በኢትዮጵያ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በሰላም ተጠናቅቋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በሰኔ 14 ምርጫ ማካሄድ ባልተቻለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም ምርጫ
ይካሄዳል፡፡ በምርጫው አሸናፊ የሆነው ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች አሸናፊነቱ/አሸናፊነታቸው እንደተረጋገጠ መንግሥት የሚመሰርት/የሚመሰርቱ ይሆናል፡፡ አዲስ ከሚመሰረተው መንግሥት ሕዝቡ አፋጣኝ መፍትሄ ከሚሻባቸው ጉዳዮች አንዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የኑሮ ውድነት ማስታገስ ነው፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ያለውን የኑሮ ውድነትን አደብ ለማስገዛት አዲሱ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሲከተል ከነበረው አካሄድ የተለየ አካሄድ መምረጥ እንዳለበት የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በተለይም ሕግን በማስከበር ረገድ የሚስተዋልበትን ክፍተቶች ማስተካከል ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት መምህር ዶክተር ሞላ አለማየሁ እንደሚሉት፤ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ብዙ የቤት ሥራዎች አሉበት። ከእነዚህ የቤት ሥራዎች አንዱ የዜጎች ዋነኛው ራስ ምታት እየሆነ ያለውን የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ላለው የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ መንግሥት ሕግ ማስከበር አለመቻሉ ነው፡፡ መንግሥት ሕግ ማስከበር ባለመቻሉ ነጋዴዎች ከሕግ ውጪ ሲንቀሳቀሱ መመልከት የተለመደ
ሆኗል፡፡ አሁን አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ግን ሕግን ከማስከበር ጀምሮ ያሉትን ሥራዎች ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት አለበት።
ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ ሲያወጡ፤ ከሚሸጡት ዕቃ የተወሰነ ፐርሰንት ለማትረፍ ነው፡፡ 10 ወይም 15 በመቶ ትርፍ ለማግኘት ውል ገብተው ነው ወደ ሥራ የሚገቡት ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ነጋዴዎች ይህን ሕግ አክብረው የመንቀሳቀስ ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብዛኞቹ ነጋዴዎች የገቡትን ውል መሠረት አድርገው አይደለም የሚንቀሳቀሱት፡፡ ነጋዴዎች በዚህ ሕግ እየተመሩ አይደለም፡፡ የገበያ ሥርዓቱ መርህ አልባ ሆኗል፡፡ ነጋዴዎች ገበያውን እንደፈለጉ ለማሽከርከር ሲሞክሩ ይታያል፡፡ ያለ ምንም ተጨባጭ ምክንያት ከመሬት ተነስተው ምርትና ሸቀጥ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ የማድረግ ሁኔታ ይታያል፡፡
አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሰሞኑን ምርጫ እንደ ምክንያት አድርገው ሸቀጥ እና ምርት ብዙ ጭማሪዎችን ያደረጉ ነጋዴዎችን መመልከታቸውን የሚያነሱት ዶክተር አለማየሁ፡፡ ምርጫን ግን ከሸቀጥ ዋጋ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ይላሉ፡፡ እንዲህ በየሰበብ አስባቡ ዋጋን የሚያንሩ እና ግዴታን የማይወጡ ነጋዴዎች ሕግን ተከትለው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግና ሥርዓት ማስያዝ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ነጋዴ እስከሆነ ድረስ በእጁ የያዘውን ምርትና ሸቀጥ የመሸጥ ግዴታ ያለበት ቢሆንም አንዳንድ ነጋዴዎች የያዙትን ሸቀጥ የመደበቅ፤ አንዳንዶች ደግሞ ደስ ሲላቸው ማውጣት፤ ደስ ሳይላቸው ሲቀር ደግሞ መሸሸግ በአደባባይ የሚታዩ ችግሮች
ናቸው፡፡ የትኛውም ነጋዴ ከፈለገ የመሸጥ ካልፈለገ የመደበቀ መብት የለውም፡፡ በሕጉ መሠረት እንደዚያ ማድረግ አይችሉም፡፡ በንግድ ዘርፍ የተሰማሩት ለመነገድ ነውና፡፡ ስለዚህ ሕጉን ማስከበር ከመንግሥት ይጠበቃል።
የኑሮ ውድነት የኅብረተሰቡ አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የዋጋ ንረት ማረጋጋት ሕገወጥ ንግድን ማስቆም፣ ሰላም ማስከበር ቁልፍ ጉዳይ አድርጎ ሊይዘው ይገባል። ለዚህም የሕግ የበላይነትን ማስከበር ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት አለበት ይላሉ፡፡ የንግድ ሕግ እየተከበረ እንደሆነ ማረጋገጥ የግድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በመሆኑም የሕግ የበላይነትን ማስከበር እና ዜጎች የሕግ የበላይነትን አክብረው እንዲቀሳቀሱ ማድረግ፣ አክብረው የማይገኙትን ደግሞ በሕጉ መሠረት ተጠያቂ ማድረግ አስፈላጊ እና ሕዝቡ ከመንግሥት የሚጠብቀው ነው፡፡
ከዚያ ባሻገር የንግድ ሕጉ ላይ ክፍተቶች ካሉ ክፍተቶችን በመለየት ነጋዴውን እና ሸማቹን በሚጠቅም መልኩ ማሻሻያዎች እንዲካሄዱ ማድረግ ሌላኛው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ዶክተር ሞላ አለማየሁ ይገልጻሉ፡፡
በአገሪቱ የንግድ ዘርፍ የሚስተዋሉ የሕግ ጥሰቶችን አደብ የማስገዛት እና የንግድ ሕጉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ካሉ የማሻሻያ ሥራዎች ከተሰሩ በኋላ በዘርፉ ከሚስተዋለው ሕገ ወጥነት ባሻገር የኑሮ ውድነት መንስኤ የሚሆኑ ሌሎች ችግሮችን በጥናት መለየት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ከዚህ ቀደም ነጋዴዎችን አደብ ለማስገዛት በምርጫ ሊቀጡኝ ይችላል በሚል ስጋት መስራት ያለበትን ሥራ ሳይሰራ ትቶ ከሆነ ስህተት ነው የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ የአሁኑ ምርጫ ግን መንግሥት ነጋዴው በካርድ ሊቀጣኝ ይችላል ብሎ እንዳይሰጋ ስለሚያደርገው መስራት ያለበትን ሥራ በድፍረት እንዲሰራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሕዝብ አመጽ የተወገደው የቀድሞ ገዥ ፓርቲ ያስቀመጠው እንጂ በሕዝብ ድምጽ የተመረጠ እንዳልነበር የሚያነሱት ዶክተር ሞላ፤ በሕዝብ አለመመረጡ በራሱ መንግሥት የፈለገውን እርምጃ እንዳይወስድ አንዱ እንቅፋት ሊሆንበት እንደሚችል አብራርተዋል፡፡ አሁን በሕዝብ ይሁንታ የተሰጠው መንግሥት ግን ሕጋዊነቱ የበለጠ ስለሚጠናከር ጉልበት እንደሚሰጠው ጠቁመው፤ እርምጃዎችንም ለመውሰድ እንደማይቸገር ተናግረዋል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013