ማክሰኞ ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል አካባቢ 24 ቀበሌ ልዩ ስፍራው ሰቦቃ ሜዳ በሚገኝ ክፍት ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን ለመሥራት ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ የአካባቢው ምእመናን ጋር በተፈጠረ ግጭት ሁለት ሰዎች (ሚኪያስ ፋኖስ እና ሚሊዮን ድንበሩ) ሕይወታቸውን ሲያጡ ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ያልታወቁ ሰዎች መቁሰላቸው ተሰምቷል።
አዲስአበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ክስተቱ ካጋጠመ በኋላ ፈጥነው ሐዘናቸውን በመግለጽ አጥፊዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ቃል የገቡ ሲሆን የተጎጂ ቤተሰቦችን በአካል አግኝተው አጽናንተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሐዘናቸውን ከመግለጽ ባለፈ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ የሚመለከተው የመንግ ሥት አካል አስፈላጊውን ማጣራት እንዲያደርግና ተጠያቂዎችን ለህግ እንዲያቀርብ ም ጥሪ አቅርበዋል።
የሁለቱ ሟቾች ሥርዓተ ቀብር ላይ ከወዳጅ ቤተሰቦቻቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ብጹአን አባቶች፣ የቤተክርስቲያን ልጆች እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም ተፈጽሟል።
የጉዳዩ አመጣጥ
ዮሐንስ መኮንን፤ የጉዳዩን አመጣጥ በድረገጹ እንደሚከተለው አስፍሯል። አዲስ አበባ ከተማ ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል አካባቢ 24 ቀበሌ ባለው ክፍት ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን ለመሥራት የአካባቢው ምእመናን በአቶ ድሪባ ኩማ ጊዜ ለከንቲባ ጽ/ቤት ጥያቄ አቅርበው ነበር።
እንደሚታወቀው የአካባቢው ምዕመናን ቤተክርስቲያን በአቅራቢያቸው የላቸውም። ቦሌ መድኃኔዓለም፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ የካ ሚካኤል፣ ገርጂ ማርያምም በተለይ ለአቅመ ደካማዎች ሩቅ ናቸው። በዚህ ምክንያት ህዝበ ክርስቲያኑ በአካባቢው ባለ ክፍት ቦታ ቤተክርስቲያን ይሠራልን ብለው በኮሚቴ ተደራጅተው ፊርማ ካሰባሰቡና ለሚመለከተው አካል ካሳወቁ ሰንብተዋል።
ምእመናኑ በወቅቱ ምላሽ ባለማግኘታቸው ጉዳያቸውን ለቤተክህነት እንደገና ያቀርባሉ። በዚህም መፍትሔ ሳያገኙ ቆይተው ከለውጡ በኋላ ጉዳዩን እንደገና በማንቀሳቀስ ለኢንጅነር ታከለ ኡማ አስተዳደር በማቅረብ ተጠንቶ እንዲቀርብ በተወሰነው መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ክብርና መብት ለማስጠበቅ የሚሠራው “ጴጥሮሳውያን” የተባለው ኅብረት ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር ለመፍትሔው በመነጋገር ላይ ነበር።
በዚህ ሂደት ነው እንግዲህ ምእመኑ ከቤተክህነት ባገኘው በደብዳቤ የተደገፈ ይሁንታ የቅዱስ ገብርኤልና የቅድስት አርሴማ ፅላትን ይዘው መጥተው ቅዳሜ (በ23) ቀን ላይ ተሰርቶ በተዘጋጀለት ጊዜያዊ መቃኞ አስገብተው እሁድ ጠዋት መንፈሳዊ አገልግሎት የጀመሩት።
የግንባታውን መጀመር ተከትሎ የቦሌ ክፍለከተማ ግንባታው እንዲፈርስ ያሳሰበ ሲሆን ቀደም ብሎ በቀረበው የምእመኑ ጥያቄ አፈጻጸም ላይ ከጴጥሮሳውያን ኅብረት ጋር ውይይት ይጀምራል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ ይህ ሁሉ ግርግር እና ግድያ የተፈጸመው።
የቀውሱ መነሻ
የቦሌ ክፍለ ከተማ አመራሮች እንደተናገሩት ሕገወጥ ነው ያሉትን ይዞታ ለማስለቀቅ ፖሊስ ያሰማሩት ጥር 26 ቀን 2012 ምሽትን ተገን በማድረግ ነበር። የአካባቢው ወጣቶች ታቦቱን አናስነካም ማለታቸውን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሉ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ወደመውሰድ መግባቱ ለሰዎች ሞትና ጉዳት መንስኤ ሆኗል። እስካለፈው ሐሙስ ዕለት ድረስ ወደሰባት የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ የሰጡ አመራሮች መኖራቸውን ከኢንጅነር ታከለ መግለጫ ፍንጭ የተገኘ ቢሆንም ሰዎቹ እነማን እንደሆኑ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከክተቱ ጋር ተያይዞ በግርግር የታሰሩ የ24 ቀበሌ ወጣቶች እንዲፈቱ ማድረጋቸውንም ዕረቡ እለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል
የተከሰተው የይዞታ ውዝግብ በመንግሥት ያልተፈቀደ በመሆኑ ስህተት ነው ብንል እንኳን ስህተቱን ለማረም የተሄደበት ጭካኔ የተሞላበት መንገድን መመርመር እና ተገቢውን የእርምት እርምጃ መውሰድ አሁንም ከመንግስት የሚጠበቅ ተግባር ነው።
ሕግና ሥርዓትን ወይንም ደንብ ማስከበር እንዴት?
ከቤተክርስቲያን ይዞታ ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች እጅግ በርካታ ናቸው። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የሚመራው የከተማው አስተዳደር፣ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ለሚገኙ 75 ያህል የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እየሠራላቸው መሆኑን፣ በቅርቡ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
ሐራ ተዋህዶ እንደዘገበው የባሕረ ጥምቀት ቦታዎቹ ካርታ፣ በከተማው አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት የቦታ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 2/2004 መሠረት፣ በውበትና መናፈሻ ኤጀንሲ ሥር ሆኖ ቆይቷል፤ ቤተ ክርስቲያንም ለክብረ በዓሉ የመጠቀም መብት ብቻ ነው የነበራት። ሆኖም፣ በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ፣ አከባበሩንና ዕሴቱን ጠብቆ ለማቆየት፣ የአብሕርተ ምጥማቃቱ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ባለቤትነት በቤተ ክርስቲያን ሥር እንዲሆን፣ በከተማው አስተዳደር የልዩ ፕሮሰስ ካውንስል መወሰኑ ታውቋል።
ከ75 የሀገረ ስብከቱ ጠቅላላ አብሕርተ ምጥማቃት መካከል፣ የ38ቱ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 11 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በሚከናወነው መርሐ ግብር ላይ፣ ምክትል ከንቲባው ኢንጅነር ታከለ ዑማ ተገኝተው፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎቹን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ማስረከባቸው ተሰምቷል።
ይኸም እርምጃ አስተዳደሩ የቤተክርስቲያኒትዋን ይዞታ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ያለውን ዝግጁነት የሚያሳይ ነው። ይሁን እንጂ ሰሞኑን በ22 አካባቢ ያልተመጣጠነ እርምጃ በመውሰድ ዜጎችን ለሞትና ለመቁሰል አደጋ የተዳረጉበት ክስተት አስተዳደሩ ከጀመረው ሥራ ጋር የሚቃረንና መንግሥትና ሕዝብን ሆድና ጀርባ የሚያደርግ ትልቅ ስህተት ነው። በተለይ የጸጥታ ኃይሉ እርምጃ ጨለማን ተገን አድርጎ መሆኑ እና እርምጃውንም ለመውሰድ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይኑር ፣ አይኑር ሳይታወቅ የተፈጸመ መሆኑ ጥፋቱን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል።
የአዲስአበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ከክስተቱ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ይህን ጉዳይ ጠቅሰውታል። “ከየትኛውም ጊዜ በተለየ ከኃይማኖት ተቋማት ጋር ተቀራርበን እየሰራን እንገኛለን። ከሥራችን ጅማሬ አንስቶ የደከምንበት የሃይማኖት ተቋማት ጥያቄዎች ምክንያት አንድም የሰው ሕይወት ይጠፋል ብለን አስበን አናውቅም።
በተለይም የይዞታ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ረጅም ርቀት ሄደን ጥያቄዎችን ስንመልስ ቆይተናል። ይሁን እንጂ በመንግሥት እና በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ጥቂት አጥፊዎች ምክንያት በከተማችን ይሆናል ያላልነው፤ እንዳይሆንም የለፋንበት ድርጊት ተፈጽሟል።
ከተማችንን በመለወጥ ሂደት ውስጥ ህይወታቸው ይለወጣል ብዬ ከማስብላቸው ወጣቶች ሁለቱን አጥተናል። እነዚህን ወጣቶች ለማጣት ያበቁንን በየትኛውም ወገን ያሉ የጥፋቱ አካላትን በሕግ እንዲጠየቁ እናደርጋለን። በጥፋቱ ወንድሞቻችንን አጥተናል። ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ” ብለዋል።
ዓለም አቀፍ እና ብሄራዊ የህግ ማእቀፎች ምን ይላሉ?
ይህ ሁሉ አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ በአንቀጽ 3 ላይ እያንዳንዱ ሰው የሕይወት፣ የነጻነት እና የተሟላ የድህንነት መብት እንዳለው ያሰፈረ ሲሆን በአንቀፅ 9 ደግሞ ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ፣ ሊታሰር ወይም ሊያዝ አይችልም በማለት በግልፅ ደንግጎ እናገኘዋለን። ይህ ድንጋጌ በሌላ መልኩ ስናነበው– ማንኛውም ሰው በዘፈቀደ ነፃነቱን ማጣት አይችልም የሚል አጠቃላይ መርህ ደነገገ እንጂ ሀገራት በህጎቻቸው ላይ በግልጽ ተለይተው በተቀመጡ ምክንያቶች እና በተዘረጉ የአያያዝ ስርአቶች መሰረት መያዝ ወይም ማሰር ክልክል ነው ማለት ግን አይደለም።
ለ) የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አለምአቀፍ ቃልኪዳን ፡-
በዚህ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 9(1) ላይ በግልፅ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው የግል ነጻነቱ እና ደህንነቱ እንዲረጋገጥለት መብት አለው።ማንኛውም ሰው ከህግ ውጭ አይያዝም፣ አይታሰርም። ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ምክንያት እና ስርአት ውጭ የግል ነፃነቱ አይገፈፍም። የተባበሩት የአለም ሃገራት ደርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ይህን አንቀጽ መሰረት በማድረግ የሰጣቸውን ትርጉሞችና አስተያየቶችን በጥቂቱ እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን።
ምሳሌ አንድ፡-አንድ ግለሰብ በከባድ የወንጀል ተግባር ተጠርጥሮ የተሰወረ ወንድሙን ፈልጎና መርቶ እንዲያስዝ ቢገደድም መፈጸም ባለመቻሉ ምክንያት ብቻ ለአንድ ወር ቢታሰር ከህግ ውጭ መያዝና ማሰር በመሆኑ አግባብነት የሌለው ተግባርና የህጋዊነት መርህን የሚጥስ ነው ብሏል።
ምሳሌ ሁለት፡-አንድ ግለሰብ የመያዣ ትእዛዝ ሳይቆረጥበት ወይም መጥሪያ ሳይደርሰው ከተያዘ በኋላ ወደ ፍርድቤት ሳይቀርብ ለረዥም ጊዜ ማሰር የግለሰቡን የነፃነት መብትን ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ህገ-ወጥ የመያዝና የማሰር ተግባር ነው ብሏል። በተመሳሳይ መልኩ አንድ ግለሰብ በህጋዊ መልኩ ከተያዘ ወይም ከታሰረ በኋላም ቢሆን ፍርድቤቱ መለቀቅ አለበት ብሎ ካዘዘ በኋላ በፖለቲካ ባለስልጣናት ወይም በሌላ አካላት ትእዛዝ ምክንያት በእስር ላይ እንዲቆይ ማድረግ ኢ-ህጋዊ ተግባር ነው ብሏል።
ሐ) የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ቻርተር (አንቀጽ 6)
ማንኛውም ሰው ነፃነቱ እና አካላዊ ደህንነቱ ተጠብቆለት የመኖር መብት አለው።ቀድሞ በህግ በተደነገጉት ሁኔታዎች እና ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ነፃነቱን እንዲያጣ ሊደረግ አይችልም። በተለይም ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊታሰር ወይም ሊያዝ አይችልም።
የአውሮፓ ሰብአዊ መብቶች መግለጫ እና የአሜሪካ ሃገራት ሰብኣዊ መብቶች መግለጫም ከላይ ከተጠቀሱት የህግ ማእቀፎች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ማንኛውም ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ ሆነ ሊታሰር እንደማይችል ደንግገዋል።
መ) የኢፌድሪ ህገ መንግሥት
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 17(1) ስር እንደተመለከተው በህግ ከተደነገገው ስርአት ውጭ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን /ቷን አያጣም /አታጣም በማለት ደንግጓል። ፤በተጠቃሹ አንቀጽ ንኡስ ቁጥር ሁለት ላይም ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ስርአት ውጭ ሊያዝ ፣ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሣይፈረድበት ሊታሰር አይችልም በማለት ደንግጓል።
ሠ)የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአት
ማንኛውም ሰው በህግ መሰረት ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው አንደኛ ሊያስይዘው ወይም ሊያስጠይቀው የሚችል የወንጀል ተግባር መፈጸሙ ሲረጋገጥ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የተጠረጠረበትን/የተከሰሰበትን የወንጀል ተግባር በህግ መሰረት የሚያስይዘው/ የሚያሳስረው መሆኑን ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ አንቀጽ 25፣ 26 እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው የስነስርአት ህጉ ድንጋጌዎች ይዘት እና መንፈስ ያስረዳሉ።
በረቂቅ ደረጃ ያለው የወንጀል ስነስርአት እና የማስረጃ ህግ በአንቀጽ 8 ላይ ስለመያዝና ማሰር በሚል ርእስ ስር እንደተመለከተውም “ማንኛውም ሰው ወንጀል ስለመፈፀሙ በቂ ጥርጣሬ ሳይኖር ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረደበት ሊታሰር አይችልም” በማለት ደንግጓል።
ከላይ የተጠቀሱት አጠቃላይ መንግስታዊ ግዴታዎች የሚያስገነዝቡን፤ በመርህ ደረጃ ማንኛውም ሰው ካለ ምንም ህጋዊ ምክንያት ሊያዝ ወይም ሊታሰር እንደማይችል የሚያስረዱና የተፈጥሮ ችሮታ የሆኑ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች እንዲከበሩ እውቅና የሚሰጡ አለም አቀፍ ግዴታዎችና ድንጋጌዎች ናቸው።ህገ-መንግስቱን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህጎችም ከአለም አቀፍ ህጎችጋር ተመሳሳይ አላማ በመያዝ የተቀረፁ ናቸው።
በዚሁ መሰረት የነጻነት መብት ህገ መንግስታዊ መብት ከመሆኑ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ህጎች እና በሌሎች ዝርዝር የስነ ስርአት ህጎቿ ላይ በግልጽ ሰፍረው ይገኛሉ።ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ይህ መርህ በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀፅ 17፣ በዓለም አቀፍ ፖሊቲካ እና ሲቪል ስምምነት ሰነድ አንቀጽ 9፤በሰብአዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ አንቀጽ 3 እና 9፣በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ አንቀጽ 25 እና 26 እንዲሁም በረቂቁ የወንጀል ስነ ስርአት እና የማስረጃ ህግ አንቀጽ 8 ላይ እና ሌሎች ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ህጎች ላይ በግልጽ ተደንግጓል። ሆኖም ግን አንድ ግለሰብ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ የሚፈለግ ከሆነ አጠቃላይ የህብረተሰቡ ሰላም እና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል በህግ ተለይተው በተቀመጡ ስነስርአታዊ አካሄዶች መሰረት መያዝ ወይም ማሰር ይቻላል።
ይህ ማለት አንድ ግለሰብ ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው በአንድ ፖሊስ የግል ፍላጎት ወይም በባለስልጣን ፈላጭ ቆራጭነት ወይም በማንኛውም ግለሰብ ጥላቻዊ ጥቆማ ወይም ቂም በቀልነት ሳይሆን ጉዳዩ በአንድ ምክንያታዊ ታዛቢ ሰው ሲለካ እንዲሁም በግልጽ እና በሚያሳምን ሁኔታ እውነታዎቹ ሲታዩ እና ማስረጃዎቹ ሲመዘኑ ወይም ሲመረመሩ ለማስያዝ እና ለማሳሰር በቂ ሆኖው ሲገኙ ብቻ ነው። ዝቅተኛ የህግ ግንዛቤ እና እውቀት ባለበት እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ሃገራት ማሰር እና መያዝ ካለምንም ገደብ እና ቅድመ ሁኔታ በዘፈቀደ ለፖሊስ የተሰጠ ስድ እና ያልተገራ ስልጣን የሚመስለው የህብረተሰብ ክፍል ስፍር ቁጥር የለውም። ብዙዎቻችን ደንብ ልብስ ለብሶ ካቴና ይዞ የመጣ ፖሊስ ሁሉ ህግን እያስከበረ ነው የሚል የተሳሳተ ህብረተሰባዊ እምነት እና ልማዳዊ አሰራር ስለምናራምድ እና ለዚሁ ጸረ-ነጻነት የሆነውን አሰራር ተገዢ ስለምንሆን ለመብታችን ስንታግል አይታይም። ይህ ስል ግን ራሳችንን ከህግ ውጭ በማድረግ ለሚደርስብን ኢ-ፍትሀዊ ተግባር ኢ-ፍትሀዊ ግብረመልስ እየሰጠን ወደአላስፈላጊ እሰጣ እገባ እና ንትርክ ውስጥ በመግባት በህግ አስከባሪ አካላት ላይ ችግር የመፍጠር መብት አለን ለማለት ሳይሆን ብያንስ ግን በህግ እና በመብታችን ላይ የተሟላ እውቀትና ግንዛቤ ኖሮን ህግን መሰረት በማድረግ መጓዝ እና ንቁ ዜጋን በመፍጠር አምባገነን መንግሥትን እና ፈላጭ ቆራጭ ባለስልጣንን የምንከላከልበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል። ይህ ደግሞ መንግሥት ጠንካራ ስርዓት እና ተቋም እንዲመሰርት፤ተጠያቂነት እና ሃላፊነት መሰረት በማድረግ ስራውን የሚያከናውን ባለሙያ (ባለሥልጣን) እንዲኖር መንግሥት በአንክሮና በቁርጠኝነት እንዲሰራ በር ለመክፈት ያስችላል። (ማጣቀሻዎች፡- የአ/አ ከንቲባ ጽ/ቤት ድረገጽ፣ ዮሐንስ መኮንን ድረገጽ፣ ገብረእግዚአብሄር ወልደገብሪኤል፤ አቢሲኒያ ሎው ድረገጽ ላይ ያሰፈሩት ሐተታ…)
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ፍሬው አበበ