ከአዲስ አበባ ከተማ በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው የሆለታ ከተማ። ወይዘሮ ሙላቷ ደምሴ ደግሞ ከ50 ዓመታት በላይ ኖረውባታል። ከትንሽ ስራ ተነስተውም ዛሬ ላይ አንቱታን ያተረፉ ሴት ባለሀብት ለመሆን በቅተዋል። እኛም በዓለም አቀፉ ደረጃ በሚከበረው የሴቶች ቀን (ማርች 8) ልዩ መሰናዶ እኚህን ተምሳሌት የሆኑ ሴት አጭር የስራና የህይወት ታሪክ በዚህ መልኩ ቃኝተነዋል።
ወይዘሮ ሙላቷ ውልደታቸው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ውቲ በምትባል አካባቢ ነው። አርሶ አደር የሆኑት ቤተሰቦቻቸውም ልጅ እየወለዱ በተደጋጋሚ ይሞትባቸው ስለነበር እርሳቸው ሲያድጉላቸው እንደ ብርቅ ከማየታቸውም በላይ ዘመድ አዝማድ እኛ ጋር ትደግ ብለው እንኳን ቢለምኗቸው አሻፈረኝ አሉ።
ቤተሰቦቻቸው አርሶ አደር ይሁኑ እንጂ ኑሯቸው የተደላደለ በመሆኑ የችግርን ውጣ ውረድን እምብዛም አላዩም። በቤተሰቦቻቸው ቤትም የድርሻቸውን ድጋፍ እያደረጉ በፍቅር ሲኖሩ እስከ 15 ዓመታቸው ቢቆዩም የኋላ ኋላ ግን የማይቀረው የትዳር ጥያቄ ቤታቸው ደጃፍ ድረስ ከተፍ አለ።
ገና በለጋነት እድሜያቸው የትዳር ጓደኛ የመጣላቸው ወይዘሮ ሙላቷም ጥያቄውን ይቀበላሉ፤ ቤተሰቦቻቸውም ልጃቸውን ለመዳር ሽር ጉድ ማለቱን ተያያዙት ዘመድ አዝማድም ከያለበት ይጠራል። በተለይም የእናታቸው ዘመዶች የሆኑና ሆለታ ከተማ የሚኖሩ ዘመዶቻቸው መምጣት ግን የወይዘሮ ሙላቷን የጋብቻ ፍላጎት ሸረሸረው፤ ምክንያቱ ደግሞ ከሆለታ የመጡት እንግዶች እጅግ ተውበው ጥሩ ልብስ ለብሰው አጊጠው መምጣታቸው እንደነሱ የመሆን ፍላጎት እንዲያድርባቸው አደረገ።
‹‹ለኔ ቀለበት ዝግጅት የመጡት ዘመዶቼ ጥሩ ጫማና ልብስ እንዲሁም ወርቅ አድርገው ነበር እኔም እነሱን ሳይ ከተማ ቁጭ ተብሎ የሚበላ መስሎኝ እናትና አባቴን ትዳሩን አልፈልግም፤ ከእነሱ ጋር ነው የሚሄደው አይ ካላችሁኝ ደግሞ ታንቄ እሞታለሁ አልኳቸው›› ይላሉ ወቅቱን ሲያስታውሱ፤ እባክሽ አትሂጂ የሚለው ልመና ከዚህ ከዚያም ቢሰማም መልሳቸው ግን አምቢታ እንደውም እሞታለሁ ብሎ ማስፈራራት የሆነባቸው ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ተስማሙና ፈቀዱላቸው። እርሳቸውም የልባቸው ሞለቶ ከዘመዶቻቸው ጋር በመሆን ሆለታ ከተማ ገቡ።
ሆለታ ከተማ ሲገቡ ግን ያሰቡትን ያህል በምቾት ቁጭ ብሎ መብላት፣ ጥሩ መልበስና መጫማትን አላገኙም፤ ተመልሰው አገራቸው እንዳይገቡ ደግሞ ዘመድ አዝማድ ሲለምናቸው አሻፈረኝ ብለው መውጣታቸው እየታያቸው በምቾት ማጣት ውስጥ ሆነው መኖርን ምርጫቸው አደረጉ።
‹‹እኔ ከጎተራ ጎተራ እንደ አይጥ ዘልዬ ነው ያደኩት፤ የከተማ ኑሮ በኛ ኑሮ ስመለከተው የድህነት ነው የሆነብኝ፤ ሁሉም ነገር ችግር ነው›› ይላሉ ወይዘሮ ሙላቷ ሁኔታውን መለስ ብለው ለማነፃፀር እየሞከሩ።
በሆለታ ኑሯቸው በተለይም አክስታቸው ከብቶች ስለነበሯቸው ለእነሱ ምግብ የሚሆን የጠላ አተላ መሸከም የከብቶችን ቤት ማጽዳት ሌሎችም ብዙ ስራዎች የእርሳቸው ሆነ፤ ምንም እንኳን ጓጉተውለት የወጡበት ከተማ በዚህ መልኩ ሊያሰቃያቸው ጅማሬውን ቢያሳያቸውም አገራቸውም መግባትን አልፈለጉም፤ ይልቅ የሚደርስባቸውን ሁሉ ችለው እነዛ ለሰርግ ተጠርተው መጥተው ልባቸውን ያሸፈቱት ዘመዶቻቸው የደረሱበት መድረስን ያሰላስሉ ገቡ።
ወይዘሮ ሙላቷ ዓመት ያህል በዚህ መልኩ ቆዩ ግን ያ የጠበቁት ለውጥ አሁንም አልታየም እንደውም ከአገራቸው ይዘውት የመጡትን ልብስ መቀየር አልቻሉም። በመሆኑም ሌላ መላ ማሰብ ነበረባቸውና ለሌላ አክስታቸው ሲያማክሩ ‹‹ውጪና እኔ ጥሩ ቤት በሰራተኝነት አስቀጥርሻለሁ›› የሚል ምላሽ ያገኛሉ።
በዚህም የመናገሻ አውራጃ ተጠሪ የሆኑ ትልቅ ሰው ቤት ይገባሉ። ቆየት ብለውም ሰውየው ላግባሽ በማለታቸው ትዳር ይመሰርታሉ። ነገር ግን በትዳሩ ቤተሰቦቻቸው ደስተኛ ሊሆኑ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት በፍጥነት የሰውየውን ቤት ጥለሽ ካልመጣሽ ዘራችን አይደለሽም የሚል ጉትጎታ በዛባቸው። የእርሳቸው መልስ ግን ዝምታ ሆነ። ነገሩ ያላማራቸው ቤተሰቦቻቸው ሰውየውን አስጠርተው ልጃችንን መልስ አለበለዚያ ለህግ ነው የምናቀርብህ በማለት አስጠነቀቋቸው። ሰውየውም እባካችሁ ብለው ከመለመንና ከመማፀን ያለፈ ምንም ሊያደርጉ አልቻሉም ነበር።
‹‹ወንድን አምኜ እንዴት ቤተሰቦቼን እክዳለሁ ብዬ ባለቤቴ እየለመነኝ ትቼው ወደ አክስቴ ቤት መጣሁ፤ በዚህን ጊዜ ደግሞ አባቴና አጎቴ መጥተው ኖሮ እናትሽ በነብስ ታማለች ብለው አገር ቤት ይዘውኝ ገቡ። እዛ ስደርስ ግን እናቴ አልታመመችም። ውሸት ነበር። እኔ ግን ታመምኩ። አስራ አምስት ቀን አልጋ ይዤ ስተኛም አባቴ ተደናግጠው ሞተች ከምንል አለች ብንል ይሻላል ወደ መጣችበት ትመለስ። ሆለታ ሳይሆን ግን አዲስ አበባ ነው ኑሮዋን ማድረግ ያለባት ብለው ተስማምተው ወደ አባቴ ዘመዶች ጋር አዲስ አበባ መጣሁ›› እያሉ ከትዝታ ከረጢታቸው ውስጥ ጆሮ ማራኪ የሆነውን ትዝታቸውን መተረክ ቀጠሉ።
‹‹አዲስ አበባ ሰው ቤት ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ፤ እዛ ደግሞ የሴት ልጅ መከራ ብዙ ነው ሰውየው ጾታዊ ጥቃት ካልፈጸምኩ እያለ በማስቸገሩ ትቼ ወጣሁ›› በማለትም ወዲያው መርካቶ በአስር ብር ደመወዝ ጠጅ ቀጂነት መግባታቸውን ይናገራሉ። ቀን ይሰራሉ ማታ ለጎናቸው ለማሳረፊያ በተሰጠቻቸው አንዲት ክፍል ቤት ውስጥ ሁለት ከቆዳ የተበጀ ‘ ድብዳብ’ አንጥፈው ከአገር ቤት ያመጧትን ኩታ ከላይና ከታች ደርበው ያድራሉ።
ይህ አይነት ኑሮ የዘለቀው አስከ 6 ወር ብቻ ነበር። ከዚህ በኋላ ባጠራቀሟት ደመወዛቸው ለጎናቸው ማሳረፊያ የሚሆን ፍራሽና አንሶላ ገዙ። ዓመት ሲሞላቸው ደግሞ ደመወዛቸውም ከአስር ወደ አስራ አምስት ብር ከፍ አለ። እሷኑ ከሰውየው ተቀብለው ሴትየዋ ጋር እያስቀመጡ 480 ብር አጠራቀሙ።
ወይዘሮ ሙላቷ በወቅቱ ባለቻቸው ትንሽ አቅም ሌላ እርሳቸው ደሃው ወንድሜ የሚሉትን ወንድማቸውን ይረዱ ነበር። ኋላም በስራ አማካይነት የተዋወቋቸውን ሰዎች በመጠየቅ ወንድማቸው ውትድርና እንዲቀጠር አደረጉ።
በመካከልም ከአገራቸው ያወጧቸው ሆለታ የሚኖሩት አክስታቸው እንደ አጋጣሚ ባለቤታቸው ታመው ለህክምና አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ይገናኛሉ ‹‹እባክሽ ባለቤቴ እስኪድን ድረስ ቤቴን ጠብቂልኝ ›› በማለታቸው እርሳቸውም አባታቸውን እንዲሁም ወንድሞቻቸውን አስፈቅደው መልካም ምላሽ ስላገኙ ወደ ሆለታ ተመልሰው ይሄዳሉ።
የድል መስመራቸው የሆነችው ሆለታ ደግሞ አሁን ጥሩ ልትሆንላቸው ያሰበች ይመስላል። ወይዘሮዋ በአደራ ለመጠበቅ የተረከቡትን ቤት ለባለቤቶቹ ካስረከቡ በኋላ እዛው ተከራይተው የሆቴል ስራ መጀመርን ያስቡና ያጠራቀሟትን 480 ብር፣ አባታቸው የሰጧቸውን 50 ብር እንዲሁም የአክስታቸው ባል እህት ባል ባህር ዛፍ ሸጦ 150 ስሪበት ብሎ በሰጣቸው ቤት ተከራይተው የሆቴል ስራ ንግድ ይጀምራሉ። በጣም ታታሪ ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ሙላቷ የጀመሩትን የሆቴል ስራ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ሌት ተቀን መስራት ተያያዙ። ሰባቱንም ቀንና ሌሊት ያለ እረፍት ይሰሩ ጀመር።
በዚህ መካከል አለሁሽ የሚላቸው ከጎናቸው የሚቆም የትዳር አጋር ያገኙና ያገባሉ። ባለቤታቸው የሳቸውን ያህል ታታሪ ሰራተኛ ባይሆኑም በችግራቸው ጊዜ ግን ከጎናቸው በመቆም ያግዟቸው ነበር።
‹‹በኪራይ ቤት እየሰራሁ እያለሁ ባለቤቴ በመካከል ቤት ሰራ›› የሚሉት ወይዘሮዋ ቢሆንም የሆቴል ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ‹‹ፎቅ መስራት አለባችሁ›› በማለት እንዳስጨነቃቸው ያስታውሳሉ። በወቅቱ ያንን ለማድረግ አቅም ስላልነበራቸው ይጨነቃሉ። ሆኖም የባለቤታቸው ጓደኛ ዛሬም ድረስ ሐምሌ 19 በማለት እየሰሩበት ያለውን ሆቴል ይሰሩበት ዘንድ ቦታ እንዲመሩ ያግዛቸዋል።
ልበ ሙሉዋና ጠንካራዋ ወይዘሮ ቦታውን ይዘው ቤት መስሪያ ገንዘቡን ደግሞ ያላቸውን አራት አልጋ߹ የቢራ ጠርሙሶችና ሌሎች ቁሳቁሶች በማስያዝና ዋስ በመጥራት ከባንክ 12 ሺ ብር ተበድረው ቤታቸውን አቆሙና ገቡ። ባለቤታቸው የግብርና ጣቢያ ሰራተኛ ሲሆኑ በወር የሚያገኙት 120 ብር ለባንክ ብድር እንዲከፈለም ይስማማሉ ።
ጥሪት ለመያዝ የሚያደርጉት ጥረት ብዙ ችግርን ይወልድ ስለነበር ያንን ሁሉ ማለፍ ግዴታቸው ሆነ። ጎን ለጎን ደግሞ የጀመሩት የሆቴል ስራ ማደግ መመንደግ ከእርሳቸው አልፎ ለከተማው ህዝብም የስራ እድል መፍጠር እንዳለበት ልባቸው ያስብ ስለነበር ችግርን ለማለፍ ዘዴ ማበጀት እንደሚያስፈልግ ገባቸው፤ በዛው መንገድ ሆቴሉ ላይ የቡና ማሽን በማስቀመጥ ጥሩ ስራ ጀመሩ። ማሽኑ ወተትና ማክያቶ መስራት ስለነበረበት ወተት ተከራዩ። ግን አዋጭ ስላልሆነ ‹‹ለምን ላም አልገዛም›› ብለው ላም በመግዛት ወተቱን እያፈሉ መሸጥ ጀመሩ።
‹‹በወቅቱ እንሰራለን እንጂ አንበላም ነበር። የምናገኘውን እቁብ እንጥላለን። የተቀረውን ለሆቴል የሚያስፈልገውን ግብዓት እናስገባለን። በአጠቃላይ የምናገኘውን በሙሉ ወደ ስራችን እንጂ ኪሳችን አውለን አሳድረን አናውቅም በዚህም ነው ከሰው ተርታ ለመመደብ የቻልነው›› ይላሉ። ነገር ግን ሀዘን ልባቸውን እየመታው ‹‹ሰርተን ሰርተን እንደ ሰው መሆን ልንጀምር ሰንል ባለቤቴ ሞተብኝ›› ይላሉ ወይዘሮ ሙላቷ እጅግ በሚያሳዝን ትካዜ። ሆኖም ባላቸው ሞተ ብለው ሌላ ኑሮ አላማራቸውም። የእህታቸውንና የወንድሞቻቸውን እንዲሁም ባለቤታቸው ከሌላ ሴት የወለዳቸውን ልጆች ሰብስበው ከጎናቸው በማኖር ስራቸውን መስራት ቀጠሉ።
‹‹ነብሴን ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ ከመስራት በስተቀር እረፍት የሚባለውን ነገር አላውቀውም›› የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ታመው እንደማይተኙ፤ ነጠላቸውን ታጥቀው እንደሚሰሩ ይናገራሉ። ለምሳሌ አንድ ጊዜ በሆለታ ከተማ ላይ ስፖርታዊ ውድድር ይዘጋጃል። ብዙ ሰዎችም ወደ ከተማዋ በመምጣታቸው ስራውም የውድድር ሆነ። ለመኝታ እንኳን ጊዜ እስከሚያጡ ነበር የሚሰሩት። ሶሰት አራት ምጣድ ጥደው መጋገር ወጥ መስራት ግዴታቸው ነበር። በዚህም ለ27 ቀናት በተከታታይ ቆመው በመስራት ጠንካራነታቸውን አስመስክረዋል።
አሁን በ 680 ብር የተነሳው ስራ ዛሬ ላይ ሌላ ታሪክ ፈጥሯል፤ ወይዘሮ ሙላቷ ከሐምሌ 19 ሆቴላቸው በተጨማሪ በከተማዋ ላይ ባለ አራት ወለል ህንጻ በመስራት ለአገልግሎት አብቅተዋል። ‹‹ሆቴል እየሰራሁ ከብቶች እያረባሁ የተለያዩ ስራዎችን በትጋት እየሰራሁ የያዝኳትን ጥሪት ደግሞ ከሃምሳ ዓመት በላይ ለኖርኩባት ሆለታ ከተማ አንድ ቅርስ ላስቀምጥ ለወገኖቼም የስራ እድልን ልፍጠር በማለት አራት ወለል ያለው ፎቅ ለመስራት ችያለሁ፤ ይህንን ስራ ሳስበው በእኔ በብቸኛዋ ሴት የተሰራ ሁሉ አይመስለኝም›› ይላሉ ልፋት ጥንካሬያቸው እየደነቃቸው።
‹‹ስራ ሴት ወንድ አይልም›› የሚሉት ወይዘሮ ሙላቷ በተለይም ሴቶች ጠባቂነትን ከውስጣቸው በማውጣት ‹‹እችላለሁ›› ብለው በመነሳት መስራት ለውጤት ያበቃቸዋል። በመሆኑም በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ስኬትን ለመጎናጸፍ ‹‹ሀሞተ መራራ፣ ቆራጥና አልበገር ባይ መሆን የግድ ነው›› በማለት የማጠቃለያ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2012
እፀገነት አክሊሉ