አስመረት ብስራት
በዓል ሲነሳ ዝግጅቶቹን ማሰብ የተለመደ ነው። አባወራው የበግና የቅርጫ ገበያውን ሲያጧጡፍ እማ ወሪት ደግሞ ዶሮ ቅቤ ምን ቅጡ ሁሉንም የጓዳ ባልትና መከወኛዋን ስታዘጋጅ ትሰነብታለች።
የበዓሉ ቀን ሲደርስ አባወራው በአብዛኛው ቤት ውስጥ የተዘጋጀውን እየቀማመሰ የዓመት በዓል ፕሮግራሞችን በመገናኛ ብዙኃን ሲመለከት እማወሪት ደግሞ በኩሽና ሥራ ተጠምዳ ታመሻለችም፣ ታድራለችም።
ሴቶች በተፈጥሯቸው ኑሮ አድማቂ የቤት ሞገሰ ውበቶች ናቸው። በተለይ በዓል ሲሆን ደግሞ ያለነሱ ቤቱም አይደምቅ በዓሉም አይሞቅ። የበዓል ሥራ እጅግ አድካሚ ቢሆንም እንኳን የወግ ባህላችን አካል ነውና አይቀሬ ከሚባሉት የበዓል ዝግጅቶች አንዱ ሆኖ ይቀርባል። እና በዚህ ሁሉ መካከል በሥራ ላይ የምትሆነው እማወራ የቤቷንስ ነገር እንዴት አድርጋ ታሳልፈዋለች የሚለው ጥያቄ ትልቁና ዋንኛው ሆኖ ይነሳል።
በበዓል ሰው በቤቱ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ሰብሰብ ብሎ የሚመለከተው የዓመት በዓል ዝግጅቶች በሀገር ባህል ልብስ የደማመቁ ቆነጃጅት ኢትዮጵያውያን እንስቶቻችን ካልታከሉበት በምንም መስፈርት ደማቅ ሊሆን አለመቻሉ ደግሞ ሌላው ጉዳይ ነው።
እነዚህ በቤታቸውም በሥራቸውም ላይ በጣም ተፈላጊ የሆኑት ሴቶቻችን በዓልን እንዴት ሊያሳልፉት ይችላሉ የሚል ጥያቄ ይዘን በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሰሩ ሴት ጋዜጠኞችን የበዓል ውሎ ጠይቀናል።
ጥያቄያችንን በፍልቅልቅ ፈገግታዋ የመለሰችልን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ወቅታዊና ፖለቲካ ፕሮግራሞች አዘጋጅ ወይዘሮ ወይኒቱ አባተ ናት። ወይኒቱ ከአስር ዓመታት በላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ መስራቷን ተናግራ እንደ እድል ይሁን ሌላ አንድም ቀን የዓመት በዓል ዝግጅት ሥራ አልፏት እንደማያውቅ ትናገራለች።
በዓመት በዓል ወቅት ለወንድም ሆነ ለሴት ጋዜጠኛ ከተለመደው ሥራ በተጨማሪ ሌሎች የሚደራረቡሥራዎችና ጫናዎች ይኖራሉ ትላለች። በዓል በመሆኑ ለሚድያ ባለሙያዎች የሥራ መደራረብ ይከሰታል። ያንን የሥራ መደራረብ ሁሉም የሥራው አካል በኃላፊነት መንፈስ ሊያሳልፈው ተፍ ተፍ የሚልበት ወቅት በመሆኑ ጫናው ከፍ ያለ ነው።
በዓል ደግሞ ለሴት ጋዜጠኛ እንደተጨማሪ ሸክም ሆኖ ነው የሚመጣው። ሴት ቤት ውስጥ ተደራራቢ ሥራዎች፤ ከባድ የሥራ ጫና ይኖራል፤ ከወንዱ በተለየ ማለት ነው ትላለች። በተለይ በዓል ልጆች ላሏቸው ከቤተሰብ ጋር በዓልን ማሳለፍ የግድ ለሚላቸው ሴቶች እጅግ ከባድ ይሆንባቸዋል። ወላጆች በበዓል በልጆቻቸው መጠይቅ ያፈልጋሉ።
ከጓደኛ ከዘመድ ጋር ማክበር መጠያየቅ የተጠበቀ ይሆናል፤ ከሚሰሩበት ተቋም ደግሞ ተጨማሪ ሥራ ይጠበቅባቸዋል። ያኔ ሴቶች ሁልን ነገር በጥንካሬ ማለፍ የሚችሉበትን አቅም አሳይተው የማያልፉበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው ስትል ታብራራለች።
ሕፃናት ልጆች ሁልጊዜ እናታቸው ቤት እንድትሆንላቸው ይፈልጉ ይሆናል፤ ከዚህም ሌላ የእኛ ሀገር ባህላዊ ምግብ ዝግጅት ደግሞ ጫናው ከፍተኛ ነው የምትለው ወይዘሮ ወይኒቱ በጣም ብዙ ዋዜማዎችን ሥራ አምሽታ ሌሊት የቤቱን ሥራ ሰትሰራ ያሳለፈችባቸው ብዙ በዓሎችን ታስታውሳለች።
«በአጋጣሚ በዓል አንድም ቀን ከሥራ ውጪ ሆኜ አላውቅም። ጋዜጠኛ ከሆንኩ በኋላ በልጅነት ያሳለፍኳቸው የበዓል አከባበሮች ይናፍቁኛል። እኔ ሥራዬ ብዬ ብቀበለውም ልጆች ቤተሰቦቼ ግን መቀበል ይከብዳቸዋለ።» ትላለች። «ቤተሰቦቼ በአንድ ላይ ተሰባስበን በዓልን እንድናከበር ብንቀጣጠርም በበዓል ሥራ ተመድቤ ስቀር ሁልጊዜ ሲማረሩ ማየቴ በጣም እንዲሰማኝ ያደርጋል። እኛ እንደ ጋዜጠኛ ሁሉንም ተቀብለነው በደስታ የሌሎችን ደስታ እየፈጠርን መኖርን እንወደዋለን።» ብላለች።
ወይዘሮ ወይኒቱ ጋዜጠኝነት ሱስ ሆኖ ሥራና ኑሮን በጋራና በፍቅር የመስራት ልምድ መዳበሩን ተናግራ የመልካም ምኞት መግለጫዋን በዚህ መልኩ አስቀምጣለች።«በዚህ አጋጣሚ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እንኳን ለገና በዓል በሰላም በጤና በደስታ አደረሳችሁ።
በዓል ሲመጣ የምንሰባሰበው አብረን መሆኑ ደስታ ቢኖርም በየቦታው የምንሰማው የሞት የግጭት ዜና በዓልን በሰላም ለማሳለፍ ምቾት የማይሰጥ የሚጎረብጥ ስሜት ያለው በመሆኑ ይህ እንዳይኖር በመደማመጥ በዓልን ብናከብር መልካም ነው እላለሁ።»
ሌላዋ በስልክ ያነጋገርናት የአማራ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት ኤፍ ኤም ባህር ዳር 96 ነጥብ ዘጠኝ ሪፖርተር ትእግስት ተስፋዬ ናት። ትእግስት ዓመት በዓልና ጋዜጠኝነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች እንደሆኑ ነው የምትናገረው። እንደ እሷ ገለፃ የዓመት በዓል የሚደምቀው መገናኛ ብዙኃን በሚሰሩት ፕሮግራሞች በመሆኑ የእነዚህ ተቋማት አካል መሆኗንም በደስታ የምትቀበለው መሆኑን ትገልጻለች።
ዓመት በዓል ሲታሰብ ሁሉም ሰው ለበዓሉ ድምቀት የሚጥረውን ያህል አየር ላይ የሚውሉ በዓል በዓል የሚመስሉ ፕሮግራሞችን ለማሳመር መጣር ጋዜጠኛው አመዛኙን ጊዜ የሚያሳልፍበት ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ ቤት በዓል በዓል እንዲሆን የሚያደርጉ ዝግጅቶችንም ማድረግ የሴት ኃላፊነት መሆኑ ጫናው ድርብርብ እንዲሆን ያደርገዋል።
«በተቋማችን ሃይማኖታዊም ሆነ ሀገራዊ በዓል በተራ ቢሮ እንገባለን። ከበዓሉ ቀን ቀድሞ ፕሮዳክሽኖች ይሰራሉ፤ በበዓሉ ቀን ደግሞ መስተንግዶው ቦታውን ይረከባል። በዓልን ሥራ ላይ ሆኖም ቤት ይናፍቃል ለዚህም ነው አብዛኞቻችን ምንም በሌለበት እስቱዲዮ ውስጥ ዳቦው ቡናው ጠላው እያልን ስናወራ የምንውለው።» ትላለች።
የሴት ጋዜጠኛ ቤተሰቦች የሥራ ጉዳዩን አምኖ ለመቀበል በጣም ይቸገራሉ የምትለው ትዕግስት የሚፈለገውን ያህል ጥረት በማድረግ የማሳመን ሥራ እየሰራን የቤቱም የውጪውም አንዳይጎድል ይደረጋል ትላለች። የትዳር አጋሯ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ባይሆንም ሙያው የሚያስከፍለውን ዋጋ በመረዳቱ ሙሉ ለሙሉ የበዓሉን ሁኔታ በመምራት አጋርነቱን በአግባቡ በማሳየቱ ክብር ይስጥልኝ ስትል አመስግናለች። በአብዛኛው የቤቱን ኃላፊነት ባለቤቴ ስለሚወጣ ጭንቀቴን በእሱ ላይ ጥዬ በጥንካሬ ሥራዬን በውብ ሁኔታ እንዳከናውን ረድቶኛል ስትል አብራርታለች።
ጋዜጠኛ ትዕግስትም በበኩሏ በሥራ ላይ የገጠማትን በዚህ መልኩ አጫውተናለች። «አንድ ዓመት በዓል ነው እስቱዲዮ ውስጥ ሆነን ፕሮግራሙ ውብ እንዲሆን ተፍ ተፍ እንላለን። እንደተለመደው የዓመት በዓሉን ድባብ በምስል ለማስቀመጥ ዳቦው፤ ጠላው፤ ቡናው፤ሁሉም በዓይነት በዓይነት ተሰናድቷል።
በሙዚቃውም በፕሮግራሙም ዘና እያላችሁ እንደሆነ አንጠራጠርም እያልን በዓሉን ሞቅ ሸብረቅ እያደረግን እያወራን እያለ አንድ አድማጭ ደውሎ እኔ ብቻዬን ነኝ በዓልን ከእናንተ ጋር ለማሳለፍ እየመጣሁ ነው ብሎ ያሸማቀቀንን ቀን አልረሳውም።» ስትል ትዝታዋን አውግታናለች።
ጋዜጠኛ ትዕገስት በበኩሏ «ለመላው የሀገራችን ሕዝበ ክርስቲያን እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ። በዓሉን በሰላም በመከባበር በመፈቃቀር እንሳልፍ ዘንድ ምኞቴ ነው።» በማለት የመልካም ምኞት መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ሌላዋ እንግዳችን ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ጋዜጠኛ የሆነችው ሃይማኖት ክበበ ናት። የሚድያ ሰው በዓልን የሚያሳልፈው ሰዎች በቤታቸው የሚዝናኑበትን ነገር በማዘጋጀትና በማስተላለፍ ነው። የሥራው ባህሪ የግድ በዓልን በቤታቸው ለማሳለፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ጊዜ የማይሰጥ ነው ትላለች።
ሃይማኖት እንደምትለው በዓልን በቤት ውስጥ ማሳለፍ የቤተሰቦች ፍላጎት ቢሆንም ያንን ለማድረግ የሞያው ባህሪ አይፈቅድም። በአብዛኛው የበዓል ዝግጅት ሲሰራ ጋዜጠኞች ተራ በማውጣት የሚሸፍኑ መሆኑን ነው የምታስረዳው።
የበዓል ቀን በሥራ ላይ ማሳለፍ የግድ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች በርካታ በመሆናቸው በዓልን ቀድሞ አክብሮ ወደ ሥራ መግባት ወይም ከሥራ መጥቶ በዓል የማክበር ነገር የተለመደ መሆኑን ነው የነገረችን።
በዓልን ስናነሳ የቤትስራ ኃላፊነቶችም በይበልጥ ሴቶች ላይ የሚወድቅ በመሆኑ የቤቱ ሥራንም ሆነ የተቋምን ኃላፊነት አቻችሎ ለማለፍ የተቻልነውን ሁሉ ማድረግ የሴት ጋዜጠኛዋ ኃላፊነት ነው ትላለች።
በበዓል ወቅት በርካታ ገጠመኞች ቢኖሯትም አንዱን ልታጫውተን የወደደችው ጋዜጠኛ ሃይማኖት የአዲስ ዓመት በዓል ዝግጅት መድረክ መሪ ሆና ስትሰራ እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ቆይታ ነበር ወደ ቤቷ የሄደችው። በማግስቱ በአጋጣሚ በራድዮ የዓመት በዓል ዝግጅት መክፈቻ ላይ ነበር የተመደበችው።
በጠዋት ተነስታ 12 ሰዓት ላይ እስቱዲዮ መግባት ይጠበቅባት ነበር። የፕሮግራሙ ጀማሪ ብትሆንም የምሽቱ ድካም ተጨማምሮ ከእንቀልፏ የነቃችው 12ከ30 ላይ እንደነበረ ታስታውሳለች። ያን ቀን በተኛችበት ልብስ ፊቷን እንኳን ሳትታጠብ የአውዳመት ማለዳን በሩጫ ሄዳ ሥራ ገበታዋ ላይ ተገኝታ የሰራችበትን አጋጣሚ እንደማትረሳው ታስረዳለች።
ጋዜጠኛ ሃይማኖት «እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ። በዓሉ የጤና የሰላም የደስታ የፍቅር ይሆን ዘንድ ምኞቴ ነው» በማለት መልካም ምኞቷን አስተላልፋለች።
እኛም እንደ ዝግጀት ክፍላችን ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን። በዓሉ የስጦታ እንደመሆኑ እውነተኛውን ስጦታ ፍቅርን በመሰጣጠት የኢትዮጵያን አንድነት የምናበስርበት፤ የአብሮነት መልካም እሴቶቻችንን የምናዳብርበት፤ ፍቅርና ሰላምን እንደሸማ የምንለብስበት ያደርግልን ዘንድ ምኞታችን ነው። መልካም በዓል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2013