በኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ክስተቶች መስተናገዳቸውን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአዎንታና በአሉታዊ ሃሳባቸውን ሲገልፁ ተደምጠዋል፡፡ ከእነዚህ የሕብ ረተሰብ ክፍሎች መካከል ወጣቶች ልዩ ትኩረት ተስጥቷቸዋል፡፡ በመሆኑም ከሥራ አጥነት እንዲገላገሉ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት ወጣቱን መሰረት ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በተለይ ወጣቱን የስራ ባለቤት ከማድረግ አኳያ ምን ምቹ ሁኔታዎችስ ተደላድለዋል? ያጋጠሙ ችግሮችስ ምን ነበሩ? በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና አንዳንድ የአገሪቱ ከተሞች የወጣቱ ለግጭት ያለው ቅርበት በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በበጀት ዓመቱ አይንና ጆሮን ከሳቡት አበይት ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹን እነሆ ብለናል፡፡
የስራ እድል ፈጠራ
የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መጀመርን አስመልክቶ የ2011 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫዎችን ይፋ ባደረጉበት ወቅት የወጣቶችን ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደተቸረው ጠቁመዋል፡፡ በሀገሪቱ የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የፍትሀዊ ተጠቃሚነት እና ከወጣቶች ሥራ አጥነት ጥያቄ ጋር ሳይጣጣም መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡
በመሆኑም ለወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል ከተቀረጸው የሥራ እድል መርሃ ግብር ጋር መሳ ለመሳ የኢኮኖሚ ምህዳሩን የበለጠ ለማስፋት፣ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማሳደግ እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ተጨባጭ የማሻሻያ እርምጃዎችን መንግስት እንደሚወስድም አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም 65 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ ወጣት በመሆኑ ለዚህ አካል ሥራ የመፍጠርን ጉዳይ ዋና አጀንዳ አድርጎ መስራት ይገባል፤ ከብሔራዊ የደህንነት ጉዳይ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም ያሉት ፕሬዚደንቱ የሥራ አጥነቱን ችግር ለመቅረፍም መንግስት ቀን ከሌት ሳይታክት ይሰራል ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
የወጣቱ ሀብት ጉልበቱ በመሆኑ ያለውን ሀብት በአግባቡ የማይጠቀም ከሆነ ሥራ አጥነት እየተስፋፋ የራሱን ሕይወት እንኳን ለማኖር ችግር ውስጥ ይገባል። ይሄ ደግሞ በሀገር ደረጃ አደጋ ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ሥራ የሚገባ ከሆነ ግን ከመጠቀም አልፎ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ ይሆናል፡፡ በሥራ ላይ ማሰማራት ካልተቻለ ወጣቱ የሀገር ሀብት መሆኑ ቀርቶ አጥፊ መሆን የሚችልበት እድል ይሰፋል የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚክስ) ምሁራን ሲገልፁ ሰንበተዋል፡፡
ልክ እንደ ቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ሁሉ መምህሩም የወጣቶች ሥራ አጥነት ችግር የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ ስለሆነም ሥራ አጥነትና የሀገር ሰላም የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው የሀገርን ደህንነት አስጠብቆ ለማስቀጠል ወጣቱን የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ሙያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ለውጡን በመምራት ላይ የሚገኘው የመንግስት አካል በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ በተለያዩ መድረኮች በሚያራምደው ወጥና ጽኑ አቋም ምክንያት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከሚኖሩ ሥራ ከሌላቸው ወጣቶች ጋር የሰላ ውይይት በማድረግ ተግባሩን መሬት በማስነካት በኩል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ቀዳሚውን ይይዛሉ፡፡
ይሄን ተከትሎም 38 ሺህ ካሬ የካባ ድንጋይ ማውጫ ቦታ በ28 ማህበራት ለተደራጁ 1ሺህ 238 ወጣቶች ተላልፎ መሰጠት ችሏል፡፡ በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አስቸኳይ ውሳኔ በማሳረፍ ለሥራ አጥ ወጣቶች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በኩል በጥቅምት አጋማሽ ለንባብ በበቁ የሕትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በማሳያነት ተጠቃሽ የሆነ የበጀት ዓመቱ ፈር ቀዳጅ ተግባር ነበር፡፡
ከ2 ቢሊዮን ብር በላይም ተዘዋዋሪ ፈንድ
ለወጣቶች ብድር በማመቻቸት ተግባራዊ ማድረጉ ተጠቃሽ ትልቅ ተግባር ነበር፡፡ በዚህ መልክ የተወጠነው የሥራ እድል ፈጠራ ርብርብ ከዚህ በፊት እንደነበሩት ዓመታት በእሳት ማጥፊያነት ተሰልቶ የሚከወን መሆኑ ቀርቶ በዘላቂነት የወጣቶቹን ሕይወት በሚለውጥ ስልትና በተጠና መንገድ መተግበር እንዲችል በፌዴራል ደረጃ የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን በቅንጅት መቋቋሙ የሚታወስ ሲሆን በገጠር ለሚገኙ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶች እና በከተማ ለሚገኙ 1 ነጥብ 5ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችል ተጠቁሟል። በክልሎችም ተጠናክሮ መቀጠሉ ለወጣቶችና በአጠቃላይ ለዜጎች የሰነቀው ተስፋ በሰፊው ያነጋገረ ጉዳይ ነበር፡፡
ወጣቶችና ግጭት
በሌላ በኩል በሀገሪቱ የተቀጣጠለው የለውጥ ሂደት ሥር የሰደደና የተጠናከረ ባለመሆኑ አልፎ አልፎ ግጭቶች መከሰትና የወጣቱን ሕይወት እንደዋዛ ማሳጣት በሰፊው የተስተዋለ ክስተት እንደነበር በርካቶች ያነሳሉ፡፡ በየአካባቢውም ማን እንደሚያደራጃቸው በውል የማይታወቁ፣ በማን እንደሚመሩ ያልተለዩ፣ የአባላት ስብጥሩና ቁጥሩ ልኬት የሌለው፣ እንደየአካባቢው ሥም አውጥቶ ለሥራ የተሰለፉ ወጣቶችን፣ የአካባቢውን ማህበረሰብና መንግስትን ጭምር ሰላም በማወክና ንብረት በማውደም ቀላል የማይባል ጥፋት ማድረሱን የሚናገሩት ዜጎች ሥፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ይሄን ድርጊት ያልኮነነ የሚዲያ ተቋምም በአገሪቱ አይገኝም።
በሚከሰቱት ግጭቶች ምክንያት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ለጋ ወጣቶች ጭምር የተንኮለኞች ኢላማ እየሆኑ መምጣታቸው ያሳሰባቸው ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድም ‹‹ የዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ተማሪዎች ማለት የአንዲት አገር ነገዎች ናቸው። የአንዲት ሀገር መጻኢ እድል በዋነኛነት የሚወሰነው ያችን ሀገር ለመረከብ እየተዘጋጀ ባለው ትውልድ ማንነት ነው፡፡ ››
‹‹ለእኛ የነገውን የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ የምትወስኑት እናንተ የዛሬዎቹ ተማሪዎች የነገዎቹ አገር ገንቢዎች ናችሁ፡፡ ሀገር ስትገነቡ መዶሻችሁ የሚሆነው እውቀት፣ መጋዝና ሜትራችሁ የሚሆነው ክህሎት ነውና እነዚህን መሳሪያዎቻችሁን ከዩኒቨ ርሲቲዎችና ኮሌጆች ገብይታችሁ ስትወጡ ያን ጊዜ ኮርታችሁ ኢትዮጵያን የምታኮሩ የተማረ አገር ተረካቢዎች ትሆናላችሁ›› ብለዋል፡፡
‹‹የተማረ ሰው ማለት እውቀት የሰበሰበ ሰው ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የተማረ ሰው ማለት ተንትኖና አንጥሮ ማሰብ የሚችል ነው፡፡ እንዴትና ምን መማር እንዳለበት የሚያውቅ፣ ነጻ ሆኖ የሚያስብ፣ ለነገሮች ትክክለኛ ብያኔ የሚሰጥ እና የሚጠበቅበትን ለመስራት ራሱን በራሱ የሚቀሰቅስ ነው፡፡›› ሲሉም መክረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
የተማረ ሰው ማለት ከሌሎች ጋር ሲኖር ልዩነቶችን በሠለጠነና ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ ለመፍታት የሚችል፣ ችግሮችን በመጠናቸው ልክ የሚረዳና መፍትሄ የሚያፈልቅ፣ የራሱን ስሜትና ጸባይ እንዴት ማስተዳደር እንደሚችል የሚያውቅ፣ የሥራና የኑሮ ሥነ-ምግባር የተላበሰ ነው፡፡ ጾታ፣ ጎሳ፣ ሀይማኖት፣ ቀለምና እድሜ ሳይለይ ለሰው ዘር ሁሉ እኩል አመለካከት ያለው፣ ከለውጥ ጋር እንዴት መራመድ እንዳለበት የሚያውቅ ነው፡፡ ለኪነጥበብ፣ ለተፈጥሮ፣ ለእውቀት ልዩ ፍቅር ያለው፤ የማያውቃቸውን ባህሎች፣ ቋንቋዎችና አካባቢዎች ለማወቅ የሚተጋ ነው፡፡
በየትኛውም ዓለም የተማረን ሰው ለመበየን የሚቀርቡት መመዘኛዎች ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡ እናንተ የእኛ ነገዎች ራሳችሁን በእነዚህ መመዘኛዎች እንደምትለኩ እተማመናለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ሐሳቦች የሚስተናገዱባቸው መሆናቸውን ተረድታችሁ በትናንሽ ሳይሆን በትላልቅ ጉዳዮች፣ በመንደር ሳይሆን በሀገር አጀንዳዎች ተጠምዳችሁ ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ተስፋ አድርገዋል፡፡ የሕይወት መመሪያዬ አድርጌ በተገቢው ተጠቅሜበታለሁ፡፡ ምን አለበት ሰው ሁሉ በዚህ የሰውነት ሚዛን መለካት ቢችል? በማለት ሀሳቡን እና ስሜታቸውን የገለፁ ወጣቶች በርካቶች ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ባሳለፍነው በጀት ዓመት በሀገሪቱ የተከናወኑ ወጣት ተኮር ተግባራት፡-በወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራ፣ በወጣቶች ስብዕና ግንባታ፣ በሀገራዊ እድገትና ሰላም ማስፈን የወጣቶች ሚና፣ ሀገራዊ አንድነትን መፍጠር በሚችሉ የሞራልና የሥነ- ምግባር ልዕልና ግንባታዎች እና ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር በኩል የመንግስት ጽኑ አቋም፣ ከቀለም ባሻገር ማወቅ በሚገባን የሰው ማንነቶች ዙሪያ የሚያጠነጥን ይዘትን የተላበሱ እንደነበሩ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2011
ሙሐመድ ሁሴን