መልካምስራ አፈወርቅ
የጠጅ ቤቱ ደጃፍና አካባቢው በሰዎች ትርምስ ታጀቧል፡፡ አብዛኞቹ እንዲያውም ሁሉም የሚባሉት የቤተ ታዳሚዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል በርካቶቹ በስካርና በሞቅታ ናውዘዋል፡፡ የዕለቱም ጫጫታ እንደተለመደው ነው፡፡ በቤቱ በራፍና በውስጥ በኩል የተደረደሩት አግዳሚዎች ብርሌዎችን በላያቸው አሰልፈው ደንበኞችን ያስተናግዳሉ፡፡
እዚህ ስፍራ የኮሮና ጉዳይ ተሰምቶ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ እንዳንዶቹ እንደነገሩ ከአገጫቸው ስር ያዋሉት የአፍ መሸፈኛ በጠጅ ጠብታ ሲዋዛ መክረሙን ያሳብቃል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከአፍ መሸፈኛቸው ጋር ተያይተው የሚያውቁ አይመስልም፡፡ በእጃቸውም ሆነ በአፋቸው ላይ ማስክ ይሉት ነገር አይታይም፡፡
ከወዲያወዲህ እየተራወጠ የጎደሉ ብርሌዎችን የሚሞላው አሳላፊ በእጁ አጥብቆ ከያዘው የጠጅ ማንቆርቆሪያ ውጪ ሌላ ጉዳይ ያለው አይመስልም፡፡ ዓይኖቹን ከወዲያወዲህ እያንቀዠቀዠ ወጪና ገቢውን ይቆጣጠራል፡፡ የጠጅ ቤቱ ሁካታና የታዳሚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ዛሬም ሁኔታዎች እንደቀድሞው እንደትናንትናው ቀጥለዋል፡፡
አስገራሚው ጉዳይ እንዲህ መሆኑ አይደለም። እኔን በእጅጉ ያስደነቀኝ እውነት ከጠጅ ቤቱ መግቢያ ላይ በጉልህ የተለጠፈው ማስታወቂያ ሆኗል፡፡ ይህ የማስታወቂያ መልዕክት ተደራሽነቱ ለጠጅ ቤቱ ደንበኞች መሆኑ ነው፡፡ ማስታወቄያው የዘመኑን የኮሮና በሽታ አስመልቶ ለደንበኞች የሚሆን መልዕክት የያዘ ነው፡፡
ለደበኞች ማስገንዘቢያ ይሆን ዘንድ ጀባ የተባለ የእንግሊዝኛ ፅሑፍ እንዲህ ይነበባል፡፡ NO MASK NO SERVICE ድንቄም ማስታወቂያ ድንቄም መልዕክትና ማስጠንቀቂያ ጉድ እኮ ነው፡፡ እናንተዬ ማስታወቂያው የተለጠፈው ለጠጅ ቤቱ የዘወትር ደንበኞች መሆኑ እኮ ነው የሚገርመው፡፡ NO MASK NO SERVICE ለነገሩ ስምና ግብራችን አልመሳሳል ብሎን መንገዳገድ ከጀመርን ቆይተናል፡፡
እውነት እኮ ነው፡፡ ስንቶቻችን ነን የማንተገብረውን ህግ ቀርጸን የማንሞክረውን መንገድ ጀምረን የምንንገታገት ፣ አረ ምን ያህሎቻችን እንሆን ለእኛም ሆነ ለሌሎቻችን በማናውቀው ቋንቋ ተፋጠን መፍትሔ አልባትነን የምናስተናገድ፡፡
አንዳንዴ ግርም የሚሉ ጉዳዮች ይስተዋላሉ። በአንዳንድ መንግሥታዊ ተቋማት ጎራ በተባለ ጊዜ የሚያጋጥሙ የስርዓት አልባ መስተግዶዎች ለዚህ አባባል ማሳያ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ተቋማቱ ከተሸከሙት ኃላፊነትና ከተሰጣቸው ጉልህ ስያሜ አኳያ ባለጉዳዮችን ገና ከበር የሚቀበሉ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ድንቄም መቀበል አምረው በተገነቡ ሕንፃዎች ውስጥ የተኮፈሱ ኃላፊ ነን ባዮች አማካኝነት የሚወጡና የማይተገበሩ ደንብና መመሪያዎች አንጀት ያሳርራሉ ፤የደም ዕንባ ያስነባሉ፡፡
አይበለውና ወደ እነዚህ ተቋማት ጉዳይ ብጤ ኖሮ ጎራ ከተባለ ዓይን ብዙ ያያል፡፡ ለደንቡ ያህል በጉልህ የቀለማት ጹሑፍ አድምቀው የለጠፉት ትርጉም አልባ ማስታወቂያ የሥራ ቅልጥፍናቸውን፣ የደንበኞች መልካም መስተንግዶንና የጉዳዮች መከወኛ ቆይታን እንግለጽ ባይ ናቸው፡፡ “ ድንቄም“ አሉ እማማ ተዋቡ፡፡
ድርጊታቸው ሁሉ ልክ እንደ ጠጅ ቤቱ የእንግሊዝኛ ጽሑፍ የማስክ አድርጉ ማስታወቂያ ግራ የገባው መድረሻና ተግባር አልባ ነው፡፡ በማስታወቂያው በ30 ደቂቃ ያልቃል የተባለ ጉዳይ በተግባር ሦስት ቀን ይፈጃል፡፡
ቀረበ ብሎ ግልጋሎትን ለሚሻ ባለጉዳይ የማሞና የመታወቂያውን መለያየት በግልጽ ያስመሰክራል። እንግዲህ እኛ እንዲህ ነን፡፡ ስምና ግብራችንን ሲለያይ ዕቅድና ግባችን ሲተላለፍ አንዳች አይሰማንም። እንዲያውም አንዳንዳችን እግራቸው እስኪቀጥን የሚመላለሱ ባለጉዳዮች ጉዳይ የተከታታይ ፊልም ያህል ያዝናናል፡፡
ዕንባቸው ፣ ለቅሷቸው፣ ትካዜና ቁዘማቸው ያረካናል፡፤ ሠው መረዳትና ማገዝ ይሉት ብሂል የጎጂ ባህል ያክል ነውር ጉዳይ ይመስለናል፡፡ ሁሌም በአልተገናኝቶ ጉዟችን የተሰጠንን ስልጣንና ወንበር ተመክተን ሌሎችን ስንጎዳ በርካቶችን ስናሳዝን እንውላለን፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ግብራችን ብዙ ከሚባልለት ማንነታችን ጋር ባለመግጠሙ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ብሩህ በሆነ ፈገግታቸው እያዋዙ በርካቶችን ያዘናጋሉ፡፡
ውጫዊ ገጽታቸውን ያስተዋሉ፡፡ ምስኪኖች ደግሞ የውስጡ እንደውጭ ቢመስላቸው ማንነታቸውን በአውንታ አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ ቆይታ ግን ምስጢርና እውነታው ሌላ ሆኖ ይገኝና የነበረውን እንዳልነበረ መሆኑ ይረጋገጣል ምን ዋጋ አለው፡፡ ጉዳይ ሁሉ ጅብ ከሄደ ውሻ —-እንዲሉ ሆኖ የተጎጂዎች ሚዛን አጋድሎ ይገኛል። በአንጻሩም የክፉ አሳቢዎች ፀሐይ ደምቃ ትታያለች፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ የስምና ግብር አለመናበብና አለመመሳሰል እውነት ነው፡፡ ድንቄም መመሳሰል አሉ እማማ ተዋቡ፡፡
የነፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ጉዳይ ብዙ ነው፡፡ ልክ ሽፋኑ እንደሚያምር መልከኛ መጽሐፍ ላያቸውን አስውበው ‹‹ቢከፍቱት ተልባ›› ይሏቸው ዓይነት አይታጡም፡፡ በእናውቅልሀለን ስሜት በአፈቀላጤነታቸው የሚታወቁ አንዳንድ ሹሞች ለእዚህ ዓይነቱ እውነታ ማሳያዎች ናቸው፡፡
እንዲህ ዓይነቶቹ በአጋጣሚ በሚያገኙት ስልጣንና ኃላፊነት ከህብረተሰቡ የሚወዳጁበት አጋጣሚን አያጡም፡፡ ታዲያ እነአጅሬ በሚያገኙት መድረክ ሁሉ የሚናገሩት ርዕሰ ጉዳይ አይጠፋቸውም፡፡ እናወያይህ ያሉት ሕብረተሰብ አለብኝ የሚላቸውን ችግሮች በሙሉ በአትኩሮት ለማዳመጥ የሚያህላቸው የለም፡፡ እነዚህ አካላት ከብሶተኛው ነዋሪ የሚሰነዘሩ አስተያየቶችን የሚቀበሉትም ያለአንዳች መሰልቸት ሲሆን፤ ነገሩ እንደገባቸው ሁሉ ደግመው ደጋግመው ራሳቸውን ይወዘውዛሉ፡፡ ይነቀንቃሉ፡፡
ወዳጆቼ! ሰዓታትን ከፈጀ ውይይትና ቃለ ምልልስ በኋላ ሹመኞቹ ነዋሪውን ተሰናብተው መንደሩን ሲለቁ የሚገቡት የቃልኪዳን ብዛት በአህያ ቢጫን የሚቻል አይመስልም፡፡ ደግመው ደጋግመው እንስፈጽማለን፣መፍትሔ እንሰጣለን የሚለው ቃላቸው ዕውን ሲሆን ውሎ የሚያድር አይመስልም፡፡
ቆየት ብሎ ግን ብዙ ቃል የተገባለት ህብረተሰብ የሹመኞቹን ወርቃማ ቃላት እያስታወሰ ቀናትን በጉጉት ይጠብቃል፡፡ ውጥን እያሰፈረ ደጅ ደጁን ይቃኛል፡፡ ቀናቶች ያልፋሉ፡፡ ሳምንታት ተቆጥረው ወራት ይተካሉ። ሹመኞችም ሆነ ቃል የተገባው የልማት ጉዳይ ግን የውሃ ሽታ ይሆናል፡፡
ከጊዜያት በኋላ እነዚሁ ብዙ ባዮች ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውንና በእነሱ ቦታ ሌሎች መተካታቸውን ይሰማሉ፡፡ እነዚህኞቹም በተራቸው ቀን ጠብቀው ጊዜና ቀጠሮ አስይዘው በወንበሩ ይዘልቃሉ፡፡ የተለመደውን አጀንዳ ያነሳሉ፡፡ ህብረተሰቡ ብሶቱን፣ ሹመኞቹ ቃላቸውን ያሳፍራሉ፡፡ ውይይቱ ይቀጥላል፡፡ የአምናው ካችአምናው ተለምዷዊ ጉዳይ እየተነሳ ችግር ይደ ረደራል፡፡
ተረኞቹ ሽመኞች ብዕራቸውን ከወረቀት አዋደው ቃላትን ይከትባሉ፡፡ የተለመደውን የቃል ኪዳን ሰነድ ይዘረጋሉ፡፡ ነዋሪው ዳግመኛ ችግሩን እንደሚፈቱለት እያሰበ ተስፋ ያደርጋል፡፡ አፈጮማዎቹ- ሹመኞች አሁንም እንፈታልሃለን ያሉትን ችግር ሳይፈቱ ወንበሩን ተሰናብተው ይሄዳሉ፡፡ እነሱም አይመለሱም የተባለውም አይፈጸምም፡፡
አሁንም ልብ በሉልኝ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ከራስ መውደድ በመነጨ አጉል ስሜት መነሻ ነው። ስምና ግብር አልሰምር በሚል ጊዜ አገልጋይ ነን ባዮች ትርጓሜያቸው ይለያል፡፡ ይባሱኑ በህዝቡ ተጋልጋይና ተጠቃሚዎች ይሆኑና ፍትሕ ይጓደላል፡፡ በስመ- ስልጣን መዋቅርም በህብረተሰቡ ትከሻ መሰላል ይፈጠራል፡፡ ይህ መሰላልም ለህሊና ቢሶቹ አገልጋይ ነን ባዮች የጥቅም መወጣጫና መውረጃ ይሆንና ነገር ሁሉ ይበላሻል፡፡
ሌላ ምሳሌ ላክል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የከተማችን አካባቢዎች ዓይን ያወጣ ዝርፊያ መካሄዱ እንደቀጠለ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ በጠራራ ፀሐይ ንጥቂያ ሊፈጸም፣ የረቀቀ ዝርፊያም ሊኖር ይችላል፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ በደል የተፈጸመበት ወንጀለኛውን ከመከተል ይልቅ በዓይኖቹ የፖሊስ አባላትን ሊፈልግ፣ ስለችግሩም መፍትሔና መላሽ ግድ ይለው ይሆናል፡፡ አንዳንዴ ግን ነገሮች ባልታሰበ መንገድ ሊጓዙ ይችላሉ። መፍትሔን እሻለሁ፣ የበደለኝንም አስይዛለሁ የሚለው ተበዳይ ሌላ በደል ያገኘዋል፡፡
አንዳንድ ፖሊሶች የተዘረፈውን ግለሰብ ቃል እንደነገሩ ከመስማት ባለፈ፣ መፍትሔ ሊጠቁሙ ቀርቶ የረባ አስተያየት አይሰጡም፡፡ እንደማንኛውም የመንገድ ላይ ተመልካች መሆንን ልምድ አድርገዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ፖሊሶች የተለየ ቁምነገር አይፈይዱም፡፡ በተለምዷዊ አገላለጻቸው ‹‹ይህ የእኛ ቀጠና አይደለም። ምንም ማድረግ አንችልም›› ብለው ያልፋሉ፡፡ በእርግጥ እንዳሉት ሆኖ ወንጀሉ የተፈጸመበት ቦታ ቀጠናቸው ላይሆን ይችላል፡፡ ጉዳዩ ግን ከማንኛውም ተመልካች በላይ ለእነሱ የቀረበና መፍትሔን የሚሻ ነው፡፡ የፖሊስ አባላቱ በቀጥታ ቃል ተቀብለው ተጠርጣሪዎችን ባያፈላልጉም መሆን ስለሚገባው ሂደት አቅጣጫ ቢያሳዩ መልካምና ድንቅ ተግባር በሆነ ነበር፡፡
ወዳጆቼ ! ይህ እንዳይሆን ግን አስቀድሜ እንዳልኩት የስምና ግብር መለያየት ጉዳይ ያግደዋል። አንድ ሰው ሙያውን አምኖበት ከተቀበለውና ‹‹ይሁነኝ›› ብሎ ከያዘው መስመሩ በሚፈቅድለት አግባብ የማይፈፅመው ውዴታና ግዴታ አይኖርም። ሆኖም በልክ ካልተሰፋለት ፍላጎትና ስሜት ውጪ ሆኖ የሚከውነው ተግባር ምሬትና ጥላቻን ከማትረፍ የዘለለ የሚፈይደለት ቁምነገር የለም፡፡
እንዲህ ዓይነቱ የላሸቀ፣ የደቀቀ ሞራል በኖረ ጊዜ ደግሞ ሙያና ሙያተኛው አብዘተው ይቃረናሉ፡፡ ዓላማና ግብ ይሏቸው እውነታዎችም በእጅጉ አይዋሃዱም፡፡ ይሄኔ ወገን ይበደላል፡፡ የሙያ አደራ በሊታዎቹ ሲበራክቱም ተሰፋና ፍላጎት ይቀጭጫሉ፡፡ ህዝብም መሬቱ እየከፋ ይሄዳል፡፡
አሁን የምርጫ ዘመን ላይ ነን፡፡ በቅርቡ 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ተፍ ተፍ ማለት ጀምረናል። ምርጫና ተመራጮች መነሳት ሲጀምሩ ደግሞ አይሰሜ ታሪክ የለም፡፡ ራሳቸውንና ድርጅታቸውን ከፍ ለማድረግ ዕጩዎች ከሌሎች ልቀው ለመታየት የማይናገሩት፤ ለእኛም የማያስገምጡን የተስፋ ዳቦ አይኖርም፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ወንዝ በሌለበት መስክ አይበገሬና ጠንካራ የብረት ድልድይ እንደሚሠሩልን ዓይነት ሆነው ይሰበኩናል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ፍላጎት የዘለለ ፖሊሲ ከሽነው ምራቅ ሊያሰወጡን ሆዳችንንም ሊያስጮሁት ይዳዳሉ፡፡ ድንቄም ፖሊሲ፡፡
ወዳጆቼ ! መቼም የምርጫ ጉዳይ ሲነሳ ብዙ ነገሮች ትዝ ተውስ ይላሉ፡፡ አዎ! ምርጫ ነውና በልጦና ተሽሎ ለመገኘት ምርጥ ሃሳብን በልዩነት ማስቀመጡ አይከፋም። የአንዳንዶቹ የምረጡኝ ቅስቀሳ ግን በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ እነዚህኞቹ ቀስቃሾች ጭራሽ መተግበር አይደለም መታሰብ የማይገባውን እውነት እያጣቀሱ ማቅረብ ከሁሉም ያስመርጥ ያስወድድ ይመስላቸዋል፡፡
የሚያነሱት ርዕሰ ጉዳይ ከሌላው ዓለም ዕድገት የተቀዳና በሀገሪቱ ከተለመደው የህይወት ልምድና ተሞክሮ ውጪ የሆነውን ትልቅ ሃሳብ ያለውን ይዘት ነው፡፡ ምንአልባትም እንዲህ ዓይነቱ ሃሳብ ያደጉ ሀገራት እንኳን በወጉ ሊተገብሩት ቀርቶ በዕቅድ ሊያስቀምጡት የማይቻላቸው ዓይነት ሊሆን ይችላል። እነ እንቶኔ ግን ዓይናቸውን በጨው አጥበው የእኛን ዓይን መከለል ይፈልጋሉ፡፡ እነደልጅ እያባበሉም የማይላስ የማይገመጥ ዳቧቸውን እንካችሁ ይሉናል። አንዳንዶቹማ ፊታቸውን በፈገግታ ሞልተው አዛኝና ለህዝብ የቆሙ መስለው ዳገቱን ሜዳ ፣ ረጅሙን አጭር እንደሚያደርጉ ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡
ወደቀደመው ነገሬ ልመለስ፡፡ ወደ ጠጅ ቤቱ እድምተኞቹና ወደ ማስክ አድርጉ ማስታወቂው ጉዳይ፡፡ በጠጅ ቤቱ ያሉ ሰዎች ሁሉም በሚባል መልኩ በመጠጥ ዓለም የሚጓዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ዕድምተኞች አብዛኞቹ ያላቸው አቅም እምብዛም እንደሚሆን ይገመታል። እነሱ በሚገኙበት ስፍራ ይድረስ ተብሎ የተለጠፈው ማስታወቂያ ግን በእንግሊዝኛ የተጻፈ፣ ምንአልባትም ከሌሎች ተገቢ ስፍራዎች ላይ ቃል በቃል የተገለበጠ ነው፡፡ ይህ ስለመሆኑ አንዳቸውም እንደማይረዱት ማወቁ ደግሞ ግልጽና ቀላል ይሆናል፡፡
እንግዲህ የስምና ግብር አለመጣጣም ነገር እንዲህም ሆኖ ይገለጻል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ድርሻችንን ተወጣን ኃላፊነታችንን ተገበርን የሚሉ አካላት በሚፈጥሩት ስህተት ችግርን እያመጡ ስለመሆኑ ልብ ሊሉት ይገባል። አለበለዚያ ‹‹ዝም አይነቅዝም›› ነውና ዝምታን ይምረጡ። አዎ! ዝም !
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 14/2013