሮ መፍትሔ በማግኘቱ የእፍይታ አየር እየተነፈሱ ነው፡፡
‹‹በቆሻሻ የተፈተነ የሕፃናቱ የትምህርት ጉዞ››
በሚል ርዕስ በመዲናችን በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13፤ በአዲሱ ክፍለ ከተማ ለሚ ኩራ ወረዳ 2 ውስጥ የሚገኘውን የቡርቃ ቦሪ የመጀመሪያ ትምህርት ቤትና አሶሳ አጸደ ሕፃናት ዘንድ በመገኘት ያዘጋጀነውን ዘገባ ‹‹በቆሻሻ የተፈተነ የሕፃናቱ የትምህርት ጉዞ›› በሚል ረቡዕ መጋቢት 8 ቀን 2013 ዓ.ም እትማችን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡በወቅቱ ቦታው ላይ በመገኘት የተመለከተነው ችግር እንደሚከተለው አቅርበን ነበር ፡፡ለዓይን አስቀያሚ፤ ለአፍንጫ ሰንፋጭ የሆነ የቆሻሻ ክምር አካባቢውን በክሎታል፡፡ ችግሩ በጣም አሳሳቢ የሚሆነው ደግሞ ቆሻሻው በአጸደ ሕፃናቱ በር አካባቢ መገኘቱ ነው፡፡ በገንዳው አካባቢ በጣም ብዙ የቆሻሻ ክምር ይታያል። ቆሻሻው ላይ ደግሞ በርከት ያሉ ውሾች ወዲያና ወዲያ ይላሉ፡፡በትምህርት ቤቱ ደጃፍ የሚደፋው ቆሻሻ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ብቻ የሚሰበሰብ ሳይሆን ከሌላ አካባቢ እየመጣ የሚከማች እንደሆን ነጋሪ ሳያስፈልግ መረዳት የሚያስችል ነው፡፡ በአጸደ ሕፃናት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኙ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጋር ቆይታ አድርገን ስንወጣ በዚያው ቅጽበት የደረሱት የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚና ምክትል ሥራ አስፈጻሚው እንዲሁም የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ቆሻሻው በመሰብሰብ ላይ የተሰማሩትን ወጣቶች ሰብስበው በማወያየት ላይ እንዳሉ አግኝተናቸዋል፡፡
የሕዝብ ጥያቄ ነውና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታው ላይ ሆነን ያንን ሁሉ ሽታ ተቋቁመን ከወረዳው አመራሮች ጋር ቆይታ አድርገን ነበር። በቆይታችን በአካባቢው ያለው አፍንጫ ሊበጥስ የሚደርስ የቆሻሻ ሽታ የሚፈጥረው የጤና ዕክል ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል ታዝበናል፡፡ ለጊዜያዊ ቆይታ ለከፍተኛ ጉንፋን እና ለሳምንታት የማያቋርጥ የራስ ምታት ህመም ከዳረገ፤ ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ምን ያህል ከባድ እና አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም፡፡ በወቅቱ የትምህርት ቤት ማህበረሰብ፣ የተማሪዎችን ፣ የወላጆች ቅሬታና የሚመለከታቸውን ሥራ አመራር ምላሽ አቅርበን ነበር፡፡ ረቡዕ ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም እትማችን የትምህርት ቤቱ ችግር የተወገደበት ሁኔታ የሚያሳይ ዘገባንም አቅርበናል። በመጀመሪያ እትማችን ያቀረብነውን ዘገባ ችግሩን አጉልቶ የሚያሳይ ነበር፡፡ አሁን ላይ የትምህርት ቤቱ ችግር ተወግዶ ለተማሪዎች ንጽህ የመማሪያ ቦታ መኖሩን በቦታው ድረስ በመሄድ አይተናል። ይህ ለመማር ማስተማሩ ጋሬጣ የነበረው ችግር ተፈትቶ የትምህርት ቤት ማህበረሰብ የመማር ማስተማር ሂድት ቀጥሎ በማየታቸን እንደዝግጅት ክፍል የተሰማን ደስታ ከፍ ያለ መሆኑን እንገልጻለን። ትምህርት ቤቱም ለዝግጅት ክፍሉ የም ስጋና ደብዳቤ ልኳል፡፡
ያለመናበብ መዘዝ
ቄስ ዳዊት መለስ ይባላሉ፡፡ በአማራ ክልል በአዊ ቤሔረሰብ አስተዳደር በሳንጆ ወረዳ የበታ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ እርሳቸውም በአካባቢው እንደሚገኝ ማንኛውም ሰው ሁሉ መሬታቸው በአሲዳማ አፈር ስለተጎዳባቸው ኑሯቸውን በከሰል ምርት ላይ አድርገዋል፡፡ ቄስ ዳዊት በህጋዊ ወኪላቸው አቶ ጌታሁን አስፋው አማካኝነት ያመረቱትን ከሰል ወደ መሐል አገር ማለትም ወደ አዲስ አበባ እና አዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች በጅምላ ለሚረከቡ ነጋዴዎች ይሸጣሉ፡፡
ነገር ግን የቄስ ዳዊት መለስ ህጋዊ ወኪል ከሰል ለመሸጥ ሲንሳቀስ በሰበታ ፖሊስ ከሰሉ ተያዘ፡፡ በዚህ ሳቢያ የቄስ ዳዊት ወኪል አቶ ጌታሁን የአስተዳደር በደል ተፈፀመብኝ በማለት ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ህዝብ ይፍረደኝ ሲሉ አቤት ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ጌታሁን ገለፃ፤ ከአዊ ዞን በአንድ ቀን ከ50 አስከ 60 መኪና ከሰል ተጭኖ ወደ አዲስ አበባ ይገባል፡፡ ከሰሉ ከአዊ ዞን ተጭኖ ሲወጣ ደረሰኝ ይቆረጣል፡፡ ደረሰኙ የሚቆረጠው ለግብርና ቢሮ እና ለፌዴራል ገቢዎች ነው፡፡ በዚህም ደረሰኝ ከሰል የጫነው ሰው ህጋዊ መሆኑ ተረጋግጦ የይለፉ ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡
አቶ ጌታሁን እንደሚገልፁት፤ ከሰል ለማክሰል ፈቃድ እንዲሁ አይሰጥም፡፡ ፈቃድ ሲሰጥ መጀመሪያ ለከሰል ጥቅም ሊውል የታቀደው ወይም ለከሰል ምርት የተዘጋጀው እንጨት ከሰል አክሳዩ ግለሰብ ለግብርና ባለሙያ ያሳያል፡፡ የግብርና ባለሙያው ገምግሞ ፈቃድ ይሰጣል ወይም ይከለክላል፡፡ በዚህም መሰረት ከግብርና ባለሙያ ፈቃድ ከተገኘ ከሰል የማክሰል ሥራ ይከናወናል፡፡ ይህን የከሰል ማምረት ሥራ የሚያከናውነው አርሶ አደሩ ነው። አርሶ አደሮች ልክ አትክልት ወይም አዝዕርት አምርተው ለነጋዴዎች እንደሚሸጡት ሁሉ ከሰሉንም ለነጋዴዎች ይሸጣሉ፡፡ ነጋዴውም በግብርና ባለሙያ ፈቃድ ካገኘ አርሶ አደር ውጭ ከማንኛውም አርሶ አደር መግዛት አይችልም፡፡
ነጋዴው ከአርሶ አደሩ ከተረከበ በኋላ ወደ መሃል አገር አምጥቶ ለመሸጥ ደግሞ የራሱ ህጋዊ አካሄድ አለው፡፡ በዚህም መሰርት ከአርሶ አደር የተገዛን ከሰል ወደ መሃል አገር አምጥቶ ለመሸጥ ነጋዴው በኩንታል ዘጠኝ ብር ቀረጥ ይከፍላል፡፡ አቶ ጌታሁን ይህን ሂደት ተከትለው በቀን 28 ጥር ወር 2013 ዓ.ም ከአዊ ዞን የሰሌዳ ቁጥሩ ኦሮ 53102 በሆነ የጭነት አይሲዙ አራት መቶ ኩንታል ከሰል ጭነው መዳረሻቸውን ዓለም ገና ከተማ አድረገው መንገዳቸውን ወደ አዲስ አበባ ሲያመሩ፤ አዲስ አበባ በሌሊት ይደርሳሉ፡፡ ሲነጋጋ ከሰሉን ለደንበኛው ዓለም ገና ከተማን አልፈው ሰበታ ማድረስ ስላለባቸው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ይሁን እና ከአዊ ዞን ጀምሮ በየኬላው ህጋዊ ማስረጃቸውን በኬላ ላይ ለሚገኙ የፀጥታ አካላት እያሳዩ ያለምንም ችግር ዓለም ገና ከተማ ይደርሳሉ፡፡ ዓለም ገና ከተማ ወደ ሰበታ መውጫ ላይ ሲደርሱ ግን ፤ በሞተር ብስክሌት የሚንቀሳቀሱ ሁለት ፖሊሶች ያስቆሟቸዋል፡፡
እንደ አቶ ጌታሁን ገለፃ፤ ዓለም ገና ላይ ያስቆሟቸው ሁለት ፖሊሶች ስለጭነቱ ህጋዊነት የሚያረጋግጥ ማስረጃ ጠይቀው ማስረጃ ቢሰጣቸውም፤ ፖሊሶች ደረሰኙን ካዩት በኋላ ‹‹ህጋዊ አይደለም›› ይላሉ፡፡ ፈቃድ የሰጠውን ቢሮ ደውላችሁ ማረጋገጥ ትችላላችሁ ቢባሉም ፖሊሶቹ፤ ‹‹ይህ ሰነድ ኦሮሚያ ክልል ላይ አይሰራም›› በማለት በኦሮሚያ ክልል የከሰል ፈቃድ ብሎ ነገር አይሰራም፤ የሚል መልስ ይሰጠሉ፡፡
ሾፌሩን ከመኪናው በማስወረድ መኪናውን እያሽከረከሩ ፖሊስ ጣቢያ ለመውስድ ቢሞክሩም፤ ከሰሉ ብዙ በመሆኑ መኪናውን ለማሽከርከር ጥንቃቄና ልምድ ስለሚጠይቅ ሌላ ሹፌር አስመጥተው መኪናውን ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ አስረውታል ፡፡ አቶ ጌታሁን ያቀረቡት ማስረጃ እንደሚያመለክተው በሕጉ መሰረት ለተጫነው አራት መቶ ኩንታል ከሰል 3 ሺህ 6 መቶ ብር ቀረጥ ከፍለዋል፡፡ ክፍያም 3 ሺህ 3 መቶው ለገቢዎች ቢሮ ሲሆን፤ ቀሪው 3 መቶው ብር ደግሞ ለግብርና ቢሮ የተከፈለ ቢሆንም ህጋዊውን መንገድ ተከትለው የተበደሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ለዝግጅት ክፍሉ አቤት ብለዋል፡፡
መኪናው የተያዘው ጥር በ29 ቅዳሜ ስለነበር፤ ሰኞ የካቲት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሄደው ቢጠይቁም የሚያስተናግዳቸው አጥተው፤ በሦስተኛው ቀን ለሰበታ የፖሊስ መምሪያ ሃላፊ አቤቱታ ቢያቀርቡም የመምርያ ሃላፊ ‹‹ እዚያው ከእነሱ ጋር ጨርስ›› የሚል ምላሽ ተሰጥቷዋል። በዚህም ምክንያት ከማንም ምንም ምላሽ ሳያገኙ መንገላታታቸውን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም የዝግጅት ክፍሉ የሰበታ ከተማ የክፍለ ከተማ አንድ ፖሊስ ጽህፈት ቤትን ያነጋገረ ሲሆን፤ አሁንም ባለንብረቱ ህጋዊ ንግድ ፈቃድ ወይም መረጃ ይዞ ከቀረበ ከሰሉ በጨረታ ተሽጦ ገንዘቡ በገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ስለሚገኝ፤ ቀርቦ ህጋዊነቱን በማስረዳትና ህጋዊ ንግድ ፈቃዱን በማቅረብ ገንዘቡን መውሰድ እንደሚችል ገልፀዋል። በሌላ በኩል የሰበታ ከተማ አስተዳደር ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት በምን አግባብ ከሰሉ ሕገወጥ መሆኑን አጣርቶ በጨረታ ሽጦ ገንዘቡን ገቢ ለማድረግ ሊወስን እንደቻለ ለመጠየቅ፤ የዝግጅት ክፍሉ ቢሯቸው ድረስ ቢሄድ ጥያቄ ቢያቀርብም ሙሉ ሠራተኛው ስብሰባ ላይ በመሆኑ መረጃ የሚሰጥ አካል ለማግኘት አልተቻለም፡፡
እንዲሁም ቅሬታ አቅራቢው በወቅቱ ከሰሉ ሲያዝባቸው ለሰበታ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ቅሬታቸውን አቅርበው እንደነበር በገለጹት መሰረት፤ ፖሊስ መምሪያውን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጠን የዝግጅት ክፍላችን በአካል ተገኝቶ ቢጠይቅም በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ አቤት ባዩ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ባደረግነው ክትትል ከሰሉ ተሸጦ የተገኘው ገንዘብ የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡
እነዚህ እና ሌሎችም ጉዳዮች በዚህ አምድ ላይ ተስተናግደው መፍትሔ የተገኘባቸው ሲሆን፤ ሌሎችም በደል የደረሰባቸው አንባቢያን ወደ ዝግጅት ክፍሉ ቢመጡ የምናስተናግድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12/2013