ተወልደው ያደጉት በቀድሞ አጠራር ትግራይ ክፍለሃገር ራያቆቦ አውራጃ አላማጣ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው አላማጣ ከተማ በሚገኘው ታዳጊዋ ኢትዮጵያ በተባለ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት። ዘጠነኛ ክፍል ሲደርሱ ግን ሃይቅ ከተማ እንዲሁም 11ኛ ክፍል ደሴ በሚገኘው ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ከተከታተሉ በኋላ ተመልሰው ወደ አለማጣ ከተማ በመመለስ ታዳጊዋ ኢትዮጵያ በተሰኘው ትምርት ቤት 12ኛ ክፍልን ተማሩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በቀጥታ ፖሊስ ሰራዊት ውስጥ ተቀጠሩ። በሰራዊቱ በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በጡረታ እስከተገለሉበት 2012 ዓ.ም ድረስ ሲያገለገሉ ቆዩ። የለውጡን መምጣት ተከትሎም ለውጡን በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በሰላምና ፀጥታው ዘርፍ ሲያበረክቱ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅትም በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የደቡብ ምስራቅ ዞን የሀገረ ሰላም ከተማ ሚሊሻ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በህግ ማስከበር ዘመቻውም ሂደት የጁንታውን አከርካሪ ለመምታት በሚደረገው አገራዊ ጥረት ህዝቡን በማስተባበር ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። የዛሬው የዘመን እንግዳችን ኮማንደር ገ/መስቀል ወ/ሚካኤል ናቸው። እኛም ከእሳቸው ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– እንደአንድ የትግራይ ክልል ተወላጅ አሸባሪው ሕወሓት በህዝቡ ላይ ያደርስ የነበረውን ጭቆና እና ግፍ እንዴት ይገልፁታል?
ኮማንደር ገ/መስቀል፡– ይህ አሸባሪ ቡድን በትግራይ ህዝብ ስም የተቋቋመውን ፓርቲ ስያሜ ልንሰጠው ይገባል ብዬ አላምንም። የትግራይ ህዝብ አይደለም ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ይቅርና አሁንም በጭቆናና በድህነት ውስጥ እየኖረ ነው የሚገኘው። ይህ ቡድን በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግድ፤ ሃገሪቷን የሚያተራምስ ሃይል ስለሆነ እኔ ትክክለኛ ለህዝብ ነፃነት የቆመ ድርጅት ነው ብዬ አልወስደውም። እንደሚታወቀው ደግሞ የዚህ ድርጅት አመራር ፀረ-ዲሞክራሲ አካሄድ ነበረው። በአፈናም የተሞላ ስርዓት ነበረው። እኔ በዘመኔ የትግራይ ህዝብ የዲሞክራሲው ተጠቃሚ የሆነበት ጊዜ አላስታውስም። እስካሁንም ድረስ በፀረ ዲሞክራሲ አሰራሩ የትግራይን ህዝብ እያታለለ ነው የኖረው። በነገራችን ላይ ከፍተኛ የሚባል የመልካም አስተዳደር ችግር ነበረበት። ህዝቡን ከፋፍሎ በመግዛት በክልሉ ህዝብ መካከል ቅሬታ እንዲፈጠር አድርጓል። ያልሆነና ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የእነሱን ፖለቲካ ባሪያ አድርገውት ነው የቆዩት። ይህ ህዝብ እንደሌላው የሃገሪቱ አካባቢ ህዝብ እኮ አማራጭ ሃሳብ አግኝቶ አያውቅም። ስለአማራጭ ሃሳብ የሚያነሳም ካለ እንኳን ወይ ይታፈናል፤ አልያም ይገደላል። አሁንም እየታየ ያለው ከዚሁ የተለየ አይደለም። እናም የትግራይ ህዝብ በከፍተኛ ሁኔታ ጭቆና ላይ ነበር ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን– በክልሉ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካው ተጠቃሚ የነበሩት የአንድ አካባቢ ሰዎች እንደነበሩ ይታወቃል። በዚህ ረገድ ህዝቡ ከዚህ የጭቆና ቀንበር ለመውጣት ያነሳው የነበረው ቅሬታ ምን ይመስል እንደነበር ያስረዱን?
ኮማንደር ገ/ መስቀል፡– እንዳልሽው የክልሉም ሆነ መላው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ተይዞ የቆየው በአንድ አካባቢ ሰዎች የበላይነት ነው። እኔ የተወለድኩበት የራያ ህዝብም ቢሆን ከዚህ ጭቆና አላመለጠም። እንዳውም ዋነኛ የጭቆናው ገፈት ቀማሽ ነበር ማለት ይቻላል። ህዝብ ከህዝብ በሚለያየው እና በከፋፋዩ ስትራቴጂ ሁሉም ህዝብ ተጎጂ ሆኖ ነው የቆየው። እንዳልኩሽ ሰፊ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ነበሩ። የአንድ አካባቢ ቡድን አባላት ተቆጣጥሮት የነበረ ኢኮኖሚ ነበረን። ሰዎች በችሎታቸው፤ በብቃታቸው ሳይሆን የሚለኩት በቤተሰብ፤ በዘመድ አዝማድ፤ በውግንና ነበር። ይህ የተደራጀ ቡድን ተሰባስቦ በተለያየ ወቅት ይህንን ሃይሉን እያደራጀና እያጠናከረ ጭቆናውን ገፍቶ ቆይቷል። አድሎና መገለል ነበር። በተለይም ትንሽ ወጣ ያለ ሃሳብ ያለው ሰው አይስተናገድም ነበር። ከነጭራሹ ከምድረ-ገፅ ሊጠፋም ይችላል።
በዚህ ምክንያት በግሌ ከመጀመሪያውም ቢሆን ይህንን ድርጅት እቃወመው ነበር። የምቃወመው በተደራጀ መልኩ ሳይሆን በግሌ ነው። ምክንያቱም የመደራጀት መብቱና እድሉ ስላልነበር ነው። በመሆኑም ያለኝ አማራጭ የድርጅቱን አሰራር መጥላት ነው። ነገር ግን የፖሊስ ሰራዊት አባልም ስለነበርኩ ወጣ ባለ መልኩ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመሰለፍ የተቋሜ ደንብ ስለማይፈቅድ ያ ይዞኝ ነበር። ግን ጭቆናውን ተቋቁሜ ነው ለዓመታት ያለፍኩት። አሁን ደግሞ ጊዜ መጣና እነሱም ከነበሩበት ማማ ወረዱ። ይሁንና በዚያ ጊዜ ይህ ቡድን በህዝቡ ላይ ይፈፅም የነበረው አድሎ ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ አልነበረም። ሌላው ይቅርና በፖሊስ ሰራዊቱ ውስጥ ሙያው ከሚጠይቀው መስፈርትና ስርዓት ውጭ ለቦታው የማይመጥኑ ሰዎች እየመጡ የሚሾሙበት፤ የራሳቸው የሆኑ ሰዎች ያለአግባብ የሚያድግበትና ጥቅማ ጥቅም የሚያገኝበት ሁኔታ ነበር። አንድ ቤተሰባቸውን አምጥተው የማይመለከተው ቦታ ላይ ያስቀምጡታል። በመሰረቱ ይህንን የሚያደርጉት ለጥቅም እንጂ ግልጋሎት ለመስጠት አይደለም። በዚህ ሁኔታ ብዙ ምቾት አልነበረኝም። ልገልፀው የማልችለው የቁጭት ስሜት ነበረብኝ። የዚህ ስርዓት የሚወገድበትን ቀን እናፍቅ ነበር። እንደተመኘሁት አልቀረሁም፤ ለውጥ በሃገሪቱ መጥቷል። አሁን ላይ የዚህ የለውጥ አካል በመሆኑም የበኩሌን አስተዋጽኦ እያደረኩኝ እገኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ የጁንታ ቡድን በክልሉም ሆነ በአጎራባች አካባቢዎች ላይ እያደረገ ያለው የፀረ ሰላም እንቅስቃሴ በእርግጥ እታገልለታለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብ ምንአይነት ፋይዳ ይኖረዋል ብለው ያምናሉ?
ኮማንደር ገ/መስቀል፡- ለእኔ ይህ አሸባሪ አካል አሁን እያደረገ ያለው ህገወጥ እንቅስቃሴ ከዚህ ቀደም ያደርገው ከነበረው የተለየ አይደለም። በአጠቃላይ ዘረኛ፣ ወገናዊ፣ ከፋፋይ፣ በህዝቦች መካከል ጥላቻን የሚለፍፍ፣ ሰላም እንዲጠፋ፣ አንድነት እንዳይኖር ሌት-ተቀን ይተጋ የነበረ ድርጅት ነው። ሰዎች በፍቅር፤ ተማምነው እንዳይኖሩ ይሰራ የነበረ ሃይል ያልነቃውንና ያልተደራጀውን፣ ስለፖለቲካ በቂ ንቃት የሌለውን የዋሁን የትግራይ ህዝብ እያታለለ ነው የኖረው። በዲሞክራሲ ስም እየነገደ ህዝቡን ‹‹አንተ ጀግና ነህ›› እያለ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር እያጣላው ነው የኖረው። ከብሔር በሔረሰቦች ጋር እያናቆረ፤ እያፋጀ ነው የቆየው። በተለይም በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የራሱን ህፃናት ልጆች ለማስጨረስ ሲል በግድ ከጎኑ እያሰለፈ ነው ያለው። በጣም የሚያሳዝነኝ ደግሞ ወጣቱ እያለቀ ‹‹ጀግና ነህ›› እያለ ማታለሉና በእሳት እንዲማገድ ማድረጉ ነው። የትግራይን ህዝብ አፍ አውጥቶ ‹‹ልጅህ ሞቷል፤ ስለዚህ አንተ ጀግና ነህ›› ሲለው ፈፅሞ አያፍርም። ለእኔ እርግጥ ነው፤ የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ የጀግንነት ታሪክ አለው። ነገር ግን የገዛ ልጁን ላልተገባ ጦርነት እንዲማገድ ማድረጉ በራሱ ከጀግንነት አያስመድበውም። አሁንም በሃይል አፍኖ ወስዶ ያንን ሁሉ ወጣት አስጨርሶ ሳለ የስነ ልቦና ጫና እንዲደርስበት ለማድረግ ሲል ነው ከልብ ያልመነጨው የጀግንነት ዲስኩር የሚደሰኩርለት። ለመሆኑ ሰዎችን የሚያስጨርስ የትግራይ ህዝብ አለን?። ግን በእኔ አመለካከት ንፅሁ የትግራይ ህዝብ ሰው የማስጨረስ አላማም፤ አስተሳሰብም የለውም።
ይህ ቡድን ከመጀመሪያው ጀምሮ ልዩነት እንዲፈጠር የሰራ፤ ኢትዮጵያ እንድትበታተን ያለአንዳች እረፍት የተጋ ሃይል ትግራይን ሊመራ አይችልም። ሊያውም በአሁኑ ሰዓት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር የተፈረጀበት ሁኔታ እያለ ለትግራይ ህዝብ ቆሜያለሁ ቢል ሊቀበለው የሚችል አካል የለም። የማይሆን ነገር ነው። በዚህ አጋጣሚ ከተፈቀደልኝ እኔ ለትግራይ ህዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር አለ። ወጣቶችህና ህፃናቶችን እያስጨረሰ፣ ስደት እንድትሄድ ምክንያት እየሆነ፣ የጦርነቱ ጀማሪ ራሱ ጅንታው እንደሆነ እያወቅህ ለምን የእሱ ተባባሪ ትሆናለህ? ብዬ መጠየቅ እፈልጋለሁ። በተለይም በህግ ማስከበር ዘመቻ በየቤተክርስቲያኑ እየሄደ አንተን ካስጨፈጨፈ አካል ጋር በምን አግባብ ነው ከጎኑ ልትሰለፍ የምትችለው? ማለትም እሻለሁኝ። በሰላማዊ ቀጠና ውስጥ እየገባ ሆን ብሎ ጥይትና እሳት ይዞ ገብቶ ራሱ በጀመረው ጦርነት፤ በትምህክተኝነት ስሜት በረሃብ እያስጨረሰ እንዴት ‹‹ጀግና ነህ›› ሲል ትቀበለዋለህ?። በመሰረቱ በዚህ ጁንታ ምክንያት በየሰው ሃገር ወገኖቻችን ተሰደው እየተዋረዱ በምንም መልኩ ህዛባዊ ድጋፍ ሊኖረው አይችልም። የትግራይ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድም እንዲጠላ እየቀሰቀሰ ሲያደርግ ነው የኖረው። ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ የትግራይ ህዝብ ዝም ብሎ መቀመጥ እንደማይገባው መልዕክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡– የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር እንደሆነ ይታወቃል። ይሁንና ጁንታው ህልውናውን ለማስቀጠል ሲል ብቻ በተለይ የወጣቱን አስተሳሰብ በመቀየር ፀረ– ኢትዮጵያ ትግል እንዲያደርጉ መልምሎ አሰማርቷቸዋል። ይህ ትግራይን የመገንጠል አጀንዳ በእርግጥ የትግራይ ህዝብ አጀንዳ ሆኗል ተብሎ ይታመናል?
ኮማንደር ገ/መስቀል፡– እንደእኔ እምነት ይህ ‹‹እገነጠላለሁ›› የሚለው ሃሳብ ጥቂት የጁንታው ተጠቃሚ የሆነው ዲያስፖራ እንጂ የትግራይን ህዝብ አይወክልም። የትግራይ ህዝብ አጀንዳም፤ ከዚህ ቀደም ይህንን አላራመደም፤ ሆኖም አያውቅም። ጥቂት የዲያስፖራ ሃይሎች ከምዕራባውያን ጋር በመመሳጠር ጁንታው በቀመረው የፖለቲካ ቅስቀሳና ከፋፋይ ፖለቲካ መሰረት በማድረግ እያሴሩት ያለ ነው። መታወቅ ያለበት ዋናው ጉዳይ ግን አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ዛሬም ሀገሩን ኢትዮጵያን የሚወድ፤ ለሀገሩ አንድነትም ዋጋ እየከፈለ ያለ ህዝብ መሆኑን ነው። የትግራይ ህዝብ ከመጀመሪያውም ይህንን ጥያቄ አያስበውም። ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተነጥሎ የመኖር ፍላጎቱም፤ አላማውም አልነበረውም፤ አሁንም የለውም። መሰረታዊ ችግሩ ጁንታው የሚባለው ሃይል የጫነበት የፖለቲካ ቅስቀሳ ነው። በሃይል የጫነበት፤ አማራጭ ሃሳብ እንዳይኖረውና ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በሰላምና በፍቅር እንዳይኖር የመጀመሪያ ፍላጎቱ ስለሆነ ነው። እያተራመሱ ያሉ እነዚህ ሃይሎች ናቸው በቋሚነት።
በነገራችን ላይ ይህንን አጀንዳ እያስፋፉ ያሉት ጥቂት የዲያስፖራ አባላት ብቻ አይደሉም። ምዕራባውያንም አሉበት። ጁንታው በሚቀይሰው ተንኮል ተታለው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሱ አካላት መኖራቸው መታወቅ አለበት። የትግራይ ህዝብ ግን ከውድ ወገኖቹ ጋር አንድም ቀን ተለይቶ የመኖር ፍላጎት እንደሌለው መታወቅ አለበት። ሲጀመር የትግራይ ህዝብ መሬት ውረርልኝ አልያም ተገንጠልልኝ አላለውም። የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ከኢትጵያ ህዝብ ጋር በሰላም መኖርና ማደግ ነው። ጁንታው ራሱ የሸረበው ወይም ያቀደው ሴራ ነው። ህሊናቸውን ከሸጡ ዲያስፖራዎች፤ እንዲሁም ከምዕራባውያን ጋር በመሆን የፈጠረው ተንኮል ነው። ደግሞም ራሱ በቀሰቀሰው እሳት እንደሚጠፋ ምንም ጥርጥር የለኝም። የትግራይም ህዝብ የሚያዋጣውን ያውቃል። የጥላቻ ፖለቲካ በተለይም ህዝቡ አሁን በተፈጠረው ሁኔታም ያዝናል። አሁን ህዝቡ የሚፈልገው ወደተረጋጋ ሁኔታ መግባት ነው። ህዝቡ ጦርነት እንደማያስፈልገው ትምህርት ይሰጡ የነበሩ የትግራይ ልጆችን በግፍ ገድለዋቸዋል።
በተለይም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰራተኞች ላይ ይደረግባቸው የነበረው ጫና ከባድ ነበር። እነዚህ ሰዎች ይሰሩ የነበሩት ስራ ግልፅ ነው፤ የእርዳታ እህል በአግባቡ ለተረጂው ህዝብ እንዲደርስ፣ የመሰረተ ልማቶች ተጠግነው ቶሎ ስራቸውን እንዲጀምሩ፤ ማህበራዊ ግልጋሎቶች በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲጀምር ነበር። እነኚህ ሰዎች ግን የትግራይን ህዝብ በማታለል ብልፅግና እና ባንዳ፤ ፀረ ትግራይ ህዝብ የሚል ስም እንዲሰጣቸው ነው ያደረጉት። በዚህ ምክንያት መንገድ ላይም ሆነ በተገኙበት እየመጣ፤ እያሰሰ፤ መንገድ ላይ እንደ ፍየል አርዷቸዋል። በየቤታቸው እያንኳኳ ወስዶ አንዳንዶችን አድራሻቸውን አጥፍቷቸዋል። ያሉበት ቦታም አሁን በትክክል መታወቅ አልቻለም። የእነ ኢንጂነር እምብዛን ሁኔታን ማንሳት ይቻላል። በእነ ሃይላይ አምዶም ላይ የተፈፀመውን መጥቀስ ይቻላል። የሌሎችንም ሰዎች ደብዛ አጥፍቷል። ሌሎች ቁጥራቸው ከ50 በላይ የሆኑ እኛ የማናቃቸው ሰዎች አሁንም ተመሳሳይ እጣ ደርሷቸዋል። አሁን ላይ በአሸባሪው ሕወሃት የተገደሉትና የታፈኑት የትግራይ ልጆች ቁጥራቸው ከ100 በላይ ሆኗል። ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ በትግራይ ወገኖች ላይ ሊገለፅ የማይችል በደል ነው እየፈፀመ ያለው።
በመሆኑም እንዲህ በገዛ ወገኖቹ ላይ ግፍ የፈፀመ አካል ለፍርድ ማቅረብ ይገባል። በመሰረቱ ወንጀለኛን ለፍርድ ማቅረብ የትግራይ ህዝብ ባህል ነበር። አሁን ላይ እንዴት ይህ ባህል ተረስቶ ከጁንታው ጎን ሊቆም ይቻለዋል?። ለምንስ በጁንታው ፕሮፓጋንዳ ሊመራ ቻለ?። በጁንታው የሞቱ ሰዎች መብት በህግ ፍትህ ሊያገኝስ አይገባም ነበር?። እኔ የትግራይ ህዝብ ይህ ሁሉ በደል እየተፈፀመበት ምን እየሰራ ስለመሆኑ መጠየቅ እፈልጋለሁ። እነ እምብዛ ሲሞቱ ማንገደላቸው ብለህ ጥያቄ ለምንስ አታነሳም?። ይህንን የጥላቻ ፖለቲካ ከመቼ ወዲህስ ነው መቀበል የጀመርከው?። ደግሞም ይህ የጥላቻ ፖለቲካ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። መንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻ እያደረገ ያለው በተወሰኑ ሃይሎች ላይ ብቻ መሆኑን ልንረዳ ይገባል። ጁንታው የፌደራል መንግስት በህዝቡ ላይ እንደዘመተብህ አድርጎ የሚዘራው ፕሮፓጋንዳ ፈፅሞ ሊቀበለው አይገባም። ችግር ካለ እንኳ በውይይት እንጂ የሚፈታው ከጁንታው ጋር በማበር አይደለም። እኛ እየሰራን ያለነው ስራ ለትግራይ ህዝብ የማይጠቅም ከሆነ በመነጋገር እንጂ አብሮ በማመፅ አይሆንም። በዚህም ምክያንያት መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ሊያውቅ ይገባል። የህግ ማስከበር ዘመቻው እንዲራዘም ጉልበት፤ ግብዓት፤ ጊዜ ቆጣቢ እንዳይሆን እያደረገ መሆኑንም መገንዘብ አለበት። ህዝቡ ጁንታው በገዛ ህይወቱ ላይ እየቀለደ መሆኑን መረዳት አለበት። ብልፅግና ማለት ወንጀል ማለት ነው ወይ? ምን ወንጀል ፈፀመ ብሎ ህዝቡ ሊጠይቅ የሚችለው?። ህዝቡ ጠላቱንና ወዳጁን መለየት የሚችለው ከመጠየቅ ነው። ወንጀል የፈፀመን የሚጠቃ ማህበረሰባዊ የሆነ ጠንካራ የዳኝነት ስርዓት አለን። ሰውን የሚገድል ሽፍታ እንጂ መንግስት አይደለም። መንግስት ወንጀል የፈፀመን አካል በህግ ዳኝቶ ይቀጣዋል እንጂ እንደ ጁንታው በየመንገዱ አይገድለውም። ፀረ-ህዝብ ማነው? ጁንታው ወይስ መንግስት? ሃገሪቷን ለመሸጥ ከምዕራባውያን ጋር እየተደራደረ ያለ ባንዳ ሂሳብ እናወራርዳለን ይላል። ግን በትግራይ ህዝብ ላይ ሂሳብ እያወራረደ አይደለም እንዴ? ከህዝብ ጋር ተጣላ እያለ ሂሳቡን አወራርዶ ጨርሶ አይደለም እንዴ? ሲኦልም እንኳን ቢሆን እንገባለን ቢልም አስቀድሞ እሱ ሲኦል ገብቷል። በአጠቃላይ ህዝቡ ግራና ቀኝ አይቶ ወደፊት መገስገስ መቻል አለበት።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ጁንታውን ለፍርድ ማቅረብ አለበት የሚል እምነት አለኝ። ጁንታውን ለፍርድ ማቅረብ የፌደራሉ መንግስት ሃላፊነት ብቻ አይደለም። በዋናነት የትግራይ ህዝብ ተዋናይ መሆን ይገባዋል። የትግራይን ህዝብ እጉያው ውስጥ ሆኖ ‹‹ጀግና ነህ›› እያለ እያታለለና በእሱ ደም እየነገደ፤ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የተነሳ ሃይል እንዴት ያታልልሃል? ለምንስ አትነቃበትም? በርቀት ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ የጁንታውን ማንነት ጠንቅቆ አውቆት ሳለ እንዴት የትግራይ ህዝብ ሊነቃበት እንዳልቻለ ለእኔ አይገባኝም። ምንአይነት የማደንዘዣ መድሃኒትስ ቢወጋው እንደሆነ የትግራይ ህዝብ ይህንን ያህል በደል እየደረሰበት ዝምታን ሊመርጥ የቻለው አላውቅም። ከዚህ ቀደም ግን የትግራይ ህዝብ ለሞተ ሰው የሚቆረቆር ነበር። ታዲያ አሁን እንዴትስ ነው ብልፅግናን ደግፈሃል እያሉ የገዛ ልጆቻችሁን ሲገሉ እያያችሁ ዝም የምትሉት? ብዬ መጠየቅ እፈልጋለሁ።
ጁንታው አማራን ዋነኛ ጠላቱ አድርጎ የትግራይ ህዝብ እንዲያስብ ተፅዕኖ ሲፈጥርበትና ሲያስፈራራው ነው የኖረው። በነገራችን ላይ፤ በዚህ ዙሪያ ብዙ ስራ መሰራት አለበት ብዬ አምናለሁ። በትግርኛ አንድ ተረት አለ። ይኸውም ‹‹ካብ ምጉያይ ምውዓዋ ክሳድ ምሓዝ ›› ይባላል። ይህም ማለት እየሮጡ ከመዋል ቁልፉን መያዝ ማለት ነው። እናም ኢትዮጵያ እድትተራመስ ያደረገው ዋናው ቁልፍ አካል ስላልያዝነው ነው። እዛው ያለው ህዝብ ተደራጅቶ ነቅቶ ጁንታውን ለህግ እንዲያቀርብ የሚያደርግ ስራ አልተሰራም። አሁን እየታየ ያለው እኮ የጉልበት፣ የቁሳቁስ የሃብት ብክነት አይመጣም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት 100 ቢሊዮን ብር ለትግራይ ክልል ብቻ ወጥቷል። ታዲያ ይህ ሁሉ ብር የት ገባ? በህግ ማስከበር ዘመቻው ላይ የነበሩት ተግዳሮቶች በርካታ ነበሩ። መንግስት ይህንን ህዝብ ለማረጋጋትና የተወሰኑ ወንጀል የፈፀሙ የጁንታው ሃይሎችን በቁጥጥር ስር ማዋልና ለፍርድ ማቅረብ ነው። ትግራይ ላይ ጦርነት አላወጀም።
በዚህ ሂደት ሲጀምር ጁንታው መሰሪ ስለሆነ ህዝቡንም ሆነ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሳይቀር በማጭበርበር ፖለቲካ በማፈን የሱ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ነው ያደረገው። ከዚህ ለህዝብ እርዳታ ሲላክ በቀጥታ ለጁንታው ይሄድ ነበር። በአጠቃላይ ህዝቡን ውስጥ ውሥጡን በስውር ሲያደራጅ ነው የቆየው። በመሰረቱ ከጁንታው ጋር የሚተባበሩ ሰዎች የጁንታው ታናሽ ወንድሞች እንጂ የትግራይ ህዝብ ነው የሚል እምነት የለኝም። እነዚህ ሰዎች መረጃ በመስጠት፣ እህል በማቀበል ጁንታውን ነበር ሲተባበሩ የነበሩት። የጊዜያዊ አስተዳደር አካል በነበሩ ሰዎች እኮ የተገደሉ የጊዜያዊ አስተዳደር ሰራተኞች አሉ። ጉያችን አብረውን እየሰሩ በእኛ ላይ ያሴሩ ነበር። መንግስት እዚህ ላይ መፈተሽ አለበት። እኔ እንዳውም እዚህ ድረስ መጥቼ ቃለመጠይቅ ለማድረግ ከገፋፋኝ ነገሮች አንዱ ይኸው ጉዳይ ነው። መንግስት ከራሱ መዋቅር ጀምሮ እናቀርባለን፤ ግን አይተገበርም። እየሮጡ ከመዋል ቁልፉን መያዝ ነው የሚገባው ያልኩትም ለዚህ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የፈለገውን ያህል ቢደክምና ጉልበት ቢያወጣም ውጤታማ ላይሆን ይችላል። ዋናው የመስመር ማጥራት ስራ መሰራት ይገባል። እንዳውም መንግስት እኛን ቢያነጋግረን ደስ ይለናል። በነገራችን ላይ የጊዜያዊ አስተዳደሩን አካላት እዚህ ከመጣን ጀምሮ ያነጋገረን የመንግስት አካል የለም። እዚህ ለአንቺ ብዙ ነገር እንድነግርሽ አትጠብቂ፤ ለመንግስት ግን ብዙ የምንለው አለን። ስለዚህ ያነጋግረን። ይነስም፤ ይብዛ ይጠቅማል ብለን ያሰብነውን ነገር የመጨረሻ ላይሆን ይችላል ግን ግብዓት ሆኖ ለመንግስት ሊያገለግል ይችላል። መንግስት እስካሁን ለምን ሊያነጋግረን እንዳልፈለገ አልገባኝም። በትግራይ ያንን ያህል መስዋዕት ከፍለን ስምንት ወር ሙሉ ያለእንቅልፍ አድረን በሰቀቀን ኖረን ሳያበቃ ወደዚህ ስንመጣ እኮ ‹‹ለምን መጣችሁ?›› ያለን የመንግስት አካል ነበር። ይህ በጣም የሚያሳዝን እና የሚያስተዛዝብ ነው። ምክንያቱም እዚያ ብንቆይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እሙን በመሆኑ ነው። ባንዳ እየተባልን እኮ በጁንታው ስንሳደድ ነው የኖርነው። በአጠቃላይ መንግስት ጁንታውን የማጥፋት ጊዜ ከመርፈዱ በፊት እኛም የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት የምንችልበትን እድል ሊፈጥርልን ይገባል። እርግጥ ነው፤ በውስጣችን የሚጎዳ ሰው እንዳለ ሁሉ የሚጠቅም ሰው እንዳለ መንግስት መገንዘብ መቻል አለበት። ስህተቶችንና ክፍተቶችን አብረን በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል። በነገራችን ላይ መንግስት እኛን ሰብስቦ አለማናገሩ በራሱ የሚያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ስለዚህ ይንንም ማጤን ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሽብር ተግባሩን ወደአማራና ወደ አፋር ክልሎች ማስፋቱ ምን ያህል የፀብ አጫሪነት ባህሪውን ለመግታት ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ኮማንደር ገ/መስቀል፡– ይህንን እኮ ነው የምልሽ፤ መንግስት ይጥራን እንጂ ጁንታው የጀመረውን የመስፋፋት ዘመቻ ለማስቆም እኛ ዝግጁ ነን። ጁንታው የተረጋጋች ትግራይ እንዳትፈጠር እኮ ነው መንግስት ለህዝቡ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ በመጠቀም እየተስፋፋ የመጣው። መንግስት ከእርዳታው ጎን ለጎን ሰራተኛውን ምንም ስራ ሳይሰራ ደመወዝ ከፍሎታል። ይህንን እያደረጉ ያሉት በውስጣችን የተሰገሰጉ ሃይሎች ናቸው። አሁንም የኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ ወደ ትግራይ ከመላክ አልቦዘነም። እንደእኔ እምነት ይህ እርዳታ ምዕራባውያን ባቀነባበሩት ተንኮልና ዘዴ ለህዝቡ በማስመሰል በቀጥታ ጁንታው ነው እንዲጠቀም እየተደረገ ያለው። ቀጥታ ወደ ጁንታው ተጭኖ እንደሚሄድ አልተጠራጠርም። ይህንን የምልሽ ዝም ብዬ አይደለም፤ ከልምድ አንፃር እንጂ። ስለዚህ አሁን የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ህዝብ እርዳታ ማግኘት የለበትም የሚል እሳቤ ከመጀመሪያውም የለውም። እንዳውም በአንፃሩ የትግራይ ህዝብ እንዲጠቀም ይህ ነው የማይባል በጀት መድቦ ነው ሲደግፍ የነበረው። አሁን ግን እርዳታው ለጁንታው እየሄደ መሆኑ ያሳዝናል። ለጁንታው 150 ተሽከርካሪ መላኩን ሰሞኑን ሰምተናል። ይህንን የእርዳታ እህል ህዝቡ ያገኘዋል ብዬ ስለማላምንም በሁኔታው ቅር ተሰኝቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እዚህ ጋር የመንግስት ስህተት ምኑ ላይ ነው?
ኮማንደር ገ/መስቀል፡- እርግጥ ነው መንግስት ለህዝቡ እርዳታ የመላ ሃላፊነት አለበት። ሆኖም ለህዝቡ የተላከውን እየተቀበለ ያለው ጁንታው በመሆኑ ምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ከችግር ልንታደገው አልቻልንም። ይህ ሁኔታ እንደአንድ የክልሉ ተወላጅ ያሳዝነኛል። ነገር ግን ይሄ ስህተት እንዳይደገም ይህንን ቦታ ቶሎ መቆጣጠር ነው የሚገባው። እንደዚህ አይነት ጫወታና ቀልድ ውስጥ እያስገቡን ያሉትን ምዕራባያውን ሃሳብ ፈፅሞ ልንቀበል አይገባም። ይህ የሃገራችንንም ሉዓላዊነት የሚዳፈር ተግባር በመሆኑ በእርዳታ ስም ጁንታውን እደግፋለሁ የሚል የውጭ ሃይል በአፋጣኝ ማስወጣት ነው ያለብን። አሁን በመላው የሃሪቱ አካባቢዎች የተነሳውን ሰራዊት እንቅስቃሴ በፍጥነት ወደ ውጤት መምጣት ይገባል ባይ ነኝ። ይህንን ማድረግ ስንችል ነው ህዝቡን ከሞት መታደግ የምንችለው። እርግጥ ነው ይህ ጉዳይ ጥናት ይፈልጋል። ለእኔ ግን ከምንም በፊት መንግስት ክልሉን በቁጥጥሩ ስር ማስገባት ይኖርበታል። ደግሞስ ጁንታው እህል እንዲያከፋፍል ስልጣን የሰጠው አካል ሊኖር አይችልም። ከምዕራባውያን ጋር ተሻርኮ እህሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገባበትን ስራ እንዳለ እሙን ነው። ስለዚህ ይህ ጉዳይ መታሰብ አለበት።
አዲስ ዘመን፡– የአሜሪካ መንግስትና አንዳንድ የውጭ ሃይሎች ከጁንታው ጋር ድርድር እንዲደረግ ጠይቀዋል። በእርግጥ ከአሸባሪ ቡድን ጋር የኢትዮጵያ መንግስት መደራደሩ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል?
ኮማንደር ገ/መስቀል፡– በመሰረቱ ድርድር ማለት ምን ማለት ነው? ድርድር እኮ የሚያስፈልገው የሰው ህይወት፤ ንብረት ፤ ጉልበት ሳይጠፋ አስቀድሞ ልብ ያለው አካል የሚያደርገው ነው። አሁን ያለውን የሃገራችን መንግስት በዚህ ረገድ ሊመሰገን ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ወደዚህ ሁኔታ ከመገባቱ በፊት ብዙ ለምኗል፤ አማልዱኝ ብሏል፤ ታግሷልም። ጦርነት ይብቃን እናንተ የዘረፋችሁት የገደላችሁትን ሁሉ ይዛችሁ አርፋችሁ ተቀመጡ ብሏል። ኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ አዝላ ተቀምጣለች፤ ይብቃን ከዚህ በኋላ አብረን እንበልፅግ፤ አብረን እናልማ ቢልም አሻፈረኝ አለ። ለእርቅ የተላኩ ሽማግሌዎችን እንኳን አዋርዶ እንደላከ ይታወሳል። በዚህም አላበቃም፤ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የማይነካ መስመር ነክቶ ሀገሪቷን አሁን ለገባችበት ውጥንቅጥ ውስጥ ዳረጋት። የኢትዮጵያ መንግስት ከመጀመሪያውም ህግ የማስከበር ግዴታ ስላለበት ነው ተገዶ ወደዚህ ጦርነት የገባው። ስለዚህ ከዚህ አካል ጋር አሁንም ድርድር ማድረጉ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም።
መንግስት አሁንም ህዝቡን ከጎኑ ስላሰለፈ ድል እንደሚቀናው አምናለሁ። የአሸባሪውን ሕወሃት ርዝራዦች ከገባበት ጉድጓድ ውስጥ አስወጥቶ ለፍርድ እንደሚያቀርበውም ምንም ጥርጥር የለኝም። ደግሞስ በህግ ከሚፈለግ አሸባሪ ጋር ምንስ አይነት ነው ድርድር የሚደረገው?። በህግ ከሚፈለግ አካል ጋር በየትኛው አለምስ ነው እስካሁን ድርድር የተደረገው? እኔ ምን አይነት የፖለቲካ ፍልስፍና እየተከተለ እንዳለ አይገባኝም። ይህንን ሁሉ ከፈፀመ በኋላ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ንቀት ነው የሚያሳየው። ትግራይ ሃላፊነት የሚሸክም ወጣት እንዳይኖራት ህፃናትን ሁሉ በጦርነት ከማገደ በኋላ እንዴት ነው ከዚህ ወንጀለኛ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ተብሎ ውይይት የሚያደርገው። አይኑን በጨው አጥቦ እንደንፁህ የመደራደሪያ ነጥብ ማቅረቡ በራሱ እኔ ለመስማት እንኳን ይከብደኛል። ይህ በተግባሩ የማያፍር ዘራፊ፣ ፀረ- ኢትዮጵያ ከሆነ ሃይል ጋር ድርድር ያስፈልጋል ብዬ አላምንም። ድርድር የሚደረገው እኮ ህጋዊና ሰላማዊ ከሆነ አካል ጋር ነው። እንዴት ከወንበዴ ጋር ድርድር እንቀመጣለን?። ይህ ፈፅሞ የማይታሰብ ነው። ጁንታው የአለም የመጨረሻው የተባለውን ወንጀል ነው የፈፀመው። በዘር ማጥፋት የተሳተፈ፤ የሃገሪቷን ሃብት ሙልጭ አድርጎ የበላ ነው። የኑሮ ውድነት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ያደረገውም እሱ ነው። ከዚህ ሃይል ጋር እንዴት ነው ድርድር የሚታለመው?። ይሄ ቀልድ ነው። እኔ ከዚህ በኋላ ቃሉን እንኳን ባልሰማው እመርጣለሁ።
ጁንታው ሀገሪቱ እድሜዋን ሙሉ የማትወጣው እዳ ነው ጭኖባት የሄደው። በእጅ አዙር ቀኝ ግዛት ለምዕራባውያን ሀገር ሸጧል። ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመደራደር የዘመናት ቁጭታችን ውጤት የሆነውን የታላቁን ህዳሴ ግድብ ለመሸጥ ተስማምቶ ሲያበቃ ሲነቃበት ዶክተር አብይ ላይ ማላከኩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። በአጠቃላይ እንደራደር የሚለው ቀልድ ትንሽ ቦታውን ቢይዝ ጥሩ ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ። በነገራችን ላይ ይህ ሃሳብ ለትግራይ ህዝብም አይመጥንም። ከዚህ በኋላ ይህንን መሰሪ ሃይል ከምድሪቱ ማጥፋት ነው የሚገባው። እስካሁን በንጹሃን ላይ ያወራረደው ሂሳብ አይበቃውም? አሁን ጊዜው የእኛ ነው ፤ ጁንታው የዘራውን ማሳጨድ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል የሚል መልዕክት ነው ያለኝ። በተለይ ለአሸባሪው ጌታቸው ረዳ የማስተላልፈው መልዕክት አንተ ሳትሆን እኛ ነን የምናወራርደው ሂሳብ ያለን የሚል ነው። ምክንያቱም የሱ ሂሳብ አሁን ላይ አልቋል።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የተለያየ በአጀንዳ ያላቸው የምዕራባውያንን ተፅዕኖ በምን መልኩ ልንከላከለው እንችላለን ብለው ያስባሉ?
ኮማንደር ገ/መስቀል፡– እንደእኔ እምነት በውጭ አካላት የሚደረግብንን ጫናም ሆነ ተፅዕኖ መከላከል የምንችለው ህብረታችንን ማስቀጠል ስንችል ነው። የምዕራባውያኑ ጫና በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግልፅ እየሆነ ነው የመጣው። ከዚህ ቀደም የነበሩት ጫናዎች በግልፅ አልነበሩም ሲካሄዱ የነበሩት። በስውርና በደባ ነበር። አሁን ላይ ግን ጎልቶ እየወጣ ነው። ሰሞኑን የመጡት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ሃላፊ እንደእኔ ከሆነ ሌላ ተልዕኮ ስላላት እንጂ እህሉን ወስዳ ለጁንታው ባላስረከበች ነበር። በመሆኑም በአለም ላይ ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ይህም ማለት ህሊናቸውን የሸጡ ዲያስፖራዎችን ሳይጨምር ሀገር ወዳድ የሆኑ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለማተራመስ እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴ በአንድ ልብ በመሆን መቃወም እና ለሀገራቸው መታገል ነው የሚገባቸው። ይህ ድርጊታቸውን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለአለም ማሳወቅና ማጋለጥ ይኖርባቸዋል።
ከዚህ ሰብዓዊ መብት ጥሰት በገፍ እየፈፀመ ካለ ቡድን ጋር ውል የተፈራረሙ አካላትም እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ሊያነሱ ይገባል። ውሸታቸውን በአለም መገናኛ ብዙሃን ሁሉ እየቀረብን ማጋለጥ አለብን። በተለይ ወገንተኛ የሆኑ ሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑ አካላትን ሴራ ተባብረን ማፍረስ አለብን ብዬ አምናለሁ። ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ የምትገነጣጠል ሀገር እንዳልሆነች፤ የትግራይ ህዝብ የመገንጠል ሃሳብ እንደሌላው ማስረዳትም ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። ሌላው ጉዳይ አሁንም ሊሰመርበት ይገባል ብዬ የማስበው የህግ ማስከበር ዘመቻው ጊዜ መውሰድ የለበትም። ኢትዮጵያውያን በአንድነት የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው። አሁን በአንድነት ካልቆምን የምዕራባውያንና የወያኔ መፈንጫ መሆናችን የማይቀር ነገር ነው። ጦርነቱ በተጓተተ ቁጥር ኢኮኖሚያችን እየቆረቆዘ፤ ድህነት እየተስፋፋ ነው የሚመጣው። ጁንታ በመሰረቱ እሱ ስልጣን ከለለቀ ወዲህ ሀገሪቱ ከጦርነት እንዳትወጣና በድህነት አዝቅት ውስጥ እንድትዘፈቅ ነው የሚፈልገው። ስለዚህ ከመቼውም በላይ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባናል። አሁን ላይ ህዝቡ ከሃዲውን ቡድን ለመምታት በቆራጥነት መነሳቱ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው። ለዚህ አድናቆት አለኝ። ተጠናክሮ ሊቀጥል ግን ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካሎዎት እድሉን ልስጥዎት?
ኮማንደር ገ/መስቀል፡– እኔ በዋናነት መልዕክት ማስተላለፍ የምፈልገው ለትግራይ ህዝብ ነው። ጁንታው በጀመረው ጦርነት ግራ ተጋብቶ ያስከፈለው የህይወት፤ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ፤ ስደት ሁሉ አልበቃ ብሎ አሁን ወደባሰ ችግር ውስጥ ሊከተው መሆኑን ተገንዝቦ ዝምታውን ሰብሮ መውጣት ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ። ከጁንታው ሊለይም ይገባዋል። እየተገደሉ ያሉ የጊዜያዊ አስተዳደር ሰራተኞችን ህይወት በከንቱ የመጥፋቱን ነገር ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባዋል። አሁን ላይ በጁንታው የተገደሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት ቁጥራቸው ከ150 እየበለጠ ነው ያለው። በመሆኑም ይህ ሃይል ለቀረው ህዝብም የማይተኛ በመሆኑ ህዝቡ ወደ ቀልቡ መመለስ አለበት። ጁንታው ወደ ፍርድ እንዲቀርብ ዋነኛውን ሚና የትግራይ ህዝብ ሊወጣ ይገባል። ሌላው በግሌ አዲስ አበባ መጥቶ ያለስራ የተቀመጠው የጊዜዊ አስተዳደሩ ሰራተኞች ስራ ሊሰጣቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ። ምንአልባት ድጋፍ ልናደርግ የምችለው ነገር ሊኖር ይችላል ብዬ ስለማስብም ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ኮማንደር ገ/መስቀል፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013