የመርካቶ ገበያና አካባቢው ሁሌም ግርግር አያጣውም። በየቀኑ በርካቶች ሲገበያዩና ሲሸጡ ይውሉበታል። መንገዱን ሞልተው ከላይ ታች የሚተራመሱም ከመረጡት ዘልቀው ያሻቸውን ያገኙበታል። ግዙፉ የገበያ ስፍራ ሆደ ሰፊና መልከ ብዙ ነው። ቦታውን ለሥራ የረገጡ ደክመውና ለፍተው ያተርፉበታል። ያጭበረበሩና የዘረፉም በረቀቀ ስልት ኪሳቸውን ይሞሉበታል ።
በአካባቢው ያሉ የጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆች እንደሌሎች ሁሉ በደራ ገበያ ፈክተው ይውላሉ። በየቀኑ ከእነሱ ቀርቦ የሚገዛና የሚሸጥ ደንበኛን አያጡም። አመዴ ገበያን ይዞ ዙሪያ ገባውን የከበቡ መደብሮች ዓይነ ግቡ እንደሆኑ ዓመታትን ዘልቀዋል።
ሳምንቱን ሙሉ በገበያ ሲተራመስ የሚከርመው መርካቶ ዕለተ ዕሁድን ተግ ብሎ ይውላል። በዚህ ቀን በርካቶች በቦታው አይገኙም። አንዳንዶች ግን ሱቃቸውን ከፍተው ደንበኞችን ይቃኛሉ። ጥቂቶች ደግሞ ቀኑን ለአዳዲስ ሸቀጦች ማከማቻ ይጠቀሙበታል።
ሰንበትን እየጠበቀ የአመዴ ገበያን ማዘውተር የያዘው ገረመው ታዬ ዓይኖቹን በአንድ ጉዳይ ላይ ካሳረፈ ቆይቷል። ሰውዬው ይህን ቀን መርጦ የመመላለሱን ምክንያት ጠንቅቆ ያውቀዋል። በየጊዜው በስፍራው መገኘቱም መረቡ እንደያዘለት ዓሣ አጥማጅ ያስደስተው ይዟል።
ነጋዴው ኪሮስ…
አቶ ኪሮስ ግደይ ከአመዴ ማዞሪያ የወርቅ ቤት ባለቤቶች መሀል አንጋፋው ናቸው። ዓመታትን በሠሩበት የጌጣጌጥ መደብር በርካታ ደንበኞችን አፍርተዋል። ወርቅ ቤቱን ከአባታቸው በውርስ የተረከቡት ነውና ቅርሱን ጠብቀው ለተተኪዎች ለማሳለፍ ሲተጉበት ቆይተዋል።
ኪሮስ በሥራ ቀልድ አያውቁም። ሌሎች በሚያርፉበት የዕረፍት ቀን ጭምር ከመደብር እየገቡ አመሻሽተው ይወጣሉ። ለእሳቸው የሥራ ጊዜ በሆነው የሰንበት ቀን አረፋፍደው የመግባት ልምዳቸውን በርካቶች ያውቁታል። አንዳንዴ ኪሮስ የቀን ዕንቅልፍ ሸለብ ያደርጋቸዋል።
አቶ ኪሮስ ወፍራምና ግዙፍ ናቸው። በመልካም ትህትና በርካቶችን ሲያስተናግዱ ግን አካላቸው አይከብዳቸውም። የአካባቢው ጥበቃዎች እሳቸውን ጨምሮ አንዳንድ ባለሱቆች ዕለተ ዕሁድን ብቅ እንደሚሉ ያውቃሉ። ሰዎቹ ቆይታቸውን ጨርሰው ሲወጡም አካባቢውን ቃኝተው የመደብሮቹን ደህንነት ያረጋግጣሉ።
የቅኝት መቋጫ …
ገረመው ሳምንታትን የቆጠረበት ቅኝት አሁን ሊጠናቀቅ ጊዜው ደርሷል። ዕለተ ዕሁድን መርጦ የተመላለሰበት ጉዳይ እውን ከሆነለትም ምኞቶቹ እንደሚሳኩ ተማምኗል። ይህን ለማድረግ ግን ተጨማሪ እጆች ሊያግዙት ይገባል።
ገረመው ደጋግሞ ከራሱ ጋር ተማከረ። ለመጨረሻው ውሳኔ ከመድረሱ በፊት ምስጢር ጠባቂና ደፋር አጋዦችን መምረጥ አለበት። እነሱ ከጎኑ ቆመው ጉዳዩን በስልት ከቋጩት የዓመታት ህልሙ ይፈታል። ይህን እያሰበ ውስጡ በተስፋ ሲመላ ተሰማው። የፊቱ ፈገግታ እንደፈካ የእጅ ስልኩን አነሳ።
የመጀመሪያውን ስልክ የደወለው የቅርብ ባልንጀራው ተካልኝ ዘንድ ነበር። ተካልኝ ስልኩን እንዳነሳለት የጉዳዩን ጫፍ አስይዞ እንደነገሩ አማከረው። በሃሳብ እንደተግባቡ በአካል ሊገናኙ ወስነው ተቃጠሩ።
ባልንጀራሞቹ ደጋግመው እየተገናኙ በጥልቀት አወሩ። አሁንም ያሰቡትን ዳር ለማድረስ ተጨማሪ ኃይልና ብልሀት ያሻቸዋል። ይህን ሲያውቁ ጠንካራና ብርቱ ያሏቸውን እየመረጡ ለዩ። በመጨረሻ ሦስት ሰዎችን መልምለው ዳግም ለምክር ተቀመጡ።
መኮንን ፣ቢተውና አያሌው ከሁለቱ ባልንጀሮች የቀረበላቸውን ሃሳብ ለመቀበል አላንገራገሩም። እነሱም ቢሆኑ እንደሌሎች ባለሀብትና ታዋቂ መሆንን ይሻሉ። ሁሉም ከአገራቸው ለመውጣት ምክንያታቸው እንጀራን ፍለጋ ነው። ከእነሱ መሀል መኮንንና አያሌው በውትድርና ህይወት አልፈዋል።
መኮንን በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የመከላከያ አባል የነበረና ቆይቶም በቦርድ የተሰናበተ ወታደር ነው። ከስንብቱ በኋላ ትውልድ አገሩ ተመልሶ ከሁለት ትዳሮች አምስት ልጆችን አፍርቷል። አዲስ አበባ በሥራ ፍለጋ ሰበብ ከመጣ በኋላ ‹‹እንጀራዬ›› የሚለው መተዳደሪያ ከልቡ ሳይደርስለት ዓመታትን ቆጥሯል። ሁሌም በአንድ ጊዜ የመክበር ፍላጎቱ ከውስጡ ጠፍቶ አያውቅም።
ቢተው ቀደም ሲል በፖሊስነት የቆየ አባል ነው። በአንድ ወቅት በሥራው ላይ በፈጸመው የስነምግባር ግድፈት ከሥራ ከተሰናበተ በኋላ በህገወጥ ሥራዎቹ ገንዘብ ሲቆጥር ቆይቷል። ቢተው እሱን ጨምሮ አንዳንድ ፖሊሶች ሙያውን ተተግነው የሚሠሩትን ወንጀል ጠንቅቆ ያውቃል። አሁን ለታሰበው ዕቅድ ይህን ልምዱን ቢተገብር እንደሚያዋጣው ገምቶም ሃሳቡን ለሌሎቹ አጋርቷል።
አያሌው የታቀደውን ሁሉ ተቀብሎ ለማጽደቅ የቸኮለ ይመስለል። እሱም ቢሆን አብሮት የቆየው ከእጅ ወደአፍ ህይወቱ እንዲቀጥል አይፈልግም። የባልንጀሮቹን ሃሳብ ተቀብሎ ህልሙን አውን እስኪያደርግ ዕንቅልፍ አጥቶ ሰንብቷል። ሻንጣና ገመድ አዘጋጅቶም የስልክ ጥሪ ሲጠብቅ ቆይቷል።
አምስቱ ሰዎች ሲመክሩ የቆዩበትን ጉዳይ ለመቋጨት ማድረግ ያለባቸውን ድርሻ ለይተዋል። የመረጡት ቀን ዕለት ሰንበትን እንደመሆኑ የሚኖረው ጭርታ ተመችቷቸዋል። ከታሰበው ደርሰው ያቀዱትን ለመፈጸምም በእጅጉ ቸኩለዋል።
የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም
ገና በማለዳው አመዴ ማዞሪያ የደረሱት አምስቱ ሰዎች አስቀድመው ባዘጋጁት ስፍራ አረፍ ብለው አካባቢውን መቃኘት ይዘዋል። የገበያ ቀን ባለመሆኑ የተከፈቱ ሱቆች እምብዛም ናቸው። ከወዲያ ወዲህ የሚሉ የጥበቃ ሠራተኞች አንደወትሮው ሥራቸውን አልዘነጉም።
በዓይናቸው እየተያዩ የአንዱን ወርቅ ቤት መከፈት በጉጉት ናፈቁ። እነሱ እንዳሰቡት ሆኖ መደብሩ በቶሎ አልተከፈተም። ሰዓቱ ረፋፍዶ እኩለ ቀን ሲዳረሰ አብዛኞቹ ተስፋ ቆርጠው መቁነጥነጥ ጀመሩ። ሁኔታቸውን ያስተዋለው ገረመው ግን በትዕግስት እንዲጠብቁ መክሮ ማድረግ የሚገባቸውን መመሪያ በድጋሚ ከለሰላቸው።
ከቀኑ ሰባት ሰዓት ከሠላሳ ሲል በወርቅ ቤቱ አጠገብ ከደረሰ አንድ መኪና የሞተር ድምፅ ሲጠፋ ተሰማ። ይህኔ በስፍራው የነበሩ አምስት ሰዎች ዓይናቸውን ጥለው የበሩን መከፈት ናፈቁ። ጥቂት ቆይቶ ወፍራምና ግዙፍ ሰው ከመኪናው ሲወጡ ታየ። የወርቅ ቤቱ ባለቤት አቶ ኪሮስ ግደይ ናቸው። ሰውዬውን እንዳዩ ሁሉም አፍጥጠው ትዕዛዝና መመሪያን ከገረመው ጠበቁ።
ገረመው የአቶ ኪሮስን ወደ መደብር መግባት ሲያይ ለሁሉም በእጁ ምልክት ሰጠ። በፈጠነ ዕርምጃ ከሰውዬው ጀርባ ደርሶም ከኋላው የቆሙ ጓደኞቹን አስከተለ። አቶ ኪሮስ ገና መግባታቸው ቢሆንም እንግዶቻቸውን ለማስተናገድ አልዘገዩም። ወደ ወርቅ ቤታቸው የገቡት እንግዶች የተለመዱ ደንበኞች መሆናቸውን ገምተው በሰላምታ ንግግር ጀመሩ።
አምስቱ ሰዎች ለአቶ ኪሮስ ሰለምታ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ አልነበራቸውም። ፊታቸውን ኮስተር አድርገው ስለሳቸው መረጃ ደርሷቸው እንደመጡ ተናገሩ። በዚህ መሀል የቀድሞው ፖሊስ ቢተው መታወቂያውን አውጥቶ ማንነቱን ሊያሳያቸው ሞከረ።
ሁሉም በሥራቸው ተጠያቂ እንደሚሆኑ እያዋከቡ ግራ አጋቧቸው። ኪሮስ ይህን ሲሰሙ አልደነገጡም። እሳቸው ህግ አክባሪና ግብር ከፋይ ነጋዴ መሆናቸውን በልበሙሉነት ገልጸው ሁሉም ቤቱን ለቀው እንዲወጡላቸው በአግባቡ ጠየቁ።
ገረመውና ጓደኞቹ የሰውየውን ሁኔታ ባዩ ጊዜ በክርክር መቀጠል አልፈለጉም። ጠጋ ብለው ገንዘብ እንዲሰጡ አስገደዷቸው። ኪሮስ ይህን ሲሰሙ በንዴት ጦፉ። ከእሳቸው ሽራፊ ሳንቲም ማግኘት እንደማይችሉ አስረግጠው ነገሯቸው። ሰዎቹ ይበልጥ ተናደዱ። በድንገት ደርሰው አንገታቸውን አነቋቸው። ከመሬት ወደቁ። ድምፅ አውጥተው እንዳይጮሁ አፍና አፍንጫቸውን አፍነው ትንፋሽ አሳጧቸው። እጅና እግራቸውን አስረው እንዳይላወሱ ጠፈሯቸው።
ወፍራሙ ሰው የሁሉንም ጉልበት የመመከት አቅም አልነበራቸውም። በቁማቸው ሲዘረሩ እያንዳንዳቸው በጭካኔ እየደበደቡ አዳከሟቸው። ጭንቅላታቸው በደም ተነክሮ ትንፋሻቸው ሲቋረጥ በወደቁበት ትተው ጓዳ ወዳለው የወርቅ ካዝና ተንደረደሩ።
ውስጥ ገብተው ከፍ ያለውን ካዝና ለመክፈት ታገሉ። ገረመው የካዝናው ቁልፍ ከአቶ ኪሮስ እጅ እንደማይለይ ያውቃል። በስፍራው ደርሶ ለቀናት ባጠናቸው ጊዜም በወገባቸው ከሚገኝ ሰንሰለት ላይ ይዘውት እንደሚጓዙ አስተውሏል።
በደም ተነክሮ ወደወደቀው የአቶ ኪሮስ አስከሬን ተጠግቶ ወገባቸውን ዳሰሰ። በርከት ብለው ከሚታዩት ቁልፎች መሀል በወጉ የለየውን የካዝና ቁልፍ አውጥቶም በጉጉት ወደሚጠብቁት ጓደኞቹ አመራ። ጓደኞቹ ቁልፉን ከእጁ መንጭቀው ካዝናውን ወለል አድርገው ከፈቱት።
በካዝናው ውስጥ…
ካዝናው እንደተከፈተ ሁሉም ውስጡ ያሉትን ውድ ጌጣጌጦች ለማውጣት ተረባረቡ። እጃቸውን ሰደውም የአቅማቸውን ይዘው ለመውጣት ተሸቀዳደሙ። የሁሉም እጆች እየዘገኑ የሚያወጧቸው ውድ ንብረቶች አፍታ ሳይቆዩ ወለሉን ሞሉት። በርካታ የአንገት ሀብሎችና የእጅ ብራስሌቶች፣ የጣት ቀለበቶችና የእግር አልቦዎች፣ የፀጉር ወለባዎችና የወርቅ ቀበቶዎች ለቁጥር አዳገቱ።
ያልተጨፈለቁ የወርቅ ድንጋዮች፣ ውድ የሚባሉ የአልማዝና የብር ጌጦች፣ የከበሩ የማዕድን ድንጋዮችና ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው አርቴፍሻል ጌጣጌጦች፣ የወርቅ ሰዓቶችና ቁጥራቸው የበዛ የወርቅ ሳንቲሞች፣ ቁልፎች፣ ፈርጦችና ሌሎችም እየተዘረገፉ ተቆለሉ። ሁሉን በየመልኩ መዝኖ ለመለየት ያላሻቸው ዘራፊዎች በዓይን ለመቁጠር ያታከቷቸውን ውድ ንብረቶች በግምት እየመደቡ ለመካፈል ቅርጫ ገቡ። ይህ ሁሉ ሲሆን የአቶ ኪሮስ ትኩስ ደም ከወለሉ ወርዶ መድረቅ እየጀመረ ነበር።
ሰዓታትን የፈጀ የወርቅ ክፍፍላቸው እንዳበቃ እምብዛም ሳይደክሙ ያገኙትን ብርና የውጭ አገራት ገንዘቦች፣ የጠገራ ብሮችና በአደራ ተለይቶ የተቀመጠ ተጨማሪ ገንዘብን አክለው ከድካማቸው አረፍ አሉ።
አምስቱ ዘራፊዎች ያሰቡትን በስኬት እንዳጠናቀቁ በፈገግታ ሲተያዩ ቆዩ። ምሽቱ ሳይገፋ ከገቡበት መውጣትን አልፈለጉም። ሬሳ ቢያጋድሙም አንዳቸውም የተፀፀቱ አይመስልም። በወርቅ ቤቱ ከወዲያ ወዲህ ሲሉ ቆዩና ሰዓታቸውን ተመለከቱ። ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ከሠላሳ ሆኗል። ሰዎቹ ከዚህ በኋላ መቆየትን አልፈለጉም። በአስቸኳይ ታክሲ ጠሩና የየድረሻቸውን ተሸክመው ከወርቅ ቤቱ ወጡ።
ከደጅ ያሉት ዘቦች የአቶ ኪሮስን ወደወርቅ ቤት መግባት እንጂ ተመልሶ መውጣትን አላዩም። አንዳንዴ ሰውየው ከድካማቸው ለማረፍ ሸለብ እንደሚያደርጋቸው ያውቃሉ። የዛሬውን ያህል በራቸውን ክፍተው ሲተኙ ግን አጋጥሟቸው አያውቅም። የዕለቱ ጥበቃዎች የበዛ ጥርጣሬ ቢያድርባቸው ከደጅ ሆነው ደጋግመው ተጣሩ። ምላሽ አልነበረም። እንደተደናገጡ ገርበብ ያለውን በር ከፍተው ወደውስጥ ዘለቁ ።
ጉዞ… ህልምን ለማሳካት
አምስቱ ዘራፊዎች የድርሻቸውን እንደያዙ ‹‹ህልማችን›› የሚሉትን መንገድ ለማቃናት ውጥን ያዙ። መኮንን በእጁ የገባውን በርከት ያለ ወርቅና ገንዘብ ተሸክሞ ምን እንደሚሠራበት ሲያወጠነጥን ቆየ። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም የመጣለትን ሃሳብ ለመፈጸም ከውሳኔ ደረሰ። በዕለቱ በጥሬ ገንዘብ ከወሰዱት 465 ሺ ብር ውስጥ ለጊዜው 93ሺ ብር ደርሶታል። ውድ ጌጣጌጦቹን ጨምሮ ከውጭ ሀገራት ገንዘቦች ያገኘው ድርሻም በቀላሉ የማይገመት ሀብት ያካብትለታል።
ይህን እያሰበ ሚስቱን ጠርቶ በርከት ያለ ወርቅ ሰጣት። ከሚታወቅ ወርቅ ቤት እያስመዘነች እንድትሸጥና ብሩን ቆጥራ እንድትቀበል አዘዛት። ከየት እንዳመጣ ጠየቀቸው። በትርፍ ለመሸጥ እንደገዛው ነገራት። አመነቸው። ቆይቶም 700 ሺ ብር ተቀበላት። ወዲያው ባህርዳር ወዳለው በርበሬ ነጋዴ ወንድሙ ደወለ። ለጥብቅ ጉዳይ እንደሚፈልገው ነግሮም በማግስቱ እሱ ዘንድ ገሰገሰ። በእጁ ካሉት መሀል ከሦስት የወንድ ቀለበቶች ሽያጭ 13 ሺ ብር ቆጥሮ ከወንድሙ ተረከበ።
ገረመው የደረሰውን በርከት ያለ ገንዘብና ጌጣጌጥ ይዞ የወንድሙ ልጅ ዘንድ ደወለ። በስሙ አይሱዙ ሊገዛ ማሰቡን ሲነግረው ወጣቱ ተደስቶ በሃሳቡ ተስማማ። ቃሉን ጠብቆ አዲስ አበባ ሲደርሰ አጎት ሁሉን ጉዳይ አጠናቆ ጠበቀው። መኪናው ተገዝቶ ሥራ ጀመረ።
ቢተው ከባልንጀሮቹ የተጋራውን ገንዘብና ጌጣጌጦች ይዞ ዴዴሳ ወላጅ አባቱ ቤት ተጓዘ። ከቡና ማሳ ውስጥ ቀብሮም ጥቂት ገንዘብ ይዞ ተመለሰ። ወርቆቹ በቁጥር አራት መቶ አርባ ይሆናሉ። አንድ ኪሎ ግራም የሚመዝኑ የብር ጌጣጊጦችና በርከት ያሉ ማርትሬዛ ብሮች ታክለውበታል።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ስፍራ ደርሶ የግለሰቡን በሰዎች መገደልና ግምቱ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መዘረፉን አረጋግጧል። በመርማሪ ዋና ሳጂን ሲሳይ ተሾመ የሚመራው ቡድንም የተጠርጣሪዎችን ማንነትና መገኛቸውን ለማወቅ እጅግ ፈታኝ ትግል አካሂዶ በመጨረሻው በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።
ውሳኔ
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012
መልካምስራ አፈወርቅ