ከመኮንን አበበ ተሰማ
ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮችን አሳልፋለች ።በችግር የወጠራትም ግን በእሳት ተለብልቦ ተቃጥሏል ።በዓለም አገራት ሆነ በአፍሪካ እስቲ ኢትዮጵያ በተንኮል ሌላውን ትተናኮላለች የሚል ምስክር ይቅረብ።
ኢትዮጵያ በውጭም በውስጥም ተተናኳይ ይበዛባት ይሆናል እንጂ አንዳችም በሌላ ላይ ችግር አልፈጠረችም። በአፍሪካም ውስጥ ቢሆን ችግሮችን በድርድር ለመፍታት ከመሞከር በስተቀር በድንበር መግፋት የታማችበት ጊዜ የለም።
ዳሩ ግን አጭበርባሪዎች፣ ሸፍጠኞች፣ ሽብርተኞች እና ጉልበተኛች በዓለም ላይ እየጠነከሩ በሄዱ ቁጥር የኢትዮጵያ ድንበርን በአጭበርባሪዎች በጉልበተኞች እና በብልጣ ብልጦች እየተሸረሸረ ሄዷል ።ቅኝ ገዢዎች በሸረቡት ሴራ የአፍሪካ ሀገራት በድንበር ውዝግብ ግዜያቸውን እንዲያጠፉና ሁልጊዜም የግጭት መንስኤ እንዲሆን ቆጠሮ አስረው ሄደዋል።
የሌላው እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ በኩል የተረጋገጠ ይዞታዋን የአፍሪካ ሀገራት ቅኝ ገዢ ሰላቶች የነበሩ በተጫወቱት ቁማር በየጊዜው የአፍሪካ ቅኝ ተገዢዎች የነበሩ በኢትዮጵያ ወሰን ላይ በመንፏቀቅ ድንበር ለመግፋት ይሞክራሉ ።ግን አይሆንላቸውም እራሳቸውን እሳት ውስጥ አስገብተው በጭቅጭቅና በጭንቀት ለመኖር ያህል እንጂ ።
ሱዳን በህልሟ ያየችውን ሁሉ ከእንቅልፏ ብንን ስትል የኢትዮጵያ መሬት ፊቷ ድቅን ይልባታል። ምኞቷንም ለማስፈፀም በየጊዜው ትወራጫለች። ኢትዮጵያ በውስጥ ሰላሟ ስትዳከምና አልፎ አልፎም የውጭ ወራሪ ሲያጋጥማት የሱዳን ጠብ ጫሪነት ይበረታል ። አላመች ሲላት ደግሞ ወዳጅ መስላ ትታያለች።
ያለፈ ጭንቀትም ሆነ መልካም ነገር በሰው ዘንድ ቶሎ ይረሳል እንጂ ሱዳን ኢትዮጵያን ከጥንስሱ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሌት ተቀን ሲሰራ የነበረው የጁንታ ወያኔ መናኸሪያ እና አደራጅ አጋዥ ሀገር የነበረች ናት።
በኢትዮጵያውያን ዘይቤ አባባል የራሷ ሲያርባት የሌላውን ታማስላለች ይባላል ።ሱዳን እራሷ ቋሚ የሆነ መንግስት እንኳን የላትም በፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ በመንሳፈፍ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች።
በቅርብ ጊዜ ፕሬዝዳንት አልበሽርን ከስልጣን አስወግዶ ለስልጣን ሲሉ እርስ በርስ ሲበጣበጡ የነፍስ አባት ሆኖ ያረጋጋቸው የእኛው መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ነበሩ ። ኢትዮጵያ ምንግዜም ቢሆን ለሱዳን መድህን ነች ።በችግሯ ጊዜ ከጎኗ የምትቆም የክፉ ጊዜ ወዳጇ ነች ።
ሌላው ቢቀር በዳርፉር የነበረውንና አሁንም ስጋት ያለበትን የዳርፉር ግዛት በማረጋጋት ኢትዮጵያ የተጫወተችው ሚና በቀላሉ የሚረሳ መሆን አልነበረበትም።
ከደቡብ ሱዳንም በድንበርና በነዳጅ ክፍፍል እንደተቆራቆሰች ነው ያለችው። በውክልና ኢትዮጵያን ለመውጋት የወገነችላት ግብፅ ጋራም ከፍተኛ የድንበር ጭቅጭቅ እና ሁከት አለባት ።እንግዲህ ሱዳን ይህ ሁሉ ጫና እያለባት ኢትዮጵያ በሌላ ጉዳይ በተወጠረችበትና ችግር ላይ ባለችበት ወቅት የሌለ ምክንያት ፈጥራ የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግራ ለመቆጣጠር ሞክራለች ። ሆኖም ኢትዮጵያን ንክቶ በሰላም መተኛት አይቻልምና ሳይውል ሳያድር ሱዳን የኢትዮጵያ እግር ላይ ተደፍታ ማሪኝ ማለቷ አይቀርም።
ሀገራትን በዝርዝር ባልገልፅም መንግስት አልባ እየሆኑና እየፈራረሱ ያሉት ሀገራት ኢትዮጵያን የተተናኮሏት ናቸው:: ዶናልድ ትራንፕ ኢትዮጵያን በመተንኮሳቸው የሽንፈት ማቅ ተከናንበዋል ።ቀደም ሲልም በ1990ዎቹ ውስጥ ስለጁንታ ወያኔ አወዳደቅ በሞገደ ጋዜጣ ላይ ያስተላለፍኩት ትንቢቶች ሁሉ ደርሰዋል ።
በሀገር ውስጥም ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲዳክሩ የቆዩትና በመጨረሻም የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ከኋላው ለመውጋት የሞከሩት ከሀዲ ጁንታዎች ምን እንደደረሰባቸው ልጅ ለናቷ ምጥ አስተማረች እንደሚባለው እንዳይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሚያውቀው እዚህ ላይ መግለፁ አስፈላጊ አይሆንም። አሁንም ኢትዮጵያን የስንዝር ያህል የተተናኮለ ወዮላት እሳት ውስጥ ይገባል። ሱዳን ብቻ ሳትሆን ሁሉም ይጠንቀቅ።
ያለፈውንም ሆነ የአሁኑን ጠንቅ ሁሉ ያመጣብን ጁንታው ወያኔ ነው። ወያኔ ለሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ቆርሶ በመስጠት ከሃዲነቱን አረጋግጧል ።ስንቶች የተዋደቁለትን ዳር ድንበር በካሃዲነት አባዜ ለውጭ ጠላት አሳልፎ በመስጠት ታሪክ የማይዘነጋው ክህደት ፈጽሟል። የሆኖ ሆኖ ግን ኢትዮጵያን የነካ ዋጋውን ማግኘቱ አይቀርምና በጀግናው መከላከያ ሰራዊት ድምጥማጡ ጠፍቷል።
ጁንታ ወያኔ ሱዳንን ተጠግቶ ወይም ማረፊያ ቦታ አድርጎ ከሽፍትነት ወደ መንግስትነት ተለውጦ ኢትዮጵያን አሰቃይቶ ለ27 ዓመታት ከመግዛቱ ባለፈ አሁንም የጁንታ ወያኔ እርዝራዦች በውጪ ያሉትና ከሀገር ውስጥ ያመለጡት ከጠላት ጋር በመሆንና ጠላትን በመርዳት መልሰው ለማንሰራራት የማይቆፍሩት ድንጋይ የለም ።ሆኖም የወያኔ ማንሰራራት የህልም ቅዠት ካልሆነ በስተቀር ሞቶ የተቀበረ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ የማትራራና ለነኳት ሁሉ ልኳን የምታሳያቸው ትንታግ ሀገር ነች፤ ከጦርነትና ግጭት በፊት ጉርብትናን፤ መተሳሰብንና መተባበርን የምታስቃድም ችግሮች ሁሉ በውይይት እንዲፈቱ ተግታ የምትሰራ ዘመናዊነት የገባት ድንቅ ሀገር ነች ።የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር በሚማቅቁበት ወቅት ለነጻነት የታገለች ከእራሷ አልፋ ለሌሎች መብት የተሟገተች የነጻነት አርማ ነች።
ይህንን ውለታዋንና ለነጻነት የከፈልውን ተጋድሎ ችላ በማለት ሱዳንን የመሳሰሉ ሀገራት ጠብ ጫሪ ሲሆኑ ይታያሉ ።ኢትዮጵያውያን እንኳን አፍሪካ ሀገራትን ቀርቶ ዘመናዊ ጦር ታጥቆ የመጣውን የጣሊያንን ወራሪ ኃይል አሳፍረው በመለስ ታሪክ የማይረሳው ገድል ፈጽመዋል ። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የሰውን ሀገር መሬት አትፈልግም የራሷንም አሳፍል አትሰጥም ከነበረችበት ወደኋላም ወደፊትም ፈቀቅ አትልም።
የዓለም ሀገራትም መንጫጫት በእውነትና በህግ ላይ የተመረኮዘ ብይን መስጠት ይጠበቅባቸዋል ።ከዚያ ውጭ በወያኔ ቡችሎችና ተላላኪዎች አማካኝነት የሚደረጉ ፍትህ የማዛባት እንቅስቃሴዎች ድፍረት የተቀላቀለባቸው የተስፋፊነት አባዜዎችን ኢትዮጵያውያን አምርረው ይቃወሙታል ።
ኢትዮጵያውያን ከምንም ነገር በፊት ሰላምንና ዲፕሎማሲን ስለሚያስቀድሙ በሱዳን በኩል የተፈጸመው ድርጊት አሳፋሪና ድፍረት የተሞላበት ቢሆንም አሁንም ሱዳን ወደ ቀልቧ እንድትመለስ ከመምከር አይቆጠቡም።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2013