
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ሀገራቸውን ቅኝ ለመግዛት ቋምጦ በመምጣት ዓድዋ ላይ የመሸገውን ወራሪውን ኃይል ድባቅ በመምታት የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አስከብረው ሰንደቃቸውን ከፍ ያደረጉበትን የዓድዋ ድል ቀን እነሆ ዛሬ ለ129ኛ ጊዜ በድምቀት እያከበሩ ይገኛሉ::
ድሉ ታላቅ ነው፤ የኢትዮጵያ ብቻም አይደለም፤ በቅኝ ግዛት ውስጥ ሲማቅቁ የነበሩት መላ አፍሪካውያን እና ጥቁር ሕዝቦችም ጭምር ድል ነው::
ኢትዮጵያውያን ይህን ታላቅ የድል ቀን ስናከበር እነዚያ ጀግኖች በከፈሉት መስዋዕትነት የነፃነት አየር እየተነፍስን መሆኑን ልብ ልንል ይገባል:: በደርስንበት ሁሉ አንገታችንን ቀና አድርገን በኩራት የምንናገርለት ይህ የቀደምት አባቶችችን ገድል፣ ዛሬም ድረስ ነፃነታችንን ተጋፍቶ ለሚመጣ ምንኛውም ምድራዊ ኃይል ሁሉ እንዳንበረከክ፤ እጅ እንዳንሰጥ ፅናት ሆኖ አቁሞናል::
ኢትዮጵያውያን ያ ታላቅ ድል ባጎናጸፋቸው ጽናት ላይ ተመሥርተው ከዚያም በኋላ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ሊዳፈሩ የመጡ ጠላቶቻቸውን ድል በማድረግም ይታወቃሉ::
አሁንም ዳር ድንበር አልፎ ለመግባት የሚዳዳው አካል ይጠፋል ተብሎ ባይታሰብም፣ ለእዚህም ዝግጁነትን ማጠናከር እንደሚገባ ይታወቃል፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ድህነታችንን ተገን አርገው በእጅ አዙር ቅኝ ሊገዙን የሚሞክሩ ኃይሎችን መታገልም ሌላው የዘመኑን ክተት የሚፈልግ ጉዳይ ነው::
ወራሪዎች በግንባር ጦር ሰብቀው አይምጡብን እንጂ ድህነታችንን አስታከው፤ ርዳታን ተገን አድርገው እጃችንን ከመጠምዘዝ ቦዝነው አያውቁም:: በተለይም ደግሞ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞም ሆነ የአመራረት ሂደታችን ከዝናብ ጥገኝነት አለመላቀቁን ሰበብ አድርገው በሚለግሱን ሽርፍራፊ ገንዘብና ስንዴ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛታቸውን ለመስፋፋት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል::
ለዚህም ነው መንግሥት ላለፉት ስድስት ዓመታት የሀገራችን ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው በሚል፤ ከድህነት ለመውጣት ሀገሪቱ ካላት ሀብት ከፍተኛውን ለግብርናው ዘርፍ በመመደብ፣ ሕዝብን በማስተባበር መጠነ ሰፊ ተግባሮችን እያደረገ የሚገኘው:: ከምንም በፊት ደግሞ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችል ዘንድ ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እድገት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው::
በዚህ በኩል በዋናነት ደግሞ ለዘመናት የሌሎችን እጅ እንድናይ ተገደን የኖርንበትን ስንዴን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተከናወነ ያለው ተግባር ይጠቀሳል:: በዚህም ስንዴ በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን ማስቀረት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ተግባር እንደ ትልቅ እመርታ ተደርጎ ይታያል:: በእነዚህ በጣት በሚቆጠሩ ዓመታት ሀገሪቱ የትናንቱን የስንዴ ጠባቂነት ታሪክ ተረት አድርጋ ወደ ውጭ መላክም ውስጥ ገብታለች::
እንደቀደሙት አባቶች ሁሉ አሁንም መንግሥት በሀገሪቱ ላይ በርዳታ ሰበብ የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማቆም ያስችል ዘንድ የሀገሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት ለማስከበር በትኩረት እየሠራ ይገኛል::
ይህ ትልቅ ሀገራዊ እቅድ ከግቡ እንዲደርስ አሁን ካለው ትውልድ ምን ይጠበቃል? ይህ ትውልድስ ከዓድዋ ጀግኖች ምን ይማራል? በተለይም ምርታማነትን ለማሳደግ ምንስ ሊሠራ ይገባል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን ያነሳንላቸው በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ምርምር ዳይሬክተርና ተመራማሪ የሆኑት ታደለ ማሞ (ዶ/ር) የቀደሙት አባቶቻችንና እናቶቻችን ዓድዋ ላይ ድል ማድረግ የቻሉት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፈው በመንቀሳቀሳቸው ነው ሲሉ ይገልጻሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ከእነዚህ ስትራቴጂዎች መካከል እንደ ሀገር የፈጠሩት ሕዝባዊ አንድነት አንዱ መሆኑ ይታመናል:: የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ተዳፍሮ የመጣው ወራሪ ጠላት መሆኑን ተገንዝበው ሁሉም በአትንኩኝ ባይነት መንፈስ የሃይማኖት፣ ብሔር ወይም ጎሳና እድሜ ልዩነት ሳይገድባቸው አንድ ላይ መዝመታቸው ለድሉ አብቅቷቸዋል::
የአሁኑ ትውልድም የሀገርና የሕዝብ ጠላት የሆነውን የድህነትን አከርካሪ መስበር፤ የሀገሩንም የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚችለው ልዩነቱ ሳይገድበው በአንድነት ሲሠራ ብቻ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል::
‹‹ሀገሪቱ በጠላት ስትወረር ሁሉም በእኔነት ስሜት ያለውን ይዞ ወጥቶ ታግሏል›› የሚሉት ታደለ (ዶ/ር)፤ ይህም ሌላኛው ድል የማድረጋቸው ምስጢር መሆኑን ይጠቅሳሉ:: የምግብ ሉዓላዊነትንም ለማረጋገጥ እንዲሁ ሁሉም ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና ቴክኖሎጂ በጋራ በመጠቀም፤ እንደልብ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በልማቱ በመሠማራት፣ አንዱን ሌላውን በመደገፍ በጋራ ለማደግ ሊታትር ይገባል የሚል እምነትም እንዳላቸውም አመልክተዋል::
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በልማቱም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር መፍጠር ያስፈልጋል:: የእኔ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው የሚል አስተሳሰብ መፍጠር ይኖርበታል:: በጋራ መሆን የሀገሪቱን የጋራ ጥቅም ይመጣል ብሎ በአንድነት ስሜት ላይ ተመሥርቶ መሥራት ያስፈልጋል፤ በአንድነት ስሜት ከተሠራ የምግብ ሉዓላዊነትንም ማረጋገጥ ይቻላል::
አሁን ያለው ትውልድ ከዓድዋ ጀግኖች ሊማር የሚገባው ሌላው ዐቢይ ጉዳይ የርስበርስ ትስስርና የመናበብ ስትራቴጂን ነው:: በዓድዋው ዘመቻ የወሎ፣ የጎጃም፣ የጅማና የተለያዩ ንጉሦች ቢኖሩም፣ ሀገር በውጭ ኃይል ስትወረር ተናበውና ተባብረው በመታገላቸው ለድል በቅተዋል::
በወቅቱ የመገናኛ መንገድ፣ ስልክና መሰል ቴክሎጂዎች ባልነበሩበት ሁኔታ ዓፄ ምኒልክ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር፤ በመግባባት ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በአንድ ማሰለፍ ችለዋል::
የአሁኑ ትውልድም በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ድህነትን ማሸነፍ ይጠበቅበታል ሲሉም አስገንዝበዋል:: በተለይም በኢኮኖሚያቸው ካደጉና ቴክኖሎጂ ሊያስኮርጁ ከሚችሉ ሀገሮች ጋር የተጠናከረ ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባም ታደለ (ዶ/ር) ያመለክታሉ::
ይህንንም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ ‹‹ምርታማነትን ለማሳደግ እንደ ሩቅ ምሥራቅ ካሉ ሀገራት የመስኖ፣ የግብይት፣ ዲጂታል ግብርናን ማሳለጥ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች መቅዳት፣ ማላመድና ማሻገር ይገባል›› ብለዋል:: በተለይም ውሃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው በመስኖ ልማት ውጤታማ የሆኑ ሀገሮችን አሠራር በመኮረጅ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ያስገነዝባሉ::
ቦታዎችን ለይቶ ማወቅና በጥንቃቄ መጠቀማቸው ሌላው በዓድዋው ጦርነት ወቅት አባቶችን ለድል ያበቃ ስትራቴጂ እንደሆነ ተመራማሪው ጠቅሰው፣ ‹‹የእኛ አርበኞች ከወራሪው ጣሊያን ወታደሮች በበለጠ የሚዋጉባቸውን ቦታዎችን ያውቁ ነበር፤ ይህ መሆኑም በቀላሉ ጠላትን ለማጥቃት አስችሏቸዋል፤ በተቃራኒው ደግሞ የጠላት ወታደሮች የት ቦታ እንዴት መግባት እንዳለባቸው አለማወቃቸው ለሽንፈት ዳርጓቸዋል›› ይላሉ::
አሁን ያለው ትውልድም ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣትና ወደ ብልፅግና ለማሻገር በእጁ ላይ ያሉ ፀጋዎችን ማወቅ፣ መለየትና በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባው አስታውቀዋል::
‹‹የት ቦታ ምን አይነት ሀብት አለ? እንዴትስ ነው መጠቀም ያለብን? የሚሉትን ጠንቅቆ ማወቅም ይጠበቃል›› ሲሉ ታደለ (ዶ/ር) አመልክተው፣ ‹‹የውሃ አካላት የት አካባቢ አሉ? ያሉበትን አካባቢስ በምን መልኩ ልናለማ እንችላለን? ዓሣን መሠረት አድርገን ልናለማ የምንችላቸው ቦታዎች የትኞቹ ናቸው?›› የሚሉትን ጥያቄዎች በመመለስና ያሉንን ሀብቶች በሚገባ በማወቅ ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል›› ሲሉም ይመክራሉ::
እንደ ታደለ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያውያን የጦር አመራሮች በጦርነቱ ውጤታማ አመራር መስጠት መቻላቸውም ሌላው ጣሊያኖች ድል እንዲመቱ ያደረገ ምክንያት ነው:: እነ ራስ አሉላ፤ እነ ባልቻ አባነፍሶና የመሳሰሉት ጀግኖች መሪዎች ለወታደሮቻቸው የተለየ ለውጤት የሚያበቃ ትዕዛዝ ይሰጡ ስለነበር ከጠላቶቻቸው ይልቅ የበላይነት ማግኘት እንዲችሉ አርጓቸዋል::
አሁንም በግብርናው ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ ለመውጣት የዘርፉን የልማት እቅዶች በመተግበር ሂደት ትክክለኛ አመራር የሚሰጡ አመራሮችን ማስቀመጥ ወይም ማፍራት ያስፈልጋል:: በብቃት ላይ የተመሠረተ አመራር በልማቱ ውጤታማ ለመሆን በእጅጉ ያስፈልጋል:: ዘርፉን በትክክል የሚያውቁና አመራር ሊሰጡ የሚችሉ አመራሮችን መሰየምም ይገባል::
በብዛት መታገልም ሌላው የዓድዋ ጀግኖች የድል ምስጢር እንደሆነ ተመራማሪው ጠቅሰዋል:: ‹‹ጠላት ዘመናዊ መሣሪያ ይዞ ነው የመጣው፤ እኛ ደግሞ የነበረን የሰው ሀብትና ባሕላዊ መሣሪያ ብቻ ነበር:: እነሱ ወደ 17ሺ ወታደር ይዘው ሲመጡ፤ እኛ ደግሞ ከመቶ ሺ በላይ ነው ማሰለፍ የቻልነው፤ እነሱ ዘመናዊ መሣሪያ ቢኖራቸውም እኛ ግን በብዛታችን አሸነፍናቸው›› በማለት ያብራራሉ::
አሁንም የኢትዮጵያ ትልቁ ሃብትና ከተጠቀመችበት ብልፅግናዋን ልታረጋግጥ የምትችልበት መሣሪያ የሕዝብ ብዛቷ እንደሆነም ያስረዳሉ:: በተለይ ከአጠቃላዩ ሕዝብ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጣት ኃይል መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን በአግባቡ መጠቀም ለእድገት ወሳኝ እንደሆነም አመላክተዋል::
በሌላ በኩል የመሬት ጥበት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የተወሰነው ግብርና ላይ በማሰማራት በሌላ መስክ የሥራ ዕድል እንዲያገኝ ማድረግ አልያም የራሱ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባም ይመክራሉ:: ‹‹በተለይ በራሳቸው ሥራ እንዲፈጥሩ ማድረግ፤ የብድር፤ የሥልጠና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው መደገፍ ይገባል፤ ይህ ሲሆን ሁሉም ዜጋ አምራች ይሆናል›› ሲሉ አብራርተዋል:: ሁሉም አምራች ከሆነ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርታማነት እንደሚጨምርና፤ ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አንዱ መንገድ እንደሆነ ነው ያስረዱት::
ከዘመኑ ቀድመው የሄዱት እነዚያ የዓድዋ ጀግኖች የተለየ አስተውሎት እንደነበራቸውም ተመራማሪው ጠቅሰው፣ ይህም በጠላቶቻቸው ላይ የበላይነት መቀዳጀት ካስቻሉት መካከል እንደሚጠቀስ ተናግረዋል::
‹‹በተለይ የጣሊያኖችን መውጫና መግቢያ፣ ምን እንዳቀዱ፣ ምን ማድረግ እንደፈለጉ መረጃ የሚያቀብሏቸው አነፍናፊዎች የነበራቸው መሆኑ በቀላሉ ቀድመው ለማጥቃት አስችሏቸዋል›› በማለት ገልጸዋል:: ያንን ተሞክሮ በመውሰድ አሁንም በልዩ ዝግጅትና በሰው ሠራሽ ኢንተለጀንስ (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን) በመጠቀም በቀላሉ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚያሻም ያስገነዝባሉ::
ተመራማሪው እንዳብራሩት፤ ሞራልና መነሳሳትም የዓድዋው የጦር ዓውድ አድባሮች በተምሳሌትነት የሚያስጠቅሳቸው ጉዳይ ነው:: በተለይም ከእነሱ በፊት የነበሩ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በሀገር ወዳድነት፣ በወኔ ተፋልመው ዳር ድንበራቸውን ያስከበሩበትን የድል ታሪክ ጠንቅቀው የሚያውቁ የአባቶቻቸው ልጆች ነበሩ:: በዚህ የድል ሞራል ስንቅ ይዘው በመታገል ለስኬት በቅተዋል ይላሉ::
ተመራማሪው እነሱ ወኔው ስለነበራቸው ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ የመጣን ኃይል ድባቅ መምታት መቻላቸው አሁንም ላለው ትውልድ የሚያስተምረው ብዙ ጥበብ አለ ባይም ናቸው:: ‹‹አሁን ከእነሱ በእጥፍ የሚሻል ጊዜ ላይ ነን፤ ቴክኖሎጂውና የተሠሩ ምርምር ሥራዎች ጭምር ያግዙናል፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ ቴክኖሎጂዎችንና ሳይንስን ተጠቅመን ሀገራችን ከችግር ማውጣት እየቻልን እንዴት የድህነት ባሪያ እንሆናለን?›› ሲሉም ይጠይቃሉ::
በሌላ በኩል በወቅቱ ኢትዮጵያውያን የታጠቁት መሣሪያ ዘመናዊ ባይሆንም ያለውን መሣሪያና ጥይት ሳያባክኑ ውጤታማ በሆነ መልኩ በመጠቀም ጠላትን በመምታት ማሸነፍ መቻላቸውንም ያስታውሳሉ::
ታደለ (ዶ/ር) ከዚህም የአሁኑ ትውልድ መሣሪያዎችን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ብዙ ሊማረው የሚችለው እንዳለም አመላክተዋል:: ‹‹ያለንን ሃብት ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም፤ ለሙስና ሳይጋለጥ ሥራ ላይ ማዋል ከቻልን የምግብ ሉዓላዊነታችንን ማረጋገጥ እንችላለን›› ሲሉም ያስገነዝባሉ:: ሀብትን በአግባቡ፣ በቁጠባ፣ ውጤታማ ለሆነ ሥራ ብቻ መጠቀም ከቀደሙት አባቶች መማር ብልህነት እንደሆነ አመልክተዋል::
እንደ ተመራማሪው ማብራሪያ፤ የዓድዋ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት ሰፊ መረብ ዘርግተዋል:: የየትኛውም የአፍሪካ ሀገር ጩኸት ተደማጭነት አልነበረውም::
አሁን ግን ቢያንስ አፍሪካውያን ርስ በርስ አልያም ከኤዢያና ከሌሎች አሕጉሮች ጋር የልማት ትብብሮችን ማድረግ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል ተፈጥሯል:: በመሆኑም ከየትኛውም ሀገር ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግኙኝነትን በማጠናከር በትብብር መሥራት ይገባል:: በተለይም የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እንዲፈጠር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል::
‹‹ሌላው ጣሊያኖች ድል የተመቱበትና እኛም ልንማርበት የሚገባው ጉዳይ ከልክ ያለፈ በራስ መኮፈስ አስፈላጊ አለመሆኑን ነው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ እኛ እነሱን ለስህተት የዳረገውን በራስ የመኮፈስ ስሜት ማስወገድ አለብን ይላሉ:: ከዚህ ይልቅ የራሳችንን ዐሻራ ለማስቀመጥ መትጋት ይገባል ሲሉ መክረዋል:: ታሪክንም ሆነ ሀብትን ወደ ሥራ መቀየር ካልተቻለ ትርጉም እንደሌለውም አፅዕኖት ሰጥተው አስገንዝበዋል::
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደ መንግሥት እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች እንደሆነ ተመራማሪው ጠቅሰው፣ በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየታየ ያለው እመርታ ቀጣይነት እንዲኖረው መሥራት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ::
ከዚህ ጎን ለጎንም አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውንና ውሃን በማጥለቅለቅ ላይ የተመሠረተ የመስኖ ልማት ስትራቴጂ ውሃ ቆጣቢ በሆነ ዘዴና ቴክኖሎጂ በመቀየር ልማትን ማሳለጥ ወሳኝ እንደሆነም ያስረዳሉ:: ይህም ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን የአፈር አሲዳማነት ከመከላከል ባሻገር የውሃ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም ዕድል እንደሚሰጥ አስታውቀዋል::
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም