– ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር
በኢትዮጵያ ፊት አውራሪነት ሲሰራበት የቆየው የናይል የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት በስድስት አገሮች በመፈረሙ ከወራት በፊት ሕግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሕግ ሆኖ መጽደቁን ተከትሎ ”የናይል ሪቨር ኮሚሽን” እንደሚቋቋም ሲነገር ቆይቷል፡፡ የዚህ ኮሚሽን መቋቋም ሒደት ምን ይመስላል? ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በምን ያህል ልክ እየተጠቀመች ነው? ከዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ ቀጣይ ስራ ምን ይመስላል የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን አስመልክተን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)ን የዛሬ የወቅታዊ እንግዳ አድርገናቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ በውሃው ዘርፍ ያላት አቅምና ሀብቱን እየተጠቀ መችበት ያለው አካሔድ እንዴት ይገለጻል?
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያ 12 ተፋሰሶች አሏት፡፡ ከ12ቱ ተፋሰሶች ለልማት መሆን የሚችል ውሃ ያላቸው ስምንቱ ናቸው፡፡ ስምንቱም ለኃይል ማመንጫነት /ለኃይድሮፓወር/ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ለመስኖ እና ለመጠጥ ውሃም የሚሆኑ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደምም ያለንን የውሃ ሀብት ለኃይል ማመንጫነት፣ ለመጠጥ ውሃና ለግብርና ሥራዎች ስንጠቀምባቸው ቆይተናል፡፡ ይሁንና ለኃይል ማመንጫነት ልንጠቀምበት ከምንችለው ወደ 45 ጊጋ ዋት አቅም ውስጥ እስካሁን እየተጠቀምንበት ያለው ከእስር እና ከአስራ አንድ በመቶ የማይሞላውን ነው፡፡ ይህን ቁጥር ስናይ ብዙ መልማት የሚችል ሰፊ የውሃ ሀብት እንዳለን አመላካች ነው፡፡ በመስኖም በመጠጥ ውሃ ያለን አቅም እንደዚያው ነው፡፡ በጣም ትልቅ ሀብት በእጃችን አለ፡፡ ይህ እምቅ ሀብታችን ነው፡፡
የሀገሪቱ ትልቁ ውሃ ያለው በዓባይ ተፋሰስ ነው። የዓባይ ተፋሰስ የምንለው የዓባይ ወንዝ ያለበትን ነው። በሌላኛው በኩል ስናይ ደግሞ ባሮ አኮቦ ለኃይል ማመንጫነት ሆነ ለመስኖ የሚለማ ቦታ አለው፡፡ ከዚህ ባሻገር እነ ኦሞ፣ ጊቤ፣ ዳዋ፣ ዋቤ ሸበሌ ለኃይል ማመንጫም ለመስኖም የሚሆኑ ናቸው፡፡ የአዋሽ ተፋሰስም እስካሁን ካሉን ተፋሰሶች በጣም የለማና በጣም ትልቅ ሀብት ያለበት ሲሆን በመስኖ ጭምር እየለማ የሚገኝ ነው፡፡
ውሃን በማልማት በኩል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ለኃይል ማመንጫነት ነው፤ ሁለተ ኛው ለግብርና መስኖ ነው፤ ሶስተኛው ደግሞ ለመጠጥ ውሃ፣ አራተኛው ለጎርፍ መከላከል ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚያስቡት ጎርፍ አደጋ ሳይሆን በረከት ነው፡፡
ምክንያቱም ጎርፍ ማግኘት ማለት ውሃ ማግኘት እንደማለት ነው፡፡ እኛን የቸገረን ጎርፍን በረከት ማድረግ የሚያስችል አቅም ማጣት እንጂ ክረምት ላይ የሚዘንበውን ዝናብ ይዘን ማቆየት ብንችል በጋ ላይ ለሚያጋጥመን ማንኛውም የውሃ እጥረት እንጠቀምበታለን፡፡
በሌላ በኩል ግድቦቻችንን ስንገነባ ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ በረከቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ዓሳን መጥቀስ ይቻላል። ግድቦቻችን የሚያለሙት መስኖን ብቻ ሳይሆን ዓሳንም ጭምር የሚያመርቱ ናቸው፡፡ ከዚህ ሰፋ ስናደርግ ደግሞ ለቱሪዝም መስህብም መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡
ውሃን ማልማት ማለት ከጠቀስናቸው በተጨማሪ ከእነርሱ ጋር ተዛማጅ የሚሆኑ ልማቶችን ማካሔድ መቻልን የሚያካትት ነው፡፡ ከዓሳና ከመዝናኛነት ከማገልገል በተጨማሪ ለትራንስፖርት አገልግሎት መጠቀም እንችላለን፡፡ የውሃን የመልማት አቅም ስናስተውል ሰፋ የልማት ሥራዎችን ታሳቢ የሚያደርግ ነው፡፡ ለአብነትም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴን ግድብ ትሩፋት ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት አስተዳደር ምን ይመስላል ? ያለንን የውሃ ሀብት በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ስርዓት አለን?
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡– በሚኒስቴሩ ከተያዙ የስራ ዘርፎች አንደኛ የኢነርጂ፣ ሁለተኛው የመጠጥ ውሃ፣ ሶስተኛው የውሃ ሀብት አስተዳደር ናቸው፡፡ የውሃ ሀብት በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚመራ ነው፡፡ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በመዋቅር ራሱን ችሎ መሬት እንዲረግጥ ለማስቻልም ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በሁሉም ተፋሰሶች ማለትም በስምጥ ሸለቆ፣ በአዋሽ እንዲሁም በዓባይ ተፋሰሶች የየራሳቸው ጽህፈት ቤቶች አሉን፡፡
ሶስተኛው ጉዳይ የውሃ ሀብት አስተዳደር ነው፣ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሲባል የአንድ ተቋም ብቻ አይደለም። በጣም ብዙ ተቋማት በቅንጅት የሚሳተፉበት ነው።ግብርና፣ ጤና እና ሌሎችም በፌዴራል ደረጃና በክልል ደረጃ ያሉ አካላት በቅንጅት የሚሰሩት ነው፡፡
ይህን ታሳቢ ያደረገ ‹‹የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት ማሕቀፍ›› የሚባል ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤት አቅርበናል፡፡ ሕግ ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሁሉም የሚሳተፉበት የጋራ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይህን በማስፈጸም ሂደት ትልቁ ድርሻ የእኛ ነው፡፡
የውሃ ሀብት አስተዳደርን በተመለከተ የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመዋቅር፣ በአሰራር፣ በሕግና በስርዓት ተደግፎ ወደመሬት እንዲወርድ የሰራቸው ስራዎችና የጀመራቸው በጣም መልካም ክንውኖች አሉ። አሁን ባለን ደረጃ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማሳካት የሁሉንም የውሃ ተፋሰሶች ማስተር ፕላን እየተሰራ ነው፡፡ እየተሰራ ያለው ማስተር ፕላን በእያንዳንዱ ተፋሰስ ውስጥ ምን መሰራት እንዳለበት አመላካች ነው፡፡
ለምሳሌ መንገድ ሲሰራ፣ ከተማም ሲቆረቆር የራሱ ማስተር ፕላን አለው፡፡ ልክ እንደዚያው ከባሮ አኮቦ ውጪ የሁሉንም ተፋሰሶች ማስተር ፕላን ይዘናል፡፡ የባሮ አኮቦ ግን ትንሽ ይቀረናል፡፡ እሱም በዚህ ዓመት ያልቃል። ማስተር ፕላኑ ካለ ሁሉም በፕላኑ መሰረት በአግባቡ ይተገበራሉ፡፡
ለሁሉም የውሃ ልማት የምንመክረው ይህ ተግባራዊ እንዲደረግ ነው፡፡ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ያለበት ጅምር እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነው የሚያስብል ነው፡፡ ማሕቀፉ ሲያልቅ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል እንዲሳተፍ ይደረጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ባላት የውሃ ሀብት መስኖን ጨምሮ ለሁሉም የልማት ሥራዎች እየተጠቀመችበት ነው ማለት ይቻላል?
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡– በአሁኑ ወቅት እንደድሮ አይደለም፡፡ የትም ቦታ መስኖን መጠቀም ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም መስኖን ለመጠቀም ረባዳ አሊያም ሜዳማ ቦታ ተፈልጎ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በቴክኖሎጂ በመታገዝ በተለያዩ የውሃ ጠብታ መሳሪያና በፓምፕም ጭምር በመጠቀም ተራራ ማልማት ይቻላል፡፡
ከውሃም ከአቀማመጥም አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ማንኛውም የእርሻ መሬት መስኖ መጠቀምን የሚከለክል አይደለም፡፡ ዋናው በአካባቢው ውሃ መኖሩን ብቻ ማረጋገጥ ነው፡፡ ለምሳሌ በአቅራቢያው ውሃ ከሌለ መሬቱ ቢለማም ትርጉም አይኖረውም፡፡
ስለዚህ እኛ ያለን የውሃ መጠን በአብዛኛው ወደምዕራቡ ነው፡፡ ትልቁን የያዘው የዓባይ ተፋሰስ ነው። የዓባይ ተፋሰስ ከአቀማመጡ የተነሳ ወጣ ገባ ነው፡፡ ስለዚህም ለመስኖ ቀላል የማይሆን ቴክኖሎጂን የሚጠይቅ የመሬት አቀማመጥ አለው። ያንን ማልማት ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ ከውሃ አንጻር ሀብት አለን። ገና ያልተነካ ሰፊ መሬትም አለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ባለፉት ዓመታት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የጀመሩት የስንዴ ኢንሼቲቭ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ቀደም ሲል በተለይ ኢትዮጵያ ላይ ስንዴን በመስኖ ማልማት እምብዛም አይታወቅም ነበር፡፡ ይህ ግን በኢትዮጵያ ላይ አሁን ተችሏል፡፡
ውሃ እስካለ ድረስ በጣም ብዙ ቦታ ማምረት ይቻላል። ስንዴ ብቻ ሳይሆን ሩዝም በመመረት ላይ ይገኛል፡፡ ባሮ አኮባ በታችኛው በኩል ብናይ ለሩዝ ልማት የሚመች ነው፡፡ አዋሽ ላይ ስናይ ደግሞ ቀደም ሲል የስንዴ ልማት ያልተለመደ ነበር፤ አሁን ግን በሚያስገርም ሁኔታ ተጀምሯል፡፡ ፍራፍሬም በስፋት እየለማ ነው፡፡ መሬትም ውሃም አለንና በስፋት መጠቀም ይቻላል፡፡ በዚህ ትልቅ ተስፋ አለን፡፡
ውሃ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ጥራት ያለው ውሃ መሆኑ ደግሞ በራሱ በረከት ነው፡፡ ጨዋማ የሆነ ውሃ የለንም፡፡ ምክንያቱም የምናገኘው የዝናብ ውሃ እንደመሆኑ በጣም ንጹህ ውሃ ነው፡፡ ይህን በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፤ ይህም ተጀምሯል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ታዳሽ ኃይል ከማመን ጨት አኳያ ባለን የውሃ ሀብትም ሆነ ከጸሐይ፣ ከነፋስና ከእንፋሎት ምን ያህል መጠቀም ችለናል?
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ በጣም ከምትታወቅበት አንዱ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ባለቤት ነች ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ውሃ ነው። ከዚያም ጸሀይ፣ ነፋስ እና እንፋሎት እንደየቅደም ተከተላቸው ታዳሽ ኃይል የሚገኝባቸው ናቸው፡፡
እስካሁን ባለን መረጃ ከውሃ ኃይል ወደ 45 ጊጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል አቅም አለን፡፡ እስካሁን ያመረትነው ግን ወደ አራት ነጥብ ስምንት ጊጋ ዋት ብቻ ነው፡፡ ይህ በመቶኛ ሲሰላ አስር በመቶ አካባቢ ነው። እስካሁን ካመረትናቸው ኢነርጂዎች ደግሞ የነፋስም፣ የእንፋሎትም የቆሻሻንም ጨምሮ ስናይ ከውሀ ኃይል የሚመነጨው 92 በመቶ ነው። ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ውሃ ነው ማለት ነው፡፡ ተቋማችንም ስያሜውን ‘ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር’ ያደረገው ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ከውሃ ጋር ተያይዞ ኢነርጂ ስለሚጣመር ነው ፡፡
ለአብነት የታላቁ ሕዳሴ ግድብን መጥቀስ ይቻላል። ከግድቡ የሚመነጨው ኃይል ትልቅ ነው፡፡ ይህ ግድብ አልቋል፡፡ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ወደምርታማነት ሲገባ ለውጥ ይኖራል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ኃይል ማግኘት ያለባቸው ኬብሎች ይኑሩ እንጂ የኃይል መቆራረጡ ብዙ ነውና እሱን የሚቀንስ ይሆናል፡፡ የተመረተው ኃይል ያለብክነት በሁሉም አካባቢ እንዲደርስም ማድረግ ይጠበቃል፡፡ እኛ ከምንሰራው ውስጥ አንዱ ይህንን ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ከዋናው ቋት ውጭ የሆኑ ማለትም ራቅ ያሉ አሉ፡፡ ኃይል የምናደርሰው ከቋት ውጭ በሆነ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ አንደኛ ምርጫችን የጸሐይ ኃይል ነው፡፡ በርካታ ቦታዎችን ከዚህ አንጻር ለይተናል፣ በርካታ ድጋፍም እያገኘን ነው፡፡ ወጣ ወጣ ያሉ የገጠር ቀበሌዎችንና ከተሞችን ጭምር ሶላር እንዲያገኙ ማድረግ ላይ የምንተገብረው ሁለተኛ ስራችን ይሆናል፡፡
ሶስተኛው ኢነርጂን በመጠቀም የምናመጣቸው አገልግሎቶችን ማሻሻል ነው፡፡ ለምሳሌ የመጠጥ ውሃ ብናይ በየገጠሩ የሚጠቀሙት ጀነሬተርን ነው፡፡ ጀነሬተር ደግሞ አካባቢ የሚበክል ነው፡፡ ነዳጅም እንደልብ አይገኝም፡፡ ስለዚህ እሱን በሶላር መተካት ያስፈልጋል፡፡ ለእሱ የሚሆን ብዙ ቦታ ያለ ከመሆኑ በተጨማሪ በቅርቡም ብዙ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
ሌላው ከነፋስ ኃይል ጋር በተገናኘ የግሉ ባለሀብት በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት እያሳየ ነው፤ ለምሳሌ አይሻ ላይ የተሰራው ስራ አለ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደ አገር የተፈራረምናቸው ውሎች አሉ፡፡ ባለሀብቱ በዘርፉ መሳተፍ የሚያስችለው እድልም አለ፡፡
በጥቅሉ በኢነርጂ ላይ አንዱና ትልቁ ስራችን ከውሃ ኃይል ማመንጨት ነው፣ ትልቁን ድርሻ መያዙ እንደተጠበቀ ሆኖ የሶላርንና የነፋስን ድምር ውጤት ማሻሻል የሚጠበቅብን ይሆናል፡፡ ሶላር እስካሁን ባለው ደረጃ ሲታይ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ስለዚህ እሱን ከፍ ማድረግ አለብን፡፡ ከውሃ ኃይል ማመንጨትን ግን አጠናክረን የቀጠልነው ሥራችን ነው ፡፡
አዲስ ዘመን፡– በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ጸድቆ ወደስራ የገባው የናይል ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሕግ ሆኗል፤ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በአግባቡ ማልማት እንድትችል ምን አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል?
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ይህ ማሕቀፍ በተፋሰሱ ውስጥ ያሉ አገሮች የወንዙን ውሃ በጋራ ለመጠቀም የራሳቸው ሕግ ማድረግ ማለት ነው፡፡ በዓለም ላይ ባለው ተሞክሮ በጣም ብዙ ቦታ በሚባል ደረጃ ይህ ሕግ እንዲሰራ መፈለግ ያለባቸው አገሮች የታችኞቹ ናቸው።
ምክንያቱም ሕጉ የእነርሱን ጥቅም የሚያስከብር ነውና፡፡ ኢትዮጵያ የላይኛው ተፋሰስ አገር ብትሆንም ጉዳዩ ፍትሃዊ እንዲሆን ለማድረግ እና ማሕቀፉ ስኬታማ እንዲሆን በጋራ ከሌሎቹ አገሮች ጋር በመሆን ትልቅ ስራ ስትሰራ ቆይታለች። ተሳክቶላትም ባለፈው ጊዜ ሕግ መሆን ችሏል፡፡
ሕግ ከሆነ በኋላ አገራት በሙሉ የሚገዙት በዚህ ሕግ ሆነ ማለት ነው፡፡ ሕጉ ደግሞ እንዴት አድርጎ ውሃን መንከባከብ እንደሚቻል፣ እንዴት አድርጎ ውሃውን መጠበቅ እንደሚገባ፣ እንዴት አድርገው መረጃ እንደሚለዋወጡ የሚያስገድዷቸውን ስርዓት ያካተተ ነው።
ውጤቱ እኛ የምንኮራበት ነው፤ አሳክተነዋልም። ምክንያቱም ወደ ስድስት የሚሆኑ አገራት ይህንን ፈርመው በአገር ደረጃ ሕጋቸው አድርገውታል፡፡ በቀጣይ ሕጉን ተግባራዊ የምናደርግበት ተቋም ያስፈልገናል፡፡ እሱም ተቋም የ”ናይል ሪቨር ኮሚሽን” የሚባል ነው፡፡ የሚቀረውም እሱን ማቋቋም ነው፡፡
ኮሚሽን ሲቋቋም የሕጉን ተፈጻሚነት ይከታተላል። በአሁኑ ወቅት ያለን የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማሕቀፍ (ናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ) ነው። ይህ ኢንሼቲቭ ሀገራት ወደውና ፈቅደው የሚሳተፉበት እንጂ አስገዳጅ ሕግ የለውም፡፡ እንዲሁ በመሰባሰብ የሚወሰኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ኮሚሽን ከሆነ ግን አቅም ያለው ይሆናል፡፡ ስርዓት አለው፤ ተጠያቂነትን ያረጋግጣል፡፡
አሁን ያንን ኮሚሽን ለማቋቋም እንቅስቃሴ ጀምረናል። ከዚህ ጋር ተያይዞም በቅርቡ ዑጋንዳ ኢንቴቤ ላይ አንድ ስብሰባ ነበረን፡፡ በስብሰባው ላይ የተገኘው ስብስብ የውሃ ሚኒስትሮች ካውንስል የሚባለው ነው፡፡ በስብሰባችን ወቅት አንድ ሀሳብ አቅርበናል፡፡
ያቀረብነው ሀሳብ የታችኞቹ አገሮች እና ሌሎቹ ያልፈሩሙ አገሮች እንዲፈርሙ ማግባባት ላይ ነው። ለዚህ ሥራ ደግሞ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ በእኛ እምነት የትኛውም የተፋሰሱ አገር ከዚህ ውጭ መሆን የለበትም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ይጠቀሙበታል ብለን ማመናችን ነው፡፡
ሁለተኛው ስምምነቱን የፈረሙት ስድስቱ አገራት የኮሚሽኑን አካሔድና በቀጣይ እንዴት መቋቋም አለበት በሚለው ላይ መነሻ ሰነድ ማዘጋጀት ነው፡፡ ለዚህም ኮሚቴ አዋቅረናል፡፡ ይህንን እናሳካዋለን ብለን እናምናለን። እንደ አገር ካየን ግን የትብብር ማሕቀፉ ከእኛ በላይ ተጠቃሚ የሚያደርገው ሌሎቹን ነው፡፡ እንዲያውም ከእኛ በላይ ማሕቀፉ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ጫና መፍጠር የነበረባቸውም፤ ያለባቸውም እነርሱ መሆን ነበረባቸው፡፡
በተለይ ግብጽና ሱዳን ያንን ማድረግ አለባቸው። እኛ አሁን እያንዳንዱን ውሃ ወይም የፈለግነውን ውሃ እንጠቀማለን ካልን የሚያስገድደን ሕግ የለም፡፡ ምክንያቱም መጠቀም መብታችን ነው። ማሕቀፉ ሲመጣ እኛን አያግደንም፡፡ ምክንያቱም እኛ የምናምነው በፍትሐዊ ተጠቃሚነት ነው፡፡ ሁሉም ይጠቀም የሚል አመለካከት አለን፡፡
ለእኛ ትልቁ ስኬት ከማሕቀፉ ሕጋዊ መሆን ጋር በተያያዘ ቀድሞ የነበሩ ሕጎች መሻራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የ1959ኙን ሕግ ሁለት አገሮች ብቻ ወስነው እንዳሻቸው የሚያደርጉትን አካሔድ ለውጦታል፤ ለእኛ ይህ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ ኮሚሽኑ ከመጣ እሰየው ነው። መምጣትም አለበት፤ እኛም እንደግፈዋለን፡፡ ይህ ሕግ ግን ለእኛ ሰላም የሚሰጥ ነው፤ ለሁሉም የሚጠቅም ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ መጥቀስ የምሻው፤ አሁን ከኢትዮጵያ ውጪ ብዙ አገሮች ስለማሕቀፉ ሆነ ስለኮሚሽኑ ስለገባቸው ተፈጻሚነቱ እንዲፋጠኑ እየተንቀሳቀሱ ነው። እኛም የምንፈልገው ይህንኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ፍትሃዊነት የሚለውን ቃል ዑጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን በማቀንቀን ላይ ናቸው። ቀደም ሲል ስለፍትሃዊነት ስንጮህ የነበረው ብቻችንን ነበር፤ በአሁኑ ወቅት አጋዥ አግኝተናል። በአሁኑ ወቅት ስድስት አገሮች ስምምነቱን ፈርመው የሀገራቸው ሕግ አካል ስላደረጉት፤ ስለዓባይ በአግባቡ በዓለም መድረክ ላይ ማውራት ጀምረዋል። ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው፡፡
በዚያው ልክ ደግሞ ፈተናዎች አሉብን። የታችኞቹ አገሮች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ፤ ሚዲያዎችንም በመጠቀም ጭምር በተለይ ግብጽ የትብብር ማሕቀፉን ማጣጣሉን ተያይዘዋለች። ከዚህ ጋር ተያይዞም ምንም አይነት ገንዘብም ሆነ ድጋፍ እንዳይገኝ በተለያየ ቦታ በመንቀሳቀስ የማከላከል ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይህን ጉዳይ እኛ በአግባቡ ተረድተን መግለጽና ማስረዳት አለብን። ምክንያቱም ሌሎቹ እንዲረዱ ማድረጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ፈተናም ያለብን እዚህ ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብጽ ዛሬም የነበረ ጠላትነቷን ቀጥላለች፤ ይህ ምን ያህል ትርፋማ ያደርጋታል ይላሉ?
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ትርፍ አታገኝ በትም፤ እንዲያውም ይህን በማድረጓ ተሸናፊ ናት። ምክንያቱም ከዚህ ቀደምም እኛ አሸንፈን ስለምናውቅ ነው፡፡ የዓባይ ግድብ ላይ ያላደረጉትና ያልሞከሩት ክፋት አልነበረም፡፡ ዛሬ ሲታይ ግን እነርሱ ያሉት ሳይሆን እኛ ያልነው ትክክል ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ገና ከጅምሩ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ስትጀምር፤ ግብጽ ኢትዮጵያ ግድቡን የጀመረችው እኛን ለመጉዳት ነው አለች፡፡ ዛሬ የዓባይ ግድብ ከበፊት ይልቅ ከነበረው የውሃ መጠን አራት እጥፍ የሚለቅላቸው ሆኗል፡፡ ከሶስት ሳምንት በፊት ወደ ሕዳሴ ግድብ አምባሳደሮችን ይዤ ሄጄ ነበር፡፡ አምባሳደሮቹ ባዩት ነገር በጣም ሲገረሙ ነበር፡፡
ለግብጻውያን የሚሄደው የውሃ መጠንንም በግራፍ በማየታቸው “ይህ ሁሉ ውሃ ይሔዳል ማለት ነው” ሲሉ ሲደነቁም ነበር፡፡ ለእኛ የግብጾች መሸነፍ ማለት ይህ ነው። ግብጾች፣ ኢትዮጵያ ስትገድብ የነበረው ግድብ ሙሉ በሙሉ እነርሱን የሚጎዳ አድርገው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲናገሩ የነበረ ቢሆንም እነርሱ ሲያስቀምጡት የነበረው ትርክት መሬት ላይ ያለ እውነታ አለመሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ችሏል፡፡
ግብጾች፣ በዚህ ብቻ ተረትተው የሚያቆሙ እንዳልሆነ ከድርጊታቸው መረዳት ይቻላል፡፡ አይሳካላቸውም እንጂ በቀጣይም ሌላ ከመሞከር አይቦዝኑም፡፡ እኛ ማድረግ ያለብን ስራችንን በአግባቡ መስራት ነው፡፡ ዓባይ ግድብ ላይ በጣም ብዙ ነገር ሞክረዋል፡፡ በእርግጥ ሴራቸው እኛን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ የዓባይ ግድብ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር የተከፈለበት ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆነን ግንባታውን ማሳካት ችለናል፡፡ እውነትን ይዘን አሸናፊ መሆን ችለናል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በዓለም መድረክ ላይ ስለ ዓባይ ግድብ እምብዛም እያወሩ አይደለም፡፡ ያንን ትተው አሁን እያደረጉ ያለው ጎረቤት አገሮችን ኬንያን፣ ሶማሊያን፣ ሱዳንን ..ወዘተ በኢትዮጵያ ላይ ለማነሳሳት መጣር ነው፡፡ እኛ ይህን ጉዳይ መንገር፤ ማስረዳት አለብን፡፡
ከኬንያውያን ጋር የምንሰራው የጋራ ልማት ነው፡፡ እኛ ዓባይ ላይ ባለማነው ኢነርጂ፣ በቀጣይም በምናለማው ኢነርጂ ኬንያ ተጠቃሚ ናት። ዛሬ ኢትዮጵያ ለኬኒያ ኢነርጂ ትልክላታለች። በተመሳሳይ ጅቡቲም ተጠቃሚ ናት፡፡ እንዲሁ ሱዳንም ከኢትዮጵያ ተጠቃሚ ናት፡፡ ለየአገራቱ ኢነርጂ እየሸጥንላቸው ነው፡፡
እነሱ ጩኸታቸውን ይጩሁ ከእኛ የሚጠበቀው ትልቁ ነገር ስራችንን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አጠናክረን መቀጠል ነው፡፡ አንደሚታወቀው ሕዳሴ ግድብን ስንጠቀምበት የነበረው ለኢነርጂ ብቻ ነበር። እውነቱን ለመናገር በአካባቢው በመስኖ ሊለማ የሚችል አቅም አለን፡፡ ስለሆነም በጣም ገፍተው ከመጡ መሬቱም ውሃው የእኛ ነው፤ ሉዓላዊ አገር ነን፡፡ በአካባቢው ያለው ሰፊ መሬት ነው፡፡ ስለዚህ መጠቀም እንችላለን፡፡ እነሱ ያላሰብነውን ጭምር እንድናስብ እያደረጉን ነው፡፡
ለግብጻውያን የሚሻለው ነገር ባልተገባ መንገድ ወዲህና ወዲያ ማለት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩው እና አዋጩ መንገድ የትብብር ማሕቀፉ ነው፡፡ ሕግ ሆኖ የጸደቀው ማሕቀፍ ሁሉንም የተፋሰሱ አገሮች ማስጠለል የሚችል ትልቅ ጥላ ነው፡፡ እኛ ለዜጎቻችን የምናስበውን ያህል ለግብጾችም ለሱዳኖችም እናስባለን፡፡
ኢትዮጵያን በመረበሽ የሚያገኙት ትርፍ የላቸውም። ምናልባት ሕዝባቸውን “ኢትዮጵያን እንዲህና እንዲያ አድርገናታል” በሚል ለወሬ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር የሚገኝ ፋይዳ አይኖርም፡፡ ዓባይ ግድብ ላይ ሕዝባቸውን ሲዋሹ ነበር፤ ነገር ግን በመጨረሻም እውነታው ሌላ ሆኖ በመገኘቱ ሕዝቡ ራሱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጥያቄ የሚያነሳባቸው ይሆናል፡፡
እንደማይሳካለቸው የሚታወቀው ደግሞ የሄዱት ጎረቤቶቻችን ዘንድ ነው፤ እኛ ደግሞ ብዙ ጊዜ የጎረቤቶቻችንን እንቅስቃሴ እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ ሶማሊያን ብንወስድ ለራሷ ችግር ውስጥ ያለች አገር ናት፡፡ እዛ ሔደው ኢትዮጵያ ላይ ማበር የማይቻል ነገር ነው። ሌላው ኤርትራ ጋር መሄድ ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ኤርትራውያንም የራሳቸው ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ አካሄዳቸው እንዲሁ ኢትዮጵያን የመጉዳት ሀሳብ እንጂ መሰረት የሌለው ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ሊጎዱም፤ ሊሳካላቸውም አይችሉም፡፡
ለኢትዮጵያውያን ትልቁ አዋጭ ጉዳይ በአንድነት መቆም ነው፡፡ የሚያወዋጣን የተጀመረውን ስራ መቀጠል ነው፡፡ ሕዳሴን ገንብተን አጠናቅቀናል። ይህም በጣም የተሳካ ሥራ ነው፡፡ ከዓባይ በኋላ በጣም ብዙ ሕዳሴዎች መገንባት አለባቸው። ዳቡስ፣ ዴዴሳ፣ በሽሎ፣ አንገር እነዚህ ትልልቅ የዓባይ ወንዝ ገባር ወንዞች ናቸው፡፡ በሌላኛው በኩል ደግሞ በለስ ወንዝ አለ፡፡ እነዚህን ሀብቶቻችን አስበንበት ለኢነርጂ፣ ለመስኖና ለሁሉም የልማት ስራዎች ለማከናወን ቆርጠን መነሳት ያስፈልገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ መጠናቀቁ እየተነገረ ይገኛል፤ አሁን ላይ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል? በቀጣይስ ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል?
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ዓባይ ግድብን ስናነሳ ኢትዮጵያውያን መያዝ ያለባቸው ሁለት ነገሮችን ነው። ግድቡን ጨርሰናል ስንል ግንባታው አበቃ ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም አሁንም ድረስ የሕዝብን ድጋፍ የሚሻ ስራ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ማወቅ የሚገባቸው ዓባይን ጨረስን ስንል ውሃውን መያዝ የሚያስችል የውሃ መጠን ላይ መኖራችን ነው፡፡ ሲቪል ዎርኩ የግድቡ አካል ነው፡፡ ይህ አልቋል ማለት ሌሎች የሚሰሩ ሥራዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የሚጠናቀቁ ሥራዎች አሉ፡፡ ሁሉም የሕዝቡን ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው፡፡
ሌላው በዓባይ ግድቡ አካባቢ የሚሰሩ ተጨማሪ ሥራዎች አሉ፡፡ ዓባይን ለኢነርጂ መጠቀማችን እውነት ነው፤ ትልቁም ሥራ እሱ ነው፡፡ ይሁንና ብዙ ጥቅም የምናገኝባቸው ሌሎች ሥራዎችም አሉ፡፡ እነሱ ቀጣይነት ይኖራቸዋል፡፡ ይህ የሕዝብ ድጋፍ የሚፈልግ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያውያን በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ ማድረጋቸውን ማቋረጥ የለባቸውም እላለሁ፡፡ ከሕዳሴ ጋር ተያይዞ በቀጣይ የሚሰሩ ሥራዎችን ማገዝ ያስፈልጋል።በዚህ አጋጣሚ ለዜጎቻችን ጥሪ ማስተላለፍ እወዳለሁ ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ያልተዳረ ሰባቸው አካባቢዎች ለማድረስ እየተሰራ ያለው ምንድን ነው?
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- የሚኒስቴር መ/ቤታችን ተቋማት የትኩረት አቅጣጫ ከሆነው አንዱ የመጠጥ ውሃ ነው፡፡ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ላይ ትኩረት እናደርጋለን። እንደ አገር ያለውን ስሌት ትተን በሰው ቁጥር ስናይ ወደ 71 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆን ሰው የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆኗል። ይህ ቁጥር የከተማውንም የገጠሩንም የሚያጠቃልል ነው።በቂ ነው ወይ ከተባለ የሕዝቡ ቁጥር ስለሚታወቅ በቂ አይደለም፡፡
ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር አሁን ያለው የውሃ መጠን ተመጣጣኝ አይደለም። በጣም ከፍተኛ የሆነ ስራ የሚፈልግ ነው፡፡ እንዴት ነው የሚሰራው ወደሚለው ሲመጣ አንዱ መንግስት በቻለው አቅም የሚሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ከተለያየ ድጋፍ ሰጪ አካላት፣ ከዓለም ባንክ፣ ከዩኒሴፍና መሰል ከሆኑ ተቋማት ድጋፍ የሚሰሩ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ማንሳት የምፈልገው ዜጎች በራሳቸው ተነሳሽነት / ኢኒሼቲቭ የራሴ የሆነ ውሃ ሊኖረኝ ይገባል ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል ፡፡
እኛ እንደ ሚኒስቴሩ “ግድቤን በደጄ” የሚል አንድ ኢኒሼቲቭ ጀምረናል፡፡ “ግድቤን በደጄ” ማለት ዝናብ ሲዘንብ ሰው የሚወርደውን ዝናብ ይዞ አቆይቶ የተጣራ ውሃ በራሱ ማግኘት እንዲችል ማስቻል ነው። ይህን የጀመርነው በትምህርት ተቋማት ላይ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ደሃ አገር ቀርቶ ሌላውም ይህን መጠቀም ግድ ይለዋል፡፡ ምክንያቱም ያደጉ አገሮችም ይህን ይጠቀሙበታል ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአመለካከት ችግር መንግስት ሁሉን እንዲያቀርብ መፈለጉ ላይ ነው፡፡ ይህ በጣም ከባድ ከመሆኑም በላይ ሊደረግ የማይችል ነው፡፡ በተፈጥሮ ፈጣሪ ዝናብ ሰጥቶናል፡፡ ዝናብ በየጊዜው እየዘነበ በደጃችን ሲያልፍ እያየን በነጋታው ግን ሰው ውሃ የለንም ብሎ ሲቸገር ይስተዋላል፡፡ ሩቅ ሰፈርም ውሃ ፍለጋ ይኳትናል፡፡
ነገር ግን በደጁ የሚያልፈውን ውሃ ይዞ ለነገ ለአትክልቱም፤ የዝናብ ውሃ ስለሆነ ንጹህ ነውና ለመጠጡም ማዋል ይቻላል፡፡ ከብትም የሚጠጣው ይሆናል፤፤ እንደዚህ አይነት ተነሳሽነቶች /ኢኒሼቲቮች ያስፈልጋሉ፤ እኛ ጀምረናቸዋል፡፡ የዝናብ ውሃን አሰባስቦ መጠቀምን እንደ ተጨማሪ አማራጭ ካደረግን አዋጭ ነው። ዋጋው ርካሽ ነው፡፡ ጊዜንም የሚወስድ አይደለም። ሰው ከቀዬው ውሃ ሳያጣ ለተለያየ ዓላማ መጠቀም ይችላል፡፡
ከዚህ ባሻገር በከተማ ውስጥ ያጋጠመን ትልቁ ችግር ከተሞች ለሌሎች የልማት ሥራዎቻቸውም ሆነ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳይ በጀት እንደሚመድቡት ሁሉ ለመጠጥ ውሃም በጀት አለመመደባቸው ነው፡፡ ስለዚህ ለመጠጥ ውሃም እንደሌሎቹ ሁሉ በጀት ሊይዙለት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ውሃ ሳይኖር መንገድም ሆነ ሌላ ነገር አይታሰብም፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ በአግባቡ መስራት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰፋ ያለ ማብራሪያ ስለ ሰጡን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም