አዲስ አበባ ከተማ አደሬ ሰፈር ተወልደው ያደጉት አቶ ሙሀመድ የሱፍ ፊደል መቁጠር የጀመሩት በአረብኛ ቋንቋ ነው። አረብኛ ቋንቋን ከተማሩ በኋላ የዘመናዊ ትምህርታቸውን በልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም በኮሜርስ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ) ገብተው የአካውንቲንግ ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል። በአራት ዓመት የትምህርት ቆይታቸው በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ነበር ያገኙት።
ከትምህርት በኋላ በግል ኩባንያ ተቀጥረው በሙያቸው የሂሳብ ሥራ ሰርተዋል። ጥቂት ዓመታት እንደሰሩ በግላቸው ለመስራት ወስነው ድርጅቱን የተሰናበቱት አቶ ሙሀመድ፤ በወቅቱ ወጣት እንደመሆናቸው ፈጣን፣ ቀልጣፋና አዲስ ነገር ለማወቅ ከፍተኛ ጉግት ያላቸው ነበሩ። ወጣትነታቸው ያጎናጸፋቸውን ጥንካሬ ከግል ባህሪያቸው ጋር በማቀናጀት የተለያዩ የግል ንግዶችን ሲሰሩ ቆይተዋል። ከተሰማሩባቸው የንግድ ዘርፎች መካከልም የጨው ንግድ ተጠቃሽ ነው። በወቅቱ ከምጽዋ ጨው ገዝተው ወደ ጅቡቲ ከጅቡቲ ደግሞ በባቡር ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ሲነግዱ ቆይተዋል።
በወቅቱ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሰማርተው ከላይ ታች ሲሉ የቆዩት አቶ ሙሀመድ፤ ከመሸጥ መለወጥ ያልዘለለውን የንግድ ሥራ ገታ በማድረግ አምራች ኢንደስትሪውን ተቀላቅለዋል። ከዛሬ 30 ዓመት በፊት በአይነቱ ለየት ያለና በአገሪቱ ብቸኛ የሆነውን ላይላክ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያና የሕጻናት ዳይፐር ማምረቻ ድርጅትን አቋቁመዋል። ማምረቻ ፋብሪካውን የገነቡት የኢንዱስትሪ መንደር ተብለው ከተከለሉ አካባቢዎች አንዱ በሆነው አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነው። ቦታውን በደርግ ዘመነ መንግሥት የገዙ ቢሆንም ወደ ሥራ የገቡት በኢህአዴግ ጊዜ እንደሆነ አጫውተውናል።
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ያሳለፉት አቶ ሙሀመድ፤ በጊዜው የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች የቱን ያህል አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆኑ ተረድተዋል። በወቅቱ እነዚህን ምርቶች በአገር ውስጥ የሚያመርት አምራች ድርጅት ባለመኖሩ ምርቶቹ በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው አገር ውስጥ እንደሚገቡ ያውቃሉ። በአገሪቱም ምርቶቹ በስፋት እንደሚፈለጉና ሰፊ ገበያ ያላቸው ስለመሆናቸው መረዳት ለእሳቸው ቀላል ነበርና በሚገባ ተረድተዋል።
በመሆኑም ከዛሬ 30 ዓመት አስቀድመው የንጽህና መጠበቂያ ምርቶቹን በአገር ውስጥ ለማምረት ወሰኑ። ፋብሪካ ገንብተው ማሽን አስመጥተው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅታቸውን ባጠናቀቁበት ወቅት የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ ስልጣን የተቆጣጠረበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ሥራውን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት አቶ ሙሀመድ፤ ሥራውን በሙሉ አቅማቸው ለማስቀጠል የተለያዩ እንቅፋቶች ገጥመዋቸዋል። ይደርስባቸው ከነበረው ወከባና እንግልት በተጨማሪ ከሁለት ወንድሞቻቸው ጋር እስር ቤት ገብተዋል። ‹‹እውነት ትመነምናለች እንጂ አትበጠስም›› እንዲሉ ታድያ ያለበቂ ምክንያት ከሰባት ዓመት በላይ በእስር ያሳለፉት ወንድማማቾች ነጻ ተብለው ቢለቀቁም አንድ ወንድማቸው ግን ነጻ የወጡበትን ዕለት ማየት አልቻለም። ምክንያቱም አንድ ወንድማቸው እስር ቤት እንዳለ ሕይወቱ አልፏል።
እርሳቸውን ጨምሮ ከሁለት ወንድማቸው ጋር እስር ቤት የገቡት አቶ ሙሀመድ፤ የወንድማቸው ሀዘን አጥንታቸውን ዘልቆ በመግባቱ በእጅጉ አዝነው እንደነበር ሲገልጹ ሀዘናቸው ዛሬም ድረስ አብሯቸው እንዳለ ገጽታቸው ይናገራል። የወቅቱን ሁኔታም ዕንባ እየተናነቃቸው ሲገልጹ ‹‹ሶስት ሆነን እስር ቤት ገብተን፤ ሁለት ሆነን ወጥተናል›› በማለት ነው።
እስር ቤት በነበራቸው ቆይታ ወንድማቸውን ማጣታቸው የሁልጊዜ ሀዘናቸው ቢሆንም በቆይታቸው ጊዜ ሁሉ እስር ቤት ውስጥ የሰሩት መልካም ሥራ ዛሬም ድረስ የሚያስደስታቸው እንደሆነ የገለጹት አቶ ሙሀመድ፤ ማንኛውንም አስቸጋሪ ሁኔታ በጸጋ ተቀብሎ የማለፍ ትልቅ ጸጋ አላቸው። አቶ ሙሀመድ፤ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ፍቅር ያላቸው በመሆኑ ከሰባት ዓመታት በላይ በእስር ቤት ውስጥ ሲያሳልፉ የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ነው። በዚህም እስር ቤቱን በተለያየ መልኩ መቀየር ችለዋል። ለአብነትም እስረኞች የሚፀዱበትንና የሚዝናኑበትን ቦታዎች ማዘጋጀትና ማስዋብ፣ ትምህርት የማስተማርና የተለያዩ ስልጠናዎችን የመስጠት ይጠቀሳሉ።
እረፍት የማያውቁት አቶ ሙሀመድ፤ ከእስር ከወጡ ከትንሽ ጊዜ ቆይታ በኋላ ተስፋ ሳይቆርጡ በጅምር የቀረውን ሥራ ለማስቀጠል ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው ተነስተዋል። በወቅቱም ከልማት ባንክ ብድር ወስደው ላይላክ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያና የሕጻናት ዳይፐር ማምረቻ ድርጅታቸውን በአዲስ መልክ በማቋቋም ወደ ሥራ መግባት ችለዋል። ይሁን እንጂ በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሚፈልጉት ልክ ሊያስኬዳቸው ባይችልም በቻሉት አቅም ሁሉ ታግለዋል።
እሳቸው እንዳሉት ወደ ሥራው ስገባ ደረጃውን በጠበቀና ከፍተኛ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት ነው። ነገር ግን ዛሬም በአንዳንድ አከፋፋዮችና ነጋዴዎች ለጥራት የሚሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ ፈተናው ከባድ ነው። ላይላክ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያና የሕጻናት ዳይፐር በአገር ውስጥ የመጀመሪያው ድርጅት ከመሆኑም በላይ በዓለም ደረጃ ጥራቱን የጠበቀና ተመራጭ ነው። ማምረቻ ማሽኖቹም አሜሪካን ስታንዳርድ የሆኑና በቻይና አገር የተመረቱ ናቸው። ምርቱ አሜሪካን አገር በሚገኙ የጥራት መመዘኛዎች ተወዳድሮ የጥራት መስፈርቱን ያሟላ ስለመሆኑ የተመሰከረለትና የዕውቅና ሰርተፊኬትም ከአሜሪካኖቹ ማግኘት ችሏል።
ከዛሬ 30 ዓመት አስቀድመው ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲገቡ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ምርጫቸው ያደረጉት አቶ ሙሀመድ፤ ሥራውን በጀመሩበት ዓመት ጀምሮ በተለያዩ የሕይወት ፈተናዎች ሲፈተኑ ቆይተዋል። ይሁንና ለፈተና አልንበረከክም ያሉት አቶ ሙሀመድ፤ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ላይላክ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያና የሕጻናት ዳይፐር ማምረቻን በአዲስ መልክ ያቋቋሙት በ2009 ዓ.ም ነበር። ቀድሞ የነበረው ማምረቻ ማሽን በመጠኑም ሆነ በጥራቱ ያነሰ በመሆኑ የተሻለና ዘመናዊ ማሽን እንዲሁም ባለሙያዎችን ከቻይና ወደ አገር ውስጥ በማስመጣት ሥራውን ጀምረዋል።
አሜሪካን ስታንዳርድ የሆነውና ዘመናዊ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን የሚያመርተው ይህ ማሽን 20 አይነት ጥሬ ዕቃዎችን መቀበል የሚችል ነው። ያሉት አቶ ሙሀመድ፤ ማሽኑ ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ መስመሩን ጠብቆ እያመረተ የመጨረሻ ውጤቱን የሚሰጠው በተዘጋጀለት ቦታ ነው። እሳቸው እንዳሉት፤ በወቅቱ ማሽኑን ለመግጠምና ሥራውን ለማስጀመር ሶስት የውጭ አገር ዜጎች ለአንድ ወር መጥተው ሰባት ወራት ቆይተው ሄደዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አለመሟላት ነበር።
ማሽኑ በዓለም ደረጃ የመጨረሻውን የጥራት ደረጃ ጠብቆ የሚያመርት ቢሆንም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እግር ከወርች አስሯቸው እንደቆየ አቶ ሙሀመድ ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት ፋብሪካው አስፈላጊ የተባሉ ማሽኖችን ያሟላና በእጅጉ ጥራቱን የጠበቀ ቢሆንም እስካሁን ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ማምረት አልቻለም። ነገር ግን አሁን ላይ መንግሥት ለአምራች ኢንደስትሪው እየሰጠ ያለውን ትኩረት አጠናክሮ በማስቀጠል በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ማምረት ያቆሙ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። አሁን ያለው ጅምር እንቅስቃሴም የሚበረታታ ቢሆንም ቀሪ ስራዎች ስለመኖራቸው አንስተዋል።
በተለይም በቅርቡ ተግባራዊ የሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ብዙ ተስፋ ይዞ ይመጣል። የውጭ ምንዛሪው በገበያ መመራት መቻሉ የግል ዘርፉን የሚያነቃቃና ወደ ሥራ የሚያስገባ ነው። በመሆኑም ለዓመታት ተዘግተው ለቆዩ ፋብሪካዎችም ትልቅ መነቃቃት የሚፈጥር ነው። ላይላክ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያና የሕጻናት ዳይፐርም በተመሳሳይ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት በሙሉ አቅሙ ማምረት ያልቻለ ቢሆንም በአሁን ወቅት ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት የሚችልበት ዕድል እየመጣ ነው። ለዚህም ድርጅቱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን በቅርቡም ወደ ምርት የሚገባ ይሆናል።
መንግሥት በተለይም የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየሰራ እንደሆነ ይታመናል። ያሉት አቶ ሙሀመድ፤ የተለያዩ ምርቶችን በጥራት በተገቢው መንገድ የሚያመርቱ አምራች ድርጅቶችን ለይቶ እገዛ ማድረግ ቢችል ደግሞ መንግሥትና ሕዝብ በብዙ ይጠቀማል ይላሉ። በተለይም የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ከማምጣት ይልቅ ጥሬ ዕቃውን ብቻ አምጥቶ በአገር ውስጥ ማምረት መቻል የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት እንደሆነም አስረድተዋል።
የንጽህና መጠበቂያ ምርቶቹን ለማምረት ጥሬ ዕቃው ሙሉ ለሙሉ ከውጭ የሚገባ በመሆኑ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይፈልጋል። ለዚህም ተግባራዊ በሆነው የውጭ ምንዛሪ ግብይት አማካኝነት ዶላር ገዝተው ሥራውን ለማሳለጥ ዝግጁ የሆኑት አቶ ሙሀመድ፤ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶቹ ገበያ ውስጥ ካሉት ምርቶች ጋር ሲወዳደር በጥራት የተሻለና ተወዳዳሪ የሌለው ስለመሆኑ ዕምነታቸው የጸና ነው። እሳቸው እንዳሉት፤ ላይላክ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያና የሕጻናት ዳይፐሩ ምንም አይነት እርጥበት የማይኖረው፣ ፈሳሽ የማያሳልፍና በተለይም ለሕጻናቱ ቆዳ ተስማሚ የሆነ ቅባት ያላው ደረጃውን የጠበቀ ምርት ነው። ያም ሆኖ አሁን ላይ ገበያ ውስጥ ካሉት ምርቶች ጋር በዋጋ ሆነ በጥራት የተሻለና ተመጣጣኝ ነው ብለዋል።
ፋብሪካቸውን እንዲሁም መኖሪያቸውን በአንድ ቦታ ያደረጉት አቶ ሙሀመድ፤ ፋብሪካውን በአዲስ መልክ ባቋቋሙ ጊዜ ማስፋፊያ በማድረግ የማምረቻ ቦታውን አስፋፍተዋል። የንጽህና መጠበቂያ ምርቶቹን ለማምረት በጥራት የተዘጋጀው ቦታም ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ዘመናዊ ማሽኖች ይዟል። ከፍተኛ የማምረት አቅም ያለው ዘመናዊ ማሽኑ ዲዛይን የተደረገው በደቂቃ 500 ዳይፐር ማምረት የሚችል ሲሆን በጥቅሉ በዓመት 72 ሚሊዮን ዳይፐር የማምረት አቅም አለው። በተመሳሳይ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ወይም ሞዴስ ደግሞ በደቂቃ 600 በዓመት 84 ሚሊዮን ሞዴስ የማምረት አቅም ያለው ግዙፍና ጥራት ያለው ማሽን ነው።
ፋብሪካው በዚህ መጠን የማምረት አቅም ቢኖረውም እስካሁን በነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሙሉ አቅሙ ማምረት አልቻለም። ይሁንና በቀጣይ ጥሬ ዕቃውን በስፋት በማምጣት ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት የሚችልበትን ዕድል ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ያነሱት አቶ ሙሀመድ፤ እንዲህ አይነት ትልቅ አቅም ያለው ፋብሪካ በጥሬ ዕቃ እጥረት ለዓመታት ተዘግቶ መቆየቱ ብዙዎችን ያስቆጨ እንደሆነና ፋብሪካው ትልቅ የአገር ሃብት መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ግዙፍ አቅም ያለው የአገር ሃብት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም ወደ ሥራ ለመገባት ዝግጁ እንደሆነ ሁሉ የሚመለከተው የመንግሥት አካላም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።
ፋብሪካው ሲቋቋም ጀምሮ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ቢሆንም ባጋጠሙት የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሰው ኃይሉ ቀንሷል። ያሉት አቶ ሙሀመድ፤ በአሁን ወቅት 30 ሠራተኞችን ይዞ ቀጥሏል። እነዚህ 30 ሰራተኞችም በዘርፉ ስልጠና ያገኙና ብዙ ወጪ የተደረገባቸው ናቸው። ይሁንና በቀጣይ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲችል የሥራ ዕድሉን በእጥፍ የሚጨምር ይሆናል ብለዋል።
ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ አቶ ሙሀመድ፤ ከልጅነት እስከ ዕውቀት በጎ ሥራን በመስራት የሚታወቁ እንደሆነና በጎ ሥራ መስራት ነብሳቸውን የሚረካበት መሆኑን ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት ከሕጻናት ዳይፐር ጀምሮ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በተለያዩ ሆስፒታሎች እርዳታ በመስጠት ያግዛሉ። በተለይም አቅም ለሌላቸውና ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለመውለድ ወደ ሆስፒታል የሚመጡና ዝግጁ ላልሆኑ እናቶችና አዲስ ለሚወለዱ ሕጻናት በተለያየ ጊዜ ዳይፐር ለሕጻናቶቹ ያቀርባሉ።
የሕጻናት ዳይፐሩን በተለያዩ ሆስፒታሎች ተደራሽ በማድረግ ለብዙ እናቶች እፎይታን መፍጠር የቻሉ ሲሆን፤ ለአብነትም ተደራሽ ከሚሆኑባቸው ሆስፒታሎች መካከል ጥቁር አንበሳና ጋንዲ ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም አበበች ጎበናና ሌሎች የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ የዳይፐር ድጋፍ ያደርጋሉ። በመኖሪያ አካባቢያቸውም ለሚገኙ አቅመ ደካሞችም እንዲሁ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ይታወቃሉ። ከዚህ በተጨማሪም በወረዳቸው አማካኝነት ለሚቀርብላቸው ጥያቄ እንዲሁም አገራዊ ለሆኑ ማንኛውም ጥሪ እጃቸውን በመዘርጋት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2016 ዓ.ም