የአምባሰል የዜማ ስልት (የሙዚቃ ቅኝት) ኢትዮጵያዊ ቃና ያለውና በአድማጮች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ነው። ይህን ስልት ስናነሳ ሁሌም ከትውስታችን የማትርቀው ድምፀ መረዋዋ ‹‹የአምባሰሏ ንግስት›› ድምፃዊት ማሪቱ ለገሰ ነች። የአምባሰልን ቅኝት በድምጿ ስትጫወተው የተደመሙ የሙዚቃ ባለሙያዎች ‹‹አምባሰልን ከተ ራራው በላይ ያገነነች›› ይሏታል። የወሎ ዩኒቨር ሲቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷታል። በዛሬው የኪነ ጥበብ አምዳችን ይህችን ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ፈርጥ አንስተን ጥቂት ስለ ሥራዎቿ እና የህይወት ተሞክሮዋ ልንጨዋወት ወደድን።
የአምባሰል ንግስቷን የሙዚቃ መንገድ ለመዳሰስ ስናስብ በቀዳሚነት ጥረት ያደረግነው የዜማና የግጥም ደራሲ የሆነውን እና በርካታ ሥራዎችን ከማሪቱ ለገሰ ጋር የሰራውን ዳምጤ ምትኩን (ባቢ) በማግኘት ምልከታውን በቃለ ምልልስ ማግኘት ነበር። ይህ ጥረት ተሳክቶልንም ስለማሪቱ ያልተነገሩ በርካታ ጉዳዮችን አጫወተን። እኛም ውልደቷና የህይ ወት ጉዞዋ በስፋት በኢትዮጵያውያን አድናቂዎቿ ስለሚታወቅ ከዳምጤና ሌሎች የሥራ አጋሮቿ ጋር ሙዚቃዎቿን ስትሰራ የነበረውን ያልተነገሩ ጥበባዊ ታሪኮች ላይ ለማተኮር ወደድን።
ጋሽ ቀለምወርቅ ደበበ የወሎ ላሊበላ ኪነትን ከአራት አሥርት ዓመታት በፊት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ መሰረት የጣሉ በርካታ የባህል እና ዘመናዊ የሙዚቃ ባለሙያዎች እና ተወዛዋዦች እንዲያፈራ በማሰብ መሰረቱት። ማሪቱ እና ዳምጤ ደግሞ በ1973 ዓ.ም ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ይዘው ሥራዎቻቸውን በሙያ ዊ መንገድ ለማስኬድ ጥረት ሲያደርጉ ነው በላሊበላ ኪነት ውስጥ የተገናኙት።
‹‹ማሪቱን ነፍስ ካወኩ ጀምሮ አውቃታለሁ›› የሚለው ዳምጤ የሙዚቃ ሥራዎቿና የመረዋ ድምጿ አድናቂ ሆኖ መቆየቱን ይናገራል። እርሱም በኪነ ጥበቡ ዘርፍ የህይወት መንገዱን እንደሚያቀና ሲገባው ላሊበላ ኪነትን መቀላቀሉን እና በዚያም ዜኒት ሙሃባንና ማሪቱ ለገሰን ማግኘት እንደቻለ ይገልጻል። የመጀመሪያ ሥራው የዜኒት ተወዳጁ ‹‹ከምበል ደፋ›› የሚል ርእስ የያዘ ሙሉ አልበም ሲሆን፣ በ1975 ዓ.ም በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘውን የማሪቱን ‹‹አምባሰል›› የተሰኘ ሙሉ አልበም መስራት ቻለ። በዚህም ከማሪቱ ጋር መልካም ወዳጅነቱ የመጀመሪያዎቹን የትውስታ ጊዜያት መፃፍ ጀመሩ።
የግጥም እና ዜማ ደራሲው ዳምጠው ‹‹ማሪቱ ማለት ድንቅ ሙዚቀኛ ፣ጓደኛ ፣ መካሪ እንዲሁም የእናትነት ባህሪ ያላት ተወዳጅ›› እያለ ይገልፃታል። የሙያ ስነ ምግባሯ በጓደኞቿ ዘንድ የተመሰገነ መሆኑ ንም እርሱም ሆነ ሌሎች ይመሰክሩላታል። በዚህ የተነሳ የአምባሰሏ ንግስት በሙያ እህት ወንድሞቿ ‹‹ማሬዋ›› በሚል የቁልምጫ ቅፅል ስም ትጠራለች።
የስቱዲዮ ትዝታ
የላሊበላ ኪነት በወቅቱ አንድ ጥብቅ ባህል ነበረው። አንድ አዲስ ዜማ ወይም ሙዚቃ ሲሰራ የወንድ ከሆነ ሁሉም ወንድ ድምፃዊያን፤ የሴት ከሆነ ደግሞ ሁሉም ሴት ድምፃዊያን በጋራ በመሆን ሥራውን ያጠኑታል። በዚህ ሂደት ውስጥ ሲያልፍ አዲሱ ዜማ የትኛው አርቲስት የተሻለ ይሰራዋል የሚለው በግልፅ ይታወቃል። ማሬዋም ይህን ሂደት ተከትላ ነው ያለፈችው። ዳምጤ ትውስታውን ወደ ኋላ መልሶ በተለየ መንገድ የእርሷን የሙዚቃ ጥናት ስልት ሲያስታውስ እንደሚገረም ይናገራል። ምክንያቱ ደግሞ የእርሷ ድምፅ በተፈጥሮ የታደለችው እና ምንም የተለየ ልምምድ እና ንክኪ የማይፈልግ መሆኑ ነበር። አራቱንም የሙዚቃ ቅኝቶች ስትጫወት አብረዋት የሚሰሩ የሙዚቃ ባለሙያዎችን የማያስቸግርና የተገራ እንደነበር ይመሰክሩላታል።
‹‹አስተዳደጓ በአዝማሪ ሙዚቀኛ መንገድ›› ነበር የሚለው ዳምጤ ግጥም የመቀበል ችሎታዋ ብሎም ዜማውን ሙያዊ መንገድ እንዲከተል በሚደረገው ጥረት ላይ የሚያስቸግር ባህሪ እንዳልነበራት ያስረዳል። በቀለም ትምህርት ውስጥ ባለማለፏ ማንበብም ሆነ መፃፍ እንደማትችል ገልፆ በጊዜው እርሱ እና ሌሎች ጓደኞቿ እያነበቡላት ታጠና እንደነበር ይናገራል። ያን ጊዜ ያጠናችውን እስካሁንም ድረስ ሳትረሳ በመጫወት ትታወቃለች። ከፍተኛ የማስታወስ ችሎ ታ እንዳላት የሚያሳይም ነበር። ይህንንም ከአንድ ዓመት በፊት እንደ አዲስ በአወጣችው አልበም ላይ ማስመስከር ችላለች።
በደሴ ገራዶ ደጁ የተወለደችው የአምባሰል እና የባቲ ፈርጧ ማሬዋ ብዙ ያልተነገሩ እጅግ መሳጭ የሆኑ ታሪኮች ባለቤት ነች። ይህን ትዝታዋን ደግ ሞ ዳምጤና ፀሐይ ካሳን የመሰሉ የሙያ አጋሮቿ ተጋርተውታል። ወቅቱ ሙዚቃን ወደ ሸክላ አሊያም ካሴት ለመቅዳት ረጅም ልፋት የሚጠይቅበት ነበር። ይህን ውጣ ውረድ ደግሞ የወሎ ላሊበላ ኪነትም ተፈትኖበታል።
ይህ ታሪክ በወሎ ላሊበላ ኪነት ውስጥ እስካሁንም የሚታወስ ነው። ክራሪስት መሰለ አስማ ማው፣ ዳምጠው እና ሌሎች የሙዚቃ ባለሙ ያዎች የማሬዋን አልበም በካሴት እየቀዱ ነበር። ድምፀ ስርቅርቋ ማይክራፎን እና የጆሮ ማዳመጫዋን አድርጋ አምባሰልን ታንቆረቁረዋለች። ክራር የሚጫወተው መሰለ ደግሞ የድምፅ ቅላፄዋን ይበልጥ የሚሞሽር ውብ ሙዚቃዎችን እየተጫወተ ነው። በድንገት አንድ የጦር መሳሪያ የሚመስል የክራር ድምፅ ማሬዋ ሳታስበው ይጫወታል።
ስሜት ውስጥ የነበረች ማሬ ደግሞ ይህን ድምፅ ስትሰማ የእውነትም የጦር መሳሪያ ነበር የመሰላት። ደነገጠች። ሳታስበው ዘፈኗን አቋርጣ ‹‹አለቅን›› ስትል ድምፅ ማጉያውን እና ማዳመጫውን ጥላ ከስቱዲዮው ተፈተለከች። ይህን ጊዜ ቤቱ ውስጥ ሳቅ ተፈጠረ። የኪነት ቡድኑ ጥሩ መዝናኛ አገኘ። በክራሩ ድንጋጤ ውልቅ ብላ የወጣችው ማሬዋ ስርቅርቅ ድምጿን ብቻ ሳይሆን ይህን መሰል ትዝታ ለሙያ ባልደረቦቻ በትዝታ መልክ አኖረች።
የመጀመሪያ አልበሟን አምባሰልን ለመስራት በደሴ ባህል አምባ ከተደረገው ልምምድ ጨምሮ ስድስት ወር የሚፈጅ ጊዜ ወስዷል። ይህን አልበም ስትሰራ ግጥሙ በንባብ እና በካሴት ተቀርፆ እየተ ሰጣት እያጠናች ከዜማው እና ከስርቅርቅ ድምጿ ጋር በማዋሀድ ነበር። የወቅቱ የሪከርዲንግ ቴክኖሎጂ ደግሞ የጊዜውን ርዝመት ወስኖታል። ለዚህ አልበም ቅንብር እንዲሁም ግጥም እና ዜማ ከፍተኛውን ድርሻ ዳምጤ ተጫውቷል።
እርሱ ‹‹ማሬዋ ካርቦን ናት›› ይላል አንዴ ያጠናችውን ሙዚቃ ከማንነቷ ጋር የማዋሃድ መግነጢሳዊ ሃይል እንዳላት ሲገልፅ። የመጀመሪያው አልበም 12 ዘፈኖች የያዘ ሲሆን ሙሉውን ሥራ የሰጣት እሱ ነው። ከታንጎ ሙዚቃ ቤት ጋር ትዝታ ባቲ፣ አንቺሆዬ ቅኝቶችን የያዘውን ተወዳጅ አልበም በስኬት ሰርተው አጠናቀቁ። እርሷም የመጀመሪያዋን አልበም ለአድማጭ እነሆ በረከት ብላ የስኬት መንገዷን ተያያዘችው።
ማሪቱ አሜሪካን አገር በሥራ ምክንያት ከሄደች በኋላ የሙያ አጋሯ ዳምጤ ሌሎች ተጨማሪ አስር ዘፈኖችን ልኮላታል። እርሱ እንደሚለው በዚያ አገር የኑሮ ሁኔታ የጊዜ መጣበብ በመኖሩ ምክንያት ብዙ አልበሞች መስራት አልቻለችም። ነገር ግን በርካታ ሥራዎቿ አሁንም ድረስ ከአድማጭ ልብ ውስጥ የማይጠፋ እንደሆነ ይመሰክራል።
የመድረክ ላይ ብቃት
ማሬዋ በቁጥር ለማስቀመጥ በሚከብዱ መድረኮች ላይ አድናቂዎቿን በስርቅርቅ ድምጿ አዝናንታለች። አብዛኛውን መድረክ ደግሞ ከዳምጤ ጋር በጋራ ሰርተዋል። እርሱ እነዚያን ጊዜያቶች ሲያስታውስ ‹‹እንዲህ አይነት ተፈጥሮ አይቼ አላውቅም›› ይላል፤ በመድረክ ላይ ያላት ግርማ ሞገስ እና የማዝናናት ኃይል ማንነቷን አጉልተው ከሚያሳዩ ልዩ ብቃቶቿ ውስጥ የሚጠቀሱ መሆኑን እየተናገረ። አብዛኛውን ጊዜ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ጋር የሚፈጠር የቅኝት አለመግባባት ሲፈጠር እርሷ በተፈጥሮ በተሰጣት ክህሎት ሳትረበሽ የመስራት ብቃት እንዳላት የሙያ አጋሮቿ ሁሌም እያነሱ የሚደነቁበት ነው።
‹‹በመድረክ ላይ የተለየ ተሰጦ አላት›› የሚለው ዳምጤ አብዛኛው ድምፃዊ በተመሳሳይ ሥራዎች ላይ የመደናገጥ ባህሪ እንዳላቸው በማንሳት እርሷ ግን ይህ አይነት ጉዳይ እንደማያስጨንቃት ይገልፃል። ሆኖም አንዳንድ አዝናኝ አጋጣሚዎች እንዳላትም ይናገራል። በተለይ በደርግ ዘመነ መንግሥት የላሊበላ ኪነት በየጦር ሜዳው በመሄድ ሠራዊቱን ለማዝናናት የተለያዩ ሥራዎችን ያቀርብ ነበር። እርሷ መድረክ ላይ ወጥታ ሥራዎቿን ስታቀርብ ታዲያ በዘፈኑ ደስ ያለው አንድ ወታደር ሳይታሰብ በሞቅታ መሳሪያ ወደ ሰማይ ከተኮሰ ማሬዋ ከመቅፅበት መድረኩን ጥላ ትወርዳለች። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው ማሬዋ የሚፈነዳ ነገር አትወድም።
የክብር ዶክትሬት ለማሬዋ
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሰኔት ለማሪቱ ለገሰ ሰኔ 8 ቀን 2008 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በህይወት ዘመኗ ላበረከተችው የላቀ አስተዋጽዖ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷታል። ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት ጋር በተለይም ከወሎ አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች መካከል አምባሰል የሙዚቃ ቅኝት ለእሷ ብቻ የተፈቀደላት እስከሚመስል በማዜም ለወሎ የሙዚቃና ኪነ ጥበብ እድገት የአበረከተችው አስተዋፆኦን ከግምት በማስገባት ነበር።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በውስጡ ያቀፈውን የወሎ ላሊበላ የባህልና ኪነ ጥበብ ማእከል የበላይ ጠባቂ እንድትሆንና ያላትን ልምድ ለዩኒቨርሲቲው የሙዚቃ ትምህርት ክፍል የምታካፍልበት እድል ሰጥቷታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ቋሚ ገቢና የተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ እንዲኖራት በዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ኮሚቴ ተወስኗል። ይህንንም ወደተግባር ለመቀየር የአርቲስቷን ወደ ሀገር መመለስ ከተለያዩ አካላት ጋር ምን ማድረግ እንደሚገባ በመስማማት ጉዳዩን ለማስፈፀም በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ከዚህም ባለፈ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር በአሜሪካን ሀገር ባደረገው ጉብኝት እርሷን በአካል አግኝቶ ያናገራት ሲሆን የመኖሪያ ፈቃድ ጋር ተያይዞ ያላትን የፍርድ ቤት ጉዳይ ጨርሳ እንደምትመጣ ገልፃላቸው እንደነበር አሳውቀዋል። የህመሟ ሁኔታም በታወቀ ጊዜ በአቅራቢያዋ ካሉ ሰዎች ጋር በመገናኘት ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት ክትትል አድርገው ነበር።
ከዓመታት በፊት ክብርት ዶክተር አርቲስት ማሪቱ ለገሰ ያጋጠማት የጤና መታወክ በአድናቂዎቿ ዘንድ እንዲሁም በቅርብ ወዳጆቿ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር። ሆኖም ጤንነቷ ተመልሶ ከረጅም ዓመታት በኋላም የጀመረችውን የአሜሪካን አገር የመኖሪያ ፍቃድ ጨርሳ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዩኒቨርሲቲው የአርቲስቷን የጤና ሁኔታ ለማሻሻልና ወደ ሀገሯ እንድትገባ የሚደረግን ማንኛውንም ተግባር የሚደግፍ መሆኑን በተለ ያየ አጋጣሚም ሲገልፅ ቆይቷል። ወደ አገሯ እንድ ትመለስ እና በጥበብ አምባሳደርነቷ በክብር አገሯን እንድታገለግል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
እንደ መውጫ
ሴቶች ወደ ጓዳ ግቡ እየተባሉ በሚጨቆኑበት በዚያን ዘመን ማሪቱ ካረጀና ካፈጀ ተፅእኖ በመላቀቅ የትዳር አጋርዋን ወደሙያው አሳምና በማስገባት በድፍረት ወደ መድረክ የወጣችና የተሳካላት አርቲስት መሆንዋን የሙያ ባልደረቦቿ ይገልፃሉ።
የህዝብ ለህዝብ የኪነ ጥበብ ጉዞ የተሰጣትን ኃላፊነት በመቀበል ወደ አሜሪካንና አውሮፓ በመዝለቅ ለተጎዳው የአገሯ ህዝብ ከፍተኛ እርዳታ የለገሱ አገራትን ካመሰገኑ የኪነት አምባሳደሮች ውስጥ ናት፤ በሶማሊያ ወረራ ኢትዮጵያን እስከ አዋሽ ድረስ ለመቀማት የጦር ነጋሪት እየጎሰመ በገባ ጊዜ ለእናት አገሩና ለባንዲራው ክብር ለመዋደቅ በረሃ ለወረደው የጦር ሰራዊት ግንባር ድረስ በመዝለቅ ወኔ የሞላቸውን ዘፈኖች በማቀንቀን ሠራዊቱ የአገሩን ድንበር እንዲያስከብር ቀስቃሽ ሞተር እንደሆነችም ይገለፃል። የባህል አምባሳደር ናት። በዘፈንዋም ሆነ በአልባሳቶችዋ አገሯን ታስተዋውቃለች። ሁሌም ፀጉሯ ሹርቤ ነው። ወደ 300 የሚጠጉ የሃበሻ ቀሚሶች ያላት ሲሆን በመድረክ ሥራዋ ሁሌም የባህል አልባሳትን ለብሳ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ታደርጋለች።
አዲስ ዘመን ኅዳር 7/2012
ዳግም ከበደ