መልካምስራ አፈወርቅ
ዕድገትና ውልደቱ ደቡብ ክልል ከምትገኝ ማሻ ወረዳ ነው።የልጅነት ህይወቱ ከአካባቢው ልጆች የተለየ አይደለም።እንደ እኩዮቹ መስሎና ተመሳስሎ ከመስክ ሲቦርቅ አድጓል።ከጓሮው እሸቱን ከማጀት ቤት ያፈራውን አላጣም።
ደረጀ የጨቅላነት ዕድሜውን ጨርሶ ከፍ ማለት ሲጀምር ወላጆቹ ትምህርት ቤት ላኩት።እነሱ ቀለም ቆጥሮ ፣ዕውቀት ጨብጦ ቢመለስ ደስታቸው ነው።ልጃቸው እንደሌሎች ተምሮና ተመራምሮ ቢያስከብር ፣ቢያስወድሳቸው ይወዳሉ ።
ደረጀ የአንደኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ሁለተኛ ክፍል ተሻገረ።ለቀጣዩ ዓመት መዝለቁን ሲያስብ ደስታው ቀጠለ።ክረምቱ አልፎ መስከረም እስኪጠባ ናፈቀ።ጊዜው ደርሶ ተማሪዎች ሲመዘገቡ እነሱን መሰለ።የጀመረውን የሁለተኛ ክፍል ትምህርት ሲያጠናቅቅ ለሶስተኛው ዓመት ራሱን አዘጋጀ።
ታዳጊው ተማሪ ልቡ በሀሴት ሞልቶ ለአራተኛ ክፍል አዲስ ሃሳብ ሰነቀ።ከአምና ካቻምናው ተሽሎም ብርቱ ለመሆን አቀደ ።ደረጀ በአዲሱ ዓመት ያሰበው ተሳካለት።የአራተኛ ክፍል ተማሪ መሆኑን አውቆ ብርታት ጨመረ።ከጓደኞቹ ልቆ አሸናፊ ሊሆን ‹‹ሙያን በልብ›› አለ።ቀድሞ የጀመረው ጥናት ለውጤት ያበቃው ዘንድ ጥረቱን ቀጠለ።ጠዋት ማታ ከደብተር ውሎም ከቀለም አበረ።
የትምህርት ዓመቱ እንደተጋመሰ በደረጀ ልቦና አዲስ ሀሳብ ይመላለስ ጀመር።ለዚህ ጉዳይ ጊዜ ሰጥቶ አሰበበት።ሀሳቡ በየቀኑ ውል ባለው ጊዜ ትኩረት ይሰጠው ያዘ።ይህኔ ትምህርት ይሉት ቁምነገር ከውስጡ ጠፋ ።ስለደብተር ስለቀለም ማሰቡን አድርጎ ተወ።ስለነገ ስለከርሞ ማቀዱን ረሳ።
አሁን የደረጀ ውጥን አዲስ ጎጆና ትዳር ማሰብ ብቻ ሆኗል።ይህን ጉዳይ ደጋግሞ ባሰበ ጊዜ ለትምህርት ያጠፋቸው ጥቂት ዓመታት ይቆጩታል።ትዳር ይዞ ልጆች መውለድ እንደነበረበት ሲገባውም ዕቅዱን ፈጥኖ ለመከወን ይጣደፋል።
ደረጀ ትምህርቱን በድንገት አቋርጦ ወደ እርሻው ተመለሰ።ከበሬ ቀንበሩ ውሎም ነገውን አሰበ።አሁንም ሀሳቡ ትዳር ከመያዝ አላለፈም።
የልጃቸውን አዲስ ውጥን የተረዱ ወላጆች ዕቅዱን አልተቃወሙም።ጎጆ እንዲወጣ ፈቀዱ።ሚስት አግብቶ ልጆች እንዲወልድ መከሩ። ደረጀ በእርሻ ሥራው ጥቂት ቆየ። ለአዲሱ ጎጆ ጥሪት ጉልበቱን ገብሮ መሬቱን አረሰ።ኪሱ ዳጎስ ሲል እጁን ለትዳር ሰጥቶ ያጫትን ጉብል አገባ።
ትዳር …
አሁን ደረጀ ባለትዳር ነው።ትናንት ጀምሮት የነበረው ትምህርት ውል ብሎት አያውቅም።ማልዶ ሲነሳ እርሻውን ያስባል፤ሲያርስ ውሎ ቤት ሲገባ ሚስቱ ቤት ባፈረው እህል ውሀ ትቀበለዋለች ።አንዳንዴ በባህሪይው ለሚስቱ አይመችም።ደርሶ የሚቆጣበት ልማድ እሷን ጨምሮ ሌሎችን ያስከፋል።
ባህሪውን የሚያውቁ ቤተሰቦቹ እንደአመሉ ያግባቡታል።ድርጊቱን ያልለመዱት አንዳንዶች ቅያሜን አልፈው ለጠብ ይሹታል።ደረጀ እንደዓመሉ ከያዘችው ወይዘሮ ጋር በትዳር ዘልቋል ።ለጎጇቸው ድምቀት ያገኙት የመጀመሪያ ልጅ ፍሬም ጥምረታቸውን አጽንቷል።
ልጅ ሲመጣ አባት የሆነው አባወራ አሁንም ነገን ያልማል።ሁሌም ቢሆን አፈር ገፍቶ በሬ ስቦ የሚያመጣው ገቢ በቂ ሆኖት አያውቅም።ከእጁ ያለው ጥሪት፣ ከኪሱ ያኖረው ገንዘብ አያኮራውም።ባለቤቱ እጁን ከማየት ያለፈ ልትረዳው አልቻለችም።የልጅ እናት መሆኗ ከቤት አውሏታል።
ደረጀ ይህን ሲያስብ ብዙ ያቅዳል ።ከእርሻው ይልቅ የከተማን ህይወት ይናፍቃል፣ ወጣ ብሎ ቢሰራ ገንዘብ እንደሚያገኝ ይገምታል ።ግምቱ እርግጠኛ የሆነ ሲመስለው እግሮቹ መንገድ ያስባሉ።ልቡ ይነሳሳል፣ ዓይኖቹ አሻግረው ይቃኛሉ።
ደረጀና ባለቤቱ እንደወጉ ባቀኑት ጎጆ ልጃቸው እያደገ ነው።ህጻኑ ባለ ጊዜ ሳቅ ጨዋታ ይደምቃል።ኩርፊያ ጠፍቶ ሰላም ይወርዳል።ንትርክ ቀርቶ እፎይታ ይነግሳል።ልጁ የቤቱ ዓለም ሆኗል።
ደረጀ በግብርናው ቀጥሏል።ጉልበቱን ገብሮ ላቡን አፍስሶ ጎጆውን ያቀናል።ሚስት ቤቷን አክብራ ፣ልጇን እንደያዘች ከጎኑ ሆናለች።ለአባወራው ወጥቶ መመለስ ሁሌም ቀናውን ታስባለች።
በድንገት ሁለተኛው ልጅ ተረገዘ።ጊዜው ደርሶ ሲወለድም ለጥንዶቹ ዳግመኛ ልጅ፣ ለወንድሙም ወንድም ሆነ ።ደረጀ በጨቅላው መምጣት አልተከፋም። ሁለተኛውን ፍሬ በደስታ ተቀብሎ ኑሮን ቀጠለ።ብዙ ቢያስብም የልጆቹ መኖር ለእሱ ተስፋ መሆኑ አልጠፋውም።ከትናንት ዛሬ በርትቶ ቁምነገር ሊያደርስ ተመኘ።
ሁለቱ ጨቅላዎች የቤተሰቡ ዓለም ሆነዋል።ከጎጇቸው ውለው ከመስኩ ይቦርቃሉ። የተሰጣቸውን ጎርሰው ተኝተው ይነሳሉ።በጥንዶቹ ቤት ህይወት እንደቀድሞው ቀጥሏል።ኑሮ እንደትናንቱ ነው።አባወራው ከእርሻ ውሎ ይገባል።ሚስት የቤት ድርሻዋን ትወጣለች።ልጆች በወላጆች ሀሳብ ውለው ያድራሉ።
ደረጀ አሁንም ልቡ መንገድ ያስባል።ሁሌም ስለከተማ የሚሰማው ወሬ እንደማረከው ነው ።ይህ ዕቅዱ ውል ባለው ጊዜ ውስጡ አምርሮ ይቆርጣል።ከተሜ መሆን፣ ፈጥኖ መለወጥ ያምረዋል።መልሶ ደግሞ ሚስትና ልጆቹን ያያል። ጥሏቸው ቢሄድ የሚገጥማቸውን እያሰበ ይጨነቃል።
ከቀናት በአንዱቀን ደረጀ ሚስቱ ሶስተኛውን ልጅ እንደጸነሰች አወቀ።ይህኔ ውስጡ ተረበሸ።ከዚህ በኋላ መቁረጥና መወሰን እንዳለበት ገባው።በእሱ ዕምነት የተሻለው ነገር ከተማ ገብቶ መኖር ነው።እሱ እንደሌሎች በቂ ገንዘብ ካለው ቤተሰቡን መርዳት፣ልጆቹን ማኖር ይችላል።ይህን ለማድረግ ደጋግሞ ከራሱ መምከር መመካር አለበት።
ስንብት…
በጥንዶቹ ጎጆ ሶስኛው እንግዳ ደረሰ።የጨቅላው ለቅሶ ቤቱን በአዲስ ድባብ ለወጠው።ሁለቱ ልጆች ታናሽ ወንድም አገኙ፣እናት ልጇን ታቅፋ ፈጣሪዋን አመሰገነች።አባወራው ደጅ ደጁን እያየ መንገዱን አሰበ።የበረከተው ቤተሰቡ ቁጥር አስጨንቆታል።
ደረጀ ከዚህ ቀደም ከተማ የገቡ ባልንጀሮቹ ትውስ አሉት።ባሉበት ሆነው ቤተሰብ እየረዱ ነው።በኑሮ ተቀይረው ገንዘብ ይዘዋል።የበረቱ ሀብት ንብረት አፍርተዋል።አሁን ደረጀ ከመጨረሻ ውሳኔ ደርሷል።ለሚስትና ልጆቹ መኖር ፣ ለእሱም መሻሻል ከተማ እንደሚበጅ አውቋል።
አንድ ማለዳ አባወራው ከቤት ወጥቶ ሄደ።እርግጠኛ ባትሆንም ባለቤቱ ርቆ መሄዱን አውቃለች።አውቶቡስ ተራ ገብቶ ትኬት ሲቆርጥ የመንገዱ አቅጣጫ አዲስ አበባ ሆነ።ከኪሱ የያዘው ገንዘብ ቀን እንደሚያሻግረው ያውቃል።
ከስፍራው ሲደርስ የሚያገኛቸው ሰዎችም ለእንግድነቱ አያሳፍሩትም።ደረጀ እንዳሰበው ሆኖ አዲስ አበባ ደረሰ።አካባቢው እንደሱ መንደር አይደለም።ከተማው የሰፋ ፣ህዝቡ የበረከተ ፣ኑሮው የደመቀ ነው።ጥቂት ቀናት ሁኔታዎችን ለመልመድ ቸገረው።ውሎ አድሮ ግን ሁሉን አውቆ መውጫ መግቢያውን ለየ።
የማሻው አባወራ ኮልፌ ‹‹ሎሚ ሜዳ›› የተባለው ሰፈር ሰፈሩ ሆነ።በስፍራው የአገሩን ልጆች አላጣም።የአቅሙን እየሰራ ያገኘውን እየቀመሰ ወራትን ገፋ።ውሎ አድሮ በህንጻ ሙያ የቀን ሰራተኛ ሆኖ ተቀጠረ።ጉልበቱ አላሳፈረውም።በሰራው መጠን በሚከፈለው ገንዘብ አቅሙን ደጎመ።ከብሩ ለራሱ እያስቀረ ለቤተሰቡም መላክ ጀመረ።ገጠር ያሉት ሚስትና ልጆቹ ከላቡ ወዝ ተጋሩ።
ደረጀ የከተማን ህይወት ሲላመድ ሁሉ ነገር ገባው።ሲጋራ የያዙ ወጣቶች ማረኩት።ጠጋ ብሎ ከእሳታቸው ለኮሰ፣ ጭሱን እያየ ሽታውን ወደደው ።ሲደጋግመው ሱስ ሆነበት ።አልተወውም።እየለኮሰ፣እየተረኮሰ፣ ቡን ያደርገው ገባ።
ደረጀ ሲጋራው ብቻ አልበቃውም።ከሚጠጡ ባልንጀሮች ጋር ተወዳጀ።በየቀኑ ጎራ የሚልበት ጠጅ ቤት ደንበኛ ሆኖ ዘለቀ።ከሥራ መልስ እየጠጣ መስከር ልምዱ ሆነ።እየተንገዳገደ፣እየተሳደበ ቤቱ ሲደርስ ውሎውን ይረሳል።ዛሬን ይዘነጋል።
አሁን ከተማ ገብቶ የለመደው ሱስ ባህሪውን ለውጧል።ቀድሞም ቁጠኛ የነበረ ዓመሉ ዛሬ ብሶ ከሰው ያጋጨዋል ።ግጭቱ ሰር ሲሰድ ለድብድብ ይጋበዛል።አንዳንዴ ደብድቦ፣ ሌላ ጊዜ ተደብድቦ ይገባል።
ገጠር ያሉ ልጆቹ ትዝ ባሉት ጊዜ ልቡ መለስ ብሎ ጸጥታን ይመርጣል።ይህ ጥሞናው ብዙ አይቆይም።ጠጅ ቤት ገብቶ ከብርሌ ሲገናኝ ክፉ ዓመሉ ይነሳል፣ከሰው ይጋጫል።ጠብ ፈጥሮ ተደባድቦ ይወጣል።
አንድቀን ደረጀ ከአንድ ሰው ጋር ድብድብ ያዘ።ጠቡ የከፋ መሆኑን ያወቁ ሊገላግሉ መሀል ገቡ።ደረጀ ሀይሉ በረታ፣ተፋላሚውን አጠቃ።በሰውዬው የደረሰው ጉዳት አካል እስከማጉደል ደረሰ።ደረጀ በቁጥጥር ስር ሲውል ህግ በዋዛ አልተወውም።ለድርጊቱ አስመስክሮ፣ ለጥፋቱ ሁለት ዓመት እስራት በየነበት።
ደረጀ በማረሚያ ቤት ሁለት ዓመታት ሲቆይ ገጠር ያሉ ቤተሰቦች ከችግር ገቡ።የእጁ ሲሳይና የድምጹ መጥፋት አሳስቧቸው ቆየ።በእስር ቆይታው ታራሚው አባወራ ራሱን ሊቀይር ፣ በባህርይ ሊለወጥ ወሰነ።በስህተቱ ያለፈውን ላይደግም ለራሱ ቃልገባ።
በእስር የተፈተነው ደረጀ ቅጣቱን ጨርሶ በተፈታ ጊዜ ከነባር ሥራው ተመለሰ።ገጠር ወርዶም ሚስትና ልጆቹን ጎበኘ ።አባወራው ቤቱ መቅረት አልፈለገም።ከተማ የሚሻው ልቡ እያጣደፈ ከነበረበት መለሰው።
ህይወት እንደገና…
ደረጀ ከእስር ከተፈታ በኋላ በቀን ሥራው ቀጠለ።ለጥቂት ጊዜያት ከቀድሞ መገኛው ላይታይ ሞከረ።ቁጡ ባህርይውን ውጦ ከጠብ ርቆ ታየ።ከመጠጥ ያልተለየው አባወራ ሞቅ ባለው ጊዜ ውስጡ ይፈተናል።አንዳንዴ ትዕግስት ሲያጣ ለጠብ ይጋበዛል።ባህርይውን የሚያውቁ ከሩቅ ይሸሹታል።
አንድ ቀን ደረጀ ከፍርድ ቤት ችሎት ተከሶ ቀረበ።የክሱ ዝርዝር እንስሳትን በግፍ አሰቃይቶ መግደሉን ጠቆመ ።ስለድርጊቱ ምስክርና ማስረጃ የቀረበበት ተከሳሽ ወንጀሉን ማስተባበል አልቻለም።ጥፋተኝነቱን አምኖ እስሩን ተቀበለ።ፍርድ ቤቱም ለጥፋቱ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ፈረደበት።
በደረጀ እስር ገጠር ያሉ ሚስትና ልጆቹ ከችግር ወደቁ ።እሱም እንደለመደው ለራሱ ቃል ገባ።ከእስር መልስ ባህርይውን ሊያድስ በውስጡ ማለ። ዳግም ድርጊቱን ላይፈጽም ወሰነ።ሚስትና ልጆቹን ከችግር ሊያወጣ ቆረጠ።
አሁንም የእስር ጊዜው አበቃ።ደረጀ ከእስር ወጥቶ የውጪውን ህይወት ተጋራ።እንዳለው ሆኖ ለቀናት ባህርይውን የለወጠ መስሎ ታየ።ቀናት አልፈው ሌሎች ቀናት መጡ።ውሎ አድሮ የቀደመ አመሉ አገረሸ ።የጠጅ ቤት ስካሩን ቀጥሎ ከብዘዎች መጋጨት ያዘ።
ህዳር 3 ቀን 2010 ዓም …
መሽቷል ።የህዳር ቅዝቃዜ አጥንት ሰብሮ የሚገባ ይመስላል።ከጠጅ ቤቱ የታደሙት ደንበኞች ከቦታቸው ተቀምጠው ብርሌ ጨብጠዋል።አብዛኞቹ የጨለጡትን ያስሞላሉ።ብዙዎቹ አይደማመጡም። ጫጫታው ጨኸቱ፣ሳቅና ሁካታው ደርቷል።
የዛን ቀን ምሽት ደረጀ ከሎሚ ሜዳ ጠጅ ቤት ሲጠጣ አምሽቷል።ከሶስት ሰዓት በኋላ ወደ ቤቱ ጉዞ ጀመረ።ጤና ጣቢያው አካባቢ ሲደርስ ፤በመንገዱ ላይ ሰዎችን አገኘ።ሁሉንም ያውቃቸዋል ። ከትውልድ አካባቢው የመጡ ናቸው።ከእነሱ መሀል ሁለቱን ወንድማማቾች እየገላመጠ፣ስድብ ጀመረ።የእሱን አገር ከእነሱ እያወዳደረ አንቋሸሻቸው።ተናደዱ።
ሌሎቹ ንግግሩን ሲሰሙ ለጠብ ተጋበዙ።ደረጀ ከአገርቤት የመጣለትን አዲስ ጩቤ አውጥቶ ሰነዘረ ።ከወንድማማቾቹ አንዱን ከትከሻው ወጋው።የወንድሙን መወጋት ያየው መንገደኛ ዱላ ሰንዝሮ ትከሻውን መታው።ደረጀ መልሶ ጩቤውን ሰነዘረ። በዱላ የመታውን ሰው አንገቱን አገኘው።ተጎጂው በጀርባው ወደቀ ።ጨኸት ግርግሩ በረከተ ።ደረጀ እየሮጠ ወደጠጅ ቤቱ አመራ።
የፖሊስ ምርመራ…
መረጃ ደርሶት ከስፍራው የደረሰው የፖሊስ ቡድን በአካባቢው ካሉ ሰዎች እውነታውን ተረዳ።የደረጀን ዱካ ተከትሎ ወደተባለው ስፍራ አቀና ።ደረጀ ከጠጅ ቤቱ ገብቶ እየጠጣ አገኘው።በቁጥጥር ስር ሲውል ያደረገውን አልደበቀም።ድርጊቱን አንድ በአንድ አስረዳ።መርማሪው ዋና ሳጂን መስፍን ሀይለሚካኤል ተጠርጣሪውን ከህግ አድርሶ የተጎጂውን ሁኔታ አጣራ።ግለሰቡ በተመላላሽ ህክምና ቆይቶ ህይወቱ ማለፉን አወቀ።ይህንኑ በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 449/10 ላይ በአግባቡ መዘገበ። ዓቃቤህግ ክስ ይመሰርት ዘንድም የምርመራ መዝገቡን አስተላለፈ።
ውሳኔ…
ነሐሴ 13 ቀን 2012 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሹ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮ ተገኝቷል።በፖሊስና ዓቃቤ ህግ የተሰነደውን መረጃ መርምሮም የተከሳሽን ጥፋተኝነት አረጋግጧል።ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ባሰለፈው ውሳኔ ደረጀ ሞገስ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአሥራ ዘጠኝ ዓመት እስራት ይቀጣ ሲል ብይን ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013