አዲስ ዘመን ድሮ

በርካታ ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ብለን በኢትዮጵያ ምን አይነት ኩነቶች እንደነበሩ የምናስታውስበት አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ለዛሬ በርከት ያሉ ጉዳዮችን ያስቃኘናል። ለዚህም በተለይም በ1950ዎቹና 70ዎቹ የነበሩ ዘገባዎችን መርጠናል። ከመራረጥናቸው ዘገባዎች መካከል የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ 67ኛ ዓመት የልደት በዓል አከባበር፣ የሶቪየት ኅብረት ሕጻናት ስጦታ፣ 28 ሠራተኞች ሳንሠራ ደሞዝ ይከፈለናል ስለማለታቸው፣ 22 ጠንቋዮች እራሳቸውን ስለማጋለጣቸው፣ የ40 ዓመት ሴትም በአንድ ጊዜ 3 ልጆችን መገላገላቸው የሚያስታውሱን ዋነኞቹ ናቸው። በመጨረሻም “አብረን እንሳቅ አብረን እንኑር” እያልን፤ ከሚለው ገጽ ላይ ሁለቱን በመምረጥ አሰናድተን እንደሚከተለው አቅርበናል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የተወዳጁን ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የስድሳ ሰባተኛውን ዓመት የልደት በዓል እጅግ ከፍ ባለ ደስታ ያከብራል

ይህ ዘመን የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አርቆ አስተዋይነት በአሜሪካና በኤውሮፓ፣ በእስያ፣ በአፍሪካ ክፍለ ዓለማት ከሚገኙት የወዳጅ አገሮች ጋር የኢትዮጵያን ሕዝብ በፍቅርና በወዳጅነት ያስተሳሰሩበት አዲሱ ሰለሞን የተባለው የግርማዊነታቸው ሰውነት በመላው ዓለም ውስጥ ዓለምን ያስደነቁበት ጊዜ ነው።

ከዚህም በቀር ደግሞ ይህ የዛሬውን የልደት በዓል ብዙ ዘመን ሙሉ በአስደናቂ ሥራ ሲጌጥ ለቆየው ለግርማዊነታቸው ዘመነ መንግሥት ወደ 68 ዓመት መተላለፊያ በር ስለሆነ ከፍ ባለ ሁኔታ እናከብረዋለን።

ሐምሌ 16 ቀን 1954 ዓ.ም የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘ ኢትዮጵያ የስድሳ ሰባተኛው የልደት በዓል አከባበር ፕሮግራም

1ኛ. ሐምሌ 16 ቀን 1954 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት 21 መድፍ ይተኮሳል

2ኛ. ግርማዊት እቴጌ መነን በታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ በኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ፀሎት ያደርሳሉ

3ኛ. ግርማዊት እቴጌ መነን ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል መሳፍንት፣ መኳንንቶች፣ ወይዛዝርቶችና የመንግሥት ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሆኑት ነጋዴዎችና ታላላቅ ሰዎች በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ይቀበላሉ

4ኛ. በአራት ሰዓት ተኩል ግርማዊት እቴጌ መነን በቤተ መንግሥት ሠገነት ወጥተው ለተሰበሰበው ሕዝብ ይታያሉ። በዚህ ጊዜ በከተማው በአዲስ አበባ ሕዝብና በራሳቸው ስም ንግግር ያደርጋሉ።

5ኛ. በስድስት ሰዓት የውጭ አገር መንግሥታት እንደራሴዎች በቤተ መንግሥቱ የክብር መዝገብ ላይ ስማቸውን ይፈርማሉ።

ልብስ ሚሊቴር ወይም ገበርዲን ሲቢል ሞርኒንግ ኮት ወይዛዝርቶች የከተማ ልብስ

6ኛ. ግርማዊት እቴጌ መነን በስድስት ሰዓት ስለ በዓሉ ክብር መንግሥት ለኢትዮጵያ መሳፍንት ሚኒስትሮች፣ መኳንንቶችና ለመንግሥት ሠራተኞችና ለካህናቶች፣ በከተማው ነዋሪ ለሆኑት ታላላቅ ግብዣ ያደርጋሉ።

7ኛ. በዚሁ ቀን ከምሽቱ በ2 ሰዓት ስለ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በዓል ክብር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት የራት ግብዣ ያደርጋሉ።

ልብስ ነጭ ክራባት ከዚህ በኋላ የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል።

(አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 1954ዓ.ም)

የሶቪየት ኅብረት ሕጻናት ለኛ ሕጻናት ስጦታ ላኩ

በሶቪየት ሕብረት በኪርጌዚያ ሪፐብሊክ የተለያዩ መንደሮች የሚኖሩ ሕጻናት በትርፍ ጊዜያቸው በእርሻ ቦታዎች በመሠማራት እየሠሩ ባጠራቀሙት ገንዘብ የገዟቸውን አሻንጉሊቶችና ልዩ ልዩ መጫዎቻዎች ለኢትዮጵያ ሕጻናት እንዲውል በርዳታ ልከዋል።

……..

ስጦታውን የላኩት የሶቪየት ኅብረት ሕጻናት የኢትዮጵያ ሕጻናት የደስታ ኑሮ እንዲኖሩ እንደሚታገሉ ከስጦታው ጋር በላኩት ደብዳቤ ማረጋገጣቸውን ጓድ አምባሳደር ኪርናሶቪ ስኪይ ገልጠዋል።

(አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 1971 ዓ.ም)

28 የገጠር ፕሬዤዎች ሠራተኞች ሳንሠራ ደመወዝ ይከፈለናል ይላሉ

በገጠር ፕሬዤዎች ድርጅት በአዋሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 28 አናጢዎችና ግንበኞች ለአራት ወራት ሥራ በማስፈታት 14ሺህ 892 ብር ደመወዝ በነፃ የከፈላቸው መሆኑንና በመሥሪያ ቤቱ ውስጥም ከፍተኛ የሥራ መዝረክረክ መኖሩን ከገጠር ፕሬዤዎች ድርጅት አጠቃላይ የሠራተኞች ማኅበር ጽሕፈት ቤት ሁኔታውን እንዲያጣራ የተላከው ቡድን አጋለጠ።

(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 12 ቀን 1971ዓ.ም)

የ40 ዓመት ሴት በአንድ ጊዜ ሦስት ልጆች ወለዱ

ሐረር (ኢ.ዜ.አ) ወይዘሮ ፋጡማ ኢብሮ የተባሉት የ40 ዓመት ሴት ሐረር ከተማ በሚገኘው በምሥራቅ አርበኞች ሆስፒታል ውስጥ ባለፈው ዓርብ 3 ሕጻናትን በአንድ ጊዜ መገላገላቸውን አቶ ሽፈራው አቢቢ የሆስፒታሉ አስተዳደር አስታወቁ።

ከሕጻናቱም መካከል መጀመሪያ የተወለደው ወንድ 4 ኪሎ ከሃያ አምስት ግራም ክብደት ሲኖረው ተከትለው የተወለዱት ሌሎች አንድ ወንድና ሴት ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ኪሎ ከ20 ግራም ክብደት እንዳላቸው ተገልጧል።

(አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 1971ዓ.ም)

22 ጠንቋዮች ራሳቸውን አጋለጡ

ደሴ,(ኢ.ዜ.አ) ወሎ ውስጥ በደላንታ ወረዳ የኢላና ትምህርት ቤት መምህራን ከጣርዳት፣ ከደሀናንና ከዝባን የገበሬ ማኅበራት ጋር በመተባበር በመካከላቸው የተሰገሰጉትን 22 ዓባይ ጠንቋዮች ራሳቸውን አጋልጠው ክቡር ወደሆነው የሥራ መስክ እንዲሠማሩ አደረጉ።

እነዚሁ 22 ዓባይ ጠንቋዮች በተሰጣቸው ትምህርት አምነው ድቤዎችን(ከበሮዎችን)፣ እንዲሁም በእጃቸው ይገኙ የነበሩትን ልዩ ልዩ የጥንቆላ ዕቃዎችንና መጽሐፍት ለገበሬ መኅበራቱ በራሳቸው ፈቃድ አስረክበዋል። ዓባይ ጠንቋዮቹ ካስረከቧቸው ዕቃዎች ውስጥ በተለይ ከበሮዎቹ በአካባቢው ለሚቋቋመው የኪነት ቡድን መገልገያ እንዲሆን መሰጠቱ ተገልጧል።

(አዲስ ዘመን መጋቢት 23 1971 ዓ.ም)

አብሮ መሣቅ

አብሮ መኖር

ከቤቱ ሠርግ አለው

ስትተኛ ሙቃ

ስትኖር ተሳስቃ

ስትሄድ ገንዘብ ንቃ።

ሸጋ መልከ መልካም ድቡልቃ ሚስት ያለው ከሰው ሠርግ አይሄድም ከቤቱ ሠርግ አለው።

ስትኖር ተነዛንዛ

ስትተኛ ቀዝቅዛ

ስትሄድ ገንዘብ ይዛ።

ነዝናዛ የሆነች ፈዛዛ ሚስት ያለው ከሰው ለቅሶ አይሄድም ከቤቱ ለቅሶ ነው።

………

ቃጫ ፋብሪካ

ሸበቶ:- የኔ ወንድም ይህ አስፋልት ወዴት ይወስዳል?

መላጣ:- ቃጫ ፋብሪካ ያደርስኃል

(አዲስ ዘመን መስከረም 20 ቀን 1958 ዓ.ም)

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You