ሁለቱም ቀላ ያሉ ናቸው፤ ኧረ እንዲያውም አንዷ ብስል ቀይ የሚሏት አይነት ነች። ተክለ ቁመናቸውን ላስተዋለ ደግሞ ቀጠን ብለው መለል ያሉ ናቸው። ፊታቸው ላይ የወጣትነት ስሜት ሲፍለቀለቅ ይስተዋላል። ወጣቶቹ የልጅነት ህልማቸው አውሮፕላንን ማብረር ነው። ከዚህ ህልማቸውም የሚያስተጓጉላቸው ነገር እንደማይኖር በልጅነት እድሜያቸው ለራሳቸው ቃል ገብተዋል፤ እናም ህልማቸው ቅዠት ሆኖ እንዳይቀር ሳይታክቱና ተስፋ ሳይቆርጡ ጥረዋል። ከእነዚህ ወጣት ሴቶች ጋር የዛሬውን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ አዲስ ዘመን የኢትዮጵያውያን ኩራት ወደሆነው ወደኢትዮጵያ አየር መንገድ በማቅናት እንግዳው አድርጓቸዋል።
መጀመሪያ ያነጋገርናት ወጣት ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ ቦሌ አትላስ አካባቢ ነው። የተማረችው ናዝሬት ስኩል ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ደግሞ የህንዳውያን ስሪሳይ ኮሌጅ በኮምፒውተር ሳይንስ ይዛለች። በእርግጥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፋርማሲ ትምህርት ቤት ተመድባ ቢሆንም፤ ህልሟ ዋና አብራሪ መሆን ስለነበር ያንን በመተው ነው ኮምፒውተር ሳይንስ ለመማር የወሰነችው። ለዚህ ዋና ምክንያቷ ደግሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመቀላቀል ቢያንስ አንዱ መስፈርት ኮምፒውተር ሳይንስ ማጥናት መሆኑን የምትናገረው – ወጣት ረዳት አብራሪዋ የዓለምወርቅ ፊጣ ናት።
በዓለም አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ፈር ቀዳጅ ድሎችን ካስመዘገቡ ጠንካራና ጀግና አትሌቶች መካከከል አንዱ የሆነው የአትሌት ፊጣ ባይሳ ልጅ የሆነችው ወጣት የዓለምወርቅ፣ በአየር መንገዱ አመልክታ ከተቀላቀለች በኋላ ለአንድ ዓመት ስልጠና ወስዳለች። በረዳት አብራሪነት ስራ ከጀመረች ደግሞ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ሊሞላት ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተዋል።
የመጀመሪያ በረራዋን ያደረገችው ሶስተኛ ረዳት አብራሪ ሆና ወደመካከለኛው ምስራቅ ባህሬን ነው። በወቅቱ የተሰማትን ስሜት ‹‹ህልሜም ስለነበር በወቅቱ በጣም ደስታን ፈጥሮልኛል። ›› ስትል ትገልፃለች። የምታበረው አውሮፕላን ቦይንግ 373 የሚባል ሲሆን፣ ይህም አውሮፕላን ይበልጥ አገር ውስጥ፣ አፍሪካ አገሮችና ቅርብ ወደሆኑ አረብ አገሮችም የሚበር ነው። ረዳት አብራሪ በመሆንም ከአንድ ሺህ ሰዓት በላይ በሰማይ በመሆን አየሩን ቀዝፋለች።
በእስካሁኑ ሂደት በሴትነቷ ያጋጠማት ችግር የለም። ሁኔታዎች አሁን ላይ እንደተለወጡና ሴትን አሳንሶ ማየት ኋላቀርነት እንደሆነም መረዳት ላይ እየተደረሰ ነው የሚል እምነት አላት። ነገር ግን ከእነሱ ቀድመው በነበሩ ዋና አብራሪ ሴቶች ላይ ይደርስ የነበረ ነገር እንዳለ የምታውቅ መሆኗን ትናገራለች። ዛሬ የሰው ንቃተ ህሊና እንደተቀየረ ጠቅሳ፤ ‹‹ሴት ልጅ አትችልም›› ከሚለው ይልቅ ‹‹እድሉን ካገኘች የሚያቅታት ነገር የለም›› ወደሚለው መሻገሩ ታምናለች። እንዲያውም በዙሪያዋ ያሉትም ሆኑ ከዛ ውጭ ያሉ ወንዶች ሲያበረታቱ ማስተዋሏን ነው የምትጠቅሰው። ሴት በመሆኗ ያጋጠማት ተግዳሮት እንደሌለ አጫውተናለች።
አየር መንገዱ ‹‹የእኔ ነው›› የሚል ስሜት አላት። ምንም እንኳ የበረራ አቅጣጫዋ ወደ ቻይና ባይሆንም ነገር ግን ወደቻይና ብረሪ ብትባል ያለአንዳች ማቅማማት በረራዋን እንደምታከናውን በልበ ሙሉነት ትናገራለች። በዚህም ጥንቃቄዎችን በማድረግ የተሰጣትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናን አረጋግጣለች። ምክንያቱም አሁንም ሌሎች አብራሪዎች እያደረጉት እሷም እንደምታደርገው ነው የገለፀችው። አክላም ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ እድሉን ሰጥቶን ያለንን አቅም እንድናወጣ ስለረዳን እናመሰግናለን። ››ትላለች።
‹‹ሴቶች ከተጠናከሩ ህልማቸውን ከማሳካት የሚያግዳቸው ኃይል የለም። ሊያልፏቸው ግድ የሚሉ የኑሮም ሆነ ሌላ ውጣ ውረድ ሊኖር ይችል ይሆናል።›› ያለችው ወጣቷ፣ ህልም ላይ ለመድረስ ግን በዓላማ መንቀሳቀስ ከግብ ያደርሳል የሚል እምነት አላት። አንዲት ሴት የራሷ የሆነ ግብም ሊኖራት ይገባል ባይ ናት። ደግሞም ሴት ፈተና የማለፍ ጥበብና ብልሀት አላት ከሚሉት ጎን መሆኗንም ትናገራለች። የእርሷም የረጅም ጊዜ ግብ ከአምስት ዓመት በኋላ ዋና አብራሪ መሆን እንደሆነ ጠቅሳ፤ ከዛ ቀጥሎም በአየር መንገድ ውስጥ መምህር የመሆንና ሌሎች ብቁ አብራሪዎችን ለሀገሯም ለዓለምም የማፍራት ራዕይ ሰንቃለች።
እርሷ እንደምትለው ከሆነ፤አውሮፕላን ማብ ረር በጣም ቀላል ነው፤ እንዲያውም ከመኪና ማሽከርከር ይልቅ ይቀላል። ምክንያቱም አውሮፕላን ቴክኖሎጂው ጥሩ ተደርጎ የተሰራ ነው። ብዙ ነገር የሚያልቀው መሬት ላይ በመሆኑ አየር ላይ የሚበዛ ስራ አለመኖሩን ነው የምትናገረው።
‹‹አባቴ በሩጫው ዘርፍ አገሩን አስጠርቷል። እኔ ደግሞ በበረራው ዘርፍ አገሬን የሚያስጠራ ተግባር ብከውን ደስ ይለኛል። አትሌት ፊጣ ባይሳ አስር ሺህ፣ አምስት ሺህ እንዲሁም አንድ ሺህ አምስት መቶ ሮጧል። ከአባቴ የወሰድኩት ነገር ቢኖር ወኔ ነው። ›› ስትል በወኔ መንቀሳቀስ አሸናፊ እንደሚያደርግ ትገልጻለች።
ሌላኛዋ ያነጋገርናት ወጣት ደግሞ ረዳት አብራሪ ፍሬህይወት በላይ ትባላለች። የተወለደችው በጅማ ዞን በደሌ ከተማ ነው። ወላጆቿ መምህራን በመሆናቸው ቆይታዋ በደሌ ላይ አልተገታም፤ በወላጆቿ የስራ ላይ ዝውውር ምክንያት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በጅማ ዞን በሚገኙ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተከታትላለች። ግማሹን የልጅነት ዘመኗን ያሳለፈችው በዚሁ በጅማ ከተማ መሆኑን አጫውታናለች።
ከጅማ ቆይታዋ በኋላ በድጋሚ በወላጆቿ የስራ ዝውውር ሳቢያ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አዲስ አበባ አጠናቀቀች። የመጀመሪያ ዲግሪዋንም የሰራችው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአምስት ኪሎ ሲሆን፣ የተመረቀችው በሲቪል ኢንጂነሪንግ ነው።
ከዩኒቨርሲቲው ተመርቃ ከወጣች በኋላ የልጅነት ምኞቷ አብራሪነት ስለነበር አየር መንገዱን የመቀላቀል ህልሟን እውን ለማድረግ ስትል ወደተቋሙ ለመግባት ሞክራ ነበር። ከአንዴም ሁለቴ ያደረገችው ሙከራ ግን ሊሳካላት አልቻለም። ይሁንና ደግማ የመሞከሯ ጉዳይ ተስፋ አላስቆረጣትም፤ ህልሟ እውን የሚሆነው አንድ በር ብቻ በማንኳኳት እንዳልሆነ በመረዳት ለጊዜውም ቢሆን ሌላ አማራጭ እንዳለ በመረዳቷ ‹አልተሳካም› ብላ መቀመጥን አልፈለገችም። በሰለጠነችበት ሙያ አመልክታ መቀጠር ቻለች። በዚህም መሰረት ስራዋን በትጋት ማከናወን ጀመረች።
ይሁንና በያዘችው ስራ ረክታ እና ተወስና መቀመጥን አልፈለገችም። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሴቶች በሁለተኛ ዲግሪ ነፃ የትምህርት ዕድል ለመስጠት ማስታወቂያ ማውጣቱን ሰምታ አመለከተች፤ተቀባይነትን ስላገኘችም ትምህርቷን ቀጠለች። እንዲያም ሆኖ የልጅነት ህልሟ አብራሪ መሆን ስለነበር አየር መንገዱን ለመቀላቀል የተለያዩ ሙከራዎችን ከማድረግ አልቦዘነችም። ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ መልሳ የመግባት ሙከራ አደረገች። ባደረገችውም ያላሰለሰ ጥረት መግቢያውን ማለፍ ስለቻለች የቀድሞ ስራዋን ሙሉ ለሙሉ በማቆም አየር መንገዱን ተቀላቀለች። በዚህም መሰረት በአቬየሽን አካዳሚው ለሁለት ዓመት ትምህርቷን ተከታትላ በማጠናቀቋ የረዳት አብራሪነትን ስራ ጀመረች፤ እነሆ አሁን ህልሟ እውን የሚሆንበትን መስመር ከተቆናጠጠች ስድስት ወራትን አስቆጠረች።
ወጣት ፍሬህይወት፣ የመጀመሪያ በረራዋን ረዳት አብራሪ በመሆን ያደረገችው በመካከለኛ ምስራቅ ውስጥ ወደምትገኘው ሪያድ ነው፤ በወቅቱ የነበራትም ስሜት ድብልቅልቅ ያለ እንደሆነ ታስታውሳለች። አንድም ደስታ ሌላው ደግሞ ኃላፊነትን መሸከምና ያንን በብቃት መውጣት። ብቻዋንም የዋና አብራሪው መቀመጫ ላይ ተቀምጣ ራሷን ባስተዋለች ጊዜ ‹ትወጣዋለች› የሚል ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለባት በማሰቧ ላቅ ያለ ደስታ እንደተሰማት ትናግራለች።
ልክ እንደ ወጣት የዓለምወርቅ ሁሉ እርሷም በቦይንግ 373 አውሮፕላን በረራ በማድረግ ወደ 400 ሰዓት ያህል በአየር ላይ ቆይታለች። ይህ አውሮፕላን በአብዛኛው ከአገር ውስጥ በረራ ጀምሮ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ መዳረሻውን እንደሚያደርግ ነው ። ስለዚህም ወደ ኢስታንቡል፣ እስራኤልና ሌሎች አገሮችም በረዳት አብራሪነት የመካከለኛውን ምስራቅ ክፍል አየር ቀዝፋለች።
እንዲያው ህልምን እውን ለማድረግ በሚደረግ ሩጫ በሴትነትሽ ያጋጠሙሽ ተግዳሮቶች ይኖሩ ይሁን ለሚለው ጥያቄ፣ፈተና ሆነውብኛል ብላ የምትጠቅሰው ነገር የላትም። ይህ የሆነበት ምክንያት ብላ የምታስበው ደግሞ ባለችበት የስራ ዘርፍ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ ከማድረግ በተጨማሪ ቀደም ሲል ለሴት ልጅ የነበረ የ‹‹አትችልም›› አመለካከት በአሁኑ ወቅት ግንዛቤው ስለሰፋ የሚሰነዘር ባለመሆኑ ተግዳሮት እንዳልተፈጠረ ትገልፃለች።
ለወጣት ፍሬህይወት፣ ሌላም አንድ ወቅታዊ ጥያቄ አነሳንላት፤ ይኸውም የኮሮና ቫይረስ በስፋት ብዙ ጉዳት እያደረሰ ነው ወደሚባለው ቻይና፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራውን እያደረገ ነውና ወደዚያ ብረሪ ብትባይስ የሚል ነበር፤ ምላሽዋ የነበረው የአየር መንገዱን ስራ በአግባቡ እንደምትወጣ ነው። ‹‹ዋናው ነገር አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ነው እንጂ የማልጓዝበት ሁኔታ አይኖርም። ›› ብላለች። ‹‹ለዚህ ደግሞ አየር መንገዱ ጥንቃቄ የሚያደርግ እንደሆነ አምንበታለሁ። ›› ስትልም ታክላለች።
ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ስትናገር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሴቶችም ሆነ ለወንዶች ጥሩ እድልን የሚያመቻች እንደሆነ ነው የምታስረዳው። በስራ ላይ ሆነው ሴቶችን ከማበረታት አኳያ የተሻለ መሆኑንም ጠቅሳ፤ ‹‹ለሴት አብራሪዎች ያለው አመለካከትም ቀና ነው። ዋና አብራሪዎቹም መልካም የሆነ እይታ ነው ያላቸው። በዚህም እንድንበረታታና የተሻለም ነገር እንድናስብ ያደርጉናል። ስለዚህም አየር መንገዱን ማመስገን እፈልጋለሁ። ››በማለት ነው ስሜቷን ያጋራችው።
‹‹ሴቶች በራሳቸው የደረጃ ገደብ ማስቀመጥ የለባቸውም።›› የምትለዋ ወጣት፣‹‹ዲግሪ ካለኝ ወይም እዚህ ደረጃ ከደረስኩ በቃኝ በማለት በራሳችን ላይ ገደብ ማስቀመጥ የለብንም።›› ትላለች። ‹‹እስከመጨረሻው ድረስ መሄድና ህልማችንን ማሳካት ይቻላል። ይህን ስል እኔን ብቁ ምሳሌ አድርጌ አይደለም። ከእኔ አልፈው ርቀው የሄዱ በርካታ አርዓያ የሚሆኑን ሴቶች አሉና በራስ በመተማመን ወደፊት መጓዝ ይቻላል።
ምክንያቱም እኔም ራሴ የተነሳሳሁት እነርሱን አይቼ ነው። ስለዚህም ሴቶች ቀድመን በአዕምሯችን ውስጥ ገደብ ባናስቀምጥ መልካም ነው። ምንም እንኳ የአስተዳደጋችን ሁኔታ ገደብ እንድናስቀምጥ የሚያደርገን ቢሆንም ያንን አስተሳሰብ መስበር እንደምንችል በማመን መስራት ይኖርብናል። እኔ ዛሬ ጀማሪ አብራሪ ብሆንም ቀጣይ ህልሜ ደግሞ ካፕቴን መሆን ነው። ›› ስትል ግቧ ሩቅ መሆኑን ነው ያጫወተችን።
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2012
አስቴር ኤልያስ