ውስብስብ የቢዝነስ ስራዎችን አከናውኗል። የመጀመሪያውን የስራ ዓመታት ያሳለፈው በኔትዎርክ ማርኬቲንግ ቢዝነስ ውስጥ መሆኑ ዛሬ ለሚያከናውናቸው የኤቨንትና ኤግዚቢሽን ዝግጅት ስራዎች ትልቅ መሰረት ጥሎለታል። በ2000 ዓ.ም. ኤክስፖ ቲም ከተባለ የሱዳን ኩባንያ ጋር ያካሄደው የዶሮ እርባታ ኤክስፖ ደግሞ ወደ ኤቨንት ኢንዱስትሪው ለመግባት በር ከፍቶለታል።
የራሱን የኤቨንት አዘጋጅ ኩባንያ አቋቁሞም በርካታና ውጤታማ ኤግዚቢሽኖችን በተለያዩ ዘርፎች አከናውኗል። ይህም በብዙ ዘርፎች ላይ የንግድ ትርኢቶችን በመስራትና በርካታ አለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶችን በማዘጋጀት ኩባንያውን ከኢትዮጵያ ቀዳሚ እንዲሆን አስችሎታል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመውን የኤቨንትና ኤግዚቢሽን ማህበር በምክትል ፕሬዚዳንትነት በመምራትም ኢንዱስትሪው እንዲያድግ የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል- የፕራና ኤቨንትስ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ።
አቶ ነብዩ እድገትና ውልደቱ አዲስ አበባ ላንቻ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቅዱስ ያሬድ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በከፍተኛ ሀያ እና በአብዮት ቅርስ ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በአዲስ አበባ ንግድ ስራ ኮሌጅ ገብቶ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በ1996 ዓ.ም በዲፕሎማ ተመርቋል።
ዲፕሎማውን ካገኘ በኋላ የተወሰኑ ዓመታት በኢትዮጵያ ቀዳሚ በሆነው የኩዌስት ኔት የኔትዎርክ ማርኬቲንግ ቢዝነስ ውስጥ ያሳለፈ ሲሆን በግዜው በስፋት እንቅስቃሴ ሲያደርግ ከነበረ ፍለጋ ከተባለ ቡድን ውስጥ እስከ አመራር ደረጃ ደርሷል። ይህም አሁን ለደረሰበት ደረጃ ጥሩ መሰረት ጥሎለታል።
ይህ የኔትዎርክ ማርኬቲንግ ቢዝነስ በተለያዩ ምክንያቶች መቀዛቀዝ ሲጀምር አፍሪካ ቫኬሽን ክለብ በተሰኘ ኩባንያ ውስጥ በመግባት በሰርቬየርነት ለአራት ወራት ያህል አገልግሏል። በዚህ መስሪያ ቤት በነበረው የአጭር ጊዜ ቆይታው ትልቅ ልምድ አግኝቷል።
በንግድ ስራ ኮሌጅ አብራው ስትማር የነበረች የትምህርት ቤት ጓደኛው በኤግዚቢሽን ማእከል ማርኬቲንግ ክፍል ውስጥ ተቀጥራ በምትሰራበት ወቅት ኤግዚቢሽኖች ሲኖር መጥቶ እንዲያይ ተጋብዘው ነበር። እርሱም በተከታታይ መጥቶ ከማየት አልቦዘነም። ይህም በኤግዚቢሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ገብቶ እንዲሰራ ምክንያት ሆነው ።
በ2000 ዓ.ም ኤክስፖ ቲም የተባለ የሱዳን ኩባንያ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ የዶሮ እርባታ ኤግዚቢሽን ለማሳየት አብሮት የሚሰራ ሰው ሲፈልግ በኤግዚቢሽን ማእከል ተቀጥራ የምትሰራው ጓደኛው አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ደውላ ጠየቀችው። እርሱም ስራውን ለመስራት አላቅማማም። የመጀመሪያውን የዶሮ እርባታ ኤክስፖም ከኩባንያው ጋር በማዘጋጀት በኤቨንት ኢንዱስትሪው ውስጥ ለመግባት በር ተከፈተለት። በተመሳሳይ ዓመትም በዚህችው ጓደኛው አማካይነት በተገኘው ዕድል ከሶስት የቀድሞው የኩዌስት ኔት ማርኬት ቢዝነስ አጋሮቹ ጋር በመሆን የመጀመሪያው የኦል አፍሪካ ሌዘር ፌር ሲዘጋጅ በሽያጭ ስራው ላይ ተሳተፈ። ከዚያም በአንዱ ጓደኛው ቤት በ200 ብር የንግድ ፍቃድ አውጥተው በጋራ መንቀሳቀሳቸውን ቀጠሉ።
ከዶሮ እርባታ ኤክስፖው ጎን ለጎን ከሱዳኑ ኤክስፖ ቲም እና ከአጋር ጓደኞቹ ጋር በመሆን በ2002 ዓ.ም የፕሪንቲንግና ፓኬጂንግ ኤግዚቢሽን አካሄደ። እነዚህን ኤግዚቢሽኖች በሚሰራበት ወቅትም ዘርፍ ተኮር የሆኑ ኤግዚቢሽኖች እና ንግድ ትርዒቶች ዝግጅት ምን ያህል ለሀገር ጠቃሚ እንደሆነና ለኢኮኖሚው ትልቅ አስተዋፅኦ ሊያደርግ እንደሚችል በሚገባ ተረዳ።
በ2002 ዓ.ም. በጓደኛቸው ስም የነበረውን የንግድ ፈቃድ በመመለስ ‹‹ፕራና ኢምፖርት ኤክስፖርት ኃ/የተ/የግ/ማ የተባለ ድርጅት አቋቁመው በአቶ ነብዩ ስራ አስኪያጅነት በኤግዚቢሽን እና የማስታወቂያ፣ የማነቃቂያ ስልጠና እና ንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው እንቅስቃሴያቸውን ቀጠሉ። የኤግዚቢሽን ስራውንም “ፕራና ፕሮሞሽን” በሚል የንግድ ስያሜ ኤግዚቢሽን ማዕከል ስትሰራ የነበረችውን ጓደኛውን በአጋርነት በማስገባት እና ሁለት ሰራተኞችን በመቅጠር የቢዝነሱን እንቅስቃሴ አንድ እርምጃ ወደፊት ማራመድ ቻለ። ከአንድ አመት ተኩል ጥረት እና ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በተገኘ ፍቃድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን “ኢትዮ ኸልዝ” የተሰኘ የጤና እና የሜዲካል ኤግዚቢሽን በ2002 ዓ.ም አካሄደ። ይህም ፕራና ፕሮሞሽን ለብቻው ያከናወነው የመጀመሪያው ኤግዚቢሽን ለመሆን በቃ። በጊዜው ኤግዚቢሽኑ ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱም ከኤግዚብሽን ማእከል “በመጀመሪያው ዓመት ውጤታማ የሆነ ኤግዚቢሽን” በሚል ሽልማት አገኘ።
የኤግዚብሽን ስራዎችን በየአመቱ በማከናወን በ2003 ዓ.ም. ደግሞ ከሌላ የሱዳን ኩባንያ ጋር በመሆን የኬሚካልና የፕላስቲክ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገና ‹‹አፍሪ ኬሜክስ›› የተሰኘ ኤግዚቢሽን አከናወነ። በቀጣይ ዓመትም “ኢትዮ ቢውቲ እና የፋሽን ኤክስፖ” ጨመረ። ከህንድ እና ኬንያ ኩባንያዎች ጋር በመተባበርም ሁለት የህንድ የትምህርት ኤክስፖዎችን አዘጋጀ። በ2006 ዓ.ም የዶሮ እርባታ ላይ ብቻ አተኩሮ ሲሰራ ከነበረው የኢትዮ ፖልተሪ ኤክስፖ ጎን ለጎን የስጋ እና የወተት ዘርፉን ለማስተዋወቅ የአፍሪካ ላይቭ ስቶክ ዓውደ ርዕይን እና ጉባዔን ጀመረ። ከዚህም በኋላ ቢዝነሱን በእውቀት ለመደገፍ የኢኮኖሚክስ ትምህርቱን በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተከታትሎ በ2008 በዲግሪ ተመረቀ። ለሶስት ዓመታት እየሰራባቸው ያሉትን የኤግዚቢሽን ፕሮጀክቶች ለማሳደግ ጥረት ካደረገ በኋላ በ2009 ዓ.ም. በዘርፉ ትልቅ ልምድ ካለው ፌር ትሬድ ከተባለ የጀርመን ኩባንያ ጋር በመሆን በግብርና እና የምግብ ሰንሰለት ላይ ትኩረት ያደረገ “አግሮ ፉድ ፕላስት ፓክ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ጀመረ። በተመሳሳይ ዓመትም መሰረቱን ዱባይ ካደረገ ኤም አይ ኢ ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር በመተባበር ‹‹ቻይና ትሬድ ዊክ›› የሚል ጥራት ባላቸው የቻይና ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ትልቅ የንግድ ትርኢት አከናወነ። በመቀጠልም 8ኛውን የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ የጋስትሮኢንትሮሎጂ ኮንግረስን ለማዘጋጀት በቃ።
በዚሁ ዓመት ከስራ መስፋት እና ከፍላጎት መለያየት ጋር ተያይዞ ድርጅቱ ለሶስት መከፈል ግድ ሆነ። ሁለቱ አጋሮቹ የስልጠናውን ክንፍ ይዘው ሲወጡ ሁለቱ ደግሞ የንግዱን ክንፍ እና የማስታወቂያ ስራውን የግል ድርጅቶቻቸውን አቋቁመው መስራት ቀጠሉ። አቶ ነብዩም ፈታኙን የኤግዚቢሽን እና የኢቨንት ስራውን “ፕራና ኢቨንትስ” በሚል የንግድ ስም ለብቻው ተጋፈጠ።
እስካሁን ሲሰራባቸው ከቆዩት ዘርፎች ባሻገር በ2011 ዓ.ም. ሻክረክስ ከሚባል የሀገር ውስጥ የንግድ ትሪኢት አዘጋጅ ጋር በመሆን “ፊንቴክስ” የተባለ በፈርኒቸር ኢንቴሪየርና ፊኒሺንግ ማቴሪያል ላይ ያተኮረ ኤክስፖ አካሄደ። በአጠቃላይ ከአስራ አምስት በላይ በሚሆኑ ዘርፎች ላይ 40 አለም አቀፍ የንግድ ትሪኢቶችን አዘጋጅቷል። በዚህም በብዙ ዘርፎች ላይ የንግድ ትርኢቶችን በመስራት እንዲሁም በርካታ አለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶችን በማዘጋጀትም ታዋቂ መሆን ችሏል።
አቶ ነብዩ በተማረው የኢኮኖሚክስ ትምህርቱ ሳይገታ ባለፈው ዓመት ደግሞ ከአለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ኢንዱስትሪ አሶሴሽን በኤግዚቢሽን ማኔጅመንት ሌላ ዲግሪ አግኝቷል። በዚህ የትምህርት መስክ የተማረ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነው ።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ኢንዱስትሪውን ክፉኛ በጎዳበት ወቅትም 12 ሰራተኞችን የቀጠረ ሲሆን ዛሬ ላይ ካፒታሉ በሚሊዮን የሚቀጠር መሆኑን ይናገራል። ስራውንም በሶስት የቢዝነስ ክፍሎች አሳድጓል አንደኛው ከአጋሮች ጋር ወይም በራስ የሚሰሩ የኤግዚቢሽን ፕሮጀክቶችን ይሰራል። ሁለተኛው የቢዝነስ ክፍል ደግሞ የኮርፖሬት ኤቨንቶችን የሚያዘጋጅ ሲሆን ሶስተኛው የቢዝነስ ዩኒት የኤቨንት ቴክኖሎጂ እና ዕቃዎች አቅርቦት እና ኪራይ ስራዎች ናቸው ።
በቀጣይም ኩባንያው በአፍሪካ ካሉ ተመራጭና ቀዳሚ የኤቨንት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የመሆን እቅድ እንዳለው አቶ ነብዩ ይጠቁማል። ኩባንያው በዚሁ የእቅዱ መንገድ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ታዲያ ብዙ መሰራትና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንደሚቀሩ ይጠቅሳል። ለዚህም ኩባንያው ለብቻው መሮጥ ሳይሆን የኤቨንት ኢንዱስትሪው መቀየርና መሻሻል እንዳለበትና ከዚህም ጋር በተያያዘ በሀገር ውስጥ ከኢንዲስትሪው ጋር በተገናኘ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ይገልፃል። ከዘርፉ ቁልፍ አዘጋጆች ጋር በመሆንም የኤቨንትና የኤግዚቢሽን ማህበር አቋቁሞ የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በዚሁ ማህበር በኩልም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ይጠቅሳል።
‹‹ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የኤቨንት ኢንዱስትሪው ስለሚያመጣው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ግንዛቤ ደካማ ነው›› የሚለው አቶ ነብዩ፤ በማህበሩ በኩል ግንዛቤ የመቀየር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ያብራራል። ከዚህም ባለፈ የማይስ (MICE) ኢንዱስትሪው ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ እና ለኢንዱስትሪው በቱሪዝም ኢትዮጵያ ስር የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ እንዲቋቋም መደረጉንም ይገልፃል። የቢሮው ዋነኛ አላማም የማይስ ኢንዱስትሪውን በመደገፍና ማሳደግ እንዲሁም አለም አቀፍ ኹነቶችን ተወዳድሮና ተጫርቶ ማምጣት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ መዳረሻ ማድረግ በመሆኑ ማህበሩ ከኮንቬንስን ቢሮው ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ ቀጣይ ስራዎችን ለመስራት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ይጠቁማል። ለአብነትም ማህበሩ የማይስ ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ላይ ምን አይነት ተፅእኖ እንደሚያሳድር የኢኮኖሚ ተፅእኖ ጥናት እየሰራ እንደሚገኝ ይጠቅሳል።
ኢንዱስትሪው የራሱ ፖሊሲ፣ እንዲኖረው በጥናት የተደገፈ መረጃ ለመንግስት ለማቅረብ ማህበሩ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሶ፤ ከዚህ በዘለለ አዳዲስ የስብሰባ እና የኤግዚቢሽን አዳራሾች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲገነቡ እና ፕሮፌሽናል የኢቨንት እና የኤግዚቢሽን አዘጋጆች ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ይጠቁማል።
‹‹ በዚህ የኤቨንትና ኤግዚቢሽን ቢዝነስ ውጤታማ ነኝ›› የሚለው አቶ ነብዩ፤ ለዚህ ውጤት ማሳያው በግሉም ሆነ ከጓደኞቹ ጋር ሰርቶ ያመጣው ውጤት መሆኑን ይናገራል። ስራው ከባድ ከመሆኑ አኳያ ብዛት ያላቸው ኤግዚቢሽኖችን ማካሄድ በራሱ ለዚህ ውጤት ሌላኛው ማሳያ መሆኑንም ይገልፃል። ኩባንያው ወደ አስራ አምስት በሚሆኑ ሴክተሮች ላይ የሚሰራ ከመሆኑ አኳያም የውጤቱ ማረጋገጫ መሆኑንም ይመሰክራል። በቀጣይም በዚሁ ውጤታማነት እንደሚቀጥልና በተለያዩ ዘርፎች በአመት እስከ 24 የሚሆኑ አለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖችንና የንግድ ትርኢቶችን የማዘጋጀት ውጥን እንዳለውም ተናግሯል። እስካሁን ድረስ ኩባንያው በርካታ ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት ቀዳሚ መሆኑንም ይገልፃል።
የውጪ ሀገራት የኤግዚቢሽን አቅራቢዎችን በማሳተፍም ኩባንያው ከፊት ተርታ ካሉት ውስጥ መሆኑንም ይጠቅሳል። በዚህም በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ በንግድ ትስስር፤ በቴክኖሎጂ እና እውቀት ሽግግር እንዲሁም በኢንቨስትመንት መሳብ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አድርጓል።
በዚህ ፈታኝና ውስብስብ የኤቨንትና ኤግዚቢሽን ቢዝነስ ውስጥ አስራ አራት አመታትን የቆየው አቶ ነብዩ በተመሳሳይ በዚሁ የቢዝነስ መስክ ውስጥ ገብተው መስራት ለሚፈልጉ ሁሉ በቅድሚያ መጀመሪያ ስራውን ማወቅና ከታች ተነስተው በብርታት ወደ ከፍታው መጓዝ እንዳለባቸው ይመክራል። ስራው በቀላሉ ገንዘብ የሚታፈስበት አለመሆኑና ገንዘብ ወደማግኘት ለመሸጋገርም ትግል የሚጠይቅ በመሆኑ የግል ጥረትና የገንዘብ አቅም እንደሚፈልግም ይገልፃል። ከዚህ አኳያ ወደዚህ ቢዝነስ የሚገቡ ሰዎች እውቀታቸውን፣ ልምዳቸውንና ገንዘባቸውን አጣምረው መስራት እንዳለባቸው ይመክራል። ቢዝነሱ ለራስ ብቻ የሚኖርበት ሳይሆን ለብዙኃኑም ጭምር ጥቅም የሚሰጥ በመሆኑ በዚህ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸውም መልእክቱን ያስተላልፋል። ቢዝነሱ ለግል ጥቅም ብቻም ሳይሆን ሀገርን፣ የሀገር ምርቶችን በማስተዋወቅና ቱሪስቱን በመሳብ የጎላ ሚና አለው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013