ስደተኛው የሙዚቃ አትሮኖስ

ዘመኑ በ1916 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ ወደ ዙፋኑ በመገስገስ ላይ የነበሩት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ለጉብኝት እየሩሳሌም ይገባሉ። ከጉብኝታቸው አንዱ የነበረው ደግሞ በእየሩሳሌም የሚገኘውን የአርመን ገዳም ነበር። በዚሁ መሠረት ጉብኝታቸውን የጀመሩት አልጋ ወራሹ ገዳሙ ውስጥ የተመለከቱት አንድ ነገር ቀልባቸውን ሳበው። ውስጥ የነበሩ የአርመን ቤተሰቦች አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው፣ ከሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው ጋር ሙዚቃን ሲጫወቱ ተመለከቱ።

ዓይንና ጆሮዎቻቸውን የሳበውን ሙዚቃዎቻቸውን ሲሰሙ ከልብ ተማረኩበት። አንድ ምኞትም ውስጣቸው ዘልቆ ገባ። በኋላም ወደ አርመኑ ፓትሪያርክ ጠጋ ብለው፤ ከእነኚህ አርመናዊ ዘመዶቻቸው መካከል ጥቂቱን እንኳን ወደ ኢትዮጵያ ቢሰዱላቸው ደስ እንደሚሰኙ ገለጹላቸው። ጥያቄው በፓትሪያርኩ ዘንድ ተቀባይነት አገኘና ፈቀዱላቸው።

በወቅቱም 40 አርመናዊያን ሙዚቀኞች የኢትዮጵያን ምድር ለመርገጥ ተመረጡ። ከእነዚህ መካከል የልዑካኑ አውራና ትልቁ የሙዚቃ መምህራቸው የነበሩት ሰው ኪቮርክ ናልቫንዲያን ነበሩ። ይህ ሰው ኋላ ላይ አልጋ ወራሹ ዙፋኑ ላይ ከወጡና ከነገሡ በኋላ የነበረውን “ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ” ብሔራዊ መዝሙር ዜማ የሠሩና ያቀናበሩ ናቸው። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት ሲደራጅም፣ የመጀመሪያው ሥራ አስኪያጅ ነበሩ። ከአርባዎቹ ጋር ቡድኑን እየመሩ ከመጡ ጊዜ አንስቶ፣ በሙዚቃና በሌላም፤ በርካታ ነገሮችን ለኢትዮጵያ ለማበርከት ችለዋል። ካበረከቷቸው ሁሉ ግን፤ ዛሬ ስለምናወራለት ታላቅ ሰው ድልድይ መሆናቸው ነው። በኪቮርክ የተጀመረው ታሪክ፣ ለወንድማቸው ልጅ ትልቁ መነሻ ሆነ።

1933ዓ.ም የኪቮርክ ናልቫንዲያን ወንድም አንድ የ15 ዓመት ዕድሜ ያለውን ልጃቸውን አስከትለው ኢትዮጵያ ገቡ። ይሄ ልጅም የዚህ ሁሉ ታሪክ ባለቤት ለመሆን የበቃው ሙሴ ነርሲስ ናልቫንዲያን ነበር። የዚህ ትንሽ ልጅ ሕይወት ገና ሲወለድ ጀምሮ በስደት የተሞላ ነበር። በ1918 ዓ.ም የተወለደው ሙሴ ነርሲስ ገና ጨቅላ ሳለ ከአባቱ ጋር ወደ ሶርያ ምድር ለማቅናት ተገዶ ነበር። በወቅቱ ኦቶማን ቱርኮች በአርመናውያኑ ላይ ሲፈጽሙት ከነበረው የዘር ማጥፋት ከተረፉ ጥቂቶች መካከል እርሱና ወላጅ አባቱ ይገኙበታል። አባቱ እንግሊዝኛን አቀላጥፎ መናገር የሚችል ስለነበረ እንግሊዞች ከጎናቸው አደረጉት። ከእነርሱ ጋር በአስተርጓሚነት ለመሥራት ልጁን ሙሴን ይዞ ወደ ሶሪያ ሄደ። በወቅቱ አርመናውያኑ ሁሉ ከዘር ጭፍጨፋው ለማምለጥ በየዓለማቱ በመሸሽ ተበታትነው ነበር።

እየሩሳሌም ውስጥ ለግርማዊነታቸው ክብር በማርሽ ባንድ አጅበው ሲያዜሙላቸውና በሙዚቃ ቀልባቸውን ሲያሰውሯቸው የነበሩትም፤ ወላጆቻቸው በኦቶማኖቹ የተጨፈጨፉባቸውና በስደት የሄዱ ወላጅ አልባ ልጆች ነበሩ። በሀገራችንም “አርባዎቹ የአርመን ልጆች” ተብለው ሲጠሩ የነበሩት፣ ከእነዚህ መካከል ተመርጠው ለግርማዊነታቸው የተላኩት ልጆች ናቸው።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከአባቱ ጋር ሆኖ አጎት ኪቮርክ ጋር የደረሰው ሙሴ ነርሲስም አርባዎቹን ተቀላቀለ። የአጎቱ ልጅ የነበረው ሙሴ ነርሲስ ናልባዲያን ከጥቂት ቆይታ በኋላ ታሪካዊ ሥራውን መሥራት ጀመረ። በመጀመሪያ የተላከው ወደ ማዘጋጃ ቤት የሙዚቃ ክፍል ነበር። ወደዚያ እንዳቀናም የሙዚቃ ቡድኑን አንድ በአንድ ማደራጀቱን ጀመረ።

ለሀገራችን ሙዚቀኞች እንግዳ ከነበረው ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር አስተዋወቃቸው። የዘመናዊ ኦርኬስትራ በማደራጀት አብሮ ይሠራና ያሠለጥንም ነበር። አጎት ኪቮርክ መሠረቱን በጣሉት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤትም በተመሳሳይ መልኩ በዘመናዊው የሙዚቃ መሣሪያዎች ማስተማሩን ቀጠለ። እያበራ የሚነድ፣ እየነደደ የሚያበራ አትሮኖስ ሆነ።

ሙሴና ሙሴ ነርሲስ… በመጀመሪያ ሁለቱም በቅርጫት ነበሩ። ባሕርን ለሁለት የከፈለው ሙሴ አስቀድሞ በባሕር ላይ የተጣለ ሕጻን ነበር። ወላጅ እናቱ እንዳይሰምጥ ቅርጫት ላይ አድርጋ በባሕር እንዲንሳፈፍ ስታደርገው እርሱን ለሞት ሳይሆን ከሞት ልታድነው ነበር። የሙሴ ነርሲስ አባት ልጁን ለማዳን ተሰደደ። የሁለቱ ሙሴዎች መጀመሪያ ያመሳሰለው፤ ሁለቱም በዜግነትና ማንነታቸው ላይ ከተቃጣ ሞት ያመለጡ ሕጻናት ናቸው። የመጀመሪያው ሙሴ የግብፁ የፈርኦን አገዛዝ፣ በእስራኤላውያን ወንድ ልጆች ላይ ካወጀው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የተረፈ ነው። ሁለተኛው ሙሴም የኦቶማን ቱርክ አገዛዝ በአርመናውያን ላይ ካደረገው የሞት ዘመቻ ያመለጠ ነው። ሁለቱም በስደት ተንገላተዋል።

አንደኛው እስራኤላዊ ሳለ ከግብፅ ነገሥታት ቤተሰብ ጋር በግብፅ አደገ። ሁለተኛውም አርመናዊ ሳለ በኢትዮጵያ ከዘውዳዊው ዙፋን ተጠግቶ ኖረ። አንዱ በፈርኦን ቤት፣ ሌላኛውም በጃንሆይ ግዛት አደጉ። እስራኤላዊ ሳለ እንደ ግብፃውያን ሆነ። አርመናዊ ሳለ እንደ ኢትዮጵያዊ ተቆጠረ። አንደኛው ለመንፈሳዊ ዓለም፣ ሁለተኛውም ለጥበብ ዓለም ተቀባ። ቀዳማዊው ሙሴ እስራኤላውያንን እየመራ ባሕር ከፍሎ አሻገራቸው። ያ ሙሴ በትሩን ወደ እባብ ቀይሮ ተዓምር ሠራ። ይሄኛው ሙሴ ነርሲስም የሙዚቃ መሣሪያዎቹን፤ ጊታሩን አንስቶ የሙዚቃ ተዓምር ሠራ።

ዳግማዊ ሙሴ ደግሞ ዘመናዊ ሙዚቃን ገልጦና አስተምሮ፤ ኢትዮጵያውያኑን ወደ ታላቁ የዘመናዊ ሙዚቃ አብዮት አሸጋገራቸው። ባደጉበት ሀገርም ታላቅና ገናና ለመሆን በቁ። ሁለቱም ሙሴዎች የየራሳቸውን ገድል አጻፉ።

ሙሴ ነርሲስ ናልቫንዲያን ዕድሜው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ሁሉ፤ ከአርመናዊነቱ እየራቀ፣ ለኢትዮጵያዊነት ሲቀርብ ነበር። ሁሌም ሲሠራ እንደ ባዕድ ሀገር ዜጋ ሆኖ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ እናት ሀገሬ ናት በሚል መንፈስ ነበር። ኢትዮጵያም በ1955 ዓ.ም፤ ልጄ ያለችበትን ዜግነቱን ሰጥታ አረጋግጣለታለች። እስትንፋሱ ልትነጠቅ በደረሰች የመጨረሻዋ ሰዓትም ከአንደበቱ ያወጣት ቃል ይህንኑ የምታረጋግጥ ነበረች። በአጎቱ ኪቮርክ የተቀረጸው የሙዚቃ ሕይወቱ እጅግ ታላቅና በድንቅ ችሎታ የሾረ ነበር። ከማዘጋጃ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤቶች፣ ከፖሊስ ሠራዊት እስከ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ድረስ፤ የዘመናዊ ሙዚቃን ገመድ በመዘርጋት መሠረቱን ጣለ።

በጊዜው ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች በሚገባ ስለሙዚቃ ያውቁና ይሠሩም የነበረ ቢሆንም፤ ግን አንዱም ጋር በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች የታጀበ ሥራ አልነበረም። በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች የተቀነባበረ ሙዚቃም አልተሰማም ነበር። የሙሴ ነርሲስ ጉዞ ለሁሉም እንግዳና ደስ የሚያሰኝ አዲስ መንገድ ነበር። ሙዚቀኛው ሁሉም ወደ አዲሱ መንገድ እየገባ፣ የሙዚቃ አፍቃሪውም ሰምቶ የማይጠግበውን ማድመጥ ጀመረ።

በሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የታላላቅ ሙዚቀኞች መፍለቂያ የነበረው የዘመናዊ ኦርኬስትራ በውል ራሱን የገለጠው ከዚህ በኋላ ነው። በየኦርኬስትራው ምድቦች ውስጥ፣ በመንፈሳዊ ቅናት በታሸ ጥበባዊ የበላይነት ከፊት ለመውጣት ሲደረግ የነበረው ትንቅንቅ መጧጧፉ ከዘመናዊ ሙዚቃ ትውውቅ ጋር ይጀምራል። ዛሬም በፍቅር የምናደምጣቸው ዘመን አይሽሬ ሥራዎች የወጡትም ከዚህ ውስጥ ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ፤ ሙሴ ነርሲስ የዘመናዊ ሙዚቃ አጨዋወትን በማስተማር ታላላቆችን ሲፈጥር ነበር። ራሱ እያቀናበረም ጥዑም የሙዚቃ ሥራዎችን ሲያበረክት ነበር። ከምንም ነገር በላይ ሙሴ ነርሲስ ናልቫንዲያን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ራሱን በመስጠት፣ ከውለታም ያለፈ መስዋዕትነት ከፍሏል እንድንለው የሚያደርገን አንድም እዚህ ጋር ነው። ከላይ የጠቀስናቸውን ጨምሮ በኮሜርስ ኮሌጅ፣ በናዝሬት የሴቶች ትምህርት ቤት እና በአርመን ትምህርት ቤቶች ውስጥ፤ በድምሩ ከሰባት በሚበልጡ ስፍራዎች እየዞረ ያስተምር ነበር። ታዲያ ይህን ሲያደርግ የነበረው ሁሉንም በአንድ ሳምንት ውስጥ ነው። ያለምንም እረፍት ከአንዱ ወደ አንዱ እየዞረ ከሁሉም ዘንድ ይደርሳል።

ከሙሴ ነርሲስ የመጀመሪያዎቹን የዘመናዊ ሙዚቃ ማዕድ ከቆረሱት መካከል ተስፋዬ ሳሕሉ፣ ምኒልክ ወስናቸው፣ መልካሙ ተበጀ፣ ጌጡ አየለ፣ ሂሩት በቀለ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ግርማ ነጋሽ እና ሌሎችም ነበሩ። በወቅቱ ሙዚቃን ይሠራ የነበረው ለድምፃውያኑ ብቻ አልነበረም። ያኔ ይሠሩ ለነበሩ ፊልምና ቲያትሮችም የማጀቢያ ሙዚቃ በመሥራት፣ ሌላ አዲስ መልክ እንዲኖራቸው አድርጓል። ከሁለቱም ትዕይንቶች ጀርባ ይሰማ የነበረው በሙዚቃ መሣሪያዎች የተቀነባበረ ማጀቢያ፤ ተመልካቹን ይበልጥ የሚስብና በስሜት የሚያነሆልል ነበር። እንደ ፊልም የመጀመሪያ በሆነው “ሂሩት አባቷ ማነው” ሙሴ ነርሲስ በማጀቢያው ዐሻራውን አኑሮበታል።

ሙሴ ነርሲስ መጋረጃው ውስጥ ነው። በጊዜው ምስጢራዊ የነበረው አጋጣሚ የተፈጠረው እንዲህ ነበር…ጃንሆይ ከአንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች ሙግት ገጠማቸው። ሙግቱም ስብሰባው አዲስ አበባ ላይ ሊሆን አይገባም ነው። በስተመጨረሻ ግን ጃንሆይ ረቱና አዲስ አበባ ላይ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተያዘ። ከዚህ በኋላም ንጉሡ መዲናዋን ወደማሰናዳት ገቡ። በስንት ትግል ያመጡት ነገር ነውና ሁሉንም ነገር የተሳካና ቆንጆ አድርጎ የተጋፉትንም መሪዎች ማሳመን ነበረባቸው። ለአፍሪካ መሪዎች ይመጥናሉ የተባሉ ነገሮች በሙሉ ተዘጋጁ። ከዝግጅቶቹ መካከልም አንደኛው መሪዎቹን ለማዝናናት የሚዘጋጅ የኪነ ጥበብ ድግስ ነበር። በቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በአሁኑ ብሔራዊ ቲያትር የሚቀርብ ነበር። ከእያንዳንዱ የኪነ ጥበብ ዘርፍ የሚቀርብ የጥበብ ቡፌ ለማሰናዳትም ሁሉም በየፊናው መሯሯጥ ጀመረ። በዚህ ጊዜ የሙዚቃው ዘርፍ ኃላፊነቱ የወደቀው በሙሴ ነርሲስ ላይ ነበር።

የኢትዮጵያ ክብር የእርሱም ክብር ነውና ሙሴ ይህን ከሰማበት ቅጽበት አንስቶ ወደ ሥራ ገባ። ስለሚያዘጋጀው ሙዚቃ ሲያውጠነጥን ከቆየ በኋላ፤ ዛሬም እንደተወደደ ያለውን “አፍሪካ አፍሪካ” የሚለውን ሙዚቃ ሠራው። ይህን ኅብረ ዝማሬ በድምፅ የሚያዜሙትንም ለማግኘት የሄደው ወደ አርመን ቤተ ክርስቲያን ነበር። የቤተ ክርስቲያኗን ኳየር ዘማሪዎችን መርጦም ልምምዱን አስጀመራቸው። መሪዎቹ አዲስ አበባ ሊገቡ የቀሩት ጥቂት ቀናት ናቸው። ሁሉም ነገር መልክ መልክ እየያዘ ነው በተባለበት ሰዓት ግን ድንገት የአራት ኪሎን አካባቢ ያተራመሰ አውሎ ንፋስ ተነሳ። እየጠነከረ ሄዶም ሚዲያዎች ድረስ ዘለቀ። “የአርመን ቤተ ክርስቲያን ዘማሪያን፤ አማርኛን በትክክል መናገር ስለማይችሉ፣ ይህ ኅብረ ዝማሬ በኢትዮጵያውያን ይዘመር” የሚል ጽሑፍ የያዙ ጋዜጣና መጽሔቶች በረከቱ።

የሆነውን ነገር የተመለከተው ሙሴ ነርሲስ፤ ለእነርሱው ብዬ በሠራሁ የሚል አንዳችም የመከፋትና የቁጭት ስሜት አላደረበትም ነበር። ቀኑ መጥቶ ዓይን ስር የደረሰ ቢሆንም ነብሱ የነበራት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሳይበርድ፣ በተቻለው ሁሉ ፈጥኖ ከቲያትር ቤቱ ድምፃውያን ጋር በድጋሚ ለመሥራት ተነሳ። ሙሴ አሁንም ሳያጎድል ቆንጆ አድርጎ በመሥራት፣ ዝግጁ መሆኑን ገለጸ። ቅሉ እንዲህ ቢሆንም፤ ለሙሴ ቅሬታና ባይተዋርነት ሊፈጥርበት የሚችል ሌላ ሀሳብ ተነሳ። ስብሰባው የአፍሪካ መሪዎች ነው። ጊዜ ደግሞ በውል አልባ የቅኝ ግዛት ጥላቻና አመጽ የከረረበት ነው። ታዲያ ከእነዚህ የጥቁር መሪዎች የግል መድረክ ፊት፣ ሙዚቃው በነጭ ሲቀርብ ለሀገራችን ስምም ጥሩ አይደለም። ሌላ ነገር ያለን ያስመስልና ያሳማናል፤ የሚል ፍራቻ ስለነገሠ አንድ መላ ተዘየደ። በዕለቱ የአፍሪካ መሪዎች ቦታ ቦታቸውን ይዘው ሙዚቃው ሊቀርብ ሆነ። ከመድረኩ ፊት መሆን የነበረበት ሙሴ ቢሆንም፤ በቦታው አቶ ተፈራ አቡነ ወልድ ፊት እንዲሆኑ ተደረገ። ሙሴ ነርሲስ ግን መልኩ እንዳይታይ፣ ከኋላ በመጋረጃ ተሸፍኖ ኅብረ ዝማሬውን አቀረበ። እንዲህ ዓይነቱ ነገር ለብዙ ሰው የሚያስከፋና ሆድ የሚያስብስ ቢሆንም ሙሴ ነርሲስ ግን አንዳችም ቅር ሳይለው አደረገው።

የኢትዮጵያን የሙዚቃ ታሪክ በቅርበት የሚያውቅ ማንም የናልቫንዲያን ቤተሰብ ሊዘነጋ አይችልም። የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት የነበረው፣ የአሁኑ ብሔራዊ ቲያትር ቤት ውስጥ ከየትኛውም ቦታ በላይ ስምና ዐሻራዎቻቸው አለ። ለዚህም ይመስላል በአንድ ወቅት “ትዝታ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም በማዘጋጀት የቤተሰቡን ኢትዮጵያዊ የጥበብ ሠንሠለት ማስቃኘታቸው። ሥራና ታሪኮቻቸውን በሚተርከው በዚህ ፊልም፤ ከኪቮርክ ናልቫንዲያን እስከ ሙሴ ነርሲስ ናልቫንዲያን ተዳሰውበታል። በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ ጉዳዮች ያበረከቱት ብዙ ቢሆንም፤ በዋናነት የሚዳስሰው ገዝፎ በወጣው የሙዚቃ ገጸ በረከቶቻቸው ዙሪያ ነው። ስለ ሙሴ ነርሲስ በአንደበታቸው የሚናገሩም ሆነ የሚጽፉ ሁሉ፤ እርሱን የሚገልጹበት አንድ ዓይነት የጋራ ዐረፍተ ነገር አላቸው። “ዕድሜውንና ሕይወቱን ሁሉ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ የሰዋ ሰው ነው” የሚል ነው። ከትንሽ ልጅነቱ አንስቶ ከጉልምሳና ያለፈ ዕድሜው ድረስ፣ ከማንም በላይ ሲፋተግና ሲወድቅ ሲነሳ፣ ሲያዝንና ሲደሰትም፣ ሲሠራና ሲያሠራ ያለ አንዳች እረፍት ራሱን መስዋዕት ያደረገ ሰው ነው። ኢትዮጵያን ከረገጠበትና ሀገሬ ብሎ መኖር ከጀመረበት አንስቶ፤ ለግል ሕይወቱ ሲል እንኳን ያባከነው ጊዜ አነበረም።

ሙሴ ነርሲስ ስለ ሀገሩ ኢትዮጵያ የገበራት ነብሱ ከመነጠቁ አስቀድሞ፤ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኦርኬስትራ ባንድን ይዞ፣ ልዑኩን እየመራ ወደ ሌጎስ ከተማ አቀና። ምክንያቱ ደግሞ፤ በሌጎስ ለተዘጋጀው የአፍሪካ አርት ፌስቲቫል ነበር። ለዓመታት በዘመናዊ ሙዚቃ ከቃኛቸው የጥበብ ልጆቹ ጋር በመልካም ሁኔታ ሌጎስ ላይ ነበሩ። ግን የሕይወቱን አቅጣጫና የጉዞ መስመሩን ያስለወጠ መጥፎ አጋጣሚ ተፈጠረ። ሰውነቱ እየራደ፣ ጤናው መታወክ ጀመረ። ነገሮችም እየከፉና እየበረታበት ሄደ። ለካስ ሙሴ ነርሲስ ሌጎስ ላይ ሆኖ በወባ በሽታ ተይዞ ኖሯል። ከዚህ በኋላ ሕመሙ ሲበረታበት ለሕክምና ወደ እንግሊዝ ሀገር አቀና። ግን ያቺ ሰበበኛ የወባ ትንኝ፤ በሽታ አምጪ ብቻ ሳትሆን የሞት መልዓክም ነበረች። ሕክምናው ሙሴ ነርሲስን ሊታደገው አልቻለም። በ1969 ዓ.ም እዚያው እንዳለ እስከወዲያኛው አሸለበ።

ሙሴ ነርሲስ ሲኖርም ሲሞትም ኢትዮጵያዊ ነበር። እንደ እናቱ እንጂ አንዴም እንደ እንጀራ እናቱ ሳይመለከታት ለሀገሩ ኢትዮጵያ መስዋዕትነትን የከፈለላት የምን ጊዜም ጀግና ነው። ሀገሩን ምን ያህል እንደሚወዳት የገለጸበት ቃል በእስትንፋሱ መጨረሻ ተናገራት። “እኔን በሀገሬ መሬት ላይ ቅበሩኝ። የኢትዮጵያን አፈር አቅምሱኝ” አለ፤ ይህ ታላቅ ሰው። እንኳንስ ለእርሱ ዓይነቱ ባለውለታና የሀገሬ ሰው ለማንም ኑዛዜን አይገፋምና አስከሬኑ ወደ ሀገሩ መጣ። ቀብሩም በአዲስ አበባ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።

4 ኪሎ ላይ ሠርቷት የነበረችው መኖሪያ ቤቱ ዛሬ በቅርስነት ተይዛለች። በአራት ኪሎና ፒያሳ መካከል ስንመላለስም ሆነ፤ ሰባ ደረጃን ስንወጣና ስንወርድ ዞር ብለን ያቺን የአርመን ቤተ ክርስቲያን እናስተውላት። በተመለከትን ቁጥር ሁሉም አርባዎቹን እናስታውስበታለን። አጎት ኪቮርክን እናመሰግናቸዋለን። ለታላቁ ሙሴ ነርሲስ ግን “የጥበብ አርበኛ” ብሎ ዝም ከማለት በቀር ቃላት የሉም።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You