ምህረት ሞገስ
ፍቅር ሁሉን ያስረሳል። ማስረሳት ብቻ አይደለም፤ አፍቃሪው ያፈቀረው ሰው ምኑንም ቢወስድ ቅር አይለውም። ነገ መጣላት መለያየት ይኖራል ብሎ ማንም አያስብም። ለዚህም ይመስላል፤ ብዙ ሰዎች ተፋቅረው ሲጋቡ ስላላቸው ንብረት አይሰስቱም።
ስለዚህ ጋብቻ ሲፈፀም ‹‹ይህ ንብረት የግል ንብረቴ ነው›› ብለው አያስመዘግቡም። ‹‹ንብረቱ የጋራ ሀብታችን አይደለም፤ ንብረቱ የግል ንብረቴ ነው›› የሚለው ሃሳብ መገለፅ የሚጀምረው በተፋቃሪዎቹ መካከል ቅራኔ ሲፈጠርና ፍቺ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ብቻ ነው።
አቶ አለማየሁ መንግስቴ እና ወይዘሮ አዜብ ቱፋ ይባላሉ። የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ፤ በፍቅር ቆይተው ለጋብቻ በቅተዋል። በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደተለመደው ሁሉ ጋብቻቸውን ሲመሰርቱ፤ ‹‹ንብረቷ ንብረቴ፤ ንብረቱ ንብረቴ›› በሚያስብል እሳቤ የተሳሰረ ነው ለማለት ያስደፍራል። ምክንያቱም አንዳቸውም ‹‹ከጋብቻ ውጪ ተቆጥሮ እንዲመዘገብልኝ የምፈልገው የግል ሀብት አለኝ›› አላሉም።
አቶ አለማየሁ ወይዘሮ አዜብን ከማግባታቸው በፊት በ1994 ዓ.ም ለመኖሪያ ቤት መስሪያ የሚሆን 180 ካሬ ሜትር መሬት ከመንግሥት ወስደው፤ በ1999ዓ.ም ትዳር ይመሰርታሉ። ጋብቻው ሲፈፀም አቶ አለማየሁ መሬቱ ‹‹የግል ንብረቴ ነው›› አላሉም።
ወይዘሮ አዜብም የትዳር አጋራቸው የአቶ አለማየሁ ሀብትን የራሳቸው ሀብት እንደሆነ አምነው ተቀብለዋል። እርሳቸውም እንደአቶ አለማየሁ ሁሉ የኔ ሀብትም የእርሱ ሀብት ነው ብለው በማመን፤ ምንም ዓይነት ሀብት የግሌ ነው በሚል አላስመዘገቡም። ለዚህ ማሳያው ወይዘሮ አዜብ አሁን ላይ አቶ አለማየሁ የግል ሀብቴ ነው በሚሉት መሬት ላይ በጋራ ሀብታቸው ቤት መገንባታቸው ነው።
ወይዘሮ አዜብ አቶ አለማየሁ ከመንግሥት በወሰዱት መሬት ላይ ቤት ሲሰሩ የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 63 (1) ላይም እንደተቀመጠው ‹‹አንደኛው ተጋቢ የግል ሀብቱ መሆኑን ካላስረዳ በስተቀር ማንኛውም ንብረት በአንደኛው ተጋቢ ስም ብቻ የተመዘገበ ቢሆንም እንኳን የጋራ ሀብት እንደሆነ ይቆጠራል።›› የሚል በመሆኑም ጭምር ነው። ስለዚህ ወይዘሮ አዜብ የአቶ አለማየሁ መሬት የኔም የጋራ ሀብት ነው በማለት ወይዘሮ አዜብ ከአቶ አለማየሁ ጋር ተደጋግፈው እና ጎንበስ ቀና ብለው በመተባበር የመኖሪያ ቤት ገንብተዋል።
በጋራ ሀብታቸው በአዳማ ከተማ ቀበሌ 01 ሦስት ቤት ሰርተው ከጨረሱ በኋላ ካርታ እና ፕላን በ2005 ዓ.ም ወስደዋል። ይህንኑ የአዳማ ከተማ የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ኤጀንሲ አረጋግጦታል።
በእርግጥ በፍቅራቸው ወቅት አቶ አለማየሁ ይህንኑ ቤት የጋራ ንብረት መሆኑን በመጥቀስ፤ በ2007 ዓ.ም ለፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሀብትነት ማስመዝገባቸውም ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ነገር ግን አቶ አለማየሁ እና ወይዘሮ አዜብ በጋብቻ ተጣምረው አብረው ቢኖሩም፤ ባለመግባባታቸው ጋብቻቸው በፍቺ ይጠናቀቃል። እንደነበራቸው ፍቅር እና እንደፍቺው የንብረት ክፍፍሉ ሂደት ግን ቀላል አልሆነም።
ወይዘሮ አዜብ በማይንቀሳቀሱ እና በሚንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ የአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ክፍፍል ያድርግልኝ በማለት፤ አቤቱታ ያቀርባሉ። አቶ ዓለማየሁ ግን ‹‹ቤቱ ለወይዘሮ አዜብ አይገባም የግል ሀብቴ ነው›› ይላሉ።
ወይዘሮ አዜብ ‹‹አቶ አለማየሁ ቀደም ብሎ ባዶ መሬት የተረከበ ቢሆንም ለመሬቱ የተሰጠው ማስረጃ ተሰርዞ በሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም ካርታ ተሰጥቶናል። ቤቱን ሰርተን ያጠናቀቅነው በጋብቻችን ወቅት ነው። ባለቤቴ ይህንኑ ስለሚያውቅ በ2007 ዓ.ም ቤቱን ለፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በጋራ ሀብትነት አስመዝግቧል።››
በማለት የተከራከተሩ ሲሆን፤ አቶ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ ጋብቻቸው በ1999 ዓ.ም ከመመሥረቱ በፊት ተሰርቶ የተጠናቀቀ መሆኑን፤ ነገር ግን ለሴቶች የውበት ሳሎን የሚሆን አንድ ክፍል ቤት በጋብቻ ውስጥ ሆነው መሰራታቸውን የሰው ምስክር በማቅረብ ለፍርድ ቤቱ አስረዱ።
ፍርድ ቤቱም በጋብቻ ውስጥ የተሰራው አንድ ክፍል ቤት ተገምቶ የግምቱን ግማሽ ገንዘብ አቶ አለማየሁ እንዲከፍሉ ወስኗል። ንብረቱ በፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በጋራ ሀብትነት ተመዝግቧል መባሉ ሀብቱን የጋራ አያስብለውም በሚል ውሳኔ አስተላልፏል።
ወይዘሮ አዜብ፤ በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበዋል። ቀጥለውም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ያቀረቡ ቢሆንም የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ አፅንተዋል። በጉዳዩ ላይ የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩ አቤቱታ አያስቀርብም ሲል ወስኗል።
ወይዘሮ አዜብ አሁንም ተስፋ አልቆረጡም። የሕገመንግሥት ትርጉም ጥያቄ በመያዝ ጉዳዩን ለኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አጣሪ ጉባኤ አድርሰውታል። የምክር ቤቱ አጣሪ ጉባኤ ጉዳዩን የመረመረ ሲሆን፤ የአዳማ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ኤጀንሲም ጥያቄው ቀርቦለታል።
ኤጀንሲውም መሬቱ ምንም እንኳ በ1994 ዓ.ም በአቶ ዓለማየሁ ስም የተሰጠ ቢሆንም፤ ካርታ እና ፕላን የተሰጠው በ2005 ዓ.ም ማለትም ከጋብቻው በኋላ መሆኑን አረጋግጦ ለአጣሪ ጉባኤው ጥያቄ በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል።
ወይዘሮ አዜብ ‹‹አቶ አለማየሁ ለፌዴራል ሥነምግባር እና ፀረሙስና ኮሚሽን ያቀረበው ማስረጃ ያስረዳልኛል›› በማለታቸው፤ ጉባኤው ከኮሚሽኑ እና ከአዳማ የወረዳ ፍርድ ቤት ከአባሪ ጋር የተፃፈ ደብዳቤ አስቀርቦ የወይዘሮ አዜብ ማስረጃን አረጋግጧል።
በመጨረሻም አጣሪ ጉባኤው በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 63(1)ም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 79 (1) በተመሳሳይ ‹‹ አንደኛው ተጋቢ የግል ሀብቱ መሆኑን ካላስረዳ በስተቀር ማንኛውም ንብረት በአንደኛው ተጋቢ ስም ብቻ የተመዘገበ ቢሆንም እንኳ የጋራ ሀብት እንደሆነ ይቆጠራል።››
በሚል የተደነገገ ሲሆን፤ በዚሁ መሰረት ተጋቢዎች ከፍቺ በኋላ በአንድ ንብረት ላይ የግል በመሆኑ ክርክር የሚያነሱ ከሆነ በሕጉ የተቀመጠውን ግምት የሚያስተባብል ማስረጃ ሊያቀርቡ የሚገባ ሲሆን፤ በተያዘው ጉዳይ አመልካች ባቀረቡት ክርክር መነሻ የሕጉን ግምት የሚያጠናክር የሰነድ ማስረጃ የቀረበ ከሆነ ተቀባይነት ያገኛል የሚለውን ድንጋጌ በመያዝ ወይዘሮ አዜብ ተቀባይን የሚያገኙበትን ሁኔታ አረጋግጧል።
ወይዘሮ አዜብም፤ በፍርድ ቤቶች የሕጉን ግምት ሊያስተባብል የሚችል ማስረጃ ማቅረብ መቻላቸውን አጣሪ ጉባኤው ካረጋገጠ በኋላ፤ አቶ አለማየሁ የሰው ማስረጃ አቅርበዋል በሚል በጉባኤው የወይዘሮ አዜብ ማስረጃ ተቀባይነት አግኝቷል። በተጨማሪ የወይዘሮ አዜብ ማስረጃ፤ በማስረጃ አቀባበል ሕግ ወይም መርህ መሰረት በሰነድ የቀረበ ማስረጃ በሰዎች የማስረጃነት ቃል ሊስተባበል እንደማይችል በግልፅ የተደነገገ መሆኑም የወይዘሮ አዜብ ሃሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያደርግ መሆኑን ጉባኤው አምኖ አስቀምጧል።
ጉባኤው በተያዘው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቶች በግልፅ ይበልጥ ተቀባይነት ያለውን ማስረጃ ባለመቀበል ግልፅ ድንጋጌን በመጣስ የሰጡት ውሳኔ የወይዘሮ አዜብን በፍቺ ጊዜ ያላቸውን የእኩል መብት የሚጥስ መሆኑን በመጥቀስ፤ በሕገመንግሥቱ አንቀፅ 34(1) ‹‹በሕግ የተወሰነ የጋብቻ ዕድሜ ላይ የደረሱ ወንዶችና ሴቶች በዘር፣ በብሔር ወይም በሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግባቸው የማግባትና ቤተሰብ የመመስረት መብት አላቸው።
በጋብቻ አፈፃፀም በጋብቻው ዘመን እና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት አላቸው። በፍቺም ጊዜ የልጆቹን መብትና ጥቅም እንዲከበር የሚያደርጉ ድንጋጌዎች ይደነገጋሉ›› በማለት ፍርድ ቤቶቹ የተጠቀሰውን ድንጋጌ መጣሳቸውን አረጋግጫለሁ ይላል።
እንዲሁም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የአመልካችን ንብረት የማፍራት መብት የሚጋፋ ሲሆን፤ በሕገመንግሥቱ አንቀፅ 35 (7) ‹‹ ሴቶች ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብት አላቸው። እንዲሁም ውርስን በሚመለከት በእኩልነት የመታየት መብት አላቸው›› በሚል የተጠቀሰውን ድንጋጌ የሚጥስ ሆኖ የተገኘ መሆኑንም አጣሪ ጉባኤው አመላክቷል።
በተጨማሪ የወይዘሮ አዜብ እና የአቶ አለማየሁ ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቶች በግልፅ ድንጋጌ ባለመመራት የሰጡት ውሳኔ በሕገመንግሥቱ አንቀፅ 79(3) ‹‹ ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት ያከናውናሉ። ከሕግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩም›› በሚል የተጠቀሰውን ድንጋጌ የሚጥሱ ሆነው ተገኝተዋል። በማለት ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተላልፈዋል።
ምክር ቤቱ የአጣሪ ጉባኤውን የውሳኔ ሃሳብ መሠረት በማድረግ በጉዳዩ ላይ የምክር ቤቱ የሕገመንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በመመርመር የአዳማ ከተማ መሬት ልማት እና ማኔጅመንት ኤጀንሲ ባረጋገጠው መሰረት ወይዘሮ አዜብ ካቀረቡት ክርክር ጋር በሚቀራረብ መልኩ አቶ አለማየሁ ቤት ለመስራት በ1994 መሬት ቢወስዱም ካርታና ፕላኑን ያወጡት ትዳሩ ከፀና በኋላ በ2005 ዓ.ም ነው ብሏል።
ሆኖም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የወይዘሮ አዜብን ንብረት የማፍራት መብት የሚጋፋ ከመሆኑም በላይ፤ በሕጉ የተጠቀሰው በጋብቻ አፈፃፀም፣ በጋብቻ ዘመን እና በፍቺ ጊዜ ተጋቢዎች እኩል መብት አላቸው የሚለውን ድንጋጌ የሚጥስ መሆኑን አረጋግጠናል ካለ በኋላ፤ በመሆኑም በአጣሪ ጉባኤው ጉዳዩ የሕገመንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ማለቱ ተገቢ መሆኑን በመግለፅ፤ የአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ተሰጥቶ በየደረጃው ባሉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ፍርድ ቤቶች እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲፀና የተደረገው ውሳኔ በሕገመንግሥት አንቀፅ 9(1) መሠረት ተፈፃሚ ሊሆን አይገባም በማለት፤ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ በመወሰን ወይዘሮ አዜብ እስከ ሰበር ደርሰው ተከራክረው የተረቱበት ውሳኔ ተቀባይነት አይኖረውም በማለት ወስኗል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2013