የማይደገሙ ሁኔታዎችና ክስተቶች ግጥምጥሞሽን ይወልዳሉ፡፡ ኮቪድ 19 ቫይረስ በዓለም ተማሪዎች ዘንድ ይሄን ክስተት ፈጥሯል፡፡ የሁሉም ዓለማትና አገራት የትምህርት ተቋማት ለመዘጋት ቀንና ሰዓት ጥቂቶቹም ወራት ከመለያየታቸው በመስተቀር ክርችም እንዲሉ ሆነዋል፤ አሁንም አልተከፈቱም፤ እስከ መቼ ይከፈታሉ የሚለውም መልስ የለውም፡፡ በዚህ የተነሳም የየአገራቱ የትምህርት ዘርፍ የበላይ መሪዎችና አስተዳዳሪዎች መፍትሄ ያሉትን ማማተርና መተግበር መጀመራቸውን መረጃዎች ያሳያሉበመፍትሄነትም የቴክኖሎጂ አሠራሮችን በማበልፀግ ከቤታቸው ድረስ ትምህርቱን ማንቆርቆር በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መገለላቸውን በማስረሳት ከአስተማሪዎቻቸው፣ ከክፍል ጓደኞቻቸውና ከለመዱትን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያልተለያ ያስመስላል፤ ይሄ መሆኑ ለተማሪዎች ሥነ ልቦናዊ መረጋጋት መልካም እንደሆነም ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
ኢትዮጵያም ከትምህርት ገበታዎች የራቁት ተማሪዎች በቤታቸው ተቀምጠው መማር የሚችሉባቸውን አማራጮች ስታማትር ቆይታለች፡፡ አሁን ላይ ሬዲዮና ቴሌቭዥንን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ድረስ ለማስተማር ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ እኛም በዛሬው ቅኝታችን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተዘየደላቸውን መላ ምንድነው ስንል የሚመለከታቸውን አካላት ጠይቀናል፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ እንዳሉት፣ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀው መቆየታቸው ተገቢ አይደለም፡፡ ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ የሚፈጥርባቸው ሥነ ልቦናዊ ጫና ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ባሉበት ሆነው በቴክኖሎጂ የሚማሩበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ ዕድሉን አግኝተው ለሚከታተሉ እሰየው ነው፡፡ ዕድሉ የሌላቸውም ምንም የሚፈጠር ተጽዕኖ ባለመኖሩ ሊያሳስባቸው አይገባም፡፡ ተማሪዎች ዝም ብለው ከሚቀመጡ በሚል የሚሰጥ የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ታግዘው ሊሰጡ በሚሞከሩ ትምህርቶች ገጠርም ሆነ ከተማ፣ ቆላም ሆነ ደጋ የሚኖሩ ተማሪዎች እኩል ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳ ሊፈጠሩ በሚችሉ ልዩነቶችም ተማሪዎች በፍፁም ሊያስቡ አይገባቸውም፡፡ የከተማ ልጆች ብቻ በኦንላየን እየተማሩ ነው ብለውም ማሰብ አይገባቸውም፤ ሊያስጨንቅና ሊያሳስባቸውም አይገባም፤ ምክንያቱም ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ትምህርት የሚጀምረው ለሁላቸውም ተማሪዎች እኩል በሆነ አግባብ ነው፤ ከበፊትም ቢሆን ከገጠራማው የአገሪቱ ክፍል የሚመጡና ከተማ ያደጉ ተማሪዎች እኩል ዕድል አግኝተው ማደግ አለማደጋቸው ችግር ፈጥሮባቸው አያውቅም፡፡ ስለዚህ በተፈጥሮም ልዩነቶች የሚኖሩ በመሆናቸው በቴክኖሎጂ የመማር ዕድሉን ከመከልከል ዕድሉን አመቻችቶ መጠቀም የሚችሉት ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረጉ ተመራጭ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እንኳን በተማሪዎች መካከል በአገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከልስ እኩል የሆነ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይችላሉ ወይ? በእነሱ በኩል ለተማሪዎቻቸው የሚደረጉ እገዛዎችስ ይኖሩ ይሆን በሚል ለተነሳላቸው ዳይሬክተሩ ሲያብራሩ፤ ዩኒቨረሲቲዎቹ ተማሪዎቻቸው በቴክኖሎጂ (በኦንላይን) ትምህርታቸውን መከታተል የሚያስችላቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ግዴታቸው ነው፡፡ በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በሕጋዊ አሠራር የተደገፈ ነው፡፡ መምህራንም ሆኑ ማንኛውም ሠራተኛ በሥራ ላይ ናቸው፡፡ እነሱ መደበኛ ሥራቸው በመሆኑ የቀሩትን ምዕራፎችና፣ የትምህርት አይነቶች በ‹‹ኦንላይን›› እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ይገባቸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ መንገዶች በዌብሳይት፣ በቴሌግራም እና በሌሎችም ቴክኖሎጂዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት አካል የሆነ ራሱን የቻለ ተቋም በመኖሩ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ያግዛል፡፡ ተማሪዎች የትኛውንም አማራጭ ተጠቅመው ትምህርቱን ለማግኘት ሲሞክሩና ‹‹ዳታ›› ሲከፍቱ ገንዘብ እንዳይቆጥርባቸው ለማድረግ ከቴሌ ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን አቶ ደቻሳ ገልፀዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች ጋር ተማሪዎች ባሉበት ሆነው ትምህርት ማስቀጠል በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ሚያዝያ ስምንት መክረዋል፡፡ በውይይቱም ሚንስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም፣ የድህረ ምረቃና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በ‹‹ኦንላይን›› እንዲከታተሉ አቅጣጫ ተቀምጧል፣ ዩኒቨርሲቲዎቹ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጥሩና መምህራንም በ‹‹ኦንላይን›› የሚሰጡ ትምህርቶችን በማመቻቸት በተለያዩ መንገዶች ተደራሽ በማድረግ እንዲያስቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ምርምሮቻቸውን ለማድረግ መረጃ ማሰባሰብ አዳጋች ካልሆነባቸው በስተቀር የጨረሱት ተለይተው ከአማካሪዎቻቸው ጋር በምርምሮቻቸው ላይ በ‹‹ቪዲዮ ኮንፈረንስ›› የሚወያዩባቸው ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ሲሉም አክለዋል፡፡
የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችም በበኩላቸው ባሉበት ሆነው በንባብ የሚያሳልፉባቸው ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው አቅጣጫ ተቀምጧል፤ ይሄን የሚያስተገብሩ ዩኒቨርሲቲዎችም ተለይተዋል፡፡ በመሆኑም የሁለተኛ አጋማሽ የሁሉም ትምህርት ዓይነቶች ሞጁሎች፣ አጋዥ ንባቦች እና ሌሎችም በየትምህርት ዓይነቱ ተሰንደው የሚገኙባቸው ዌብሳይቶች በመሟላት ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም በ( http://ndl.ethernet.edu.et/ ) ‹‹ዲጂታል›› ቤተ መጽሐፍት ዝግጁ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡
በርካታ ይዘቶችን የያዘ የTechin ቤተ መጽሐፍት ዝግጁ ሆኗል፡፡ ( http://liberary.techin.et) የ‹‹ኦን ላይን›› ትምህርት መስጠት የሚያስችል የ Learning Management System /MOOCS ዝግጁ መደረጉም ተጠቅሷል። (https://courses.ethernet.edu.et)ተማሪዎች በስልካቸውም ይሁን በሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ወደእነዚህ ዌብሳይቶች ገብተው ሲጠቀሙ በነፃ እንዲሆኑላቸው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ሥራዎች በመፀራት ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ ወረርሽኙ መቼ እንደሚገታ ባይታወቅም ሥጋት አለመሆኑ ተረጋግጦ ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እስኪመለሱ ድረስ በተጠቀሱት አድራሻ የቀረቡላቸውን መርጃ ቁሳቁሶች እያነበቡ መቆየት አለባቸው፡፡ ሲመለሱም እንደየ ተቋማቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ቀሪ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁባቸው ቀሪ ፕሮግራሞች እንደሚመቻቹም ተመላክተዋል፡፡
የምረቃና ድሕረ ምረቃ ተማሪዎችን በሚመለከት አብዛኛዎች የማስተርስና የፒኤች ዲ ተማሪዎች በምርምር ላይ እንደመሆናቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንደየራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ትምህርቱን በ‹‹ኦን ላይን›› ለማስቀጠል እንዲያመቻቹ ሆኗል፡፡
ለመማር ማስተማሩ የሚያግዙ ቁሳቁሶችም በ‹‹ኦን ላይን›› ፣ በኢሜይል እና ሌሎች ዘዴዎች ለተማሪዎች እንዲቀርብ እየተሠራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ከአማካሪዎቻቸው ጋር የሚገናኙበት የ‹‹ኦን ላይን›› የምስል ውይይት ማካሄድ፣ ማንኛውንም ሰነዶች ማጋራት እና ሌሎችንም የምስል ግንኙነቶች ማድረግ የሚያስችል የ0.365 Teams ቴክኖሎጂ ተዘጋጅቷል፡፡ በተጨማሪም በአገር ውስጥ የተሠሩ የመመረቂያ ጥናትና ምርምሮች (ቴሲስ ኤንድ ድዝርቴሽን) ሰነዶች ለማጣቀሻ ይሆኑ ዘንድ (https://nadre.ethernet.edu.et/ ) ዝግጁ መደረጋቸውን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ዩኒቨርሲቲዎች እንደየትምህርት ክፍላቸውና የትምህርት አይነቶቹ እና እንዳስፈላጊነቱ ተጨማሪ የመገናኛ አማራጮችን ማመቻቸት እንደሚችሉም ተፈቅዶላቸዋል፡፡
ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት በበኩላቸው ሐሳባቸውን ሲቋጩ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር በዓለም ያጋጠመውን ፈተና ከግምት በማስገባት በሁሉም ዘርፍ በኢትዮጵያ ትምህርትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡ https://t.me/MinistryoSHE መረጃ ማግኘት የሚያስችል ተጨማሪ አማራጭ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከ80 ሺህ በላይ መጽሐፍት፣ የአንደኛ ዓመት የትምህርት አይነቶች እና የተለያዩ የመመረቂያ ጥናቶች ዝግጁ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16 ቀን 2012
መሃመድ ሁሴን