በዓለም ዙሪያ ላሉት ሙስሊሞች ረመዳን በዓመቱ ውስጥ በጣም ከተከበሩ ወራት አንዱ ነው፡፡ በእስላማዊው የቀን አቆጣጠር ወይም አልሂጅራ መሠረት በዚህ ዘጠነኛው ወር አላህ ከቅዱስ ቁርአን የመጀመሪያዎቹን ዓረፍተ ነገሮች (አያ) ለነቢዩ መሐመድ በመልዕክተኛው ጂብሪል አማካኝነት እንዲገለጥለት አድርጓል ተብሎ ይታመናል።
ከዓለማችን አጠቃላይ ሕዝብ ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጉት ሙስሊሞች በዓመት አንዴ በረመዳን ወር እንዲፆሙ ኃይማኖታዊ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። አንድ ሙስሊም ሙስሊም ለመባል ከሚፈፅማቸው መንፈሳዊ ግዴታዎች በቀን አምስት ጊዜ መስገድ እና በረመዳን ወር (በጤና አሊያም በጉዞ ላይ ያለ ሰው ካልሆነና በዚህም የተፈቀደለት ካልሆነ በቀር) መፆም መሠረታዊዎቹ ምሰሶዎች ናቸው። በዚህም በወሩ ውስጥ ባሉት ሰላሳ ቀናት ከእኩለ ሌሊት እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ ለአካለ ፆም የበቃ ወይም «ባሊግ» በሆነው የእምነቱ ተከታይ ሁሉ ከምግብና መጠጥ በመታቀብ ቀኑን በፆም ያሳልፋሉ። እናም አስተምህሮቱ በሚያዘው መሠረት የረመዳንን ወር መግባት የምታበስርውን አዲስ ጨረቃ ተከትለው ይፆማሉ። ሙስሊሞች በጾም አማካይነት ከፈጣሪያቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚችሉ፣ መንፈሳዊ ብርታትን እንደሚጎናፀፉ እና ከድሃው ጋር ልባዊ ትብብርን እንደሚያጎለብቱ ያምናሉ።
በወሩ እያንዳንዷን ቀናት በሚከውኗቸው እንደ ሶላት፣ ቅዱስ ቁርዓንን ማንበብ እና ምፅዋት መስጠት ያሉ የሥነአምልኮ ተግባራት ከእምነታቸው ጋር ያላቸውን መንፈሳዊ ትስስር ያጠናክራሉ እንዲሁም ከወዳጆቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደገና ለማደስ ይሞክራሉ።
ከረመዳን ወር ትሩፋቶች አንዱ የሆነውና በብዙዎቻችን አእምሮ የሚሳለው ልክ ፀሐይ እንደጠለቀች የሚከናወነው የፆም ፍቺ ወይም ኢፍጣር የሚባለው ሥነሥርዓት ሲሆን ብዙውን ጊዜ በዚህ ሰዓት ሙስሊሞች ከበርካታ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በመሆን በመኖሪያ ቤታቸው አልያም በየቤተ እምነቶቻቸው ማዕድ የሚቋደሱበት ሰፊ የአብሮነት መድረክ ነው።
የጾም መግደፊያ ሰዓታት በፀሐይ መግቢያ እና በፀሐይ መውጫ ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን ይህም ከቦታ ወደ ቦታ ያለውን የጊዜ ልዩነት ይወስናል። ለምሳሌ ያክል በዚህ ዓመት የረመዳን ጾም በለንደን ከሲድኒ ይልቅ ረዘም ላለ ጊዜ ይቆያል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሲኮን አካላዊ ብቃት ያላቸው ብቻ መጾም ይጠበቅባቸዋል፣ ማለትም የታመሙ ሙስሊሞች ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ጾመኛ የሆኑ ሰዎች መብላትና መጠጣት በሚፈቀድበት ከምሽት እስከ ንጋት ባለው ጊዜ መጠቀም እንዲችሉ እና ሰፋ ያለ ሰዓት ለማሳለፍ ዘግይተው ይቆያሉ፡፡ ለፀሐይ መጥለቅ፣ ቅድመ-ጠዋት ምግብ መቀስቀስ ባህላዊ ነው፣ ይህ ካልሆነ በስተቀር ለቁርስ አማራጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡
ቁርአን ለነቢዩ ሙሐመድ «ሌይለቱል ቀድር» በመባል በሚታወቁት የረመዳን የመጨረሻዎቹ 10 ምሽቶች በአንዱ እንደተገለፀላቸው ይታመናል። አንዳንድ የእምነቱ ተከታዮች የሃይማኖታዊ እውቀታቸውን ከፍ በማድረግ ላይ በማተኮር በመጨረሻዎቹ ቀናት መስጊድ ውስጥ ለመኖር እና ለመተኛት ይመርጣሉ፣ አሁን ኳራንታይን የምንለው ዓይነት ማለት ነው።
ኮሮናቫይረስ በጾሜ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
ለአቅመ አዳም ለደረሰ ማንኛውም ጤነኛ ሙስሊም በረመዳን ወቅት መጾም ግዴታ ነው። በዚህ አስገዳጅ ያልታቀፉት ልዩ ሁኔታዎች ለልጆች፣ ነፍሰጡር ለሆኑ ሴቶች፣ የወር አበባ ላይ ለሆኑ እንስቶች፣ ለሚያጠቡ እናቶች እና የታመሙ ወይም ተጓዥ ለሆኑ ሰዎች የተሰጡ ናቸው፡፡ የኮቪድ -19 ምልክቶች የሚታዩባቸው ሰዎች በአካል አቅም ከሌላቸው በረመዳን ወቅት መጾም አይጠበቅባቸውም።
በበርካታ ማህበረሰቦች ዘንድ የረመዳን ቀን ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው ንጋት ከመጀመሩ በፊት ነው። በዚህን ጊዜ ሙሳሃራቲ የተሰኘው የስሁር አዛን ጿሚዎችን በመቀስቀስ የቀጣይ ቀን ፆም ዝግጅት እንዲያደርጉ የማንቂያ ጥሪ ያስተላልፋል። ለቅድመ-ንጋት ሥነ-ሥርዓት በወቅቱ ነዋሪዎችን የሚቀሰቅሳቸው እና የተባረከ ወር እንዲመኙ የሚያደርገው ይኸው ሙሳራቲ ነው፡፡ ነገርግን በዘንድሮው ዓመት ከወረርሽኙ እገዳ ጋር ተያይዞ ሀገራት በጣሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳቢያ የሙዝሃራቲ አዛንም
በነዚሁ ሕጎች የሚገዛ በመሆኑ በሌሊት የመመገቢያ ሰዓት ቀስቃሽ አይኖርም፡፡
በረመዳን የቀን ወቅትም ሙስሊሞች እንደሌላው ጊዜ ሁሉ መደበኛ የሕይወት እንቅስቃሴዎቻቸው አይቋረጥም። ሥራ ይሰራሉ፣ ትምህርት ይማራሉ፣ ወዘተርፈ ከምግብና ከመጠጥ ከመታቀብ ባሻገር የተለመደው የኑሮ እንቅስቃሴያቸው በነበረበት ይቀጥላል። ይሁን እንጂ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ አስገድዷቸዋል። ይህ የማህበራዊ ግልጋሎት መስጫ ተቋማት መዘጋት ለአንዳንዶቹ ጿሚዎች እፎይታን ሊያመጣ ይችላል-ብዙውን ጊዜ ወደ ሥራ ሲሄዱ እና ሲመለሱ የሚያባክኑትን ሰዓት ይልቁንም ማታ ማታ በፆም ምክንያት የሚያጠፉትን የእንቅልፍ ጊዜ ቀን ላይ ለመተኛት ሊተኩበት ይችላሉ።
በእስልምና እምነት ዘንድ ታላቁ ነቢይ ተደርገው በሚወሰዱት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰላምና እዝነት በርሳቸው ላይ ይውረድ) ቅዱስ ቁርአን የተገለጠበት ወር ነው የረመዳን ወር፡፡ በዚህ ጊዜ ምእመናን ከንጋቱ እስከ ውድቅት ድረስ ይጾማሉ፤ ከተከለከሉ ተግባራትም ይታቀባሉ። ልክ ፀሐይ እንደጠለቀችም ፆማቸውን በመግደፍ የምግብ፣ የጸሎት እና የአብሮነት ጊዜን ያሳልፋሉ፡፡ የወሩ አንድ ታዋቂ መለያም ረመዳን አስከትሎት የሚመጣው አብሮነት ነው፡፡
በዚህ ዓመት በሁሉም ሀገሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ካለው ወረርሽኝ አንጻር ሲታይ ሙስሊሞች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ እሙን ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሙስሊሞች ቀኑን ሲጾሙ እና በተመደቡት የጸሎት ጊዜያት ደግሞ በቡድን ወይም በጀማኣ ፀሎቶች ይካፈላሉ፣ ይህ በእምነቱ የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ግን ዛሬ ላይ ይህ ሥነአምልኮ አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህኛው ረመዳን፣ የጤና ባለሙያዎች እና የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ባስቀመጡት መመሪያ መሠረት አካላዊ ፈቀቅታን ተግባራዊ ማድረግ ተመራጭ ነው።
ኮሮናቫይረስ ከሰው ወደ ሰው በጥግግት መተላለፉ ተረጋግጧል። እናም ለዚህ ሲባል በርካታ ሀገራት (የሙስሊም ሀገራት ሳይቀሩ) የቡድን ሥነአምልኮ የሚከናወንባቸውን ቤተ እምነቶች አግደዋል። ይህ የጀማኣ የፀሎት ሥነ ሥርዓት ደግሞ በረመዳን ወቅት እጅግ እንደሚበዛ ይታወቃል። መንግሥታት ይህንኑ ከግምት በማስገባት በረመዳን ወር የሚከናወኑ የቡድን ስግደቶችን ማገዳቸው ተገቢ ነው ማለት ይቻላል፤ ከሕዝቡ ደህንነት አኳያ ሲታይ።
የዘንድሮው ፆም ከሌላው ጊዜ በምን ይለያል?
በረመዳን ቅዱስ ወር ሙስሊም አማንያን ከንጋት በፊት ሱሁር የሚባለውን ማእድ ለመቋደስ ቀደም ብለው ይነቃሉ እንዲሁም ቀኑን በፆም አሳልፈው ልክ ፀሐይ ስትጠልቅ ደግሞ ኢፍጣር በተሰኘው ማእድ ፆማቸውን ይገድፋሉ። ብዙውን ጊዜ ኢፍጣር በጋራ የሚከናወን ሥነሥርዓት ነው። በተለይም በመስጊዶች ትላልቅ የኢፍጣር መርሀግብሮችን በማዘጋጀት ድሆችን ማስፈጠር የተለመደ ነው።
ነገርግን ከሁለት መቶ በላይ በሆኑ የዓለም ሀገራት የተዛመተው ወረርሽኝ የሱሁርም ሆነ የኢፍጣር ማእድ ዝግጅቶች የተለመደውን የጀማኣ ማእድ በማስቀረት ዜጎች በቤታቸው በግል ወይም በቤተሰብ አባላት ብቻ እንዲቋደሱ አስገድዷል። ለምሳሌ በግብፅ ሁሉም የረመዳን ሥነአምልኮዎች የጀማኣ ኢፍጣር እና የሰደቃ ማእዶችን ጨምሮ በመንግሥት እገዳ ተጥሎባቸዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት ለእንዲህ ዓይነት ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ መድረኮች በተቻለ መጠን ዜጎች እንዲያስወግዱ እና ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ ይመክራል።
በበርካታ ሀገራት ወሩን ሙሉ የሚከናወኑ ትላልቅ የምግብ የመጠጥ እንዲሁም የአልባሳት ባዛር ማዕከላት ዝግ ሆነው እንዲቆዩ እገዳ ተጥሏል። ይህ ከመንፈሳዊነቱ ባሻገር በተለይም በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ተቋማት ላይ መጠነሰፊ የኢኮኖሚ ተፅእኖ እንደሚያሳድር እና የገቢ ምንጫቸው በዚህ ላይ ለተመሰረተ ዜጎች እጅግ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው።
በነገራችን ላይ ረመዳን የምግብ ፍጆታ የሚንርበት ወቅት ነው። ካለንበት ዓለምአቀፋዊ ሁኔታ አንፃር ዜጎች እገዳው በሚያሳድርባቸው ስጋት ከረመዳን ወቅት የግዢ ፍላጎት ማሻቀብ ጋር ተደምሮ ከፍተኛ የገበያ እጥረት እንደሚያጋጥም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የአካላዊ እና የማህበራዊ መራራቅ መመሪያዎች በራሳቸው የረመዳንን የአብሮነት መንፈስ በእጅጉ ያደበዝዙታል። ራመዳንን የምናስታውሰው የፍቅር ትስስራችን፣ ዘመድ ለዘመድ የምንጠያየቅበት፣ ጎረቤት ለጎረቤት የምንዋሃድበት፣ ተቃቅፈን የምንሳሳምበት፣ የምንጨባበጥበት ወር ሆኖ ሳለ የኮሮናቫይረስ ያንን ሁሉ እሴታችንን በአንዴ አስወግዷል።
በጋራ መስገድ አሁንስ ይፈቀዳልን?
የጀማኣ ስግደት በበርካታ ሀገራት ኢትዮጵያንም ጨምሮ ተከልክሏል። በርካታ መስጊዶችም በጊዜያዊነት እንዲዘጉ ተደርጓል። ልብ አድርጉ ዓመቱን ሙሉ በመስጊድ ደጃፍ አልፈው የማያውቁ የኔቢጤ የተዘናጉ ሙስሊሞች ከፈጣሪያቸው ጋር ለመታረቅ በመስጊድ ለመገኘት ቀጠሮ የሚይዙት በረመዳን ወር ነበር። ከረመዳን ወቅት የጀማኣ ስግደቶች በፊት የዕለተ ዓርብ የጁምአ ሰላት ነበር በኮቪድ ምክንያት እንዲቀር የተደረገው። መንፈሳዊ መሪዎቻችን በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ፈትዋ ወይም ብይን አማኞች አምስቱን መደበኛ ሰላቶች ከቤታቸው ሁነው እንዲሰግዱ መመሪያ አስተላልፈዋል። ጀመኣም ከቤተሰብ መጀመር እንዳለበትም አፅንኦት በመስጠት ለሕዝቡ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በሳኡዲ አረቢያ ንጉሥ ሰልማን በሁለቱ ታላላቅ የእስልምና ቅዱስ ስፍራ በሆኑት መካናት መዲና መስጊዶች የሚደረገው የተራዊህ ስግደት በዝግ ቁጥሩም አጥሮ እንዲሰገድ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። እንደ ፓኪስታን ያሉ ሀገራት ደግሞ የጀማኣ ሰላትን ቀደም ሲል የእምነቱ አስተምህሮ ወጣ ባለ መንገድ አማኞች እንደወትሮው ትከሻ ለትከሻ ገጥመው ሳይሆን ስድስት ጫማ ያክል ርቀት በመካከላቸው ትተው በግል የመስገጃ ምንጣፎቻቸው ላይ እንዲሰግዱ ፈቅዳለች።
ድሮ ድሮ በአካል ብቻ የሚደረጉ መንፈሳዊ ተግባራት አሁን እንደማንኛውም ዓለማዊ የሕይወት መስክ በቴክኖሎጂ መስመር መሰጠት ጀምረዋል። የጁምአ እና የጀማኣ ስግደቶች በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ይተላለፋሉ። ኃይማኖታዊ ትምህርቶች ላይ ምእመናን በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲታደሙ እየተደረገ ይገኛል።ሌላም ሌላም። አሁን በዓለም ዙሪያ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዕድሜ ለኮሮና ወረርሽኝ የወትሮውን ኃይማኖታዊ ባህላቸውን ወደ ጎን በመተው አዲስ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ኢስላማዊ ባህልን በማላመድ ላይ ይገኛሉ።
ለድሆች የሚበረከተውን ምፅዋት በተመለከተ
ከእስልምና መሠረቶች አንዱ የሆነው ሰደቃ እና የዘካት ምፅዋት ተግባር በረመዳን ወቅት እጅግ የሚወደድ ሃይማኖታዊ ተግባር ነው።
ለደህንነት ሲባል ይህንኑ የተቀደሰ ምግባር ሙስሊሞች የሚያበረክቱትን ሰደቃ ወይም ዘካ በእርዳታ ድርጅቶች በኩል እንዲለግሱ የእምነት ተቋማት መሪዎችና የጤና ባለሙያዎች መመሪያ ሰጥተዋል። በዚህ መልኩ የሚሰባሰበው እርዳታም በወረርሽኙ ለተጎዱ ዜጎች ከአንድ ቋት የሚከፋፈል ይሆናል። ይህም በእርዳታ አሰጣጥ ዙሪያ የሚፈጠሩ የሰዎች ጭንቅንቅ እንዲቀር በማድረግ የበሽታውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ይረዳል በማለት የዓለም የጤና ድርጅት ከመመሪያው እንዲካተት አድርጓል። በሀገራችንም በዚህ ረገድ አበረታች በጎ ጅማሮች የሚስተዋሉ ሲሆን ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
የተራዊህ ስግደት በኮሮና ወቅት
አብዛኛው ኡለማኦች በኦንላይን የሚደረገውን የጀማኣ ሰላት ቢቃወሙም የተወሰኑ መስጊዶች ቀደም ሲል የተከለከለውን የጁምአ ሰላት ራሱ ቀደም ብለው በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍ ጀምረዋል። የተራዊህ ስግደትም ከዚህ የተለየ አይሆንም። በወረርሽኙ ምክንያት መስጊዶቻችን በመዘጋታቸው ምእመናን ከቤታቸው ሆነው በቤተሰብ ጀማአ መስገድ እንደሚችሉ ሃይማኖታዊ ብይን ተሰጥቷል። እርግጥ ነው የቡድን ሰላት በተለይም ደግሞ በረመዳን ወቅት የላቀ ምንዳ እንደሚያስገኝ ይታመናል። ነገርግን አሁን ካለንበት አስቸጋሪ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ያ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በወረርሽኙ ምክንያት ሁሌም ክፍት የሚቆዩ ቤተ አምልኮዎች በመላው ዓለም ተዘግተው እንዲሰነብቱ ተደርጓል። እስልምና ከሁሉም በላይ ለጤናና ለደህንነት ቅድሚያ ይሰጣል። የጀማኣ ምንዳን ለማግኘት ደግሞ ከአንድ በላይ ሆኖ መስገድ ከተቻለ ተመጣጣኝ ምንዳ እንደሚያስገኝ የእውቀት ባለቤቶች ያስተምራሉ።
ቸር ያገናኘን
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ