እፀገነት አክሊሉ
በአገሪቱ የእድል ጨዋታዎችን በማጫወት ብቸኛ ተቋም ነው፤ ከዚህ ስራና ሃላፊነቱ ባሻገር የተለያዩ ድርጅቶችና መንግስታዊ ተቋማት ለሚያወጧቸው የእድል ጨዋታዎች ፍቃድ በመስጠት፣ በመቆጣጠርና ችግር ሲኖርም እንዲታረም በማድረግ በጠቅላላው የአገሪቱን ህግና ደንብ አክብረው እንዲሰሩ በመከታተል የድርሻውን የሚወጣ ነው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ።
60 ዓመታትን በስራ ላይ የቆየው ይህ ተቋም በእነዚህ አመታት ያጋጠሙትን ችግሮች እንዲሁም በስራው ላይ ያለውን ስኬት እና ሌሎች ተዛማጅ ነገሮችን በተመለከተ ከኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ከአቶ ቴዎድሮስ ንዋይ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የተሰጠው ተግባርና ሃላፊነት ምን ይመስላል?
አቶ ቴዎድሮስ፦ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በመቋቋሚያ ደንብ 160 /2001 መሰረት በዋናነት ሁለት አላማዎች አሉት። አንደኛው የሎተሪ ስራ በማካሄድ የሚገኘውን የተጣራ ትርፍ ለመንግስት ገቢ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ የእድል ጨዋታዎችን ፍቃድ የመስጠትና የመቆጣጠር ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከእነዚህ ተግባርና ሃላፊነቶቹ አንጻር እያከናወነ ያለው ስራ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ቴዎድሮስ፦ አዎ አሁን ባለው ሁኔታ የተለያዩ ሎተሪዎችን በዓመታዊ እቅዱ መሰረት ለገበያ በማዋል የተሸጡትንና ያልተሸጡትን በመለየት እጣ የማውጣት ስራ ይሰራል። በዚህም መሰረት ለመንግስት ሪፖርት አድርጎ የተጣራ ትርፉንም ገቢ እያደረገ ነው። በሌላ በኩልም ፍቃድ የሚሰጥባቸውን የእድል ጨዋታዎች መሰረት በማድረግ አራት መመሪያዎችን አውጥቶ ስራዎችን እያከናወነ ነው።
በተለይም የእድል ጨዋታዎችን ለመቆጣጠርና ፍቃድ በመስጠት በኩል ህገ ወጥ ተግባራት እንዳይፈጸሙ ለማድረግ ይሰራል። ለምሳሌ” ኮንቬንሽናል ቢንጎ” የሚባለውና በተለያዩ መዝናኛ ስፍራዎች ውስጥ ሰዎች በአንድ አዳራሽ ሆነው እድላቸውን ለመሞከር የሚጫወቱትን ጨዋታ አስተዳደሩ በመመሪያው መሰረት ፍቃድ ይሰጣል ቁጥጥርም ያደርጋል።
ሌላው የቶምቦላ ፍቃድ ነው፤ ይህም ፍቃዱን ያወጣው ድርጅት ለሚወክለው ማህበረሰብ የቶምቦላ ሎቶሪውን በመሸጥና በዓይነት የተዘጋጁ ሽልማቶችን በመስጠት የሚያጫውተው ሲሆን በዚህ የሚገኘው ገቢ ለወከለው ማህበረሰብ መሰረተ ልማት እንዲሰራ የሚያስገድድ በመሆኑ ይህም በመመሪያው መሰረት መከናወኑን እንከታተላለን።
ሌላው የስፖርት ውርርድ መመሪያ ሲሆን ይህም አጫዋቹ ድርጅት በሚያዘጋጃቸውና ዓለም ላይ የሚደረጉ የስፖርታዊ ውድድሮችን መሰረት በማድረግ የሚካሄድ ተወራራጆቹም የአንድን የስፖርት ጨዋታ ውጤት አስቀድመው በተነበዩት መሰረት አሸናፊ መሆን አለመሆናቸውን የሚለይበት ነው።
የመጨረሻው የፕሮሞሽን ሎተሪ ሲሆን ይህም የተለያዩ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ለማስተዋወቅ የእድል ጨዋታ በማዘጋጀትና ህብረተሰቡም አገልግሎታቸውን ሲያገኝ የእድል ቁጥሮቹን በመስጠትና እድሉን በመሞከር አሸናፊ ከሆነ ለእጣው የተዘጋጀውን ሽልማት የሚወስድ ድርጅቱም ምርትና አገልግሎቱን እያስተዋወቁ የሚሸጡበት ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በተለይም ተቋማት የንግድ ስራቸውን ለማስተዋወቅና ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ለመሸጥ የእድል ጨዋታ ሲያዘጋጁ ፍቃድ የምትሰጡ ከሆነ በተገባው ቃል መሰረት ስለመፈጸሙስ የምትቆጣጠሩበት መንገድ ምን ይመስላል ?
አቶ ቴዎድሮስ፦ ፍቃድ ለመጠየቅ ሲመጡ የሚያስገቡት አጠቃላይ የስራ ዝርዝር (ፕሮፖዛል ) አለ፤ በዚህ መሰረት የሚያሰራጩት የትኬት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ፣ ትኬቱ ዋጋው በየትኛው አካባቢና ለምን ያህል ጊዜ እንደሚሸጥ ይገልጻሉ፤ እነዚህ ደግሞ በውል ይታሰራሉ። በመቀጠል ድርጅቶቹ በውላቸው መሰረት መስራት አለመስራታቸው ክትትል ይደረግበታል።
ብሔራዊ ሎተሪ በዚህ መሰረት መሸጡን የጊዜ ገደቡን በትክክል መጠቀማቸውን እንዲሁም እጣው በግልጽ መውጣቱንና የአሸናፊዎች ስም ዝርዝርም በውሉ መሰረት በግልጽ መጠቀሱን እንዲሁም ሽልማቱ በአግባቡ ለእድለኛው ማስረከባቸው ላይ ክትትል ይደረጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ብሔራዊ ሎተሪን ጨምሮ እነዚህ ተቋማትም እጣ ይወጣል ብለው ያስቀመጡትን ጊዜ የሚያራዝሙበት ሁኔታ አለ ፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ለእናንተ ያስታውቃሉ ማለት ነው?
አቶ ቴዎድሮስ፦ አዎ ሁሉም የእድል ጨዋታዎች ትኬቱን እንዲሸጡ የሚሰጣቸው ጊዜ ሶስት ወር ነው፤ ለምሳሌ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ አንድ መቶ ሺ ትኬት ለመሸጥ አስበው ሃምሳ ሺ ትኬቶችን ብቻ ቢሸጡ መስሪያ ቤቱ ለተጨማሪ ሶስት ወር ጊዜውን እንዲያራዝሙ ይፈቅድላቸዋል። ከዛ በኋላ ግን እጣውን ማውጣት ስላለባቸው ወደ ማስገደዱ እንሄዳለን።
አዲስ ዘመን ፦ በተለይም የቶምቦላ ጨዋታዎች ፍቃዱም የሚሰጠው ለተወሰኑ ድርጅቶች እንደሆነ ነግረውኛል፤ የሚገኘው ገቢም ተመልሶ ወክለነዋል ለሚሉት ማህበረሰብ እንደሚውልም እንደዛው፤ ብሔራዊ ሎተሪ ይህንንስ በአግባቡ ስለመፈጸሙ የመከታተል ሃላፊነት አለበት? ካለበት እየተከታተለ ነው?
አቶ ቴዎድሮስ ፦ እዚህ ላይ ይህንን የቶምቦላ እጣ ፍቃድ ወስደው የሚሸጡት የልማት ድርጅቶች ናቸው፤ ለምሳሌ የአማራ ፣የኦሮሞ ፣የደቡብ ልማት ማህበራት ሲሆኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ይጠቀሳል። እነዚህ ደግሞ አንድን ማህበረሰብ ለመጥቀም የሚሰበስቡት ገቢ በመሆኑ ይህም በምን ያህል ደረጃ ማህበረሰቡ ጋር ደረሰ የሚለውን እንቆጣጠራለን።
ለምሳሌ የህዳሴው ግድብ ቶምቦላ አገራዊ ነው፤ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በግንባታው ላይ አሻራውን እንዲያሳርፍ ለማድረግ የተዘጋጀ ቶምቦላ በመሆኑ አስተዋጽዖውም በጣም ትልቅ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ብሔራዊ ሎተሪ ፍቃድ ከሚሰጥባቸው ዘርፎች አንዱ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን ውጤት በመገመት የሚካሄድ ገንዘብ አስይዞ የመወራረድ ሂደት ነው፤ ይህ ሂደት ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበረሰቡን ካለማስደሰቱም በላይ ትውልድንም የሚያበላሽ ነው በሚል ተቃውሞ ተነስቶበት እናንተም ፍቃድ መስጠቱን ላልተወሰነ ጊዜ አቋርጣችሁ ነበርና እስኪ ስለዚህ ጉዳይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
አቶ ቴዎድሮስ፦ አዎ ፍቃድ መስጠቱ ላልተወሰነ ጊዜ ቆሟል፤ በስራ ላይ የነበሩት ግን እየሰሩ ነው፤ ይህም የሚሆነው ስራውን እስከምናስተካክልው ድረስ ነው። እንግዲህ የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ ) የሚባለው በዓለም ላይ ከሰው ልጅ ስልጣኔ ጋር አብሮ እያደገ የመጣ ነው። በጣም የተስፋፋው ደግሞ ሁሉም በእጁ ዘመናዊ ስልኮችን መያዝና የበይነ መረብ ተጠቃሚ መሆን ከጀመረ በኋላ ነው።
በአገራችንም በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 160/2001 መሰረት እውቅና አግኝቶ ከዛ በኋላ ደግሞ ለስራው የሚሆነው መመሪያ በ2005 ዓ.ም ወጥቷል ፤ ጨዋታውም ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው። በዚህ ጊዜ ይጀመር እንጂ ወደ ህብረተሰቡ ቶሎ ስላልገባ አልተስፋፋም ነበር። ከ2011 ዓ.ም ግንቦት ወር ወዲህ ግን በጣም ብዙ ሰው መሳተፍም በመጀመሩ ብዙ ድርጅቶችም ወደ ስራው ተቀላቀሉ። መስፋፋቱን ተከትሎ ደግሞ የሚታዩ አንዳንድ ከአላማው ውጪ የሆኑ ችግሮች በመከሰታቸው ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጥናት ማድረግ ጀመረ።
አዲስ ዘመን፦ መስፋፋቱን ተከትሎ የተፈጠሩትና ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን ወደ ጥናት ያስገቡት ችግሮች ምንድን ነበሩ?
አቶ ቴዎድሮስ፦ አዎ በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የስራ ሂደቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከተቋሙ ውጪ ያሉ አካላት ጥናት እንዲያደረጉ ቢሞከርም የኮሮና ቫይረስ በመከሰቱ ምክንያት ስራው ተቋረጠ፤ አሁን በቅርቡ ግን እንደ አዲስ ወደ ስራ ተገብቷል።
የጥናቱ ዋና አላማም በተለይም የስፖርት ውርርዱ ላይ ያለው የደንበኞች አካሄድ ምን መምሰል አለበት? የሚነሱት ጥያቄዎችስ ምን ያህል አግባብነት ያላቸው ናቸው? የሚሉ ናቸው ።
በሌላ በኩል ደግሞ ጨዋታውን ማንም ድርጅት ፍቃድ ስላወጣ ብቻ እንደፈለገ ገብቶ የሚሰራው ስለነበር ለመቆጣጠር የማያስችል ነበርና ይህንን መመሪያም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የማሻሻል ስራ ተሰርቷል። በጥቂት ጊዜያት ውስጥም ለማኔጅመንቱ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።
አዲስ ዘመን፦ ይህ ዓይነት ስፖርትዊ ውርርድ ብዙዎች እንደሚሉት ተማሪዎችን ከትምህርት ውጪ ያደረገና ሱስ ያስያዘ፤ ወጣቶችን ስራ ፈት ያደረገ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎችንም በኢኮኖሚ እንዲጎዳ ስለመሆኑ ይነገራልና እርስዎ በዚህ ላይ ያልዎት ሃሳብ ምንድን ነው?
አቶ ቴዎድሮስ ፦ እነዚህን መሰል ጥያቄዎች ማየት የጀመርነው በ2011 ዓ.ም ነው። ጥያቄዎቹ ተነሱ ተብሎ ግን ስራ ይቅር አይባልም ። በራሳችን መለየትና ማየት የፈለግነውን እያየን በውጭ አካል ደግሞ ጥናቶችን እያስጠናን፤ በአስተዳደሩ በኩል ያለውን አስተካከልን በሌላኛው ጎን ያለውን ችግር በትክክል ከተረዳን በኋላ ደግሞ የሚስተካከሉትን ነገሮች ለማየት እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ከሚነሱት ቅሬታዎች አንጻር በጥናቱ ውጤትና በእናንተም አረዳድ መሰረት ችግሮቹን ከለያችሁ ምን ያህሉን አስተካከላችሁ? እንደው እንደ ምሳሌ የሚነሳ ካለ፤
አቶ ቴዎድሮስ፦ በጣም ብዙ ነገሮች ናቸው የተስተካከሉት በተለይም ከገቡት የመንግስት ግዴታዎች፣ ከድርጅቶቹ ቅርንጫፎችና አቋም አንጻር ፣ እዚህ ላይ ለምሳሌ ድርጅቶቹ እንደ ድርጅት በራሳቸው የቆሙና ለመንግስት ህግና ደንብ ተገዢ ሆነው ስራውን እየተቆጣጠሩ መስራት ይችላሉ ወይ? የሚለውን አይተናል ። በሌላ በኩልም እነዚህ የስፖርት ውርርድ ቦታዎች ከተቋማት እና ከትምህርት ቤቶች አካባቢ ርቀው እንዲከፈቱ የማድረግ እርምጃዎች ተወስደዋል።
አዲስ ዘመን ፦ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች በስፖርት ስም ውርርድ እየተባለ በየቦታው የሚደረገውን ጨዋታ ቁማር ነው ትውልድንም ያጠፋል በማለት ከስራ አግደውታል ይባላልና እኛ ደግሞ በርካታ ችግሮችን እያስከተለብንም ሳይቋረጥ የቀጠለበት ሁኔታ አለ፤ እንደው እንደ አገር የቁጥጥር ስርዓታችን አስተማማኝ ነው ብለን ነው ቀጥለንበት ያለነው?
አቶ ቴዎድሮስ፦ በነገራችን ላይ በእኛ አገር የስፖርት ውርርዱ ብሔራዊ ሎተሪ ፍቃድ ከመስጠቱ በፊት ጀምሮ የነበረ ነው፤ አሁን ከህግ ውጪ የነበረውን ነገር ህግና ስርዓት እንዲበጅለት ነው የተደረገው፤ እኛ ብንተወው ደግሞ ይህ ነገር ይቆማል ወይ የሚለው በራሱ ከባድ ጥያቄ ነው።
ምክንያቱም በህብረተሰቡ ውስጥ የመጫወትና የማጫወትም ፍላጎት አለ፤ ይህ መሟላት አለበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ያህል ፍላጎት እያለ በቃ ጨዋታው በአገሪቱ እንዳይሰጥ ተከልክሏል ቢባል ይቆማል ወይ የሚለውንም በደንብ መፈተሽ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ሁሉም በእጁ ዘመናዊ ስልኮች አሉት፤ እነዚህን ተጠቅሞ ማንም ሳያውቅ የማይጫወትበት ምንም ምክንያት የለም፤ እንደውም ከዛ በኋላ ለሚፈጠረው ነገር መቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ ሁሉ ሊከሰት ይችላል።
ግን ደግሞ ህግና ስርዓት ተበጅቶለት መዝናኛነቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል ማድረጉ እንደ አማራጭ መታየት እንዳለበት ነው የእኛ እምነት። የስፖርቱ ውርርድ አንደኛ ዝም ብሎ መተንበይ ሲሆን ሌላው ጎኑ ደግሞ የሚተነበይለትን ቡድን ጥንካሬና ደክመት ለማወቅ የሚደረግ ንባብ አለ፤ በዚህ ውስጥ ደግሞ እውቀትም ይገኛል፤ መዝናኛ የሚሆነውም እነዚህን ሁለት ነገሮች አሟልቶ መያዝ ሲችል ነው።
አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ከህግ ውጪ የሆነባቸውን ነገር ለመቆጣጠር የሚያስችል መመሪያ ነው ያወጡቱ እንጂ አልዘጉም። ለምሳሌ የውጭ አገር ዜጎች በውርርድ ጨዋታው ላይ እንዳይሳተፉ የከለከሉ አሉ፤ ሌሎች ከህግ ውጪ ሆነው የነበሩ ነገሮችን ጠበቅ የማድረግ ስራም ሰርተዋል። እኛም በዓለም ላይ ያለውን ነገር ወስደን ግን ደግሞ መዝናኛ አድርገን ለማዘጋጀት እየጣርን ነው፤ ውሳኔያችንን ስናስተላልፍ ደግሞ እነሱ ስላሉ ሳይሆን ጥናቶች የሚያመጡትን ውጤት እንዲሁም በአገር ላይ የሚያስከትለውን ነገር አጢነን ነው ።
አዲስ ዘመን ፦ ከገቢ አንጻርም ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እንዲሁም አገር የጠቀሙት ነገር ምን ያህል ነው?
አቶ ቴዎድሮስ፦ ለጊዜው ገቢው እጄ ላይ ባይኖርም ገቢ ግን ተገኝቷል። ዋናው ነገር ግን ሁኔታውን የምናየው ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንጻር ነው። መመሪያም ወጣ አዋጅም ወጣ በህብረተሰቡ በኩል ፍላጎት ስላለ እኛ መመሪያ ባናወጣም በህገ ወጥ መንገድ ሊካሄድ ይችላል። በመሆኑ ስራው ወደእኛ መጥቶ በባለቤትነት እንድናስተዳድረው የሆነው በመሰረታዊ አላማው ገቢ መሰብሰብ አይደለም።
ግን ደግሞ ህገወጥ አካሄድ የነበረውን መስመር አስይዘን መዝናኛነቱንም ጠብቀን እየሰራን በመቀጠል ገቢን በሁለተኛ ደረጃ ማምጣት ይቻላል ብለን እየሰራን ነው። ይህም ቢሆን ግን ለአስተዳደሩም ይሁን ለመንግስት ገቢን እያስገባ አይደለም ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፦ በከተማዋ አንዳንድ ህገ ወጥ የእድል ጨዋታዎች በመሸታ ቤቶች፣ በገበያ ቦታዎችና በሌሎችም አካባቢዎች ላይ ይደረጋሉ፤ እነሱን ከመቆጣጠር አንጻር ተቋሙ ሚናውን ተወጥቷል ብለው ያስባሉ?
አቶ ቴዎድሮስ፦ አዎ ትክክል ነው፤ አሁን ላይ መቆጣጠር እጅግ ከባድ የሆነው ህገወጥ የእድል ጨዋታዎችን ነው። ፍቃድ የምንሰጣቸው የምናስገባቸው ውል ስላለ በዛ መሰረት ካልሰሩ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ ፍቃዱን እስከመሰረዝ የደረሰ እርምጃ እንወስዳለን። ግን ይህ በየመንደሩና በመሸታ ቤቶች የሚካሄዱ የእድል ጨዋታዎች ለቁጥጥር በጣም አስቸጋሪ ሆነዋል።
አዲስ ዘመን፦ ከደንበኞቻችሁ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል ? ጠንካራ ነውስ ማለት ይቻላል?
አቶ ቴዎድሮስ፦ ይህንን እንግዲህ ከሎተሪ ስራችን ጋር ማየት ነው የሚያስፈልገው፤ ማለትም የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር 60ኛ ዓመቱን የሚያከብረው በሚቀጥለው ዓመት ነው፤ እነዚህን ዓመታት ለመዝለቁ ደግሞ ዋነኞቹ ሞተሮቹ ደንበኞቹ ናቸው፤ እድገቱም መልካም በመሆኑ ከደንበኞቻችን ጋር መልካም ግንኙነት አለን ብለን ነው የምናስበው።
ከ 1987 እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ትልቁ ሽልማት የነበረው 1 ሚሊየን ብር ብቻ ነበር። ከዛ በኋላ ባሉት ዓመታት እየጨመረ ሄዶ አሁን
ላይ የሽልማቱ ገንዘብ 20 ሚሊየን ብር ደርሷል። ይህ እድገት ደግሞ ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን ከደንበኞቻችን ጋር በፈጠርነው መልካም ግንኙነት የመጣ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ ሎተሪ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በቅርንጫፍ ደረጃም ብዙ ካለመስራቱም በላይ ከ33 የማይበልጡ ነበሩ ፤ አሁን ላይ የቅርንጫፎቹን ብዛት 58 አድርሷል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ክልል ከተሞች ሁነው ግን ወጣ ወዳሉ ስፍራዎች ላይ ሎተሪን ወስደው የሚሸጡ ወኪሎች ተፈጥረዋል፤ እነዚህም ቢሆኑ እስከ ዛሬ አራት ዓመት በፊት ድረስ ከ60 የማይበልጡ የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ከ70 በላይ ደርሰዋል። በመሆኑም ከደንበኞቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት በዚህ መልኩ ነው የምናየው፤ ደንበኞቻችን ሎተሪ ይገዛሉ፣ ይሳተፋሉ የእኛም የሽልማት መጠን ጨምሯል ወኪሎቻችን ቅርንጫፎቻችን በዝተዋል።
አዲስ ዘመን፦ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በአገሪቱ ብቸኛ እንደመሆኑና 60 ዓመታትንም በስራው ላይ እንደማሳለፉ ምናልባት ሽልማቱ ጨምሯል ምናምን ሊባል ይችላል፤ ግን ደግሞ በሌሎች አገሮች ያለው የሎተሪ ሽልማት እጅግ የሚያስደምም ነውና ከዚህ አንጻር አስተዳደሩ ምን ላይ ነኝ ብሎ ያስባል? የሚሰጠው ሽልማትስ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ያማከለስ ነው ለማለት ይቻላል?
አቶ ቴዎድሮስ፦ ሽልማቱን አሁን ካለው በላይ ለመጨመር ወይም እንደ ሌሎች አገሮች እጅግ አስደማሚ ለማድረግ የእድገት ሁኔታ ይጠይቃል፤ የአገሪቱም አጠቃላይ ገቢ እንዲሁም የግለሰቦች አመታዊ ገቢም ወሳኝ ነው፤ ሌላው በከተሞችና በገጠር ያለው የመሰረተ ልምት ሁኔታም ወሳኝነት አለው ፤ ይህም ሲባል ወደ አንድ የገጠር ከተማ ገብቶ ሎተሪ ለመሸጥ ምን ያህል የመሰረተ ልማቱ ምቹ ነው? እንዴት ተጉዞ እዛ አካባቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል መድረስ ይቻላል የሚለውን ሁሉ ማየት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው።
ይህም ቢሆን ሽልማቱ እድገት እያሳየ መሆኑን ነው የምንረዳው። ለቀጣዩ ደግሞ ያዘጋጀነው የአስር ዓመት መሪ እቅድ ላይ የምንሰጠው ሽልማት አጓጊና ሳቢ እንዲሆን ለማድረግ እንሰራለን ብለናል።
በነገራችን ላይ ያለፉት የመጨረሻ አምስት ዓመታት የስትራቴጂ እቅድ አማካይ እድገቱ ስምንት በመቶ ነበር፤ ይህም ጥሩ እድገት ቢሆንም የእቅድ አፈጻጸሙን ግን አላሟላም ፤ በመሆኑም የአስር ዓመቱን የብልጽግና መሪ እቅድ ስናዘጋጅ እንደ ራዕይ የወሰድነው በቴክኖሎጂ የዘመኑ የእድል ጨዋታዎችን በማስፋፋት የላቀ ገቢን ማግኘት የሚል ነው። ይህ ደግሞ ለበለጠ ስራ ያነሳሳል።
እዚህ ላይ ግን ባለፉት ዓመታት ለእቅዱ ደካማነት ወይም ደግሞ ተቋሙ በሚፈለገው ደረጃ ላለማደጉ እንደ ምክንያት ከሚነሱ ነገሮች መካከል የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋናውን ቦታ የሚይዝ ሲሆን በዚህ ምክንያት ደግሞ ውጪ አገር የምናሳትመው ሎተሪ እንዲዘገይና ተቋሙም በእቅዱ መሰረት እንዳይሄድ አድርጎታል።
ሌላው የአገር ውስጥ አታሚዎች አቅም ማነስ ሲሆን አሁን ሎተሪን የሚያትመው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ብቻ ነው። ይህ ድርጅት ደግሞ በራሱ ችግሮች ምክንያት እኛ በምንፈልገው ጊዜ ህትመቶችን አያደርስልንም፤ ሎተሪው ባለመታተሙ ገበያ ላይ መቆየት የነበረበትን ጊዜ ይቀንሰዋል ይህ በአሰራር እንዲሁም በገቢው ላይ ችግር እየተፈጠረ ነው።
ሌላው አሁን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልሎች አካባቢ እየተከሰቱ ያሉ የጸጥታ ችግሮች ሎተሪ በአግባቡና በወቅቱ እንዳይሸጥ እያደረጉ በመሆኑ በገቢውና በእድገቱ ላይም የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እስከ አሁን በቴክኖሎጂም ሳይታገዝ የቆየ መሆኑ ራሱን የቻለ ችግር ነው። የስራ ክፍሎችም በመረጃ ቴክኖሎጂ አለመተሳሰራቸው ችግር ፈጥሮ የነበረ ሲሆን ይህንን ለማስተካከል በአሁኑ ወቅት 75 በመቶ ያህል ከሽያጭ ጀምሮ እጣ ወጥቶ ሪፖርት እስከሚደረግ ድረስ ያለውን ሁኔታ በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር እየተሰራም ነው።
የእድል ጨዋታዎች ቁጥጥርም በቴክኖሎጂ አለመደገፍ ሌላው ችግር ሲሆን ለምሳሌ አንድ የስፖርት አወራራጅ ድርጅት በሚገባ ገቢውን መሰብሰቡን በቴክኖሎጂ መቆጣጠር የሚያስፈልግ ቢሆንም እስከ አሁን አልነበረም ፤ ለዚህም ችግር መፍትሔ ለመስጠት አሁን በጀት አስይዘን ለመስራት እየሞከርን ነው።
ሌላው ተቋሙ በመልዕክት ብቻ ሁሉም ጋር ሊደርሱ የሚችሉና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሎተሪዎችን ማዘጋጀት አለመቻሉ ችግር በመሆኑ ይህንንም በመፍታት መስሪያ ቤቱን አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እየሰራን ነው። እነዚህ ነገሮች ከተከናወኑ ደግሞ ድርጅቱ አንድ እርምጃ ወደፊት ሊራመድ ይችላል።
ብሔራዊ ሎተሪ ወደፊት በባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ላይ “የካዚኖ” ጨዋታን ለመጀመር እቅድ አለው፤ የእድል ጨዋታው እውቀት ያለው መመሪያም የሚጠይቅ በመሆኑና በበፊቱም መቋቋሚያ ደንቡ ላይ ስለሌለ ይህንን ለመጀመር ህግና ደንቦች እየተዘጋጁ ነው።
እነዚህ ሲሆኑ ደግሞ መስሪያ ቤቱ በከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ ከመፈጠሩም በላይ በተለይም በቴክኖሎጂ የሚሸጡ ሎተሪዎች እያደጉ ይመጣሉ።
ብሔራዊ ሎተሪ በዓመት በእቅድ ከሚይዛቸው በተጨማሪ ከተለያዩ አካላት የሚመጡና በብሔራዊ ሎተሪ የሽያጭ መዋቅር እንዲሸጡ የሚታዘዙ ሎተሪዎች አሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ ከተቋሙ እቅድ ጋር ይደራረባል። አንዳንድ ጊዜ የእነሱም የእኛም ሳይሸጥ ይቀርና ኪሳራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ ህብረተሰባችን በሎተሪ ጨዋታ ላይ ያለውን እምነትና ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ቴዎድሮስ፦ የሎተሪ ስራ በጣም ትልቅ እምነትን ይጠይቃል፤ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርም ሎተሪዎችን ከማሳተም ጀምሮ ያለውን አሰራር ግልጽ በማድረግ እጣው በሚወጣበት ጊዜም በአዳራሽና ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ የቀጠሮ ቀኑን ሳያዛባ ያወጣል። በዚህም ብዙ ደንበኞችን ለማፍራትና እምነት ለማሳደር እየሞከረ ነው። እጣው ከወጣ በኋላም 2 መቶ 4 ሺ ተከታዮች ባሉት የማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዲሁም በሌሎች መገናኛ መስመሮች ወዲያውኑ እንዲሰራጭ ይደረጋል። ክልሎች ደግሞ ጠዋቱን የእጣው አሸናፊ ቁጥሮች ታትመው እንዲደርሱ ይደረጋል። እድለኞቹንም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን እናሰራጫለን።
ይህም ቢሆን ግን በመላው ዓለም ህብረተሰቡ ሎተሪን የማመን ችግር አለ፤ ስለዚህ መሆን ያለበት ሁሌም ቢሆን እጣው በቀጥታ ስርጭት በቴሌቪዥን ማውጣት ፣ ህብረተሰቡ እድለኞችን እንዲያይ ማድረግና እድለኛው የሚኖርበት አካባቢ ድረስ በመሄድ አደባባይ ላይ በሰፈሩ በአገሩ እንዲሸለም ማድረግ ነው ፤ ይህንንም ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እያደረገ ይገኛል።
በነገራችን ላይ የህብረተሰቡን እምነት ለማግኘት ይህ ብቻ በቂ አይደለም ፤ ይልቁንም በሎተሪ የተገኘው ገቢ ህብረተሰቡን በሚጠቅም የልማት ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ይህም ማለት ለምሳሌ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሚያገኘውን ገንዘብ ገቢ የሚያደርገው ለገንዘብ ሚኒስቴር ነው፤ በዚህ ገቢ ደግሞ መንግስት መንገድ የሚሰራ ከሆነ “ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የተገኘ “ ቢባልበት በደንብ ህብረተሰቡ ውስጥ እምነትን ማስረጽ ያስችላል። ይህ እንዲሆን በ2001 ዓ.ም የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ ደንብ 2001/160 ላይ የወጣ ቢሆንም ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም።
አዲስ ዘመን ፦ አንዳንድ ግለሰቦች ሎተሪ ደርሶኝ መታወቂያ ስለሌለኝ እርዱኝ በማለት ሰዎችን የማጭበርበር ስራ ሲያከናውኑ ይስተዋላል ፤ አስተዳደሩ ለደንበኞቹ የሚያደርገው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ምን መልክ አለው?
አቶ ቴዎድሮስ ፦ አዎ በዚህ መልኩ ከገጠር የመጡ በመምሰል እንዲሁም ሌሎች የማጭበርበሪያ መንገዶችን በመጠቀም ሎተሪ ደርሶን ነው መታወቂያ የለንም በማለት የሰዎችን ንብረት በጠራራ ጸሀይ የሚዘርፉ እንዳሉ እናውቃለን፤ አስተዳደሩ ደግሞ ማድረግ የሚችለውን ማለትም የማህበራዊ ትስስር ገጹን ጨምሮ ሌሎቹንም በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ነው እሱንም እያደረገ ይገኛል። በነገራችን ላይ ብዙዎችም በድርጊታቸው ተቀጥተዋል ።
አዲስ ዘመን ፦ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ ሩብ ምን ያህል አቅዶ ምን ያህሉን ከግብ አደረሰ?
አቶ ቴዎድሮስ ፦ በበጀት ዓመቱ ሩብ ሰባት ዓይነት ሎተሪዎችን ለገበያ በማቅረብ 263 ነጥብ 5ሚሊየን ብር ገቢ ማግኘት ችሏል። ይህም ከእቅዱ አንጻር 92 ነጥብ 9 በመቶ አፈጻጸም አሳይቷል። ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ24 ነጥብ 8 በመቶም እድገትም ያለው ነው። ለእቅዱ ከፍ ብሎ መሳካት ደግሞ እንደ አዲሱ የእንቁጣጣሽ ሎተሪ ፣ ቢንጎና ፈጣን አምስት የተባሉ ሎተሪዎች መምጣት ይጠቀሳል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ቴዎድሮስ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2013