መርድ ክፍሉ
የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ያለባቸውን የክህሎት ማነስ፣ ትክክለኛ፣ ወቅታዊ እና ጠቃሚ መረጃን የማግኘት ችግሮች፣ የገንዘብ እጥረት፣ በመንግሥት የሚወጡ ፖሊሲዎችና ሕጎች ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ያላማከሉ መሆናቸው፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት ለወጣቶች ሥራ ዕድል አሳታፊ አለመሆን እንዲሁም በልዩ ልዩ ችግሮች ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች አላማቸውን ለማሳካት መቸገራቸውን በማስተዋል ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች አላማቸውን በመተግበር ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማድረግ ታስቦ የተመሰረተ ማህበር ነው። ስለ ማህበሩ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከማህበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት ወጣት ሳሚያ አብዱልቃድር ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡-የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር የተቋቋመበት አላማ ምንድነው?
ወጣት ሳሚያ፡- በመጀመሪያ ሥራ ፈጣሪ የሚባለው ችግር የታየውና ለችግሩ መፍትሄ የያዘ አካል ማለት ነው። ስለዚህ ማህበሩን ለመመስረት ችግር ታይቶናል ማለት ነው። የታየውን ችግር እስከ መፍትሄው በማዘጋጀት መፍትሄውን ለማምጣት እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሥራ ፈጣሪ ይባላል። በየትኛውም ዘርፍ በቴክኖሎጂውም፣ በግብርናውምና በትምህርቱም በሁሉም መስክ ማለት ነው፡፡
በአሜሪካ አገር ስምንት ሥራ ፈጣሪዎች ናቸው አሜሪካንን አሜሪካ ያስባሏት። የተለያዩ አገራት እዚህ ደረጃ የደረሱት በሥራ ፈጣሪዎች ነው። ችግር ሲታያቸው ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት አድምተው የሰሩ ሰዎች በመኖራቸው ከነሱም አልፎ እኛ እየተጠቀምን ነው። እያንዳንዱ ሕይወታችንን እያቀለለ ያለውና ችግር እየፈታ ያለው ነገር ሥራ ፈጣሪዎች የፈጠሩት ነገር ነው። በዚህ ሁኔታ ሲታይ በኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች አሉ። ብዙ ችግር አለ ማለት ብዙ የሚፈጠር ሥራ አለ ማለት ነው። አገራቸው ትልቅ ደረጃ የደረሰ ሰዎች የሚቸግራቸው ነገር መቀጠር ነው። እዚህ አገር ግን ቅጥር ሳይሆን ሥራ ተፈጥሮለት የሚሰራበት ዘርፍ ነው የሚያስፈልገው።
ይህን ችግር ይዘን ስንነሳ ምንድነው የታየን ከታሰበበት ቦታ ለመድረስና መፍትሄውን ተደራሽ ለማድረግ በጣም ብዙ መንገዶችን እየሄድን እንገኛለን። ይህን ነገር ይጠቅምሃልና ይህ ነገር ይስተካከል ተብሎ ወደ መንግሥት መስሪያቤቶች በሚኬድበት ወቅት ልክ ውለታ የተጠየቀ ያክል ይቆጥራሉ። ሥራ ፈጣሪዎች ራሳቸው መኖር ይችላሉ። ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሚተርፉ አካላት መሆን ይችላሉ። እነዚህን ሥራ ፈጣሪዎች ለምን እርስ በርስ አንደጋገፍም፣ እርስ በርስ የምንተጋገዝበት እንዲሁም በአገሪቱ ሌሎች ተከታዮችን ለምን አናፈራም በሚል የማህበሩ መስራቾች ሀሳብ አመጡ፡፡
እኔ በራሴ ሥራ ፈጣሪ ነኝ። ዕድሜዬ 25 ሲሆን ከሰባት ዓመት በፊት አሁን እየሰራሁት ያለውን ሥራ ፕሮጀክት ቀረፅኩ። በወቅቱ ትምህርት ላይ የነበረው ችግር እንዴት መፈታት እንዳለበት ሀሳብ ታየኝ። ትምህርት ላይ ያለው ችግር የታየኝ በወቅቱ ኬሚስት ለመሆን ህልም ቢኖረኝም ኬሚስት መሆን አልቻልኩም። ምክንያቱም ደግሞ ቤተሙከራዎች ባለመኖራቸው ነው። ምንም ዓይነት በተግባር የተደገፈ ነገር አላየሁም። አብዛኛው ትምህርት በፅንሰ ሀሳብ የተሞሉ ነበሩ። ስለዚህ የትምህርት ሥርዓቱ ችግር አለበት በሚል በተግባር የተደገፈ ትምህርት አደርሳለሁ በማለት መፍትሄ ይዤ መጣሁ። የአገሪቱን የትምህርት ችግር ለመቅረፍ ከሁለት ዓመት በፊት ድርጅቱን ለመመስረት ቻልኩ። በመሰረትኩት ድርጅት ውስጥ ብዙ መንገዶችን ለማየት ችያለሁ። የተለያዩ እንቅፋቶች ቢኖሩም ሳልቆም እዚህ ደርሻለሁ። ድንገት ዕድለኛ ሆኜ ወይንም የቤተሰብ ድጋፍ ስላለኝ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን በጣም አስቸጋሪ ነገሮች አሉ።
ማህበሩ ሲመሰረት የመጀመሪያው አላማ ክህሎት መስጠት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለወጣቶች ተብሎ የተዘጋጀ የክህሎት ስልጠና የለም። እንዲሁም እራስን ማሳደግ ላይም በተለይ እንዴት መኖር እንደሚቻል፣ ምን ዓይነት አስተሳሰብ መያዝ እንደሚገባ እንዲሁም በሌሎች ነገሮች ላይ የተሰራ ነገር የለም። ከትምህርት ቤት ጀምሮ የተሰራ ነገር የለም። ወጣቱ ስልጠና የሚያገኝበት መንገድ የለም። በተለይ በመገናኛ ብዙኃን በኩል ለወጣቱ ተብሎ የተዘጋጀና ታላላቆቻችን የሰጡን የክህሎት ስልጠና የለም። ሌላው ደግሞ ለአንድ ችግር መፍትሄ ሲታይ እንዴት መሬት ማውረድ ይቻላል የሚለው በተለይ ከፕሮፖዛል አፃፃፍ ጀምሮ አናውቅም። የትምህርት ሥርዓቱ ስለታመመ አልተማርንበትም። የምርምር ሥራም ተሰርቷል ተብሎ በአግባቡ ውጤት ላይ አይውልም። በክህሎት ችግር ምክንያት ብዙ ነገሮች ያመልጣሉ፡፡
ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ መረጃ መስጠት ነው። ወቅታዊ የሆነ መረጃ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የሚያገኙበት መንገድ የለም። አንድ ወጣት ሥራ ፈጣሪ አንድ ድርጅት ጋር መስራት ሀሳብ ይዞ ሄደ። ሀሳቡ ይዞ ወደ ፈለገበት ድርጅት ለመሄድ የድርጅቱን አድራሻ አያውቀውም። ምን ይዞ መሄድ እንዳለበትም አያውቅም። ድርጅቱ ውስጥ ምን ምን ነገሮች አሉ ለምሳሌ ይዞት የሚሄደው ሀሳብ የተደገመ ሊሆን ስለሚችል ጠቃሚና ትክክለኛ የሆነ መረጃ ለመስጠት ታስቧል። ሦስተኛው ትስስር መፍጠር ነው። ለምሳሌ እኔ በራሴ ትምህርት ላይ ለመስራት ተነስቻለሁ። ሌላ ትምህርት ላይ ለመስራት የተነሳ ወጣት ካለ ከእኔ ጋር አብሮ መስራት ይችላል። መንግሥት፣ ኢንቨስተሮች እንዲሁም የተለያዩ አካላቶች አንድ ዓይነት ትስስር ተፈጥሮ እርስ በእርስ የምንተጋገዝበት፣ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት እንዲሁም ልምድ ልውውጥ ማድረግ ነው፡፡
አራተኛው ደግሞ ፖሊሲ አድቮኬሲ ነው። በመንግሥት በተለያዩ ጊዜ የሚወጡ አዋጆች አሉ። የሚወጡት ሕጎች ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ያማከሉ ናቸው ወይ የሚለውን ማየት ነው። ከታክስ ጀምሮ ብንመለከት አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎች ወደ ሥራ ሲገቡ ከነባሩ እኩል እንዲከፍሉ ይደረጋል። በመንግሥት የሚወጡ ፖሊሲዎችና ሕጎች እያንዳንዳቸው አዋጆች ለሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። እዚህ ውስጥ ወጣት ሥራ ፈጣሪ ብዙ መንገዶች መጥቶ በመንግሥት አሠራር ውስጥ የሚገጥመው ችግር ምክንያት ተስፋ እንዳይቆርጥ የፖሊሲ አድቮኬሲ ሥራ ይከናወናል።
አምስተኛውና የመጨረሻው ፋይናንስ ነው። ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ብዙ መንገድ ተጉዘው ሀሳባቸውን መሬት ላይ ለማውረድ ፋይናንስ ያስፈልጋቸዋል። እንደሚታወቀው መሬት፣ መኪና ወይም ቤት ከሌለህ ባንክ ብድር አይሰጥም። የሀሳብ ኢንቨስትመንት የሚባል ነገር ባለመኖሩ ኢንቨስተሮች ትብብር አያደርጉም። መንግሥትም ተጠንቶበት ሀሳብ ላይ ኢንቨስት የሚያደርግበት ሁኔታ የለም። የፋይናንሻል ተቋማት ለሥራ ፈጣሪ ወጣቶች እገዛ እንዲደርጉ ማህበሩ ለመስራት አላማ አለው።
አዲስ ዘመን፡- ማህበሩ ለሥራ ፈጣሪዎች ምን ዓይነት ጥቅም ይሰጣል ተብሎ ይታሰባል?
ወጣት ሳሚያ፡- አላማው ጥቅሙን ይገልፃል። በመጀመሪያ ምንድነው የምናደርገው ወጣቱ የማህበሩ አባል ለመሆን ምዝገባ ያደርጋል። እዚህ ጋር መታየት ያለበት በአገሪቱ ብዙ ዓይነት ማህበሮች አሉ። የመምህራን፣ የጠበቃዎች፣ የነጋዴዎች እንዲሁም ለሌሎች ዘርፎች ማህበራት ተቋቁመዋል። ለሥራ ፈጣሪ የተመሰረተ ምንም ዓይነት ማህበር አልነበረም። በአገሪቱ የሚገኙ ሥራ ፈጣሪዎች በተበታተነ መልኩ ነበር ሲሰሩ የነበረው። በመጀመሪያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ተሰባስበው እርስ በእርስ የምንተጋገዝበት ሁኔታ ለመፍጠር ነው፡፡
ይህን ማህበር ለመመስረት ስነሳ ለወጣቱ የምሰጠው ምን ነገር አለኝ ብዬ አስቤ ነበር። የራሴን ሥራ ለመፍጠርና ወደ ተግባር ለመግባት ብዙ ቦታዎች በመሄዴ ብዙ አድራሻዎችን አውቃለሁ። ስለዚህ ያወኩትን ነገር መስጠት እችላለሁ ማለት ነው። አንድ ሥራ ፈጣሪ ወደ አንድ መስሪያ ቤት መሄድ ፈልጌ ነው ቢል ምን ምን ይዤ ልሂድ የትስ ነው አድራሻው ቢለኝ መናገር እችላለሁ። ስለዚህ ወጣቱ በመምጣት መረጃ ያገኛል ማለት ነው፡፡
በክህሎት በኩል ብንመለከት ለምሳሌ ፕሮፖዛል በመስራት ብዙ ታሽቻለሁ። ስለዚህ ጥሩ ፕሮፖዛል መስራት እችላለሁ። ስለዚህ ያንን ፕሮፖዛል ለመስራት ድጋፍ ማድረግ እችላለሁ ማለት ነው። ይህንን ወጣቱን ሰብስቤ ማስተማር እችላለሁ። ሌላው ደግሞ ገንዘብ ሊኖረው ይችላል። ስለዚህ እርስ በእርስ አንድ ላይ በመሆን በመተጋገዝ የሚሰራበት ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል። በአላማዎቹ ክህሎት፣ ትስስር፣ ፖሊሲ አድቮኬሲ እንዲሁም ፋይናንስ ዙሪያ በመተጋገዝ የሚሰራበት ነው። ከውጪ አካል መንግሥትም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች መጥተው እኛን ለማገዝ ከፈለጉ በራችን ክፍት ነው። በውጭ አገር የሚገኙ ሰዎችን ባሉበት ቦታ ያሉ አዳዲስ ነገሮችን ማምጣት ይችላሉ። ወጣቱ ወደ ማህበሩ ሲመጣ መረጃ ከማግኘት ጀምሮ እስከ ፋይናንስ ያሉ ነገሮችን መታገዝ ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን:- ቀደም ብሎ የሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ሲጋጥሟቸው የነበሩ ችግሮች ምን ነበሩ?
ወጣት ሳሚያ:- የመጀመሪው የነበረው የእውቀት ችግሮች፣ መረጃ እጥረትና ሀሳባቸውን የመሰረቅ ሁኔታዎች ነበሩ። እኔም በግሌ ሀሳቤን ተሰርቄ ነበር። ብዙ ጊዜ አብረን እንስራ ተብሎ ሀሳብ ተይዞ ሲኬድ ፕሮጀክቱ ይሰረቃል፣ መጉላላቶች ይኖራሉ፣ ሀሳብን ያለማዳመጥ እንዲሁም እንደ ሌላ ወገን መቆጠሮች ይኖራሉ። ጥፋት ከጠፋ እንኳን የምንማማርበት ሳይሆን የምንጠቋቆምበት ሁኔታ ነው ያለው። የመንግሥት ቢሮ በር ለአነስተኛ ኢንቨስትመንት ለተሰማሩ ባለሀብቶች ብቻ ነው ክፍት የሚሆነው፡፡
በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ድርሻ በጣም አነስተኛ ነው። ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የመረጃ ችግር፣ ትስስር አለመኖር እንዲሁም የመንግሥት አሠራርና የአንዳንድ አመራሮች ሀሳብ ስርቆት ወደ ኋላ እንዲሉ አድርጓቸዋል። ሌላው የሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ሀሳብ አለመተግበርና የሲስተም ችግር እንቅፋት ፈጥሯል። ፖሊሲዎች አለመቀየር ችግር ይፈጥራል፡፡
አዲስ ዘመን:- ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በማህበር መደራጀታቸው ምን የተለየ ነገር ይፈጥራል?
ወጣት ሳሚያ:- ማህበሩ የተለየ ነገር ይዞ የሚመጣው ነገር ብዙ ነው። አብዛኛው ሥራ ፈጣሪ በአገር አቀፍ ደረጃ ሽልማት ይሰጣቸዋል። ወጣቶቹ የሚያውቁት መፍጠራቸውን ነው። ማህበር ውስጥ ሲካተቱ የአስተዳደር እውቀት ድጋፍ ያገኛሉ። ሥራ ፈጣሪዎች እንደ ተቋም እንዲቆሙ እገዛ ያደርጋል። ወጣቶቹ በሰሩት ሥራ ከተሸለሙ በኋላ ወደ ምርት እንዲገባ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልጋቸው እውቀት፣ መረጃ እንዲሁም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ማህበሩ ያግዘዋል።
ለሥራ ፈጣሪዎች ትስስር እንዲፈጠር አድርጎ ወደ ተግባር እንዲገቡ ማህበሩ ያግዛል። ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ድርጅቶችም በማህበሩ በኩል ሥራ ፈጣሪዎችን እንዲያገኙ ያደርጋል። በዚህም አዳዲስ ቴክኖሎጂ የፈጠሩ ወጣቶች በፋብሪካ ደረጃ ሥራቸው ይመረታል። የተለያዩ ወጣቶች ብዛት ያላቸው ቴክኖሎጂዎችን ፈጥረዋል። ነገር ግን የአስተዳደርና የመምራት ክህሎት የላቸውም ስለዚህ በማህበሩ በኩል ድጋፍ ይደረግላቸዋል። የተሻለ ፋይናንስ በመፈለግ ፈጠራዎቹ ወደ ምርት እንዲገቡ ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን:- ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን በምን መልኩ ተደራሽ ለማድረግ ታስቧል?
ወጣት ሳሚያ:- ማህበሩ ሲመሰረት በግሌ ተነሳሽነቱን ወስጄ የሰራሁት እኔ ነኝ። በየክልሉ ተወካዮች ያሉ ሲሆን ተወካዮቹ የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው የሚሰሩ ናቸው። መጀመሪያ የመረጃ ቋት ውስጥ ገብተው ሀሳባቸውን የሚፅፉበት ሁኔታ በዋና ዋና ቋንቋዎች ይፈጠራል። በየክልል ከተማዎች ላይ ጽሕፈት ቤት በመክፈት ሥራ ይጀመራል። አማካሪና ሠራተኞች ይኖራሉ። ለዚህ ደግሞ የመረጃ ቋቱ እየተሰራ ይገኛል። በውጭ አገራትም ቅርንጫፎች በመክፈት የራሳችን ቢሮ ይኖረናል፡፡
አዲስ ዘመን:- ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ ከመንግሥት የተደረገ ድጋፍ አለ?
ወጣት ሳሚያ:- እስካሁን ከሚመለከታቸው ጋር ትስስር ለመፍጠር ደብዳቤዎች ተልከዋል። በተለይ መገናኛ ብዙኃን ስለማህበሩ ሲዘግቡ በደንብ ትስስር ሊፈጠር ይችላል። ማንኛውም ነገር ሲጀመር ከባድ ይሆናሉ። አይደለም በመንግሥት ሌሎች ወጣቶች እንኳን በተሳሳተ መንገድ የሚገነዘቡ አሉ። እንዲያውም ማህበሩ ከመንግሥት ስር የወጣ አድርገው የሚያስቡ ወጣቶች ያጋጥማሉ። ማህበሩ እስካሁን ምንም ዓይነት ግንኙነት ከመንግሥት ጋር የለውም። ከመንግሥት ጋር እንኳን ግንኙነት ቢኖር ከመደጋገፍ ጋር የተያያዘ ነገር እንጂ ሌላ ነገር የለም፡፡
ማህበሩ ከመንግሥት ድጋፍና ትስስር ለመፍጠር እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። እስካሁን ተበታትናችሁ እንጂ አንድ ላይ ሆናችሁ መንቀሳቀሳችሁ ጥሩ ነው። ነገር ግን የመንግሥት አካላት በአንድ ጊዜ የመቀበሉ ሁኔታ አይታሰብም። እስካሁን ያለው ነገር አበረታች ነው። ቅድሚያ ግን ዓይናችንን እርስ በእርስ ነው ማድረግ ያለብን። በሁሉም ሰው ውስጥ ያለው እምቅ ሀብት ቀላል አይደለም። አንዱ ወጣት ጋር የሌለ ነገር ሌላው ላይ ሊኖር ስለሚችል መተጋገዝ ያስፈልጋል። ማህበሩ ከኢንቨስተሮች ጋር ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ ነው። ቅድሚያ ግን ወጣቱ እርስበርስ የሚተጋገዝበት ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ ነው። ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ ብዙ ወጣቶች መጥተዋል። ከወጣቶቹም በግሌ ብዙ ነገሮችን ተምሬያለሁ። ወጣቶቹ ያለፉበት ውጣ ውረድ ለሌሎች ትምህርት የሚሆን ነገር ነው። በውጭ የሚገኙ ወጣቶችም የሚሳተፉበት ሁኔታም እየተመቻቸ ነው፡፡
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ወጣት ሳሚያ:- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2013