መልካምስራ አፈወርቅ
ደቡብ ክልል ቱለማ ቀበሌ ያፈራት ጨቅላ ከፍ እስክትል በወላጆችዋ እንክብካቤ አደገች። እድሜዋ ሲጨምር እንደ እኩዮቿ ትምህርት ቤት መሄድ ነበረባት። ቤተሰቦቿ የትምህርት ፍላጎቷን አይተው የሚያስፈልገውን አሟሉላት።
ቀለም መቁጠር የጀመረችው ልጅ የልቧ ደረሰ። ደብተር ይዛ ከትምህርት መዋሏ ደስታ ፈጠረላት። አንደኛን ክፍል አልፋ ሁለተኛ ስትዘልቅ የነገውን እያሰበች ተጓዘች፤ ብዙም ባይሆን በእነሱ ቀዬ የተማሩ ወጣቶችን ታውቃለች። ሁሉም ክብር ይሰጣቸዋል። የፈለጉትን ለማንበብ፣ ሂሳብ ለመስራትና ለመጻፍ ብቁ ናቸው።
ደስታ እነሱን ስታስብ ፊቷ ይፈካል። ስለ ነገው መልካሙን ታልማለች። ከፍ ስትል የሚሆነውን እያሰበችም በራሷ ትመካለች። ሶስተኛ ክፍል ስትገባ ወላጆቿ ትምህርት ቤት እንዳትሄድ ከለከሏት። ደስታ ለምን? ስትል ጠየቀች። ከዚህ በኋላ እሷን ማስተማር እንደማይችሉ ነገሯት።
ደስታ የቤተሰቦቿን ሁኔታ ጠንቅቃ ታውቃለች ። ለእሷ ትምህርት የሚተርፍ አቅም የላቸውም። እውነቱን ቢገባትም ከልቧ ተከፋች። ጓደኞቿ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እያየች አነባች፤ አለቀሰች።
ልጅነት ሆነና ጥቂት ቆይታ ሁሉን ረሳች። ከወላጆቿ የስራ ድርሻን ስትረከብ የትናንት ተስፋዋ ጥሏት ሸሸ። ውሎ አድሮ እርሻ መዋልን ስትለምድ ጉልበቷን መገበር ያዘች። ትምህርት ይሉትን ትታ ዓላማና ግቧን ቀየረች። የጠዋት ማታ ልምዷ ወላጆቿን ማገዝ ሆነ።
ዕድሜዋ ከፍ ሲል ልቧ አርቆ ማሰብ ጀመረ። ከእነሱ መንደር በርከት ያሉቱ ወደ ከተማ ዘልቀዋል። አብዛኞቹ የእሷ እኩዮች ናቸው። ከእነዚህ መሀል ጥቂት የማይባሉት ጥሩ ገቢ እንዳላቸው ታውቃለች።
አዲስ አበባ ያሉ የአገሯ ልጆች አንዳንዴ ወደመንደሩ ብቅ ይላሉ። ይህኔ የደስታ ዓይኖች የተለየ ነገር ያስተውላሉ። ሁሉም በአለባበስ የተዋቡ፣በአነጋገር የተለዩ ናቸው። ቀድሞ በዚህ መልኩ የማታውቃቸው ወጣቶች ተለውጠው ስታይ ይገርማታል። ተመልሰው ሲሄዱ ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብና ስጦታ ያበረክታሉ።
ደስታ እነሱን ባየች ቁጥር እግሯ ለመንገድ ይጣደፋል። አገር ቤት ተቀምጣ ከእርሻ መዋልን ትጠላለች። ሁሌም ዓይኖቿ ባሻገር እያዩ መሄድን ይናፍቃሉ። የደስታ ልብ ቆርጦ ሊርቅ ወስኗል። እሷም እንደሌሎች ከተሜ ሆና መለወጥ ተመኝታለች። በአለባበስ፤ በአነጋገሯ መቀየር ምኞቷ ከሆነ ሰንብቷል። ነገ ወደቤት ስትመጣ ለወላጆቿ ብዙ ማድረግ ትሻለች ።
ምኞት፡- በአዲስ አበባ
ደስታ ስታቅድ የቆየችው ሀሳብ ከግብ ደርሷል። የተወለደችበትን ቀዬ ለቃ የከተማን ኑሮ መወሰኗ ትክክል መሆኑን አምናለች። ሁሌም እንደምታየው አዲስ አበባ ከሄዱት ብዘዎቹ ተለውጠዋል። ገንዘብ ይዘው አምሮባቸው ይኖራሉ። እሷም ከእነሱ አንዷ ለመሆን እግሯ ሸገርን ረግጧል።
አዲስ አበባ ስትገባ በርከት ያሉ ሰዎች አወቀች። አብዛኞቹ ያገሯ ልጆች ናቸው። ሁሉም በመረጡት ስራ ሲሮጡ ይውላሉ። አቅማቸው እስኪጠነክር በአንድ ቤት ተበራክተው መኖራቸው ተለምዷል። እንዲህ መሆኑ ለገንዘብ ቁጠባ ነው። በአኗኗራቸው አይከፉም።
ደስታ ኮልፌ አካባቢን ለመኖሪያ መርጣለች። እንደሌሎች ሁሉ የቤት ኪራዩን ተጋርታ የድርሻዋን ትከፍላለች። እሷ የምትኖርበት ቤት ስምንት ሴት ተከራዮች አሉበት ። ሁሌም ሰላም የሌለው ጎጆ በሴቶቹ ጠብና ጭቅጭቅ ታምሶ ይውላል። አብዛኞቹ ተከራዮች የሚጣሉበት ምክንያት አያጡም። አንዳንዶቹ በሚጠቀሙባቸው ዕቃዎች፣ ሌሎቹ በሚለብሷቸው ልብሶች፣ ገሚሶቹ ደግሞ በሚያመጧቸው አሉባልታዎች ይጨቃጨቃሉ።
ደስታ አዲስ አበባ ከገባች ወዲህ ጸባይዋ ተቀይሯል። በየአጋጣሚው ከሰዎች የሚያጋጫት ምክንያት በርክቷል። አንዳንዴ ጠቡ ሲካረር መደባደብ ያምራታል። ስትሸጥ የምትውለው የጥፍር መቁረጫ ገቢ ባያሳጣትም ደስተኛ አይደለችም።
በየቀኑ በምታክለው ሌላም ሽያጭ ትርፍ ታገኛለች። ትርፉን እየቆጠበች ገንዘብ ታኖራለች። ገንዘቡ ፍላጎቷን ሞልቶ ለወላጆቿ ይተርፋል። ወላጆቿ ወጉ ሲደርሳቸው ይመርቋታል። ይህን ስታውቅ ፊቷ በመጠኑ ይፈካል፤ መልሳ ደግሞ ሰማሁ በምትለው አሉባልታ ልቧ ይጎሻል። ወዲያውም ጠብ ያምራታል።
ሌሎች ጓደኞቿ ልክ እንደሷ የአቅማቸውን ይሰራሉ። ከሰሩት እየቆጠቡም አገር ቤት ይልካሉ። ሁሌም የሚሮጡበት ስራ ላይሞላ ይችላል፤ አንዳንዴ ከኪሳራ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከትርፉ ይጋራሉ። ብዙዎቹ ከደንብ አስከባሪዎች ጋር መሯሯጡን ለምደዋል፤ እንዲህ ሲሆን ልምምጥና ጠብ ይከሰታል።
ደስታ ሁሌም የምትሸጠውን ዘርግታ ገዥዎችን ትጠብቃለች። ገበያ በቀናት ጊዜ፣ ደስ ይላታል። ባለቀው ልትተካ፣ በጎደለው ልትሞላ መርካቶ ትሮጣለች፤ በየቀኑ ግርግር የማያጣው የነደስታ መዋያ ሻጮችን ከገዢ ሲያገናኝ ይውላል።
አንዳንዴ በገበያው መሀል አሉባልታ ይናፈሳል። የአንድ አገር ልጆች ጎራ ለይተው፣ቡድን አዋቅረው ነገር ይቀምራሉ። ‹‹እከሌ እንዲህ አለ፣እከሊት እንዲህ ሆነች›› ይላሉ። ይህን የሰሙ ሌሎች የተባሉትን ይዘው፣ የታሙትን አንጠልጥለው ቀን ይጠብቃሉ።
አሉባልታው በአውጫጭኝ ታግዞ በቂም በቀል ሲበስል ይከርማል። ‹‹አውርቷል›› የተባለው ተጠርቶም ይጠየቃል። ቢያምን ባያምን ጠቡ አይቀርም። ‹‹ታማሁ‹ስሜ ተነሳ›› ያለው ወገን ጥርሱን እንደነከሰ ግንባሩን እንደቋጠረ ይከርማል። መገለማመጥ መፋጠጡ ይቀጥላል።
ደስታ ሁሌም በዚህ አይነቱ ድርጊት ተሳታፊ ነች። የሚያውቋት ‹‹ስማችንን አነሳች›› ሲሉ ይወቅሷታል። ከነዚህ መሀል ጥቂቶቹ አካባቢና ማንነታችንን አጉድፋለች እያሉ ይወቅሷታል። ይህን ሲያስቡ የሚናደዱት ደግሞ ማንነቷን ከእነሱ ማስበለጧ ያበሽቃቸዋል።
ብዙጊዜ ብሄርን አስታከው ጠብ የሚያነሱት የራሳቸውን ከሌላው ማስበለጥ ልምዳቸው ነው። ይህን ሲያደርጉ ስለሌላው ስም መጉድፍ አይጨነቁም። ከፍ በሚያደርጉት ማንነት እየኮሩ ቡድን ለመፍጠር ይጥራሉ።
ይህ ቦታ ከማለዳ እስከ ምሽት ወሬ ከስራ ይደወርበታል። በዚህ ስፍራ ሁሉን ሰምተው ዝም የሚሉ፣ ዝም ብለው የሚያወሩ፣አውርተውም የሚያስወሩ ብዙ ናቸው።
መንደርን ከቀዬ ፣ጎጥን ከአካባቢ እየለየ የሚቀመረው ሀሜት ሁሌም ገበያውን አድምቆት ያመሻል። በዚህ ልምድ አንዱ የሌላውን እየነቀፈ፣ሌላውም የራሱን እያደነቀ ይውላል።
በየቀኑ እልህና ቁጭት በሚታይበት ቦታ ሁሉም እራሱንና አመጣጡን አሞካሽቶ፣ ማንነቱን ለማሳየት ይሞክራል፤በዚህ መሀል በንግግር ተበለጥን ባዮቹ፣ቡድን ይለያሉ። ቋንቋቸውን አጉልተውም ራሳቸውን ይክባሉ።
ተቃራኒዎቹ ላለመበለጥ ይሻሉ። የአሸናፊነት ህልማቸው ሳይረግብ፣የሽንፈት መንገድ ሳይዙ ክብራቸውን ይጠብቃሉ። ይህ አይነቱ ጎራ ‹‹አይመቸንም›› የሚሉ ህይወታቸው ስራ ብቻ ነው። ሁሌም ‹‹እኔ አሽንፍ እኔ›› በሚለው ቡድን አይሳተፉም።
ሰሞኑን ደስታ ጸባይ ነስቷታል። በየምክንያቱ የምትጣላቸው ሰዎች በዝተዋል። አጋጣሚው የደረሰባቸው አንዳንዶች በሁኔታዋ መማረር ይዘዋል። ብዙዎች እንደሚሉት እሷ ካገሯ ልጆች በቀር ወዳጅ ይሉት የላትም። በስራ ሰበብ የቀረበቻቸው ቢኖሩ እንኳን አብረዋት አይዘልቁም።
ከብዙዎች የማይስማማ ባህርይዋ ሰሞኑን በኩርፊያ ታጅቧል። ከአንዳንዶቹም በክፉ መተያየት ጀምራለች። ጥቂቶቹ ‹‹ተሰደብን›› በሚል ቂም ይዘዋል። እሷን ባዩ ቁጥር የሚበሳጩት ወጣቶች አገራቸውን ለይታ አንቋሻለች መባሉ እያንገበገባቸው ነው።
‹‹ተደፈርን›› ባዮቹ ዕቃ ዘርግታ ከምትሸጥበት ሄደው ሊያናግሯት ሞክረዋል፤ሁኔታውን ማጣራት የፈለጉም በአውጫጭኝ እውነቱን እንድታወጣ አስገድደዋል። እሷ ስለሙከራቸው ደንታ አልሰጣትም። የመጡትን አባራ የተጋፈጧትን ልትደባደብ ተጋበዘች።
የዛን ቀን የነገሩን መክረር ያዩ ከመሀል ገቡ። በግልግል አለያይተው ሰላም እንዲወርድ ሞከሩ። ይህኔ ደስታ እልህ ያዛት፤ ብለዋለች የተባለውን ማንቋሸሽ እየደጋገመች ስድብ አከለች፤ንግግሯን የሰሙ የአንድ አገር ልጆች ሊደበድቧት ተመለሱ።
ጉዳዩ ያሰጋቸው አንዳንዶች ስድቡን ተወት አድርገው ለመረጋጋት ሞከሩ። ንዴት ያላቸውን አግልለው ሰላም ለመፍጠር ተጠጉ።ይህን ካደረጉት አንዷ ማሪቱ ጉዳዩን ለማብረድ ጥራለች። ማሪቱ ተሰደብን ከሚሉት ወገን ነች። እሷም እንደሌሎች የስድቡ ጉዳይ ሲያናድዳት ቆይቷል። በዕለቱ ግን ጠቡን አልፈለገችም። የተናደዱትን ተቆጥታ የተሰማቸውን አባብላ ሰላም ፈጥራለች።
ሀምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም
የሀምሌ ዝናብ በጭጋግ እንደታጀበ ውሏል፤ ወቅቱን ጠብቀው ገበያ የሚያመቻቹ አንዳንዶች ገዢዎች የሚሹትን ዕቃ ይዘዋል። ብርዱን የፈሩ ገበያተኞች በወፍራም ልብስ ተጀቡነው ያሻቸውን ይገዛሉ፤ ጭቃ ዝናቡ ግድ ያልሰጣቸው ነጋዴዎች የያዙትን ለመሸጥ በገበያው ይዞራሉ። ዛሬም የአስኮ ሰፈር ገበያ ከነአጀቡ ይተራመሳል።
ደስታ በማለዳ ከቦታዋ የዘረጋችውን ስትሸጥ አርፍዳለች፤ ትናንትና ሰለምን ሲሉ የሞገቷትን አልረሳችም። ሴቶቹን ባሻገር እየቃኘች መገላመጧን ይዛለች። በውስጧ ያደረው ቂምና ጥላቻ ለዛሬ አድሮ ውስጧን እየፈተናት ነው። በእሷ ዕምነት የተናገረችው ሁሉ እውነት ነው። ማንም ያሻውን ቢላት ሀሳቧን አትቀይርም።
ከአጠገቧ አለፍ ብለው ዕቃቸውን የዘረጉ ገበያ ለማግኘት ይቃኛሉ። አብዛኞቹ የሚሸጡት ተመሳሳይ ነው፤ ገዢዎች የእነሱን አልፈው ከሌሎች ሲወስዱ ውስጣቸው ይከፋል። ይህኔ በልጠው ለመታየት ዘዴ ይጠቀማሉ፤ አላፊ አግዳሚውን እየጠሩ፣ በፍቅር ይማጸናሉ።
የትናንትናዎቹ ጠበኞች የሆነውን ሁሉ አልረሱም። በይደር ያቆዩት ጉዳይ ዛሬም ያንገበግባቸው ይዟል። ደስታ አካባቢያቸውን ለይታ ተሳድባለች መባሉን በቀላል አልተውትም። አሁንም ያላቸውን አንስተው ማውጣጣት ይሻሉ።
ሁኔታቸውን ያየችው ደስታ ዛሬን እንደትናንቱ ላለመሆን እየሞከረች ነው። ወደ እሷ የሚያዩት ሴቶች ጠብ ፈልገው መምጣታቸው ገብቷታል፤ በርከት ማለታቸው እያሰጋት ባሻገር ቃኘች። ሴቶቹ ጉዳዩን አልተውትም ።
ጥቂት ቆይቶ ሴቶቹ ወደ እሷ ቀረቡ። ከእነዚህ መሀል ማሪቱን አየቻች። ማሪቱ የትናንቱ ጠብ ሲነሳ ገላጋይ ነበረች፤ ከመሀል ገብታ ነገር ስታበርድ ቆይታለች። ዛሬ ግን ይህ ስሜቷ አብሯት ያለ አይመስልም። ከሁሉም ብሳ ለምን ማለት ጀምራለች።
ደስታ ሰብሰብ ብለው የመጡት የአገር ልጆች ዛሬም እንደሚጣሏት አውቃለች። ማሪቱና ጓደኞቿ ንዴት በፊታቸው እየታየ ቀረቧት። ቀርበውም ‹‹ሰድበሽናል ምክንያቱን ንገሪን›› ሲሉ ሞገቷት ።
ደስታ ለመረጋጋት ሞከረች። ያሉትን እንዳልተናገረች ነግራም ልታሳምናቸው ቀረበች። በምላሿ ያልረኩት ጠያቂዎች በቀላሉ አልተዋትም፤ እየደጋገሙ እንዴት ብለው ወተወቱ። ክርክሩ አይሎ መተማመን ሲጠፋ ደስታ ስትናገር ሰማን ያሉ እማኞች ካሉ እንዲያመጡላት ጠየቀች፤ የሰማት የለም። ይህ ካልሆነ ‹‹በህግ ጠይቁኝ›› ስትል ወሰነች።
የደስታን ምላሽ የሰሙ ተሟጋቾች ‹‹ለአንቺ ህግ አያስፈልግም›› ሲሉ ቀረቧት። ደጋግመውም እሷና መሰሎቿ ከማንም እንደማይበልጡ ፣እነሱም ከማንም እንደማያንሱ ሊነግሯት ሞከሩ። በዚህ መሀል የማሪቱ ፊት በንዴት ሲለወጥ ታየ። የትናንቷ ገላጋይ ዛሬ ትህትናውን መድገም አልፈለገችም። በግርግሩ አልፋ ደስታ ላይ ተጠመጠመች።
ሁለቱ ሴቶች ሲያያዙ ገላጋዮች መሀል ገቡ። ከግልግሉ በኋላ ፈንጠር ብለው መሰዳደብ የያዙት ሴቶች በውስጣቸው ንዴትና እልህ ጦፈ ። ከአካባቢው ያራቋቸው ሰዎች ዳግም እንዳይጣሉ መክረው ነገሩን አበረዱ።
ከደቂቃዎች በኋላ
አሁን ጠብና ግርግሩ በርዶ ሁሉም ወደስራው ተመልሷል። የተረጋጋ የሚመስለው ገበያም ገዥና ሻጭን ማገናኘት ቀጥሏል። ከደቂቃዎች በኋላ ደስታ ካለችበት የደረሰችው ማሪቱ ከቀድሞው ንዴቷ ብሳ፣እየሮጠች መጣች። አፍታ ሳትቆይም የበረደውን ጠብ አስቀጠለች።
ማሪቱ ያላትን ሀይል ተጠቅማ የጠበኛዋን አንገት ያዘች። ጸጉሯን ጨምድዳ እግሯን ለእርግጫ ሰደደች። ሆዷን የተመታችው ደስታ በሆነው እየበሸቀች ከማሪቱ መታገል ያዘች ። ድብድቡን በትዝብት የሚያዩ አንዳንዶች ለግልግል አልፈጠኑም። ከዳር ቆመው ለፍጻሜው አንጋጠጡ።
የሴቶቹ ድብድብ ቀጥሏል። አሁንም ከመሀል የገባ የለም። እንዲህ መሆኑ የጠቡን ፍጥነት አጣድፎ ሀይል አክሎበታል። ዳር ተመልካቾቹ እንደቀድሞው ለግልግል አልቸኮሉም። ይህ አጋጣሚ ለደስታ አንዳች ነገር ውል እንዲላት አድርጓል።
የጠበኛዋን አንገት እንደያዘች ድንገት እጆቿን ከተቋጠረው ማዳበሪያ ሰደደች። ከመዳፏ የገባውን አንዳች ነገር ጨብጣም ወደ ጠበኛዋ አንገት ሰነዘረች። የያዘችው ጥቁር ቢላዋ ከማሪቱ አንገት አረፈ። ማሪቱ ተዝለፍልፋ ወደቀች።
ወዲያው እየተንፈራገጠች ራሷን ለማዳን ሞከረች። በደም ተነክራ በጀርባዋ የወደቀችውን ወጣት ያዩ ተጣድፈው ደረሱ። ነፍስ ይዟት መጨነቅ ጀምራለች። ይህኔ ደስታ የከበቧትን ገፈታትራ ወደፊት ሮጠች። ከህዝብ መጸዳጃው ገብታ ለመቆለፍ አፍታ አልፈጀባትም።
በጀርባዋ ወድቃ ስትንፈራፈር የቆየችው ማሪቱ አሁን ትንፋሿ ተቋርጧል። መሞቷን ያዩ ሮጠው ከመጸዳጃው ደረሱ። ደስታን እየጠሩም ካለችበት እንድትወጣ ጠየቁ። ድምጻቸውን የሰማችው ደስታ ፖሊስ ሳይመጣ እንደማትወጣ ተናገረች። ቃሏን ያደመጡ ተጣድፈው የፖሊስ ሀይል ጠሩ።
የፖሊስ ምርመራ
ወንጀሉ ከተፈጸመበት ስፍራ የደረሰው ፖሊስ ተጠርጣሪዋን ካለችበት አውጥቶ በተገቢው ጥንቃቄ የሟቿን አስከሬን አነሳ። በህግ ጥላ ስር ያለችውን ደስታ ስለድርጊቱ ታስረዳው ዘንድም ጠየቀ፤ መርማሪው ዋና ሳጂን ቢኒያም በሪሁን የተጠርጣሪዋን ቃል በመዝገብ 092/12 ላይ ማስፈር ያዘ። የጠቡ መነሻ ብሄርና ቋንቋን መነሻ ያደረገ ነበር። በ‹‹እኔ እበልጥ እኔ›› የተነሳው ችግርም የህይወት ዋጋ አስከፍሏል።
ውሳኔ
የፖሊስና የዓቃቤህግ የምርመራ ውጤት ተጠናቆ የደረሰው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሿ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ ሀምሌ 11 ቀን 2012 ዓም በችሎቱ ተሰይሟል ። በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም ደስታ መኮንን በፈጸመችው የነፍስ ማጥፋት ወንጀል፣ እጇ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ የሚታሰብ የአስር አመት ጽኑ እስራት ይገባታል ሲል በይኗል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013