መልካምስራ አፈወርቅ
የተወለደው ደብረማርቆስ አካባቢ ከምትገኝ አንዲት የገጠር ቀበሌ ነው።ልጅነቱ ከእኩዮቹ ህይወት የተለየ አልነበረም።የገጠር ማጀት ካፈራው በረከት ያሻውን ሲያገኝ ቆይቷል።
ደምሴ እድሜው ከፍ እንዳለ ትምህርት ቤት መግባት ፈለገ።ለትምህርት የነበረው ፍላጎት ሲጨምር ወላጆቹን ‹‹አስተምሩኝ.›› ብሎ ጠየቀ።ፍላጎቱ ከሃሳብ አልዘለለም።ቤተሰቦቹ እሱን የማስተማር አቅም እንደሌላቸው እቅጩን ነገሩት።ውስጡ እያዘነ ከቤት መዋል ልምዱ ሆነ፡፡
የመንደሩ ልጆች ደብተር ይዘው ትምህርት ቤት መሄድ ጀመሩ። ደምሴ ዓይኑ ውሃ እየሞላ፣ ሆድ እየባሰው ቤት መዋል ቀጠለ። እናት አባቱ ገበሬዎች ናቸውና የግብርና ሙያን አወረሱት።ከአውድማ እየዋለ የእርሻ ስራውን ያዘ።ትምህርት ይሉትን ረስቶም መልካም ገበሬ ሆነ፡፡
ደምሴ በእድሜው መጎልበት ሲጀምር ወላጆቹን በስራ ለማገዝ ወደከተማ ዘለቀ። በጉልበቱ በላቡ ወዝ ካፈራው እያካፈለም የጎደለውን ማሟላት ጀመረ።ገንዘብ ማግኘቱ በእጅጉ አበረታው። ራቅ ማለቱ አርቆ እንዲያስብ ሰበብ ሆነው። ካለበት ስፍራ ወደሌላ ቢሄድ የተሻለ መሆኑ በገባው ጊዜ ከራሱ መከረ። ምክሩ ያሰበውን ይፈጽም ዘንድ ምክንያት ሆነው። አዲስ አበባ ቢሄድ ኑሮው፣ ህይወቱ ገቢው እንደሚለወጥ አስቦ ለጉዞ ተዘጋጀ፡፡
ህይወት በአዲስ አበባ…
አሁን ደምሴ የአዲስ አበባ ልጅ ሆኗል።ከተማ ሲገባ ከሌሎች ለመግባባት አልተቸገረም።አካባቢውን ተላምዶ ጥሩ ወዳጆች አፈራ፤ ከብዘዎች ተዋውቆም እንጀራውን ፈለገ። ያሰበውን አላጣም። በእሱ አቅም የሚሆን ስራ ተገኘለት። የዕለት ጉርሱን እየቻለም ጥቂት ጥሪት ቋጠረ።የአቅሙን ቤት ተከራይቶ ራሱን አደረጀ፡፡
ዓመታትን በቀን ስራ ያሳለፈው ወጣት አዲስ አበባን ከእግር እስከራሷ አወቃት።ይህ መሆኑ የተሻለ እንጀራ እንዲያገኝ ረዳው። ከአንዱ ወደ አንዱ ስራ እየለወጠ ጊዜያትን ቆጠረ፡፡
ውሎ አድሮ ወዳጆቹ የሆቴል መስተንግዶን አላመዱት። ደምሴ ሙያው አድርጎ ከስራው ተላመደ፣ እንጀራዬ ባለው ውሎም የተሻለ ገቢ ማግኘት ያዘ። አጋጣሚው ከበርካቶች አስተዋውቆ ኑሮውን ለወጠለት። የገጠሩ ወጣት የትናንት ማንነቱን ለመርሳት ጊዜ አልፈጀም። በአለባበስ በአነጋገር ተቀይሮ አካባቢውን መሰለ።
ደምሴን የሚያውቁ በጸጉር ቁርጡ ይለዩታል። አለባበሱም ቢሆን ከሌሎች የተለየ ነው። ከስሙ በፊት በሚጠራበት ስም ደስተኛ ነው።ጸጉሩን አይተው ‹‹ባጂዮ›› ለሚሉት ሁሉ አቤት ለማለት ፈጣን ነው፡፡
ወጣቱ የሆቴል ሰራተኛ ባካበተው ልምድ የሰራተኞች ሃላፊ ሆኖ መስራት ጀመረ። ይህ ለውጥ ከታዛዥነት አውጥቶ ብዘዎችን እንዲያዝ እድል ሰጠው።ደምሴ አጋጣሚውን ሲያገኝ አመሉ ተቀየረ። ከመግባባት ይልቅ ጠብና ነገር ይቀድመው ጀመር።የቀረቡትን ማመናጨቅ ያናገሩትን መጣላት ልምዱ ሆነ፡፡
ጠበኝነት የለመደው ወጣት ጉዳዩን በድብድብ ቢፈታ ይወዳል።ትዕግስት ማጣቱ ያስከተለው ችግር ከብዙዎች እያጋጨው ነው። ግዙፍ ሰውነቱን ያዩ አንዳንዶች በሩቁ አይተው ይሸሹታል።ካለመግባባት የሚመጣውን ችግር የሚገምቱ ደግሞ ጉዳዩን በሰላም ሊፈቱ ይጥራሉ፡፡
ደምሴ ከብዘዎች እንደመዋሉ ዓመሉ የበዛ ሆነ።ተደባዳቢነት ባህሪይው ሆኖም ከብዙዎች ይጣላ ጀመር። ከሁሉም ግን አንድ ቀን በአንድ ሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት የከፋ ሆነ።በጠብ መሀል በተፈጠረ ድብድብ ሰውዬውን እንዳይሆን አድርጎ ቀጠቀጠው።
ባደረሰው የከፋ ጉዳት በህግ ጥላ ስር የዋለው ወጣት ክስ ተመሰረተበት።ምስክሮች ያዩትን መሰከሩ፣ ጥፋተኝነቱን ያረጋገጠው ፍርድቤት ያደረሰውን ጉዳት ከግምት አስገብቶ ማረሚያ ቤት እንዲቆይ ትእዛዝ ሰጠ።
ደምሴ በፈጸመው የድብድባ ወንጀል በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለስምንት ወራት እንዲታሰር ተፈረደበት።የእስር ጊዜውን እስኪጨርስ ታርሞ ለመውጣት ራሱን አዘጋጀ። ለወራት በእስር መቆየቱ እልህ አጋባው።ከስህተቱ ተምሮ ነገን የተሻለ ለማድረግ ማሰብ ያዘ።ቀናትን ከወራት እየቆጠረም የመፈቻ ቀኑን ጠበቀ፡፡
ከእስር መፈታት…
አሁን ደምሴ የቅጣት ጊዜውን አጠናቆ ከእስር ተፈቷል። የቆየበትን ጊዜ ሲያስብ ጥፋተኝነት ይሰማዋል። መልሶም ባለፈበት መንገድ ላለመሄድ ይወስናል። ቆይታውን አጠናቆ ወደ ስራው ሲመለስ ትዕግስት ተላብሶ ሊቆይ ሞከረ።ይህ ሙከራው ለጥቂት ጊዜ ተሳክቶም ከብዘዎች ሰላም ሆነ፡፡
ደምሴና የሆቴል ሙያው እንደትናንቱ ሰምረዋል። አሁንም የተለመደው የባጂዮ ጸጉር ቁርጥ ከእርሱ ጋር ነው። ውፍረትና ግዙፍነቱ መለያው እንደሆነ አብሮት ዘልቋል።በሚሰራበት ሆቴል ያሉ ሰራተኞች አክብሮታቸው ከፍራቻ ጋር መሆኑ ያስታውቃል።ሲጠራቸው ‹‹አቤት›› ፣ሲልካቸው ‹‹ወዴት›› ብለው ያድራሉ፡፡
አንዳንዴ በሆቴሉ ደንበኞች ሰክረው ይጣላሉ።ይህኔ ደምሴ ውሰጡ ይፈተናል።ከመገላገል ይልቅ በጠቡ ቢታደም ፈቃዱ ነው።ነገር በርዶ ሰላም ከወረደ ነገሮች ይረሳሉ።ይህ ካልሆነ ግን መጨረሻው በእሱ ቡጢ ሊቋጭ ይችላል፡፡
ጓደኛሞቹ…
አምስቱም የአንድ አገር ልጆች ናቸው።አዲስ አበባ የመኖራቸው ሚስጥር እንጀራ መፈለጋቸው ነው።ሁሉም በቀን ውሏቸው ሲሮጡ መዋል ልምዳቸው ነው።አብዛኞቹ ለፍቶ አዳሪዎች ናቸው።ጀብሎ ያዞራሉ ፣ ሰው ቤት ይሰራሉ፡ ጉልበት በፈቀደው ሁሉ ይገኛሉ፡፡
አንዳንዴ ባልንጀርነታቸውን ለማሰብ በቀጠሮ ይገናኛሉ። በተገናኙ ጊዜ የአቅማቸወን አዋጥተው መዝናናት ልምዳቸው ነው።ሲዝናኑ ከምግብ መጠጡ ያሻቸውን ያዛሉ።ምሽቱ አያሰጋቸውም።ሙዚቃ ካለ ተነስተው ይጨፍራሉ። ይደንሳሉ፡፡
ከአምስቱ ባልንጀሮች ሁለቱ በትዳር ተጣምረው ጎጆ ቀልሰዋል።ይህን የሚያውቁ ሌሎች ለእነሱ አክብሮት አላቸው። ጥንዶቹ ወጥቶ ለመዝናናት ወደ ኋላ አይሉም። በትዳር አሳበውም ከሌሎች መለየት አይሹም። ባልንጀሮቻቸው ባለቡት ተገኝተው እነሱን ይመስላሉ፡፡
አንዳንዴ ጓደኛሞቹ ለጨዋታ ሲገናኙ ቦታ እየቀየሩ ይዝናናሉ። ከምግብ ከመጠጡ ሲሉም ከምሽቱ ይደርሳሉ። ምሽቱ አስግቷቸው አያውቅም። እንዳሻቸው ይቆያሉ። በቆይታው ተደስተው ወዳሉበት ይገባሉ።እንዲህ ሲሆን አንድነታቸው ፍቅርን ያሳያል።ተሳስበው ተደማምጠው መሸኛኘት ልምዳቸው ነው ፡፡
ህዳር 3 ቀን 2010 ዓም
ምሽቱ ገፍቷል።ገና በጊዜ የተዘጉት የንግድ ሱቆች በጭርታ ተውጠዋል።አቅራቢያቸው ያሉ የምሽት ቤቶች አሁንም እንግዶችን እየጠበቁ ነው።ጎን ለጎን ያሉ የመጠጥ ግሮሰሪዎች በተለመደ ሁካታ ውስጥ ናቸው።በየመንገዱ የሚንገላወዱ ሰካራሞች ያሻቸውን ይናገራሉ።በመጠጥ ቤቱ ሙዚቃው ያንባርቃል።ብርጭቆ የጨበጡ አንዳንዶች ቆመው፣ ተቀምጠው ይወዛወዛሉ፡፡
ስፍራው አውቶቡስ ተራ ነው።የነገን ሩቅ መንገድ ያሰቡ በጊዜ አልጋ ይዘዋል።ከነሱ መሀል መዝናናት የፈለጉ ካሉበት ወጣ ብለው በየጥጉ መሽገዋል።ሙዚቃው ከመጠጥ ሽታ ተዳምሮ ናላን ማዞር ጀምሯል፡፡
የቶፕ ሆቴል ደንበኞች ዛሬም በቦታው ናቸው። ከመጠጡ ይጎነጫሉ፣ በሙዚቃ ይወዛወዛሉ፣ ከሴት አስተናጋጆች ጋር ይጫወታሉ።የሰራተኞቹ አለቃ ስራ በዝቶበታል።ዓይኖቹን ከወዲያ ወዲህ እየጣለ ቤት ደጁን ይቃኛል። ወጪ ገቢውን እየለየ አስተናጋጆችን ያዋክባል።
ደምሴ ስራና ደንበኛ በበዛ ቀን እንዲሁ ነው። አለቅነቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ይታዩበታል። በየሰበቡ መቆጣት መነታረክ ይወዳል። ያለምክንያት መጮህ መነጫነጭ ያበዛል፡፡
አሁን ከምሽቱ አራት ሰአት ተኩል ሆኗል።አምስቱ ባልንጀሮች ሲዝናኑ ካመሹበት ስፍራ ቤት ለመቀየር ፈልገው ቶፕ ሆቴል ደርሰዋል።ቦታው ቢጨናነቅም መቀመጫ አላጡም።ከአንድ ጥግ ወንበሮችን መርጠው ተቀመጡ።ሙዚቃው አሁንም ያንባርቃል።እዚህም እዚያም በሞቅታ የሚጨፍሩ ጠጪዎች ይታያሉ።
ከአስተናጋጆቹ አንደኛው የእንግዶቹን መቀመጥ ተከትሎ ትዕዛዝ ለመቀበል አጠገባቸው ደረሰ። ባልንጀሮቹ እንደፍላጎታቸው የሚፈልጉትን መጠጥ አዘዙ። ከደቂ ቃዎች በኋላ ከበው የተቀመጡት ጠረጴዛ በቀዝቃዛ የቢራ ጠርሙሶች ተሞላ። ሁሉም ጠርሙሶቻቸውን እኩል አጋጭተው መጠጡን ተጎነጩ፡፡
በሆቴሉ የተከፈተው አገርኛ ሙዚቃ ጠጪውን ማነቃቃት ይዟል። አምስቱ ጓደኞች በሙዚቃው እየተዝናኑ ነው። ተራ በተራ እየተነሱ ጭፈራውን ማስነካት ይዘዋል። ባልና ሚስቱ ከባልንጀሮቻቸው አልተለዩም። አንዳቸው ሲነሱ አንዳቸው እየተቀመጡ እኩል ይጨፍራሉ። ሙዚቃው እየደራ መጠጡ እየታዘዘ
ነው።ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገቡ እንግዶች መቀመጫ እየፈለጉ ጠጪውን ይቀላቀላሉ።አስተናጋጁ በየጠረጴዛው የጠጪውን ፍላጎት እያየ ይታዘዛል። ደምሴ የእንግዶቹን ሁኔታ እየቃኘ ቤቱን ይቆጣጠራል። ሙዚቃው ጨዋታው ደርቷል።ጠጪዎች ተወዛዋዦች በዝተዋል፡፡
ከምሽቱ ስድስት ሰአት ተኩል
አሁን ደምቆ የቆየው ሙዚቃ በሌላ ሙዚቃ ተተክቷል። ዘፈኑ ለስለስ ያለ ለጭፈራ የማይጋብዝ ሆኗል። ይህ የገባቸው ከውዝዋዜው ተመልሰው ከወንበራቸው አርፈዋል።ከነሱ መሀል አብዛኞቹ ለድካማቸው ቀዝቃዛው ቢራ እንዲደገም አዘዋል፡፡
ከቆይታ በኋላ ለስለስ ያለው ሙዚቃ አብቅቶ ደማቁ ዘፈን ተከተለ። ይህን የሰሙ ዳግም ከመቀመጫቸው ተነሱ። በአዲስ ወኔና ስሜትም ጭፈራውን ጀመሩ። በጠረጴዛ ዙሪያ ሰብሰብ ያሉት ባልንጀሮች አዲስ የተከፈተው ዘፈን ውስጣቸውን አሞቀው። ካሉበት ተነስተው ወደ መሀል ዘለቁ፡፡
ጥንዶቹ የእነሱን ውዝዋዜ እያዩ ሌሎችን በጭብጭበዛ አጀቡ። የሙዚቃ ስልቱ እየደመቀ ጨፋሪዎቹ ሲበዙ ባል ሚስትን ካለችበት ትቶ ከወንበሩ ሊነሳ ተዘጋጀ። ሃሳቡ ሙዚቃው ሳያበቃ ለመድረስ ይመስላል፡፡
ባል በቢራ ጠርሙሶች የተሞላውን ጠረጴዛ ተመርኮዞ ከመቀ መጫው ተነሳ። ይህን ከማድረጉ ከጫፍ የተቀመጡ ሁለት የቢራ ጠርሙሶች ተንሸራተው ከወለሉ ወደቁ። ከመሬት የተጋጩት ጠርሙሶች ድምጽ ከሙዚቃው ተዳምሮ የቤቱን ድባብ ቀየረው፡፡
ሙዚቃው አብቅቶ ሁሉም ወንበሩን እንደያዘ አስተናጋጁ ሲሮጥ ደረሰ። ወደባልንጀሮቹ ጠረጴዛ ተጠግቶም ጠርሙስ ወደሰበረው ሰው አፈጠጠ። የጠርሙሶቹን ሂሳብ እንደሚከፍልም ተናገረ።ቁጣውን ያዩ ባልንጀሮች አስተናጋጁን እያግባቡ ሂሳቡን እንደሚከፍሉ በአንድ ድምጽ ተስማሙ።
ከነበረበት ድንገት ብቅ ያለው ደምሴ በቁጣ ተሞልቶ ወደጠረጴዛው ተጠጋ።ፊቱ ላይ ቁጣና ንዴት ይነበባል። ሃላፊ መሆኑ የገባቸው ባልንጀሮች ደግመው የጠርሙሶቹን ሂሳብ እንደሚከፍሉ አረጋገጡለት።በእጁ ድንጋይ የጨበጠው ደምሴ ሊሰማቸው አልፈለገም።በቁጣ እንደተሞላ ጠርሙሶቹን ሰብሯል ወደተባለው ሰው ተጠጋ፡፡
ጓደኛሞቹ ሁኔታውን አይተው ሊያረጋጉት ሞከሩ። የጠርሙሶቹን ሂሳብ ለመክፈል መፍቃዳቸውንም ደጋግመው ተናገሩ።ደምሴ የሚሉት ሁሉ አናደደው። የሚናገሩት አበሳጨው።ዓይኑን እንዳፈጠጠ የከበቡትን ገፈተረ። የጨበጠውን ትልቅ ድንጋይ ወደሰውዬው ወረወረ።
ድንጋዩ በጆሮ ግንዱ ያረፈው ሰው ደሙን እያዘራ ከመሬት ተዘረረ፤ ጉዳቱን ያስተዋሉ ራሱን የሳተውን ተጎጂ ለማንሳት ተረባረቡ።የሆቴሉ አስተናጋጆች አለቃቸውን እየገላገሉ ከአንድ የጓሮ ክፍል በር ዘግተው ሸሸጉት፡፡
ቤቱ በጩኸትና ትርምስ ታመሰ።የባልንጀራቸውን ጉዳት ያዩ አምስቱ ነፍሱን ለማትረፍ ወደሆስፒታል ይዘው ሮጡ።የቀኝ ጆሮ ግንዱን ክፉኛ የተጎዳው ሰው በሚስቱ ደረት ተደግፎ ከሆስፒታል ደረሰ፡፡
የፖሊስ ምርመራ…
ፖሊስ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ሆቴል ተገኝቶ መረጃዎችን አጣራ።የተጠርጣሪውን ማንነት ለይቶም ሌሎችን ለጥያቄ ወሰደ።ሲነጋ ከስፍራው ተመልሶ ተፈላጊውን ጠየቀ።ደምሴ ከድርጊቱ በኋላ በቦታው እንደሌለ ተነገረው።ውሎ አድሮ የተጎጂው ህይወት ማለፉ ተሰማ።ፖሊስ ፍለጋውን አጠናክሮ ደምሴን ማሰሱን ቀጠለ፡፤
ቀናት ተቆጠሩ። የአዲስ አበባ ፖሊሰ መርማሪ ዋናሳጂን አማረ ቢራራ ምርመራውን ከፍለጋ አጠናክሯል። በየቀኑ የሚገኙ መረጃዎች በመዝገብ ቁጥር 554/10 እየተመዘገቡ መሰነዳቸው ቀጥሏል።ተፈላጊው እየታሰሰ ነው። አልተገኘም። ከቀናት በኋላ አንድ የስልክ ጥሪ ወደ አንድ ፖሊሰ ዘንድ ደረሰ።
ፖሊሱ የደዋዩን ማንነት አውቋል።ቁጥሩን እንዳየ በጥንቃቄ ሊያዳምጠው ጆሮቹን አቆመ። የደወለው ተፈላጊው ደምሴ ነበር። ፖሊሱ የቅርብ ጓደኛው ነው።ድምጹን እንደሰማ ተለሳልሶ ሆነ ያለውን ይተርክለት ያዘ፡፡
ፖሊሱ ደምሴ የሚለውን ሁሉ አደመጠ።ከቀናት በፊት አንድ ደንበኛ የሆቴሉን መስታወት በድንጋይ እንደሰበረበት እየነገረው ነው። ድርጊቱ እሱን እንደሚያስጠይቀውና በዚሁ ምክንያት አገሩ እንደገባ አሳወቀው።
ፖሊሱ ጓደኛው በነፍስ ማጥፋት ተጠር ጥሮ እንደሚፈለግ ያውቃል። እሱ ዘንድ መደወ ሉም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እንደሆነ ተረድቷል።ፖሊሱ ይህኔ ለሙያው የገባው ቃልኪዳን ትውስ አለው። ጓደኛው እንዳይጠረጥር ተረጋግቶ አወራው። እንዳይሸሽ ነገሩን አቅልሎ አግባባው።ደምሴ በሁኔታው ተረጋጋ፡፡
ጥቂት ቆይቶ ደምሴ ለሳጂን ጓደኛው ናዝሬት እንደሚገኝ ነገረው። ሳጂኑ አሁንም ተረጋግቶ ነገሩን አቀለለው። ተመልሶ እንዲመጣና ስራውን እንዲቀጥል አግባባው። ደምሴ ምንም እንዳልተፈጠረ ራሱን አሳምኖ እዲስ አበባ ደረሰ።ፖሊሱ ጓደኛውን በካቴና አስሮ ለህግ አሳልፎ ሰጠ፡፡
ውሳኔ…
ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ደምሴ አበበ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል።ፍርቤቱ በተከሳሹ መዝገብ የቀረቡ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አጣርቶም ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግ,ጧል።በዕለቱ በሰጠው ፍርድም ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የሰምንት አመት ጽኑ እስራት ይቀጣ ሲል ወስኗል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2013