መልካምስራ አፈወርቅ
የድሀ ልጅ ነው። የልጅነት ህይወቱን በፈተና አሳልፏል። ወላጆቹ እሱን አስተምሮ ቁምነገር ላይ ለማድረስ የአቅማቸውን ያህል ሞክረዋል። እንዳሰቡት ሆኖ ቀለም እንዲቆጥር ከትምህርት የላኩት በጠዋቱ ነበር።
በቀለ እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ትምህርት ቤት ሲሄድ ደስታው ወሰን አጣ። ለእሱ ደብተር ይዞ መታየት፣ ተማሪ ተብሎ መጠራት ትርጉሙ ተለየ። ትምህርት ተጀምሮ ቀለም መቁጠር ሲይዝ ከባልንጀሮቹ አላነሰም። እነሱ የገባቸውን ያህል ተምሮ ከቤት ተመለሰ።
ማግስቱን ህጻኑ በቀለ ዳግመኛ ደብተሩን አነሳ። ጓደኞቹን ጠርቶም ከእነሱ ጋር እያወጋ ትምህርት ቤት ተጓዘ። ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው ክፍል የደረሱት ልጆች መምህሩ ሲመጡ ከወንበራቸው ተነስተው ተቀበሉ። ጥቂት ቆይቶ የተጀመረው ትምህርት ከትናንቱ ቀጠለ።
ቀድሞ ቀለሙን ያወቁት ተማሪዎች በትኩረት መከታተል ያዙ። በወጉ የገባቸውም ለተጠየቁት ምላሽ መስጠት ጀመሩ። መምህሩ አዲሶቹን ተማሪዎች እያገዙ፣ ለጎበዙት እያስጨበጨቡ አበረቷቸው። ይህ ሁሉ ሲሆን በቀለ አንዳች አልተነፈሰም።
በሌሎች ቀናት
አሁንም በቀለና የዕድሜ እኩዮቹ ትምህርት ቤት መሄድ ቀጥለዋል። የአንደኛ ክፍል ትምህርታቸውን በወጉ የጀመሩት የበቀለ ባልንጀሮች ደስታቸው አልቀዘቀዘም። ከዕውቀታቸው ሳያጎድሉ፣ ከተነገራቸው ሳይዘነጉ ከቀለሙ ዘልቀዋል።
ዝምታ የሚያበዛው በቀለ ግራ እንደገባው ነው። መምህሩ ስለቆይታው ሲጠይቁት አይመልስም። ስለተረዳው እንዲያስረዳ ሲጋበዝ አንዳች አይተነፍስም። የበቀለ ልማድ ተደጋገመ። ባልንጀሮቹ ድርጊቱን ከስንፍና እየቆጥሩ አላገጡበት። እራሳቸውን ከእሱ መዝነው ማነሱን ሊያሳዩት ሞከሩ። አዲሱ ተማሪ ሆድ ይብሰው ጀመር። እያደር ራሱን አገለለ ። በዝምታም አንገቱን ደፋ ።
ከጥቂት ጊዚያት በኋላ የበቀለ ችግር ታወቀ። ዓይኑ በወጉ አጣርቶ ማየት አይችልም። እንዲህ መሆኑ ፊደሎቹን በቅርበት እንዳይለይ አግዶታል። በአግባቡ አለመማሩም ከሌሎች አቻ እንዳይሆን ሰበብ ፈጥሯል። ይህን ያወቀው ልጅ ብስጩ ባህርይ መገለጫው ሆነ።
መምህራኑ ችግሩን ተረድተው ሊያግዙት ሞከሩ። ከፊት ተቀምጦ እንዲማር ቅድሚያውን ሰጡት። በዕድሎ ተጠቅሞ ማየት የጠላውን ፊደል ሊቆጥር ጀመረ። እንደታሰበው አልሆነም። ወትሮም ከዓይኑ ያልገቡት ቀለማት ዳግመኛ አመጹበት። ይሄኔ ትንሹ ልጅ ንዴቱ ጨመረ። በየሰበቡ የሚፈጥረው ጠብ ከበርካቶች አላስማማው አለ።
ተማሪው በቀለ ንዴቱን ተከትሎ ሌላ ችግር ይታይበት ጀመር። በተበሳጨ ቁጥር አዙሮ የሚጥለው ልማዱ ደጋገመበት። ይህን ያዩ ጓደኞቹ ይበልጥ ሸሹት። ጉዳዩን አውቀነዋል ያሉትም ችግሩ ልክፍት መሆኑን ያስወሩ ያዙ።
አሁን ብዙዎች በቀለ ልክፍት እንዳለበት አውቀዋል። በተበሳጨ ጊዜም ህመሙ እንደሚጥለው ተረድተዋል። ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ›› የሆነበት ተማሪ የትምህርቱ ነገር አልሆነለትም። እንደምንም ሊቆጥር ፣ ሊለየው የሚሻው ፊደል ልክፍት በተባለ ደዌ ይሰናከልበት ያዘ።
ውሎ አድሮ
ከቀናት በኋላ በቀለ ትምህርቱ አስጠላው። ክፍል ደርሶ የሚገጥመውን ሲያስታውስ መሳቀቅ ጀመረ። ይሄኔ አበክሮ ማሰብ የያዘው ውስጠቱ ከቤት እንዲውል ሹክ አለው። ሁሌም ጓደኞቹ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ያያል። ነገር ግን አብሯቸው መሆን አልፈለገም። በአይኑ እየሸኘ ከቤት መዋልን ለመደ። ከእናቱ ጋር ሲሆን ያጣውን ፍቅር ያገኘ መሰለው። ለጊዜው አብሮት የከረመ ንዴት ገለል አለለት።
ዓመቱ ተጠናቆ ትምህርት ቤት ተዘጋ። የእረፍት ጊዜ አልፎ መስከረም ጠባ። በቀለ እንደአምናው ለአዲስ ትምህርት አልተዘጋጀም። አሁንም ባልንጀሮቹን ባሻገር እያየ ሸኛቸው። እሱና ትምህርት እስከወዲያኛው ተለያዩ።
አሁን በቀለ ስለትምህርት አያስብም። ክፍል ገብቶ ከፊደል ጋር ግብግብ አይፈጥረም። በማንነቱ የሚያፌዙ፣ የሚቀልዱ ባልንጀሮቹ ጉዳይም ጉዳዩ አይደለም። ዛሬ እሱን የሚያስጨንቀው ራስን መቻል ብቻ ሆኗል።
በቀለ በዕድሜ መጎልበቱ ጥንካሬ ሆኖታል። አቅመ ደካማ እናቱን በስራ ለማገዝ አይቦዝንም። በጉልበቱ ድካም፣ በላቡ ወዝ ከሚያገኘው ገንዘብ እየቆጠበ ያሻውን ይገዛል። የገንዘብን ጥቅም ሲያውቅ ስራን ማዘውተር ልምዱ ሆነ።
ልጅነቱ አግዞት የታዘዘውን ሁሉ ይሰራል። በዋጋ ተስማምቶም ከተባለበት ተሸክሞ ያደርሳል። ቀኑን ሙሉ ሲሮጥ የሚውልበት ስራ የልፋቱን አሳጥቶት አያውቅም። አንዳንዴ አለመማሩን ሲያስብ የበታችነት ሊሰማው ይሞክራል። መልሶ የሆነውን ሲያስታውስ ግን ራሱን ያጽናናል።
የአሜሪካን ግቢ አካባቢው የነበቀለ ሰፈር ነው። ሰፈሩ በሮጦ አዳሪና ነጥቆ ነዋሪዎች ይታወቃል። አብዛኛው ሰው ራሱን የሚያሳድረውም በየምክንያቱ በሚያገኘው ገቢ ነው። ስፍራው በተሰረቁ ዕቃዎች ሽያጭና ሱስ ባጠቃቸው ወጣቶች ይታወቃል።
ስለ አካባቢው የሚያውቁ ብዙዎች ንብረት በጠፋቸው ጊዜ ወደስፍራው ያቀናሉ። የራሳቸውን ዕቃም ተደራድርው ተከራክረው ይገዛሉ። ይህ አይነቱ እውነት ለአካባቢው ብርቅ አይደለም። ዘራፊዎችና ደላሎች የራስን ንብረት ለራስ ለማሸጥ መትጋታቸው ነውር ሆኖ አያውቅም ።
በቀለና ጓደኞቹ በመልከ ብዙው የአሜሪካን ግቢ ክፉ ድርጊቶችን ሲቃመሱ አድገዋል። ሲሰርቁ፣ ሲሸጡና ሲደልሉ ኖረዋል። ቆይቶ ሰፈሩ ለልማት ተፈለገ። በርካታ ቤቶችም እንዲፈርሱ ሆነ። የመፍረስ ተራው ያላገኛቸው ቤቶች ነዋሪዎችን ይዘው ቀጠሉ። ስፍራውን የሻቱ የጎዳና ነዋሪዎች በፈረሱ ግድግዳዎች ተተግነው መዋል ማደር ያዙ።
አካባቢው እንደተጎሳቆለ ጎስቋሎችን አቅፎ ያድራል። ቀን ህይወት የምታሮጣቸው ምሽቱን ከድካማቸው ሊያርፉ በየጥጉ ይደርሳሉ። ከነዚህ አብዛኞቹ ጎን ለጎን ተቀምጠው፤ ጀርባ ለጀርባ ገጥመው ሙቀት ይጋራሉ። ይህ አልበቃ ያላቸው፤ እሳት እያነደዱ፣ ቤንዚን እና ማስቲሽ ይስባሉ። ለቅዝቃዜው መላ ያጡለት ደግሞ እራፊ ቡትቶ እየተጓተቱ ከሌሊቱ ውርጭ ጋር ይታገላሉ።
በፈረሱት ቤቶች መሀል ህይወትን የሚጋሩ ባልንጀሮች አካባቢውን ያውቁታል። አብዛኞቹ አብሮ አደጎች ናቸው። በስፍራው ሲቦርቁበት አድገዋል። በአካበቢው ክፉ ደግን አልፈዋል። ሰፈሩ ሲፈርስ መንደሩን ያልተውት አንዳንዶች ማደሪያቸውን ከግድግዳዎቹ ጥግ ካደረጉ ሰንብተዋል። ጣራ አልባ ቤቶቹ የቀረቧቸውን ያስጠጋሉ። የፈለጓቸውን ያቀርባሉ።
የነ በቀለ ቤት ካልፈረሱት አንዱ ነው። በዚህ ሳቢያም መላው ቤተሰብ ሰፈሩን አልለቀቀም። አንዳንዴ በቀለ እሳት እየሞቁ ከሚያድሩ ባልንጀሮቹ ዘንድ ያመሻል። ሌቱን አጋምሶም ወደቤቱ ያመራል። ይህ ድርጊት ለበቀለ የየዕለት ልማዱ ነው።
ሰኔ 15 ቀን 2009 ዓ.ም
የሰኔ ወር ተገባዷል። ቀን ጠንክሮ የዋለው ሀሩር ምሽቱን በብርድ ይመላለስ ይዟል። ለክረምቱ መግባት ምልክት መስጠት የጀመረው ቅዝቃዜ በስስ ካፊያ እየታጀበ ነው። የአሜሪካን ግቢ ፍርስራሽ መንደሮች ዛሬም እንግዶችን አላጡም። በግድግዳዎች ጥግ አረፍ ያሉት ደጅ አዳሪዎች ከጨለማው ትግል ይዘዋል።
ምናምኑን ከእሳት እየጨመሩ፣ እንጨት ካርቶኑን ያነዳሉ። የእርስ በርስ ወጋቸው እንደወትሮው ነው። ከነዚህ መሀል ጥቂቶቹ አጥብቀው የያዙትን ማስቲሽ ከአፋቸው ለጉመው ለአፍንጫቸው ያደርሳሉ። መልዕክቱ ከውስጣቸው ሲደርሰ ሁሉን የረሱት ይመስላል። በአካላቸው የወረደው ውርጭ ለአፍታ ለቀቅ ያደርጋቸዋል።
ጨዋታው ደርቷል፤ እንደተለመደው ብሽሽቅ የያዙት ቡድኖች መሀላቸው መደማመጥ የለም። ድርጊታቸው ሁሉ ብርዱን ለመሸሽ እንደሆነ ያሰታውቃል። በቀለ ከመሀላቸው ተቀምጦ ከእሳቱ ሙቀት መጋራት ይዟል። የሰዓቱ መግፋት ያሳሰበው አይመስልም።
አሁን ከሌሊቱ ሰድስት ሰዓት ተኩል ሆኗል። ድንገት በባልንጀሮቹ የደመቀው ጨዋታ ዝምታ ዋጠው ። የሁሉም ዓይን ወደ አንድ አቅጣጭ ተሰክቶ ትኩረታቸው ተሳበ። ሳያስቡት አጠገባቸው የደረሰችውን ወጣት አፈጠጡባት። ልጅቷ የከፋት ይመስላል። በዝምታ እንደተዋጠች ስትቀርባቸው ፈራ ተባ እያለች ነው።
ጎስቋላዋ ወጣት የረባ ልብስ አልደረበችም። በአሮጌ ሱሪዋ የተሸፈነው አካሏ የጠረቃ አይደለም። በወጉ ያልተያዘው ዞማ ጸጉሯና ድካም ያጠላበት ገጽታዋ ማንነቷን ያሳብቃሉ። መራብ መጠማቷን ያልሸሸገው ከናፍሯ እህል ውሀ እንዳለየ ይናገራል።
ሁኔታዋን ያስተዋለው በቀለ ከጓደኞቹ መሀል ተሰፈንጥሮ ተነሳ። አጠገቧ ደርሶም ምን እንደምትሻ ጠየቃት። ወጣቷ በብርድ እየተንዘፈዘፈች ማደሪያ እንደምትፈልግ ነገረችው። በቀለ ለጥያቄዋ ምላሽ ለመስጠት አልዘገየም። እጁን በትከሻዋ እያኖረ ከእነሱ ጋር ማደር እንደምትችል አሳወቃት።
አሁን ወጣቷ በእሳት ዙሪያ ከበው ጨዋታ ከያዙት ባልንጀሮች መሀል ገብታለች። ሙቀቱ ከአካሏ ሲደርሰ ቀድሞ የታየባት ድብርት ለቋታል። አሁንም እሳት አንዳጆቹ ምናምኑን እየጨመሩ ነው። በወጉ የጋመው ፍም እየተቆሰቆሰ ለበረዳቸው መድህን ሆኗል።
ከጓደኛሞቹ መሀል አንደኛው ከሌሎች ይበልጥ የምሽት እንግዳዋን መቅረብ እየሞከረ ነው። እጇን በእጁ እያሸ፣ አካሏን በአካሉ ይዳስሳል። የባጥ የቋጡን እየቀባጠረ ያጫውታታል። ጥቂት ቆይቶ ልጅቷን ወደ አንድ ጥግ ወሰዳት። የመቃወም ምልክት አላሳየቸውም።
ሁኔታው የገባቸው አምስቱ ጎረምሶች ጥንዶቹ የሄዱበትን ቦታ ባሻገር እያዩ በአይናቸው ተናበቡ። የባልንጀራቸው ቀድሞ መሄድ ያበሸቃቸው ይመስላል። ጥቂት ቆይቶ ቀድሞ የሄደው ጎረምሳ ተመልሶ መጣ። የእሱን መመለስና የእሷን አለመምጣት ያስተዋለው ሁለተኛው ወጣት ጓደኛው የነበረበትን ቦታ ተክቶ ስፍራውን ተቆጣጠረ።
ወጣቷ ሁለተኛው ሰው መምጣቱን ባየች ጊዜ ድርጊቱን ለመቃወም ሞከረች። እየታገለች እና እየገፋተረች ላለማስቀረብ ጣረች አልቻለችም። ጉልበተኛው ጎረምሳ እጇን ጠምዝዞ ያሰበውን ፈጸመ።
እሱ ቦታውን ለቆ ወደነበረበት ሲመለስ ሶስተኛው ጎረምሳ ተከተለ። ወጣቷ ከወደቀችበት ሆና እየጮኸች ልትታገለው ሞከረች። የሰማት የለም። እሱም እንደጓደኞቹ ያሰበውን አድርጎ አራተኛውን ሰው ሊተካ ቦታውን ለቀቀ።
አራተኛና አምስተኛውን ወጣት ጨምሮ ነውረኛ ድርጊት የፈጸሙ ባልንጀሮች ያደረጉት አልበቃቸውም። ባልተገባ ድርጊት በልጅቷ ላይ ተፈራረቁ። ያሻቸውንም ፈጸሙ።
ይህ ሁሉ ሲሆን የእንግዳዋ ድምጽ እንደቀድሞው አልሆነም። ለመጮህ ለመታገል አልሞከረችም ። የደፋሪዎቿን ጥቃት የመቋቋም አቅሙ አልነበራትም። አምስቱ ጎረምሶች ያሻቸውን እንደጨረሱ በቀለ ስድስተኛው ተረኛ ሆኖ ተጠጋ ። አጠገቧ ደርሶም አፏን አፍኖ እጇቿን ይዞ ደፈራት። ያሰበውን ሲጨርሰ አካሏ እንደበረዶ መቀዝቀዙን አወቀ። መዳከሟ ሲገባው ውሀ አምጥቶ ደረቷ ላይ እያፈሰሰ ቀሰቀሳት። ምላሽ አልሰጠችውም። መሞቷን ሲረዳ አካባቢውን ለቆ ተሰወረ።
የፖሊስ ምርመራ …
ማለዳ ከፈረሰው የአሜሪካን ግቢ መንደር የደረሰው የፖሊስ ቡድን የሟችን አስከሬን በጥንቃቄ መርምሮ አነሳ። በአካባቢው ያገኛቸውን እማኞች ለጥያቄ አቅርቦም ምርመራውን ቀጠለ። የወንጀሉን ጉዳይ የያዘው መርማሪ ዋና ሳጂን መስፍን ሀይለሚካኤል በመረጃዎች እየታገዘ የተጠርጣሪዎችን ዱካ አሰሰ። በየዕለቱ የሚገኛቸውን ጉዳዮች በዶሴው እያሰፈረም በመዝገብ ቁጥር 066/10 ላይ አኖረ።
ከቀናት በኋላ ከስድስቱ ተጠራጣሪዎች መሀል በቀለ ካለበት ተይዞ በህግ ጥላ ስር ዋለ። በቀለ ድርጊቱን ያለመፈጸሙን ጠቅሶ ወጣቷ በሌሎች ባልንጀሮቹ ተደፍራ ስለመሞቷ ተናገረ። ፖሊስ አላመነውም። የዕምነት ክህደት ቃሉን ተቀብሎ ክስ ይመሰረትበት ዘንድ መዝገቡን ለዓቃቤ ህግ አሳለፈ፡፡
ውሳኔ
ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሹ በቀለ ደጀኔ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል። በቀለ ድርጊቱን አምኖ በመቀበሉና በማስረጃዎች በመረጋገጡ ጥፋተኝነቱን ተረጋግጠዋል። በዕለቱ ፍርድ ቤቱ ባሳለፈው ብይንም በቀለ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ስምንት ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጣ ሲል ወስኗል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013