ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ይባላሉ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ20 ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡ በምክትል አፈጉባኤነት ብቻ 16 ዓመታት ያህል ያገለገሉ ናቸው። የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባልና ለ10 ዓመት ያህል የአፍሪካ ፓርላማ ህብረት የኢትዮጵያ ቡድን መሪ ሆነው አገልግለዋል። መምህር፣ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ባለሙያና በኢትዮጵያ ፓርላማ አባልነት ታሪክ ብቸኛ ሴት ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ነበሩም፡፡ ፖለቲካውን የተቀላቀሉት ገና የአስረኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ሲሆን፤ የኢህአፓ አባል በመሆን ነው፡፡ ከዚያ ጀምሮ ሁሉንም መንግስታት እያሳለፉ ዛሬ ላይ የደረሱና በተለያየ ደረጃ የሰሩ ናቸው፡፡ እናም ይህ ሁሉ የህይወት ጉዟቸው በርካታ ተሞክሮን ያነገበ በመሆኑ ትማሩበት ዘንድ ለዛሬ ‹‹የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል፡፡ መልካም ቆይታ ተመኘን!
ለሽታ ትሁነኝ
የተወለዱት በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በባህርዳር አውራጃ በይልማና ዴንሳ ወረዳ ከተማ ቀመስ በሆነችው አዴት ውስጥ ነው፡፡ ለእናታቸው የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ፤ በአባታቸው በኩል በርከት ያለ ልጅ ነበር። ከእርሳቸው በኋላም ቢሆን እናትና አባታቸው ብዙ ልጆችን ወልደዋል። በዚህም ምክንያት የቤተሰቡ በተለይም የእናታቸው የበረከት ልጅ እንደሆኑ ይታመናሉ፡፡ ምክንያቱም እርሳቸው ከመወለዳቸው በፊት እናት በተደጋጋሚ ልጅ ይሞትባቸው ነበር፡፡ እንደውም ስማቸውም ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደወጣላቸው ያስታውሳሉ፡፡
ስማቸው ሽታዬ የተባለው ቢያንስ ለሽታ ለማስረሻና ለበረከት ለእናቷ ብትሆንላት በሚል ታስቦ አባታቸው እንዳወጡላቸው ይናገራሉ፡፡ እናታቸው ደግሞ ‹‹ያሳብ›› ነበር የሚሏቸው፡፡ እንደውም ጎረቤት ሳይቀር በዚህ ስም እንደሚያውቃቸው ይናገራሉ፡፡ ብዙዎችም እርሷ ታድግላታለች ብለው አያምኑም፡፡ ግን ፈጣሪ የፈቀደው ሆነና የስጦታ ሁሉ መጀመሪያ ሆኑ፡፡ ሌሎችም ብዙ ደስታ የሚፈጥሩ ልጆች እንዲኖራቸው በር ከፋችነታቸው በአምላክ ፈቃድ አገኙ፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ቤተሰብ በስስት እንዲያያቸው አድርጓቸዋል፡፡
ወይዘሮ ሽታዬ በጣም ፈጣንና መብታቸውን አሳልፈው መስጠት የማይወዱ ልጅ ናቸው፡፡ ከሰው ጋር መጣላትን አጥብቀው የሚጠሉና በጨዋታም ከእድሜ ጓደኞቻቸው ሻል ያለ አቅም ነበራቸው፡፡
ወይዘሮ ሽታዬ የመጀመሪያ ልጅ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ሴት ልጅ ለጋብቻ ዝግጁ መሆን አለባት ተብሎ ስለሚታሰብ የወንድ ሥራ ሳይቀር እንድትለምድ ይደረጋል። ለዚህ ደግሞ ትልቁን ሀላፊነት የምትወስደው እናት ነች፡፡ እናም እንግዳችን የቤት ውስጥ ስራ የማይሰሩት ነገር የለም። እንደውም በአቅማቸው ተሰጥቷቸው ከአቅማቸው በላይ ይሰሩ እንደነበር አይረሱትም፡፡ ከሁሉ ነገር ግን የሚወዱት እናታቸው እፎይ የሚሉበትና ምግብ የሚቀምሱበትን ጊዜ መስጠትን ነው፡፡ እርሳቸው ቤተሰቡን ለመመገብ 11 ሰዓት ተነስተው ሰባት ሰዓት ይተኛሉ፡፡ ስለዚህም የእረፍት ጊዜያቸው በጣም ጥቂት ናት፡፡ ለዚህም በቻሉት ሁሉ ከትምህርት በኋላ እርሳቸውን ማገዝ ያስደስታቸዋል፡፡
በመብት ማስከበርና በመቻል ሁኔታ ሴት መሆናቸውን አስበው አያውቁም፡፡ ምን ያንሰኛል የሚሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በሴት ላይ ያለውን ጫና ሲያስቡት ግን እናታቸው ፈጥነው ፊታቸው ላይ ድቅን ይላሉ፡፡ አንድ የገጠር ሴት የሚደርስባትን ጫና በእርሳቸው አይተዋል። አባታቸው ባይታገሉላቸው ኖሮም ይህ እጣ ፋንታ የእርሳቸውም እንደሚሆን ያስታውሳቸዋል፡፡ ስለዚህም ዛሬ ድረስ ለሴቶች ተሟጋች እንዲሆኑ ያስቻላቸው ይህ ሁለቱ ነገር ነው፡፡ በእርግጥ ለዚህ ሁሉ መሰረቱ አንድ ነገር እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ይህም የአስተዳደጋቸው ሁኔታ ሲሆን፤ ባህላዊ እንደሆነ ቤተሰብ አንቺ ይህንን አታድርጊ ተብለው አያውቁም፡፡ በነጻነት እንዲናገሩ፣ እንዲወያዩና የፈለጉትን እንዲያደርጉ ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለታናናሾቻቸው ጭምር ሁሉም ይፈቅድላቸዋል። ስለዚህም ከእናታቸው እስከ አካባቢው ድረስ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና የሚሟገቱትም ለዚህ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
‹‹ጭር›› የሚባል ጨዋታ ከልጅነት ጨዋታዎች የማይረሱትና የሚወዱት ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ክረምት ላይ የሚጫወቱት ነው፡፡ ሳር በብዛት ተጠቅልሎ ሳር ውስጥ ተደብቆ ፈልጎ በማግኘት የሚከወን የጨዋታ አይነት ሲሆን፤ ያገኘው ሰው ታዝሎ እስከዳኛው ድረስ እንክብካቤ ይደረግለታል፡፡ በዚህም እርሳቸው ብዙ አሸንፈው እንደታዘሉበት የማይረሱት ጨዋታቸው ነበርና ልጅነቴን ሳስብ ይህንን አልረሳም ይላሉ፡፡
በልጅነታቸው መሆን የሚፈልጉት ነገር እንደ እድሜያቸው ከፍ እያለ የሚሄድ ግን በአንድ ነገር ላይ ብቻ ያረፈ ነው፡፡ ይህም መምህር መሆን ሲሆን፤ መጀመሪያ ላይ በቅርብ እንደሚያዩዋቸው ጥንቁቅ፣ ጎበዝ፣ ራሳቸውን የሚጠብቁና የተከበሩ መምህር መሆን ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ ከፍ እያሉ ሲሄዱ ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ይዘው የዩኒቨርሲቲ መምህር ወደ መሆኑ ያስቡ ጀመር፡፡ ህልማቸውንም ለማሳካት ብዙ ጥረዋል፣ ተሳክቶላቸዋልም።
የአባት ዋጋ ለልጅ
ከትምህርት ጋር የተዋወቁት በፊደል ቆጠራው በቤት ውስጥ በአባታቸው አማካኝነት ቢሆንም ዘመናዊው ትምህርት ግን በአዴት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በራሳቸው ሄደው ተመዝግበው ነው፡፡ ምክንያቱም ጊዜው እድሜ ደረሰ አልደረሰ የማይጠየቅበት፣ ተያዥ አምጣ የማይበልበት እንዲሁ ገብቶ እንዲማር ብቻ የሚፈለግበት ስለነበር እርሳቸውም ወደዚያ ሲያቀኑ ደስተኛ ሆነው ነበር የተቀበሏቸው፡፡ እንደውም የተለየ ድጋፍ ሁሉ ይደረግላቸው እንደነበር አይረሱትም፡፡ ምክንያቱም አካባቢው በተለይ ሴትን ልጅ ለትዳር እንጂ ለትምህርት አይልካትም፡፡ እስከ 15 ዓመት ባሉት ጊዜያት አግብታ የራሷን ቤት መመስረት እንዳለባት ይታመናል፡፡
እንግዳችን ወደጋብቻ ሳይሆን ወደ ትምህርት እንዲያቀኑ ያገዟቸው አባታቸው ሲሆኑ፤ ብዙ መስዋዕትነት እንደከፈሉባቸው ያስታውሳሉ፡፡ አባታቸው ባህሉን፣ ቤተሰባቸውን፣ ሚስታቸውን ታግለው ለእርሳቸው ነጻነትን ሰጥተዋቸዋል፡፡ እምነትም አሳርፈውባቸዋል። በዚህ ነጻነትም የአባታቸውን ትዕዛዝ ፈጻሚ ለመሆን እርሳቸውም ብዙ ጥረዋል፡፡ ያሰቡት ላይም ደርሰዋል፡፡
‹‹የተጻፈ ነገርን ለእኔ ካለው ማንም አይወስደውም ብዬ እንዳምን የሚያደርጉኝ በህይወቴ ውስጥ ብዙ ናቸው። ምክንያቱም የእኔ እህት በዘጠኝ ዓመቷ ተድራ እኔ ግን እንድማር እድል ተሰጥቶኛል፡፡ እንዲህ አይነት ገጠመኞች ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም ለእኔ የሆነን እኔ ብቻ አገኘዋለሁ የሚል እምነት አሳድሮብኛል›› የሚሉት ባለታሪካችን፤አባታቸው ቤተክህነቱን ጠንቅቀው የተማሩና በዘመንኛው ግብር ስብሰባ ላይ የሚሰሩ ናቸው፡፡ በዚህም ትምህርት ያለውን ዋጋ ጠንቅቀው ያውቃሉና እርሳቸው እንዲማሩ ከእናታቸው ሀሳብና ከባህሉ ጋር ጭምር ብዙ የታገሉ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
የአባታቸው በእርሳቸው ላይ እምነት ማሳደር ፈጣንና ጎበዝ ተማሪ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ሽታዬ፤ በተለይ በንባብ ብቃታቸው ዛሬ ድረስ እንደሚገረሙና መምህራን ሳይቀሩ ክፍለጊዜው ካለቀባቸው ወጥተው እንዲያነቡ እርሳቸውን ይጋብዟቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ የሚገርማቸው ከስድስተኛ ክፍል በኋላ በአዴት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ግድ ወደ ባህርዳር መጓዝ አለባቸውና ያ አይሆንም ብሎ የሚጠብቀው ሰው ብዙ ሆኖ ሳለ አባታቸው ግን ከወንዶቹ በተለየ መንገድ እንደማያዩዋቸውና እርሳቸው ያሰቡት ላይ እንደሚደርሱ እቅጩን ነገረው መላካቸው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በወቅቱ አይደለም ሴት ልጅን ብቻዋን እንድትማር ሌላ ከተማ መላክ በቅርብም ለማስተማር እድል የለም፡፡ በባህሉ እንደ ግዳጅ የሚታየው መዳር ብቻ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ጠንካራ ነን የሚሉ እንኳን ቤተሰቦች ቢኖሩ ከአዴት ውጪ ተሻግረው እንዲማሩ ለልጆቻቸው የሚሰጡበት ሁኔታ አናሳ ነበር፡፡ እንግዳችን ግን በአባታቸው እምነት ሰጪነት ባህርዳር ሄደው እንዲማሩ ሆነዋል፡፡
አባታቸው ‹‹እኔ ሽታዬን ልኬ ማስተማር ወንድ ልጅ ልኬ ከማስተማር ለይቼ አላየውም›› ያሉት ዛሬ ድረስ እንደማይረሳቸው ያጫወቱን ወይዘሮ ሽታዬ፤ በባህርዳር ብቻቸውን ሆነው የሚማሩበት እድል አልገጠማቸውም። የአባት ልጆች ስለነበሩ እነርሱ ጋር በመሆን እንዲማሩ ሁሉ ነገር ተመቻችቶላቸዋል፡፡ የተለየ ነጻነት ኖሯቸውም ነው የቆዩት፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ግብረገብ የሚባል ትምህርት በቋሚነት እንደ አንድ ትምህርት ይሰጣቸው ነበርና ብዙ እውቀትና ተስፋ እንዳላበሳቸው ያስታውሳሉ፡፡ የአገር ፍቅር በተለይም የባንዲራ ፍቅር፣ የሰው መውደድና አክብሮት ላይ ትልቅ አቅም የፈጠረላቸው እንደነበርም አይረሱትም፡፡ ይህ አወንታዊ ተጽዕኖ ደግሞ ዛሬ ድረስ ባንዲራ ሲወጣና ሲወርድ ካዩ መኪና ውስጥ ጭምር ሆነው ባሉበት እንደሚቆሙም ይናገራሉ፡፡
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በባህርዳር ከተማ አጼ ሰርጸድንግል ወይም በዛሬ ስሙ ጣና ሀይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት የተከታተሉት ባለታሪካችን፤ ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል በዚህ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በፖለቲካ ምክንያት ታስረው ስለነበር ከአራት ዓመት ያልተናነሰ ጊዜን ከቋሚ ትምህርቱ ተለይተው ነበር፡፡ በእርግጥ ይህንን ጊዜ እርሳቸው ተምሬበታለሁ ይላሉ። ምክንያታቸውም በህይወት እንደመማር የሚያጠነክር ቀለም የለም ብለው ያስባሉ፡፡ በዚህ ቆይታቸው በማረሚያ ቤት ብዙ ነገሮችን ተምረዋል፤ አንብበዋልም። ትምህርታቸው የበለጠ ጠንክሮ የሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ያለምንም መቆራረጥ እንዲቀጥል የሆኑበት የመሰረት ድንጋይም ይህ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
እንግዳችን የትምህርት ጊዜያቸውን ሲያስታውሱት በተለይ ሁለት ነገሮችን አይረሷቸውም፡፡ የመጀመሪያው የቤተሰብ ናፍቆት ሲበረታባቸው ቢያንስ በወር አንዴ ከባህርዳር እስከ አዴት ያለውን የ42 ኪሎሜትር ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ሌሊት በመነሳት በእግራቸው ይጓዙ የነበረበትን ጊዜ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አባታቸው የእርሳቸውን ስንቅ በአህያ ጭነው ሲደክማቸው መንገድ እያደሩ ይዘውላቸው የሚመጡትን ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ መኪና ሲሆን፤ በሳምንት አንድ ጊዜ ለያውም አንድ መኪና ብቻ መሆኗ ነው፡፡ እናም የአባታቸው ስንቅ ለማቀበል ሲባል የወረደባቸው ዝናብና ውርጭ መቼም ከህሊናቸው የሚጠፋ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡
በእስርና በአለመረጋጋታቸው ምክንያት የ12ኛ ክፍል ውጤት አልመጣላቸውም፡፡ ስለዚህም በማታው የሚማሩበትን እድል ብቻ ነው ማግኘት የሚችሉትና ይህንን አጋጣሚ በአግባቡ ተጠቀሙበት፡፡ በባህርዳር መምህራን ኮሌጅም ዲፕሎማቸውን በጆግራፊ የትምህርት መስክ መማር ቻሉ፡፡ ዲፕሎማቸውን ሲጨርሱ በዲግሪ በቀን የሚያስተምራቸውን ውጤት በማምጣታቸው ወዲያው ትምህርቱን መቀጠል ቻሉ፡፡ በዚህም በዚሁ ከተማ በፔዳ ግቢ በፔዳጎጂካል ሳይንስ የትምህርት መስክ መማርና መመረቅ ቻሉ፡፡
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ሲሆን፤ የትምህርት መስኩ ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ይባላል፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ምቹ ሁኔታ አልነበራቸውምና የተለያዩ ስልጠናዎችን በተለያዩ አገራት ከመውሰድ ውጪ አልቀጠሉም፡፡
ከሮቤ እስከ ምክር ቤት
በጊዜው ክልል የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ ስለዚህም ሰው በተመደበበት ይሰራል፡፡ እናም እንግዳችንም ከትምህርት በኋላ መጀመሪያ የተመደቡት ሮቤ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ ነው፡፡ ሁለት ዓመት ተኩል በዚህ ካገለገሉ በኋላ ኢህአዴግ ክልሎችን ወደ መፍጠሩ በመግባቱ በእርሳቸው ምትክ አንድ የኦሮሚያ ነዋሪ መጥቶ እርሳቸው ደግሞ ወደ ምስራቅ ጎጃም ደብረወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት እንዲዘዋወሩ ተደረጉ፡፡ የጆኦግራፊ መምህር ሆነው አራት ዓመታትን በዚያም አሳለፉ፡፡
ምዕራብ ጎጃም መቅረብ በመፈለጋቸው ሌላ ዝውውር ጠይቀው ቡሬ ሽጉዳድ በሚባል ሁለተኛ ደረጃ ማስተማራቸውን ቀጠሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በዚያ መቆየት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ክልሉ ሲዋቀር የትምህርት ዝግጅቶች አስፈላጊ ናቸውና በመስኩ የተመረቀ ሰው በመፈለጉ እርሳቸው ተመራጭ ሆኑ፡፡ በተለይ ለዚህ ደግሞ ሴት መሆናቸው ተመራጭ እንዳደረጋቸው ያስታውሳሉ፡፡ ስለዚህም በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ በትምህርት ቢሮ ውስጥ የስርዓተ ትምህር ዝግጅት ባለሙያ በመሆን ተቀጠሩ፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በቢሮው ውስጥ ብቸኛ ሴት በመሆናቸው የሴቶችን ጉዳይ ደርበው እንዲሰሩም ተደረጉ፡፡ ከሦስት ዓመታት በላይም በቦታው አገለገሉ፡፡
ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ያለው ጊዜ በምክርቤት ውስጥ ያሳለፉ ሲሆን፤ መጀመሪያ እንደገቡ ምክርቤት አባልና የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአንድ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በምክርቤቱ የሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ በመሆን 10 ዓመት ሰርተዋል። በክልል ፓርላማ ደረጃ ጭምር ኮከሱ እንዲቋቋም አድርገዋል፤ በተጨማሪ የሴቶች በምርጫ የመሳተፍ አቅምን በ38 ነጥብ 7 በመቶ እንዲጨምር ከታገሉ መካከል ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ብዙ የአገሪቱን ክፍሎች ከማየትም በላይ የምክርቤቱን አካሂድና ሥራ ጠንቅቀው እንዲያውቁና እንዲማሩ ሆነዋል፡፡ እንደውም እስከዛሬ ካሳለፍኳቸው ጊዜ የምወደውና ብዙ ሰርቼበታለሁ የምለው ይህ ጊዜ ነበር ይላሉ፡፡ ምክንያቱም በነጻነት የሚሰሩ ብዙ ሥራዎች ነበሩበትና ባይ ናቸው፡፡ አገር ላይ ያለውን መልካምም ሆነ ችግር ተረድቶ መስራት ብዙ መፍትሄ ለመስጠት አስቻይ ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ጊዜ ለእኔ እድል የተሰጠበት ነበርና ተጠቅሜበታለሁም ብለውናል፡፡
‹‹በዚህ ጊዜ አዲስ ሀሳብም ማመንጨት የምንችልበት ነበር፡፡ የመንግስት ሀሳብ ሳይሆን ጭምር የለውጥ ሀሳብ ማንሳት እንችል ነበር፡፡ የድርጅት ጫናም ቢሆን ብዙ አልነበረብኝም፡፡ ስለዚህም ለአብነት ቴሌ መሸጥ አለበት አይነት ሀሳቦች እንደልብ ይነሳሉ፡፡ በተለይም የተማረ ሀይል ሲሆን ብዙ ሰው ያዳምጠዋል፡፡ ምክንያቱም ምክርቤቱ ብዙም የተማረ ሀይል የለበትም፡፡ እናም አገርን ሊያሳድግ የሚችል ሀሳብ ሁሉ ማንሳትና ማመንጨት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ብዙዎቻችንን ነጻ ሆኖ መስራትና መንቀሳቀስ እንድንችል ያደረገን እንደነበር ያስታውሰኛል›› ይላሉ፡፡
ቀጣዩ ሁለተኛ ዙር በግምገማ እዚያው እንዲቀጥሉ የሚደረግበት ሲሆን፤ እርሳቸው ግን በሚናገሩት ንግግር ብዙዎቹ አልወደዷቸውም ነበር፡፡ እናም የወረዳ አመራር ሆና ትቀጥል እንጂ እዚህ መቆየት የለባትም ተባሉ። በዚህም ብዙ ክርክር በድርጅቱ ውስጥ ተነሳ፡፡ ሆኖም ብቸኛ ሁለተኛ ዲግሪ ያላትን ሴት አንስቶ ብአዴን ማንን ሊያመጣ ነው በሚል ሀሳብና ከላይ ከድርጅቱ የወረዳ አመራር ድረስ የሚደርሱ ሴቶች ውጤታቸው ዝቅ ተደርጎ በዚያው እንዲቆዩ ይደረግ የሚል መመሪያ በመተላለፉ እርሳቸው ቀጣዩን ዙር ተሳታፊ እንዲሆኑ አደረጋቸው። ስለዚህም ለውድድር ተዘጋጁ፡፡ ይሁን እንጂ በ97ቱ ምርጫ በምዕራብ ጎጃም ሁሉንም ቦታ አሸናፊው ቅንጅት በመሆኑ አንድም ሰው በኢህአዴግ በኩል የሚገባ ጠፋ። ነገር ግን ኢህአዴግ ቅንጅት አጭበርብሮኛል በማለቱ ዳግም ምርጫው እንዲካሄድ ሆነና ከ17 ወንበር ውስጥ እርሳቸው ብቻ ድርጅቱን ወክለው አለፉ፡፡
መስከረም ላይ ስራ ለመጀመር ሲገቡ ከሰልፍ ላይ እንደተጠሩ የሚያስታውሱት እንግዳችን፤ በወቅቱ የምርጫ ኮሚቴ የሚባል ነበርና በዚያ አባልነት እንዲሳተፉ ፈልገዋቸው እንደነበር አስበው አፈ ጉባኤው ቢሮ ተጓዙ ፡፡ ነገር ግን ያልጠበቁት ነገር ነበር የገጠማቸው፡፡ ይኸውም አስፈላጊው ሰው ተቀምጦ እየጠበቃቸው ነበርና የመምጣታቸው ጉዳይ ምክትል አፈጉባኤ እንደሚሆኑ ሊነገራቸው መሆኑን አወቁ፡፡ በወቅቱ በጣም ተደናግጠው እንደነበር፣ ሆኖም በድርጅት ሲገባ ለአገልጋይነት መሆኑን ስለተረዱ መናገር ያለባቸውን ተናግረው ለልብስ ቅየራ ወደቤታቸው አመሩ፡፡ መሀላ የፈጸሙት ልብስ ቀይረው መጥተው እንደነበርም አይረሱትም፡፡ ከዚህ ጊዜም በኋላ ምክትል አፈጉባኤ ሆነው እስከዛሬዋ ጊዜ ድረስ ማገልገል ችለዋል፡፡ ይህ ማለት እስከተራዘመው ዓመት 16 ዓመታትን በዚህ የአመራርነት ደረጃ ላይ ማገልገል ችለዋል ማለት ነው።
በዚህ ቆይታቸው ብዙ ውጣውረዶችን አሳልፈዋል። በተለይም ውስጥ የሚደረገው ፍትጊያና ክርክር ወደ መድረክ ሲወጣ የተለየ ሀሳብና ትግበራ ይዞ መምጣቱ በጣም ሁልጊዜ የራስ ምታት የሚሆንባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በመንግስት ተወስኖ የመጣን ነገር መቀየር አለመቻላቸውና አስፈጻሚ ብቻ መሆናቸውም እንዲሁ ልባቸውን የሚሰብረው ጉዳይ እንደሆነ ያወሳሉ፡፡ ህዝብ ጋር ሲሄዱና ቃል የገቡትን ሳይፈጽሙ መቅረታቸው፣ ተመሳሳይ ሀሳብ በየዓመቱ ማቅረባቸው፣ ምን ያህል በድርጅት በአንድ ጉዳይ ላይ ፍትጊያ እንደሚያደርጉና ተፈጸሚ እንዲሆን እንደሚፋለሙ ህዝቡ አለማወቁ በቆይታቸው የሚያስቆጫቸው እንደነበር ያነሳሉ፡፡
በኢህአዴግ ጊዜ እንደፈለገ መናገር ይቻላል ግን ተፈጻሚነት የለውም፡፡ ይህ ደግሞ ምክርቤቱን እጅ አውጥቶ ማጽደቅ ብቻ የሚችል፣ የተማረ ሰው የሌለበትና ሌሎች ሌሎች ነገሮች አስብሎት እንደቆየ ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህም በህገመንግስት የተሰጠውን መብት ተጠቅሞበት አልፏል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ እንደውም ትክክል ያልሆነ ነገር እንዲያምኑ ለምን አልጫናችሁም ተብሎ ተጠያቂነት አለ፡፡ ስብሰባ መሪውም ለምን ለእንትና ሀሳብ ረጅም ሰዓት ሰጠህ የሀሳቡ ደጋፊ ነህ ተብሎም ከስራ እስከመነሳት ይደረሳል፡፡ ስለሆነም በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገሮችን ገድቤ አልፌያለሁ ይላሉ፡፡
ፓርላማው የማያውቀውና የማይሰማው አገራዊም ሆነ አለምአቀፋዊ ነገር የለም፡፡ ግን ማንም ስለማይሰማውና ስለማይፈጽምለት በብዙ ችግር ውስጥ ጊዜ እንዲያሳልፍ ተገዷል፡፡ አቅምንና ችሎታን እንዳንጠቀም ሆነን ነው የቆየነውም፡፡ ይህ ደግሞ የሁላችንም ራስ ምታት ነበር ይላሉ፡፡
በፓርላማ ሥራቸው አውሮፓም ሆነ ኢስያን እንዲሁም አፍሪካን የዞሩት ባለታሪካችን፤ የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባልና ለ10 ዓመት ያህል የአፍሪካ ፓርላማ ህብረት የኢትዮጵያ ቡድን መሪ ሆነው ያገለገሉ ናቸው። ከዚህ በኋላ ደግሞ በግላቸው አገራቸውን የሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ እንዳቀዱም አጫውተውናል፡፡
አራት ዓመት የተጠጋው እስር
ለውጥ የሚፈልግ ወጣት ሁሉ ይህንን አጋጣሚ በምንም መልኩ ማለፍ አይፈልግም፡፡ ስለዚህም እርሳቸውም በአገር ላይ ለውጥ ለማምጣት ሲሉ ኢህአፓን ተቀላቀሉ፡፡ በእርግጥ ከሌሎች ድርጅቶች ቀድሞ ያሳመናቸውና ያገኛቸው እርሱ ስለነበረ እንጂ የሌላ ድርጅት አባልም ይሆኑ ነበር፡፡ ነገር ግን አጋጣሚዎች ወደ ኢህአፓ እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋልና በድርጅቱ ውስጥ ሆነው ከአባል ምልመላ እስከ ግንዛቤ መፍጠር ድረስ የሚደርሱ ሥራዎችን ይሰሩ ነበር፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ነው፡፡ በዚህ አባልነታቸው ሦስት ዓመታትን በእስር አሳልፈዋል፡፡
‹‹የእኛ አገር ፖለቲካ ሲጀመር ሀሳቡም እንቅስቃሴውም መነቃቃቱም እጅግ ጠንካራ ነው፡፡ ሆኖም ወደ ውጤት ሲመጣና ከትግል በኋላ ወደ ተግባር ሲገባ ግን ብዙ ነገሮች ብልሽትሽታቸው ይወጣል፡፡ የታገልኩት ለዚህ ነው ወይም የሚያስብሉ ክስተቶች ይፈጠራሉ›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ኢህአፓ ውስጥ እንዲገቡ ያስቻላቸው መሰረታዊ ነገር ሁሉም ለሁሉ የሚለው አስተሳሰብ ነው። ሰዓት ረፈደ ተብሎ የተቀጠሩት ቦታ ከመሄድና ሌላ ተጨማሪ ጊዜ ከመፍጀት ይልቅ ማንኛውም መስሪያ ቤት በተሰጠ ደረጃ ገብቶ መስራት አገርን ማገልገል እንደሆነ ድርጅቱ ማመኑ እርሳቸውን የሳበው ጉዳይ ነበር፡፡ የሶሻሊዝም አስተሳሰቡ መሬት ላይ ገነትን እንደሚፈጠር አድርጎ ነው የሚያሳየው። እያንዳንዱ እንደችሎታው ለእያንዳንዱ እንደፍላጎቱ ይሰጠዋልም ስለሚል ከዚህ አስተሳሰብ ተቋዳሽ አለመሆን ደግሞ በምንም ተአምር አይቻልምና እርሳቸውም ተቀብለውት በሙሉ እምነት ወደመስራቱ እንደገቡ ያስታውሳሉ፡፡
የኢህአፓ መጠንከርና የሥርዓቱ ፈተና መሆኑን ሲያይ ደርግ እየፈለገ መግደልና ማሰር ጀመረ፡፡ እርሳቸውም የዚህ ተቋዳሽ የሆኑት በዚህ ምክንያት ነው። እንደውም አያያዙ እጅግ ይገርማቸው እንደነበርም ያነሳሉ፡፡ እንጀራ ጋግረው ጨርሰው እየታጠቡ እያለ ነው የአቢዮቱ ህግ አስከባሪዎች ሊወስዷቸው የመጡት። ከዚያ በፊት ይህንን ያውቃሉ። ብዙዎችን ወስደው እንደገደሏቸውም ሰምተዋል። ቤተሰቦቻቸውም ቢሆን ራቅ ያለ ቦታ እንውሰድና እንደብቅሽ ብለዋቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በደበቃቸው ቤተሰቦቻቸው ላይ ምን አይነት ዘግናኝ ነገር እንደሚያመጣ ያውቃሉና የሚመጡበትን ቀን እየተጠባበቁ ቆዩ። ሲመጡ እያዩዋቸው እንኳን ለማምለጥ አልፈለጉም፡፡ ምክንያቱም ቤተሰቦቻቸውን ወስደው ከማሰቃየትም በላይ ይገሏቸዋል። እናም በፈቃዳቸው እጃቸውን ሰጥተው ማረሚያ ቤት ገቡ።
ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገቡ ያደረጋቸው ደርግ የኢህአፓ አባል የሆነ ራሱን ያጋልጥ ብሎ በማወጁ ምክንያት ብዙዎች ራሳቸውን ሰጡ፡፡ ወደ ደርግም አስተሳሰብ ተቀላቀሉ፡፡ እንቢኝ ያሉት ደግሞ እየተደበደቡ ጭምር ከእነርሱ ጋር ማን እንደነበር ተናግረው እንዲረሸኑ ሆኑ፡፡ በዚህ ውስጥም ራሱን ያላጋለጠ ብዙ ሰው ተገኘ፡፡ ከእነዚህ መካከልም እርሳቸው አንዱ ሆነው በመገኘታቸው ለእስር ተዳረጉ፡፡
‹‹ፖለቲካ ፍራቻ ሁሉ የሚጠፋበት፣ ላለሙበት ነገር የሚሰዋበትና ግብን ለማሳካት ወደኋላ የማይባልበት የትግል መንገድ ነው፡፡ በዚህም ገና 20 ዓመት ሳይሞላኝ ጀምሮ ምንም ሳደርግ ፈርቼ አላውቅም፡፡ ጥይት ተደቅኖብኝ ማስፈራሪያ ሲደረግብኝም ድንጋጤ በውስጤ የለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ማረሚያ ቤት ወደላይ እግሮቼ ተሰቅለው በተላጠ ኤሌክትሪክ የተገረፍኩት ግርፍ መቼም የማረሳው ሆኖብኝ እንኳን ግቤን አረሳሁም። ምክንያቱም ለአገሬ፣ ለህዝቤ ነጻነት እሞታለሁ የሚል ጽናትን ተላብሼ ድርጅቱን ተቀላቅያለሁና፡፡›› የሚሉት ወይዘሮ ሽታዬ፤ መጀመሪያ ማረሚያቤት ሲገቡ ብቻቸውን እንደታሰሩና ብቻዋን አታድርም ብለው እስከ እኩለ ሌሊትና ሌላ እናት ልጃቸው በመጥፋቱ እርሳቸው እንዲታሰሩ እስከመጡበት ድረስ ከአባታቸው ጋር እንዳደሩ ያስታውሳሉ፡፡
መፈክር እያሰሙ ከፊታቸው ሰው እየተገደለ እያዩ በርቱ እያሉ መጓዝ ምን ያህል ጠንካራ እንደነበሩ የሚያሳያቸው ትዕይንት እንደነበርም ያጫወቱን ባለታሪካችን፤ በአቢዮቱ ጥበቃ ተይዘው ወደ ማረሚያቤት ሲወሰዱ እናታቸው ነብሰጡር ነበሩና በድንጋጤ ደም እየፈሰሳቸው እያዩ እርሳቸው ምንም እንዳልተፈጠረ አድርገው እናታቸውን ማጽናናታቸውን ሲያስቡት የዚያን ጊዜ ትውልድ ጨካኝ፣ ኃይለኛ፣ ለአገሩ ሟችና የራሱን ጥቅም የማያስቀድም እንደነበር ሆኜ አይቸዋለሁና እንኳን ከዚህ ተቋዳሽ ሆንኩ ይላሉ፡፡ በተለይም ማረሚያ ግቢ ሆነው አባታቸው ስለ ትግል የመከሯቸው ጉዳይ መቼም የማይረሱት እንደነበርም ያወሳሉ፡፡ ብዙ ስቃ ሲበረታባቸው ጭምር መቋቋም የቻሉት በዚያ እንደነበርም አጫውተውናል፡፡
ቀዝቃዛ ውሃ በበርሜል ተሞልቶ መከተት፤ ደም እየተፉ በተነከሩበት ቆሻሻ ውሃ ውስጥ ዳግም መግባትና ግርፋቱ እጅግ ዘግናኝ ጊዜያት ከሚታለፍባቸው መንገዶች ጥቂቶቹ ናቸው። ይህንን ስቃይ ላለማየትና ምስጢራቸውን ላለማውጣት ሲሉ ጣና ውስጥ ራሳቸውን በመክተት መስዋዕት የሆኑ ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ጽናታቸው በብዙ መንገድ የታየም እንዲሁ ጥቂት አልነበሩም፡፡ እንግዳችንም በጽናት መታገል ድል ነው ብለው ከሚያስቡት መካከል ነበሩ፡፡ ለመሞት ጭምር ራሳቸውን ከሚያጠነክሩት አንዱ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም በጊዜው በፍርዱ አይተማመኑም። ነገ አውጥቶ እንደሚገላቸው ነው የሚያስቡት፡፡ ስለዚህም ሞት መምጫው ባይታወቅም ተስፋ መኖር አለበት ብለው ያነቡ ነበር፡፡
በህይወታቸው የሚረዳዱበት ጊዜም ሰፊ እንደነበር አይረሱትም፡፡ ይህ ሁኔታቸውም በብዙ ትግል ከዚህ ማረሚያ ቤት መውጣት እንዲችሉ አግዟቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላም ፖለቲካ ለምኔ ብለው ለዓመታት እንደቆዩ ያስታውሳሉ፡፡ ምክንያታቸው አንድና አንድ ነበር፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለን የታገልንለት አላማ ውሸት ነው የሚለውን የሚያረጋግጡ ብዙ ተግባራትን ማየታቸው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ወስነው ትምህርታቸውን ብቻ መማር ላይ እንዳተኮሩም ነግረውናል፡፡
ዳግማዊ ፖለቲካ በኢህአዴግ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ መጀመሪያ ላይ መልካም መስመሮችን የሚይዝ ነው፡፡ ከደርግ ብንነሳ መሬት ላራሹ ጭምር ሰጥቷል፤ በነጻነት የመናገር መብትንም ፈቅዷል፡፡ ግን ጥቅሙና ሀይሉ መነካት ሲጀምር በራስ ወዳድነቱ ምክንያት አሻፈረኝ አለ። ብዙዎችንም በአሰቃቂ ሁኔታ ገደለ፡፡ ስለዚህም እንግዳችንም ይህንን ስለተረዱ ማንኛውም ድርጅት ውስጥ ላለመግባት ወስነው እየተጓዙ ሳለ ነበር አሁን ያሉበትን ምክርቤት የሚቀላቀሉበት መንገድ በአጋጣሚ የተፈጠረው፡፡
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እየተማሩ ሳለነበር ኢህአዴግ አገሪቱን የተቆጣጠረው፡፡ እናም ሲያጠናቅቁ ተፈላጊነታቸው በተለያየ መንገድ ይታይ ጀመር፡፡ ይሁን እንጂ ይበልጥ መፈለጋቸው የታየው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ያበቃቸው በስብሰባ ጊዜ የሚናገሩት ሀሳብ፣ ለስራ ያላቸው ተነሳሽነትና በሥራ ጥራታቸው እምነት የሚጣልባቸው መሆኑ ነው፡፡ በዚህም የድርጅት አባል እንዲሆኑ በብዙ መንገድ ወደመገፋቱ ገቡ፡፡ ሆኖም ብዙ ዓመታትን እንቢ በማለት አሳልፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለት ነገሮች እዚህ ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ አደረጋቸው። የመጀመሪያው የባለቤታቸው ተጽዕኖ ሲሆን፤ ሁለተኛው በመስሪያ ቤታቸው ያለው አወንታዊ ጫና ነው፡፡
ባለቤታቸው አዲስ አበባ በመኖራቸው የተነሳ በእርሳቸው ግፊት ባህርዳር ሄዱ፡፡ ግን መኖሪያቸው አዲስ አበባ ቢሆን ይመርጣሉ፡፡ እናም ለምክርቤት ለመወዳደር እንዳሰቡ ሲነግሯቸው በጣም ተደስተው ይገፏቸው ጀመር፡፡ በተለይ ሰበቡ ልጆቻቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ ከዚህ ትይዩ የሴቶች ጉዳይን ደርበው ይሰሩ ነበርና በስብሰባዎች ሁሉ የሚናገሩት ሀሳብ የሴቶች ጉዳይ ሆኖ በዋናነት የምትሰራውን ሴት እጅግ ይስባታል፡፡ በዚያ ላይ የተማሩ መሆናቸው ደግሞ የበለጠ እንድትገፋቸው አድርጓታል፡፡ ስለዚህም የድርጅት አባል ሳይሆኑ ተወዳድረው በማሸነፍ ምክርቤት እንዲገቡ ሆነዋል፡፡ እንደውም በጊዜው ብቸኛ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሰው እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
መልዕክት
በምክርቤት ቆይታዬ በዋናነት ለህዝቡም ለመንግስትም የማስተላልፈው መልዕክት ህዝብ የምክርቤቱ ችግር ምንድነው የሚለውን መረዳት የሚችልበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ነው፡፡ በተለይም ሁሉም የእኔ ቶሎ ይፈጸም አይነት ምልከታን ቢያቀለው ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ለእያንዳንዱ ስራ ቅደም ተከተል አለው፡፡ ከዚህ ትይዩ የምክርቤቱን ችግር እያየም ዝም ባይል ደስተኛ ነኝ፡፡ ችግራቸውን መናገር በሚችልበት አጋጣሚ ሁሉ መናገር አለበት። ምክንያቱም የተኛው እንዲነቃ ይሆናል። አሰራሮችን እንዲከልስ ያደርገዋል፡፡ ውክልናውን እንዲያስብም በር ይከፍትለታል። ስለዚህም የማንቃቱና የማገናዘቡ ሥራን አብሮ ቢያስኬድ እላለሁ፡፡
እንደ መንግስት ደግሞ ምክርቤት ሁሉን በበላይነት የሚቆጣጠርና ህዝብን ወክሎ አገርን የሚያስቀጥል ተቋም ነው፡፡ ስለዚህም በእኔ ሀሳብ ብቻ ተመሩ የሚለውን አሰራር ቢተው፡፡ ያልሰሩ ተቋማት ሲቀርቡለትም ያልሰራውን አካል እስከመጠየቅ ቢደርስና ለምክርቤቱ ስራ አጋዥ እንጂ ይህንን ተግባሬን በትክክል አስፈጽሙልኝ ብቻ ባይል፡፡ በተለይም መጀመሪያ አካባቢ ባለው ተነሳሽነት ቀጣዮቹንም ዓመታት ቢሰራበት የተሻለ ይሆናል፡፡ ሁሉም በፓርላማ የገባ ድርጅትና የሚመራው መንግስት ሲጀምረው ጥሩ ለውጦች የሚታዩበት ነው፡፡ ነገር ግን ከፍ እያለና ዓመታት ሲነጉዱ የተለየ ተግባርና ተልዕኮን ይላበሳል፡፡ በዚህም አገር ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ እንድታድግ ይሆናል፡፡ ማንም ለውጥ አምጭም አይባልም፡፡
ኢህአዴግ የኔ ሀሳብ ብቻ ይሰማ ባይል ኖሮ ዛሬ አገር ይህንን ያህል ዋጋ አትከፍልም ነበር፡፡ አሁንም አዲሱ የለውጥ ሀይል ማለትም ብልጽግና ከባለፈው ተምሮ ሞጋችና ለአገር የሚመጥን ሥራ መስራት መቻል አለበት። ህግ አውጪ፣ ተርጓሚና አስፈጻሚ አካሉ በነጻነት ሥራዎችን እንዲሰራ መፍቀድና ምቹ ሁኔታን መፍጠርም ይገባዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ለውጡን በቅርቡ የምናየው ይሆናል፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013