እስማኤል አረቦ
መሬት ለኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት ነው። መሬት ቅርስ ከመሆኑም ባሻገር በገጠርም ይሁን በከተማ የኢኮኖሚ ዋነኛ ምንጭ ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት የመሬት ዋጋ እየናረና ያለውም ኢኮኖሚያዊ ተፈላጊነት እየጨመረ በመምጣቱ በመሬት ላይ የሚፈጠሩ ውዝግቦች ሰፊውን ቦታ ይወስዳሉ። የፍርድ ቤቶችም አንዱ ጫና ከመሬት ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ውዝግቦች ናቸው።
መሬት በህገመንግስቱ ሰፊ እውቅናና ጥበቃ ከሚደረግላቸው ዘርፎች አንዱ ነው። መሬት ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር ከሰዎች ሰብዓዊ መብት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ በኢፌዲሪ ህገመንግስት ልዩ ጥበቃ ይደረግለታል። ይሁን እንጂ በከተማም ይሁን በገጠር ይህንን ህገመንግስታዊ መብት በመተላለፍ መሬት መሸጥ፤ መለወጥና ለበርካታ ዓመታት የማከራየት ተግባራት በሰፊው ይታያሉ። በከተማ የተወሰኑ ግንባታዎችን በማከናወንና ግንባታዎቹ የተሸጡ በማስመሰል መሬት የመሸጥና መለወጥ ተግባራት የተለመደ ነው።
በገጠርም ቢሆን የእርሻ መሬትን ከነተዘራው አዝርዕት የመሸጥና አልፎ አልፎም ለረጅም ዓመታት የማከራየት ልማዶች በስፋት ይዘወተራሉ። በበኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀጽ 40(4) በተቀመጠው መሰረት መሬት መሸጥም ሆነ መለወጥ አይቻልም። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳውም የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ አርሶ አደሩ ከመሬቱ ያለመነቀል መበቱን የሚያረጋግጥለት ነው።
ይሁን እንጂ በህገመንግስቱ ጥበቃ የተደረገለትን መሬትን የመሸጥና መለወጥ መብትን በመተላለፍም ሆነ ቀጥታ አርሶ አደሩን የሚመለከተውን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅን በመተላለፍ በርካታ ህገወጥ ተግባራት ሲፈጸሙ ይታያሉ። በተለይም በሚፈጸሙ ህገወጥ ተግባራት በሚፈጠሩ አለመግባባቶች በርካቶች የፍርድ ቤቶችን ደጃፍ ለማንኳኳት ይገደዳሉ። አለፍ ሲልም ፍርድ ቤቶቸ በሚሰጧቸው ብያኔዎች ባለመርካት ጉዳያቸውን ህገመንግስታዊ ጥሰቶችን ለሚመለከተው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲቀርቡ ይታያሉ።
የዛሬው የተናጋሪው ዶሴ ትኩረታችንም እዚሁ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ይሆናል። ወ/ሮ አለሚቱ ገብሬና አቶ ጫኔ ደሳለኝ በደቡብ ክልል የከፋ ዞን የጊምቦ ወረዳ ነዋሪዎች ናቸው። ወ/ሮ አለሚቱ የገጠር የእርሻ መሬት ባለቤት ሲሆኑ አቶ ጫኔ ደግሞ ከወ/ሮ አለሚቱ መሬት የተከራዩ ግለሰብ ናቸው።
አቶ ጫኔ እንደሚሉት ከወ/ሮ አለሚቱ ለ50 ዓመታት ያህል የሚቆይ የእርሻ የሚሆን የገጠር መሬት በኪራይ ወስደዋል። ከኪራይ ውሉም በተጨማሪ የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ አግኝተዋል።
በተቃራኒው ወ/ሮ አለሚቱ ያላቸውን የገጠር የእርሻ መሬት ማከራየታቸውን አልካዱም። ሆኖም ግን ያከራየሁት ለ5 ዓመት እንጂ ለ50 ዓመት አይደለም። ስለዚህም‹‹ ለአቶ ጫኔ የተሰጠው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ አግባብ አይደለም መሬቱ ለእኔ ሊመለስልኝ ይገባል›› የሚል አቤቱታ ያቀርባሉ። በዚህ ቅር የተሰኙት አቶ ጫኔ ጉዳያቸውን ይዘው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፤ ክስም ይመሰርታሉ። አለኝ የሚሉትን መረጃ አደራጅተውም ለጊምቦ ወረዳ ፍርድ ቤት አቤት ይላሉ።
በደቡብ ክልል የከፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን መመርመር ይጀምራል። አቶ ጫኔ ያቀረቡትን አቤቱታና ማስረጃ ይፈተሻል። በመጨረሻም ፍርዱን ለአቶ ጫኔ ያጸናል። ወ/ሮ አለሚቱም በፍርዱ ቅር በመሰኘት ይግባኝ እንዳይሉም ጉዳዩ ሰበር ሰሚ ችሎት እንደማያስቀርብ ፍርድ ቤቱ በተጨማሪ ውሳኔ አሳልፏል። በመጨረሻም ጉዳዩ የህገ መንግስት ጉዳይ ጥያቄ ስለሆነ ጉዳያቸውን ይዘው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤት ይላሉ።
ወ/ሮ አለሚቱ ገብሬ መጋቢት 27 ቀን 2005 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽፈው ባቀረቡት አቤቱታ በ1989 ዓ.ም ከአቶ ጫኔ ደሳለኝ ጋር ባደረጉት ስምምነት በገጠር የሚገኝ 2 ሄክታር የእርሻ መሬት ይዞታዪን ለ5 ዓመታት እንዲጠቀም ነው ያከራየሁት ቢሉም አቶ ደሳለኝ ግን ከወ/ሮ አለሚቱ ገብሬ ጋር የኪራይ ውል የተፈራረምነው ለ5 ዓመታት ሳይሆን ለ50 ዓመታት ነው በማለት በይዞታው ላይ የባለይዞታነት ማረጋገጫ ደብተር አውጥቶ ግብር እየከፈለ የሚጠቀምበት መሆኑን ያስረዳል።
ስለሆነም የገጠር መሬቱ ይዞታ ባለመብት መሆኑ ተረጋግጦ እንዲወሰንለት ለጊምቦ ወረዳ ፍርድ ቤት አቤቱታውን አቅርቧል። ወ/ሮ አለሚቱ በበኩላቸቸው በ1989 በተደረገ ውል ስምምነት 2 ሄክታር የገጠር የእርሻ መሬት ይዞታቸውን ለአቶ ጫኔ ደሳለኝ ያከራዩት ለ50 ዓመት ሳይሆን ለ5 ዓመት በመሆኑ እና የኪራይ ጊዜውም ያለቀ ስለሆነ መሬቱ ይመለስልኝ በማለት ተከራክረዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው የጊምቦ ወረዳ ፍርድ ቤትም ወ/ሮ አለሚቱ ከአቶ ጫኔ ጋር ያደረጉት የገጠር የእርሻ መሬት ኪራይ ውል ለ5 ዓመት ሳይሆን ለ50 ዓመት ነው። አቶ ጫኔ ከወ/ሮ አለሚቱ ባገኘው የኪራይ መሬት ይዞታ ላይም ለ16 ዓመታት ግብር በመገበር የባለይዞታነት ማረጋገጫ ደብተር ወስዶበታል በማለት የወ/ሮ አለሚቱ ክስ በፍትሃብሄር ህግ ቁ.1168 (1) እና 1845 በይርጋ ይታገዳል በማለት ወስኖ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም አያስቀርብም በሚል ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔው ከህገመንግስቱ አንቀጽ 40(4) እና አንቀጽ 35(7) ድንጋጌዎች ጋር ይቃረናል በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጉም እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
ጉባኤው በከሳሽ የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ክርክር በተነሳበት ይዞታ ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በማን ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝና ግብሩም በማን እንደሚገበር በተደረገው ማጣራት መሰረት የከፋ ዞን የጊምቦ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽ/ቤት በቁ.3443/Q-32 በቀን ሰኔ 11/2007 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ክርክር ከተነሳበት 2 ሄክታር የመሬት ይዞታ ውጭ 6.4ሄክታር የመሬት ይዞታ ለወ/ሮ አለሚቱ ገብሬ የተሰጣቸውና የባለይዞታነት ማረጋገጫ ደብተር በስማቸው የተመዘገበና ግብርም የሚገብሩበት ወ/ሮ አለሚቱ መሆናቸውን አረጋጧል።
አቶ ጫኔ ደሳለኝ ደግሞ ክርክር የተነሳበት 2 ሄክታር መሬትን ጨምሮ 4.2 ሄክታር የመሬት ይዞታ ያለውና በዚህ ይዞታ የባለይዞታነት ማረጋገጫ ደብተር አውጥቶበት ግብር የሚገብር መሆኑን አረጋግጦ አቶ ጫኔ ክርክር የተነሳበትን 2 ሄክታር ጨምሮ በ4.2 ሄክታር ላይ የበላቤትነት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ሊሰጠው የቻለውም ክርክር የተነሳበት ይዞታ በ1997 ዓ.ም ሲለካ ወ/ሮ አለሚቱ ተቃውሞ ባለማንሳታቸው መሆኑን ገልጽዋል።
አቶ ጫኔ ከወ/ሮ አለሚቱ ላይ በ1989 ዓ.ም በኪራይ በወሰደው የገጠር መሬት ይዞታ ላይ በስሙ የባለይዞታ ማረጋገጫ ደብተር የወሰደበት መሆኑን ከመዝገቡ መረዳት ተችሏል። የኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀጽ 40 (3) መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄርብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው በሚል የተደነገገ ሲሆን የዚህ ድንጋጌ ዋና ዓላማ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸውን ለማረጋገጥ የተደነገገ መሆኑን ስንመለከት ምንም እንኳን አቶ ጫኔ ከወ/ሮ አለሚቱ ጋር ያደረገው የ50 ዓመት የእርሻ መሬት የኪራይ ውል የሽያጭ ውል ነው ባይባልም አንድ አርሶ አደር ለ50 ዓመት ያህል መሬቱን ማከራየት አርሶ አደሩን ከመሬት የሚያፈናቅለው ተግባር ነው።
በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል መንግስት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁ.110/99 አንቀጽ 8(1) ፊደል/ ሀ/ ላይ አርሶ አደር ለአርሶ አደር መሬቱን ሲያከራይ እስከ 5 ዓመት ይሆናል የሚለውን ድንጋጌ ስንመለከት አርሶ አደሮች መሬታቸውን በማከራየት ሰበብ ከመሬታቸው እንዳይፈናቀሉ ጥበቃ ለማድረግ የተደነገገ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
ከዚህ አንጻር የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሲታይ አቶ ጫኔ በ1989 ዓ.ም ከወ/ሮ አለሚቱ ላይ ለ50 አመት በኪራይ በወሰዱት የገጠር መሬት የእርሻ ይዞታ ላይ የባለይዞታነት ማረጋገጫ ደብተር አውጥቼበታለሁ በማለታቸው ወ/ሮ አለሚቱ የሰጡትን የእርሻ መሬት ይዞታ እንዲያጡ የሚያደርጋቸው ስለሆነ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 40(4) የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው ከሚለው የህገመንግስት ድንጋጌ ጋር የሚቃረን በመሆኑ በወ/ሮ አለሚቱ የቀረበው አቤቱታ የህገመንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተስማምቶ የውሳኔ ሃሳቡ ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
የፌዴሬሽን ምክርቤትም የአጣሪ ጉባኤውን የውሳኔ ሃሳብ መሰረት በማድረግ በጉዳዩ ላይ የምክር ቤቱ የህገመንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።
ውሳኔ
በዚህ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደተረዳው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አቶ ጫኔ ከወ/ሮ አለሚቱ ላይ ለ50 ዓመታት በኪራይ የእርሻ መሬት ተከራይቻለሁ በማለት የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ከሚደነግገው ውጭ የባለይዞታነት ማረጋገጫ ደብተር አውጥቼበታለሁ በማለቱ ብቻ ወ/ሮ አለሚቱን ይዞታቸውን እንዲያጡ እና እንዲፈናቀሉ የሚያደርጋቸው ነው።
በመሆኑም የጊንቦ ወረዳ ፍርድ ቤት በክርክሩ ላይ የሰጠው ውሳኔ በህገመንግስቱ አንቀጽ 40(4) የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው ከሚለው የህገመንግስቱ ድንጋጌ ጋር የሚቃረን ስለሆነ በህገመንግስቱ አንቀጽ 9(1) ድንጋጌ መሰረት ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም በማለት ወስኗል።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013