ግርማ መንግሥቴ
መቸም በተዋጣለት የፈጠራ ስራ ውስጥ “ተምሳሌት”ም እንበለው “ትእምርት”ን ስራ ላይ ማዋል የሚጠበቅ ነው። የሚጠበቅ ብቻም ሳይሆን የተለመደም ነው። በስነቃልም በተመሳሳይ መንገድ ተግባራዊ ሲሆን ነው የኖረው።
እንደውም ጥናቶች እንደሚያሳዩትም ሆነ እኛም እንደምንገነዘበው ዘመናዊው ሥነጽሑፍ ይህንን ጥበባዊ አሰራርና ፋይዳውን የቀሰመው ከዚሁ ከስነቃል ሲሆን፤ ልዩነቱ ዘመናዊው ሥነጽሑፍ ከጊዜው ጋር እየዘመነ፤ በእውቀትና ክሂል እየታሸ መምጣቱና በቅርፅና ይዘት እየተራቀቀ መሄዱ ነው።
ልክ እንደ ፕሮፌሰሩ (ከታች) ሁሉ፤ እንደውም በላይ ትእምርት (Symbol)ን አብዝቶ የተጠቀመ ደራሲና ባለቅኔ ቢኖር ከበደ ሚካኤል (በ”ተረትና ምሳሌ” መጽሐፋቸው) ሲሆኑ “ፋኖስና ብርጭቆ”፣ “የብረት ድስትና የሸክላ ድስት”፣ “ጽጌረዳና ደመና” እና ሌሎች በርካቶች ስራዎቻቸው ከበቂ በላይ ማሳያዎች ናቸው።
ይህን ስንል ስለ”መሰላል” አንዳንድ ነገሮችን ለማለትና ወዳለንበት ሁኔታና ይዞታ በመምጣት “አንዳንድ ነገሮች”ን ለማንሳት ነው። (የጥላሁን ገሠሠን “አንዳንድ ነገሮች” አስገራሚ ሙዚቃ በትንሹ ከፍቶ ይህንን ጽሑፍ (በተለይም ግጥሙን) የሚያነብ ሰውና ያለዚህ ሙዚቃ የሚያነብ ሰው እኩል ስሜታቸው በጽሑፉ ወይም በግጥሙ ይነካል ማለት ዘበት ባይሆን እንኳን ትክክል አይደለም።)
መሰላል
መሰላል ለመውጣት
አለው ትልቅ ብልሀት፡፡
የላዩን ጨብጦ፤
የታቹን ረግጦ፣
ወደላይ መመልከት
እጆችን ዘርግቶ በሀይል መንጠራራት፡፡
ጨብጦ መጎተት የላዩን፣
ላይ ታች እንዲሆን፡፡
አንድ በአንድ እየረገጡ
መሰላል የወጡ፣
ብልሆች የማይጣደፉ
ሞልተዋል በያፋፉ፡፡
ዘርግተው የጨበጡትን መርገጥ
የመውጣት ሕግ ነው የማይለወጥ፡፡
ሲወርዱ ግን ያስፈራል
የረገጡትን ያስጨብጣል፡፡
(መስፍን ወልደማሪያም፣ እንጉርጉሮ (1967))
ሙሉ ግጥሙ ይህን ይመስላል። ስንኞቹ በራሳቸው ገላጭና ተናጋሪ፤ ለስሜታችን ብቻ ሳይሆን ለህሊናችንም ቅርብ ናቸው። መሰላል ወጪዎቹም ሆኑ ወራጆቹ ይታዩናል። ማን በህግና ማን ከህግ ውጪ፤ ማን በብልሀት፤ ማን ደግሞ በማን አለብኝነት እንደወጣ፤ እየወጣ፣ ሲወጣና ሲወርድ እንደነበረ ሁሉ “እንዲሰማን” የሚያደርግ ግጥም ነው። በተለይ በምድረ አፍሪካ ይህ የየዘመኑና መሪዎቹ፤ እንዲሁም ምስኪን አገራትና ህዝቦቻቸው ከላይ የተሰጣቸው እስኪመስል ድረስ መሰላሉን በአግባቡ የመውጣት ብልሀቱም ሆነ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ስለመኖራቸው እንካችሁ ያለን የለም።
ሁሉም ጋር ስንሄድ የምንመለከተው ነገር ሲወጡ የጨበጡትን ሲወርዱም እየጨበጡት አይደለም። የጨበጡትን ሲረግጡ እንጂ ሲወጡ የጨበጡትን ሲወርዱም ሲጨብጡት አናይም። ሲወጡ የጨበጡትንም ሲወርዱ ሲጨብጡ አይደለም። ባጭሩ የነበረው፣ ያለው (እና ወደ ፊትም የሚኖረው፤ አፍሪካ ለለውጥ ካልተዘጋጀች በስተቀር) ተመሳሳይ ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለም።
ለዚህ ደግሞ “የት ይደርሳሉ” የተባሉት የዩጋንዳው ሙሴቬኒ ለስልጣን ሲሉ እስከ ሕገ መንግስት ማሻሻል ጥግ ድረስ መሄዳቸው ነው። የምእራብ አፍሪካ አገራትም፣ ለአፍሪካ ህብረት እንኳን ሳያሳውቁ፣ ተሰብስበው ምርጫ ነክ ሕገ መንግስታዊ አንቀፆቻቸውን መለወጣቸውን ሰምተናል።
ይህ ግጥም ባለ15 ስንኝ ነው። ይሁን እንጂ በ15 መጻሕፍት ሊሸፈኑ የሚገባቸውን መሰረታዊ የዲሞክራሲ፣ ህገመንግስት፣ ስልጣን፣ የህዝብ አገልጋይነት፣ ሥነህግ፣ አምባገነናዊ ስርአት ወዘተ ጉዳዮችን ነው ድብን አድርጎ ቋጥሮ የያዘው።
ግጥሙ ከወረቀት ላይ ቃላት ድርደራ ባለፈ መሬት አውርደን ስንመለከተው አንድ፣ ሁለት – – – ብለን ቆጥረን ልናረጋግጣቸው በሚችሉ እውነታዎች የታጨቀ (የቆመበትም መሰረት ይኸው ነው) ሲሆን ይህ ደግሞ በአገራችን የፖለቲካና አስተዳደር ህይወትና ሂደት ውስጥ የአንድ ወቅት ክስተት ሳይሆን ያለ፣ የነበረ፣ ምናልባትም ወደፊትም ቶሎ የማይነቀል ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን (ፈጣሪ ከታረቀን ማለት ነው) አብሮን የሚቆይ መዥገር ባህርያችን ሆኖ የሚቆይ ነው። የአሁኑ የፖለቲካ “ስርአታችን”ም የሚያሳየን ይህንኑ እንጂ ሌላ አይደለም።
ገጣሚው በ1960ዎቹ የነበረውን የተጋጋለ የፖለቲካ ፍልሚያና የስልጣን ጥም ተመልክተው መሰላልን ይግጠሙ እንጂ ግጥሙ ግን ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ እስከ አሁን ድረስ፤ ምናልባትም ወደ ፊትም ያለውን የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊያንን ፓርቲ ተብዬ ፓርቲዎች ገበና አይን ከሰበከት እያገላበጠ የሚያሳይ የተዋጣለት ስራ ለመሆኑ መከራከር አይቻልም።
በተለይ ይህን ግጥም ኣጣጥሞ፣ ወቅቱን (1960ዎቹን) አስመልክቶ የተሰሩ ሌሎች ስራዎችን መርምሮና የነበረውን ሁኔታ ላገናዘበ ሰው፤ ከዛም አልፎ እስካሁን ድረስ ያለውን የሰከረና ያሳከረ፣ ስግብግብ ፖለቲካችንን ከተጣባው የዘር በሽታ ጋር አያይዞ ለቃኘ፤ ቃኝቶም ምን ያህል ሽክርክሪት (የሰሞኑ የ”ፍትሕ” የሽፋን ሥእል “ከደደቢት እስከ ደደቢት” እንዳለው) ውስጥ እንዳለን ይረዳልና ያኔ የገጣሚውን ጥልቀትና ብቃት፤ የግጥሙን ዘመን አይሽሬነት በሚገባ ይገነዘባልና “መሰላል ተመችቶኟል” ለማለት አይመለስም። በተለይ ጉዳዩ ከ”መሰላል” መጨበጥና መርገጥ አልፎ ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ እስከመግባት ማድረሱን ለተመለከተ ሰውየው ለትህትና ብለው እንጂ በዚህ መልክ የገለፁት ጉዳዩ በመጨበጥና መርገጥ እንደማያበቃ ስተውት እንዳልሆነ ይረዳል።
መሰላል ስለተገኘ ብቻ የተንጠለጠሉ፤ እየረገጡ የወጡና እየጨበጡ የወረዱ አምባገነን ሀያላን ብዛታቸው ቢቆጠር ህልቆ መሳፍርት ነው። የሰሩት ሀጠያት፣ የፈፀሙት ወንጀል (ሲሞካሽ “የሰብአዊ መብት ጥሰት” የምንለው)፣ የነቀሉትን ጥፍር ጨምሮ፣ ቢሰፈርና ቢለካ ኪሎም ሆነ ቶን አይገልፀውም። እንደው በቃ ጥላሁን ገሰሰ እንዳለው “ሆድ ይፍጀው” ብሎ ማለፍ ካልሆነ። ታዲያ ምን ያደርጋል፣ ትርፉ በየጓጥ ስርጓጉጡ መቅረትና የእሳት ራት መሆን፣ ገጣሚው “ሲወርዱ ግን ያስፈራል” እንዳሉት በየገደሉ ወድቆ መቅረት ሆነ እንጂ ሌላ ምንም።
በየትኛውም ቦታና ጊዜ፣ በየትኛውም መስፈርት፣ በማናቸውም ሁኔታና ይዞታ ክፉ ስራ “የረገጡትን ያስጨብጣል” እንጂ ሌላ ምንም አይነት ውጤትን አያስገኝም። ያዋርዳል እንጂ አያስከብርም፤ ያከስማል እንጂ ለፍሬ አያበቃም፤ ያስወቅሳል እንጂ አያስሞግስም። ባጭሩ ሄዶ ሄዶ መንግስቱ ኃይለ ማሪያም እንዳሉት ነው የሚኮነው – የታሪክ አተላ።
ይህ ደራሲው በ2007/8 አካባቢ ለንባብ ባበቁት “ዛሬም እንጉርጉሮ” ውስጥ በመካተት እንደገና የህትመት ብርሀን ለማየት የበቃው “መሰላል” በፈጣሪው አማካኝነት እንደገና ወደ እዚህ ዘመን እንዲመጣ ሲደረግ ያለ ምክንያት አይደለምና ከአሁኑ ወቅት ጋር አሰናስሎ ለማየት ሌላም እድል ይሰጣል።
ይህን እድል ተጠቅሞ “አሁን”ን በግጥሙ ውስጥ ለተመለከተ የንስር አይን ባለቤት ደግሞ ጉዳዩ ተጨባጭ ሆኖ ያገኘዋል። በየቦታው የረገጡትን የጨበጡ በሽ በሽ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን የመጨበጥ እድልን እንኳን ሳያገኙ በወጡበት የቀሩ ብዙዎች መሆናቸውን አፍታም ሳይቆይ ወዲያውኑ ይረዳል።
ፕሮፌሰሩ በአንድ “ኢትዮጵያ አትፈርስም” የጋዜጣ ጽሑፋቸው “ይህች ኢትዮጵያ የምትባል አገር ስንት የመከራ ወንዞችን ተሻግራለች! ገና ስንት ትሻገራለች! ስንት የግፍ ተራራዎችን አቋርጣለች! ገና ስንት ታቋርጣለች! ስንት የበደል ሰይፎችንና ጦሮችን አምክናለች! ገና ስንት ታመክናለች! ስንት የውጭ ኃይሎችን አሳፍራለች! ገና ስንቱን ታሳፍራለች! ስንት አምባገ- ነኖችን እያለቀሰች ቀብራለች! ገና ስንቱን ትቀብራለች! ጭቆና ከኢትዮጵያውያን ደም ሙልጭ ብሎ ወጥቶ በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በዳኝነት በጠራ ደም እስቲተካ ድረስ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ ትጸልያለች! እግዚአብሔርም ቃል ኪዳን አለበት ይሰማታል! የኃያላን ኃያል ኢትዮጵያ እንድትፈርስ አይፈቀድም።” እንዳሉት ሆኖ እንጂ አንዳንዶች ይህችን አገር ለማፍረስ ያልበጠሱት ቅጠል፣ ያልነጩት ሳር፣ ያልሄዱበት ርቀትና ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም። “ጉድጓዱን ማን ገባበት?” የሚለው (ይጠና?) ካልተባለ በስተቀር ማለት ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 20/1013