ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የተሻገረው የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት መስጠትን የሚከለክለው ህግ ሥራ ላይ ባለበት ወቅት ነበር ስላልታቀደ እርግዝናና ጽንስ ማቋረጥ ማስተማር የጀመረው። በዚያ ዘመን በማኅበረሰቡ ዘንድ ደግሞ ብዙ ልጆችን መውለድ እንደ ሃብትና ዋስትና የሚቆጠርበት፣ ስለተዋልዶ ጤና በተለይም ስለወሲብ በግልጽ መነጋገር ነውር ተደርጎ በሚወሰድበት፣ ሴቶች በተዋልዶ አካላቸውና መብታቸው መወሰን በማይችሉበት፣ የወንዶች የበላይነት በነገሰበት፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ከፍተኛ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ስለቤተሰብ እቅድ ግንዛቤ ያላዳበሩበት፤ ባጠቃለይ የስል ስነ ተዋልዶ ሳይንሳዊ አመለካከት ባልነበረበት ዘመን ነበር ማህበሩ የቤተሰብ ዕቅድን በኢትየጵያ ለመጀመር ወደ እንቅስቃሴ የገባው፡፡
በማህበሩ የእቅድና ፕሮግራም ቡድን መሪ አቶ አድነው ሁሴን እንደሚናገሩት በመጀመሪያ ሃሳቡን ያመነጩት ከመስራቾቹ ውስጥ አንዱ የሆኑት ዶክተር ሽመልስ አዱኛ ነበሩ። ዶክተር ሽመልስ በህንድ አገር የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ከሌሎች ኢትጵያውያን ጋር በሚከታተሉበት ወቅት በህንድ ስለሚሰጠው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ያገኙትን መረጃ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ሃሳቡን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በማብላላት ለምስረታው መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። በዚህም ዶክተር ሽመልስ አዱኛን ጨምሮ ዶክተር ዊዳድ ኪዳነማሪያም እና ሲስተር ምህረት ጳውሎስ የተባሉና ሌሎች አራት በጎ ፈቃደኛ ምሁራን ተሰባስበው “ቤተሰብ መምሪያ” በሚል ስም በ1958 ዓ.ም ማህበሩን ለመመስረት ይነሳሉ።መርካቶ አካባቢ ጳውሎስ ሆስፒታል የነበረበት ቦታ ላይ ከአንድ ክሊኒክ ውስጥ ባለች በአንዲት ክፍል ውስጥም በአንድ በጎ ፈቃደኛ የነጻ አገልግሎት ሰጪ ዶክተርና በአንዲት ነርስ ስራውን “ሀ” ብለው ይጀምራሉ።
በወቅቱ በሀገሪቱ አንድ እናት በአማካይ ከሰባት ልጅ በላይ ትወልድ የነበረበትና በአንጻሩ የሀገሪቱ ኢኮኖሚው በሚገባው ደረጃ የማያድግበት ዘመን ነበር። ማህበሩም የተቋቋመው ከዚህ በመነሳት ነበር።የማህበሩ አላማ የህዝብን ቁጥር ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ማመጣጠን፤ የእናቶችን ጤና በማስጠበቅ ጤነኛና አምራች የሆነ ወጣት ማፍራት፤ እናት ፋታ አግኝታ ልጆቿን እንድታሳድግ ማስቻል፤ እያንዳንዱ ቤተሰብም የህጻናቱን የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች ካሟላ በኋላ ልጅ ወልዶ እንዲያሳድግ ማብቃት የሚል ነበር። በወቅቱ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ካለ እድሜ ማግባትና መውለድ የተለመደ ስለነበር ለህጻናቱም ሆነ ለእናቶች ጤንነት ከለ እድሜ መውለድም ሆነ እድሜ ከገፋ በኋላ መውለድ የየራሳቸው ችግሮች ስላሉባቸው እነዚህንም ማስቀረት አንዱ የማህበሩ አላማ ነበር። ለዚህ ደግሞ ያልታቀደ እርግዝናን መከላከልን ማህበሩ ዋናው ሥራ ያደርገዋል። ማህበሩ በቤተሰብ ዕቅድ ላይ መረጃና አገልግሎትን መስጠት ሲጀምርም እንዲህ አይነት አገልግሎቶች በሌሎች ሃገሮች ተግባራዊ መደረግ ከጀመሩ ብዙም ሳይዘገይ ነበር።
በዚህ አይነት የተመሰረተው ቤተሰብ መምሪያ ማህበር እስከ አስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ አጋማሽ በስፋት ማስተማሩ ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ ሲሰራ ይቆያል። የቤተሰብ እቅድ አስተማሪዎች እስከ ባሌ፤ ሐረርጌ፤ ቦረና ሳይንት፤ ይርጋ አለም፤ ጅማ ድረስ በመሄድ ገጠር ውስጥ በመግባት እስከ ሁለት ወር እየቆዩ እንዲያስተምሩ ይደረግ ነበር ። ነገሩ ግን ስራው አልጋ በአልጋ የሚከናወን አልነበረም።የግንዛቤ ክፍተቱ ፊደል በቆጠረውና ቅቡልነት በነበራቸው የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም ላይ የነበረ በመሆኑ ኅብረተሰቡ በቀላሉ ተቀብሎ ለመተግበር ይቸገር ነበር። በዚህ ሁኔታ ለዓመታት ከቆየ በኋላ ነበር ማህበሩ ዘመናዊ የወሊድ መከላከያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት የጀመረው።
ለመጀመሪያ ግዜም በማህጸን ውስጥ የሚቀመጠው «ሉፕ» የተሰኘውንና እስከ አስራ ሁለት ዓመት እርግዝናን የሚከላከለውን፤ ነገር ግን እናቶች ያልተስማማቸው ወይንም ከጊዜው በፊት መውለድ የሚፈልጉ ከሆነ በማንኛውም ሰዓት ማቋረጥ የሚቻለውን የቤተሰብ እቅድ መቆጣጠሪያ ለህዝቡ ያቀርባል። የእርግዝና መከላከያ በመውሰድ የመጀመሪያ ለነበረችው ኢትዮጵያዊት ሴት ሉፕ የተባለውን ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ በማስገባት አገልግሎቱን በይፋ ይጀምራል።ይህንንም ተከትሎ የማህጸን ቆብ፤ በየቀኑ የሚወሰድ ኪኒን፤ በክንድ የሚቀበረውና በመርፌ የሚሰጥም ያቀርባል። ማህበሩ ሁሉንም የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶች ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ሌሎች አካላት ጋር በመተባበር በነጻ ይሰጣል። የተለየ ከውጪ የሚገዛ ነገር ካስፈለገም ከሀያ እምስት በመቶ በላይ ላለማስከፈል ከአምስት ዓመት በፊት ተወስኖ እየተተገበረ ይገኛል። ይህም ሆኖ ለሴተኛ አዳሪዎች በአስር ክሊኒኮች ማንኛውንም አገልግሎት በነጻ የሚሰጥ ሲሆን እንደየሁኔታው መክፈል የማይችሉ በተለይ ወጣቶች ሲመጡ ሁሉንም አገልግሎት በነጻ የሚያገኙበት አሰራርም አለ።
ማህበሩ እንዲህ እንዲህ አያለ በ1967 ዓ.ም ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ በጎ ፈቃደኛ መንግስታዊ ያልሆነ አገር በቀል ማህበር ሆኖ በጊዜው በነበረው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የአገር ግዛት ሚኒስቴር የህዝብ ደህንነት ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ለመመዝገብ በቃ። የሚሰጠውም የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በዓለም አቀፉ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን ተቀባይነት አግኝቶ እ.ኤ.አ በ1971 ዓ.ም የዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን ሙሉ አባል ለመሆን ይበቃል።በአዲስ አበባ ብቻ የነበረውንም የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በማስፋፋት በ1968 ዓ.ም በአስመራ አንድ ክሊኒክ ይከፍታል። በዚሁ ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ዋና መሥሪያ ቤቱንና ክሊኒኩን ያቋቋመ ሲሆን በወሎ፣ በትግራይ እና በአሰብ አካባቢ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በደሴ ከተማ የአካባቢ ጽህፈት ቤት በመክፈት አገልግሎቱን ለማዳረስ እንቅስቃሴውን ያስፋፋል፡፡
በመቀጠልም በ1969 ዓ.ም የደቡብ አካባቢ ጽህፈት ቤቱን በሃዋሳ ከተማ የከፈተ ሲሆን በሥሩም የባሌና የጋሞጎፋ አካባቢዎችን አቅፎ አገልግሎት መስጠቱን ይቀጥላል። በተመሳሳይም በዚሁ ዓመት ለሰሜን ምዕራብ አካባቢ በባህር ዳር ከተማ በመክፈት የጎጃምና የጎንደር አካባቢ ቤተሰቦች ተጠቃሚ ያደርጋል። በ1976 ዓ.ም የሐረር እንዲሁም ለጅማ ለከፋ፣ ለኢሉ አባቦራና ወለጋ አካባቢዎች አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ይበቃል።በ1995 ዓ.ም ደግሞ ለመቀሌና አካባቢዋ ማህበረሰብ የተዋልዶ ጤናና የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት መስጠቱን ይቀጥላል።በ2004 ዓ.ም ደግሞ አሁን እየተገለገለበት ያለውን ባለ አራት ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ ከዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን የአፍሪካ ቢሮ፣ ከደቪድ ሉሲል እና ፓካርድ ፋውዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለመገንባት በቅቷል።
ማህበሩ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን በሥራ ላይ ያሉ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና አሰራሮች እንዲለወጡ፣ እንዲሻሻሉ ወይም አዳዲስ ህጎችና ፖሊሲዎች እንዲወጡ እንዲሁም የወጡት ህጎችና ፖሊሲዎች ተግባራዊ እንዲሆኑም ከመንግሥት ጋር በመሆን የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በልዩ ልዩ ትምህርታዊ ፕሮግራሞች አማካኝነትም ከወሲባዊ ግንኙነት ጋር ስለተያያዙ ሁኔታዎች፣ ስለወሊድ፣ ስለመካንነት፣ ስለቤተሰብ ዕቅድ፣ ስለ ወጣቶች ስነተዋልዶ ጤና በአጠቃላይ ስለተዋልዶ ጤና አገልግሎትና ተዛማጅ ጉዳዮች እንዲሁም ያልተመጣጠነ ህዝብ ዕድገት በሃገር ኢኮኖሚና በህዝብ ማህበራዊ ዕድገት ላይ በሚያስከትለው ተጽዕኖ ዙሪያ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያሰፋና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ እየሰራ ይገኛል።
የተዋልዶ ጤናን የሚጎዱ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲወገዱ ህብረተሰቡን ማስተማር፤ የምክርና የጤና አገልግሎት መስጠትና ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በቅንጅት መስራት የዓለም አቀፉ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽንን አላማዎችና ግቦች ከአገሪቱ ፍላጎት ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ማራመድ፤ እንዲሁም ፖሊሲዎችንና መርሆችን እንደወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲሰራም ቆይቷል። በተለይም ወሲባዊ ግንኙነትና ተዋልዶ ጤናን በተመለከተ ሴቶች፣ ወንዶችና ወጣቶች በነጻነትና በተሟላ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ የመወሰንና በውሳኔያቸውም መሰረት የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች አካል መሆኑን ማሳወቅና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ላይ ከግንዛቤ መፍጠር እስከ የተግባር አገልግሎት ሲያቀርብ ቆይቷል።
ማህበሩ ለቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ለማያገኙ በድህነት ለሚኖሩ፣ በትልልቅ ፋብሪካዎች፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ሰፋፊ ሜካናይዝድ የእርሻ ቦታዎች ለሚሰሩ ሰራተኞች፣ከ200 በላይ በሆኑ ውሎ ገብ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች፣ በልዩ ድጋፍ (ኮንፊደንሻል) ክሊኒኮች፣ በተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች እና በወጣት ማዕከላት የመክፈል አቅም ለሌላቸው የማህበሰረብ ክፍሎች ወዳሉበት አካባቢ በመሄድ በነጻ ያቀርባል።በማህበሩ ያለማግለል ፖሊሲ መሰረትም ማንኛውም የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ፈልጎ የመጣ ተገልጋይ መክፈል የማይችል ቢሆንም እንኳን አገልግሎቱን ሳያገኝ በፍጹም አይመለስም።እንደ ሀገር ያልታቀደ እርግዝና በስፋት የሚከሰት በመሆኑ በርካታ እናቶችም ጽንሱን ለማቋረጥ የተለያዩ አማራጮችን ይወስዳሉ። በተለይም ወጣቶች እርግዝናውን የሚፈሩትን ያህል ያንን ተከትለው ለሚመጡት ሌሎች ገዳይ በሽታዎች ግንዛቤውም የላቸውም፤ ትኩረትም አይሰጡም። በመሆኑም ማህበሩ እያንዳንዷ እናት ወደ ቤተሰብ መምሪያ ተቋም ስትመጣ የፈለገችውን አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በአማራጭ ያሉትንም እንድትመርጥ የማስተዋወቅ እንደ ስጋት የሚታዩ ነገሮችንም የማስተማር ሥራ ይሰራል። ማህበሩ በሁሉም ቦታ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች የተለያዩ ችግሮች ያለባቸውንና ልዩ ፍላጎት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችንም ከግምት በማስገባት ከእቅድ ጀምሮ በማካተት የስነ ተዋልዶ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል።
በአሁኑ ወቅትም ማህበሩ ስምንት የአካባቢ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያሉት ሲሆን በእነዚህ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችም ከ46 በላይ የተዋልዶ ጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን/ክሊኒኮችን በመገንባትና በመክፈት ጥራቱን የጠበቀና የተቀናጀ የተዋልዶ ጤና ትምህርትና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በስምንት ሞዴል ክሊኒኮች የማዋለድ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በዩኒቨርሲቲዎችም ለተማሪዎች ተንቀሳቃሽ የስነ ተዋልዶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በተጨማሪም 420 ከሚደርሱ የግል ክሊኒኮች ጋር «ጥምረት ለቤተሰብ ጤና» በሚል ስያሜ በአጋርነት በመስራት አገልግሎቱን ለኅብረተሰቡ እንዲዳረስ እያደረገ ይገኛል። በመጋቢት 22 ቀን 1967 ዓ.ም የመጀመሪያውን የስልጠና ፕሮግራም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከሚሲዮን ሆስፒታልና ክሊኒክ እና ከግል የጤና ተቋማት ለተውጣጡ አስራ ሁለት የጤና ባለሙያዎች በመስጠት ጀመረ።የስልጠና ማዕከሉ አቅም በመገንባትም በተዋልዶ ጤና፣ በቤተሰብ እቅድ፣ ጤናዋ የተጠበቀች እናት፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ እና በሌሎች ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሲያደርግ ቆይቷል።እስከ 2009 ዓ.ም ድረስም ከሃያ ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠን ችሏል።ላለፉት ሀያ አምስት ዓመታትም በመንግሥት የጤና ኮሌጆች በነርስነት ለሚሰለጥኑት የጤና ባለሙያዎች አንድ የቤተሰብ ምጣኔ ኮርስ እየሰጠ ይገኛል።
ማህበሩ በግልና በመንግሥት የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ለተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች አመርቂ ስልጠናዎችን በመስጠት ለጤናና ጤና ነክ ፖሊሲዎች ተግባራዊነት እንዲሁም ለሃገራችን ዕድገትና ልማት መሳካት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል።በተጨማሪም የእናቶችና ህጻናት ጤና፣ የቤተሰብ ዕቅድ፣ የታዳጊዎችና የወጣቶች ተዋልዶ ጤና፣ የኤች አይ ቪ ምርመራና የምክር አገልግሎት፣ የአባላዘር በሽታ ምርመራና ህክምና፣ የቅድመ ወሊድ ክትትል፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የድህረ ወሊድ ክትትል፣ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍን ኤች አይ ቪ የመከላከል አገልግሎት፣ በህግ በተፈቀደው መሰረት የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት፣ የመካንነት ምርመራና ህክምና፣ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራና ህክምና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛሉ።በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎቱም ያልታቀደ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉ የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ ጊዜ፣ የረጅም ጊዜ እና ቋሚ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን የተጠቃሚዎችን ፍላጎት መሰረት ባደረገ ሁኔታ እየሰጠ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር እየተገበረ ባለው የማህበሩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ትግበራም እስካሁን ተጠናቅሮ በተያዘው የሦስት ዓመት መረጃ መሰረት ከጥር 2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 2011 ዓ.ም ድረስ የተቀናጀ የተዋልዶ ጤና ትምህርት በመስጠት የተዋልዶ ጤናን በተመለከተ አዎንታዊ መልዕክቶችን መረጃ በማድረስ፣ ጥንዶችን ለአንድ ዓመት ያክል ካልተፈለገ እርግዝና እንዲከላከሉ በማድረግ ፣ አዳዲስ የተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅና በጎ ፈቃደኛ አባላትን በመመልመል በቤተመጻህፍት በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎትና በመዝናኛ ከሀያ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ ችሏል። ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ለ29 ሺ 698 የጤና ባለሙያዎች፣ አንቂ የማህበረስብ ክፍሎችና ወጣቶች በተዋልዶ ጤናና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት፣ በጤናማ እናትነት፣ በኤች ኤ ቪ/ኤድስ እና በሌሎች ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር በዋናው መስሪያ ቤት እና በቅርንጫፍ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች በቤተሰብ ዕቅድ እና በተዋልዶ ጤና ላይ በመንግሥትና በግል ተቋማት ውስጥ ለተሰማሩ የጤና መኮንኖች፣ ነርሶች፣ ጤና ረዳቶች እና ለገጠር የሴቶች ዕድገት ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት በተዋልዶ ጤናና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እያደረገም ይገኛል።በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተወስኖ የነበረውን የማህበሩ የሥራ እንቅስቃሴም በ1987 ዓ.ም የወጣውን የስነ ህዝብ ፖሊሲ ተከትሎ የተቀናጀ ዘርፈ ብዙ የተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በተጠናከረ ሁኔታ ወደመስጠት እንዲሸጋገር አድርጎታል።የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቀርጻቸው የስነ ተዋልዶና ጤና ነክ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና መመሪያዎች ዝግጅት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ ረገድም ግንባር ቀደም ነው።ከዚህም በተጨማሪ በመንግሥት የጸደቁ የስነ ህዝብ ፖሊሲዎች፣ የጤና ፖሊሲ፣ የኤች አይ ቪ ፖሊሲ፣ የተሻሻለ የቤተሰም ህግ፣ ከተዋልዶ ጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የተዋልዶ ጤና ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋል።
ይህም ሆኖ በአቅርቦት ረገድ ለቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የሚውሉ የወሊድ መከላከያ ድጋፎች ቢኖሩም ካለው የአገልግሎት ፈላጊዎች ቁጥር ጋር የሚመጣጠን አይደለም። በተጨማሪም የውጪ ሀገር ለጋሾች ቁጥርም ከግዜ ወደ ግዜ እየቀነሰ ይገኛል። በመሆኑም የሀገር ውስጥ የገቢ ምንጭን ለማጎልበት፤ የወጪ መጋራት አሰራርን ለመዘርጋት፤ ብሎም የውስጥ አቅምን የሚያጎለብቱ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞችን በማከናወን ማህበሩ ራሱን እንዲችል የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን አቶ አድነው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ