አስመረት ብስራት
በጉግል የሰው ሠራሽ ልህቀት የሥነ ምግባር ቡድን አጋር መሪ የነበረችው ትምኒት ከጉግል እንደተባረረች ያስታወቀችው በትዊተር ገጿ ነበር። ትምኒት እንዳለችው፤ በሰው ሠራሽ ልህቀት ዘርፍ ላለው መድልዎ ትኩረት እንዲሰጥና በዘርፉ እምብዛም ውክልና ያላገኙ ሰዎች እንዲቀጠሩ የሚያሳስብ ኢሜል ከላከች በኋላ ነው እንደተባረረች የተነገራት።
ይህንን ዜና እንደ ዋሽንግተን ፖስት፣ ብሉምበርግ እና ኒው ዮርክ ታይምስ ያሉት ግዙፍ የአሜሪካ የሚዲያ ተቋማት ይዘውት ከመውጣታቸውም በተጨማሪ በሰው ሠራሽ ልህቀትና ተያያዥ የቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚሠሩ እውቅ ባለሙያዎች የትምኒትን መባረር በመቃወም ትዊተር ላይ ድምጻቸውን አሰምተዋል። #ISupportTimnit እና #BelieveBlackWomen በሚሉ ሁለት ሀሽታጎች የጉግል ሠራተኞችን ጨምሮ በርካቶች ከትምኒት ጋር አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች ከላይ የተጠቀሰውንና የመሳሰሉ ዜናዎችን ስመለከት ይች ሴት ማናት በማለት መረጃዎችን ማገላበጥ ጀመርኩ። በምርምር አንቱ ለመባል ከበቁት ውስጥ አንዷ ዶክተር ትምኒት ገብሩ መሆኗን ከቢቢሲ አማርኛ ጋር፣ ከኢቢኤስ ቴሌቪዥንም ጋር ያደረችው ቃለ ምልልስና ከተለያዩ ደረገፆች ላይ ያገኘነውን መረጃ ያመላክታል። ይሄንን መረጃም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደሚሆን አድርገን አዘጋጅተነዋል መልካም ንባብ።
ማንነት ሲገለጽ
እንደ ማንኛውም ከተማረ ቤተሰብ የተወለደ ኢትዮጵያዊ ልጅ የተሻለ ነገር እየተመለከተች ነበር ያደገችው። ተምሮ የትምህርት ጥቅም ከገባው ቤተሰብ በመወለዳ ዝንባሌዋ ወደ ሳይንሰ እንዲሆን አግዟታል። አባቷ ኤሌክትሪካል ኢንጅነር ነበሩ። የአባታቸውን እግር ተከትለው የዚህች ድንቅ ፈጠራ ባለቤት ሁለት ታላቅ እህቶቿም ኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ነበር ያጠኑት። በ1976 ዓ.ም ነው የተወለደችው። በ ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ወይም ሰው ሰራሽ ክህሎት ዘርፍ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ባለሙያዎች አንዷ ነች።
በአሜሪካ ካሊፎርንያ ውስጥ የምትኖረው ትምኒት ጉግል ውስጥ ሪሰርች ሳይንቲስት ናት። በ ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ የጥቁር ሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ‘ብላክ ኢንኤአይ’ የተባለ ተቋምን ከመሰረቱት አንዷ ናት። የፈጠራ ሥራዎችን አካታችነት በሚፈትሹ ጥናቶቿ፤ እንዲሁም ቴክኖሎጂና የሰብአዊ መብት ጥያቄን በማስተሳሰርም ትታወቃለች። ወጣት ትምኒት ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ቅድስት ሀና ትምህርት ቤት እስከ ዘጠነኛ ክፍል ናዝሬት ስኩል፤ አስረኛ ክፍል ስትደርስ ለአንድ ዓመት አየርላንድ ሄደችና ሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርሲቲ አሜሪካ ጨረሰች ።
በልጅነቷ በጣም ትምህርት ትወድ እንደነበር ትናገራለች። “ህጻን ሳለሁ ትምህርት እወድ ነበር። ስታመም ራሱ ከትምህርት ቤት መቅረት አልወድም ነበር። ሒሳብና ፊዚክስ በጣም ደስ ይለኝ ነበር።” ትላለች በትዝታ ወደ ልጅነት እድሜዋ እየተመለሰች።
በትምህርቷ በጣም ጎበዝ ከመሆኗ የተነሳ በውጭ ሀገራት የተማረችባቸው ተቋማት የምታመጣውን ውጤትመምህራኖቿ አምነው መቀበል ይከብዳቸው ነበር። “ብዙ አስተማሪዎች ጥሩ ውጤት ሳመጣ ይገርማቸው ነበር።
ኮሌጅ ለማመልከት የሚያግዝ አማካሪ «የትም አትገቢም» ብሎኛል። እናቴ «ለምን ልጄን እንዲህ ትላታለህ? ፈትናት እንጂ ማስፈራራት አትችልም» ብላው ነበር።” ትላለች። የበርካታ ነገሮች ተፅእኖ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በድፕሬሽን ውስጥ ወይም ድብርት ውስጥ ሆና ማጠናቀቅ ግድ ሆኖባት እንደነበረ ትምኒት ትናገራለች።
ዶክተር ትምኒት በተለያዩ ትግሎች ውስጥ አልፋ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ የገባችበትን አገጣሚ እንዲህ ታወጋናለች፤ “ወደዚህ ዘርፍ የመግባት ዓላማ አልነበረኝም። ፒኤችዲ ጀምሬ መሀል ላይ ነው የገባሁበት። ያኔ ብዙ ሰው ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ አይለውም ነበር። በ’ሜዲካል ኢሜጂንግ’ ዘርፍ ላይ ፍላጎት ነበረኝ። ለምሳሌ ገጠር የሚኖሩና ሆስፒታል የማያገኙ ሰዎች በስልካቸው እንዴት ህክምና ማግኘት እንደሚችሉ እያጠናሁ ነበር።
‘ኦፕቲክስ’ የሚባል የፊዚክስ ዘርፍ እያጠናሁ ሳለ ወደ ‘ኢሜጅ ፕሮሰሲንግ’ መጠጋት ጀመርኩ። ይህ ዘርፍ ፎቶ ከወሰድሽ በኋላ ፎቶ ውስጥ የምትፈልጊውን አይነት መረጃ ለማግኘት በሂሳብ ወይም በሌላ አይነት ‘አልጎሪትም’ በመጠቀም ‘ፕሮሰስ’ ታደርጊያለሽ። ‘ሲኒማ ፕሮሰሲንግ’ የሚባል ዘርፍ ሳጠና ለ’ኮምፒውተር ቪዥን’ ፍላጎት አሳደርኩ። ‘ኮምፒውተር ቪዥን’ እየሰራሁ ሳለ ወደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ የገባሁት” ትላለች።
የትምኒት ጥናቶች
ከትምኒት ታዋቂ ጥናቶች መካከል ፌሻል ሪኮግኒሽን ሲስተም ወይም የሰዎችን ፊት ገጽታ በማየት ማንነታቸውን የሚያሳውቅ መተግበሪያን በተመለከተ የሠራችው ይጠቀሳል። መተግበሪያው የጥቁር ሰዎችን በተለይም ደግሞ የጥቁር ሴቶች ገጽታ አይቶ ማንነታቸውን ለመለየት እንዲችል ተደርጎ አለመሠራቱን የነዶክተር ትምኒት ጥናት ይጠቁማል። ጥናቱን የጀመረችው ኤምአይቲ ከምትሰራ ጓደኛዋ ጋር ነው። “ጓደኛዬ ጥቁር ሴት ነች።
ለአንድ ፕሮጀክት ‘ፌስ ሪኮግኒሽን’ ስትጠቀም ፊቷን ‘ዲቴክት’ ማድረግ ማንበብ አልቻለም። እንደሌለች ነው የሚቆጥራት። ነጭ ‘ማስክ’ ጭንብል ፊቷ ላይ ስታደርግ ግን ያነባል” በማለት የጥናቱን መነሻ አጋጣሚን ታስታውሳለች። ችግር የእያንደንዱ ጥናት መነሻ ቢሆንም ጥናት አጠኚዎች ግን እነሱን የሚወክላቸውን ብቻ መርጠው መጠቀማቸው ትክክል አለመሆኑ ዶክተር ትምኒት እንድትቃወም ያደርጋታል።
የጥናቱ መነሻ የሆናቸው አጋጣሚ ዘረኝነት እና ፆተኛ መድልዎ በብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ እንደሚስተዋል ትምኒትና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንዲያስተውሉት አድርጓል። ለዚህም ይመሰለኛል ትምኒት የመብት ተሟጓች ወይም ዳታ አክቲቪስት የሆነችው።
ተሟጓች ሃሳቦች
ዶክተር ትምኒት፤ ከበይነ መረብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ንቅናቄ ከሚያደርጉ የመብት ተሟጋቾች (ዳታ አክቲቪስትስ) አንዷ ነች። እነዚህ የመብት ተሟጋቾች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ምን ያህል አካታች ናቸው? ሲሉ ይጠይቃሉ። ክፍተት ሲያገኙም ከግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር ሳይቀር ይፋለማሉ። ለትምኒት ቴክኖሎጂ ከመብት ሙግት ጋር የተያያዘ ነው። “ለአብዛኛው ሰው የማይሠራ ቴክኖሎጂ ከተሠራ ለሰው የማይሆን ነገር እየተሠራ ነው ማለት ነው” የምትለው ባለሙያዋ፤ አፍሪካውያን ሴቶች ለራሳቸው የሚሆን ነገር እንዲሠራ ቴክኖሎጂ ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ታሳስባለች።
እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው የዘረ መል ቅንጣት ላይ የተሠሩ እንዲሁም ለተለያዩ ህመሞች የሚቀመሙ መድኃኒቶችን ነው። አብዛኛውን ጊዜ ከአፍሪካውያን ወይም ከጥቁሮች ናሙና እንደማይወሰድ፣ ቢወሰድም የናሙናው መጠን ውስን እንደሚሆን በማስረጃነት ትጠቅሳለች። ለዚህም ነው ትምኒት ቴክኖሎጂ ከሰብአዊ መብት ትግል ጋር ጎን ለጎን እንደሚሄድ የምትናገረው።
ቴክኖሎጂ አካታችና ፍትሐዊ እስከሆነና ለበጎ ዓላማ እስከዋለ ድረስ መጪው ዓለም ብሩህ የመሆን እድሉ ሰፊ እንደሆነ ከሚያምኑ ባለሙያዎች አንዷ የሆነችው ዶክተር አፍሪካ ውስጥ የድሮን ጥናት የሚሠሩ ጀማሪዎች በመኖራቸው መንገድ ሳያስፈልግ በድሮን መድኃኒት ማዳረስ ይቻል ይሆናል። ትልልቅ ሆስፒታል መሥራት ሊቀር፣ ምናልባትም በትንንሽ መሣሪያ ሕክምና መስጠት ይቻል ይሆናል ራሳቸውን የሚያሽከረክሩ መኪኖች ሲበራከቱ አይነ ስውራን በራሳቸው ይንቀሳቀሱም ይሆናል የሚል ሃሳብ አላት።
ወጣቷ በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ውስጥ ለወጣቶች የኮዲንግ ሥልጠና የተሰጠበት ‘አዲስ ኮደር’ የተሰኘ ፕሮጀክት ነበራት። ከዚህ በፊትም በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በተካሄደ የአይሲቲ ኮንፈረንስም ተሳትፋለች። ከኢትዮጵያ የወጡ የሰው ሠራሽ ልህቀት ባለሙያዎችን በብላክ ኢን ኤአይ እንዳካተተችም ትናገራለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሠራሽ ልህቀት እየታወቀ መምጣቱን የምታምነው ትምኒት “ዘርፉ መታወቅ እየጀመረ ነው። ግን የተዋቀረ አካሄድ መኖር አለበት። ሁሉም ሰው የሚሳተፍበት እቅድም መኖር አለበት። ሰዎች ወደ ቴክኖሎጂው እንዲገቡ እድል መስጠትም አለብን” ትላለች። በተጨማሪም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የግል የቴክኖሎጂ ድርጅቶች እንዲገቡ መንገዶች መመቻቸት እንዳለባቸው ትጠቁማለች።
“ሰዎች የራሳቸውን የቴክኖሎጂ ድርጅት እንዲጀምሩ ወይም ትልልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲመጡ መደረግ አለበት። በኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ የሚሆኑ ተቋማት ቢበራከቱ ጥሩ ነው። መንግሥት ገንዘብ የሚሰጠው የጥናት ተቋም ያስፈልጋል። የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች በደንብ እየተከፈላቸው በትኩረት ጥናት እንዲሰሩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች።
ከጎግል ጋር የተፈጠረው እሰጥ አገባ
በሰው ሠራሽ ልህቀት ውስጥ ካሉ ጥቂት ጥቁር ሴቶች አንዷ የሆነችው ትምኒት መባረሯ በጉግል አመራሮችና መድልዎን የሚቃወሙ ሠራተኞች መካከል የተፈጠረው ውጥረት አንድ ማሳያ ነው የሚሉ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው ይሰነዘራሉ።
ኤም አይ ቲ ባወጣው ዘገባ መሠረት ለትምኒት መባረር ምክንያት የሆነው ጥናት “On the Dangers of Stochastic Parrots: Can Language Models Be Too Big?” ይሰኛል። አራት የጉግል ሠራተኞችን ጨምሮ በስድስት ባለሙያዎች የተጻፈ ነው። ጥናቱን የተመለከተ ውይይት ላይ እንድትሳተፍ ከተጋበዘች በኋላ ጽሑፍ ውድቅ እንድታደርገው ትእዛዝ እንደተሰጣት ዶክተሯ ተናግራለች።
ይህን የጉግል ውሳኔ ያልተቀበለችው ትምኒት፤ ከጥናቱ ላይ ስሟን ለማውጣት ለድርጅቱ ቅድመ ሁኔታዎችን ታስቀምጣለች። ያስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች በጉግል ተቀባይነትን አላገኘም። በምላሹ ግን ዶከተር ትምኒት በገዛ ፍቃዷ ሥራዋን መልቀቋን እንደሚቀበል በመግለጽ ያብራራል።
ዶክተሯ ገና ሥራዋን በገዛ ፈቃዷ አለመልቀቋንና የጉግል የሰው ሠራሽ ልህቀት ምርምሮች ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊ ጄፍ ዲን እንዲሁም ሌሎችም የተቋሙ አመራሮች እንዳባረሯት አስረድታለች። የሁለቱ ጉዳይ ከመካረሩም በላይ የበርካቶችን ትኩረት ሊስብ በቅቷል። ቀደም ሲል ከሰራቻቸው ድንቅ የፈጠራ ውጤቶች በላይ ከጎግል የማባረሯ ዜና በኢትዮጵያውያን ጆሮ ገብቷል።
አሁን ያለው የትምኒት ሁኔታ
የአርቴፌሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ ልህቀት ተመራማሪዋ ትምኒት፤ ከስራ መባረሯን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጉግል ባልደረቦች በእርግጥም የዓለማችን ግዙፉ የቴክኖሎጂ ተቋም ጉግልን በዘረኝነትና መልዕክቶችን ቀድሞ በመመርመር (ሳንሱር) የሚከሰውን ደብዳቤ በመፈረም ከትምኒት ጎን ቆመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ጉግል በትምኒት ላይ የወሰደውን እርምጃ በመቃወም የትዊተር ተጠቃሚዎች ከትምኒት ጎን መቆማቸውን #ቢሊቭ ብላክ ዊመን #Believe BlackWomen በሚለው መሪ ቃል ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው። ነገር ግን ጉግል ትምኒት ከሥራዋ ስለመባረሯ ያቀረበችውን ምክንያት አስተባብሏል።
የጉግል ከፍተኛ ኃላፊ የሆነው ጄፍ ዲን በኢሜል በሰጠው ምላሽ ስለትምኒት ከሥራ መሰናበት “በርካታ በግምት ላይ የተመሰረቱ የተሳሳቱ ነገሮች አሉ” በማለት ስለጉዳዩ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቷል።
ዲን እንደሚለው፤ በዶክተር ትምኒት የተዘጋጀው የምርምር ወረቀት ከማቅረቢያው ጊዜ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የገባ ስለሆነ ጉግል ጽሁፉን የሚገመግምበት በቂ ጊዜ አልነበረውም። ወረቀቱ በርካታ አስፈላጊ ምርምሮችን ችላ ያለ ነው። ሲል ትምኒትም በኢሜል በሰጠችው ምላሽ፤ በሥራዋ ላይ ለመቆየት፤ ምርምሩን በመገምገም አስተያየት የሰጡና በግምገማው የተሳተፉ ሰዎች ማንነት እንዲሁም የሰጡት አስተያየት እንዲገለጽ ጠየቀች። ሌሎች መሟላት አለባቸው ያለቻቸውን በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችንም አስቀመጠች። የጠየቀቻቸው ነገሮች የማይሟሉ ከሆኑ ጉግልን እንደምትለቅ በማሳወቋ እኛም ውሳኔዋን ተቀብለነዋል ብሏል።
የትምኒትና የታዋቂው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ውዝግብ በዘርፉ ባሉ ባለሙያዎችና የታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ዋነኛ ርዕስ ሆኗል። ምንም ይሁን ምን ግን ያልሰራ ሰው አይታወቅምና ሰርታ የሀገራችንን ስም በዓለም መድረኮች ልታስነሳ ስለቻለች ከፈጣሪዎቹ አንዷ ብለናታል። ጥንካሬዋንም ለወጣቶቻችን መማሪያ ይደርስልን ዘንድ ምኞታችን ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013